ስለ አገራችን ፖለቲካ ብዙ ብዙ ተብሏል።ሁሉም ከቆመበት ጥግ እየተነሳ ዕይታውን አካፍሏል።ከእዚህ ሁሉ ጋር ግን ያለንበት ጊዜ ምን ያክል አጣዳፊ እና ኢትዮጵያን የማዳን ሥራ የአንድ ግለሰብ ወይንም መሪ ወይንም የፖለቲካ ድርጅት ጉዳይ አለመሆኑን በምን ያህል ደረጃ ተገንዝበነዋል? የሚለው ጥያቄ ሁል ጊዜም ወሳኝ ነው።ይህ ጉዳይ የሚመለከተው በኢትዮጵያ ምድር ላይም ሆነ ውጭ ያለ ማንኛውንም ግለሰብ፣የፖለቲካ ድርጅት፣የጦር ኃይሉን እና የትኛውንም ማኅበረሰብን ነው።
ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት አጣብቂኝ ሁኔታ በስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ/ህወሓት ስልጣን መንገዳገድ እና መንገዳገዱን ተከትሎ የሚመጣው የፖለቲካ ትኩሳት ብቻ አይደለም።ወደድንም ጠላንም ኢትዮጵያን እንደ አገር እንዳትቀጥል ለዘመናት የዋተቱ ኃይሎች በከፍተኛ ከበባ ላይ ናቸው።ይህንን አላየንም አልሰማንም ብለን የምናልፈው ጉዳይ አይደለም።ይህንን ያክል የፖለቲካ ጅልነት የሚያጠቃው ኢትዮጵያዊም የለም።ችግሩ ግን እይታችን በየገባንበት ጎጥ እና ጉራጉር ጉዳይ ውስጥ ተከለለና አጠቃላይ የሆነውን የአገሪቱን ስዕል ማየት ተስኖናል።ይህ ፅሁፍ ባጭሩ ግን አሁን ያለብን ችግር እና መፍትሄዎቹ ምን መሆን ይገባቸዋል የሚለው መሰረታዊ ነጥብ ላይ ብቻ ያተኩራል።ፅሁፉ እይታም ነውና የአንድ ዜጋ ወይንም የሕዝብ ዕይታ አካልም አድርጎ መውሰድ ይቻላል።
አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት ችግር
ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ወቅታዊ ግን ፈታኝ ችግር በአራት ነጥቦች መለየት ይቻላል። እነርሱም:
1ኛ/ በከፍተኛ ደረጃ በከፋፋይ ሥራ የተጠመደ መንግስት መኖር
በውስጥ መንግስታዊ የጎጥ ፖለቲካ ሕዝቡን እና ማንኛውንም የኅብረተሰብ አካል በከፍተኛ ደረጃ በመከፋፈል ሥራ ተጠምዷል።ይህም ስልጣኔን ያስጠብቅልኛል ከሚል ስሌት ነው።በኦሮምያ እና በአማራ ክልል ያሉ ተቃውሞዎችን እንደ አደጋም እንደ በጎ አጋጣሚም ስርዓቱ ይመለከተዋል።
አደጋው ለስልጣኑ ሲሆን መልካም አጋጣሚው ከመቼውም ጊዜ በባሰ በተዘዋዋሪ ሳይሆን በቀጥታ በህወሓት ዕዝ ስር ክልሎችን በሙሉ ለማስገባት በማሰብ ነው።የኦሮምያ በስምንት የጦር ቀጠናዎች ስር መግባት የጋምቤላ አስተዳደር መፍረስ አሁን ደግሞ በአማራ ክልል የሚሰማው ሁሉ ይህንን ያገራግጣል።
2ኛ/ ለውጥ አለመኖሩ
የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀዳሚ ችግር በአሁኑ ጊዜ የለውጥ አለመኖር ነው።ባለፉት 24 ዓመታት ውስጥም ህወሓት ብዙ ጊዜ ሕዝቡን ሊያታልለው ሞክሯል።ስለሆነም በህወሓት ጥገናዊ ለውጥ ኢትዮጵያ ምንም አይነት መሻሻል እንደማታገኝ የሕዝቡ እምነት ነው።
ስርዓቱ የኢትዮጵያን ሕዝብ ገድሎታል፣አሰድዶታል፣ማንነቱን ተጋፍቷል፣አደህይቶታል፣ኑሮ አስወድዶበታል፣ሌላው ቀርቶ በከተሞች ውሃ እና መብራት መጥፋት አስመርሮት ከስርዓቱ መወገድ ጋር እንደሚፈታ የሚያምኑ ታዳጊ ሕፃናት ሁሉ ሆነዋል። ባጠቃላይ የስርዓቱ አለመቀየር የአገሪቱ ቀዳሚ ችግር ሆኖ ቀርቧል።
