Monday, February 29, 2016

በአዲስ አበባ የታክሲዎችን የስራ ማቆም አድማ ተከትሎ የትራንስፖርት ችግር ተከሰቷል



በአዲስ አበባ የሚገኙ የታክሲ ሹፌሮች የወያኔ አገዛዝ ያወጣውን የትራንስፖርት እና መንጃ ፍቃድ ሕግ በመቃወም የጠሩት የስራ ማቆም አድማ በዛሬው እለት የአዲስ አበባን መንገዶች ከትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ውጪ በማድረጋቸው ተገልጋዩ በትራትስፖርት ችግር ሲገጥመው ተስተውሏል::
የአዲስ አበባን የታክሲ ሹፌሮች ከስራ ውጪ ለማድረግ እና ስራ ፈት ዜጎችን ለመፍጠር ታስቦ በወያኔ የወጣው አዲስ ሕግ ማንኛውም ሹፌር 21 ጊዜ ጥፋት ካለበት መንጃ ፈቃዱ ተነጥቆ ከሹፌርነት ለመጨረሻ ጊዜ የሚያግድ ሲሆን የታክሲ ሹፌሮችን ሆን ብሎ በማጥቃት ከስራ ውጪ በማድረግ የደህንነት አካላት የሆኑ አዳዲስ እየሰለጠኑ የሚገኙ የሕወሓት አባላትን የታክሲ ባለቤቶች ላይ ጫና በመፍጠር በሹፌርነት ለማሰማራት የታቀደ እንደሆነ ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ::

የወያኔው አገዛዝ በተለያዩ በዝባዥ እና ሕዝብን በሚበድሉ ሕጎች ኢትዮጵያውያንን እያሰቃየ ሲሆን ይህም ከፍተኛ የሆነ ብሶት አደባባይ ላይ መሰማቱ ሲቀጥል የስራ ማቆም አድማውም የዚሁ ብሶት አካል መሆኑ ታውቋል::በአዲስ አበባ የትራንስፖርት ተገልጋዮች በተለያዩ መንገዶች ትራንስፖርት ለማግኘት ቢሞክሩም እንዳልቻሉ ታይተዋል::የወያኔ አገዛዝ ለሶስት ወር አራዘምኩት ይሕጉን ተግባራዊነት የሚል መግለጫ ቢሰጥም ተቀባይነት አጥቶ የስራ ማቆም አድማው ተደርጓል::ሕዝቡ ብሶቱን በተለያየ መንገድ በመግለጽ ስርኣቱ እንዲወገድ ትግሉን ቀጥሏል::



በሰሜን ጎንደር ዳባት ሕዝባዊ እምቢተኝነት ተቀሰቀሰ | ወደ መቀሌና ሽሬ የሚወስዱ መንገዶች ተዘጋግተዋል

Breaking News zehabesha

(ዘ-ሐበሻ) በሰሜን ጎንደር ዳባት ሕዝባዊ እምቢተኝነት መቀስቀሱን ከአካባቢው የሚመጡ መረጃዎች አስታወቁ:: ምንጮች ለዘ-ሐበሻ እንደሚገልጹት ወደ መቀሌና ሽሬ የሚወስዱ ወይም ከዚያ ወደ ዳባት የሚያመጡ መንገዶች ተቃውሞውን ባነሳው ሕዝብ በድንጋይ እና በ እንጨት መዘጋጋቱ ተሰምቷል::
በዳባት ከተማ ሕዝቡ ሕዝባዊ እምቢተኝነቱን ያነሳው ከወልቃይት መሬት እና ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ እንደሆነ ከስፍራው የሚመጡ መረጃዎች ጠቁመው ሕዝባዊ ቁጣው እስከ እኩለሊት ድረስ እንደቀጠለ የዘ-ሐበሻ ምንጮች አስታውቀዋል::
ይህን ጉዳይ ተከታትለን እንዘግባለን::

Saturday, February 27, 2016

Breaking: የቴዲ አፍሮ የአዲስ አበባ ኮንሰርት ተከለከለ – ለምን? ዝርዝር አለን

teddy afro 2
(ዘ-ሐበሻ) የፊታችን ቅዳሜ ማርች 5, 2016 በአዲስ አበባ ጊዮን ሆቴል ሊደረግ የነበረው የቴዲ አፍሮ የሙዚቃ ኮንሰርት ተከለከለ፡፡
በመላው ኦሮሚያ እንዲሁም በአማራው ክልል በተለይም በሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል ውስጥ ውጥረት ውስጥ የገባው ኢሕ አዴግ መንግስት ጦሩን ወደ ኤርትራ ድንበር ካስጠጋና እንደዚሁም ደግሞ በኦሮሚያ በ8 ዞኖች ከፋፍሎ ወታደራዊ አስተዳደር ካወጀ በኋላ በአዲስ አበባ ከፍተኛ የሕዝብ አመጽ ይነሳል በሚል ምክንያት የተለያዩ ዝግጅቶችን በመሰረዝ ላይ ይገኛል

