Tuesday, November 4, 2014

በተለያዩ ክልሎች ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሂጃባችሁን አውልቁ በሚል ከትምህርታቸው እየተፈናቀሉ ነው

በአሶሳ እና በሽሬ እንደስላሴ ከተማ የሚኖሩ 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ሙስሊም ተማሪዎች ሂጃባችሁን አውልቁ በሚል ከትምህርት ገበታቸው እየተፈናቀሉ እንደሚገኙ ተገለፀ::
አቡ ዳውድ ኡስማን
በቤኒሻንጉል ጉምዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በአሶሳ ከተማ በሚገኙ የ1ኛ ደረጃ ት/ቤት የሚማሩ ሙስሊም ተማሪዎች ሂጃብ ለብሰው መማር እንዳይችሉ እየተደረጉ መሆናቸውን ምንጮች አስታወቁ፡፡
ፎቶ ከፋይል
ፎቶ ከፋይል
በአሶሳ ከተማ በሚገኙ ት/ቤቶች ውስጥ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሂጃብ ለብሰው በትምህርት ገበታቸው ላይ መገኘት እንደማይችሉ የት/ቤቱ አስተዳደሮች እየከለከሏቸው መሆኑ ታውቋል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉምዝ በአሶሳ ከተማ በሚገኝ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት 35 የሚሆኑ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሂጃባችሁን ካላወለቃችሁ መማር አትችሉም በመባላቸው ከትምህርት ገበታቸው መፈናቀላቸውን ምንጮች አስታውቀዋል፡:
የትምህርት ቤቱን ርዕሰ መምህርን በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር በአሶሳ ከተማ በስፋት በህዝብ ዘንድ የሚታወቀው ሰለፊያ ተብሎ የሚጠራው መስጂድ ኮሚቴዎች ሙከራ ያደረጉ ሲሆን ርዕሰ መምህሩ “እናንተ አሸባሪዎች እስካሁን አላቹ እንዴ” በማለት የተሳለቀባቸው ሲሆን ሴት ተማሪዎቹ ሂጃባቸውን እስካላወለቁ ድረስ በትምህርት ገበታቸው ላይ እንደማይቀጥሉ ምላሽ እንደሰጣቸው ታውቋል፡፡
በተመሳሳይም በትግራይ ክልል በሽሬ እንደስላላሴ ከተማ በሚገኙ 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ውስጥ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሂጃብ ለብሰው መማር እየተከለከሉ መሆናቸውን ምንጮች ዘግበዋል፡፡
በበሽሬ እንደስላሴ ከተማ የሚኖሩ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሂጃባችሁን አውልቃችሁ ተማሩ በመባላቸው ከትምህርት ገበታቸው ተፈናቅለው በቤት ውስጥ ተቀምጠው እንደሚገኙ ታውቋል፡፡
የትምህርት ቤት አስተዳደሮች የተማሪዎችን ወላጆች በመሰብሰብ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገሩ ሲሆን ወላጆችን እና ተማሪዎችን ሲያስፈራሩ እንደነበር ተዘግቧል፡፡
በመላው ሃገሪቱ የሙስሊሞች ዋነኛ የእምነታቸው መገለጫ የሆነውን ሂጃብ እንዲያወልቁ ለማድረግ በመንግስት በኩል ከፍተኛ ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ የፌደራል ጉዳዬች ሚኒስተር ዶ/ር ሽፈራው በኢስላም ላይ ባላቸው የግል ጥላቻ በመነሳት ከመሰሎቻቸው ጋር በመቀናጀት ሙስሊም ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ለማፈናቀል በክፍተኛ ደረጃ እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ የሚታወቅ ሲሆን በመላው ሃገሪቱም በሴኩላሪዝም ሽፋን ሙስሊሞች ትምህርታቸውን አልያም ሃይማኖታቸውን እንዲመርጡ በማስገደድ ሙስሊሙን ከትምህርት ገበታ ለማራቅ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡
ሂጃብ የሙስሊም ሴት ህልውናዋ እንጂ ለድርድር የሚቀርብ የፖለቲካ አጀንዳ አይደለም

የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር የ24 ሰዓት የተቃውሞ ሰልፍ ጠራ

የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር የመጀመሪያ ዙር ህዝባዊ ትግል ፕሮግራሙን ይፋ አደረገ
• የ24 ሰዓት (የአዳር) የተቃውሞ ሰልፍ ተጠርቷል
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
ጥቅምት 12 ቀን 2007 ዓ.ም 9 ተቃዋሚ ፓርቲዎች የመሰረቱት ትብብር ‹‹ነጻነት ለፍትሃዊ ምርጫ›› በሚል ለአንድ ወር የሚቆይ የመጀመሪያ ዙር የህዝባዊ ትግል ፕሮግራሙን ዛሬ ጥቅምት 25/2007 ዓ.ም በሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት ይፋ አደረገ፡፡
yilikal getenet
‹‹ነጻነት በሌለበት ፍትሃዊ ምርጫ የማይታሰብ በመሆኑ የተዘጋውን በር ለመክፈት የ‹ነጻነት ለፍትሃዊ ምርጫ› በሚል የፕሮግራም መርሃ ግብር ለመክፈት ወስኖ የመጀመሪያው ዙር እንቅስቃሴ በአዲስ አበባ ከተማ ለማድረግ›› እንዳዘጋጀ ያሳወቀው ትብብሩ የትግሉ ዓላማ ፍትሃዊ ምርጫ እንዲኖር የሚያስችል መሆኑን ገልጾአል፡፡
‹‹ምርጫ ቦርድ ለገዥው ፓርቲ ያለውን ወገናዊነትና ጉዳይ አስፈጻሚነት ፍንትው አድርጎ አሳይቷል›› ያለው መግለጫው በመጀመሪያ ዙር የአንድ ወር ፕሮግራሙ 6 ዋና ዋና ተግባራትን ለመፈጸም ዝርዝር እቅዶችን አውጥቶ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡ በህዳር ወር የሚያከናውናቸው ተግባራትም፡-
1. በቤተ እምነት ጸሎት እንዲደረግና ጥሪ ማቅረብና አማኞች እንደየ እምነታቸው ተሳትፎ እንዲያደርጉ ማድረግ
2. የአደባባይ ህዝባዊ ስብሰባዎችን ማድረግ
3. የተቃውሞ ድምጽ ማሰማት (ሰላማዊ ሰልፍ)
4. ለመንግስት ተቋማት ደብዳቤ ማስገባት
5. በምርጫ ዙሪያ የፓናል ውይይቶችን ማድረግና
6. የህዝብን ተሳትፎ ማበረታታትና ድጋፍ ማሰባሰብ እንደሆኑ በመግለጫው አሳውቋል፡፡
ከእቅዶቹ መካከልም በሶስት ተከታታይ እሁዶች በተለያዩ የአዲስ አበባ ክፍሎች 3 የአደባባይ ስብሰባዎች እንደሚኖሩ፣ በመጨረሻው መርሃ ግብርም ህዳር 27ና 28 በፕሮግራሙ ማጠቃለያነት የ24 ሰዓት (የውሎና የአዳር) የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚደረግ የትብብሩ ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ገልጸዋል፡፡
በገዥው ፓርቲና በምርጫ ቦርድ ጥምረት ይፈጸማል ያለውን ህገ ወጥ ተግባር በመታገል ለሰላማዊ ትግሉ አወንታዊ አስተዋጽኦ ለማበርከት እስከመጨረሻው በፅናት ለመቆም መዘጋጀቱን የገለጸው ትብብሩ በአገር ቤትና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ በትብብሩ ሂደት ቆይተው እስካሁን ያልፈረሙና ሌሎች ፓርቲዎች እና የዓለም አቀፉ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ከጎኑ እንዲቆሙ ጥሪ አቅርቧል

