Thursday, December 4, 2014

የ24 ሰዓቱ ሰልፍ ቅስቀሳ ተጠናክሮ ቀጥሏል • 5 የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ታስረዋል

semayawi
ህዳር 27 እና 28 2007 ዓ.ም የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር የሚያደርጉት የአዳር (24 ሰዓት) ሰልፍ ቅስቀሳ ተጠናክሮ መቀጠሉን የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃ ላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ እስካሁን ሰው በሰውና ቲሸርት በመልበስ ቅስቀሳ ሲደረግ እንደቆየና በተለይ ዛሬ ህዳር 24/ 2007 ዓ.ም ከሰዓት ጀምሮ በአዲስ ከተማ፣ ጉለሌ፣ አራዳ፣ የካ፣ ንፋስ ስልክ፣ ኮልፌና ሌሎች የአዲስ አበባ ክፍለ ከተማዎች ወረቀት በመበተን የተሳካ ቅስቀሳ መደረጉን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል አራዳ ክፍለ ከተማ ፒያሳ አካባቢ ለአዳር ሰልፉ ሲቀሰቅሱ ከነበሩት መካከል የሰማያዊ ፓርቲ አባላት የሆኑት ሜሮን አለማየሁ፣ ወይንሸት ንጉሴ፣ ባህረን እሸቱ፣ ማቲያስ መኩሪያ እንዲሁም ጉለሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ ሲቀሰቅስ የነበረው ሲሳይ በፖሊስ ተይዘው መታሰራቸው ተግልጾአል፡፡
ከአሁን ቀደም ለሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ቅስቀሳ ላይ ሲያደርጉ በርካታ የፓርቲው አመራሮችና አባላት መታሰራቸውን ያስታወሱት አቶ ዮናታን ‹‹ይህ የገዥው ፓርቲ የተለመደ እርምጃ ነው፡፡ በቀጣይነትም ሌሎች አባላትንና አመራሮች መታሰራቸው አይቀረም፡፡ ትግሉ መስዋዕትነት የሚያስከፍል እንደመሆኑ በእስሩ ሳንገታ ትግሉን እንቀጥላለን፡፡›› ሲሉ እንቅስቃሴያቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡ የዛሬው ቅስቀሳ 12 ሰዓት ላይ የተጠናቀቀ ሲሆን ነገ ጠዋት ጀምሮ በተለያዩ የአዲስ አበባ ክፍሎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

ፀረ-ኢትዮጵያዊውና ዘረኛው ወያኔ በኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ስም አይነግድም

የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ቅጥረኛ የሆነው ፀረ-ኢትዮጵያዊውና ቅኝ-ገዥው ወያኔ ባሕር ማዶ ተሻግሮ በሃገረ አሜሪካ ኮለምበስ ኦሃዮ “በስሜን አሜሪካ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የባሕል ክብረ በዓል” በሚል ስም እሑድ ኅዳር 28 ቀን 2007 ዓ/ም ( Sunday, December 7, 2014 ) ከቀኑ 1:00pm ጀምሮ በሃያት ረጀንሲ ሆቴል (Hyatt Regency Hotel @ 350 North High Street, Columbus, OH 43215) ለማክበር በዝግጅት ላይ ይገኛል። ለዚህ በዓል መሰናዶ፤ ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው የወያኔ ኢምባሲ የበላይ መሪ በመሆን፤ በአካባቢያችን ያሉትን የለየላቸው ከሃዲዎችና የባንዳ ልጆችና የልጅ ልጆች በአስተባባሪነት በማሰለፍ ነው።  —--[ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ]—--