ለቴዲ አፍሮ ኮንሰርት በአዲስ አበባ ተበትኖ የነበረው ፍላየር
ለቴዲ አፍሮ ኮንሰርት በአዲስ አበባ ተበትኖ የነበረው ፍላየር

ምንጮቻችን እንደገለፁልን ይህን ኮንሰርት ለመስራት ቴዲ በ1.3 ሚሊዮን ብር የተዋዋለ ሲሆን በርካታ ህዝብ በጉጉት ሲጠብቀው ነበር፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ ይነሳል በሚል በመንግስት ደህንነቶች በመፈራቱና በተለይም የቴዲ አፍሮ ኮንሰርት ሕዝብን በአንድ ላይ ያገናኛል በሚል ፍራቻ ኮንሰርቱ መሰረዙን የደህንነት ምንጮች ለዘ-ሐበሻ ገልጸዋል::
ለቴዲ አፍሮና አዘጋጆቹ ሐበሻ ዊክሊ ኮንሰርቱ ተከልክሏል ተብሎ የተነገራቸው ከዚህ የተለየ እንደሆነ ያስታወቁት ምንጮች ኮንሰርቱ መከልከሉን ያስተዋለው ቴዲ የቀጣይ አልበሙን ስራ ለማጠናቀቅ ወደባህር ዳር አምርቷል፡፡ የቴዲ አፍሮ አዲስ አልበም ለፋሲካ በአል እንደሚወጣ የዘ-ሐበሻ ምንጮች አስታውቀዋል::
ቴዲ አፍሮ በአዲስ አበባ ኮንሰርት ለማድረግ ፈልጎ ከዚህ ቀደም በጸጥታ አስከባሪዎች እጥረት የተነሳ በሚል ሰንካላ ምክንያት መከልከሉ አይዘነጋም::

Friday, February 26, 2016

የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ያልያዙ ኢትዮጵያውያን ሰልፈኞች መንግስት ጎረቤቶቻቸውን እና የአገሩን ቀደምት ነዋሪዎችን እንዲገድልላቸው ጠየቁ

”ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም” ይላል ደጉ ኢትዮጵያዊ። አሁን አሁን መጪውን የመከራ ዘመን ለመቀበል እራሳቸውን ያዘጋጁ፣መካሪ ሽማግሌ ያጡ እና ጥጋብ የሚሰሩትን ያሳጣቸው በእሳት ሲጫወቱ ማየት የተለመደ ሆኗ

