Saturday, February 4, 2017

ዶናልድ ትራምፕ በሰባት የሙስሊም ሃገራት ላይ ያወጡት የቪዛ እገዳ ተቀለበሰ

(ዘ-ሐበሻ) በአሜሪካም ውስጥ ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሶ የሰነበተው የዶናልድ ትራምፕ አዲሱ የኢሚግሬሽን ትዕዛዝ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከታገደ በኋላ የአሜሪካው የአገር ጥበቃና ደህንነት ባለስልጣን (ሆምላንድ ሴክዩሪቲ) የትራምፕን የቪዛ እገዳ መቀልበሱን አስታውቋል::

ዶናልድ ትራምፕ በሶማሊያ፣ በሱዳን፣ በኢራን፣ በሊቢያ፣ በሶሪያና በየመን ዜጎች ላይ ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚያግድ ከ90 ቀናት ህግ ከፈረሙ ወዲህ የሃገሪቱ ፖለቲካ ሲታመስ ቆይቷል:: ሕዝብ በየኤርፖርቱና ይመለከታቸዋል በተባሉ መንግስት መስሪያ ቤቶች አካባቢ ሰላማዊ ሰልፎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል::


የተለያይ አየር መንግዶችም የነዚህን ሃገራት ዜጎች ሲመልሱ ቆይተዋል:: ሆኖም ግና ይህን አጨቃጫቂ ፊርማ ዶናልድ ትራምፕ ካኖሩ በኋላ በርካታ የአሜሪካ ሕግ አውጪዎች ሲጨቃጨቁበት ቆይተው ትናንት ማምሻውን የዋሽንግተን ፍርድ ቤት ዳኛ ውሳኔውን በማገዳቸው ሆምላንድ ሴክዩሪቲም የትራምፕን ውሳኔ አጥፎ የተከለከሉ ዜጎችን ወደ አሜሪካ ማስገባቱን ዛሬ ጀምሯል::
ትራምፕ ስልጣን ላይ በወጡ በ2 ሳምንታቸው ደከመኝ ብለው ለ እረፍት ወደፍሎሪዳ ያመሩ ሲሆን እዚያም ተቃውሞ ጠብቋቸዋል::












ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ ግሪን ካርድ ለማግኘት ሲሉ የኢትዮጵያ መንግስትን ያጥላላሉ ሲሉ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ከሰሱ




(ዘ-ሐበሻ) የሃገር ውስጥ ጋዜጠኞችን ሰብሰበው በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ የሰጡት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ የኢትዮጵያ መንግስትን የሚያጥላሉት ግሪን ካርድ ለማግኘት እንጂ እውነት መንግስትን ጠልተው ከልባቸው አይደለም አሉ::
ሚኒስትሩ በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫቸው በኢትዮጵያ በጣለው እና በመጪው መጋቢት ስድስተኛ ወሩን በሚይዘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት ዙሪያ በቀረበላቸው ጥያቄ ላይ በሰጡት መግለጫ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታሰበለት ቀን ቀድሞ አይነሳም ብለዋል:: ይህ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ሃገሪቱን እንዳረጋጋ አስታውቀዋል::
አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውን ዜጎች ወደ ሃገራቸው ሊመልሱ እንደሚችሉ እየተነገረ መሆኑንና በርካታ ኢትዮጵያውያንም በአሜሪካ እንደሚኖሩ ጥያቄ ያቀረበላቸው ዶ/ር ነገሪ ትራምፕ ወረቀት አልባ ኢትዮጵያውያንን ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ከወሰኑ ሃገሪቱ እጇን ዘርግታ እንደምትቀበል ገልጸዋል:: በአሜሪካ ያሉ ኢትዮጵያውያን መንግስትን የሚያጥላሉት ወረቀት ለማግኘት እንጂ ከልባቸው ስርዓቱን ጠልተው አልመሆኑን እንገነዘባለን ያሉት ነገሪ እንኳን እነዚህን ዜጎች ይቅርና በይፋ መንግስትን ሲያጥላሉ የከረሙ ተቃዋሚዎችም ሃገራቸው ገብተው በኢንቨስትመንት መሳተፍ ከፈለጉ መንግስት እንደሚተባበር ተናግረዋል::