Friday, November 14, 2014

ብርቱካን በሊባኖስ ተረፈች ፣ አልማዝ በኦማን የአካል ጉዳተኛ ሆና ቀረች ! የተረፈችው የእህት ብርቱካን ጉዳይ …(ነቢዩ ሲራክ)

birtukan
የማለዳ ወግ …
ብርቱካን በሊባኖስ ተረፈች ፣
አልማዝ በኦማን የአካል ጉዳተኛ ሆና ቀረች !
የተረፈችው የእህት ብርቱካን ጉዳይ …
በሃገረ ሊባኖሰ ቤሩት  ከ4ኛ ፎቅ ወድቃ የተረፈችው እህት ብርቱካን  ጤንነት የተስተካከለና ከድካም ህመሟ ሙሉ በሙሉ እያገገመች መሆኑን መረጃዎች ማምሻውን ደርሰውኛል ። የቆንስል ሃላፊዎች አልማዝን ሲያነጋግሯት በሊባኖስ ቆይታ ስራ መስራት እንጅ ወደ ሀገር ቤት መመለስ እንደማትፈልግ እንደገለጸችላቸው አምባሳደር ሐሊማ ሙሃመድ አጫውተውኛል። በቀጣይ ቀናትም ህክምና እየወሰደች ያለችበትን መካስድ ሆስፒታልን ለቃ እንደምትወጣ ፣ በቤሩት የቆንስል መጠለያ ሆና ህክምናና ጉዳይዋን እንደምትከታተል ተረድቻለሁ !
ተስፋ የቆረጡት ኢትዮጵያውያን አስተያየት …
    በብርቱካን ጉዳይ ዙሪያ ያነጋገርኳቸው ብዙ ነዋሪዎች የቆንስል ተዋካዮች ላይ እምነት እንደሌላቸው ይገልጻሉ ። እንደ አማራጭም የብርቱካንን ጉዳይ በጠበቃ አስይዘው ለመከራከር የሚቻልበትን ንገድ ለማፈላለግ ስራ መሰራት አለበት ሲሉ  ” የቆንስል ሃላፊዎችን ዲስኩር ማመን ትቶ የተለመደው የነዋሪውን ትብብር ማስተባበር ያሻል ” ይላሉ።  ለምን በመንግስት ተወካዮቻችን እምነት አጣችሁ?  ማለቴ አልቀረም ፣ ምላሻቸው ዘርዘር ያለ መረጃና ማስረጃ ያለው እውነት ይመስላል። አንድ ያሉኝን ብቻ ላንሳው  … በሃገራ ባንዴራ ስር ፣ በቆንስሏ በር በጥጋበኛ “ጀብራሬ” አረብ  እየተጎተተች ስትደበደብ የቆንስል ሀላፊዎች ምንም አለማድረጋቸው ፣  ከዚያም  ሃኪም ቤት በገባች በቀናት ልዩነት ” ራሷን በራሷ ገደለች !” መርዶ ነጋሪና ሬሳ ተቀባይና ላኪ ከመሆን ያለፈ ስራ የመብት ማስጠበቅ ስራ በቆንስል መስሪያ ቤቱ አለመሰራቱን ያጣቅሳሉ።  ከዚሁ ጋር በተዛማጅ ከአንድ ወር በፊት እዚያው ሊባኖስ “የአሰሪዋን ህጻን ልጅ አፍና ገድላለች! ” በሚል በፍርድ ውሳኔ ያልተሰጠው ጉዳይ በመገናኛ ብዙሃን ቀርቦ ነበር። በቀረበው መረጃ ስማችን ጎደፈ ። ዳሩ ግን የቀረበው መረጃ ኢትዮጵያዊቷ ወንጀለኛ አለመሆኗ ፍንጭ ሰጠ ፣ የራሳቸው ዜጎች ከሳሽ ባቀረበው መረጃና ማስረጃ ተመርኩዘው የተገላቢጦሹን አሳዩት ። ይህ ሁሉ ሲሆን የመንግስት ተወካዮቻችን ከሳሽን ወደ ተከሳሽነት የሚያሸጋግረውን መረጃ እንኳ ይዘው ታሳሪዋ ኢትዮጵያዊት እህት በዋስ መብቷ  ተጠብቆ በውጭ ሆና  እንድትከራከር አለማድረጋቸው በቆንስሉ የብርቱካን ክትትል ላይ የረባ ውጤት የማምጣት አቅም እንደሌላቸው ማሳያ ነው በማለት የሰላ ሂስና ወቀሳ ያቀርባሉ ።
የተስፈኞቹ ኢትዮጵያውያን አስተያየት …
    ” በቤሩት የቆንስል መ/ቤት ከበፊቱ የተሻለ ለውጥ ይታያል! ”  ያሉኝ ወገኖች ፣ ለውጥ ለመምጣቱና ለመታየቱ የሚያቀርቧቸው ጥቃቅን የቆንስል ግልጋሎት አሰጣጥ መረጃዎች ናቸው ።  ያም ሆኖ የመስራት አቅሙ የላቸውም ያሉኝ  የሚያነሱትን ” …የከዚህ በፊቱን የአለም ደቻሳና ሌላው ሌላው አሳዛኝ የመብት ጥበቃ ጉድለት “ያለፈው አለፈ ፣ ይሁን !”  ቢባል አሁን ድረስ እንዳልተሻሻሉ ብዙ ማሳያ አለ። ከወር በፊት  በነፍስ ግድያ ወንጀል ያለ ተጨባጭ መረጃ የታሰረችውን እህት ቆንስሉ አያማክሯትም ። ለዋስ መብቷን አላስጠበቁላትም።  ” በማለት “የቀረበውን የሰላ ሂስ ” ለውጥ አለ! ” ባዮች በተጨበጠ መከራከሪያ መላሽ ለመስጠት አልተቻላቸውም ።  ብቻ የቀረበውን ወቀሳ ሳያስተባብሉ ” በለውጥ ተስፋ ከማድረግ የተሻለ ነገር የለም! ”  በማለት የቆንሰል መ/ቤቱ የብርቱካንን ጉዳይ በቅርብ ተካታትሎ ውል እንደሚያስይዘው ያላቸውን ተስፋ አጋርተውኛል  !  …ቀጣዩ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ቢቸግርም ዛሬ የእህት ብርቱካንን በአሰቃቂ ሁኔታ መውደቅና ከከፋ አደጋ መትረፏ በሊባኖስ ቤሩት ካሉት ባለፈ በአለም ዙሪያ ሆነን ጉዳዩን በቅርብ ለተከታተልን ሁሉ እፎይታ ሆኗል  … ተመስገን ነው !  እናም ” ያገባናል ” ባዮች በእህት ብርቱካን ሰናይ ዜና ተደስተን ፊታችን ወደ ሌላዋ ግፉዕ ማዞር ግድ ብሎን  ወደ አልማዝን እንርዳ ” ዘመቻችን ፊታችን መዞራችን እውነት ነው!
የአካል ጉዳተኛዋ የአልማዝ ጉዳይ  …
   ህዳር 2 ቀን 2007 ምሽት በሊባኖስ  የብርቱካንን ከፎቅ መውደቅ አሳዛኝ ዜና ስሰማ በሌላኛው አረብ ሀገር በኦማን የመኪና አደጋ ደርሶባት የአካል ጉዳተኛ በሆነችው በእህት አልማዝ ጉዳይ ተወጥሬ ነበር።  ከተለያዩ አረብ ሃገራት እና በሃገር ቤት በማህበራዊ መገናኛዎች ተገናኝተን የተውጣጣን ወደ ስድስት የምንደርስ ወንድምና እህቶች  ባንድ እየመከርን ነው። አላማችን ከመረጃ ልውውጡ ባለፈ የወገናችን እንባ በተግባር መጥረጉም “ያገባናል !” ብለን ነው። የእህት አልማዝን እርዳታ ለማሳካት ማድረግ ስላለብን ጉዳይ እየመከርን ባለበት ወቅት ከቤሩት የብርቱካን አደጋና  “አትተርፍም!” የተባለ መረጃ ደረሰኝ … ሌላዋን የአረብ ሃገር ኦማን ጉስቁል እህት አልማዝን አሰብኳት …
    እህት አልማዝ የአረብ ሃገሩ ስደት ሲነሳ ከመንግስት ጀምሮ እስከ ግለሰብ የእኛ ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ ድጋፍ እህቶቻችን አደጋ ላይ ጥሏቸዋል።በህግ ሽፋን ተሰጥቷቸው በሚንቀሳቀሱ ወሮበላ ህግ ይጣሳል ፣  ለህዝብ ቆመናል በሚሉ የመንግስት ተቋማት ህግ ይጣሳል ፣  በመልካም አስተዳደር እጦት ፣ በሙስና  ህይወታችን ከፍቷል ፣ በተለያያየ መንገድ በአረበወ ሃገራት ለገነነው “ዘመናዊ ባርነት ” ድጋፍ እያደረግን እያበረታታን ነው ። ይህን ማለቴ ያለነገር አይደለም ፣ በአረቡ ሃገር በኦማን አካሏ ተሰናክሎ  የእኛን እርዳታ ጠባቂ የሆነችውን እህት አልማዝ አበሳ አስታውሼ ብዙውን አውጥቸ አወረድኩት …
    …አልማዝ አንድ ፍሬ ጉብል ሳለች ካላቻ ጋብቻ   ትዳርን ሳታውቀው መስርታ ልጅ ወልዳ ነበር ፣ ብዙም ሳይቆይ ጉብሏ እናት ሆነች ፣  ኑሮ አልሞላ አልሳካ ብሏት ወደ አረብ ሀገር ወደ ኦማን ተሰደደች … ሙሉ አካሏን ይዛ ለስራ ብላ በራ ከሄደችበት ኦማን ሞስካት ብዙም ሳትቆይ ለመኪና አደጋ ተጋለጠች ፣  ሆስፒታል ገባች ፣ ለወራት በህክምና ስትረዳ ብትቆይም አዕምሮዋ ፣ እግሯና እጇ ብሎም መላ አካሏ የከፋ ጉዳት ደረሰባቸው ፣ አይሆኑ ሆነች: (  ከሃገር ቤት ጀምሮ በአረብ ሀገራት ብርቱ መረብ ያላቸው ደላሎች እህት አልማዝ ሆስፒታል ከገባች በኋላም በጉዳቷ ለመጠቀም መስገብገባቸውን ጠልቆ መረጃ መሰብሰብ አሞኛል ፣ ዛሬ ወደ ክፉዎች ባለ ጊዜ ደላላ ባለጸጎች መሰሪ ምግባር ዳሰሳ አልገባም !  … እህት አልማዝ በተስፋ አቢሲኒያ በጎ አድራጊ ቡድን  አባላት ፣ በተለይም በመስራቹ ብርቱ ወንድም በወዳጀ በመሳይ አክሊሉ ( በኑቢያ ኩሽ ቀዳማዊ  ) እና በወዳጆቹ ብርታት  በአሳር በመከራ ሃገር ቤት ገብታለች ። መቄዶንያ የአረጋውያን ደጋፊ በጎ አድራጊ ቡድን ትብብርም መጠለያም ተሰጥቷታል ።  … እህት አልማዝ እዚህ ላይ ደርሳለች …  ይህም ተመስገን ነው!
   ይህም ሁሉ ሆኖ የአልጋ ቁራኛ የሆነችው አልማዝ ” ከህመም ጉዳቷ የምታገግምበት ተስፋ አለ ” በመባሉ የእርዳታ ስራ ተጀምሯል ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በተጀመረው እርዳታ እዚህ ሳውዲ አረቢያ ውስጥ ያለውን እርዳታ ለማስተባበር ሃላፊነት ከወሰድኩ ቀናት ወዲህ ወገኖች አልማዝን ለመርዳት ያሳዪት መነቃቃት እጅግ በጣም አበረታች ሆኖ ቀጥሏል። በኮንትራት ስራ በየአረቡ ቤት የሚሰሩ እህቶቸ የ “ነግ በኔ ” ብለው በሰብአዊነት እያደረጉት ያለው መተባበር ውስጥን ስሜት የሚያረካ ለመሆኑ እማኝ ለመሆን ታድያለሁ  !  የቤት ቆሻሻ ለመጣል መውጫ ቀዳዳውን ፈልገው ያላቸውን ለአልማዝ ለማካፈል ያሳዩት ቅንነት ፍጹም በቃላት ልገለጽ የማይቻለኝን ኩራት፣ በእህቶቼ እንድጎናጸፈው ዘንድ  ምክንያት ሆኖኛል  ! ድምጻዊ  ጆሲ እንደ ሀውስ ያን ሰሞን እርዳታ ለማሰባሰብ ሲሞክር በገጠመውና በሆነው በግኖ ይመስለኛል   ” ለመስጠት መሰጠት ያስፈልጋል! ”  ማለቱ በእኔም ላይ ደርሶ  እውነት ነው ብያለሁ  ! ለእኔ እርዳታ ማድረግ ትርጉሙ ገንዘብ መስጠት ብቻ አይደለም ፣ ቀና ማሰብ ፣ መረጃ መለዋወጥ ፣ ሌላ ተዛማች ተጎጅውን የሚደግፍ ስራ መስራት ፣ የሚረዳን አለመቃወም ፣ ገንዘብ  ከመስጠት ባለፈ ለተጎጅው ወገን ወገናዊ አብሮነት  ፍቅር መግለጫ ነው… ባይ ነኝ  !
    ለማንኛውም ብርቱካን በሊባኖስ ተረፈች ፣ እሰየው ነው!   እህት አልማዝ በኦማን ተሰናክላ እንዳትቀር ወገናዊ ትብብራችን ትሻለችና እናስብበት !  በዚህ የበጎነት መንገድ በመጓዝ በጠና የተጎዱ ወገኖቻችን  በመደገፍ ልንታደጋቸው ካልቻልን ከንፈር መምጠጡ ብቻ እንዳላዋጣን ከእኛ በላይ የሚያውቀው የለም ! እናም የዜጎቹን መብት እንዲያስከብር መንግስትን ስንወተውት የዝሆን ጀሮ ሰጥቶ አልሰማን ቢልም ጩኸት በደላችን እስኪሰማ እየጮህንም ቢሆን በመደጋገፉ የተጎዱትን እየነቀስን በማውጣት የቻልነውን መስራት የዜግነት ውዴታ ግዴታ ነው ባይ ነኝ  !
ሁሉም ለበጎ ነው  !
ነቢዩ ሲራክ
ህዳር 5 ቀን 2007 ዓም

