Sunday, April 17, 2016

ውርደታችን ይኸው እንደቀጠለ ነው፤ በአንድ ቀን በጋምቤላ የሚኖሩ 170 ዜጎቻችን ለምን ተገደሉ?

ከብስራት ወ/ሚካኤል
የዜጎችን ደህንነት እና ሀገርን ዳንድንበር ሳያስደፍር መጠበቅ የነበረበት መከላከያ ሰራዊት፤ መሃል ሀገር ዜጎችን ለመግደልና ለማሸበር በመሰማራቱ ስራ ከበዛበት ሰነባብቷል፡፡ ዜጎችን ከመድገልና ከማሸበር የተረፈውም አንዴ ሶማሊያ ሞቃዲሾ በረሃ፣ አንዴ ሱዳን እና ላይቤሪያ ዜጎችን ሰላም ሊያስጠብቅ እንደተሰማራ እንሰማለን፡፡
ፎቶ ምንጭ: ሐና

ነገሩን መች አጣናውና፤ ወታደሮቻችን ለህወሓቶች ጥሩ የዶላር ምንዛሪና የኪስ ማደለቢያ መሆናቸውን፡፡ ሰላም አስከባሪ ወታደሮቹም ቢሆኑ ለገዥዎች ዶላር ምንዛሪ ከመሆን ውጭ የሞቱትና የተሰወሩት እንኳ ስላሉበት ሁኔታ ቤተሰብ ጋ ሳይደርስ እዛው የአሞራ ሲሳይ የሆኑትን ቤት ይቁጠረው፡፡
እጅግ በጣም የሚያሳዝነውና የሚያስቆጨው ትናንትና የጦር መሳሪያ እንደሸንበቆ ዘንግ ይዘው የሚዞሩ የደቡብ ሱዳን ዘላኖች ድንበራችንን ዘና ብለው በመሻገር በጋምቤላ 170 ንፁሃን ዜጎቻችንን በግፍ ገድለው በርካታዎችን አቁስለውና እስካሁንም ቁጥሩ በውል ያልታወቀ የቁም እንሰሳቶቻችን ዘርፈው ዘና ብለው ወደመጡበት ሄደዋል፡፡
በጅምላ ግድያ የተሰነዘረባቸው ዜጎች ለአካባቢው የጋምቤላ ክልል መንግሥትና በአካባቢው ላሉ የፖሊስና መከላከያ የድረሱልን ጥሪ ቢያቀርቡም ሚሰማቸው በማጣታቸው የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ ዜጎቻቸውን ድረሱልን በማለታቸው በተደረገ ትብብር ከ60 ያላነሱ የደቡብ ሱዳን ዘራፊና ገዳዮችን መግደላቸውንና ከዛም ወደመጡበት ሊመለሱ እንደቻሉ የጥቃቱ ሰለባዎች ይናገራሉ፡፡ ህወሓት/ኢህአዴግ ሰዎች ውርደት ክብራቸው ስለሆነ እንጂ ይህ የሀገሪቱና የዜጎች ብቻ ሳይሆን የነሱም ውርደት መሆኑ በገባቸው ነበር፡፡ ነገሩ ከሆድና ስልጣን የዘለለ ራዕይና ዓላማ ለሌለው ሰው ክብር መች ይገባዋል?
ኢትዮጵያዊ ስሜት ያለውና ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን መብትና ጥቅም የሚቆም መንግሥትና ስርዓት እስኪመጣ ግድያውም ሆነ ውርደታችን በዚህ የሚያበቃ ሊሆን አይችልም፡፡ የትናንቱ የመጀመሪያው አይደለምና፡፡ የሱዳን ነጋዴዎችና ሾፌሮች ካቅማቸው በየጊዜው ስንት ኢትዮጵያውያንን በራሳችን ምድር ገድለው መንገድ ላይ ወንዝ ዳር እየጣሉ ዘና ብለው ወደ መዲናቸው ካርቱም ይመለሱ የለ?
መቼም ያን በደል የፈፀሙት ደቡብ ሱዳናዊ ዘላኖች የእናት ጓዳ ይመስል ዘው ብለው በመግባት ነው፡፡ ይህም የሆነው ኢትዮጵያዊ እና የኢትዮጵያውያንን ደህንነትና ሰላም የሚያደፈርስ እንጂ የሚያስጠብቅ መንግሥት እንደሌለን ጠንቅቀው ስለሚያውቁ እንጂ በቅርባቸው ያሉ ኬንያና ዩጋንዳ ቢሆን እንዲህ ይዳፈሩ ነበር? ይባስ ብሎ በልሳኑ ፋናቢሲ የተገደሉ ዜጎችን ቁጥር ለመቀነስና የተለመደውን ደረቅ ፕሮፖጋንዳ ይነዛልኛል፡፡ ቲሽሽሽ!

