Friday, March 11, 2016

ነገሮች አዲስ የሚሆኑት፣ በእኛ ትናንትን መርሳት – ይገረም አለሙ



ሰሞኑን  በደቡብ ኢትዮጵያ በሚኖሩ ዜጎች ላይ የተፈጸመን የባሪያ ፍንገላን ዘመን የሚያስታውስ  ኢሰብአዊ ድርጊት  የሚያሳይ ፎቶ  በማህበራዊ ድረ-ገጽ ተሰራጭቶ አጀኢብ ጉድ ብለናል፡፡ ነገሩ ትናንትን እየረሳን ዛሬ ለሚያጋጥመን ነገር አዲስ እየሆንን ጉድ ጉድ ለምንለው  ለእኛ ነው እንጂ አዲስነቱ ለወያኔ ከበርሀ ጀምሮ አብሮት የኖረ ተግባሩ ነው፡፡
አይደለም ሥልጣኑን ሊነጥቁት በተቃውሞ የተሰለፉ፣  እኩይ ድርጊቱን እያጋለጡ ማንነቱን ጸሀይ የሚያሞቁ ፣ ሀሳብ እቅዱን እየተቃወሙ ጉዞውን የሚያደናቅፉ ቀርቶ የህውሀት አባል ሆነው ስህተት የጠቆሙ የዓላማቸውን መስመር መሳት የገለጹ የመሪዎቹን እኩይ ተግባር የነቀፉ ወዘተ ምን እንደተፈጸመባቸው የአይን ምስክር የሆኑ ሰዎች ሲናገሩ ሰምተናል ጽፈው አንብበናል፡፡ ባዶ ምንትስ ይባሉ በነበሩት እስር ቤቶች በውልደታቸው ትግሬ በድርጅታቸው ህውኃት የነበሩ ዜጎች ሳይቀሩ ምን አይነት ኢሰብአዊ ድርጊት አንደተፈጸመባቸው እነ ገብረ መድህን አርአያ ደጋግመው የነገሩን ነው፡፡ ዛሬም በተለያየ የሥልጣን ስም ተቀምጠው አረመኔያዊውን ድርጊት የሚፈጽሙ የሚያስፈጽሙት እነዛ የበርሀው ሲኦል እስር ቤቶች ሀላፊዎች የነበሩቱ ናቸው፡፡



