Sunday, September 27, 2015

እምቢኝ በል ወያኔን

ተጨፈኑና ላሞኛችሁ የሚለውን የወያኔን ደባ ለመቃወም አለበለዚያም የጎሳና የሃይማኖት ፖለቲካን ለማራመድ በወያኔና ሻዕቢያ አጋፋሪነት አብረው አሸሸ ገዳሜ መቼ ነው ቅዳሜ እያሉ የኢትዮዽያን ህዝብ ሲገሉና ሲያስገድሉ የነበሩ አሁን ደግሞ በውጭ በመሆን ስማቸውን በመቀያየር የሻዕቢያ ተለጣፊ በመሆን እንደ ሸማኔ ዕቃ ወዲያና ወዲህ እያሉ በሌላ በኩል ትላንት የኢትዮዽያን ህዝብ ሲገልና ሲያስገድል ሲዘርፍና ሲያዘርፍ የነበረው፣ የኢትዮዽያን ወጣት ለስደት የዳረገውና በሞት የቀጣውን መለስ ዜናዊ በማጀብ ኢትዮዽያን ሲዘርፉ የነበሩና ዛሬ ከሞት ተርፈው በውጭ ያሉ የሀገራችንን ልጆች የአበሳና የመከራ ጊዜ ለማራዘም ተንኳሽ ፖለቲካን የሚያራምዱትን ካንተ የኔ ይበልጣል አንተ በኔ ስር ዕደር በኔ ጥላ ተጠለል በማለት ከኢትዮዽያ ህዝብ ሊለያየን እየሞከረ ያለውን ይህን የወያኔ እና የሻዕቢያ ቅጥረኛ እንቢ እንበለው። በተሻለ መልኩ ኢትዮዽያዊና የኢትዮዽያ ህዝብ ዓይኑን የጣለበትን አንጋፋ የፖለቲካ ድርጅትን በየምክኒያቱ እያራከሱና ስም እያጠፉ የማድቤት ፖለቲካን በመጀመራቸው ለተጠናከረ ድጋፍ ማጣት ምክኒያቶች እየሆኑ ያሉትን እንቢኝ አሻፈረኝ እንበላቸው። በትውልዴ ነብይ ወይም የነብይ ልጅ አይደለሁም ጆሮዬ ካዳመጠው ዓይኔን ካፈዘዘው የግፍና የጣር ማስታወሻ ጨልፌ ሀገር ወዳድ ለሆኑ ኢትዮዽያዉያን ወገኖቼ የሚከተለውን ለማሳሰብ እወዳለሁ። ህይወት ተሻጋሪ ናት ለአፍታ ደስታ ትሰጠና ሳይታሰብ ደግሞ ሀዘንን ከመከራ ለቅሶ ጋር ታላብሰናለች በዚህ ዓለም የምናሳልፈው ዘመንም እጅግ ጥቂት ነው። ትላንት በሀገራችን አውራ ጎዳናዎች ክፉኛ የኢትዮዽያ ህዝብን ሲያሰቃይና ሲገድል የነበረ የወያኔ አለቃ የነበረው ዛሬ በህይወት የለም፡ አውራው ቢሞትም በሀገራችን በኢትዮዽያ ታይቶ ተሰምቶ የማይታወቅ የመከፋፈልና የማፈራረስ ዘመቻውን ወያኔ አሁንም ተያይዞታል። ህዝባችን በአንድነትና በህብረት እንዳይኖር የተቃጣበትን ጥቃት በጋራ እንዳይመክት በዘር በቋንቋ በሃይማኖት በተሰመረ የአስረሽ ምችው የፖለቲካ ዘይቤ አለቅጥ ይታመሳል። ታዲያ አንባቢ እንዲረዳልኝ የምሻው የዚህ ሁሉ ሴራ መሠሪ እራሱ የወያኔው ዘረኛ ቡድንና አሽከር ሆድ አደሮቹ በኢትዮዽያ ህዝብ ውስጥ ተሰግስገው ያሉትን ሲሆን ግብራቸው ሰይጣናዊ ስለሆነ ወያኔን በሁለገብ ትግል እንቢኝ አሻፈረኝ ልንለው ይገባል። ወያኔና ሻዕቢያ የኢትዮዽያ የውስጥ መዥገር ናቸው። አሁንም በስልጣን ላይ አለሁ የሚለውም ወያኔ የኢትዮዽያ ህዝብን ሊወክል አይችልም!! እንደሚታወቀው በምንሊክ ቤተመንግሥት ተወሽቆ ኢትዮዽያንና ኢትዮዽያዊነትን ከህዝባችን ልብ ለመፋቅና በምትኩ የጎጥንና የጎሳን ፖለቲካ የሚያራምድ ድርጅት ነው። ነገር