ከእዚህ በላይ የምትመለከቱት ፎቶ አፍቃሪ ሕወሃቱ ፋና ብሮድካስቲንግ በድረ ገፁ ላይ የሰቲት ሁመራ ነዋሪዎች የአካባቢው ቀደምት ነዋሪዎች አማራ ነን ትግሬ አይደለንም  በማለታቸው ብቻ ትግሪኛ ተናጋሪዎች ሰልፍ መውጣታቸውን ከዘገበበት ገፅ ላይ የተወሰደ ነው።
በፎቶው ላይ እንደምትመለከቱት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የለም በሚባል ደረጃ ሁለት ወይንም ሶስት ብቻ ትመለከታላችሁ።የቀረው በሙሉ ከኢትዮጵያ ጡት ያደገ በማይመስል መልክ (ተገዶ መሆኑን የሚገልፁ አሉ) የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ተሽቀንጥሮ በህወሓት አርማ ሰቲት ሁመራ ላይ ተሰልፈዋል።
ዜናውን ፋና እንዳለው ብቻ ላቅርበው እና ሰልፈኞቹ መንግስትን ጎረቤቶቻችንን ይግደልልን ማለታቸውን አንብባችሁ ፍረዱ።በመጀመርያ ደረጃ በሰቲት ሁመራ፣በታች አርማጮ የአማራ ተወላጅ ነን ትግርኛ ብንናገርም ባህላችን፣ለቅሷችን፣ ሁሉ በአማራ ባህል ነው።በሚል በሰላማዊ እና በሰለጠነ መልክ ለመጠየቅ አዲስ አበባ ድረስ ተወካይ የላከው የሁመራ ሕዝብ ተወካዮቹ ታፈኑበት።እንግዲህ ይህንን በሰላማዊ መንገድ ለተጠየቀ ጥያቄ ነው ሰልፍ ተወጥቶ እንደ ፋና አገላለፅ ሰልፈኞቹ  እንዲህ ብለዋል ይለናል-
ህዝቡ እነዚህን አካላት እስካሁን በትዕግስት ጠብቋቸዋል ያሉት ነዋሪዎቹ፥ ከአሁን በኋላ ግን መንግስት አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ እንዲወስደባቸው ጠይቀዋል።’
በትዕግስት ጠበቃቸው የተባሉት ስለ ሁለት ነገር ነው ማለት ነው? አንዱ ቀድመው ነዋሪ ስለሆኑ ባህላችን ይጠበቅ በማለታቸው ሲሆን ሁለተኛው ይህንን መብታቸውን ደጋግመው በሰላማዊ መንገድ መጠየቃቸው ነው።
ለጥያቄው ምላሽ የሕወሃቱ የምስራቅ ትግራይ አስተዳዳሪ አቶ ኢሳያስ በምላሹ እንዲህ አሉ ይላል ፋና :- ”የህዝቡን ጥያቄ ለማክበርም በእነዚህ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንወስዳለን
በቀይ ሽብር ዘመን እርምጃ ወስደናል ማለት ገድለናል ማለቱ መሆኑን ማንም ያውቀዋል።በፋና ዘገባም ሕዝብ ”እርምጃ ይወሰድ” አለ ማለት ”ይገደሉልን” ማለቱ ሲሆን ”እርምጃ እንወስዳለን” አሉ ሲል ደግሞ ”እንገላለን” ማለት መሆኑ ነው።እነማንን ሲባል ጎረቤቶቻቸውን እና ቀደምት ነዋሪዎችን።ምክንያት ባህላችን ይከበር በግድ ከመሬታችን ተገፋን ስላሉ።
ይህ አይነቱ የለየለት መንግስታዊ ፋሺዝም በኢትዮጵያ ላይ ነቅሎ ሰላም ይመጣል ማለት ዘበት ነው።በኦሮምያ በመቶ የሚቆጠሩ በጥይት እረግፈው እና የአስር እና አስራሁለት ዓመት ወጣቶች አደባባይ ወጥተው ድምፅ አሰሙ ብሎ ጥይት በተርከፈከፈባቸው እና መድረክ አዲስ አበባ ላይ ሰልፍ ለመጥራት ጠይቆ በተከለከለ ማግስት  ሁመራ ላይ የሕወሃትን ሰንደቅ አላማ የያዙ ሰልፈኞች ጎረቤቶቻችንን ግዴልልን ብለው መንግስትን ጠየቁ መንግስትም እሺ እንገላለን አለ።የሚል ዜና የሚገኘው ፋና ድረ-ገፅ ላይ ብቻ ነው።ሰልፈኞችም ባይሰልፉ ቢቀር መልካም ነበር።ሽማግሌዎች (ሽማግሌ ካለ) ተሰብስበው ቢነጋገሩ እና መላ ቢዘይዱም ጥሩ ነበር።ነበር ለማለት ነው እንጂ ለህወሓት ከሁሉ በላይ የሆነ ስለመሰለው ፋሽሽታዊ ልብሱን በደንብ እያጠለቀ ነው።ለነገሩ ከቁንጮ እስከ እግር ድረስ በአንድ አካባቢ ሰው የምትመራ አገር በፋሽሽት መሪዎች እጅ  ብትወድቅ  አይገርምም።
ይህ ስርዓት ከትናንቱ ይልቅ መጪው ፋሽሽታዊ አላማው ከመቼውም ጊዜ በላይ አሁን በግልፅ ታይቷል።
ጉዳያችን GUDAYACHNHumera

