እንግዲህ ዛሬ ደመራው በድምቀት ተለኮሰ አይደለ… (ለመሆኑ ወዴት ወደቀ… አወዳደቁስ ምን ተናገረ…. እስቲ ቅርብ የነበራችሁ አጣሩና ንገሩን….) ታድያ ደመራው በተለኮሰ በነጋታው አዲሳባ ላይ ከሆኑ፤ ማይትስ ሽሮሜዳን ነው… መኖርስ ሽሮሜዳ ላይ ነው… የምንል እኛ፤ መስቀል እና ሰኞ ሲገጥሙ ደግሞ በቃ ሽሮሜዳ አለሟ ነው፤ እና እነ ቦሌ ሳይቀሩ ምነው እርሷን ባደረገኝ እያሉ በጉምዥት ነው የሚያዩዋት… ስንል ምስክረነታችንን እንሰጣለን።
ድሮም ሽሮሜዳ ሰኞ ቀን እጣ ፈንታዋ ነው… ፈታ የሚባልበት ላንቺም ጠጪ ለኔም አምጪ ተግባራዊ የሚሆንባት…. ቸበር ቻቻ የሚነግስበት እቁብ የሚጣልበት እቁብ የሚበላበት ጠጅ እንደ ጮማ የሚቆረጥበት…. ዘገየ ዘለግ ባለ ድምጹ ”የዝናዬ…. አንቺ የዝናዬ….የዝናዬ ማሬ ወለላዬ….” ብሎ እየዘፈነ የሰፈሩን ሰው የሚያስደምምበት… እነ አቡሌ በግሩፕ ”ዴንዳ ዴንዲኪ”ን የሚያቀልጡበት… ሰኞ ለሽሮሜዳ በቃ ምን ልበላችሁ ሰኞ ነው!!!
መስቀል እና ሰኞ ሲገጥሙ ደግሞ…. ”ዮ…..ኦ……ካ መስቀሌ… ዮ….ኦ…ኦ…ኦ..ኦ” እየተባባሉ ቤት ያፈራውን ተቃምሰው ጠጅ ቤት ያፈራውንም ድጋሚ ተቃምሰው ፌሽቲያው ይደራል፤ እለቱ መስቀል ነውና… ጠጅ ቤቶቻችን ጠጅ ቤት ብቻ ሳይሆኑ የሰርግ አዳራሽም ይሆናሉ… እግር የጣለው ሁሉ የሰርጉ ታዳሚ ነው… ሞቅ ያለው ሁሉ ሙዚቃ አውጪ ነው… ጉራግኛ ዶርዝኛ ኦሮምኛ እና ሽሮሜድኛ ይዘፈናል…
ይሄኔ እነ ሰንጋ ተራ አይቀሩ እነ ስጋ ሜዳ አይቀሩ ምነው ሸሮሜዳን በሆንኩ ባይሉ ታዘቡኝ….
በድጋሚ እንኳን አደረሳችሁ!
ምችት ይበላችሁ!
No comments:
Post a Comment