12801147_966036103443554_4958790932868175941_n
ለሥልጣናቸው የሚያሰጋ፣ ያሰቡ ያቀዱትን ተፈጻሚ እንዳያደርጉ አንቅፋት የሚሆን፣ ማንም ሆነ ከየትም  ከማጥፋት የማይመለሱት ወያኔዎች (በተለይም አቶ መለስ) ዘር ሀይማኖት ሳይለዩ አስሮ ማሰቃየቱን አፍኖ መሰወሩን ገድሎ መጣሉን ብሎም ርስ በርስ ማገዳደሉን አብይ ተግባራቸው አድርገው የኖሩ ለመሆናቸው  ብዙ እጅግ ብዙ ማረጃዎችን መዘርዘር ይቻላል፡፡
የህውኃት ቀኝ እጅ የነበረው የደህንነቱ ሹም ክንፈየአግልግሎት ግዜው ሲያበቃ እንዴት እንዳስገደሉትና የግድያ ትዕዛዙን በፈጸመው የዋህ ታዛዥ ላይ ያደረጉትን የምናውቅ  በሌላው ኢትዮጵያዊ ላይ የሚፈጽሙት አረመኔያዊ ተግባር ለምን አዲስ አንደሚሆንብንና እንደሚገርመን  ራሱ የሚገርም ነው፡፡ ለህይወታቸው መድህን ለሥልጣናቸው ዘብ ሆነው የኖሩ ሰዎቻቸውን ለማጥፋት የማይመለሱ ሰዎች አንገዛም ባሉ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈጽሙት ኢሰብአዊ ድርጊት ሁሌም አዲስ የሚሆንብን እኛ ትናንትን በመርሳት በሽታ በመለከፋችን  አለያም ሞኝ የሰማ/ያየ እለት እንደሚባለው እየሆነብን እንጂ ድርጊቱ ለወያኔ አዲሰ  አይደለም፡፡ እንደውም  ትናትን የመርሳት ችግራችን ከእባብ አንቁላል ርግብ አይጠበቅም የሚለውን አባባል  አስረስቶን የተቃውሞአችን እንዴትነትና  የጩኸታችን ምንነት  ከወያኔ የባህሪው ያልሆነ ነገር የምንጠብቅ ያስመስለናል፡፡
መቅረጸ ድምጽም ሆነ ምስል ያልደረሰባቸው የአይን ምስክርም ተገኝቶ ይፋ ያላደረጋቸው ብዙ አጅግ ብዙ ዘግናኝ አረመኔያዊ ድርጊቶች በወያኔ ለመፈጸማቸው በመረጃ ከተረጋገጡት ድርጊቶቹ ተነስቶ መገመት ይቻላል፡፡እነዚህ ሰዎች ለሥልጣን የበቁት የመረጃ ማስተላለፊያው ጥበብ እንዲህ ባለልተስፋፋበትና ባልተራቀቀበት ዘመን ቢሆን ምን ያደርጉ ነበር ብላችሁ አስባችሁ ታውቃላችሁ፡፡የሚሰሩት ብቻ ሳይሆን በር ዘግተው በምስጢር የሚነጋገሩት ድምጽ ከምስል እየሾለከ ለአለም ህዝብ አይንና ጆሮ ሲበቃ የማያስደነግጣቸው፣ የማያሳፍራቸውና የማያስፈራቸው (ለነገሩ ማን ሰው ብለው) ወያኔዎች በድብቅ የሚሰሩት ሁሉ ተደብቆ የሚቀር ቢሆን የአረመኔነታቸው መጠን የክፋታቸው ደረጃ  የአገዛዛቸው ግዞት እስከምን ይደርስ አንደነበር መገመት አይገድም፡፡
ጎምቱ ጋዜጠኞች ውሻ ሰው ነከሰ ዜና አይሆንም ሰው ውሻ ቢነክስ ግን ትልቅ ዜና ነው ይላሉ፡፡ የአባባሉ ምንነት ግልጽ ነው፡፡ ውሻ ሰው መንከሱ የተፈጥሮው፣ የባህሪው፣ የሚጠበቅበት ተግባሩም ስለሆነ  ነው ዜና የማይሆነው፡፡ ሰው ግን ውሻ ቢነክስ  ያልተለመደ ብቻ ሳይሆን የማይጠበቅና የማይገመት አዲስ አስገራሚ ክስተት  በመሆኑ ነው ትልቅ ዜና የሚሆነው፡፡
ወያኔም ማሰሩ፣ መግደሉ፣ ማሰቃየቱ፣ መዋሸቱ ፣ማታለሉ ሰው በሀሰት መወንጀሉ ወዘተ  ለሥልጣን የበቃበትና ሀያ አራት ዓመታትም ለመግዛት የቻለበት የተፈጥሮ ባህሪይው እና ተግባሩ  በመሆኑ በዚህ መልክ የሚፈጽማቸው ድርጊቶች ለጋዜጠኞች ዜና ሊሆኑ ቢችሉ አንኳን ለእኛ ለኢትዮጵያውያን  አዲስ ክስተት የሆኑ ያህል ሊያስገርሙን ሊያስደንቁንም ሆነ ሊያስደደነግጡን  አይገባም ነበር፡፡ ምነው ቢሉ እየረሳናቸው ካልሆነ በቀር አብረውን ያሉ ናቸውና፡፡
ይልቁንስ ከወያኔ አንጻር ለመገናኝ ብዙኃን ትልቅ ዜና ሊሆን ከኢትዮጵያውያን አልፎ የኢትዮጵያን ጉዳይ (ለራሳቸውም ዓላማም ሆነ ለህዝቡ ጥቅም ሲሉ) በቅርብ ለሚከታተሉ አለም አቀፍ ግለሰቦች ቡድኖችና መንግሥትታ አስገራሚ ክስተት ሊሆን የሚችለው፡፡
  • ሀያ አራት አመት የተጓዝንበት መንገድ ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ እየወሰደን እንዳልሆነ ስለተገነዘብን  መሰረታዊ ለውጥ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል ቢባል፤
  • ለዘመናት አብረውን የዘለቁ ሀገራዊ ችግሮችን እየቆፈሩ  አዳዲስ ልዩነቶችን መፍጠር የዛሬ መንገዳችንንም ሆነ  የነገ ግባችንን ከማሰናከሉም በላይ ኢትዮጵያን አንደ ሀገር ለማቆየት አስጋቸሪ የሚያደርጉ በመሆናቸው በእርቅ እልባት ሰጥቶ ሀገራዊ መግባባት መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ተገንዝበናል ቢባል፤
  • የገደለ ያስገደለ፣ የሰረቀ የተባበረ፣ በህዝብ ሀብት የከበረ፣ ከህግ በላይ ያደረ፣ወዘተ ለፍትህ ቀርቦ የህግ የበላይነትን በተግባር ለማረጋገጥ የሚያስችሉ  ርምጃዎች መታየት ቢጀመሩ፣
  • የመገናኛ ብዙሀን ሰራተኞች አፋሽ አጎንባሽ መሆናቸው ቀርቶ እውነትን አነፍናፊ፣ የባለሥልጣናትን ፊት እያዩና ትንፋሽ እያዳመጡ የሚሰሩ ሳይሆን የሙያቸውን ነጻነት አክብረው ለህሊናቸው ታማኝ ሆነው መስራት የሚችሉበትን አሰራር ተግባራዊ  የማድረግ ጅምር ቢታይ፤
  • ክልሎች በህገ መንግሥቱ የሰፈረው ሙሉ ነጻነታቸው ተጠብቆ ከህውኃት የሞግዚት አስተዳደር ተላቀው ራስን በራስ የማስተዳደር መብታቸውን በተግባር የሚያረጋግጥ ጅማሮ ቢታይ ፤
  • አባልም ሆነ አጋር የሚባሉት በህውኃት ተፈጥረው በህውኃት የሚዘወሩት ድርጅቶች የአገልጋይነት ዘመናቸውን ፈጽመዋል ተብሎ  በራሳቸው መቆም የሚያስችላቸው እንቅስቃሴ ቢጀመር፡፡
  • በድርጅት ታጥሮ በታማኝነት ተወስኖ ሀገር መምራት አንዳማይቻል የሀያ አራት አመት ልምዳችን አስተምሮናል፣ ስለሆነም ከዚህ በኋላ ሀገር መምራት በእውቀትና ሁሉን አሳታፊ በማድረግ  መሆን እንለበት ተገንዝበናል  ተብሎ ይህንኑ ገቢራዊ ማድረግ የሚያስችል ተግባራዊ ርምጃ  ቢታይ፡፡ ሌላም ሌላም ተመሳሳይ ነገር ከወያኔ ሰፈር ቢታይ ቢሰማ ትልቅ አስገራሚና ማራኪ ድንቅ ዜና ይሆናል፡፡ከዚህ ውጪ መልካም አስተዳደር የፍትህ መጓደል እያሉ ማላዘንም ሆነ  ይቅርታ እንጠይቃለን ማለት ሸብረክ ያሉ መስሎ ግዜ መግዣ የወያኔ የባህሪው  ተግባር ነውና ሊደንቀን አይገባም፡፡
ነገር ግን ወያኔ ያልፈጠረበትን በምክርም በመከራም ሊቀበለው ያልቻለውን ይህን ቅዱስ ተግባር በምን ተአምር ፈጽሞት ይህ  እውነት ሆኖ ለመስማት እንበቃለን! አይታሰብም፡፡ ወያኔዎች ይህን ለማድረግ አንደገና መፈጠር ይኖርባቸዋል፡፡ እኛስ ትናንትን እየረሳን በየግዜው የሚገጥሙንን የወያኔን የባህርይ ድርጊቶች  እንደ አዲስ  ከማየት ለመላቀቅ እና ትግሉን በምሬትና በወኔ ለማጥበቅ  እንደገና መፈጠር ይጠይቀን ይሆን?
ትናትን እየረሱ የእለት የእለቱን አዲስ እያደረጉ መጮኹ በትግሉ ላይ ትልቅ አሉታዊ ተጽእኖ ያለው ለመሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ የበደል ሸክሙ የሚከብደን፣ የጥቃቱ ምሬት የሚመረን፣አንባገነናዊ አገዛዙ የሚያንገሸግሸን ከ እስከ አሁን ያለውን ስናስታውስ ነው፡፡ የዛሬው ሲያስለቅሰን ሲያስቆጣን ብቻ ሳይሆን የትናቱም ሲቆጠቆጠን ነው፡፡  የትናንቱን እየረሳን ለዛሬው አንድ ሳምንት እየጮኸን ከዛም ሌላ አዲስ ነገር እስኪመጣ ይህን እየረሳን  እኩል መብሰል ባለመቻላችን (ጥሬ  ብስልና የአረረ) ነው ሀያ አራት አመት ሙሉ ትግል እንጂ ለውጥ ማስመዝገብ ቀርቶ አዳዲስ ጥቃቶችን ማስቀረት፤ ተጨማሪ ጥፋት እንዳይፈጸም ማስቆም ወያኔን ከደደቢት ህልሙ ስንዝር መግታት  ያልቻልነው፡፡  እውቁ የጽሁፍ ሰው አቶ ከበደ ሚካኤል ልጆች ሆነን ባነበብነው አንድ ጽሁፋቸው ፤
ያለፈው ሲረሳኝ መጪውን ሳላውቀው
እኔ መቼ ይሆን የምጠነቀቀው፤  ብለው የነበረው  ከላይ ለተገለጸው  ለእኛ እኛነት  በቂ ገላጭ አይሆንም ትላላችሁ?