የሕወሓት ጦር ኦሮሚያን በ8 ቀጠናዎች ከፋፍሎ በሕዝቡ ላይ እርምጃ ለመውሰድ መወሰኑ ተጋለጠ


samora Yenus
(ዘ-ሐበሻ) የኦሮሞ ሕዝብ እንቅስቃሴ 4ኛ ወራት እያስቆጠረ ነው:: ቀደም ሲል የኦሮሞ ሕዝብ ቁጣ እየተቀጣጠለ ሲሄድ ክልሎ ከኦህዴድ አስተዳደር እጅ ወጥቶ በቀጥታ በሕወሓት መሪዎች; የደህነነት ኃይሎች እና ወታደሮች እንዲመራ መደረጉን ዘ-ሐበሻ በተደጋጋሚ ስትዘግብ ነበር::
ሕወሓት ክልሉን በደህንነት እና በወታደሮች እንዲመራ ቢያደርግም ምንም ዓይነት መፍትሄ ሳይመጣ ይበልጡኑ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ከማስተር ፕላኑ አልፎ ወደ ሰብ አዊ መብቶች እና እስከ ነፃነት ጥያቄ ተሸጋግሯል:: በአንዳንድ ከተሞች እንደውም የኦህዴድ ባንዲራዎች በኦነግ ተተክተው መታየታቸው የሚታወስ ነው::
እስካሁን 4ኛ ወሩን ባስቆጠረው የኦሮሞ ሕዝብ አመጽ ከ200 ሰዎች በላይ መገደላቸውን የሰብ አዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ይናገራሉ:: የሕዝቡ ቁጣ አሁንም ያስፈራው ሕወሓት የሚመራው መንግስት ዛሬ በኦሮሚያ በግልጽ የወታደራዊ አስተዳደር አውጇል:: በዚህም መሠረት ክልሉን በ8 ቀጠናዎች በመከፋፈል በሕወሃት ጦር እንዲመራ ወስኗል::
ይህ በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ተደረገ በተባለው የሕወሓቶች እና የድህነነቶች ስብሰባ እንደተገለጸው 8ቱን ቀጠናዎች የሚመሩት የሕወሓት አባል የሆኑ የጦር መኮንኖች ናቸው::
ይህን የሕወሓትንና የድህነንቱን ውሳኔ አንዳንድ የኦሮሞ ብሄረሰብ ተወላጅ የሆኑ የመከላከያ አባላት ቢያወግዙትም “ኦነጎች ናችሁ” እየተባሉ እንደተሽሟጠጡና ሃሳባቸውም በሕወሃት ሰዎች ተቀባይነት እንዳላገኘ ተገልጿል:: እንደዘ-ሐበሻ ምንጮች ገለጻ በሠራዊቱ ውስጥ ያሉት የኦሮሞ ተወላጆች እየተሰለሉ እንደሆነ በሌላ ሰው እንዲነገራቸው እየተደረገ ይገኛል:

Thursday, February 25, 2016

የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስተር በአንዳርጋቸው እና በሌሎችም ጉዳዮች ለመነጋገር ወደ አዲስ አበባ ሊያቀኑ ነው

(ዘ-ሐበሻ) የመን ላይ በሕወሓት መንግስት ተጠልፈው በአዲስ አበባ ባልታወቀ ቦታ ታስረው እየተሰቃዩ የሚገኙት ታጋይ አንዳርጋቸው ጽጌን በተመለከተ እንዲፈቱ ያሳዩት ባህሪ ለዘብተኛ ነው በሚል የብሪታኒያ ታዋቂ ግለሰቦችና የፓርላማ አባላት ያካተተ የ135ሺ ፌርማዎችን ለጠቅላይ ሚንስትሩ ዴቭድ ካሜሮን ካስገቡ በኋላ ጠቅላይ ሚንስትሩ በቅርቡ ለጉብኝት ወደ አዲስ አበባ እንደሚሄዱ የሃገሪቱ ሚድያዎች ዘገቡ

Andargachew Tsige David Cameron




ዴቭድ ካሜሮን በቅርቡ በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ጉብኝት በተመለከተ የብሪታኒያ የኢሚግሬሽንና ዜጎች እንዲሁም ተጓዳኝ ጉዳዮችን የሚከታተለው ሆም ኦፊስ ምክትል ቋሚ ፅሃፊ የሆኑት ኦሊቨር ሮቢንስ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር በመዲናችን አዲስ አበባ እየተወያዩ እንደሚገኙ ምንጮች አስታውቀዋል::
ዴቭድ ካሜሮን ወደ ኢትዮጵያ ሲሄዱ የአቶ አንዳርጋቸውን መለቀቅ እንደ አንድ አጀንዳ እንደሚያነሱት የሚጠበቅ ሲሆን ይህም በዚህ ጉዳይ ለዘብተኝነት አሳይተዋል በሚል ለደረሰባቸው ወቀሳ ምላሽ ለመስጠት ነው የሚሉ የፖለቲካ ተንታኞች አሉ::
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በኢትዮጵያ የት ታስረው እንደሚገኙ ባይታወቅም በቅርቡ የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር የሆኑት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ “በአባታቸው እየተጎበኙ” እንደሚገኙ መረጃ አለን ብለዋል:: አቶ አንዳርጋቸውም በቅርቡ ከ እስር ካልተለቀቁ የአ እ ምሮአቸው ሁኔታ አስጊ እንደሆነ የ እንግሊዝ ዲፕሎማቶች መግለጻቸውን ዘ-ሐበሻ መዘግቧ አይዘነጋም::

የአባይ ወልዱ በወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ላይ የጦርነት ነጋሪት መጎሰም የህይወት ዋጋ ያስከፍላል! | ጎንደር ህብረት