የጽዮንን በዓል አክብረው ከተመለሱ ምዕመናን ውስጥ መኪና ተገልብጦ የአራት ሰዎች ሕይወት አለፈ

ከዘመድኩን በቀለ
በየዓመቱ ህዳር 21 ቀን በታላቅ መንፈሳዊ ሥነሥርዓት የሚከበረውን የህዳር ጽዮን በዓል ለማክበር ከአዲስ አበባ ተነስቶ የነበረው የአቡነ አሮን መንፈሳዊ የጉዞ ማኅበር መኪና 60 ተጓዥ ምእመናንን ይዞ ከበዓሉ መልስ ዛሬ ከወልድባ ሰቋር ጉብኝት በኋላ ወደ ጎንደር በመመለስ ላይ ሳለ ከአንባ ጊዮርጊስ ወጣ ብሎ ልዩስሙ 44 ተብሎ ከሚጠራው ሥፍራ ላይ አደጋ ደርሶበት ብዙ ሰው ተጎዳ ።
axum
 በአደጋው እስካሁን 3 ተጓዥ መንገደኞች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን ቁጥራቸው በዛ የሚሉት ደግሞ ቀላልና ከባድ የሆነ ጉዳት ደርሶባቸው በጎንደር ሆስፒታል በሕክምና ላይ ይገኛሉ ።

 ከእነዚህ መንገደኞች መሃል በተለይ ዘማሪ ምትኩ በከባድ ጉዳት ውስጥ እንደሚገኝ በአደጋው ሰዓት ወዲያው በመድረስ የሞቱትንም ሆነ የቆሰሉትን ወደ ሆስፒታል የወሰደው የማኀበረ ወይንዬው ሰብሳቢ መ/ር ደረጀ ነጋሽ በስልክ ገልጾልኛል ።
 የአደጋው አድራሽ በቅጽል ሰሙ ቀይ ሽብር በመባል የሚታወቀው የቻይና ስሪት የሆነው መኪና ሲሆን የአደጋውን መንስኤ ግን የክልሉ ፖሊስ እያጣራ መሆኑንም ደረጀ አክሎ ነግሮኛል ።
አሁን ይህን ማስታወሻ በመጻፍ ላይ ሳለሁ ደረጀ የሟቾች ቁጥር ወደ 4 ከፍ ብሏል ብሎኛል።
እንግዲህ ምን እንላለን ያረፉትን ነፍሳቸውን ይማር ።

ኦባንግ ሜቶ ከኢትዮጵያውያን ጋር በሚኒሶታ ሊወያዩ ነው

(ዘ-ሐበሻ) ታዋቂው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ኦባንግ ሜቶ ወደ ሚኒሶታ በመምጣት የፊታችን ቅዳሜ ዲሴምበር 6 ቀን 2014 ዓ.ም ከኢትዮጵያውያን እና ከትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር እንደሚወያዩ ታወቀ።
Save Ethiopian Meeting with Obang metho in Israel
ቅዳሜ ሴንት ፖል በሚገኘው ኬሊ ኢን ሆቴል ከቀኑ 3፡00 ሰዓት ጀምሮ በሚደረገው በዚህ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ ኦባንግ ሜቶ በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ዙሪያ ከሚኒሶታ ሃገር ወዳዶች ጋር ይየሚነጋገሩ ሲሆን የስብሰባው ዋና ዓላማም በተለይ በተቃዋሚዎች አካባቢ መደረግ ስላለባቸው የጋራ ትብብሮች እንደሚሆን አስተባባሪው አቶ ግርማ ብሩ ለዘ-ሐበሻ ገልጸዋል።
“እንደሚታወቀው የኢሕአዴግ መንግስት ላለፉት 23 ዓመታት ካለምንም እፍረት ስልጣኑን በእጁ እንዳስገባ ይገኛል፤ ይህ ሆኖ እያለ ግን በተቃውሚዎች በኩል እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ሁሉም በየፊናው በመሆኑ ትግሉን ወደ አንድ አቅጣጫ ለማምጣትና አንድ ግብ ያለው ትግል ለማካሄድ አቶ ኦባንግ ሜቶን ወደ ሚኒሶታ ጋብዘናል” ያሉት አስተባባሪው አቶ ግርማ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በተጠቀሰው ሆቴል ከቀኑ 3፡00 ሰዓት ጀምሮ በመገኘት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል። ኢትዮጵያውያኑ ከኦባንግ ሜቶ ጋር ቅዳሜ ዲሴምበር 3 ቀን 2014 ዓ.ም የሚያደርጉበት የሰብሰባ አድራሻ 161 St Anthony Ave, St Paul, MN 55103 ሲሆን የበለጠ መረጃም በ612-325-8690 ማግኘት እንደሚቻል አቶ ግርማ አስታውቀዋል።
በሌላ ዜና በያዝነው ዲሴምበር ወር በአኝዋክ በአንድ ቀን ከ400 ሰዎች በላይ የተጨፈጨፉበት 11ኛ ዓመት የመታሰቢያ ቀን በዚሁ በሚኒሶታ በጋምቤላ ኮምዩኒቲ አማካኝነት ይዘከራል።