9 ስደተኞችን ደብዳቤ ጽፎ ከአሜሪካ ወሰዳቸው




“ከህወሃት በላይ በራሳችን አዝኛለሁ” ኦባንግ ሜቶ
miami
ከተለያዩ አገራት አሜሪካ ገብተው የስደት ማመልከቻ ያስገቡ 9 ኢትዮጵያውያንን ህወሃት ተረከቦ ወደ አገር ቤት እንደወሰዳቸው ታወቀ። አንዱ ራሱን ለማጥፋት ሞከሮ ነበር። ወደ ኢትዮጵያ ቢሄድም የጤናው ሁኔታ አልታወቀም። ድርጊቱን አስመልክቶ አቶ ኦባንግ ሜቶ “ከህወሃት ተግባር በላይ በራሳችን አዝኛለሁ” ሲሉ ወጣቶቹን ለማዳን ያደረጉት ጥረት መረጃው ዘግይቶ ስለደረሳቸው አለመሳካቱን አመለከቱ።
“ለቤተሰቦቼ የት እንዳለሁ እንኳን ነግሬያቸው አላውቅም” ሲል የተናገረውን ወጣት ጨምሮ ህወሃት የተረከባቸው ኢትዮጵያዊያን ወግኖች አሜሪካ ለመድረስ እስከ 14 ወራት ፈጅቶባቸዋል። በብራዚል፣ በኮሎምቢያ ጫካ አቋርጠው፣ በፓናማ ወንዝ ተሻግረው፣ በሜክሲኮ አድርገው በአጠቃላይ እስከ 16 የሚደርሱ አገራትን አልፈው በተለያዩ መንገዶቸ አሜሪካ ደርሰው ጥገኝነት የጠየቁት ወገኖች ህጉ ከሚፈቅደው ውጪ ከስድስት ወር በላይ በፍሎሪዳ ጠቅላይ ቅዛት ማያሚ እስር ቤት መቆየታቸውን ለአቶ ኦባንግ በአስራ አንደኛው ሰዓት የላኩት “የድረሱልን” ደብዳቤ ያስረዳል። መረጃቸው እንደሚያመለክተው ከተለያየ የኢትዮጵያ ክፍል የመጡት ወገኖች በፍሎሪዳ እስርቤት ከአንድ ወር እስከ አመት ተኩል ድረስ በእስር ቆይተዋል፡፡
አቶ ግርማ ብሩ የሚመሩት የህወሃት የአሜሪካ ቢሮ ስደተኞቹ ቢመለሱ ምንም አይሆኑም፣ ምንም አይደርስባቸውም፣ ሰላማዊ ኑሮ መኖር ይችላሉ፣ ወዘተ በማለት በጻፈው ደብዳቤና አዘጋጅቶ በሰጠው የመጓጓዣ ሰነድ አማካይነት ወጣቶቹ ተላልፈው ሊሰጡት ችሏል።
ህወሃት በኤርትራዊነት መታወቂያ የራሱን ወገኖች ለስደት በምዕራባውያን አገራት እየላከ ኢትዮጵያውያንን ሲያሰልል፤ በባህርና በበረሃ ተንገላተው አሜሪካ የገቡትን ምስኪን ዜጎች ላይ የወሰደው ርምጃ “ዲያስፖራውን የመበቀያ አንዱ አካል ነው” ተብሏል።
“ኑሮዬ ሳይስተካከል ለቤተሰቦቼ የት እንዳለሁ እንኳን አላሳውቅሁም። እናትና አባቴ ልሙት፣ ልኑር አያውቁም፤ ከተለየኋቸው ጊዜ ጀምሮ ስልክ ሳልደውል አራት አመት ከ11 ወራት አልፈውኛል” ሲል ለአቶ ኦባንግ የድረሱልኝ ጥሪ ካሰሙት ወጣቶች አንደኛው ተናግሯል፡፡ ዘጠኙ በአንድነት ተላልፈው ከመሰጠታቸው ጥቂት ቀናት አስቀድሞ ነበር አቶ ኦባንግ ደብዳቤያቸው የደረሳቸውና ጉዳዩን የሰሙት።
“እንደሰማሁ” አሉ አቶ ኦባንግ “ወዲያውኑ ስደተኞቹን የሚወክል ጠበቃ ያዝኩ። የወጣቶቹ ከስድስት ወር በላይ መታሰር ከህግ አንጻር አግባብ ባለመሆኑና ስደተኞቹ ሊመለሱ እንደማይገባ ለማውቃቸው እንደራሴዎችና ሴናተሮች በማስረዳት የእስር ውሳኔ ላስተላለፉት ዳኛ ደብዳቤ ሊላክ የሰዓታት ዕድሜ ሲቀር መርዶውን ሰማሁ” ብለዋል፡፡
ለወትሮው ረጋ ብለው በመናገር የሚታወቁት ኦባንግ “ለአንድ ቀን ተቀደምን” ሲሉ በቁጣ ነበር ስሜታቸውን የገለጹት። የጎልጉል የአሜሪካ ዘጋቢ ያነጋገራቸው አቶ ኦባንግ ቁጣቸውን ሊደብቁ በማይችሉበት ሁኔታ “ከህወሃት በላይ በራሳችን አዘንኩ” ብለዋል። “ለምን?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱም “በተመሳሳይ መንገድ ተሰድደው፣ ታስረው፣ ዛሬ በመልካም ሁኔታ ላይ ያሉ ወገኖች የ5 ሺህ ዶላር ዋስ ሆነው ልጆቹን ማስፈታት ይችሉ ነበር ። ዳሩ ምን ያደርጋል ሁላችንም መነሻችንን እንረሳለን” ሲሉ ጉዳዩን አስቀድመው የሚያውቁ ወገኖች ላሳዩት ቸልተኛነት ወቀሳ ሰንዝረዋል።
“አቶ ግርማስ ቢሆኑ” አሉ አቶ ኦባንግ “ይህን ደብዳቤ እንዴት ይጽፋሉ? ወይም ሲጻፍ እንዴት ዝም ይላሉ? የጉዞ ሰነዱ ተሰርቶ እንዲላክስ ለምን ይፈቅዳሉ? ምንም ቢሆን እርሳቸው ሳያውቁ የሆነ ነገር የለም፤ ኅሊና ካላቸው በጣም ሊያፍሩበት ይገባቸዋል፤ እርሳቸውም ሆኑ አብረዋቸው የሚሰሩት ራሳቸውን በእነዚህ ልጆች ጫማ አስገብተው ማየት ይገባቸው ነበር፤ እነርሱ አገልግሎታቸውን ሲጨርሱ እዚሁ ከነቤተሰቦቻቸው ጥገኝነት ጠይቀው ኑሯቸውን ይቀጥላሉ፤ በአየር፣ በምድር፣ በወንዝ በስንት ስቃይና መከራ እዚህ የደረሱትን ልጆች ግን ደህና አገር እንዳለው የጉዞ ሰነድ ልከው ባዶ እጃቸውን ወደመጡበት እንዲመለሱ ያደርጋሉ፤ ይህ ወራዳና አጸያፊ ተግባር ነው፤ አገሪቱን ወይ በትክክል አያስተዳድሩ ወይ አገሩን ለቅቀው የሚወጡትን የፈለጉበት እንዳይኖሩ በሩ ይዘጋሉ፤ ኅሊና አለኝ ለሚል ሰው ይህ እጅግ አሳፋሪ ነው” ሲሉ ይወቅሷቸዋል።
ከስደተኞቹ መካከል አንዱ ወጣት በአገር ውስጥ የሚካሄደው ሰቆቃ ያስመረረው ከመሆኑ የተነሳ ወደ ኢትዮጵያ ከሚመለስ በአሜሪካ እስርቤት ለመሞት እንደሚመኝ መናገሩን አቶ ኦባንግ ጠቁመዋል፡፡ “በረሃና ወንዝ ስናቋርጥ በርካታ ወንድምና እህቶቻችንን አጥተናል፤ ማንም ስለ እነርሱ ግድ ያለው የለም፤ ታዲያ ለምን ለኛ ግድ ያላቸው ለመምሰል ይሞክራሉ” በማለት እንዳወራላቸው አቶ ኦባንግ ጠቅሰዋል፡፡
አገር ቤት ስራ አለመኖሩን፣ ችጋር፣ ረሃብና ድርቅ ዜጎችን እየጠበሰ መሆኑንን፣ እስርና ግድያ፣ አፈና ባለበት ሁኔታ እነዚህን ምስኪኖች ሰብስቦ መውሰድ ህወሃት ዲያስፖራውን ከመበቀል ያለፈ ትርጉም እንደሌለው በመግለጽ ዜጎች ከወዲሁ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ አመልክተዋል።
የአሜሪካ እንደራሴዎች ምክርቤት አባላት ደብዳቤ ለመጻፍ ቃል ገብተው፣ ጠበቃ ተገኝቶ ወጣቶቹን ለማስፈታት የሚያስችል ርምጃ ከመጀመሩ አንድ ቀን በፊት በተፈጸመው ድርጊት ክፉኛ ማዘናቸውን የጠቆሙት ኦባንግ ሜቶ አሁንም እስር ላይ ያሉትን ለማስፈታት ጥረታቸውን እንደሚገፉበት ተናግረዋል። ከእንግዲህ ጉዳዩ የህወሃት ወይም በዋሽንግተን ዲሲ ያስቀመጠው ጽ/ቤቱ አይደለም፤ ጉዳዩ የራሳችን ነው የሚሉት “ጥቁሩ ሰው” ኦባንግ “ህወሃት የጉዞ ሰነድ እያዘጋጀ የራሱ ጽ/ቤት ባደረገው ኤምባሲው አማካኝነት እየሰጠ ስደተኞች ላይ የሚፈጽመው ይህ ተግባር የሚቆምበት ሁኔታ ከእንደራሴዎች ጋር በመነጋገር ተጽዕኖ የማድረግ ሥራ” ካሁኑ መጀመሩን ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡
ኦባንግ ስደተኛ ወገኖች ባሉበት ሁሉ ፈጥነው በመድረስና አለኝታ በመሆን የሚታወቁ ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ዜጎች የአደባባይ ምስክርነት በ“ቃላቸው” ብቻ የሚሰጧቸው ሰው መሆናቸው የሚዘነጋ አይደለም።