            የትግራይ ነጻ አዉጭ ግንባር ብሎ እራሱን የሚጠራዉ ድርጅት መሪ አቶ አባ ወልዱ እና የክልሉ የፀጥታና የአስተዳደር ኃላፊ አቶ ሐድስ ዘነበ ከዘራፊ ካድሬወቻቸው ጋር በመሰባሰብ፤ በወልቃይት፤ በጠገዴ እና በጠለምት ህዝብ ላይ የማያዳግም ጦርነት ለማካሄድ የጦር ነጋሪት እየደለቁ በማስፈራራት ላይ ይገኛሉ። ጦርነቱን በሚፈልጉት መንገድ በድል ለመወጣት እየተጠቀሙበት ያለው የሞራል መምቻ ደግሞ፤ ህብረተሰቡን፤ በገብያ፤ በቤተክርስቲያን እና ቤት ለቤት በማደን እያስፈራሩ ወደፖሊስ ጣቢ እየወሰዱ፤ ወልቃይት የትግራይ ክልል እንደሆነች እንድትቀጥል እንደሚፈልጉ በማሥመሰል በማሥገደድ እያስፈረሙ ናቸው
ጎንደር ህብረ
    abay weldu
ሌላ የዚህ ሳምንት አስገራሚዉ የወያኔ ቲያትር ደግሞ፤ ከስህተት ላይ ሥተት በመደራረብ ህዝብና ህዝብን ለማጋጨት የትግራይ ተወላጆችን ስልፍ አሰልፎ በጉልበት ይዞት የቆየዉን መሬት የትግራ ነዉ እያለ ማስጨፈሩ ነዉ። ወያኔ በመላዉ ኢትዮጵያ ሰልፍ ከልክሎ ሰላማዊ ሰልፈኞችን በታንክና መትረየስ እዬጨፈጨፈ፤ ጎንድር መሪ የሌለዉ መሆኑን የተረዳዉ ወያኔ ወገራ አዉራጃ ላይ የትግራይ ተወላጆችን ከጎንደር ህዝብ ጋር ቂም ለመትከል የዉሸት ሰልፉን አቀነባብሮ ያስጨፍራል። የተቃዉሞ ስሜትን በአደባባይ መግለጽ ከሆነማ ይህ አይነቱ ወልቃይት ጠገዴ እና ጠለምት ብሎም ለመላዉ ጎንደር/ አማራ ህዝብ መፈቀድ የግድ ይላል።
Gondor Hibret
ጦረኛ ቡድን በአሁኑ ሰዓት ሌላ ወንጀል እና ደባ ከመፈጸም ይልቅ፤ መደረግ የነበረበት፤ የወልቃይት፤ የጠገዴ እና የጠለምትን ህዝብ ባለፉት 25 ዓመታት በተፈጸመበት ግፍና በደል ይቅርታ መጠየቅ ነበር እንጂ አድሮ ጥጃ የሆነዉ የትግራይ ነፃ አዉጭ ግንባር የአማራን መሬት በሰፊዉ ለመቆጣጠር የጦርነት ክተት አዋጅ ነጋሪት መደለቅ እና በቴለቭዥን መስኮት ውሸት መርጨት አልነበረበትም። ይህ ድርጊት ታሪክ ይቅር የማይለው አሳዛኝ ተግባር ነው። ለዚህ ሰይጣናዊ ስራው የሚገጥመዉ ምላሽም በጣም የከፋ ሊሆን ስለሚችል ለጥፋት ብቻ ትግራይ መሬት ላይ የተቀመጠዉ አቶ አባይ ወልዱ በጊዜው የያዘውን ሥልጣን እና ያስታጠቀውን ሚሊሺያ ሌላ ሊበግረው የሚችል ሃይል መሥሎት በትቢት ወይም በድንቁርና ከአንድ ጥፋት ወደ ሌላ ጥፋት መሸጋገሩ ትልቅ አደጋ ነዉ። በመላው አገሪቱ በዜግነታቸው ኮርተው፤ የሚኖሩበትን ህብረተሰብ አምነው እና ተዋደው የሚኖሩትን የትግራይ ተወላጆች በወልቃይት ጠገዴ የግፍ እሳት ላለማቃጠል ቆም ብሎ እንዲያስብ እጅግ እናሳስባለን።