Tuesday, November 11, 2014

ታላቅ ሕዝባዊ የውይይት መድረክ በአምስተርዳም ከተማ * አበራ የማነ አብ * ዶ/ር አረጋዊ በርሔ እና ዶ/ር መላኩ በሚገኙበት

የፊታችን ቅዳሜ ኖቬበር 15 ቀን 2014 ከ 14:00- ጀምሮ
አድራሻ: 1e Helmersstraat 106, 1054 EG Amsterdam next to VENA office
EthioAmsterdam
-- Ze-Habesha Website may contain advice, opinions, and statements of various information and content providers. The Website neither represents nor endorses the accuracy of information or endorses the contents provided by external sources. All blog posts and comments are the opinion of the authors.--

“የምጣዱ እያለ የእንቅቡ ተንጣጣ”

አገሬ (ከስዊድን)፣ 2014-11-05
ይህን ፅሁፍ ለመፃፍ ያነሳሳኝ ዋናው ምክንያት በድረ-ገጽ ላይ ”ፕሮፌሰር መስፍንን ለቀቅ” በሚል ርዕስ በአቶ አንተነህ መርዕድ የተፃፈው ”አገም ጠቀም” የሆነና ሚዛናዊነት የጎደለው መጣጥፍ ከመቸውም በበለጠ ስለከነከነኝ ነው።
Pro Mesfin
አቶ አንተነህ እንዳሉት አንደኛ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም አይደለም ለራሳቸው፣ ለሌላም የሚተርፍ አንደበት አላቸውና ራሳቸው መልስ ይስጡ በማለ፤ ሁለተኛ ትልልቅ አገራዊ ጉዳይ እያለ በዚህ ጠባብ ነገር መጠመድ ለማን ይበጃል በሚል ቢተውት የተመረጠ ነበር። ነገር ግን ያን በማለታቸው ልክ አለመሆናቸውን አምነውበት ለንባብ ያበቁት መጣጥፍ ለፕሮፌሰር መስፍን ለመወገን ሲሉ ብቻ የአማራውን ነገድ «አለ ወይስ የለም?» ማለት እንደማይረባ ጉዳይ ቆጥረውታል። ነገር ግን በተለይ በአሁኑ ሰዓት አማራ እንደሰባዊ ፍጡር ሳይቆጠር ደመከልብ ሆኖ አጥንቱን ከስክሶ ደሙን አፍስሶ ባቆማት አገር እንዳይኖር በሚደረግበት ወቅት ”እንቶ ፈንቶ” ሲሉ ማጣጣል ትልቅ ስህተት ይመስለኛል።
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ባቋቋሙት «የኢትዮጵያ ሰብዐዊ መብት ጉባኤ (ኢሰመጉ)»፣ እርሰዎ እንደሚሉትና የኢትዮጵያም ህዝብ ተረድቶት እንደነበረው በወያኔ አገዛዝ ለሚደርሰው ገፍና በደል አለኝታ ለመሆን አልነበረም። ይልቁንም ከፕሮፌሰር መስፍን ከአንደበታቸው እንደሰማነው ከሆነ ኢሰመጉን ያቋቋሙት ወያኔን ለመርዳት መሆኑን ሰለሰማን የርስዎ የመከራከሪያ ነጥብ ”ከባለቤት ያወቀ ቡዳ ነው” የሚሉት አይነት ይሆንብዎታል። አቶ አንተነህ በውነቱ እርሰዎን ቅር ማሰኘትም ሆነ ፕሮፌሰር መስፍንን የመዝለፍ ሀሰብ በ አይምሮየ የለም ግን ፕሮፌሰር መስፍን የሚነግሩንና የሚሰሩት ነገር ካልተጣጣመ ቃልን ከተግባር በማጣጣም የምናስታርቀው ምን ብንል ነው፧ ፍርዱን ለርስዎ እተዋለሁ።
የአማራን ጉዳይ በተመለከተ አቶ አንተነህ እንደተረዱት ፕሮፌሰር መስፍን የወያኔውን መሪ መለስ ዜናዊን «አማራ የለም» ብለው «ዘረኝነት እንዳይስፋፋ አደረጉ» የሚል አስተያየትዎ እደተጠበቀ ሆኖ፣ እኔ ደግሞ ከአንድ ታዋቂ ግለሰብ መወቀስ ይበልጥ የኢትዮጵያ አገራችንና በህዝቧ ላይ የወደቀው የመከራ ቀንበር እጅጉን ያመኛል። ከወያኔ ወደ ስልጣን መምጣት ትንሽ ቀደም ብሎ ጀምሮ ያደረጓቸውን ድርጊቶች ላስታውስዎ፦
ፕሮፌሰር መስፍን እኤአ 1991ዓ.ም ለንደን ላይ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን በራሳቸው ፈቃድ ወክለው ከነወያኔና ከነኦነግ ጋር ተደራድረው ድጋፍ በመሆን አስገቡዋቸው።
የኢትዮጵያ ህዝብ «መጣብን» ብሎ የፈራውን የዘረኝነት አገዛዝ የተከበሩ ፕሮፌሰር መስፍን በግልፅ በአደባባይ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በተለይም አማራን እንደህዝብ ከሚጠላው የወያኔ መሪ ጋር በማነጋገራቸው ወያኔን እውቅና እንዲያገኝ አደረጉ።
ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ፣ የዘረኝነት አባዜ ይዟቸው ሳይሆን ተገደው፣ ለአማራ ህዝብ የተደገሰለት ድግስ አደገኛ መሆኑን ስለተረዱ ብቻ የኢትዮጵያን ህዝብ ያካተተ የአማራ ድርጅት (ተገደው በግድ በዘር መደራጀት ስለነበረባቸው ያለበለዚያ ግን እውቅና በወያኔ ስለተነፈጉ) ሲመሰርቱ አሁንም ፕሮፌሰር መስፍን በአማራ ላይ የሚፈፀመውን በደል ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው አማራ የሚባል ነገድ የለም በሚል ጎዳና ስለተሰለፉ ህዝቡ በተለይም አማራው በአንድ ልብ እንዳይቆም በደካማ ጎኑ ስለመጡበት ኢትዮጵያን እያለ ከተገንጣይና ካስገንጣይ ጉያ እንዳይወጣና ጠንክሮ እንዳይታገል እውቅናቸውን ተጠቅመው በሚያንፀባርቁት የተዛባ አስተሳሰብ ህዝብም አገራችንም ተጎድተዋል ።
የቅንጅት መሪዎች በፈጠሩት አለመግባባት የኢትዮጵያ ህዝብ ፕሮፌሰር መስፍን አስታራቂ ሀሳብ አምጠተው ቅራኔውን ይፈቱታል ተብለው ሲጠበቁ እሳቸው ለማንም የማይበጅ ምክር በመምከራቸው ህዝብ የሳቸውን ቃል ተከትሎ ቅንጅትን እንዳያንሰራራ አድርጎ አፈረሰ።
«አማራ የለም» ከማለት አልፈው «በአርባ ጉጉ የሞተው ኦሮሞ ነው» ማለታቸው ሟች በሌለበት ገዳይ አይኖርምና የአማራን ደም ደመከልብ እንዲሆን ትብብር አድርገዋል።
ለመሆኑ እኔ እንዲህ ብዬ እንደማስብና የዚህ አይነት ሀሳብ ያለን በሚሊዮን የምንቆጠር አማሮች መሆናችንን ቢረዱ ምን ይላሉ?
አቶ አንተነህ እርሰዎ እንዳሉት ፕሮፌሰር መስፍን «ትልቅ ሰው፣ አዋቂ፣ የተከበሩና የእድሜ ባለፀጋ» በሚለው ቃል እስማማለሁ። ነገር ግን «ደምመላሽ» የሚለው ቃል ሲወጣ አባባሉ ከቅንነት ይሆናል የሚል ግምት ቢኖረኝም የተጠና አልመሰለኝም። «ደምመላሽ» መሆኑ ቀርቶ የአማራ ህዝብ ተቆርቋሪ አለመሆናቸውን ደሙ ደመ ከልብ ሁኖ አንዲቀር የተወሰነበት «የለህምና አልሞትክም» የሚሉት አማራ ይመሰክራል።