Thursday, March 10, 2016

Breaking: የኢቢሲ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ስርዓቱን ከድተው አሜሪካ ቀሩ

ዘ-ሐበሻ) በመንግስት 100% ቁጥጥር ሥር የሆነው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ምክትል ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ጨምቤሳ አሜሪካ ለሥራ መጥተው በዚሁ መቅረታቸው ታወቀ::
የዘ-ሐበሻ ምንጮች እንዳስታወቁት በአሁኑ ወቅት ሥርዓቱን በመክዳት በሁለት ዲጂት የሚቆጠሩ ባለስልጣናት እና ወታደሮች ወደ ተለያዩ ሃገራት በመኮብለል ላይ ይገኛሉ::
የኢቢሲ ምክትል ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ጨምቤሳ አሜሪካ ከመጡ በኋላ በአሁኑ ወቅት ሚኒሶታ በተሰኘችው ግዛት ውስጥ እንደሚገኙ ጨምሮ ለዘ-ሐበሻ 
የደረሰው መረጃ ያሳያል:


:Breaking News zehabesha

የኢትዮጵያ ጉዳይ ከመቼውም ጊዜ በባሰ ሁኔታ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ትከሻ ላይ ወድቋል። የችግሮቹ የመፍትሄ አካላት እነማን ናቸው? መፍትሄው ምን ይሁን?


militery
ስለ አገራችን ፖለቲካ ብዙ ብዙ ተብሏል።ሁሉም ከቆመበት ጥግ እየተነሳ ዕይታውን አካፍሏል።ከእዚህ ሁሉ ጋር ግን ያለንበት ጊዜ ምን ያክል አጣዳፊ እና ኢትዮጵያን የማዳን ሥራ የአንድ ግለሰብ ወይንም መሪ ወይንም የፖለቲካ ድርጅት ጉዳይ አለመሆኑን በምን ያህል ደረጃ ተገንዝበነዋል? የሚለው ጥያቄ ሁል ጊዜም ወሳኝ ነው።ይህ ጉዳይ የሚመለከተው በኢትዮጵያ ምድር ላይም ሆነ ውጭ ያለ ማንኛውንም ግለሰብ፣የፖለቲካ ድርጅት፣የጦር ኃይሉን እና የትኛውንም ማኅበረሰብን ነው።
ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት አጣብቂኝ ሁኔታ በስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ/ህወሓት ስልጣን መንገዳገድ እና መንገዳገዱን ተከትሎ የሚመጣው የፖለቲካ ትኩሳት ብቻ አይደለም።ወደድንም ጠላንም ኢትዮጵያን እንደ አገር እንዳትቀጥል ለዘመናት የዋተቱ ኃይሎች በከፍተኛ ከበባ ላይ ናቸው።ይህንን አላየንም አልሰማንም ብለን የምናልፈው ጉዳይ አይደለም።ይህንን ያክል የፖለቲካ ጅልነት የሚያጠቃው ኢትዮጵያዊም የለም።ችግሩ ግን እይታችን በየገባንበት ጎጥ እና ጉራጉር ጉዳይ ውስጥ ተከለለና አጠቃላይ የሆነውን የአገሪቱን ስዕል ማየት ተስኖናል።ይህ ፅሁፍ ባጭሩ ግን አሁን ያለብን ችግር እና መፍትሄዎቹ ምን መሆን ይገባቸዋል የሚለው መሰረታዊ ነጥብ ላይ ብቻ ያተኩራል።ፅሁፉ እይታም ነውና የአንድ ዜጋ ወይንም የሕዝብ ዕይታ አካልም አድርጎ መውሰድ ይቻላል።
አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት ችግር
ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ወቅታዊ ግን ፈታኝ ችግር በአራት ነጥቦች መለየት ይቻላል። እነርሱም:
1ኛ/ በከፍተኛ ደረጃ በከፋፋይ ሥራ የተጠመደ መንግስት መኖር

በውስጥ መንግስታዊ የጎጥ ፖለቲካ ሕዝቡን እና ማንኛውንም የኅብረተሰብ አካል በከፍተኛ ደረጃ በመከፋፈል ሥራ ተጠምዷል።ይህም ስልጣኔን ያስጠብቅልኛል ከሚል ስሌት ነው።በኦሮምያ እና በአማራ ክልል ያሉ ተቃውሞዎችን እንደ አደጋም እንደ በጎ አጋጣሚም ስርዓቱ ይመለከተዋል።
አደጋው ለስልጣኑ ሲሆን መልካም አጋጣሚው ከመቼውም ጊዜ በባሰ በተዘዋዋሪ ሳይሆን በቀጥታ በህወሓት ዕዝ ስር ክልሎችን በሙሉ ለማስገባት በማሰብ ነው።የኦሮምያ በስምንት የጦር ቀጠናዎች ስር መግባት የጋምቤላ አስተዳደር መፍረስ አሁን ደግሞ በአማራ ክልል የሚሰማው ሁሉ ይህንን ያገራግጣል።