ላለፉት 30 ዓመታት የቃፍቲያ ሁመራ፤ ወልቃይት ጠገዴ/ጠለምት ህዝብ የአማራ ምንነቱን ተነጥቆ፤ አማራም ጎንደሬም አይደለህም ተብሎ፤ የዘር ማጽዳት ድርጊት ተፈጽሞበታል። ለዘመናት ከኖረበት መሬት ተፈናቅሎ ብዙ ትዉልድ ለስደት ተዳርጓል። ላለመሰደድ በቀየው መሞትን የመረጠ ተወላጅ፤ እጣ ፈንታው ለዘመናት ፀሐይን እንዳያይ ተወስኖበት እስር የሚማቅቀዉን ብዛት፤ የትግራ እስር ቤቶች ይቁጥሩት። በጀምላ የተቀበረዉን ደግሞ፤ ጊዜ እያወጣዉ ነዉ፤ ክቡር ገረመድን አራያ ይናገራሉ።
የዚህን አካባቢ ህዝብ ከገደለ እና ካፈናቀለ በኋላ፤ ብዛት ያላቸውን የትግራይ ተወላጅ የወያኔ ደጋፊዎቹን ተከዜን አሻግሮ አስፍሯል። በአሁኑ ሰዓት ደግሞ ይህን ሁሉ ግፍ እና በደል ከፈጸመ በኃላ፤ በአካባቢው ለህዝበ ውሳኔ ለማቅረብ የማጥቂያ ስልት ነድፎ ተነስቷል። በቂ የወልቃይት ተወላጆች የሉምና እኔ ያሰፈርኳቸውና አንዳንድ ሆዳሞች በድምጽ ብልጫ ለኔ ድምጽ ሊሰጡ ይችላሉ ብሎ በማመን፤ የዘወትር ዉሸትና ብልጥነቱን በማጠናከር እራሱ ፌደራል ብሎ በሰየመዉ ምክር ቤት ህዝቡ ተጠይቆ ምክር ቤት ይወስናል የሚል አጀንዳ ይዞ ብቅ ለማለት እየተዘጋጀ ነዉ። ከአሁን በኋላ፤ የወልቃይት አማራም፤ ጎንደሬም የመሆን ውሳኔ የሚጸናው፤ በወልቃይት መሬት በሰፈሩ ተከዜ ተሻጋሪ የትግራይ ተወላጆች ሳይሆን፤ የመላው ጎንደር ሕዝብ ውሳኔ ነው።
ይህ የማንነት ውሳኔ ደግሞ፤ በወያኔ መሪዎች በነ አባይ ወልዱ ችሮታ የሚለገስ ሳይሆን፤ በቆራጥነት፤ እነሱ የረገጡትን ጀግንነታችን አሥመስክረን በምንጎናፀፈው ነፃነት ብቻ ነዉ።። በዚህ መልክ ቆርጠን ስንነሳ ነው፤ የጎንደር ታሪካዊ መሬት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ወደነበረዉ ወደጥንቱ ጎንደር ክፍለ ሃገር በአስቸኳይ ሊመለስ የሚችለው ብሎ የጎንደር ሕብረት አጥብቆ ያምናል። ይህ እንደሚመጣ ወያኔ አስቀድሞ በማወቁ፤ መላ የትግራይን ወንድ ልጅ ከመንግሥት ካዝና እየዘረፈ ሙሉ በሙሉ አስታጥቋል። ይን ለመመከት፤ ካሁን በፊት ደግመን ደጋግመን እንዳስጠነቀቅነው፤ ዛሬም እንዳለፈው፤ ለአቅመ አዳም የደረሰ ጎንደሬ በሙሉ መታጠቅ አለበት። የወልቃይት ጉዳይ፤ ከአዲስ አበባው ማስተር ፕላን በላይ በዜጎች ማንነት ላይ እዬተፈጸመ ያለ አስከፊ በደል ነው። በመሆኑም በቆራጥነት መስዋዕትነትን መክፈል፤ የማንነትም፤ የተወላጅ ባለቤትነትም፤ የዜግነት ግዴታ ነው።