Monday, December 1, 2014

አስተዳደሩ የትብብሩን የ24 ሰዓት ሰላማዊ ሰልፍ እውቅና አልሰጠሁም አለ

ነገረ ኢትዮጵያ
negere-ethiopia-photo1•ትብብሩ አስተዳደሩ እውቅና ሰጭም ነፋጊም አለመሆኑን በመግለጽ ድጋሜ ደብዳቤ ጽፏል
የ9ኙ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ትብብር ህዳር 27 እና 28/2007 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ሊያደርገው ላቀደው የአዳር ሰላማዊ ሰልፍ አስፈላጊው ትብብር እንዲደረግለት፣ ህዳር 17 ቀን 2007 ዓ.ም በፃፈው ደብዳቤ መጠየቁ የሚታወስ ቢሆንም አስተዳደሩ በቁጥር አ.አ/ከፅ/10/30.4/55 ህዳር 19 ቀን 2007 ዓ.ም በፃፈው የመልስ ደብዳቤ ለሰላማዊ ሰልፉ እውቅና አለመስጠቱን አስታውቋል፡፡
ትብብሩ ለሰልፉ የመረጠው ቦታ መስቀል አደባባይ ሲሆን፣ አስተዳደሩ በበኩሉ የ24 ሰዓቱን ሰልፍ ላለማወቁ ምክንያት ነው ያለውን ሲያስቀምጥ፣ ‹‹የተጠየቀው ቦታ በልማት ምክንያት የትራፊክ መጨናነቅና ትላልቅ የመንግስት ተቋማት እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ያሉበት ስለሆን ጥያቄውን ተቀብለን ለማስተናገድ የምንቸገር መሆኑን እየገለጽን፣ የአደባባይ ስብሰባውም ሆነ ሰላማዊ ሰልፉ እውቅና ያልተሰጠው መሆኑን እናስታውቃለን›› በማለት አስፍሯል፡፡
የትብብሩን ሰልፍ እያስተባበሩ ያሉት ፓርቲዎች አመራሮች ዛሬ ለአስተዳደሩ በጻፉት ደብዳቤ እንደጠቀሱት ደግሞ፣ የሰላማዊ ሰልፍና ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 3/1983 አንቀፅ 6 ንዑስ አንቀፅ 2 “የከተማው ወይም የአውራጃው አስተዳደር ጽ/ቤት በዚህ አዋጅ አንቀፅ 6 ንዑስ አንቀፅ 1 የተመለከቱትን ሁኔታዎች በማገናዘብ ሰላማዊ ሰልፍ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባው በሌላ ጊዜ ወይም በሌላ ሥፍራ ቢደረግ ይሻላል የሚል አስተያየት ካለው ምክንያቱን በመግለፅ ይህንኑ ጥያቄው በደረሰው በ12 ሰዓት ውስጥ በጽሁፍ ለአዘጋጁ የማሳወቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሆኖም የከተማው ወይም የአውራጃው አስተዳደር ጽ/ቤት ሰላማዊ ሰልፍ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባው ምን ጊዜም ወይም በየትኛውም ቦታ ሊካሄድ አይችልም ማለት አይችልም” በማለት አስተዳደሩ እውቅና የመንፈግ ስልጣን እንደሌለው ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም፡-
‹‹1ኛ. እውቅና እንዲሰጥ የተጠየቀ ማንኛውም አካል ከላይ የተደነገገውን በማገናዘብ ለሌላ ጊዜና በሌላ ቦታ እንዲደረግ ሃሳብ ከማቅረብ ውጭ ሰላማዊ ሰልፉ ምን ጊዜም ወይም በየትኛውም ቦታ ሊካሄድ አይችልም ለማለት ለመስሪያ ቤታችሁ ስልጣን ያልተሰጠ በመሆኑ፤
2ኛ. ሰላማዊ ሰልፉና ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ የሚከናወኑት በመሰረታዊነት ለትላልቅ የመንግስትና ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ለማሳወቅ በመሆኑ በእነዚህ አካባቢ ሰልፍና ሕዝባዊ ስብሰባ ማድረግ በአዋጁ ያልተከለከለ በመሆኑ፤
ለጥያቄያችን የተሰጠን መልስ ከምክንያታዊነትና ህጋዊነት ውጭ ሰልፉ እንዳይካሄድ ለመከልከል ስለሆነ እንዲህ ዓይነቱን ኢ-ህጋዊ የሆነ ውሳኔና አሰራር ፈፅሞ የማንቀበል በመሆኑ አስቀድመን ባሳወቅነው መሰረት ሰላማዊ ሰልፉን በተጠቀሰው ቀን፣ ሰዓትና ቦታ የምናካሂድ መሆኑን እያሳወቅን በጽ/ቤታችሁ በኩል አስፈላጊው ትብብር እንዲደረግልን በድጋሚ እናስታውቃለን›› ብሏል ትብብሩ ዛሬ ለአስተዳደሩ በጻፈው ደብዳቤ፡፡

