ሐምሌ 17/2007 ሐምሌ 16/2007 ዓ.ም. ለአሥር ወራት በእስር ላይ የቆየውን ጋዜጠኛ፣ ተመስገን ደሳለኝን (ከኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር ዝምድና የለውም፤) ለመጠየቅ ወደዝዋይ ወህኔ ቤት ሄጄ ነበር፤ የወሕኒ ቤቱ ባለቤቶች ማረሚያ ቤት ይሉታል፤ ማረሚያ ቤት ማለት ሀሳቡን በነጻነት የሚገልጽና በሀሳቡም ከወያኔ ጋር በሎሌነት ለመተዳደር የማያመች ሲሆን የቀናውን በጉልበት የሚያጎብጡበት ማለታቸው ነው፤ ማረም ማለት ቀጥታውን ማጉበጥ ነው፤ እንዴት እንደሚያጎብጡት ላሳያችሁ፤– 1. የኛን እንተወውና በተባበሩት መንግሥታት ውሳኔ እስረኞች ሰዎች በመሆናቸው ሰብአዊ ደኅንነታቸውና ክብራቸው ሁልጊዜም እንዲጠበቅላቸው ያስፈልጋል፡፡ 2. የኛን እንተወውና በተባበሩት መንግሥታት ውሳኔ እስረኞች ሁሉ ከመሰቃየትና ከመጉላላት በጸዳ አያያዝ እንዲጠበቁ ይደነግጋል፤ 3. የኛን እንተወውና በተባበሩት መንግሥታት ውሳኔ አንድ እስረኛ ዘመዶቹና ወዳጆቹ ከሚኖሩበት በጣም ርቆ አይታሰርም፤ 4. የኛን እንተወውና በተባበሩት መንግሥታት ውሳኔ የታመመ እስረኛ ሙሉ ህክምናና አስፈላጊውን መድኃኒት ሁሉ ማግኘት አለበት፤ 5. የኛን እንተወውና በተባበሩት መንግሥታት ውሳኔ እስረኞች በአእምሮና በመንፈስ የሚያድጉበት ትምህርትን የማግኘት፣ መጻሕፍትን የማግኘት መብቶች አሏቸው፤ 6. የኛን እንተወውና በተባበሩት መንግሥታት ውሳኔ ማንኛውም እስረኛ በእምነቱ መሠረት አምልኮቱን የመፈጸምና የሃይማኖቱን መጻሕፍት የማንበብ መብት አለው፤ 7. የኛን እንተወውና በተባበሩት መንግሥታት ውሳኔ ማንኛውም እስረኛ ዘመዶቹና ወዳጆቹ እንዲጎበኙት መብት አለው፤ 8. እስረኞች የእስር ጊዜያቸውን ጨርሰው ከወህኒ ቤት ሲወጡ ትክክለኛ የማኅበረሰቡ አባሎች ሆነው እየሠሩ ለማኅበረሰቡ እድገት ድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ማሰናዳት ያስፈልጋል፤ በዝዋይ እንዳየነውና እንደተነገርነው የእስረኞች ሁኔታ በጣም የሚያሳዝንና ከላይ የተዘረዘሩትን የሰብአዊ መብቶች የሚጥስ ነው፤ ጤንነት ዋና ነገር ነውና በሱ እንጀምር፤ ተመስገን ደሳለኝ ወንጀል የተባለበት የፖሊቲካም ሆነ የማኅበረሰብ እምነቱን እያፍረጠረጠ በመጻፉ ነው፤ (በ1992 ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ባደረግሁት ንግግር ‹‹አትፍሩ›› ብለሃል ተብዬ ተከስሼ ነበር!) እንዲያውም ክሱን አስቂኝ የሚያደርገው መንግሥትን ነቅፈሃል የሚል መሆኑ ነው፤ ሦስት ዓመት እስራት ተፈረደበት፤ ይግባኝ ተከለከለ፤ አሁን ከታሰረ አሥር ወራት ሆኑት፤ ተመስገን በጣም ከታመመ ጥቂት ቆየ፤ አንደኛ አንዱ ጆሮው በጭራሽ አይሰማም፤ ሁለተኛ ከባድ የወገብ ሕመም ስላለበት መተኛትና መቀጥም በጭንቅ ሆኖበታል፤ ሆኖም አሳሪዎቹ ወደሀኪም ቤት ሊወስዱት ፈቃደኛ አይደሉም፤ ከዚያም በላይ መድኃኒት ከውጭ ሲመጣለት ይከለክላሉ፤ እኔም የወገብ ሕመም ስላለብኝ የወገብ ሕመሙን የሚያቀልለትን መድኃኒት ወስጄለት ነበር፤ አንድ አሥር አለቃ መድኃኒቱን አየና ከለከለ፤ መልሼ ይዤው መጣሁ፤ እንዲህ ያለውን ውሳኔ የሚያደርጉ ሁሉ ወያኔዎች ናቸው፡፡ ከተመስገን