3ኛ/ ባዕዳን ኢትዮጵያን ከመቼውም ጊዜ የመከፋፈል አደጋ አለባት ብለው እየከበቧት ነው
ሱዳን በቀጥታ የደቡብ ሱዳን አጀንዳ ተወት አድርጋ የኢትዮጵያን ድንበር ለመውሰድ ከህወሓት ጋር ውል ጨርሳ ወደ ማካለሉ ላይ ነች።የመከላከያ ሚኒስትሩ ሲራጅ ፈርጌሳ ሱዳን ደርሰው የተመለሱት ትናንት ነው።የሱዳኑ ሱዳን ትሪቡን ጋዜጣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር ካርቱም የመጡት መሬት ለሱዳን ስለሚሰጥበት ጉዳይ ለመነጋገር መሆኑን በድንበር ማካለል በሚል ስም በመስጠት ዘግቧል።በሌላ በኩል የአረብ መንግስታ ሳውዲ እና ዩናይትድ አረብ ኢምረት የጦር ጀት መንደርደርያ እና የጦር ካምፖችን በአሰብ እና ጂቡቲ ላይ እየገነቡ ነው።አንዳንዶቹን ጨርሰው ሰራዊት እያሰፈሩ ነው።በቅርቡ ሳውዲ አረብያ ለሱዳን ለጦር መሳርያ መግዣ የሰጠችው የገንዘብ መጠን ከ2 ቢልዮን ዶላር በላይ መሆኑ ከተዘገበ ገና ወራት ማስቆጠሩ ነው።(አል-ሞንተርን ይመልከቱ)።
4ኛ/ ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ የድሕነት ችግር ውስጥ ገብተናል
አሁን የኢትዮጵያ ሕዝብ በልቶ ማደር ትልቅ ፈተና ሆኖበታል።በዓለም ላይ እጅግ ድሃ ከሚባሉት አገራት ተርታ ነን።የተባበሩት መንግሥታት የድህነት ወለል ብሎ ያስቀመጠው አንድ ሰው በቀን 1 ዶላር ከ25 ሳንቲም (በቅርቡ ከ25 ወደ 90 ሳንቲም ጨምሯል) አንፃር ስንታይ ገና ብዙ ይቀረናል።
በእዚህ ሂሳብ ስናሰላው በወር አንድ ሰው በወር ኢትዮጵያ ውስጥ በአማካይ 1600 ብር ማግኘት ማለት ነው።ይህ በአማካይ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የወር ገቢ ሆነ ማለት በእራሱ የድህነት ወለል ነው።እኛ ግን የዓለም ባንክ ካስቀመጠው የድህነት ወለል እጅግ በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ነን።
ይህ ሁኔታ ከሳሃራ በታች ካሉት የአፍሪካ አገራት ጋርም ሲወዳደር የኢትዮጵያ አብዛኛው ሕዝብ የኑሮ ሁኔታ አሁንም ብዙ ልዩነት እንዳለው ማየት እንችላለን።ይህ በእራሱ ትልቅ አደጋ አለው።የድህነት መስፋፋት የፀጥታ ችግር ያስከትላል።በሌላ በኩል ደግሞ ለነፃነቱ የሚነሳ የቆረጠ ሕዝብም ይበዛል የሚሉም አሉ።ምን ይህል ትክክለኛ መሆኑ ባይረጋገጥም።
ድህነት ሲበዛ መደማመጥ ይጠፋል፣የድህነቱ ምንጭ የማንነት ችግር ተደርጎ ይወሰድ እና ወደሌላ ምስቅልቅል ፖለቲካ ይመራል።በእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ ደግሞ በመንግሥትነት የተቀመጠው ስርዓት ይህንን ብሶት እንዲባባስ ከስልጣኑ መጠበቅያ መንገድ አንፃር ብቻ ስለሚጠቀምበት በእሳት ላይ ነዳጅ የማርከፍከፍ ያክል ችግሩ ይሰፋል።
በእኛ አገር ያለው የድህነት መብዛት ብቻ አይደለም።በሀብት የናጠጡ ጥቂቶች መኖርም የሀብት ክፍፍሉን ጎድቶታል።በጎጥ፣በሙስና እና በሕገ ወጥ መንገድ ሃብታም መሆን የተለመደ የዋልጌ ባለስልጣናት መለያ ሆኗል።
የችግሮቹ የመፍትሄ አካላት እነማን ናቸው? መፍትሄው ምን ይሁን?