1255213_621181758007486_3432632376110383431_n

የሐበሻ ሬስቶራንት ሥራ አስኪያጅ ድምፃዊት ኢየሩሳሌም አስፋው (ጄሪን) ለምን ውስጥ እግሯን እና ታፋዋን በቢለዋ ወጋቻት? (ያንብቡ)

ድምፃዊት ኢየሩሳሌም አስፋው (ጄሪ) በሙዚቃ አፍቃሪያን ዘንድ ‹ሀሎ አዲስ አበባ› በተሠኘ ተወዳጅ ዘፈኗ ትታወቃለች፡፡ እስካሁን ድረስ ሁለት የሙዚቃ አልበሞች የሠራች ሲሆን ስድስት ያህል ነጠላ ዜማዎችም አሏት፡፡ ከልጅነቷ ጀምሮ ባደረባት የሙዚቃ ፍቅር የተለያዩ ድምፃዊያንን ዘፈኖች ትጫወት የነበረ ሲሆን ታዋቂው ኮሜዲያን አለባቸው ተካ በችሎታዋ ተደንቆ በተወዳጁ ‹‹አለቤ ሾው›› የቴሌቪዥን ፕሮግራሙ ላይ እንግዳ አድርጓት ነበር፡፡ የተለያዩ ነጠላ ዜማዎች ከማውጣቷ ጎን ለጎን ሶስተኛ የሙዚቃ አልበሟን እየሠራች ባለበት በዚህ ወቅት ከሠዎች በተሠነዘረባት ጥቃት ያልተጠበቀ ጉዳት ደርሶባት ህክምና እየተከታተለች ትገኛለች፡፡ የቁምነገር መጽሔት ድምፃዊቷን ያለችበትን ሁኔታ አነጋግሯል፤ መልካም ንባብ
1425440_1379530885635493_1774138377_o
ቁም ነገር፡- ሙዚቃ መጫወት የጀመርሽው መቼ ነበር?
ኢየሩሳሌም፡- ወደ ሙዚቃ ህይወት የገባሁት በልጅነቴ ነው፡፡ ወላጅ አባቴ ከመሞቱ በፊት ‹‹ልጄ ዘፍና ትጦረኛለች›› ይል ነበር፡፡ አያቴ ግን አይፈቅድልኝም ነበር፡፡ ቀበሌ እሠለጥን በነበረበት ጊዜ ከሠባ አምስት ተወዳዳሪዎች መካከል አንደኛ ወጥቼያለሁ፡፡ በውድድሩ ላይ እኔ የምዘፍነው የንዋይን ነው ስላቸው ሳቁብኝ፡፡ ከዚያም የማርታ አሻጋሪን፣ የበዛወርቅ አስፋውንና የአስቴር ከበደን ዘፈኖች ዘፍኜ አሸነፍኩና እዚያ ጀመርኩ፡፡
ቁም ነገር፡-ከዚያ በኋላስ የት የት ሠርተሻል?
ኢየሩሳሌም፡- ሴሌክት የምሽት ክለብ ለሠባትና ስምንት ዓመት ያህል የሠራሁ ሲሆን ‹ሀሎ አዲስ አበባ›› የሚለው የመጀመሪያ የሙዚቃ አልበሜ ከወጣ በኋላ ቦሌ ሚካኤል አካባቢ የራሴን ምሽት ክለብ ከፍቼ መስራት ጀምሬ ነበር፡፡ ግን አላዋጣኝም፡፡ ከዚያ ደግሞ ‹‹ከሚሚ መጋሎ››፣ ሐሊማ አብዱረህማን እና ከዝናሽ (ሀቢቢ) ጋር በጋራ የምሽት ክለብ ከፍተን ለመስራት ሞክረን ነበር፡፡ በመሀል ልጅ ወለድኩና አቋረጥኩኝ፡፡
ቁም ነገር፡- ወደ ሐበሻ ሬስቶራንት ገብተሽ መዝፈን የጀመርሽው መቼ ነበር?
ኢየሩሳሌም፡- ከአምስት ከስድስት ዓመት ምናምን በፊት ነው፡፡ በ2005 ዓ.ም ሮዛ ግዛው በተባለች ማናጀሬ በኩል ወደ ዱባይ ሄጄ ከታንዛንያ፣ ከናይጄሪያና ከኮንጎ የሙዚቃ ባለሙያዎች ጋር እየሠራሁ ሙሉውን ዓመት አሣልፌያለሁ፡፡ ገራጅ የሚባል የምሽት ክበብ ነበር የምንሠራው፡፡ እንዲያውም ሌሎቹ ባለሙያዎች በየሶስት ወሩ ሲቀያየሩ እኔ ምንም ቪዛ ሳልቀይር እዚያው መቆየት ችያአለሁ፡፡ ክለቡ ከሠባት መቶ እስከ ስምንት መቶ የሚደርሡ ሰዎች ይይዛል፡፡