ከኢሳት ሬዲዮና ቴሌቪዥን የተሰጠ የሀዘን መግለጫ


“ጋምቤላ” የሚለውን ስም ካወቅነው ድፍን ሃያ ስምንት ዓመታት ሆኖታል፡፡ ከስሙ ጋር የተዋወቅንበት አጋጣሚ ደግሞ የሚረሳ አይደለም፡፡ እንዲህ ነው!!
የአራተኛ ክፍል የህብረተሰብ ትምህርትን ታስተውሱታላችሁ… አዎን! ህብረተሰብ በፍቅር ከምንማራቸው ጥቂት የትምህርት ዓይነቶች አንዱ ነው፡፡ ትምህርቱ “ህብረተሰብ” ቢባልም ጂኦግራፊን፣ ታሪክንና ሶስዮሎጂን የሚያካትት ዓይነት ነበር፡፡ የመማሪያ መጽሐፋችን በጣም ግሩም ነበር፡፡ ከርሱ በተጨማሪ በሬድዮ የሚሰጠው የአንድ ፔሬድ (ክፍለ ጊዜ) የማጠናከሪያ ትምህርት በመጽሐፉ የሌሉ በርካታ ቁም ነገሮችን የሚያስጨብጥ ነበር፡፡


Gambella4

ታዲያ በገጠር የምትኖር አያቴ ሞታ ለሀዘኗ ስል ለአንድ ሳምንት ከክፍል ጠፋሁ፡፡ ሀዘኑ ተጠናቆ ወደ ከተማ በተመለከስኩበት በሁለተኛው ቀን የህብረተሰብ ትምህርት አስተማሪያችን የሙከራ ፈተና (“ቴስት” የሚባለው) ሰጠን፡፡ ከአስር ጥያቄዎች ዘጠኙን መለስኩ፡፡ አንደኛው ግን አቃተኝና ባዶውን ተውኩት፡፡ የሚገርመው ነገር አብዛኛው ተማሪ የመለሰው ጥያቄ ነበር የከበደኝ፡፡ እንዲህ ይላል፡፡
“በኢትዮጵያ በዱር አራዊት ሃብቱ አንደኛ የሆነው አውራጃ የትኛው ነው”
አስተማሪያችን (ጸጋ መለሰ ይባላል) ጠራኝና “ሁሉንም መልሰህ ይሄ ጥያቄ ብቻ እንዴት ከበደህ አለኝ” በማለት ጠየቀኝ፡፡ በህብረተሰብ መማሪያ መጽሐፋችን ላይ እንዲህ የሚል መረጃ እንደሌለ ነገርኩት፡፡ “ባለፈው ሳምንት” ትምህርት በሬድዮ አልተከታተልክም” በማለት ጠየቀኝ፡፡ ፈቃድ ወስጄ ገጠር እንደሄድኩ ነገርኩት፡፡ መምህራችን የተሸወድኩበትን ምክንያት አወቀ፡፡ እናም የጥያቄውን መልስ እንዲህ በማለት መለሰልኝ፡፡