2ኛ/ ለውጥ አለመኖሩ
የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀዳሚ ችግር በአሁኑ ጊዜ የለውጥ አለመኖር ነው።ባለፉት 24 ዓመታት ውስጥም ህወሓት ብዙ ጊዜ ሕዝቡን ሊያታልለው ሞክሯል።ስለሆነም በህወሓት ጥገናዊ ለውጥ ኢትዮጵያ ምንም አይነት መሻሻል እንደማታገኝ የሕዝቡ እምነት ነው።
ስርዓቱ የኢትዮጵያን ሕዝብ ገድሎታል፣አሰድዶታል፣ማንነቱን ተጋፍቷል፣አደህይቶታል፣ኑሮ አስወድዶበታል፣ሌላው ቀርቶ በከተሞች ውሃ እና መብራት መጥፋት አስመርሮት ከስርዓቱ መወገድ ጋር እንደሚፈታ የሚያምኑ ታዳጊ ሕፃናት ሁሉ ሆነዋል። ባጠቃላይ የስርዓቱ አለመቀየር የአገሪቱ ቀዳሚ ችግር ሆኖ ቀርቧል።

3ኛ/ ባዕዳን ኢትዮጵያን ከመቼውም ጊዜ የመከፋፈል አደጋ አለባት ብለው እየከበቧት ነው
ሱዳን በቀጥታ የደቡብ ሱዳን አጀንዳ ተወት አድርጋ የኢትዮጵያን ድንበር ለመውሰድ ከህወሓት ጋር ውል ጨርሳ ወደ ማካለሉ ላይ ነች።የመከላከያ ሚኒስትሩ ሲራጅ ፈርጌሳ ሱዳን ደርሰው የተመለሱት ትናንት ነው።የሱዳኑ ሱዳን ትሪቡን ጋዜጣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር ካርቱም የመጡት መሬት ለሱዳን ስለሚሰጥበት ጉዳይ ለመነጋገር መሆኑን በድንበር ማካለል በሚል ስም በመስጠት ዘግቧል።በሌላ በኩል የአረብ መንግስታ ሳውዲ እና ዩናይትድ አረብ ኢምረት የጦር ጀት መንደርደርያ እና የጦር ካምፖችን በአሰብ እና ጂቡቲ ላይ እየገነቡ ነው።አንዳንዶቹን ጨርሰው ሰራዊት እያሰፈሩ ነው።በቅርቡ ሳውዲ አረብያ ለሱዳን ለጦር መሳርያ መግዣ የሰጠችው የገንዘብ መጠን ከ2 ቢልዮን ዶላር በላይ መሆኑ ከተዘገበ ገና ወራት ማስቆጠሩ ነው።(አል-ሞንተርን ይመልከቱ)።
4ኛ/ ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ የድሕነት ችግር ውስጥ ገብተናል
አሁን የኢትዮጵያ ሕዝብ በልቶ ማደር ትልቅ ፈተና ሆኖበታል።በዓለም ላይ እጅግ ድሃ ከሚባሉት አገራት ተርታ ነን።የተባበሩት መንግሥታት የድህነት ወለል ብሎ ያስቀመጠው አንድ ሰው በቀን 1 ዶላር ከ25 ሳንቲም (በቅርቡ ከ25 ወደ 90 ሳንቲም ጨምሯል) አንፃር ስንታይ ገና ብዙ ይቀረናል።
በእዚህ ሂሳብ ስናሰላው በወር አንድ ሰው በወር ኢትዮጵያ ውስጥ በአማካይ 1600 ብር ማግኘት ማለት ነው።ይህ በአማካይ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የወር ገቢ ሆነ ማለት በእራሱ የድህነት ወለል ነው።እኛ ግን የዓለም ባንክ ካስቀመጠው የድህነት ወለል እጅግ በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ነን።

ይህ ሁኔታ ከሳሃራ በታች ካሉት የአፍሪካ አገራት ጋርም ሲወዳደር የኢትዮጵያ አብዛኛው ሕዝብ የኑሮ ሁኔታ አሁንም ብዙ ልዩነት እንዳለው ማየት እንችላለን።ይህ በእራሱ ትልቅ አደጋ አለው።የድህነት መስፋፋት የፀጥታ ችግር ያስከትላል።በሌላ በኩል ደግሞ ለነፃነቱ የሚነሳ የቆረጠ ሕዝብም ይበዛል የሚሉም አሉ።ምን ይህል ትክክለኛ መሆኑ ባይረጋገጥም።
ድህነት ሲበዛ መደማመጥ ይጠፋል፣የድህነቱ ምንጭ የማንነት ችግር ተደርጎ ይወሰድ እና ወደሌላ ምስቅልቅል ፖለቲካ ይመራል።በእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ ደግሞ በመንግሥትነት የተቀመጠው ስርዓት ይህንን ብሶት እንዲባባስ ከስልጣኑ መጠበቅያ መንገድ አንፃር ብቻ ስለሚጠቀምበት በእሳት ላይ ነዳጅ የማርከፍከፍ ያክል ችግሩ ይሰፋል።
በእኛ አገር ያለው የድህነት መብዛት ብቻ አይደለም።በሀብት የናጠጡ ጥቂቶች መኖርም የሀብት ክፍፍሉን ጎድቶታል።በጎጥ፣በሙስና እና በሕገ ወጥ መንገድ ሃብታም መሆን የተለመደ የዋልጌ ባለስልጣናት መለያ ሆኗል።
የችግሮቹ የመፍትሄ አካላት እነማን ናቸው? መፍትሄው ምን ይሁን?
የችግሮቹ የመፍትሄ አካላት እነማን ናቸው?
ከላይ በዋናነት የተጠቀሱት ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት ችግሮቹ እና አደጋዎቹ የሁሉም መሆናቸውን ማመን ሲቻል ነው።ይህ ማለት አደጋው አንድን ሕብረተሰብ በተለየ የሚያጠቃ ሳይሆን እንደ አገር የመኖር እና አለመኖር ሁኔታዎች ላይ ወሳኝ ሚና የሚጫወት ነው።በመሆኑም የመፍትሄ አካላት ሊሆኑ የሚችሉት የሚመረጡት እጅግ አግላይ በሆነ መንገድ ሊሆን አይችልም።በመሆኑም የመፍትሄ አካል መሆን የሚገባቸው የሚከተሉት ናቸው።
ሀ/ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ሰራዊት ውስጥ ገብተው የሚያገለግሉ የሰራዊቱ አባላት በእየደረጃቸው፣
ለ/ በአሁኑ ስርዓት ስር ሆነው ነገር ግን ሕዝብን እና አገርን ይቅርታ ለመጠየቅ የተዘጋጁ ባለስልጣናት፣የንግድ ሸሪኮች፣የማኅበረሰብ መሪዎች፣ምሁራን ወዘተ፣
ሐ/ ከሊቅ እስከ ደቂቅ (ከትንሽ እስከ ትልቅ) ያለ በየትኛውም የኢትዮጵያም ሆነ ከኢትዮጵያ ውጭ ባለ ቦታ የሚኖር ኢትዮጵያዊ፣
መ/ በኢትዮጵያ ጉዳይ የጋራ እሳቤ ያላቸው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ስብስቦች በሙሉ ናቸው።