የችግሮቹ የመፍትሄ አካላት እነማን ናቸው?
ከላይ በዋናነት የተጠቀሱት ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት ችግሮቹ እና አደጋዎቹ የሁሉም መሆናቸውን ማመን ሲቻል ነው።ይህ ማለት አደጋው አንድን ሕብረተሰብ በተለየ የሚያጠቃ ሳይሆን እንደ አገር የመኖር እና አለመኖር ሁኔታዎች ላይ ወሳኝ ሚና የሚጫወት ነው።በመሆኑም የመፍትሄ አካላት ሊሆኑ የሚችሉት የሚመረጡት እጅግ አግላይ በሆነ መንገድ ሊሆን አይችልም።በመሆኑም የመፍትሄ አካል መሆን የሚገባቸው የሚከተሉት ናቸው።
ሀ/ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ሰራዊት ውስጥ ገብተው የሚያገለግሉ የሰራዊቱ አባላት በእየደረጃቸው፣
ለ/ በአሁኑ ስርዓት ስር ሆነው ነገር ግን ሕዝብን እና አገርን ይቅርታ ለመጠየቅ የተዘጋጁ ባለስልጣናት፣የንግድ ሸሪኮች፣የማኅበረሰብ መሪዎች፣ምሁራን ወዘተ፣
ሐ/ ከሊቅ እስከ ደቂቅ (ከትንሽ እስከ ትልቅ) ያለ በየትኛውም የኢትዮጵያም ሆነ ከኢትዮጵያ ውጭ ባለ ቦታ የሚኖር ኢትዮጵያዊ፣
መ/ በኢትዮጵያ ጉዳይ የጋራ እሳቤ ያላቸው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ስብስቦች በሙሉ ናቸው።
መፍትሄው ምን ይሁን?
ከላይ አሁንም ባጭሩ እንደተቀመጠው ችግሩ ሁሉንም የሚመለከት መፍትሄውም እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ የሚመለከት ነው።እዚህ ላይ የችግሩ መፍተሄ አካል አሁን ያለውን ስርዓት ሙሉ በሙሉ ማድረግ (እራሳቸውን ከህዝብ ወገን ያደረጉ በይቅርታ ወደ ሕዝብ የሚመለሱትን ሳይጨምር) በእራሱ ችግሩን የበለጠ የምያወሳስበው ነው።
ይህ የጨለመ ወይንም ተስፋ ያጣ አስተሳሰብ ውጤት አይደለም።ባለፉት 24 ዓመታት ተሞክሮ ስንመለከት ህወሓት የመጀመርያ እና ቀዳሚ ተግባሩ በማናቸውም ወጪ እና የአገር ክስረት ቢሆን ስልጣኑን ማስጠበቅን የመጀመርያ ስራው እንጂ የአገር ጉዳይ ቀዳሚ ጉዳዩ ሆኖ አልታየም።ባህሪው አነሳሱ እና ሂደቱ ሁሉ ያሳየው ይህንኑ ነው።በመሆኑም የስርዓቱን አቀንቃኞች ትቶ ለኢትዮጵያ የሚቆመው እና የማይቆመው በቁርጥ መለየት ተገቢ ነው።ይህንን ከግንዛቤ አስገብተን መፍትሄው ሊሆን የሚችለው አንድ ብቻ ይመስለኛል። ይሄውም ለውጥ እና ለውጥ ብቻ ነው።
አንዳንዶች ለውጥ በእራሱ ይዞት የሚመጣው ምስቅልቅል ሁኔታ ስለሚኖር ወደባሰ ችግር ላይ አገሪቱ ትገባለች ብለው የሚያስቡ አሉ።በእርግጥ ለውጥ ሁሉ ካለምንም መንገጫገጭ አይመጣም።ቁምነገሩ ግን ተንገጫግጮ ቦታው ይገባል የሚለው እሳቤ ነው።አሁን ባለው ሁኔታ መፍትሄ ሲታሰብ ያሉት ሁለት አማራጮች ናቸው።እነኝህን አማራጮች ስናወዳድር ለውጥ መምጣቱ የበለጠ አማራጭ ብቻ መሆኑን እንረዳለን።
አንድኛው፣ ምርጫ ህወሓት በስልጣን ላይ የመቆየቱ አማራጭ ሲሆን ሁለተኛው፣ህወሓት በአዲስ ስርዓት የመለውጥ ሂደት ነው።
ህወሓት በስልጣን ላይ የመቆየቱ አማራጭ