አቶ አንተነህ ስለ አቶ ተክሌና ስለእርስዎ ግንኙነት ሲፅፉ ” ….ብዙ ህዝብ በሚርመሰመስበት የደመቀ በአል መሃል የሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት መሪ የሆኑትን አቶ ተክሌ የሻውን አገኘኋቸው። ደስ ብሎኝ ራሴን ካስተዋወቅሁ በኋላ በወጋችን መሃል በቅርቡ ከወጣው መግለጫቸው አምስት ገጽ እውነት ውስጥ ጨዋነት የጎደለው ስድብ ተገቢ እንዳልነበር ነገርኳቸው። የሰማሁት መልስና ለፕሮፌሰሩ ያላቸው ጥላቻ አስደነገጠኝ። ለአማራው ህዝብ መብት ቆሜያለሁ ብለው አደባባይ የወጡ እኒህ ሰው አንዱን ታላቅ ወገናቸውን በሰብዕናቸው ገብተው ሲዘልፉ መመልከት ዓላማቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ሆኖ አገኘሁት። ስልሳዎቹ ውስጥ የሚሆኑ እኒህ አዛውንት ሌላው በእድሜ፣ በእውቀትና በተመክሮ ለሚበልጧቸው ክቡር ሰው የሚሰጠውን የጨዋ አማራ ባህል ከውስጣቸው አላየሁም። ስለሆነም ውይይቴን ብቀጥል የበለጠ ህሊና የሚያቆስል ነገር እንደምሰማ በመገመት ተሰናበትኋቸው። ” ሲሉ አስነብበውናል።
አቶ ተክሌን ሲያገኙ ደስ መሰኘዎትን በዚህ አንቀፅ ቢገልፁም ከላይ በአንቀፅ 4 ላይ ደግሞ ”…የብዙዎችን ላቆየውና በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ካንድ ወገን የሚሰነዘረው ከባህላችን ውጭ የሆነ ዓላማው ግልጽ ያልሆነ ስድ በሚያሰኝ የመንገድ አዳሪ ቋንቋ የስድብ ውርጅብኝ በኒህ አዛውንት አባት ላይ ሲወርድባቸው ዝም ብሎ መመልከቱ ለህሊና ይከብዳል…” ሲሉ ቁጭትዎንና ቁጣዎትን ገልፀው ስለነበር አቶ ተክሌን ሲያገኙ የተደሰቱት ለምን እንደሆነ ለመረዳት አዋቂ መጠየቅ አያስፈልግም።
እንደርስዎ አገላለፅ አቶ ተክሌ በጥላቻ የተሞሉና ስነምግባር የጎደላቸው እንደሆኑ ተርከዋል። ለነገሩ አቶ ተክሌ ራሳቸውን መከላከል ስለሚችሉ አስፈላጊ ሆኖ ከታያቸው መልስ የሚሰጡበት ጉዳይ ይሆናል። ነገር ግን እኔን ያልገባኝ ነገር አቶ ተክሌ ጋር ስትነጋገሩ የተናገሩት ቃል አፀያፊ ከሆነ ቃላቶቹን በፅሁፍዎ ላይ በማስፈር መግለጫውን በተቹበት መልክ ቢያካትቱት የአንባቢውን የግንዛቤ አድማስ ስለሚያሰፉት አንባቢው በራሱ ሚዛን መዝኖ ለፍርድ በበቃ ነበር።
በተረፈ« በጥላቻ የተሞሉና ስነምግባር የጎደላቸው ስለሆኑ ለአማራው ህዝብ መቆማቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ሆኖ አገኘሁት» የሚለው ”ሾላ በደፈና” አባባልዎ፥ «ሞረሽ ወገኔ አላስፈላጊ ድርጅት ነው። አማራ መደራጀት የለበትም» ከማለት ተለይቶ አይታይም። ስድብ ነውር ከሆነ ነውር መሆን ያለበት ከተሳዳቢው አንደበት ሲወጣ እንጅ ተቀባዩ ላይ የሚያደርሰው ጫና ወይም የተሰዳቢው ማንነት ሚዛን ውስጥ እየተቀመጠ አለመሆኑን መዘንጋትዎ አስገርሞኛል። እንዲህ ለማለት ያበቃኝ ደግሞ እርስዎ ”ክደትና መሳት” የሚለውን ቃል በማስረጃነት በማቅረብ ያስነበበውን የሞረሽን መግለጫ ስድብ ካሉ በኋላ በአቶ ተክሌና በሞረሽ ላይ ”ስድ በሚያሰኝ” ”የመንደር አዳሪ ቋንቋ” በማለት አቶ ተክሌን «ስድ» ከማለት አልፎ የሞረሽ ወገኔን አባላትና ደጋፊ ሁሉ «የስድ ስብስብ» እንደማለት የስድብ ውርጅብኝ ሲያዘንቡ ውነቱን ተናገርኩ እንጅ አልተሳደብኩም ሊሉ ይሆን?
ለነገሩ «የወደቀ ግንድ ምሳር ይበዛበታል» ነውና የሚሞተው የሚሳደደው የሚፈናቀለው አማራ እንደ ህዝብ ከ34 ሚሊዮን በላይ ሲሆን፣ ያ ህዝብ ለሚደርስበት በደል ተጠያቂ እንኳዋን እንዳይኖር «የለህም» እያሉ አደባባይ ወጥተው የሚሞግቱት ፕሮፌሰር መስፍን ሳይወቀሱ፣ «የለም ማለት ስህተት ነው በደል የሚደርስበት ወገን ከተካደ በደል ፈፃሚ ነፃ ይሆናል» ያለውን ወገን ለማዳከም ብዕር ማንሳት የሚያሳዝን ክስተት ነው። ለነገሩ እርሰዎ የኢትዮጵያ ጀግኖች ብለው በፅሁፍዎ የደረደሩዋቸው ሁሉም ለኢትዮጵያ አንድነት የተሰለፉ ጀግኖች ናቸው ብየ ስለማላስብ የእርስዎም ሰልፍ ከወዴት እንደሆነ አልገባኝምና ልተወው።
ለማንኛውም እርስዎ ከፐሮፌሰር መስፍን በተለየ «አማራ» የሚባል ነገድ እንዳለና ያም ወገን የተለየ ግፍ እየተፈፀመበት እንደሆነ ውነቱን በመመስከርዎ አድናቆቴን ልቸርዎት እወዳለሁ። ምክንያቱም እርስዎ በፕሮፌሰር መስፍን ማንነትና ፍቅር ስለተሸነፉ፣ የሞረሽ ወገኔን መግለጫ በማጣጣልና «ፕሮፌሰርን በካሀዲነት ወነጀሉ» ብሎ የፕሮፌሰርን ስህተት ማደባበስ ብሎም ያላግባብ ደሙ የሚፈስ ወገን እንዳለ ማመን የተሳነውን ሰው «ደምመላሽ» በማለት ማሞካሸትዎ እንዳለ ሁኖ፣ «በፕሮፌሰር ተፃራሪ አማራ አለ፣ በደልም እየተፈፀመበት ነው፤» ብለው ሲቆሙ ሳይ ታዲያ ምነው የሚያከብሩዋቸውና የሚያደንቋቸው ፕሮፌሰር ሲሳሳቱ በክብር እንዲያስተካክሉ አልጠየቋቸውም ያሰኛል።
እንደእኔ ግንዛቤ ፕሮፌሰር መስፍን በየጊዜው ብዙ ጠቃሚም ጎጅም ፅሁፍ ለንባብ አብቅተዋል። ለዚህም የኢትዮጵያን ህዝብ «ሆዳም» ብለው መዝለፋቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። ለአማራውም «አለሁ» ሲል «የለህም»፣ «እየተገደልኩ ነው» ሲል «የት አለህና?» በማለት 23 አመት ሞግተውታልና ለመግለጫው መልስ የሚያስፈልግ ቢሆን እርስዎም እንደገለፁት እራሳቸው ፕሮፌሰር መልስ መስጠት ስለሚችሉ የእርስዎ ጥብቅና ” የምጣዱ እያለ የንቅቡ ተንጣጣ” እንድል ዳርጎኛል። ፕሮፌሰር መስፍን ነገዱን ሁሉ እየጠሩ እውቅና ሲሰጡ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ «አማራ የሚባል ነገድ የለም» ማለታቸው ግን እንቆቅልሽ ነው በማለት ሀሳቤን እቋጫለሁ።
ፀሀፊዋን agereamanu@yahoo.com ማግኘት ይቻላል።