ግን የትግራይ ህዝብ ወኔና ኢትዮዽያዊነትም በዚህ ስንኩል ድርጅት ሴራ አይለካም። የትግራይ ህዝብ ወያኔ ከደገነበት አፈሙዝ ውጭ በራሱ የሚያስብ የሀገር ፍቅር የሚያንገበግበው ቆራጥና አስተዋይ ህዝብ ነው። ለዚህም ነው የዚህ ኩሩ ህዝብ ብርታትና ኢትዮዽያዊነት በወያኔ ነኝ ባዩ ዘረኛ ድርጅት ልንለካው የማይገባን። አንዳንድ በወያኔ ጠረጴዛ ስር ፍርፋሪ ለመልቀም ጎንበስ ቀና በሚሉ ከዚህ ብሔር መካከል ወጥተው ብሎም የራሳቸውን ህሊና የሸጡና ለወያኔ ጊዜያዊ መገልገያ በሆኑ ሰዎች ምክኒያት የትግራይ ህዝብ ተወቃሽ አይሆንም። ወያኔንና የእሱ ተላጣፊዎች የሆኑትን አንተ የትግራይ ህዝብ እንቢ ልትላቸው ይገባል። እኛ የትግራይ ህዝብ ከኢትዮዽያ ህዝብ ጋር ነን በማለት የወያኔ ምፀት ልታወግዝ ይገባል። ይህን ህዝብ የፈጠራ ፕሮፓጋንዳ ለጊዜው ቢያደናግረውም ኢትዮዽያዊነቱንና አሁን በወያኔ የተያዘው አፍራሽ የፖለቲካ ዘይቤ ልክ አለመሆኑን እውነት ራሷ ትመሰክርለታለች። ከዚህም ባሻገር ሀገር በጎሳና በቋንቋ ስትከፋፈል የሚያስከትለውን መዘዝ የአካባቢ ክስተቶች ይመሰክራሉ። ጥቃት ደግሞ አመፅን ይወልዳል ግፍ በቀልን ያመጣል መከፋፈል ለውጭ ጠላት አጋልጦ ይሰጣል። አንዱ በሌላው ላይ የሚያደርሰው በደል ምንም ጊዜ ቢቆጥርም መመለሱ አይቀርም። ለጥቃት አሜን ብሎ የሚኖር ሰው አንዴ ሳይሆን በየዕለቱ ነው የሚሞተው በሌላ አባባል ህይወት የባለቤቷን ቆራጥነት ትፈታተናለች። ስለዚህ እንቢኝ በል አንበሳ ፀጉሩን ዝንብ አያስነካም። የኢትዮዽያ አንድነትን ለማስከበር ሆነ የህዝባችንን ውህደት ለማፋጠን በቅድሚያ የወያኔን ሴራ የምናከሽፈው እንቢ ስንልና ብሎም ለህዝባዊ አመፅ ስንነሳሳ ብቻ ነው። ተራ በተራ እጅና እግርህ እየታሰረ ቤትህ ተዘርፎ ሀገርህ ፈርሳ ዓይንህ እያየ ዳግመኛ ሞትን ከመሞት የሁሉንም ዘር ሃይማኖትና ቋንቋ ባቀፈ የፖለቲካ መርህ በመመራት ህዝባዊ በሆነ ድርጅት ታቅፈን ስንታገል ብቻ ነው የምናቸንፈው። በአገር ውስጥም ሆነ በየዓለማቱ ተበትነን የምንገኝ ኢትዮዽያዊ/ት የጎሳንና የቋንቋን ክልል በተሻገረ አመለካከት በመሰለፍ የኢትዮጵያ ህዝብ ስልጣን ባለቤት ለማድረግ የሚበጀን ሐዋርያው እንደመከረን እንቢ ለጋኔን እንዳለው እኛም ደግሞ እምቢኝ አሻፈረኝ ብለን ጸረ ወያኔ ትግላችንን እናፋፍም ስል ጹሑፌን በዚሁ እቋጫለሁ። ይዋል ይደር እንጂ በህዝብ ደም እና እንባ የሚሳለቁ አምባገነኖች ሁሉ በህዝብ አመፅ ተገርስሰው ህዝባዊ ፍርድ የሚቀበሉበት ጊዜ ፀሐይ በምስራቅ እንደ መውጣቷ ያለና አይቀሬ የተፈጥሮ ህግ ነው። የወያኔን አምባገነን አገዛዝ በተባበረ ትግላችን እናስወግዳለን። የኢትዮዽያ ህዝብ የስልጣን ባለቤት እስከሚሆን ድረስ ትግላችን ይቀጥላል እናቸንፋለን!

No comments:

Post a Comment