Tuesday, October 21, 2014

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ችሎት ትናንት እና ዛሬ ቀጥሎ ዋለ

የመከላከያ ምስክሮች በዋና ዋና ጭብጦች ላይ የኮሚቴዎቹን ንጹህነት እየመሰከሩ ነው!
ድምፃችን ይሰማ እንደዘገበው:-
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ችሎት ትናንት እና ዛሬ ቀጥሎ ውሏል፡፡ ችሎቱ ባለፈው ዓመት ጀምሮት የነበረውን የመከላከያ ምስክሮች ሂደት አቋርጦ በዚህ አመት ዳግም ቢጀምርም ከጥቅምት 3/2007 ጀምሮ ‹‹ኤሌክትሪክ ሄዷል፣ ኤሌክትሪክ ተቆረጠ››፣ እንዲሁም ‹‹ካርድ አልተሞላም›› በሚሉ ምክንያቶች ችሎቱ ከሳምንት በላይ ለሆነ ጊዜ ድጋሚ እንዲቋረጥ ሆኖ ነበር፡፡ ዛሬ ችሎቱ ዳግም ሲጀመር ባለፈው የመከላከያ ምስክርነታቸውን ጀምረው መስቀለኛ ጥያቄ ሳይቀርብላቸው በቀሩት አቶ አህመድ ኡመር ሲጀምር ምስክነርት በሰጡበት በጭብጥ 10 ላይ አቃቤ ህግ ለመከላከያ ምስክሩ አቅርቦ ያልጨረሳቸውን መስቀለኛ ጥያቄዎች አቅርቦ አቶ አህመድ ኡመር በቂ ምላሽ ሰጥተዋል።
muslim dim
አቶ አህመድ ኡመር 53ኛ ምስክር በመሆን በጭብጥ 11 ላይ ትናንት ምስክርነት ሲሰጡ በሐምሌ 2004 የመንግስት ታጣቂ ኃይሎች በህዝበ ሙስሊሙ ላይ የፈፀሙትን ጭፍጨፋ የገለጹ ሲሆን በታላቁ አንዋር መስጂድ በተደረገው የአንድነትና የሰደቃ ፕሮግራም ላይ ንግግር ያደጉት የህዝበ ሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ሕገ ወጥና ኹከት ቀስቃሽ፣ እንዲሁም ጸረ ሰላም ንግግር ሳይሆን ሰላማዊና ለህዝቦች የጋራ መኗኗር ጠቃሚ ሐሳብ ለህዝቡ ማስተላለፋቸውን ለችሎቱ አስረደትዋል፡፡ 54ኛ የመከላከያ ምስክር ሆነው የቀረቡት አቶ ጀማል ሽኩር ደግሞ በጭብጥ 7 ላይ ሰፊ ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡ በእማኝታቸው እሳቸው በሚኖሩበት ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 የመጅሊስን ምርጫ አጠቃላይ ሂደት ሲመሩትና ሲያቀናብሩት የነበሩት የአካባቢው የወረዳ ሀላፊዎችና የፖለቲካ ሹመኞች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የቤት ለቤት ቅስቀሳውን ጨምሮም ሂደቱ በሙሉ በመንግስት አስፈጻሚዎች ይዘወር እንደነበርም ገልጠዋል፡፡
ዛሬ በቀጠለው ችሎትም የ3 መከላከያ ምስክሮች መከላከያ ምስክርነቶች የተደመጡ ሲሆን በ2004 ከተሰጡት የአዲስ አበባ ከተማ አህባሽ ስልጠናዎች ትልቁ በነበረውና በኢትዮ-ቻይና የሙያ ኮሌጅ በተካሄደው የጠመቃ ስልጠና ከሰልጣኞቹ አንዱ የነበሩት አቶ ሰኢድ ኢብራሂም በስልጠናው ሂደት ላይ የነበሩትን የመንግስት እጆችና ሕገ ወጥ አካሄዶች ሲያስረዱ ቀጣዩ ምስክር አቶ ሙሐመድ በሐምሌ 2004 የመንግስት ታጣቂዎች አንዋር መስጂድ ውስጥ ይገኙ በነበሩ ምእመናን ላይ የፈጸሙትን ጭፍጨፋ በጭብጥ 11 ማእቀፍ መሰረት ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡
ጋዜጠኛ አቡበከር አለሙ በተከሰሰበትና በፒያሳው ኑር መስጂድ ሰላማዊ ውይይት እንዳይካሄድ በማድረግና በማደናቀፍ ለተመሰረተበት ክስ አቶ አብዱልሃኪም አስፋው የመከላከያ ምስክርነት ሰጥዋል፡፡ በምስክርነታቸውም በወቅቱ አቡበከር ኹከት ፈጣሪ ንግግር እንዳልተናገረና የመንግስት ክስ ከሚለው በተቃራኒ በወቅቱ ሌሎች ሰዎች የተሰጣቸውን ጥያቄ የመጠየቅ መብት ሁሉ ተነፍጎ መድኩን ጥሎ ለመውጣት መገደዱን አስታውሰዋል፡፡ የዛሬዎቹ ምስክሮች በሰጡት ምሰክርነት ላይ ችሎቱ መስቀለኛ ጥያቄ አቅርቦላቸው በተገቢው መልኩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ችሎቱ በነገው እለትም ሂደቱን ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በሌላ በኩል በአቡበክር አህመድ የክስ መዝገብ ተከሰው በነጻ የተለቀቁት ሸኽ አብዱህራማን ኡስማን ከሊል እና አሊ መኪ በድሩ ዳግም ወደ ወህኒ እንዲገቡ በፌደራሉ ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት እንደተወሰነባቸው ታውቋል፡፡ የፌደራሉ ከፍተኛው ፍ/ቤት 4ኛው ወንጀል ችሎት በታህሳስ 3/2006 በሰጠው ብይን ሁለቱን ተከሳሾች ጨምሮ 8 ሙስሊሞች አቃቤ ህጉ ካቀረበባቸው ክስ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ውሳኔ ካስተላለፈ በኋላ አቃቤ ህጉ ባቀረበው ይግባኝ መሰረት ጉዳያቸው ሲታይ የቆዩት ሸኽ አብዱራህማን እና አሊ መኪ ድጋሚ እንዲታሰሩ ወሳኔ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ከህዝበ ሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ጋር ተከሰው ፍርዳቸውን ሲከታተሉ ቆይተው በነጻ የተሰናበቱት ሸኽ አብዱረህማን ኡስማን ከሊል እና አሊ መኪ በድሩ በፍርድ ቤት ድጋሚ እንዲታሰሩ በመወሰኑ ሸኽ አብዱረህማን አሁን በቂሊንጦ ወህኒ ቤት የሚገኙ ሲሆን ሌላው ወንድም አሊ መኪም በተገኘበት እንዲያዝ መባሉ ታውቋል፡፡ በዚህም መሰረት የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ የሰጠባቸውና በችሎቱ ተገኝተው የነበሩት ሸኽ አብዱረህማን ኡስማንም ችሎቱ እንደተጠናቀቀ በፖሊስ ተይዘው መታሰራቸውና አሁን በቂሊንጦ ዞን 3 እንደሚገኙ ታውቋል፡፡
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምፃችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!

በሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ላይ ጫናው በርትቷል “ሰላማዊ ትግል የሚባል ነገር አይሰራም፤ ጫካ ገብታችሁ ሞክሩን›› -የብአዴን አመራሮች

 ‹‹ሰላማዊ ትግል የሚባል ነገር አይሰራም፤ ጫካ ገብታችሁ ሞክሩን፡፡››
የብአዴን አመራሮች
በምስራቅ ጎጃም ዞን የሚገኙ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ከገዥው ፓርቲ ባለስልጣናት የሚደርስባቸው ጫና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ መሆኑን ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ የምስራቅ ጎጃም ዞን የሰማያዊ ፓርቲ ጸሃፊ የሆነው ጠበቃ ሳሙኤል አወቀ በእሱና በሌሎች የፓርቲው አመራሮችና አባላት ላይ ዛቻ እንደሚፈጸምባቸው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡
blue party
የምስራቅ ጎጃም ዞን ፍትህ ቢሮ በ2006 ዓ.ም የእቅድ ግምገማ እና የ2007 ዓ.ም የስራ አፈጻጸም እቅድ በተወያየበት እና የሁሉም ጽ/ቤት ኃላፊዎችና የስራ ሂደት ባለቤቶች በተገኙበት፣ ‹‹ሳሙኤል አወቀ የሚባል በጥብቅና ሽፋን የመሬት ፖሊሲውን የሚታገል፣ ለተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና ደጋፊ አርሶ አደሮች ጥብቅና የሚቆም፣ ከአሸባሪ ጋር ግንኙነት ባለው ድርጅት አመራር የሆነን ግለሰብ በህግ ሽፋን እስር ቤት እንዲወርድ ያላደረገ አቃቤ ህግ አቃቤ ህግ አይደለም›› ተብሎ በህግ ስም እርምጃ እንዲወሰድበት ትዕዛዝ መተላለፉን ጠበቃው ገልጾአል፡፡
በተለይ የደብረማርቆስ ወረዳ ፍትህ ጽ/ቤት አቃቤ ህጎች ዋነኛ ችግራቸው ጠበቃ ሳሙኤልን በህግ ስም ማስቀጣት አለመቻላቸው እንደሆነ ተገምግመዋል ተብሏል፡፡ ጠበቃው ወዲያውኑ የፈጠራ ክስ እንደተመሰረተበት፣ የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ ‹‹ለፍትህ ስርዓቱ አጋዥ ባለመሆኑ›› በሚል መከሰሱንና ባልተከራከረበት ፍርድ ሂደትም 8000 ብር ቅጣት እንዲከፍል እንደተወሰነበት ገልጾአል፡፡
ጠበቃው በ28/1 እናርጅ እናውጋ ለቀጠሮ ባቀናበት ወቅትም የእናርጅ እናውጋ አስተዳደርና ጸጥታ ኃላፊ አቶ ስራው በረኩ እና የብአዴን የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ መኳንንት አበበ እና ሌሎችም ከፖሊስና ከጸጥታ የመጡ አመራሮች ‹‹ምን ልታደርግ ነው? ልትቀሰቅስ ነው?›› በሚል እንዳዋከቡትና አቶ ስራው በረኩ ‹‹አንጠልጥዬ ነው እስር ቤት የማስገባህ፡፡ ማንም ሊያድንህ አይችልም›› ብለው እንደዛቱበት ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡
‹‹የሰማያዊ ፓርቲ አባል ሆነህ በፍትህ ስርዓቱ መገልገል አትችልም፣ ጥብቅናህን መልቀቅ አለብህ፣ ነገረ ኢትዮጵያ ላይ ትጽፋለህ፣ የፍትህ መምሪያ ሃላፊውን (ጸጋየ መንግስቴ) ችግር እንደሚፈጽምብህ በነገረ ኢትዮጵያና በሰንደቅ ጋዜጣ ላይ ጽፈህበታል፣ እንዲህ እያደረክ መኖር አትችልም፣ አንተን ገሎ መጣል ቀላል ነው፣ ለነፍስህ የምታዝን ከሆነ አገር ልቅቅ›› ብለው እንደዛቱበት ገልጾአል፡፡
ሌሎች ጠበቃ ጓደኞቹ ከእሱ ጋር እንዳይሄዱ ‹‹እሱ ማለት ሰማያዊ ነው፡፡ ሰማያዊ ደግሞ የአክራሪ ሙስሊም ፓርቲ ነው፡፡ እናንተ ለምን ከእሱ ጋር ትሄዳላችሁ?›› ብለው እንደሚያስፈራሯቸውና ደንበኞቹ ከእሱ ጋር እንዳይሰሩ ማስጠንቀቂያ እንደሚደርሳቸው ጠበቃው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡
ጠበቃውን ጨምሮ ሌሎች የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት የሰማያዊ ፓርቲ አመራርና አባል ሆነው ማደራጀት መብታቸው መሆኑን ሲገልጹ የብአዴን አመራሮች ‹‹እናንተ እኛን ስለማትረዱን ነው፡፡ እኛ ጋር ሰላማዊ ትግል የሚባል አይሰራም፡፡ ወንድ ከሆናችሁ ጫካ ገብታችሁ ሞክሩን›› በሚል ለህግ የማይገዙና ለሰላማዊ ትግል ቁርጠኝነት እንደሌላቸው አሳይተውናል ብለዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የሰማያዊ ፓርቲና አመራር የሆኑ ነጋዴዎች ከፓርቲው እንዲለቁ ለማድረግ የንግድ ድርጅታቸውን እንደሚዘጉ እያስፈራሩ እንደሆነ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ለአብነት ያህልም አቶ ይኸይስ ቀጸላ የተባሉ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር ‹‹ሻይ ቤት ከፍተው እያደራጁ ነው፡፡ የንግድ ድርጅቱን እንደ ጽ/ቤት ይጠቀሙበታል፡፡ በመሆኑም ካላረፉ ሻይ ቤቱን እንዘጋዋለን›› እያሉ እንደሚያስፈራሩ ታውቋል፡፡
የዞኑ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት የገዥው ፓርቲ ዛቻና ማስፈራሪያ እንዲሁም እርምጃዎች እየተጠናከሩ ቢሆንም እርምጃው እነሱ ተጽዕኖ በመፍጠራቸው የመጣ በመሆኑ ይበልጡን እንደሚያበረታታቸውና የሚከፈለውን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
አቶ መኳንንት አበበን ጨምሮ ሌሎች አመራሮችን የእጅ ስልካቸው ላይ በመወደል ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፡፡