ዝምታው ለምን ነው? (አንተነህ መርዕድ)

ዝምታው ለምን ነው?
ኢትዮጵያ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለችው።
  • መንግስት እንደድሮው መግዛት ተስኖታል
  • ህዝቡም እንደድሮው መገዛት ታክቶታል
  • የተቃዋሚው ቋንቋም እንደባቢሎኖች የተከፋፈለበት ወቅት ላይ ነን
  • ከዚያም ብሶ ሚድያው ታፍኗል።
ትግሉን በተደራጀ መልክ ዳር የሚያደርስ ጠርቶ ባልወጣበት ሁኔታ ህዝባዊ ዓመጽ ሊፈነዳ ጫፍ ላይ መድረሱን ለማወቅ ሊቅነት የሚጠይቅ አልሆነም። በዚህ ሁኔታ ዐመጽ ከተነሳም የሚከተለው ትርምስና እልቂት ቀላል ስላይደለ ንፁህ ህሊና ያለው ሁሉ በግልፅ ታይቶት መፍራት አለበት። ይህ ፍርሃት በጎ ፍርሃት ሊሆን የሚችለው ወደ መፍትሄው መሄድ ካስቻለን ነው።
በእንደዚህ ዓይነት ፈታኝ ወቅት ነፃ ሚድያ ግዙፍ ሚና አለው።
  • ህዝብ ተገቢ መረጃ እንዲኖረውና እርምጃው በእውቀት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን በማድረግ
  • በእንደዚህ ዓይነት ቀውጢ ወቅት ብቅ የሚሉ የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎች ህዝባዊ ትግሉን ወደ ተለየ አቅጣጫ እንዳይመሩትና ለሌላ ተስፋ አስቆራጭ ክስተት እንዳይዳርጉት በማጋለጥ (ይህ ለታሪካችን አዲስ አይደለም)
  • የህዝቡን የጋራ ብሶትና የጋራ ተስፋውን አጉልቶ በማውጣት ወደ ብሄራዊ መግባባት ለመድረስ መገናኛ ብዙሃን ከባድ ሃላፊነት አለባቸው።
ስለሆነም አምባገነን ስርዓቱ ሚድያውን ለማዳከም ያሰደደንና በሁሉም የዓለም ክፍል ተበትነንና ተደላድለን የምንኖር ሆንነ አሁንም በወከባው ውስጥ ያለነው ተረጋግተን የምንነጋገርበት ወቅት አሁን ነው። የሃሳብ ልዩነቶች ሊኖሩን ይችላሉ። እንዲያውም “የሃሳብ ልዩነቶች ለዘለዓለም ይኑሩ”የሚለውን መፈክር ልናነግበው የሚገባ ነው። ነገር ግን የሃሳብ ልዩነት መኖሩ የሃሳብ ግብይትን ያቆመው እለት የሃገር ውድቀት እሙን ነው። የሃሳብ ልዩነት የሃሳብን ግብይትና መቀራረብን ሊያቆመው አይገባም። (ኮሙኒኬት የማያደርጉ ኮሙኒኬተርስ) ከመሆን እንውጣ።
ሀገርን የማዳን ቃል ኪዳን በሁላችንም ዘንድ እንዳለ ይታወቃል። ችግሩ ማን ይጀምረውና እንዴት ይጀመር የሚለው ነው።
  • የታሰሩ ወንድሞቻችን የሚከፍሉትን መስዋዕትነት በፀጋ ቢቀበሉትም የቤተሰቦቻቸውን ጫና የማቃለል የሞራል ሃላፊነት አለብን።
  • በጎረቤት አገሮች በስደት የሚሰቃዩ የሙያ ባልደረቦቻችን ያሉበትን ሁኔታ ያለፍንበት ሁሉ እናውቀዋለን። በችግሮቻቸው መድረስ ይኖርብናል።
  • ከሁሉም በላይ ግን ማንም ሳያስገድደን ለራሳችን ቃልኪዳን የገባነው ህዝብን ተመጣጣኝ መረጃ የመስጠት ሥራ እዚህ ደርሶ አላበቃም። እንዲያውም ተፈላጊነቱ እየጎላ ነው።
“ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ” የሚለው የህዝብ መፈክር ለተቃዋሚዎች ብቻ ሳይሆን ለጋዜጠኞችም ጭምር ነው። በነጠላ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ የማይናቅ ቢሆንም በጋራና በተቀናጀ እንደሚደረገው ፈጣንና አመርቂ ውጤት አያመጣም። አገሪቱ ያለችበት ፈታኝ ሁኔታ ፋታ የሚሰጥ ባለመሆኑ በተገኘው መንገድ ሁሉ ግንኙነቱ ይቀጥልና በህብረት ወደ አንድ አቅጣጫ እንንቀሳቀስ። ስለዚህም መነጋገር እንጀምር። “ባለቤት ካልጮኸ ጎረቤት አይደርስም” ነው ተረቱ። ህዝቡን እንዲረዳን የምንጠራው መጀመርያ ራሳችን ችግሩን አውቀን ስንንቀሳቀስ ነው። ለችግራችን እኛው መፍትሄ እንፈልግለትና በአገር ጉዳይም የማንናቅ የመፍትሄ አካል እንሁን። ዝምታው ለምን ነው?