የጊኒ፣ የታንዛኒያ፣ የናይጄሪያ፣ የኬንያ ዜጎች እንዲሁም አረቦችና ህንዶች የሚዝናኑበት ሲሆን አንዳንድ አበሾችም አልፎ አልፎ ይመጡ ነበር፡፡ ሽልማታቸው፣ ፍቅራቸው ሁሉ ልዩ ነው፡፡ የእነሡን ሙዚቃ የምሠራላቸው ያህል በተለያየ ሁኔታ ነው የሚያዩኝ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ዘፋኝ አይተን አናውቅም ብለው ነበር ገንዘብ የሚሸልሙኝ፡፡
ቁም ነገር፡- ሐብታም ሆነሽ ነበራ ከውጪ የመጣሽው? (ሣቅ)
ኢየሩሳሌም፡- ብዙ ቤተሠብ ነው ያለኝ፡፡ ቤት ተከራይቼ ነው የምኖረው፡፡ ዱባይና አቡዳቢ እየተመላለስኩ ቤተሠቦቼን ነበር የምረዳው፡፡ ያስተማርኳቸው፣ የዳርኳቸው አሉ፡፡ ለእኔ ብዬ ያደረኩት ነገር የለም፡፡
ቁም ነገር፡ እስካሁን ድረስ ምን ያህል የሙዚቃ አልበሞች ሠርተሻል?
ኢየሩሳሌም፡- የመጀመሪያ አልበሜ ‹ሀሎ አዲስ አበባ› የሚለው ነው፡፡ በ1997 ዓ.ም በህዳር ወር ነበር የወጣው፡፡ ‹ይጠራኛል› የሚል ሌላ አልበምም አሣትሜ ነበር፡፡ በአጋጣሚ የክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ህይወት ያለፈበት ቀን ላይ ነበር ሣይታሠብ የወጣው፡፡ በዚህ ምክንያት ሣይደመጥ ቀረ፡፡ በ2006 ዓ.ም ከዱባይ የመጣሁት ለአልበም ሥራ ነው፡፡ የአልበም ሥራ መስራት ጀምሬያለሁ፡፡ የሁለት ዓመት ቪዛ እያለኝ ነው የአልበም ሥራዬን ለመጨረስ የመጣሁት፡፡ ጥሩ ጥሩ ግጥምና ዜማዎች ሠብስቤያለሁ፡፡ ከአለማየሁ ይለፍ ጋር ነው የምሠራው፡፡
ቁም ነገር፡- የተለያዩ ነጠላ ዜማዎችም አሉሽ አይደል?
ኢየሩሳሌም፡- አዎ! ከ‹ሀሎ አዲስ አበባ› አልበሜ በኋላ ያወጣሁት ‹ጀነናው› የሚል ነጠላ ዜማ አለ፡፡ የሄለን በርሄ ‹‹ኦዛዛ አሌና›› የተሠኘው ዘፈን ያለበትና የሌሎች ዘፋኞችንም ሥራዎች የያዘ ፣‹ድሪም ኮሌክሽን› የሚል አልበም ላይ የተካተተ ነበር፡፡ ‹አግባ አግቢ› የሚል ነጠላ ዜማም ሠርቼያለሁ፡፡ ‹ደቅ ላይ› የሚል የባህል ዘፈን፣ ‹ዞማ ዞማ› የሚል በኮንሶ ስልት (ሪትም) የተሠራ ነጠላ ዜማም አለኝ፡፡ የተለያዩ ቪዲዮ ክሊፖችንም እሠራለሁ፡፡ አላረፍኩም፡፡ እለፋለሁ፡፡ በጣም እለፋለሁ፡፡ የተቀመጥኩበት ጊዜ የለም፡፡ እንደኔ የሚለፋ ሠው ያለ አይመስለኝም፡፡ ለምን እግዚአብሔር ይህን እንዳደረገ አላውቅም፡፡
ቁም ነገር፡- ቅድም ልጅ እንዳለሽ ነግረሽኛል፡፡ የትዳር ሁኔታ ግን አላነሣንም?
ኢየሩሳሌም፡- ልጅ ወልጄያለሁ፡፡ አባቱ ከእኔ ጋር አይኖርም፡፡ ተለያይተናል፡፡