Hiber Radio: ኢትዮጵያ የኢቦላ ተጠርጣሪዎችን ናሙና ወደ ኬኒያ እንደምትልክ አንድ የአገሪቱ ባለስልጣን ገለጹ; * ካራቱሪ በኪሳራ ሳቢያ መሬቱን አሳልፎ እየሸጠ መሆኑ ተጋለጠ

የህብር ሬዲዮ ጥቅምት 9 ቀን 2007 ፕሮግራም !
<... የተሰደድነው ጋዜጠኞች ደህንነታችን ዛሬም ስጋት ላይ ነው...ገደኛህን አስታመህ ሞቶ እሱኑ ሬሳውን እንኳን ለመሸኘት ለስንብት ዕድል ስትነፈግ ያሳዝናል። አገዛዙ ያው የለመደወን ነው ያደረገው ውሸት ስራቸው ነው። ጋዜጠኛ ሚሊዮን ሹርቤ እንደማናችንም በጫና ነው ስራውን ያቆመው እና የተሰደደው እነሱ ግን በአስከሬኑ እንኳን ፕሮፖጋንዳ ሊሰሩበት ነው። ይህ ያሳዝናል።ወቅታዊ ምላሽ ለሰጡ ወገኖቻችን ግን... >>
ጋዜጠኛ ሃብታሙ አሰፋ
ጋዜጠኛ ሃብታሙ አሰፋ

ጋዜጠኛ ኤልያስ ጉዲሳ የቃል ኪዳን መጽሔት ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር በስደት ካለበት ኬኒያ የአገዛዙ ሰዎች እንዴት በሞት የተለየውን የሙያ አጋሩን እንኳን መሰናበት እንደከለከሉት ለህብር ሬዲዮ ከሰጠው ምላሽ የተወሰደ (ሙሉውን ያዳምጡ)
<... በምርጫ አሁን ያለው ስርዓት ይወርዳል የሚል ዕምነት የለኝም። በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ ተቃዋሚዎችን ተስፋ እያስቆረጥኩ አይደለም። ግን ምርጫ እንገባለን አንገባም ሳይሆን አስቀድመው የሁኔታዎች ትንተና ጥናት መስራት አለባቸው ። የምርጫ ህጎቹን ስታይ ፣የምርጫ አስፈጻሚውን ስትመለከት ሁኔታው ግልጽ ነው።...በምርጫ 2002 ሕዝቡ ሳይመርጥ 99.6 በመቶ አሸነፍን ተብሏል አሁን እንደውም የመለስን ራዕይ እናሳካለን በሚል መቶ በመቶ ለመጠቅለል ነው የሚሰሩት ። በዕኔ ዕምነት ከጠየከኝ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በምርጫ ከስልጣን ማውረድ አይቻልም...>
አቶ ኤርሚያስ ለገሰ የቀድሞ በስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ የኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ ከህብር ሬዲዮ ጋር ካደረጉት ቃለ ምልልስ(ሙሉውን ያዳምጡት)
ኢቦላ እና ዛሬም ያልተቀረፈው ስጋት በአሜሪካ (ልዩ ዘገባ)
ዜናዎቻችን
ኢትዮጵያ የኢቦላ ተጠርጣሪዎችን ናሙና ወደ ኬኒያ እንደምትልክ አንድ የአገሪቱ ባለስልጣን ገለጹ
ሰፊ መሬት በኢትዮጵያ ያለው ካራቱሪ በኪሳራ ሳቢያ መሬቱን አሳልፎ እየሸጠ መሆኑ ተጋለጠ
በኢትዮጵአ በስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ በምርጫ ማውረድ እንደማይቻል የስርዓቱ የቀድሞ ሚኒስትር አቶ ኤርሚያስ ለገሰ ገለጹ
አቶ ሌኒጮ ለታ ምክትላቸውን ተከትለው አዲስ አበባ በቅርብ ቀን እንደሚገቡ ድርጅታቸው አስታወቀ
የዶ/ር ዲማ ነጎ ኢትዮጵአ መግባት አነጋጋሪ ሆኗል
ኤርትራ ውስጥ የመንግስት ለውጥ ያስፈልጋል ያሉ አንድ የተባበሩት መንግስታት ኤክስፐርት ስልጣናቸውን ለቀቁ
ኤርትራ አልሸባብን ሳይሆን የኢትዮጵያን ትጥቅ ያነሱ ተቃዋሚዎች እንደምትረዳ ተገለጸ
ሌሎችም ዜናዎች አሉ
-- Ze-Habesha Website may contain advice, opinions, and statements of various information and content providers. The Website neither represents nor endorses the accuracy of information or endorses the contents provided by external sources. All blog posts and comments are the opinion of the authors.--