ለሕዝብ የተላከን ምግብ ሊሸጡ ሲሉ የተያዙ የተባሉ 4 ባለስልጣናት ታሰሩ

አኩ ኢብን ከአፋር
ባለፈው ወር በአፋር ክልል በአሚባራ አካባቢ ህዝብ ላይ የደረሰው የጎረፍ አደጋን ተከትሎ ከ30ሺ በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች ከአካባቢው መፈናቀላቸው ይታወሳል። ለእነዚህ ወገኖች ከተለያዩ የእርዳታ ድርጅቶች እና ከመንግስት የተላከው እርዳታ በመንግስት ኃላፊዎች ለሙስና መዳረጉን ምንጮቻችን ከቦታው ዘግበዋል።
afar
ባለፈው ሰኞ ከአዋሽ ፋንቲ አሌ ወረዳ ወደ መትሃራ በመንግሥት ኃላፊዎች ተዘርፎ ሊሸጥ የነበረና ብዛቱ በውል ያልታወቀ ብዙ ኩንታሎች የእርዳታ እህል በመኪና ተጭኖ ሲንቀሳቀስ ከሌሊቱ 6:00 ላይ በህዝብ ተቆማ በቁጥጥር ስር ውሏል።
እነዚህ ባለስልጣናት ለጊዜው የታሰሩ ሲሆን ስማቸው ከዚህ በታች በዝርዝር ይቀመጣል፦
1 – አቶ አደም መሀመድ የአዋሽ ፋንቲዓሌ ወረዳ ምክትል አስተዳደር
2 – አቶ አባህ አባ የግብርና የገጠር ልማት ቢሮ ኃላፊ
3 – አቶ ሙስጣፋ ሀሳን የአዋሽ ወረዳ የአብዴፓ ፓርቲ ቢሮ ኃላፊ፤
4 – ወ/ሮ ፋጡማ እብራሂም የንብረት ክፍል ቢሮ ኃላፊ ሲሆኑ እነዚህ ባለስልጣናት በጊዜው ለፖሊስ በሰጡት ቃል «የተያዝነው ጊዜ ባለፈበት እህልና እቃ ሲሆን ለመንግስትም ለመመለስ እየተንቀሳቀስን በነበረበት ሰአት ነው» ብለዋል ሲሉ ምንጮች ፓሊስን ጠቅሰው ዘግበዋል።
ይህን የህዝብ እርዳታ እንዲሸጡ ያስገደዳቸው የአፋር ክልል አፈጉባኤ የሆኑት አቶ መሀመድ አንበጣ ወደ አዋሽ በመሄድ ለወረዳው ካቢኔዎች ገንዘብ አምጡ ብለው 20,000 ብር ቢሰጧቸውም ጨምሩ ሰላሏቸው የህዝብ እርዳታ እንዲሸጡ መገደዳቸው አንድ ስሙ ሊገለፅ ያልፈለገ ሊንደብቅለት የመንግስት ሰራተኛ የላክለን መረጃ ያስረዳል

“እስሬ፣ ጥሩ ክርስቲያን፣ ሰውና ታጋይ አድርጎኛል” – ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ከቃሊቲ እስር ቤት

‹‹እስሬ፣ ጥሩ ክርስቲያን፣ ሰውና ታጋይ አድርጎኛል››
‹‹ኢህአዴግ በጭቆና ውስጥ ጸጥ ብሎ የተቀመጠን ሕዝብ እየቆሰቆሰ ነው››
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ከቃሊቲ እስር ቤት
ከኤልያስ ገብሩ
ትናንት፣ በዕለተ ዓርብ እኔ እና የዕንቁ መጽሄት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ከሆነው ፍቃዱ ማህተመወርቅ (ባሪያው) ጋር ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋንና ፖለቲከኛን አቶ አንዷለም አራጌን በቃሊቲ ተገኝተን ጠይቀናቸው ነበር፡፡
Eskinder-Nega
ሁለቱም ፍጹም ሰላማዊነት፣ እርጋታ፣ ትህትናና ፈገግታ አብሯቸው ነበር፡፡ ያው ሁለቱንም በአንድ ጊዜ ማናገር ስለማይቻል ተነጣጥለን ማውጋት ግዴታ ነበርና ጥቂት ከአንዷለም ጋር ከተጨዋወትን በኋላ ከእሴው ጋር አወጋን፡፡
እስክንድር የፊታችን ማክሰኞ፣ ሕዳር 2 ቀን 2007 ዓ.ም ፍርድ ቤት ስለምቀርብበት የክስ ጉዳይ አንስቶ የሚሰማውን ነገረኝ፤ ጠንካራ ምክርም ለገሰኝ፡፡ የክሱ እንደምታንም ባላሰብኩት መንገድ አስረዳኝ፡፡ (ይህ ግላዊ ምክር ስለሆነ ልለፈው)
እስክንድርን ከታሰረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ ጠይቄዋለሁ፡፡ ስለራሱ መናገር አይፈልግም፡፡ ግን ትናንት ባተለመደ መልኩ ስለራሱ ልቡን ከፍቶ አወጋኝ፡፡ በተለይ ስለፈጠሪው! ሃሳቡን እንዲህ አስቀመጥኩት፡፡
‹‹ኤልያስ፣ እስር ለእንደእኔ አይነት፣ ቤተሰብ ለመሰረተ እና ልጅ ለወለደ ሰው ትንሽ ሊከብድ ይችላል፡፡ ስለባለቤትህ እና ልጅህ ሁሌ ታስባለህ፤ ኃላፊነት አለብህና! ነገር ግን፣ በሌላ መልኩ፣ በመታሰሬ ሎተሪ እንደወጣልኝ አድርጌ እቆጥረዋለሁ፡፡ እስሬ፣ ጥሩ ክርስቲያን፣ ሰውና ታጋይ አድርጎኛል፡፡ አሁን በጣም ሰላም ይሰማኛል፡፡ ክርስቶስን በጣም እንዳውቀው አድርጎኛል፡፡ ፍቅሩ ምን ያህል እንደሆነም ገብቶኛል፡፡ ይህን በመረዳቴ በጣም እድለኛ ነኝ፡፡ መታሰሬ መጽሐፍ ቅዱስን በደንብ እንዳነብ አስችሎኛል፡፡ ባልታሰር ኖሮ እንዲህ የምሆን አይመስለኝም፡፡ ለሌሎች ነገሮች ቅድሚያ እሰጥ ነበር፡፡ ግን ቀዳሚው መሆን ያለበት አምላክህን ማወቅ ነው፡፡ ነገ፣ ይበልጥ የተሻልኩ ሰው እሆናለሁ፡፡ …››
እስክንድር ከላይ ከጠቀስኩላችሁ ሀሳብ አስከትሎ በአሁን ወቅት በሀገሪቷ ላይ ስላለው ጭቆና በጠባቂ ፖሊሶች ፊት ሲናገር ያ ፍጹም የተለመደ ድፍረቱ እና ትህትናው አብሮት ነበር፡፡ እንዲህም አለ፡-
‹‹የስደት፣ የእስርና የክስ መብዛት ሥርዓቱ ያለበትን ከባድ ችግር በግልጽ ያሳያል፡፡ ኢህአዴግ በጭቆና ውስጥ ጸጥ ብሎ የተቀመጠን ሕዝብ እየቆሰቆሰ ነው፡፡ (ከዚህ ጋር በተያያዘ አፈታሪክ ነው ብሎ አንድ ሀገራዊ ምሳሌ ነገረኝ) ይህ ነገ በራሱ ላይ መዘዝ ያመጣበታል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፣ ሥርዓቱ እንዲህ በማድረጉ (የስደት፣ የእስርና የክስ መብዛት) ነገ ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲፈጠር ሳይፈልግ እና ባለማወቅ አበርክቶት እያደረገ ነው፡፡ አለመረጋጋት ይህን ይፈጥራል፡፡ …››
እስክንድር ውስጠ ወይራ ንግግር ተናግሯል፤ ልብ ያለው ልብ ይበል!