የመጀመርያው አማራጭ ስናየው ለጊዜው ኢትዮጵያ ያለች ይመስለናል እንጂ ”ዱር አልባው ሽፍተኝነት” ያጠቃው የኢትዮጵያ ሕዝብ በምንም አይነት አገርን የማዳን ሥራ ላይ ከህወሓት ጋር አይሰለፍም።ለእዚህ ብዙ ምክንያቶች ስላሉ መዘርዘሩ አያስፈልግም።ከእዚህ ይልቅ ህወሓት በስልጣን በቆየ ቁጥር ሕዝብ የችግሩ እና የድህነቱ ምክንያት ከማንነት ጉዳይ ጋር እየያዘው ይሄድና በመጨረሻ አገሪቱ ወደ እርስ በርስ ጦርነት የመግባት አዝማምያ ያሰጋታል።
ሁሉም ለእርስ በርስ ግጭቱ የሚሰጠው ምክንያት ደግሞ ወያኔን ለማውረድ ነው ስለሚል ጉዳዩ በተለያዩ የባዕዳን እጅ የመግባት አደጋው ይሰፋል።በመጨረሻ ወያኔ እራሱ የጎጥ ፖለቲካውን ያጦዘውና (የትግራይ ሕዝብ ምን ያክል ይተባበረዋል የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ) ትግራይን ለመነጠል ሙከራ ያደርጋል።ይህ እንግዲህ የአገሪቱ ሀብት በሙሰኛ ባለስልጣናት እና ባዕዳን የመዘረፍ ጉዳይ ሁሉ እንደቀጠለ ማለት ነው።በመጨረሻ ኢትዮጵያን የከበቡት ኃይላት በማናቸውም ጊዜ አገሪቱን በቀላሉ ከፋፍለው የማዳከም አመቺ ጊዜ እንዳገኙ ያስባሉ። ህወሓት በስልጣን ላይ መቆየት ከቻለ መጪው ጊዜ ከእዚህ ያነሰ አይሆንም።ስርዓቱ የገባበት ቅራኔ በሙሉ ሳይፈታ እና የቅራኔው መነሻ ከስልጣን ሳይወርድ የኢትዮጵያን ህልውና ማስጠበቅ ፈፅሞ አይታሰብም።ሕዝብ እንጂ ግለሰቦች አገር አያድኑም።የኢትዮጵያ ሕዝብ አገሩን በባለቤትነት እንዲያድን ይህ ስርዓት ከስልጣን መውረድ አለበት።ከእዛ መለስ ግን ህወሓት ብሔራዊ ሕብረት የሚያመጣበትም ሆነ ስልጣኑን ሕጋዊ መሰረት ለማስያዝ ምንም የቀረው ጥይት የለም።በሕዝብ ዘንድ የመንግስት ሕጋዊነት (legitimacy) በእዚህ ያህል ደረጃ ከወረደ በኃላ ለመጠገን መሞከር ትርፉ የሚፎረፎተው ፍርስራሽ አይን ውስጥ እየገባ አይን እንዲያጠፋ ከማድረግ በቀር ምንም ትርፍ የለውም።ይህንን ከስርዓቱ ጋር እየሰሩ ያሉ በሙሉ ሊረዱት የሚገባ ሀቅ ነው።
ባጭሩ የህወሓት በስልጣን ላይ መቆየት በአማራጭነት የማይቀርብ ይልቁንም ኢትዮጵያ በዘመኗ አይታ ወደማታውቀው የእርስ በርስ ግጭት የሚመራት መሆኑ መታወቅ አለበት።ይህ ሁኔታ ደግሞ እንደ አገር ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ የማትችል ወደ ማድረግ የሚመራት አሁንም በስልጣን ላይ ያለው ቡድን የታቀደ የመከፋፈል እና የማጋጨት ሥራ ነው።
ለውጥ
ሁለተኛው እና እንደ እኔ ብቸኛው አማራጭ የምለው በኢትዮጵያ አፋጣኝ ግን የሁሉም ህብረት የታየበት ለውጥ ማምጣት ነው።ለውጥ ጊዝያዊ የኃይል ክፍተት፣የህዝብ አለመረጋጋት፣ የአካባቢ እና ዓለም አቀፍ መድረኮች የመደመጥ አቅም መቀነስ ወዘተ ያጋጥሙታል።ለእዚህም ነው ከላይ የመፍትሄ አካላት መሆን የሚገባቸው ተብሎ የኢትዮጵያ ጦር ኃይል እና ሕዝብ ይቅርታ የጠየቁ የስርዓቱ አካላት የለውጡ አካል እና ኢትዮትጵያን የማዳን ድርሻ አላቸው የተባለው።ስለዚህ የኃይል ክፍተት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሥራ ብቻ ሳይሆን የጦር ኃይሉም ተግባር ነው።