“በጋምቤላው ግጭት በተሳተፉት ላይ እርምጃ አልተወሰደም” መኢአድ

“አስፈላጊው እርምጃ ተወስዷል፤ ወደፊትም ይወሰዳል” መንግስት
በቅርቡ በጋምቤላ ክልል ጎደሬ ወረዳ፣ በዜጎች መፈናቀልና ግድያ ላይ ተሳትፈዋል በተባሉ ባለስልጣናትና ካድሬዎች ላይ መንግሥት ምንም አይነት እርምጃ አለመውሰዱን የመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የገለፀ ሲሆን መንግስት በበኩሉ፤ ድርጊቱን በፈፀሙት ግለሰቦች ላይ የማጣራት ስራ ተከናውኖ አስፈላጊው እርምጃ መወሰዱንና ወደፊትም እንደሚወሰድ አስታውቋል፡፡
(ጋምቤላ ክልል)
(ጋምቤላ ክልል)

መኢአድ ሰሞኑን በፅ/ቤቱ በሰጠው መግለጫ፤ በጋምቤላ ክልል በተከሰተው የዜጎች መፈናቀልና ግጭት ከ540 በላይ ሰዎች ህይወታቸውን እንዳጡና በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው እንደተሰደዱ ጠቁሞ፤ በድርጊቱ የመንግስት ባለስልጣናት መሳተፋቸው ሁኔታውን በጣም አስፈሪና አስደንጋጭ ያደርገዋል ብሏል፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ዜጎችን ማፈናቀልና የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲቆም በተደጋጋሚ ሲጠይቅና ሲያሳስብ መቆየቱን ያመለከተው ፓርቲው፤ በመንግስት በኩል ተገቢ እርምጃ ባለመወሰዱ ችግሩ እየሰፋ መሄዱን ገልጿል፡፡
የዛሬ ሁለት ዓመት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉራፈርዳ ወረዳ ተመሳሳይ ድርጊት የፈፀሙትን ካድሬዎች መንግሥት በቁጥጥር ስር ማዋሉን ሲገልፅ እንደነበር ፓርቲው አስታውሶ፤ ነገር ግን የፖለቲካ ፍጆታ ከማድረግ ባለፈ እርምጃ ሲወስድ አለመታየቱንና አሁንም በጋምቤላው ድርጊት በተጠረጠሩት ላይ እርምጃ ይወስዳል የሚል እምነት እንደሌለው አስታውቋል፡፡ ባለፈው ሰኞ በክልሉ ቴፒ እና ጎደሬ ወረዳ ባገረሸው ግጭት የ5 ሰዎች ህይወት መጥፋቱን የጠቆሙት ምንጮች በንብረት ላይም ጉዳት ደርሷል ብለዋል፡፡ ከረቡዕ ጀምሮም አካባቢው በፌደራል የመከላከያ ኃይል አባላት ከፍተኛ የጸጥታ ቁጥጥር እየተደረገበት መሆኑን ምንጮች ጨምረው ጠቁመዋል፡፡
ከትናንት በስቲያ ከህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ዜጎችን ከመኖርያ ቀዬአቸው ማፈናቀልን አስመልክቶ ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ በአገሪቱ ያለው ስርአት የግለሰቦችንና የቡድን መብትን በእኩል የሚያከብርና የሚያስከብር መሆኑን ጠቁመው በጋምቤላ በተፈፀመው ማፈናቀል ላይ መንግስታቸው ጉዳዩን መርምሮ ድርጊቱን ፈጽመዋል በተባሉት ላይ እርምጃ መውሰዱንና ለወደፊትም እንደሚወስድ አስረድተዋል፡፡