ቁም ነገር፡- ስንት ዓመቱ ነው?
ኢየሩሳሌም፡- እግዚአብሔር የተመሠገነ ይሁን ስምንተኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ ልደቱን ለማክበር ሶስት ቀን ሲቀረው ነው የታረድኩት፡፡
ድምፃዊት እየሩሳሌም እግሯን እና ታፋዋን ከተሰፋች በኋላ
ድምፃዊት እየሩሳሌም እግሯን እና ታፋዋን ከተሰፋች በኋላ
ቁም ነገር፡- በቅርቡ አንድ አደጋ ደርሶብሽ እንደነበር ሠምተናል፡፡ ምን ነበር ምክንያቱ? ሁኔታው እንዴት ተፈጠረ?
ኢየሩሳሌም፡- ‹እስማማለሁ አልስማማም› በተሠኘው የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ እንግዳ ሆኜ ቀርቤ ነበር፡፡ እና ፕሮግራሙ በሚለቀቅበት ምሽት ቀድሜ ነው ወደ ሐበሻ ሬስቶራንት የገባሁት፡፡ ለምሽት ስራዬ ዝግጁ ሆኜ ሚኒስከርት ለብሼና ሂል ጫማ አድርጌ ነው ወደ ሬስቶራንቱ የገባሁት፡፡ ሰው ገብቷል ሙዚቃ ግን አልተጀመረም፡፡ ለባለቤቱ ደውዬ የሙዚቃ ስራ እስከሚጀመር ቴሌቪዥን እንዲያስከፍትልኝ ስነግረው እርሡ ለማናጀሯ ደውሎ ‹‹ሙዚቃ አልተጀመረም›› ሲላት ከእኔ ጋር መነጋገር ትጀምራለች፡፡ ከእሷ ጋር ስንነጋገር ሁለቱ የሬስቶራንቱ አስተናጋጆችሙዚቃ እንዳልጀመረ ለምን ነገርሽው በማለት መጥተው አንዷ ገፍታ ጥላኝ ላዬ ላይ ወጣች፤ ሌላኛዋ ደግሞ ፀጉሬን ያዘችኝ፡፡ በዚህ መሀል ማናጀሯ ቢላ ይዛ መጥታ የግራ እግሬ መሀል ታፋዬ ላይ፣ ቀኝ እግሬ መቀመጫዬ ላይ እና የቀኝ ውስጥ እግሬን ትወጋኛለች፡፡ የሠውነቴ መጋጋጥ የሚነገር አይደለም፡፡ በወቅቱ ራሴን ስቼ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ፍርድ ይስጠኝ፡፡ የደረሠብኝን ጉዳት እንደዚያ ተቀድጄ ሠውነቴ እየደማ ለሆቴሉ ባለቤት ሄጄ አሣየሁት፡፡ እሡ ሀሌሉያ ክሊኒክ ወስዶ ህክምና እንዳገኝ አደረገ፡፡ ከዚያም ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሄጄ አስመዝግቤ ሁለቱ ሴቶች በቁጥጥር ስር ሲውሉ የሬስቶራንቱ ማናጀር ትጠፋለች፡፡ በቢላ የወጋችኝ የሬስቶራንቱ ማናጀር ለአሥራ ሁለት ቀናት ጠፍታ የእነርሡን መታሠር ስትመለከት ለፖሊስ እጇን ሰጠች፡፡ አሁን ሶስቱም በሦስት ሺህ ብር ዋስ ተፈትተው የፍርድ ቤት ቀጠሮ እየተጠባበቅን ነው፡፡
ቁም ነገር፡- አድናቂዎችሽስ የደረሠብሽን ነገር ሲመለከቱ ምን ተሠማቸው?
ኢየሩሳሌም፡- ማመን ከምችለው በላይ ነው የሠው ምላሽ፡፡ ‹ስንት ዓመት ጠፍተሽብን የመጣሽ ልጅ ምን ብታደርጊያቸው ነው ይህን ያደረሡብሽ› ብለውኛል፡፡ ያላዘነ፤ የማያለቅስ የለም፡፡ ከሱዳንና ከዱባይ እየደወሉ ሲያለቅሱ እኔንም ያስለቅሡኛል፡፡ ብዙ ቦታዎች ላይ መወጋቴ ነው ትልቁ አደጋ፡፡ ደም በብዛት ነበር የፈሠሠኝ፡፡