ከዚያም በላይ! በጎንደር ህብረት አቋም እና እምነት ደግሞ፤ ይህ በጎንደር ህዝብ ላይ፤ ብሎም በሰፊዉ አማራ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ የወያኔ ቱባ መሪ አባይ ወልዱ የክተት አዋጅ ወያኔ እራሱን እንደማነቅ ሲሆን፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ አፍኖ የሚመራዉ ስርዓትም የመጨረሻዉ የሞት ጣር እና ኑዛዜ ከመሆን እንደማያልፍ እርግጠኛ ሁነን እንናገራለን። ታላቁን የአማራ እና የትግራይን ህዝብ ለማዳማት በፈጸሙት የአርባ አመታት የጭፈጨፋ እና የጥላቻ ዘመቻ በኪሳራ ስሌት እየገፋ የሁለቱ ማህበረሰብ እስከ አሁኑ ድረስ ችግርም ሆነ ደስታዉን የወያኔን ከፋፋይ መርዝ ተቋቁሞ በጋራ ህይወቱን እየገፋ ይገኛል። ይህ እንዳይደፈረስ ከታሰበ፤ “የትግራይ ህዝብ የጎንደርን መሬት በጉልበት እንድንገዛ ድጋፍ ሰቶናል” እያሉ የሥራዓቱ ሙስና እጃቸዉ የነካ ግለሰቦችን በማናገር በቴሌቢዥን መስኮት የሚያካሂዱት ቅስቀሳ በአስቸኳይ መቆም አለበት።
ሰፊዉ የኢትዮጵያ ህዝብም የአቶ አባይ ወልዱን የእርስ በእርስ ጦርነት አዋጅን በመቃወም በጎንደር ሕዝብ ላይ የተቃጣዉን ጥቃት ለመጋፈጥ አጋርነታችሁን እንድታሳዩ በአክብሮት እንጠይቃለን። እንዲሁም የብሔረ አማራ ዲሞክራሲ ንቅናቄ (ብአዴን)ብሎ የሚጠራዉ፤ የአማራን ህዝ እወክላለሁ የሚለዉ የወያኔ አጋር ድርጅት፤ የወያኔ መጠቀሚያ መሳሪያ የመሆን የባዶ ጨዋታ ዘመን አክትሞ የትግራይ ነጻ አዉጭ ግንባር የሚያካሂደዉን የመስፋፋት ዘመቻ እንቅስቃሴ ህዝቡ ተቃዉሞዉን በመግለጽ ምላሽ ለመስጠት በሚዘጋጅበት ሁኔታ ሁሉ ጣልቃ ገብቶ ተጽዕኖ ከማድረግ እንዲቆጠብ በጥብቅ እናሳስባለን።
በመጨረሻም፤ ከህዝብ አብራክ የወጣዉ ሰራዊትም የአገሩን ዳር ድንበር ከማስከበር ዉጭ የወያኔ ታዛዥ ሁኖ በዘረኛ መንግስት የተበደለ ወገኑን ተኩሶ ከመግድል እንዲቆጠብ እናሳስባለን።፤ በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን አረመኒያዊ የግፍ ሥራዓት ሊሸከም ባለመቻሉ፤ በእምቢተኝነት እየተነሳሳ ያለውን ወገንህን፤ በተለይም በሽዋ፤ በወለጋ፤ በአርሲ፤ በሃረር በጋምቤላ፤ የሚያካሄደዉን ጭፍጨፋ በአስቸኳይ እንዲቆም ወገናዊ ጥሪያችን እናስተላልፋለን። እንዲሁም፤ የወያኔ መንግስትም ብዙ ደም ሳይፈስ ስልጣን ለቆ አገሪቱን የሚያድን፤ ህዝቡን የሚያረጋጋ፤ ሁሉን ያካተተ በሕዝብ የተመረጥ መንግስት በአስቸኳይ እንዲቋቋም በጥብቅ እናሳስባለን።