ከመንግስት በኩልም ሆነ ከተቃዋሚዎች ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ብሔረሰቦችን ለማጋጨት የሚጥሩ እንዳሉ የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚህ ድርጊት በሚሳተፉት ላይ አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ ህጋዊ መስመር እንደሚያሲዟቸው፣ ጥላቻን የሚዘሩ ኃይሎችንም ሆነ በጠባብነትና በትምክህት የተለከፉ አካላትን አደብ ለማስገዛትም መንግስት ጠንክሮ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ዘጠኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ

ነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ከአዲስ አበባ እንዘገበው ዘጠኝ የኢትዮጵያ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ዛሬ ጥቅምት 11/2007 ዓ.ም በሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
semayawi party
ፓርቲዎቹ ለረዥም ጊዜ ስለ ትብብር ሲመካከሩ የቆዩ መሆኑ የታወቀ ሲሆን፣ ዛሬ ሰባት ገጽ ያለው ሰነድ ላይ የትብብር ፊርማቸውን በማኖር ትብብሩን ሊመሩ የሚችሉ አመራሮችንም መምረጣቸው ታውቋል፡፡
ዘጠኙ ፓርቲዎች የትብብር ስምምነቱ ያስፈለገበትን ምክንያት በሰነዱ ላይ ገልጸዋል፤ በዚህም ‹‹ነጻ አሳታፊና ታአማኒ ምርጫ እንዲካሄድ በትብብር ለመስራት፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትና የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ በጋራ መታገል››ን በተመለከተ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል፡፡
በዚህም መሰረት ፈራሚዎቹ ፓርቲዎች የሚከተሉትን አመራሮች ትብብሩን እንዲመሩ መርጠዋል፡-
1. ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ከሰማያዊ ፓርቲ
2. ምክትል ሊቀመንበር አቶ ኤርጫፎ ኤርጌሎ ከከንባታ ህዝቦች ኮንግረንስ
3 ዋና ፀኃፊ አቶ ግርማ በቀለ ከኦሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት
4. ምክትል ፀኃፊ አቶ ካሳሁን አበባው ከመኢአድ
5. ገንዘብ ያዥ አቶ ኑሪ ሙደሂር ከመኢዴፓ ሆነው ተመርጠዋል፡፡
በትብብር ለመስራት ሲወያዩ ከነበሩት 14 ፓርቲዎች መካከል አንድነትና መድረክ ውስጥ የታቀፉት ፓርቲዎች ትብብሩን ለመፈረም በየ ድርጅቶቻቸው ውሳኔ ባለመተላለፉ ያልፈረሙ ሲሆን ትብብሩ እስከ ቅዳሜ እንዲጠብቃቸው ጠይቀዋል፡፡ በመሆኑም በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ይፈርማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ትብብሩ ስለ ቀጣይ የትግል ሂደትና ስለ ትብብሩ አጠቃላይ ሂደት ላይ ነገ ጥቅምት 12/2007 ዓ.ም ከጠዋቱ አራት ሰዓት በሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት መግለጫ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