‹‹ሰላማዊ ትግል የሚባል ነገር አይሰራም፤ ጫካ ገብታችሁ ሞክሩን፡፡››
የብአዴን አመራሮች
የብአዴን አመራሮች
በምስራቅ ጎጃም ዞን የሚገኙ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ከገዥው ፓርቲ ባለስልጣናት የሚደርስባቸው ጫና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ መሆኑን ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ የምስራቅ ጎጃም ዞን የሰማያዊ ፓርቲ ጸሃፊ የሆነው ጠበቃ ሳሙኤል አወቀ በእሱና በሌሎች የፓርቲው አመራሮችና አባላት ላይ ዛቻ እንደሚፈጸምባቸው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡
የምስራቅ ጎጃም ዞን ፍትህ ቢሮ በ2006 ዓ.ም የእቅድ ግምገማ እና የ2007 ዓ.ም የስራ አፈጻጸም እቅድ በተወያየበት እና የሁሉም ጽ/ቤት ኃላፊዎችና የስራ ሂደት ባለቤቶች በተገኙበት፣ ‹‹ሳሙኤል አወቀ የሚባል በጥብቅና ሽፋን የመሬት ፖሊሲውን የሚታገል፣ ለተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና ደጋፊ አርሶ አደሮች ጥብቅና የሚቆም፣ ከአሸባሪ ጋር ግንኙነት ባለው ድርጅት አመራር የሆነን ግለሰብ በህግ ሽፋን እስር ቤት እንዲወርድ ያላደረገ አቃቤ ህግ አቃቤ ህግ አይደለም›› ተብሎ በህግ ስም እርምጃ እንዲወሰድበት ትዕዛዝ መተላለፉን ጠበቃው ገልጾአል፡፡
በተለይ የደብረማርቆስ ወረዳ ፍትህ ጽ/ቤት አቃቤ ህጎች ዋነኛ ችግራቸው ጠበቃ ሳሙኤልን በህግ ስም ማስቀጣት አለመቻላቸው እንደሆነ ተገምግመዋል ተብሏል፡፡ ጠበቃው ወዲያውኑ የፈጠራ ክስ እንደተመሰረተበት፣ የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ ‹‹ለፍትህ ስርዓቱ አጋዥ ባለመሆኑ›› በሚል መከሰሱንና ባልተከራከረበት ፍርድ ሂደትም 8000 ብር ቅጣት እንዲከፍል እንደተወሰነበት ገልጾአል፡፡
ጠበቃው በ28/1 እናርጅ እናውጋ ለቀጠሮ ባቀናበት ወቅትም የእናርጅ እናውጋ አስተዳደርና ጸጥታ ኃላፊ አቶ ስራው በረኩ እና የብአዴን የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ መኳንንት አበበ እና ሌሎችም ከፖሊስና ከጸጥታ የመጡ አመራሮች ‹‹ምን ልታደርግ ነው? ልትቀሰቅስ ነው?›› በሚል እንዳዋከቡትና አቶ ስራው በረኩ ‹‹አንጠልጥዬ ነው እስር ቤት የማስገባህ፡፡ ማንም ሊያድንህ አይችልም›› ብለው እንደዛቱበት ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡
‹‹የሰማያዊ ፓርቲ አባል ሆነህ በፍትህ ስርዓቱ መገልገል አትችልም፣ ጥብቅናህን መልቀቅ አለብህ፣ ነገረ ኢትዮጵያ ላይ ትጽፋለህ፣ የፍትህ መምሪያ ሃላፊውን (ጸጋየ መንግስቴ) ችግር እንደሚፈጽምብህ በነገረ ኢትዮጵያና በሰንደቅ ጋዜጣ ላይ ጽፈህበታል፣ እንዲህ እያደረክ መኖር አትችልም፣ አንተን ገሎ መጣል ቀላል ነው፣ ለነፍስህ የምታዝን ከሆነ አገር ልቅቅ›› ብለው እንደዛቱበት ገልጾአል፡፡
ሌሎች ጠበቃ ጓደኞቹ ከእሱ ጋር እንዳይሄዱ ‹‹እሱ ማለት ሰማያዊ ነው፡፡ ሰማያዊ ደግሞ የአክራሪ ሙስሊም ፓርቲ ነው፡፡ እናንተ ለምን ከእሱ ጋር ትሄዳላችሁ?›› ብለው እንደሚያስፈራሯቸውና ደንበኞቹ ከእሱ ጋር እንዳይሰሩ ማስጠንቀቂያ እንደሚደርሳቸው ጠበቃው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡
ጠበቃውን ጨምሮ ሌሎች የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት የሰማያዊ ፓርቲ አመራርና አባል ሆነው ማደራጀት መብታቸው መሆኑን ሲገልጹ የብአዴን አመራሮች ‹‹እናንተ እኛን ስለማትረዱን ነው፡፡ እኛ ጋር ሰላማዊ ትግል የሚባል አይሰራም፡፡ ወንድ ከሆናችሁ ጫካ ገብታችሁ ሞክሩን›› በሚል ለህግ የማይገዙና ለሰላማዊ ትግል ቁርጠኝነት እንደሌላቸው አሳይተውናል ብለዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የሰማያዊ ፓርቲና አመራር የሆኑ ነጋዴዎች ከፓርቲው እንዲለቁ ለማድረግ የንግድ ድርጅታቸውን እንደሚዘጉ እያስፈራሩ እንደሆነ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ለአብነት ያህልም አቶ ይኸይስ ቀጸላ የተባሉ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር ‹‹ሻይ ቤት ከፍተው እያደራጁ ነው፡፡ የንግድ ድርጅቱን እንደ ጽ/ቤት ይጠቀሙበታል፡፡ በመሆኑም ካላረፉ ሻይ ቤቱን እንዘጋዋለን›› እያሉ እንደሚያስፈራሩ ታውቋል፡፡
የዞኑ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት የገዥው ፓርቲ ዛቻና ማስፈራሪያ እንዲሁም እርምጃዎች እየተጠናከሩ ቢሆንም እርምጃው እነሱ ተጽዕኖ በመፍጠራቸው የመጣ በመሆኑ ይበልጡን እንደሚያበረታታቸውና የሚከፈለውን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
አቶ መኳንንት አበበን ጨምሮ ሌሎች አመራሮችን የእጅ ስልካቸው ላይ በመወደል ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፡፡
No comments:
Post a Comment