ቁም ነገር፡- አደጋውን ካደረሱብሽ ሠዎች ጋር የቆየ ቂም ነበራችሁ?
ኢየሩሳሌም፡- ማናጀርዋ ወደ ሬስቶራንቱ ከመጣች ዘጠኝ ወሯ ነው፡ ፡ ሁለቱ ደግሞ ከአስር ዓመት በላይ የቆዩ አስተናጋጆች ናቸው፡፡ መሀል ላይ ማናጀሯ ደሞዝ ስትቆርጥ፣ ሠራተኛ ስታባርር ለምንድነው ይህን የምታደርጊው እያልኩ እናገር ነበር፡፡ ያ ነገር ነው እዚህ ደረጃ ያደረሰን፡፡ ለሠሚም፣ ለተመልካችም፣ ለራሴም ነው (የደረሠብኝ ጉዳት) ትንግርት የሆነብኝ፡፡ እንደተገረዘ ህፃንነበር ቆሜ የምሸናው፡፡ ለሥራ ወጥቼ ያልሆነ ነገር ሆንኩኝ፡፡ ወይ እንደ ጓደኞቼ እንደሚካያ እና እንደ ኢዮብ መኮንን ታምሜ ሰው ሠምቶ ብሞት የተሻለ ነበር፡፡
ቁም ነገር፡- አሁን ያለሽበት ሁኔታ እንዴት ነው? ጤንነትሽ?
ኢየሩሳሌም፡- ከሠባት ቀን ህክምና በኋላ የቤቱ ባለቤት እኔን ማሣከም አቁሟል፡፡ የጭንቅላቴን ውጤት መስማት አልተቻለም፡፡ ህክምና ላይ ያለው ነገር በሙሉ ቆሟል፡፡ የሁለት ወር ደመወዝም አልተሠጠኝም፡፡ ቤተሰቦቼ፣ ጓደኞቼና እኔ ራሴ ነኝ እየተሯሯጥን ያለነው፡፡ አሁን ቤት ውስጥ ነው ያለሁት፡፡ መጥቶም፣ ጠይቆኝም አያውቅም፡፡ የውስጥ እግሬና ጭንቅላቴ አሁንም ያመኛል፡፡ አንደኛው ስካን ማድረጊያ መሣሪያ በሀገር ውስጥ የለም ተብሎ እየፈለግኩኝ ነው፡፡ እግሬ በጣም ነው የተጎዳው፡፡ ውስጥ እግሬ ድረስ ነ በር የተወጋሁት፡፡ ሌላውን የልጄ አምላክ አትርፎኛል፡፡
ቁም ነገር፡- ከዚህ በኋላ አበሻ ሬስቶራንት ተመልሠሽ የምትሠሪ ይመስልሻል?
ኢየሩሳሌም፡- በፍፁም፡ ፡ አሁን ለሦስተኛ ስራዬ ‹‹ውብ አዲስ አበባ›› የሚል ትልቅ ፖስተር (አበሻ ሬስቶራንት) ለጥፌያለሁ፡፡ ሰው እኔን ብሎ ነው የሚመጣው፡፡ ማናጀሯ ግን አርቲስትነቴን እንኳን አላየችውም፡፡
ቁም ነገር፡- ከዚህ ቀደም ‹‹ሐሎ አዲስ አበባ›› የሚል የሙዚቃ አልበም አሣትመሻል፡፡ አሁን ደግሞ ‹‹ውብ አዲስ አበባ›› የሚል አልበም ነው እየሠራሽ ያለሽው፡፡ አዲስ አበባ ላይ የተለየ ትኩረት የሰጠሽበት ምክንያት ምንድን ነው?
ኢየሩሳሌም፡- ጨርቆስ ነው ተወልጄ ያደግኩት፡፡ ከወላጅ አባቴ ቤተሰቦች ጋር ነው ያደግኩት፡፡ አዲስ አበባ አገርህ ናት፤ መለያህ ናት፡፡ ውጪ ሀገር በምሔድበት ወቅት ይከፋኛል፡፡ እዚህ ደግሞ አየሩ ያምራል፡፡ ባህል አለኝ፡፡ ያለው ለሌለው ያበድራል፡፡ እዚያ ናፍቆት አለ … ብዙ ነገር አለው፡፡
አሁን የምሠራው ‹‹ውብ አዲስ አበባ›› የሚል አልበም ደግሞ የአሁኗ አዲስ አበባ መጀመርያ ከነበረችው የተለየች መሆኗን የሚያሳይ ነው፡፡