መፍትሄው ምን ይሁን?
ከላይ አሁንም ባጭሩ እንደተቀመጠው ችግሩ ሁሉንም የሚመለከት መፍትሄውም እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ የሚመለከት ነው።እዚህ ላይ የችግሩ መፍተሄ አካል አሁን ያለውን ስርዓት ሙሉ በሙሉ ማድረግ (እራሳቸውን ከህዝብ ወገን ያደረጉ በይቅርታ ወደ ሕዝብ የሚመለሱትን ሳይጨምር) በእራሱ ችግሩን የበለጠ የምያወሳስበው ነው።
ይህ የጨለመ ወይንም ተስፋ ያጣ አስተሳሰብ ውጤት አይደለም።ባለፉት 24 ዓመታት ተሞክሮ ስንመለከት ህወሓት የመጀመርያ እና ቀዳሚ ተግባሩ በማናቸውም ወጪ እና የአገር ክስረት ቢሆን ስልጣኑን ማስጠበቅን የመጀመርያ ስራው እንጂ የአገር ጉዳይ ቀዳሚ ጉዳዩ ሆኖ አልታየም።ባህሪው አነሳሱ እና ሂደቱ ሁሉ ያሳየው ይህንኑ ነው።በመሆኑም የስርዓቱን አቀንቃኞች ትቶ ለኢትዮጵያ የሚቆመው እና የማይቆመው በቁርጥ መለየት ተገቢ ነው።ይህንን ከግንዛቤ አስገብተን መፍትሄው ሊሆን የሚችለው አንድ ብቻ ይመስለኛል። ይሄውም ለውጥ እና ለውጥ ብቻ ነው።
አንዳንዶች ለውጥ በእራሱ ይዞት የሚመጣው ምስቅልቅል ሁኔታ ስለሚኖር ወደባሰ ችግር ላይ አገሪቱ ትገባለች ብለው የሚያስቡ አሉ።በእርግጥ ለውጥ ሁሉ ካለምንም መንገጫገጭ አይመጣም።ቁምነገሩ ግን ተንገጫግጮ ቦታው ይገባል የሚለው እሳቤ ነው።አሁን ባለው ሁኔታ መፍትሄ ሲታሰብ ያሉት ሁለት አማራጮች ናቸው።እነኝህን አማራጮች ስናወዳድር ለውጥ መምጣቱ የበለጠ አማራጭ ብቻ መሆኑን እንረዳለን።
አንድኛው፣ ምርጫ ህወሓት በስልጣን ላይ የመቆየቱ አማራጭ ሲሆን ሁለተኛው፣ህወሓት በአዲስ ስርዓት የመለውጥ ሂደት ነው።
ህወሓት በስልጣን ላይ የመቆየቱ አማራጭ
የመጀመርያው አማራጭ ስናየው ለጊዜው ኢትዮጵያ ያለች ይመስለናል እንጂ ”ዱር አልባው ሽፍተኝነት” ያጠቃው የኢትዮጵያ ሕዝብ በምንም አይነት አገርን የማዳን ሥራ ላይ ከህወሓት ጋር አይሰለፍም።ለእዚህ ብዙ ምክንያቶች ስላሉ መዘርዘሩ አያስፈልግም።ከእዚህ ይልቅ ህወሓት በስልጣን በቆየ ቁጥር ሕዝብ የችግሩ እና የድህነቱ ምክንያት ከማንነት ጉዳይ ጋር እየያዘው ይሄድና በመጨረሻ አገሪቱ ወደ እርስ በርስ ጦርነት የመግባት አዝማምያ ያሰጋታል።
ሁሉም ለእርስ በርስ ግጭቱ የሚሰጠው ምክንያት ደግሞ ወያኔን ለማውረድ ነው ስለሚል ጉዳዩ በተለያዩ የባዕዳን እጅ የመግባት አደጋው ይሰፋል።በመጨረሻ ወያኔ እራሱ የጎጥ ፖለቲካውን ያጦዘውና (የትግራይ ሕዝብ ምን ያክል ይተባበረዋል የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ) ትግራይን ለመነጠል ሙከራ ያደርጋል።ይህ እንግዲህ የአገሪቱ ሀብት በሙሰኛ ባለስልጣናት እና ባዕዳን የመዘረፍ ጉዳይ ሁሉ እንደቀጠለ ማለት ነው።በመጨረሻ ኢትዮጵያን የከበቡት ኃይላት በማናቸውም ጊዜ አገሪቱን በቀላሉ ከፋፍለው የማዳከም አመቺ ጊዜ እንዳገኙ ያስባሉ። ህወሓት በስልጣን ላይ መቆየት ከቻለ መጪው ጊዜ ከእዚህ ያነሰ አይሆንም።ስርዓቱ የገባበት ቅራኔ በሙሉ ሳይፈታ እና የቅራኔው መነሻ ከስልጣን ሳይወርድ የኢትዮጵያን ህልውና ማስጠበቅ ፈፅሞ አይታሰብም።ሕዝብ እንጂ ግለሰቦች አገር አያድኑም።የኢትዮጵያ ሕዝብ አገሩን በባለቤትነት እንዲያድን ይህ ስርዓት ከስልጣን መውረድ አለበት።ከእዛ መለስ ግን ህወሓት ብሔራዊ ሕብረት የሚያመጣበትም ሆነ ስልጣኑን ሕጋዊ መሰረት ለማስያዝ ምንም የቀረው ጥይት የለም።በሕዝብ ዘንድ የመንግስት ሕጋዊነት (legitimacy) በእዚህ ያህል ደረጃ ከወረደ በኃላ ለመጠገን መሞከር ትርፉ የሚፎረፎተው ፍርስራሽ አይን ውስጥ እየገባ አይን እንዲያጠፋ ከማድረግ በቀር ምንም ትርፍ የለውም።ይህንን ከስርዓቱ ጋር እየሰሩ ያሉ በሙሉ ሊረዱት የሚገባ ሀቅ ነው።
ባጭሩ የህወሓት በስልጣን ላይ መቆየት በአማራጭነት የማይቀርብ ይልቁንም ኢትዮጵያ በዘመኗ አይታ ወደማታውቀው የእርስ በርስ ግጭት የሚመራት መሆኑ መታወቅ አለበት።ይህ ሁኔታ ደግሞ እንደ አገር ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ የማትችል ወደ ማድረግ የሚመራት አሁንም በስልጣን ላይ ያለው ቡድን የታቀደ የመከፋፈል እና የማጋጨት ሥራ ነው።
ለውጥ
ሁለተኛው እና እንደ እኔ ብቸኛው አማራጭ የምለው በኢትዮጵያ አፋጣኝ ግን የሁሉም ህብረት የታየበት ለውጥ ማምጣት ነው።ለውጥ ጊዝያዊ የኃይል ክፍተት፣የህዝብ አለመረጋጋት፣ የአካባቢ እና ዓለም አቀፍ መድረኮች የመደመጥ አቅም መቀነስ ወዘተ ያጋጥሙታል።ለእዚህም ነው ከላይ የመፍትሄ አካላት መሆን የሚገባቸው ተብሎ የኢትዮጵያ ጦር ኃይል እና ሕዝብ ይቅርታ የጠየቁ የስርዓቱ አካላት የለውጡ አካል እና ኢትዮትጵያን የማዳን ድርሻ አላቸው የተባለው።ስለዚህ የኃይል ክፍተት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሥራ ብቻ ሳይሆን የጦር ኃይሉም ተግባር ነው።
ሰራዊቱ ከየትም የመጣ ሳይሆን አሁንም ከኢትዮጵያ ሕዝብ የወጣ እና በየቦታው የሚነሱ ግጭቶች ሰለባ ስለሆነ ችግሩ የአገሪቱ ችግር የሚመነጨው ከመሪዎቹ እንደሆነ ይገነዘባል።ለውጥ መምጣቱ የአገራችን ችግር በጋራ መነጋገር ይስችላል፣ከልዩነታችን ይልቅ ሕብረታችንን የሚያሳዩን የመገናኛ ብዙሃን ይኖሩናል፣ ከሁለት ሚልዮን በላይ የሚገመተው በውጭ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ለአገሩ የጋራ ጉዳይ የመስራት ዕድል ይኖረዋል፣የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት በበለጠ ይነቃቃል፣ በኢትዮጵያ ላይ ከባዕዳን ጋር በማበር የሚያሴሩት በግልፅ ለሕዝብ ይጋለጣሉ፣ ሕዝብ በእራሱ የመለያየት ፖለቲካ አራማጆችን ከአገራዊ ፖለቲካ አራማጆች የመለየት ዕድል ስለሚያገኝ የመወሰን አቅሙን ያሳያል።
ይህ ሁሉ ሁኔታ ህወሓት በስልጣን ላይ ሆኖ ህዝቡ በመታፈኑ ሳብያ የሚመጣው አደጋ ጋር ሲነፃፀር ለውጥ የሚያመጣው አንድነት እና ህብረት የበለጠ የአገሪቱን አንድነት የማምጣት አቅም ይኖረዋል። እዚህ ላይ ብዙዎች በሌላ አገር ያሉ ተሞክሮዎችን በማንሳት ከአምባገነን መሪዎች በኃላ መከፋፈል እንደሚኖር ሊሰብኩ ይሞክራሉ።ይህ ግን እንደ ኢትዮጵያ ላለ የእረጅም ጊዜ ማኅበራዊ መስተሳስር ላለው ሕዝብ አይሰራም።እርግጥ ነው ይህ ማለት ማኅበራዊ መስተሳሰር በእራሱ ተአምር አይፈጥርም። ትውልድም ተቀይሯል።ስለሆነም የምሁራን አስተዋፅኦ በጣም ይፈለጋል።በዝምታ የእራስን ኑሮ እየኖሩ ከንፈር መምጠጥ በእራሱ ኢትዮጵያን ከመግደል አይተናነስም።
ባጠቃላይ ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ እንደ ውሃ ጠብታ ቀስ እያለ እየሸረሸራት ነው። ችላ ብሎ ወይንም ዝም ብሎ የሚኖረው ሕዝብ እጣው እና ህይወቱ ከአገሩ ጋር መያያዙን ማመን አለበት።በተለይ ምሑራን ቢያንስ ለአገራቸው እና ለሕዝባቸው አዳዲስ ሃሳቦች ከማፍለቅ አንስቶ የኑሮ መደላድላቸውን ብቻ እየተመለከቱ ከመኖር ባለፈ ለኢትዮጵያ ምን ላድርግ ማለት አለባቸው።ምንም እንዳልተፈጠረ ዝም ማለት በእራሱ በገዛ አገር ላይ የሚፈፀም የፀጥታ አሰቃቂ ወንጀል ነው።ኢትዮጵያ ከሌላ አገር ትለያለች።አምባገነኖች መጥተዋል፣አምባገነኖች ሄደዋል። ኢትዮጵያ ግን በሕዝቧ አስተዋይነት እና በእግዚአብሔር መሪነት ከብዙ ፈተና ድናለች።ወደፊትም ትድናለች። ለአገር ብዙ ሃሳብ እና አቅም ያላችሁ ግን ከእየተደበቃችሁበት የምትወጡበት ጊዜ አሁን ነው። የኢትዮጵያ ጉዳይ ከመቼውም ጊዜ በባሰ ሁኔታ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ትከሻ ላይ ወድቋል።እያንዳንዷ ቀን ለኢትዮጵያ ወሳኝ ነችና።