ሰራዊቱ ከየትም የመጣ ሳይሆን አሁንም ከኢትዮጵያ ሕዝብ የወጣ እና በየቦታው የሚነሱ ግጭቶች ሰለባ ስለሆነ ችግሩ የአገሪቱ ችግር የሚመነጨው ከመሪዎቹ እንደሆነ ይገነዘባል።ለውጥ መምጣቱ የአገራችን ችግር በጋራ መነጋገር ይስችላል፣ከልዩነታችን ይልቅ ሕብረታችንን የሚያሳዩን የመገናኛ ብዙሃን ይኖሩናል፣ ከሁለት ሚልዮን በላይ የሚገመተው በውጭ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ለአገሩ የጋራ ጉዳይ የመስራት ዕድል ይኖረዋል፣የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት በበለጠ ይነቃቃል፣ በኢትዮጵያ ላይ ከባዕዳን ጋር በማበር የሚያሴሩት በግልፅ ለሕዝብ ይጋለጣሉ፣ ሕዝብ በእራሱ የመለያየት ፖለቲካ አራማጆችን ከአገራዊ ፖለቲካ አራማጆች የመለየት ዕድል ስለሚያገኝ የመወሰን አቅሙን ያሳያል።
ይህ ሁሉ ሁኔታ ህወሓት በስልጣን ላይ ሆኖ ህዝቡ በመታፈኑ ሳብያ የሚመጣው አደጋ ጋር ሲነፃፀር ለውጥ የሚያመጣው አንድነት እና ህብረት የበለጠ የአገሪቱን አንድነት የማምጣት አቅም ይኖረዋል። እዚህ ላይ ብዙዎች በሌላ አገር ያሉ ተሞክሮዎችን በማንሳት ከአምባገነን መሪዎች በኃላ መከፋፈል እንደሚኖር ሊሰብኩ ይሞክራሉ።ይህ ግን እንደ ኢትዮጵያ ላለ የእረጅም ጊዜ ማኅበራዊ መስተሳስር ላለው ሕዝብ አይሰራም።እርግጥ ነው ይህ ማለት ማኅበራዊ መስተሳሰር በእራሱ ተአምር አይፈጥርም። ትውልድም ተቀይሯል።ስለሆነም የምሁራን አስተዋፅኦ በጣም ይፈለጋል።በዝምታ የእራስን ኑሮ እየኖሩ ከንፈር መምጠጥ በእራሱ ኢትዮጵያን ከመግደል አይተናነስም።
ባጠቃላይ ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ እንደ ውሃ ጠብታ ቀስ እያለ እየሸረሸራት ነው። ችላ ብሎ ወይንም ዝም ብሎ የሚኖረው ሕዝብ እጣው እና ህይወቱ ከአገሩ ጋር መያያዙን ማመን አለበት።በተለይ ምሑራን ቢያንስ ለአገራቸው እና ለሕዝባቸው አዳዲስ ሃሳቦች ከማፍለቅ አንስቶ የኑሮ መደላድላቸውን ብቻ እየተመለከቱ ከመኖር ባለፈ ለኢትዮጵያ ምን ላድርግ ማለት አለባቸው።ምንም እንዳልተፈጠረ ዝም ማለት በእራሱ በገዛ አገር ላይ የሚፈፀም የፀጥታ አሰቃቂ ወንጀል ነው።ኢትዮጵያ ከሌላ አገር ትለያለች።አምባገነኖች መጥተዋል፣አምባገነኖች ሄደዋል። ኢትዮጵያ ግን በሕዝቧ አስተዋይነት እና በእግዚአብሔር መሪነት ከብዙ ፈተና ድናለች።ወደፊትም ትድናለች። ለአገር ብዙ ሃሳብ እና አቅም ያላችሁ ግን ከእየተደበቃችሁበት የምትወጡበት ጊዜ አሁን ነው። የኢትዮጵያ ጉዳይ ከመቼውም ጊዜ በባሰ ሁኔታ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ትከሻ ላይ ወድቋል።እያንዳንዷ ቀን ለኢትዮጵያ ወሳኝ ነችና።
No comments:
Post a Comment