በድቡብ ሱዳን አራት ኢትዮጵያውያን በጥይት ተመቱ

news
በደቡብ ሱዳን በዋና ከተማዋ ጁባ አንድ ወንድና አንድ ሴት ሲገደሉ ሁለት ሴቶች ግን በጠና ቆስለው ወደ ኢትዮጵያ መወሰዳቸውን ኢሳት ወኪሎቹን ጠቅሶ ዘገበ። የሁለቱም ሟቾች አስከሬንም በኢትዮጵያውያን እርዳታ ወደ ኢትዮጵያ መሄዱ ታውቆል:: ሰዎቹ በምን ሁኔታ እንደተገደሉና እንደቆሰሉ
እንዲሁም ጥቃቱን ያደረሱትን ወገኖች ዝርዝር ለማወቅ አልተቻለም ያለው ኢሳት በደቡብ ሱዳን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ በኢትዮጵያውያን የሚደረገውን ግፍና እንግልት ከመከታተል ይልቅ በዶላር ጥቁር ገበያ ምንዛሪ መሰማራቱን የገለጸው ወኪላችን ፣ የቀድሞ የህወሃት ባለስልጣናት በጁባ ከተማ የሚያራምዱትን የቢዝነስ ተቋምና በጋምቤላ በኩል የሚያመጡትን የጤፍና የተለያየ ሸቀጣሽቀጥ ንግድ ጉዳይ ቅድሚያ በመስጠት አብዛኛው ኢትዮጵያውያን የሚያቀርቡትን አቤቱታ እንደማይሰማ ተናግሯል። ለህወሃት አባሎች ህጋዊ የመኖረያ ፈቃድና የንግድ ፈቃድ ለማስወጣት የጁባ ባለስልጣናትን ደጅ የሚጠናው ኢምባሲው ምርቶችን ወደ ደደቡብ ሱዳን በማስገባት በኩል ወኪል ሆኖ እየሰራ መሆኑን ጠቅሷል።