“በኢሉባቦር ክፍለ ሀገር ጋምቤላ አውራጃ”
አዎን! “ጋምቤላ” የሚለውን ስም ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት በዚያች አጋጣሚ ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ስለርሱ ክፉና ደጉን እየሰማን እስከ አሁን ድረስ አለን፡፡ በተለይም ስለጋምቤላ ከሚታወሱኝ መካከል በ1981 የጋምቤላ ተወላጅ የሆነው ታዋቂው ጊታሪስ ኩት ኡጁሉ የሚገኝበት የኪነት ቡድን ወደ ከተማችን መምጣቱ (ነዋይ ደበበ፣ ሂሩት በቀለና ሐመልማል አባተም በቡድኑ ውስጥ ነበሩ)፣ በተመሳሳይ ዓመት ጋምቤላ ከኢሉባቦር ስር ወጥቶ ራሱን የቻለ የአስተዳደር አካባቢ መሆኑ እንዲሁም አሜሪካዊው ኮንግረስማን ሚኪ ሌላንድ “ፑኝዶ” በተባለችው የጋምቤላ መንደር የሰፈሩትን የደቡብ ሱዳን ስደተኞችን ለመጎብኘት ሲጓዙ ደብዛቸው መጥፋቱና ከሁለት ወር ፍለጋ በኋላ አውሮፕላናቸው መገኘቷ ወዘተ…. ከማይረሱኝ ጋምቤላ ተኮር የደርግ ዘመን ትዝታዎቼ መካከል ናቸው፡፡
——–
በዘመነ ኢህአዴግ ደግሞ ጋምቤላ ወደ ክልል አደገ፡፡ በዚህ ዘመን በደምብ ከሚታወሱን ትዕይንቶች መካከል ቀዳሚ ሆኖ የሚወሳው በተከታታይ የተሾሙ ሶስት የክልሉ ፕሬዚዳንቶች “ኦኬሎ” የሚል ስም የነበራቸው መሆኑ ነው፡፡ ይህ የስም መመሳሰል ብዙዎችን ሲያነጋግር እንደነበረ አስታውሳለሁ፡፡ ከዚያ በፊት ደግሞ በጋምቤላ በመምህርነት የተመደበው “ቶማስ መንግሥቱ” የተባለ የገለምሶ ተወላጅ የተማሪዎቹን የስም መመሳሰል እንደ ትንግርት ሲያወራ እንደነበረ ከአንድ አጎቴ አንደበት ሰምቻለሁ፡፡

ከዚህ የስም መመሳሰል ጀርባ ያለው ሚስጢር የተገለጸልን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በ1992 በአሶሳ ከተማ አንድ ልዩ ዝግጅት ባቀረበበት ወቅት ነው፡፡ በዝግጅቱ ላይ የተገኙ ሽማግሌዎች የልዩ ልዩ ብሄረሰቦችን የስም አወጣጥ ሲናገሩ የጋምቤላው የአኙዋክ ብሄረሰብ እንደምሳሌ ተጠቃሽ ሆኖ ቀረበ፡፡ ሽማግሌዎቹ እንደተናገሩት በአኙዋክ ብሄረሰብ ደምብ መሠረት የመጀመሪያ ልጅ ምንጊዜም ቢሆን “ኦኬሎ” ተብሎ ነው የሚጠራው፡፡ ሁለተኛ ልጅ ደግሞ “ኡጁሉ” የሚል ስም ይሰጠዋል፡፡ የመጀመሪያ ልጅ ሴት ከሆነች ደግሞ “አሪየት” ተብላ ትጠራለች (ሁለተኛዋ ልጅ የምትጠራበትን ስም ረስቼዋለሁ፤ የምታስታውሱ ንግሩን)፡፡ በዚያው ዓመት አንድ የናሽናል ጂኦግራፊ ጋዜጠኛ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ ዘመን ፎቶዋን አንስቶ በዓለም ላይ ያስተዋወቃት የጋምቤላዋ ኮረዳ ትልቅ ሴት ሆና ለጋዜጣ ኢንተርቪው ቀርባ አንብበናታል፡፡
በዚህ ክልል በጥሩነታቸው ከሚታወሱት ዜናዎች አንዱ ነዳጅ ተገኘ መባሉ ነው፡፡ ነገር ግን ነዳጁ እስከዛሬ ድረስ አልወጣ ብሏል፡፡ ወሬው ብቻ በየጊዜው ይመላለሳል፡፡ ግምባታ ተካሂዷል፣ ዩኒቨርሲቲ ተከፍቷልም ይባላል፡፡ ይሁንና ከክልሉ የሚመነጩት ዜናዎች በአብዛኛው ጥሩ አልነበሩም፡፡ የትናንቱን ዓይነት ልብ ሰባሪ ወሬ ነው በአብዛኛው የምንሰማው፡፡ ጋምቤላዎች ሁሌም ሐዘንተኞች ናቸው፡፡ ያሳዝናል!!
የሞቱትን ነፍስ ይማር!!