ጋር ትንሽ ጊዜ ቆይተን በዚያው በዝዋይ የታሰሩ ሌሎች ጋዜጠኞችን ለመጠየቅ መጀመሪያ ተፈቅዶልን ስለነበረ ወደዚያ ስናመራ አንድ ሹም መሳይ መጥቶ ወታደሮቹን ለብቻ ለብቻ በስም እየጠራ በመንሾካሾክ ትእዛዝ ይሰጣል፤ እየተንሾካሾከ ለአንዱ ትእዛዝ ሰጥቶ ሌሎቹን እንዳናይ ከለከለንና ተመለስን፤ ምክንያቱን ብንጠይቅ በአንድ ጊዜ መጠየቅ የሚቻለው አንድ እስረኛ ብቻ ነው ተባልን፤ ቅን መንፈስ ለጎደለውና ለሙስና ለተጋለጠ አሠራር ጥሩ ምሳሌ ነው፤ በመንሾካሾክ የሚሰጠውም ትእዛዝ ዓላማው ያው ይመስላል፤ ወያኔ በሰዎች ላይ እንዲህ ያለ ጭካኔ ማሳየት የሚፈልገው ለምንድን ነው? በዝዋይ እስር ቤት ትምህርትም እንደመድኃኒት የተጠላ ነገር ነው፤ ለተመስገንም ሆነ ለሌሎች መጻሕፍት አይገቡላቸውም፤ ለምን? ብዬ ስጠይቅ አንዱ ጠባቂ ‹‹ለእውቀት የሚሆን መጽሐፍ ይገባል፤›› አለኝ፤ የእውቀትን ፍቺ ለመጠየቅ ስሞክር ቶሎ ግራ መጋባቱን አየሁና ተውሁት፤ እሱም እንዳያውቅ ስለሚፈልጉ፣ አለቆቹ የእውቀትን ፍቺ ጠበብና ቀለል አድርገው አስተምረውታል፤ ሎሌ ትእዛዝን በሹክሹክታ እየተቀበለ ማስፈጸም እንጂ፣ እውቀት አያስፈልገውም፤ እዚህ ላይ ምናልባት በደርግ ጊዜ በእስር ቤቶች የነበረውን የትምህርት መስፋፋት ማንሣት ይጠቅም ይሆናል፤ በደርግ ዘመን ብዙ የተማሩ ሰዎች ታስረው ስለነበረ እረስበርሳቸው እየተማማሩ አንዳንድ ሰዎች ጀርመንኛና ፈረንሳይና ቋንቋዎች፣ ግእዝና ታሪክ እየተማሩ ወጥተዋል፤ በተለይ በሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ወህኒ ቤቶች አንደኛ ሲወጡ እንደነበረ አስታውሳለሁ፤ ዛሬ በወህኒ ቤቶች ትምህርት ክልክል ነው፤ በቃሊቲ ሁለት የትምህርት ሙከራዎች ከሽፈውብናል፤ አንድ ጊዜ ኦሮምኛ ለመማር የፈለግን ሰዎች ተሰባስበን ተከልክለናል፤ ሕግ ለመማርም ጀምረን ታግደናል፤ እንዲሁም ጂምናስቲክ በቡድን መሥራት ክልክል ነበር፤ ማናቸውም እውቀት አደገኛ ነው! ታዲያ ማረሚያ ቤት የሚሉት ማንን ለማታለል ነው? ማረሚያ ቤት እንዲሆን በመጀመሪያ አሳሪዎቹ መታረም አለባቸው! እንደተመስገን ደሳለኝ፣ እንደአብርሃ ደስታ፣ እንደእስክንድር ነጋ፣ ከዞን ዘጠኝም በፈቃዱ ኃይሉ፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ አቤል ወበላ፣ አጥናፉ ብርሃኔ ገና አልተለቀቁም፤ በተጨማሪም ከእስልምና በኩል የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባሎች ዛሬም እንደታሰሩ ነው፤ የመፍትሔ አፈላላጊዎችን ማሰር ነገሩም ግራ ነው፡፡ በመጨረሻም መነሣት ያለበት አንድ አደገኛ አዝማሚያ አለ፤ ፖሊስ የሚባለው ፍርድ ቤት ከሚባለው ጋር ያለው ግንኙነት ሕግ የሚባለውን ከጨዋታ ውጭ አድርጎታል፤ ፍርድ ቤት የሚባለው እስረኛ እንዲፈታ ፖሊስ የሚባለውን ሲያዝ እንደማይፈጸም በተደጋጋሚ ታየ፤ ይህ የመጨረሻው የውድቀት ምልክትይመስለኛል፤ቆም ብሎ ማሰብና አስፈላጊውን የለውጥ እርምጃ መውሰድ የሚያስፈልገው አሁን ነው፡፡ - See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/45312#sthash.FrrvNzhq.dpuf
No comments:
Post a Comment