Saturday, February 4, 2017

ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ ግሪን ካርድ ለማግኘት ሲሉ የኢትዮጵያ መንግስትን ያጥላላሉ ሲሉ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ከሰሱ




(ዘ-ሐበሻ) የሃገር ውስጥ ጋዜጠኞችን ሰብሰበው በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ የሰጡት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ የኢትዮጵያ መንግስትን የሚያጥላሉት ግሪን ካርድ ለማግኘት እንጂ እውነት መንግስትን ጠልተው ከልባቸው አይደለም አሉ::
ሚኒስትሩ በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫቸው በኢትዮጵያ በጣለው እና በመጪው መጋቢት ስድስተኛ ወሩን በሚይዘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት ዙሪያ በቀረበላቸው ጥያቄ ላይ በሰጡት መግለጫ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታሰበለት ቀን ቀድሞ አይነሳም ብለዋል:: ይህ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ሃገሪቱን እንዳረጋጋ አስታውቀዋል::
አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውን ዜጎች ወደ ሃገራቸው ሊመልሱ እንደሚችሉ እየተነገረ መሆኑንና በርካታ ኢትዮጵያውያንም በአሜሪካ እንደሚኖሩ ጥያቄ ያቀረበላቸው ዶ/ር ነገሪ ትራምፕ ወረቀት አልባ ኢትዮጵያውያንን ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ከወሰኑ ሃገሪቱ እጇን ዘርግታ እንደምትቀበል ገልጸዋል:: በአሜሪካ ያሉ ኢትዮጵያውያን መንግስትን የሚያጥላሉት ወረቀት ለማግኘት እንጂ ከልባቸው ስርዓቱን ጠልተው አልመሆኑን እንገነዘባለን ያሉት ነገሪ እንኳን እነዚህን ዜጎች ይቅርና በይፋ መንግስትን ሲያጥላሉ የከረሙ ተቃዋሚዎችም ሃገራቸው ገብተው በኢንቨስትመንት መሳተፍ ከፈለጉ መንግስት እንደሚተባበር ተናግረዋል::

















No comments:

Post a Comment