Thursday, December 4, 2014

የ24 ሰዓቱ ሰልፍ ቅስቀሳ ተጠናክሮ ቀጥሏል • 5 የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ታስረዋል

semayawi
ህዳር 27 እና 28 2007 ዓ.ም የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር የሚያደርጉት የአዳር (24 ሰዓት) ሰልፍ ቅስቀሳ ተጠናክሮ መቀጠሉን የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃ ላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ እስካሁን ሰው በሰውና ቲሸርት በመልበስ ቅስቀሳ ሲደረግ እንደቆየና በተለይ ዛሬ ህዳር 24/ 2007 ዓ.ም ከሰዓት ጀምሮ በአዲስ ከተማ፣ ጉለሌ፣ አራዳ፣ የካ፣ ንፋስ ስልክ፣ ኮልፌና ሌሎች የአዲስ አበባ ክፍለ ከተማዎች ወረቀት በመበተን የተሳካ ቅስቀሳ መደረጉን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል አራዳ ክፍለ ከተማ ፒያሳ አካባቢ ለአዳር ሰልፉ ሲቀሰቅሱ ከነበሩት መካከል የሰማያዊ ፓርቲ አባላት የሆኑት ሜሮን አለማየሁ፣ ወይንሸት ንጉሴ፣ ባህረን እሸቱ፣ ማቲያስ መኩሪያ እንዲሁም ጉለሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ ሲቀሰቅስ የነበረው ሲሳይ በፖሊስ ተይዘው መታሰራቸው ተግልጾአል፡፡
ከአሁን ቀደም ለሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ቅስቀሳ ላይ ሲያደርጉ በርካታ የፓርቲው አመራሮችና አባላት መታሰራቸውን ያስታወሱት አቶ ዮናታን ‹‹ይህ የገዥው ፓርቲ የተለመደ እርምጃ ነው፡፡ በቀጣይነትም ሌሎች አባላትንና አመራሮች መታሰራቸው አይቀረም፡፡ ትግሉ መስዋዕትነት የሚያስከፍል እንደመሆኑ በእስሩ ሳንገታ ትግሉን እንቀጥላለን፡፡›› ሲሉ እንቅስቃሴያቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡ የዛሬው ቅስቀሳ 12 ሰዓት ላይ የተጠናቀቀ ሲሆን ነገ ጠዋት ጀምሮ በተለያዩ የአዲስ አበባ ክፍሎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

No comments:

Post a Comment