የዓለማችን 10ሩ ተልካሻ ፓስፖርቶች | የኢትዮጵያ 7ኛው ሆኗል


passports
የጀርመን ፓስፖርት የያዙ ሰዎች አለምን የጓዳቸው ያህል ሊመለከቷት ይችላሉ፡፡እጁ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ፓስፖርት ከሆነ ግን እንደጀርመኖቹ ነገ ስፔን ሄጄ የባርሴሎናን ኳስ ወይም ደቡብ አፍሪካ ወረድ ብዬ የጥቁሮቹን ቀዬ ፕሪቶሪያን ጎብኝቼ ልመለስ አይሉም፡፡የብዙ ኢትዮጵያዊያንም የተለያዩ አገራትን የማየት ህልምም እጃቸው ላይ የሚገኘው ፓስፖርት እርባና ቢስ በመሆኑ ተኮላሽቶ ቀርቷል፡፡
ዛሬ ረቡዕ አመታዊው የአገራት የፓስፖርቶች ደረጃ ይፋ ሲደረግም የእኛው ፓስፖርት ከአለማችን አስር እርባና ቢስ ፓስፖርቶች ተርታ ተሰልፏል፡፡ፓስፖርቶቹ እርባና ቢስ የሚሰኙት በነጻ ያለ ቪዛ ጣጣ ወደተለያዩ የአለማችን ክፍሎች የመውሰድ አቅማቸው እየተመዘነ ነው፡፡የቪዛ ሪስትሪክሽን ኢንዴክስ ባወጣው ሪፖርትም ኢትዮጵያዊያን ከእርባና ቢሱ ፓስፖርታቸው የተነሳ የሚያቀርቧቸው የቪዛ ጥያቄዎች በአብዛኛው ተቀባይነት አያገኙም በማለት ወርፉብናል፡፡
እንደ ኢንዴክሱ ከሆነም በአለማችን ያለቪዛ በዛ ወዳሉ አገራት ይገቡና ይወጡ ዘንድ ፓስፖርታቸውን ባሳዩ ቁጥር አረንጓዴ የሚበራላቸው አውሮፓውያን ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምርጥ አስር እረባና ቢስ ፓስፖርት ያላቸው አገራት አፍጋኒስታን፣ኢራቅ፣ሶሪያ፣ኤርትራ፣የመንና ሶማሊያን የመሳሰሉ አገራት ናቸው፡፡
ሄንሌይ እና ፓርትነርስ የተባሉ በህግ ባለሞያዎች የተቋቋሙ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ካለፉት 11 ዓመታት ጀምሮ የአለማችንን አገራት የፓስፖርት ደረጃዎች ሲያወጡ ቆይተዋል፡፡በዘንድሮው ዓመት የ104 አገራትን የፓስፖርት ደረጃ ሲያወጡም ኢትዮጵያን በ97 ደረጃ ላይ ከኤርትራ ጋር ዕኩል ነጥብ ሰጥተው አስቀምጠዋታል፡፡

የቪዛ ጉዳይ አገራት በሚኖራቸው ግኑኝነት ፣የጸጥታ ጉዳይ፣መሟላት ከሚገባቸው የቪዛ ፎርማሊቲዎች አንጻር ሊቀሉ ወይም ሊከብዱ እንደሚችሉ የሚናገሩት ድርጅቶቹ ከ218 አገራት የጀርመንን ፓስፖርት የያዙ ሰዎች በ177ቱ ያለምንም የቪዛ ጣጣ ጉዟቸውን ማድረግ እንደሚችሉ በማተት ኢትዮጵያዊያን ግን ወደ 37 አገራት ብቻ መሄድ ይችላሉ ብሏል፡

በእኛ ዝምታ እነሱ ጀገኑ!!