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር

ወያኔ/ኢሕአድግ እና ምርጫ 2007

በያዝነው 2007 ዓ.ም በግንቦት ወር ለሚካሄደው አገራዊ ምርጫ በገዢው ፓርቲ እንዲሁም በተቃዋሚ ፓርቲዎች ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ ሲሆን ምርጫ ቦርድም ምርጫውን በበላይነት ለመምራት ቁሳዊና ቴክኒካል ዝግጅቶችን እያደረገ መሆኑን ከገዢው ፓርቲ ልሳን ከሆነው EBC በተደጋጋሚ እየተሰማ ነው፡፡ ይህን ተከትሎ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል መከፋፈሎች እንዲሁም አለመረጋጋቶች እየተስተዋሉ ሲሆን ለዚህም ምክንያቶቹን በእርግጠኝነት መግለጽ አዳጋች ቢሆንም ካለፉት የምርጫ ተሞክሮዎች በመነሳት የገዢው ፓርቲ ረጃጅም እጆች እንዳለበት መተንበይ አዳጋች አይሆንም፡፡
በዚህ በያዝነው አመት የሚካሄደውን አገራዊ ምርጫን ለመተንበይ በቅድሚያ ከዚህ ቀደም የተካሄዱትን አገራዊ ምርጫዎች በወፍ በረር ቅኝት ማየቱ የግምቱን ይዘት ጠንካራ ያደርገዋል፡፡ በዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ እምነት እንዲሁም በተለያዩ ጊዜያቶች ከሚወጡ ጥናታዊ ጽሁፎች ለመረዳት እንደሚቻለው በአገራችን ተስፋ ሰጪ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ተካሂዷል ተብሎ የሚታሰበው በ1997ዓ.ም በተካሄደው አገራዊ ምርጫ ነው፡፡ ለዚህም በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩትም በዋነኛነት ገዢው ፓርቲ በወቅቱ ለነበሩት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የነበረው ዝቅተኛ አመለካከት (በወቅቱ ቅንጅት የምርጫው ምዝገባ ሊጠናቀቅ ጥቂት ጊዜያት በቀሩበት ወቅት ቅንጅት መፍጠሩን ልብ ይለዋል) እንዲሁም የምዕራባዊያኑን ቀልብ በመሳብ አገሪቷ ለዴሞክራሲያዊ ግንባታ እየተጋች መሆኗን ለማሳየትና ከፍተኛ ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት ሲሆን ከዚሁ ጋር ተያይዞም በወቅቱ በመንግስት ይዞታ ስር የነበሩትን የንግድ ተቋማት ወደ ግል ይዞታነት በማዞር (privatization) መንግስት ቀደም ሲል ይተችበት የነበረውን ሶሻሊስምን ወደ ጎን በመተው ዘመኑን መምሰሉን በማሳየት ምዕራባዊያንን ለማሳመን የሚተጋበት ወቅት ስለነበረም ጭምር ነው፡፡ ስለሆነም ያለፉትን የምርጫ ሂደቶችን ለመገምገም ምርጫ 97 እንደመነሻ (base year) በመውሰድ ገዢው ፓርቲ እንዲሁም ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫው ላይ የነበራቸውን ሚና በሚከተለው መልኩ ለመዳሰስ ወደድኩኝ፡
ምርጫ 97
ኢሕአድግ 1997ቱ ምርጫ ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ለተቃዋሚዎች በነበረው ዝቅተኛ ግምት ፤ ምርጫውን በበላይነት አሸንፋለው ከሚል የተሳሳተ ግምት እንዲሁም የምዕራባዊያኑን ቀልብ ለመግዛት የዲሞክራሲ በሩን ገርበብ አድርጎ በመክፈቱና ለምርጫው ቅስቀሳ ከዛ በፊት ይሰጡ ከነበሩት የመከራከሪያ ሰዓት በአንጻራዊነት ሰፊ ጊዜ ለተቃዋሚዮች በመስጠቱ ህዝቡ የሁሉንም ፓርቲዎች ፕሮግራም የሚሰማበት እድል ፈጥሯል፡፡ በወቅቱ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች አንጻር ኢሕአድግ በፖለቲካ ልምድ እንዲሁም በህብረተሰቡ ተሰሚም ታዋቂም ስለነበር ገዚው ፓርቲ ምርጫውን በበላይነት ለማጠናቀቅ ሙሉ ዕምነት ነበረው ሆኖም ግን ወደ ምርጫው ቅስቀሳ ሲገባ እየታየ የመጣው ፈጽሞ ያልተጠበቀና ገዚው ፓርቲ የከፈተውን የዶሞክራሲ በር ለመዝጋት አስቸጋሪ የነበረበት እንዲሁም ወደ ኋላ ማፈግፈግ የማይችልበት ወቅት ነበር፡፡
በተቃዋሚዎች በኩል በወቅቱ የምሁሮች ስብስብ ተብሎ ሲሞካሽ የነበረው ቅንጅት የገዢው ፓርቲ ጠንካራ ተፎካካሪ ነበር ለዚህም ምክንያቶቹ በርካታ ቢሆኑም ድርጅቱ በውስጡ ጉምቱ የፖለቲካ አዋቂዎችን ማካተቱ ፤ ድርጅቱ በመረጃ የተደገፈ ጠንካራ ክርክር ማካሄዱ፤በምርጫ  ክርክሮች ወቅት ሚያቀርባቸው ተከራካሪዎች ኢሕአዴግ ከሚያቀርባቸው የተሻሉ መሆናቸው፤ የማህበረሰቡን የልብ ትርታን መሰረት ያደረጉ ጠንካራ ትችቶችን  በገዢው ፓርቲ ላይ በማቅረባቸው (የዘር ፓለቲካን  ፊትለፊት  በመተቸታቸው ፤ ሙስናን በመረጃ አስደግፈው በማጋለጣቸው፤ በገዢው ፓርቲ  የተንቋሸሸውን  ስራ አጥ ወጣቱን ስራ ፈጣሪ ለማድረግ ንድፈ ሃሳብ ማቅረቡ ከብዙ በጥቂቱ ሚጠቀሱ ናቸው) ፤ ዘርን መሰረት ያላደረገ  የፖለቲካ አቅጣጫ (political ideology) ይዞ መቅረቡ ፤ ድርጅቱ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችን ያቀናጀ መሆኑና ሌሎች ምክንያቶች ተደማምረው የምርጫውን ግምት አፋልሰውታል፡፡
ኢሕአዴግን ለውድቀት የዳረጉ ውስጣዊ ምክንያቶች
ከላይ በጠቅላላው ለማሳየት እንደተሞከረው የምርጫ 97 ለተቃዋሚዎች የፈጠረውን እድልና ገዢው ፓርቲ ላይ ያስከተለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ሲሆን ከዚህ በታች የምንመለከተው በድርጅቱ ውስጥ የነበረውን ውስጣዊ ችግሮችን ይሆናል፡
1.ከመጠን ያለፈ በራስ መተማመን
ኢሕአዴግ ከ1997 በፊት በነበሩት ምርጫዎች ተቀናቃኝ የነበሩትን በቀጥታ እንዲሁም በተዘዋዋሪ ካዳከማቸው ከፊሎችንም ከበታተነ በኋላ አስጊ የፖለቲካ ተቃዋሚ ስላልነበረ በምርጫ 97 ፍጹም የበላይነትን ለመቀናጀት እምነት ነበረው ለዚህም ማሳይው ከሌሎች የምርጫ ጊዜያቶች በተለየ ሁኔታ ለተቃዋሚዎች ሰፊ የአየር ሽፋን መስጠቱ ፤ የተለያዩ በርካታ የመከራከሪያ መድረኮችን ማዘጋጀቱ ፤ ክርክሮቹ ቀጥታ የአየር ሽፋን ማግኘታቸው ሲሆኑ ባልተጠበቀ መልኩ ጠንካራ ሆኖ የቀረበው ቅንጅት እንዲሁም ሌሎች ተቃዋሚዎች እድሉን በሚገባ ስለመጠቀማቸው በወቅቱ የነበረው የምርጫ ውጤት አመላካች ነው፡፡
2.ጠንካራ ተከራካሪ ያለማዘጋጀት