Tuesday, February 2, 2016

በቡታጅራ ከተማ ታላቅ ህዝባዊ ተቃዉሞ ተደረገ | የሳዲቅ አህመድ የቪድዮ ዘገባ ከጽሁፍ ጋር

በቡታጅራ ከተማ ታላቅ ህዝባዊ ተቃዉሞ ተደረገ | የሳዲቅ አህመድ የቪድዮ ዘገባ ከጽሁፍ ጋር



በደቡብ ክልል በጉራጌ ዞን በመሰቃን ወረዳ በዛሬዉ እለት ህዝባዊ እምቢተኝ ተስተዋለ።ፓሊሶች ተደብድበዋል።ፖሊሶች ተጎድተዋል። የመንግስት ታጣቂ ሐይላት ክላሽ ኢንኮቫቸዉን ተቀምተዋል።
መንግስት ያወጣዉን የመሬት ይዞታ አዋጅ በመቃወም ዛሬ በድንገት የተደረገዉ ሰልፍ ፖሊሶች ህዝቡን መቆጣጠር ተስኖአቸዉ በህዝብ ቁጥጥር ስር የዋሉበት አጋጣሚ እንደነበር የሰልፉ ታዳሚዎች ያስረዳሉ። መንግስት ከአያት ቅድመ አያቶቻችን የወረስነዉን መሬት እየቀማ ለኢንቨስተሮች ይሰጥብናል የሚሉት የቡታጅራና የአካባቢዉ ነዋሪዎች ተወልደን ባደግነበት ቀዬ እንድንፈናቀል ተደርገናል ሲሉ ቅሬታን ያሰማሉ።
የአካባቢዉ ነዋሪዎች ለቢቢኤን እንደገለጹት ልክ የአዲስ አበባዉን የሚመስል ማስተር ፕላን በድብቅ ተሰርቶ ስራ ላይ እየዋለ ነዉ። በህወሃት የሚመራዉ መንግስት የመስቃንን ማህበረሰብ መሬት በተቀናጀ መልኩ ለመዝረፍና ጥቅሙን ለሚያስከብሩ አካላት ለመስጠት የምስጢር ፕላኑን ወደ መሬት ላይ ለማዉረድ ሲሞክር ነዉ ዛሬ በፖሊሶችና በህዝብ መካከል ግጭት የተነሳዉ።
የተቦን፣ዊጣ፣ወዶ፣ጆሌ ሐሙስ ገበያ በሚባሉት የመስቃን ወረዳ ቀበሌ ገበሬ ማህበራት ያሉ አርሶ አደሮች መሬታቸዉ እየተቀማ ህወሃት መራሹ መንግስት ለሚፈልጋቸዉ አካላቶች መሰጠቱን የሚያስረዱት አርሶ አደረሮች ጉዳዩ የህልዉና ጉዳይ ስለሆነ ለአቤቱታ ወደ ቡታጅራ ከተማ በመጡበት መታሰራቸዉን ይገልጻሉ።
በገዛ መሬታቸዉ ቤት የሰሩ አርሶ አድረሮች ከተማዎች በሚስፋፉበት ወቅት ቤቶቻቸዉ እንደሚፈርሱ በምሬት ይናገራሉ።እንደ ቅርስ የያዙት ቤትና ንብረት እንደመከነ የሚገልጹት አርሶ አደሮች ከከተማ ራቅ ወዳሉ የገጠር ቀበሌዎች የመሰቃን ወረዳ እና የቡታጀራ ከተማ አሰተዳደር ባለስልጣናት ከታጣቂ አጃቢዎች ጋር በመጓዝ የገጠር ቤቶች ከመንግስት ፍቃድ ዉጪ የተሰሩ በመሆናቸዉ መፍረስ አለባቸዉ ቤቶቹን ለማፍረስ ያደረጉት ሙከራ በዉርደት መጠናቀቁን ነዋሪዎቹ ለቢቢኤን ገልጸዋል።
“እኛ የገጠር ነዋሪዎች ነን፤ በገጠር ዉስጥ ልክ እንደ አያት ቅድመ አያቶቻችን ቤት እንሰራለን፤ ይህንንም ለማድረግ የማንም ፍቃድ አያሻንም!” በማለት ባለ ሰልጣናቱ የታጀብቡበትን ክላሽ-ኢንኮቭ በመንጠቅ ከየቀበሌ ገበሬ ማህበራቱ እንዳባረሯቸዉ የመስቃን ወረዳ ነዋሪዎች ለቢቢኤን ገልጸዋል።
በመሬት ነጠቃዉ የተንገፈገፉ የቡታጅራ ነዋሪዎች በዛሬዉ እለት ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ አደባባይ መዉጣታቸዉን የገለጹልን የቡታጅራ ነዋሪዎች በከተማዋ ዉስጥ እየዞሩ የተቃዉሞ ድምጽ ማሰማታቸዉን ለቢቢኤን ገልጸዋል።ሰላማዊ ሰላፍ አድራጊዎቹ “መንግስት ሌባ፣ ፖሊስ ሌባ፣መብታችን ይከበር፣የታሰሩት ይፍቱ፣ጥያቄያችን ይመለስ!” እያሉ ድምጻቸዉን ሲያሰሙ ከአገር ሽማግሌ በስተቀር ሊያቆማቸዉ የሞከረ የፖሊስ ሐይል አለመኖሩ ለማወቅ ተችሏል።
ተቃዉሞዉ በሚደረግበት ሰዓት ባንክ ቤቶች፣ቤንዚን ማደያዎች፣ሱቆች ምግብ ቤቶች የተዘጉ ሲሆን ከተማዉን ከሆሳእና፣ከአዲስ አበባ እና ከዝዋይ የሚያገናኘዉ ዋና መንገድ ተዘግቶ እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል።ማምሻዉን በደረሰን መረጃ መሰረት ፈዴራል ፖሊስ ከወልቅጤ ከተማ ቡታጅራ ድረስ በመምጣት ሰፍሯል። ዉጥረት ቡታጅራ ዉስጥ ነግሷል። ይህ ዉጥረት ወዴት እንደሚያመራ ባይታወቅም፥ የታወቀዉ ነገር ቢኖር ባልተጠበቀ መልኩ በየተኛዉም የኢትዮጵያ ክፍል ህዝባዊ እምቢተኝነት ሊከሰት እንደሚችል ነዉ። ዛሬ ቡታጅራዎች ይህንን አስመስከረዋል::