ምን ብዬት መጀመር ግራ አገባኝ……. የቱን አንስቼ የቱን ልተው…… ምንስ ብፅፍ የውስጤን ቁጭት ይገልፀዋል……!! በህዝባችን ላይ እለት ተዕለት  እየተፈፀመ ያለውን ግፍና ሰቆቃ እየሰማንና እያየን እስከመቼ…..በዝምታ እንኖራለን ግፉ ፅዋ ሞልቶ ፈሷል። ዜጎች በራሳቸው ሀገር፣ በራሳቸው መንደር፣ በራሳቸው ማንነት እንዳይኖሩ የሚደረግበት ሀገር ኢትዮጵያ!

Kalkidan

ትናንት በኦሮሞና በጋምቤላው ወገናችን ላየ በደረሰው ኢሰብዓዊ ድርጊት ምን ያህልን ውስጣችን ስንቃጠል እንደከረምን ከሁላችን የማንረሳው ነው። ይባስ ዛሬ ደግሞ የገደሉትን ገለው፣ያሰሩትን አስረው ፣ይህ አለበቃ ሲላቸው የሰው ልጅ ከሰው ጋር አስሮ ማሰቃየት ላይ ደርሰዋል። ይህን እኩይ ተግባር ማየቱንም ሆን መስማቱ እንዴት እንዴት ያማል…..!! “በእኛ ዝምታ እነሱ ጀገኑ!!”
ስማኝ ልንገርህ ወገኔ ዛሬ ሱርማ ወገናች ላይ የተፈፀመው እኩይ ተግባር ነገ በእኔና በአንተ የገዛ ቤታችን ውስጥ መተው እንደሚያድርጉት አትጠራጠር። 21 ክፍለ ዘመን ላይ እየኖረን ኑሮቻች እና ስቃያችን 18 ክፍለ ዘመን ሆኖል። ይህን ግፍና ሰቆቆ እስከመቼ በዝምታ እንደምንገልፀው!!
ጥቂቶች መብታቸውን ተከብሮ ነገር ግን ብዙሃኑ መብቱን እና ነፃነቱን ተነፍጎ የሚኖርባት ሀገር ኢትዮጵያ እየሆን ያለው በህዝባችን ላይ በእውነቱ ዝም የሚያስብል አይደለም። አሁን አሁንማ መብት ሲጠየቅ ምላሹ በመሳሪያ ሆኖል።  “በእኛ ዝምታ እነሱ ጀገኑ!!”
ይህን ግፍና መከራ እየሰማን፣ እየተመለከትን ስለምን ዝም አልን፣ ስለምን ዝምታን መረጥን፣ ስለምን በህዝባችን ላይ የሚደርሰውን ስቃይና መከራ ለማውገዝ አቅም አጣን፣ ስለምን የወገናችንን ሞት ሞታችን ማድረግ አቃተን፣ ስለምን መንገድ ዳር ስለሚገድሉብን ልጆች፣ እናቶች፣ ወጣቶች እንዲሁም አዛውንቶች እየሰማንና እያየን ዝምታን መረጥን!!
የእኛን ዝምታ እነሱን ካጀገነ ችግሩ እነሱ ጋር ሳይሆን እኛው ጋር ነው። ስለዚህ ስማኝ ልንገርህ ወገኔ ህወሓትን ከስልጣን ለማወረድ የእኛ ዝምታችን ሰባብረን በአንድነት ስንጮህ ነው። ተደራጅ፣ ተሰባሰብ፣ ተወያይ………..”የሀገር ጉዳይ ነውና” እንክፈል ጊዜችን፣ እንክፈል ገንዘባችን፣ እንክፈል ህይወታችን………ነፃነት ዋጋ ታስከፍላለችና ያለ መሰዋትነት ድል የለምና መከፈል ላለበት መክፈል አለበት……… “ኢትዮጵያ ደምና አጥንት የተከፈለባት ሀገር ናት” አሁንም ልንከፍል ግድ ነው!! “በእኛ ዝምታ እነሱ ጀገኑ!!”
በህዝቡ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ የተቀጣጠለውን ህዝባዊ እንቢተኝነት ሁሉም ኢትዮጵያዊ በህዝባዊ እንቢተኝነቱን እንዲሳተፍ የየበኩላችን ጥረት እናድርግ ኢትዮጵያና ህዝቦቾን ከዚህ ፋሽስት ስርዓት እንታደግ!!
“ህወሓት እስካለ ተቃውሞ አለ”
ኢትዮጵያ ለዘላለም በክብር ትኑር!!
ድል ለጭቁኑ ህዝብ!!

ቃልኪዳን ካሳሁን   (ከኖርዌ

Monday, February 29, 2016

በአዲስ አበባ የታክሲዎችን የስራ ማቆም አድማ ተከትሎ የትራንስፖርት ችግር ተከሰቷል



በአዲስ አበባ የሚገኙ የታክሲ ሹፌሮች የወያኔ አገዛዝ ያወጣውን የትራንስፖርት እና መንጃ ፍቃድ ሕግ በመቃወም የጠሩት የስራ ማቆም አድማ በዛሬው እለት የአዲስ አበባን መንገዶች ከትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ውጪ በማድረጋቸው ተገልጋዩ በትራትስፖርት ችግር ሲገጥመው ተስተውሏል::
የአዲስ አበባን የታክሲ ሹፌሮች ከስራ ውጪ ለማድረግ እና ስራ ፈት ዜጎችን ለመፍጠር ታስቦ በወያኔ የወጣው አዲስ ሕግ ማንኛውም ሹፌር 21 ጊዜ ጥፋት ካለበት መንጃ ፈቃዱ ተነጥቆ ከሹፌርነት ለመጨረሻ ጊዜ የሚያግድ ሲሆን የታክሲ ሹፌሮችን ሆን ብሎ በማጥቃት ከስራ ውጪ በማድረግ የደህንነት አካላት የሆኑ አዳዲስ እየሰለጠኑ የሚገኙ የሕወሓት አባላትን የታክሲ ባለቤቶች ላይ ጫና በመፍጠር በሹፌርነት ለማሰማራት የታቀደ እንደሆነ ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ::

የወያኔው አገዛዝ በተለያዩ በዝባዥ እና ሕዝብን በሚበድሉ ሕጎች ኢትዮጵያውያንን እያሰቃየ ሲሆን ይህም ከፍተኛ የሆነ ብሶት አደባባይ ላይ መሰማቱ ሲቀጥል የስራ ማቆም አድማውም የዚሁ ብሶት አካል መሆኑ ታውቋል::በአዲስ አበባ የትራንስፖርት ተገልጋዮች በተለያዩ መንገዶች ትራንስፖርት ለማግኘት ቢሞክሩም እንዳልቻሉ ታይተዋል::የወያኔ አገዛዝ ለሶስት ወር አራዘምኩት ይሕጉን ተግባራዊነት የሚል መግለጫ ቢሰጥም ተቀባይነት አጥቶ የስራ ማቆም አድማው ተደርጓል::ሕዝቡ ብሶቱን በተለያየ መንገድ በመግለጽ ስርኣቱ እንዲወገድ ትግሉን ቀጥሏል::‪