በተለያዩ የክርክር መድረኮች ኢሕዴግን ወክለው የሚቀርቡ ተከራካሪዎች ከተቃዋሚዎች ተሸለው ባለመገኘታችው እንዲሁም የሚያቀርቧቸው መከራከሪያዎች በመረጃ የተደገፉ አለመሆናቸውና  በተደጋጋሚ በተለያዩ የመንግስት ሚዲያዎች ሲሰሙ የቆዩ በመሆናቸው አሰልቺ ነበሩ፡፡ በወቅቱ በተቃዋሚዎች የሚቀርቡትን ፈታኝ ጥያቄዎች በበቂ ሁኔታ የሚመልስ ባለመኖሩ ኢሕአዴግ እየኮሰሰ ሌላው እየገነነ የመጣበት ሁኔታ እንደነበር የሁላችንም የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፤፤
3.የአባላት ታማኝ አለመሆን
የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያመለክተው ኢሕዴግ በ1997 ምርጫ ወቅት ጠቅላላ ከ6 ሚሊዬን በላይ አባላት የነበሩት ሲሆን ይህንን አባላት በማሰብ ገዢው ፓርቲ በቀላሉ እንደሚያሸንፍ መገመቱ ስህተት ላይመስል ይችል ይሆናል ነገር ግን ከምርጫው ማግስት ለመረዳት እንደተቻለው አብዛኛው አባላት የድርጅቱን የፖለቲካ ፕሮግራምን በመረዳት ሳይሆን የስራ ዕድል ለማግኘትና የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን በመፈለግ ፓርቲውን መቀላቀላቸው ነው፡፡ በአዲስ አበባ ድርጅቱ ድምጽ አገኝባቸዋለው ብሎ ባሰበባቸው በተክለሃይማኖት ፤ ቦሌ እና ሌሎች አካባቢዎች መሸነፉ አንዱ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡
4.ሙስና
ኢሕአዴግ በዋነኛነት ከሚታወቅባቸው እኩይ ባህሪያቶቹ አንዱ ሙስና ሲሆን ይህም የሚከናወነው ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ሳይሆን በተወሰኑ ቡድኖች ፤ ነባር ታጋዮች እንዲሁም ዘርን መአከል ያደረገ ስለነበር ሌሎች አጋር ድርጅቶች ውስጥ ውስጡን መከፋታቸው የነበረ ሲሆን ይህም መከፋት አባላቱ ሌሎች አማራጫ ፓርቲዎችን  እንዲመለከቱ ወይም ድርጅቱ ላይ የበቀል እርምጃ ለመውሰድ ከማነሳሳቱም በላይ ድርጅቱን የግላቸው አድርጎ ለማሰብ አዳጋች ነበር፡፡
ምርጫ 2002:- በዚህ ምርጫ ላይ ኢሕአዴግ ከ1997ቱ ምርጫ ብዙ የተማረበት እና በቂ ዝግጅት ያደረገበት ስለነበር ውጤቱን ለመቀልበት ችሎ ነበር፡፡ በዚህ ምርጫ ወቅት ድርጅቱ በአብዛኛ የፖለቲካ ተንታኞች ሲገለጽ እንደነበረው ብቻውን ሮጦ ብቻውን ያሸነፈበት ምርጫ ነበር፡፡ ለዚህም ምክንያቶቹ፡-
  • በምርጫ 97 ላይ ጠንካራ የነበረውን ቅንጅትን አከርካሪውን በመስበር የበላይ አመራሮቹን በማሰር እንዲሁም ከሀገር እንዲሰደዱ በማድረግ ፤ ህዝቡን ይቅርታ እንዲጠይቁ በማስገደድ በህዝቡ ውስጥ እምነት እንዳይኖራቸው በማድረግና በሌሎችም እኩይ የፖለቲካ ስራዎቹ ድርጅቱን በማዳከሙ /በማፈራረሱ
  • በራሱ በኢሕአዴግ የተፈጠሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በመፍጠር እንዲሁም ሌሎች ተቃዋሚዎች በኢሕአዴግ ሴራ እንዲሁም በግላቸው ምክንያት ከምርጫ እራሳቸውን ማግለላቸው
  • አጭር የክርክር መድረኮችን በማዛጋጀት እንዲሁም ለተቃዋሚዎች አጭር ጊዜ በመስጠት በተቃራኒው ለራሱ ሰፊ የአየር ሽፋን በመስጠት የድርጅቱን ፕሮግራሞች ማስተዋወቁ
  • በ1997 በቅንጅትና በሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይቀርቡ የነበሩ አማራጭ የልማት እስትራተጂዎችን በመውሰድና ከፊሎችንም በመተግበር ከተሰራው ስራ በላይ ፕሮፖጋንዳ በመስራት (ጥቃቅንና አነስተኛ ፤ ማህበራትን ማደራጀት ፤ ወጣቱን አደገኛ ቦዘኔ ከማለት ወደ ወጣት የልማት ሀይል መቀየር ፤ የጋራ የመኖሪያ ቤቶችን መገንባትና የመሳሰሉት ከምርጫ 1997 በፊት በገዢው ፓርቲ ተሰምተው የማይታወቁ ሲሆን ከምርጫ 97 በኋላ ጽንሰ ሀሳቡ ከተቃዋሚዎች ስለመሰረቁ ማሳይዎች ናቸው)
  • ቀደም ሲል ገጠርን ማዕከል ያደረገውን ልማት ወደ ከተማ በማምጣት የሚታዩ ለውጦችን በማቅረብ እነሱንም በመንግስት ሚዲያዎች አግንኖ ማቅረቡ (መንገድ ፤ ውሃ ፤ ኤሌክትሪክ ወዘተ)
  • የህዝቡ ተስፋ መቁረጥ፡ – በምርጫ 97 ወቅት በህዝቡ ተስፋ የተጣለባቸው ፓርቲዎች ከነአካቴው መጥፋታቸውና እነሱን ሊተካ የሚችል ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲ መጥፋቱ
  • ጠንካራ የፖለቲካ ቅስቀሳ መደረጉ ፡ – መንግስት የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት የተሰሩ የልማት ስራዎችን በማቅረብ ፤ ህብረተሰቡን በማወያየት እንዲሁም ትልልቅ ካፒታል የሚጠይቁ ፕሮጀክቶችን በማስፋፋቱና የረጅም ጊዜ ዕቅዶችን በማቅረቡ
  • ምርጫ ቦርድ ላይ ያለውን ስውር እጅ በማስፋፋት ጠንካራ ክትትል ማድረግና የድርጅቱ የቀኝ ክንፍ መሆኑ በዚህና በሌሎች ምክንያቶች ገዢው ፓርቲ ሙሉ ለሙሉ የምርጫው አሸናፊ ሊሆን ችሏል፡፡ ከሁለቱ ተከታታይ ምርጫዎች የምንማራቸው አበይት ጉዳዮች ቢኖሩ፡
  • ኢህአዴግ በቢሊዮን የሚቆጠር የፋይናንስ አቅም እንዳለውና ለፖለቲካ ቅስቀሳ በቂ አቅም እንዳለው በተቃራኒው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያላቸው የፋይናንስ አቅም እጅግ አናሳ በመሆኑ በራካታ አባላትን ለማፍራት እንዲሁም ቅስቀሳዎችን ለማድረግ የአቅም ውሱንነት እንዳላቸው
  • ኢሕአዴግ የ1997ቱ ምርጫ ብዙ ልምዶችን የቀሰመበትና በወቅቱ አሳይቶት የነበረው የዲሞክራሲ ጭላንጭል በማጥፋት ፍፁም አምባገነን እየሆነ መምጣቱን
  • ኢሕአዴግ የተቃዋሚዎችን ደካማ ጎን በመጠቀም እንዲሁም የስለላ መረቦቹን በመጠቀም ተቃዋሚዎችን የማዳከምና የማፈረካከስ ልምዱን ያካበተ መሆኑን እና ፓርቲዎች ለምርጫ ከመድረሳቸው አስቀድሞ ከምርጫው እራሳቸውን እንዲያገሉ ጫና ማሳደሩን
  • የምርጫ ቦርድ መመሪያዎችንና ደንቦችን ኢሕአዴግ በፈለገው መልኩ ማሻሻሉንና ህጉ ለሁሉም በእኩል ደረጃ ተጠቃሚ የማያደርግ መሆኑንና እና ሌሎች በርካታ ጉዳዮች ናቸው፡፡እነዚህን እንደ መነሻነት በመጠቀም በምርጫ 2007 ሊገጥሙ የሚችሉትን ከወዲሁ ለመገመት ያህል፡ -
ኢሕአዴግ
በገዢው ፓርቲ በኩል ለምርጫው እየተደረጉ ያሉ ቅድመ ዝግጅቶች ከዚህ ቀደም ሲደረጉ ከነበሩት በእጅጉ የላቁ ናቸው፡፡ ይህም ነፃ የግል ፕሬሶችን ያለምንም በቂ ማስረጃ  በማሰር ፤ በመክሰስ ፤ በማስፈራራት ፤ እንዲሁም አገር ለቀው እንዲሰደዱ በማድረግ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ፕሮግራማቸውን  የሚያስተዋውቁበትን  መንገድ መዝጋቱ፡፡ ከዚህም  በተጨማሪ  ህዝቡ አማራጭ የመረጃ ምንጮች እንዳይኖሩት በማድረግ ህዝቡ በሚያገኘው አንድ አገራዊ የቴሌቪዝን ጣቢያ የገዢውን ልማታዊ ስራዎች ብቻ እንዲያይ ማድረጉ ነው፡፡
የተለያዩ የማህበረሰብ ድህረ ገፆች ላይ ፤ የደህንነት ሀይሎችን በማሰማራት እና ድንገተኛ ፍተሸዎችን በማድረግ ህዝቡን በማሸማቀቅ ፤ ሀይማኖትን ከሀይማት በማጋጨት ፤ የዘር ግጭቶችን በማቀነባበር ፤ ህዝቡ ላይ ሽብር በመንዛት ህዝቡ ከኢሕአዴግ ውጭ አማራጭ እንዳያስብ በማድረግ ህዝቡ እንዲመርጠው ብሎም ደግሞ የደህንነቱን ጡንቻ በማሳየት ለማስፈራራት በመሞከር ላይ ነው ለዚህም ማሳይው የተለያዩ የፖለተካ ስደተኞችን እና እንዲሁም በተለያዩ አገራት ይኖሩ የነበሩ የተቃዋሚ ድርጅት ቁልፍ ሰዎችን  አፍኖ በማምጣት ህዝቡ ላይ ፍራቻን ሲዘራ ይስተዋላል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ እንደ ምርጫ 2002 ሁሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን  በመከፋፈል ፤ በመታተን እንዲሁም በተለይዩ ምክንያቶች አመራሮቻቸውን በማሰር ተሳትፏቸውን ማዳከምን ተያይዞታል እንደ ማሳይም በአንድነት ለዲሞክራሲና ለልማት ፤ በአረና ፓርቲ እንዲሁም በሰማያዊ ፓርቲ ላይ እያደረሰ ያለው የማፈራረስ ፤ የማሸማቀቅ እንዲሁም እስራቶችን ማየት በቂ ማስረጃ ነው፡፡
የፖለቲካ ቅስቀሳዎችን በተመለከተም በአሁኑ ወቅት በሲቪል ሰርቫንቱ እና በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንዲሁም በነዋሪው ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ስልጠናዎችን እያካሄደ ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ  ተቃዋሚ ፓርቲዎች የመሰብሰቢያ አዳራሾችን የመከራይት አቅም ማሳጣት  አቅም ያላቸውንም  ደግሞ የአዳራሽ፣ ቢሮ፣እንዲሁም  ኪራይ ቤቶች እንዳያገኙ ተጽዕኖ በመፍጠር  ላይ ነው፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲዎች
በያዝነው ዓመት ማገባደጃ ላይ ለሚከናወነው አገራዊ ምርጫ ተቃሚ ፓርቲዎች እያደረጉ ያለው ቅድመ ዝግጅት በገዢው ፓርቲ ጥብቅ ክትትል ስር ሲሆን ፓርቲዎቹ የሚደርስባቸውን ጫና ለመቋቋም እንዲሁም ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን እንዲያስችላቸው ውህደት ለመፈፀም በሂደት ላይ ሲሆኑ በገዢው ፓርቲ ስውር እጆች ምክንያት በሚፈለገው ፍጥነት እየተጓዘ እንዳልሆነ እያየን ነው፡፡ በዚህ ምርጫ በሃገር ውስጥ ትልቅ  ግምት ከሚሰጣቸው እንደ አንድነት እና ሰማያዊ ፓርቲ  በገዢው ፓርቲ ተደጋጋሚ ትንኮሳ እየደረሰባቸው ሲሆን ይህም የምርጫው ዋዜማ ላይ ሊበረታ እንደሚችል ይገመታል፡፡
ህብረተሰቡ
ካለፉት የምርጫ ጊዜያቶች በተለየ ሁኔታ ማሕበረሰቡ የፓለቲካ አድማሱ የሰፋበት ሆኔታ ሲሆን ለዚህም አበይት ምክንያቶቹ በማሕበራዊ ድህረ ገፆች የሚለቀቁ የተለያዩ አክቲቪስቶችን  ንግግር ፤ ክርክሮች ፤ በግል ፕሬሱ ይታተሙ የነበሩ የፖለቲካ ትንታኔዎች ፤ ከገዢው ፓርቲ እየሾለኩ የሚወጡ የተለያዩ መረጃዎች እንዲሁም ህብረተሰቡ አማራጭ የመረጃ ምንጭ በማግኘቱ ነው፡፡ በመሆኑም ማሕበረሰቡ ምርጫው በገዢው ፓርቲ የተለመደ ማጨበርበሮች ሊጠናቀቅ እንደሚችል ግምቱ ቢኖረውም እንደ ባለፉት የምርጫ ጊዜያቶች በቸልታ ያልፈዋል ተብሎ አይታሰብም ምክንያቱም ህዝቡ መንግስት የሚያደርገውን የመብት ረገጣ ፤ አድሎአዊ አገዛዝ ፤ ሙስና ፤ እንዲሁም በእስልምና ሀይማኖት እና በኦርቶዶክስ የዕምነት ተከታዮች ላይ እጁን በማስገባት እየፈፀመ ያለውን በደል በሚገባ ስለሚያውቅ ድርጅቱ ጉልበት ያለው ቢመስልም ውስጡ ግን ባዶ ፤ ደጋፊ ያለው ቢመስልም አባላቱ በጥቅም ፤ በዘር እንዲሁም በመልካም አስተዳደር እጦት ያኮረፉ የሚበዙበት ሲሆን ገዚው ፓርቲ ከሕወሓት ውጨ ያሉ ፓርቲዎችን በአይነ ቁራኛ መመልከቱና አብዛኛውን ስልጣን ጠቅልሎ መያዙ በአጋር ድርጅቶች ጥርስ ውስጥ እንዲገባ ምክንያት ሆነዋል፡፡
ማጠቃለያ
የምርጫውን ውጤት ከወዲሁ መተንበይ ባይቻልም በገዢው ፓርቲ ውስጥ ያሉ አባላት   በወያኔ ሕወሓት ላይ በተለይዩ ምክንያቶች ውስጣቸው የሻከረ በመሆኑ (ብአዴን በግንቦት 7 ፤ ኦሕዴድ በወጣት ተተኪዎቹ የስልጣን ይገባናል ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ፤ እንዲሁም በሌሎች አጋር ፓርቲዎች) የምርጫውን ውጤት ወዳልተገመተ አቅጣጫ ሊመሩት እንደሚችል ይገመታል፡፡ የማሕበረሰቡ ንቃተ ህሊና መጨመር ፤ ገዢውን ፓርቲ በተጨባጭ መረጃዎች መወንጀል መጀመሩ ፤ መንግስት በተደጋጋሚ የሚፈፅማቸው የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች ፤ የአገሪቱን ከፍተኛ ቁጥር የሚሸፍኑትን አንጋፋ የሀይማኖት ተቋማትን ማስኮረፉ ከሀይማኖቱ ተከታዮች የምርጫ ካርድ ሊነፈግ እንደሚችልም  ይገመታል ይሁንና ገዢው ፓርቲ በምርጫ ቢሸነፍም ስልጣኑን ለመልቀቅ ፍቃደኛ ባለመሆኑ ድምፁ የተሰረቀበት ማሕበረሰብ አልመረጥኩም ብሎ በጥያቄ  ተቃውሞ ቢነሳ  ተቃውሞውን በበቂ ሁኔታ የሚያስተባብርና ሀላፊነቱን የሚወስድ ፓርቲ ባለመኖሩ አገሪቷን ወደ አላስፈላጊ ዕልቂት እንዳይጥላት ያሰጋል፡፡ ገዢው የወያኔፓርቲ የምርጫውን ውጤት በጸጋ ተቀብሎ ለመጪዋ ኢትዮጵያ ዘላለማዊነት በቅን ልቦና ምርጫውን ለግል ጥቅም ሳይሆን የህዝቡን ድምፅ እንዲያከብር ልባዊ  ምኞቴ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!