ወያኔ በመቀሌ ከተማ “ኢትዮጵያውያንን በዘር እና ሐይማኖት ከፋፍሎ ስለሚያካሂደው ዘመቻ” ስውር ስብሰባ አደረ


ከወልቃይት ጠገዴ ብጌምድር ፤ጎንደር ኢትዮጵያ
በከፍተኛ የህወሃት ማይከላዊ አመራሮች በሆኑት አቶ ተክለወይኒና አባይ ወልዱ እንዲሁም የትግራይ ክልል የደህንነት ቢሮ ሓላፊ የሆኑ አቶ ዘነበ ሐዱሽ የተመራው ጥቂት ታማኝ ካድሬዎች ብቻ የተገኙበት የትላንት ወዲያ (የሚያዚያ 08/2008 አ/ም) የመቀሌው ስብሰባ ከአንድ በመቀሌ ኗሪ የሆነ የአዲግራት አከባቢ ተወላጅ “ባስቸኳይ ለኢትዮጵያውያንና ለመላው የአለም ህዝብ ይጋለጥ” ብሎ የደረሰኝ መረጃ፣ ልጁ በላከልኝ መረጃ መሰረትእንደወረደ ያለ አንዳች ማሻሸያ እንዲህ ከታች ቀርቧል። ዘጋቢው የህወሀት አባል ሲሆን መረጃው ያገኘው በስብሰባው ከተሳተፈው የልብ ካድሬ ጓደኛው በቀጥታ ከነገረው እንደሆነ ጠቁሞናል።
Ethiopia, TPLF officials
አመሻሹ ላይ  ይህን ዘገባ የላከልኝ ውዱ ዘጋቢ “ህወሃት መሞቱ የሚታወቀው ገና የስብሰባው አዳራሽ ሳይከፈት መረጃው ቀድሞ ህዝቡ ጋር ይደርሳል፤ ከዚህ በላይ ያንድን መንግስት ተሰባብሮ መውደቁንና መበስበሱን አማላካች ሊሆን የሚችል ነገር የለም” ብሎኛል።ምስጋናዬን ለዚህ ውድ ኢትዮጵያዊ ላቅርብና ዘጋቢው “ምንም ይሁን ምንም አገሬ ኢትዮጵያን እወዳለሁ” ያለ ሲሆን “ህዝባችን የወያኔ ተንኮል አውቆ መጠንቀቅ እንዲችል ሆኖ ባጭር ግዜ ውስጥ ማስወገደ አለበት” ብሏል።
“የወያኔ ኢትዮጵያዉያንን በዘርና ሐይማኖት ከፋፍሎ የማጋጨትን ዘመቻ ግምገማ በትላንትናው ቀን 08 ሚያዚያ 2008  አ/ም በመቀሌ ከተማ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ህልውናን ሙሉ ለሙሉ እንዲያከትም ለማድረግ በጣም አስገራሚ የሆነ ስብሰባ ተደርጓል። ስብሰባው አንድን ወሳኝ የተባለን  ኦፕሬሽን  ግምገማ በማካሔድ ለቀጣይ አፈጻጸሙ እርማት በማድረግ እንዴት በተሳካ ሁኔታ ማስኬድ እንደሚገባ አቅጣጫን ለማስያዝ ነበር። የስብሰባው ትእዛዝ የወረደውም ከአዲስ አበባ ከአቦይ ስብሓት ነጋና አባይ ጸሓየ ሲሆን ወደ ስብሰባው መጨረሻ አካባቢም አቶ አባይ ጸሐየ በስልክ ደዉለው በማያክሮፎን ላውድ ተደርጎ ቀጭን ትእዛዝ ለተሰባሳቢው ተላልፏል። ትእዛዙ ከታች ባጭሩ የጽሑፌ  መጨረሻ አከባቢ እገልጸዋለሁ።
የስብሰባው ዋና አላማም የህወሀት ካድሬዎች በኢትዮጵያ ውስጥ የዘርና የሐይማኖት መከፋፈል ወደ ግጭት እንዴት ስውር በሆነ መንገድ በባለፉት 7 ወራት ሲያካሒዱ እንደቆዩ የሚገመግም ሲሆን በጣም ብዙ የተባሉ ክፍተቶች እንደድክመት ተነስተዋል። ይህም ከግምገማው ብሗላ በተደረገው  የችግሩ ምክንያቱ የተባሉት ደግሞ አንደኛውየአንዳንድ ካድሬዎች አለመታመን ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የህዝቡ በነገሮች ላይ መጠነኛ  መባነን ሊሆን ይችላል ተብሎ ደምዳሜ ተሰጥቶታል።
ኦፕሬሽኑ  ከተግባራዊነቱ  አንጻር ከሞላ ጎደል የተሳካ አፈጻጸም ያለበት ነው ቢባልለትም  ደካማ ጎኖች  ከተባሉ ዋነኛ ነጥቦች መካከል ደግሞ ከያንዳንድዋ ኦፕሬሽን ብሗላ ህዝቡ በቀላሉ ጣቱ እኛ ጋር እየቀሰረ ነው ያለው ይላል።  ለምሳሌ የአንዋር መስጊዱ ጥቃት ህዝበ ሙስሊሙ በሚነቃበት ሁኔታ ነው  የተከናወነው ከዚህም የተነሳ የታሰበ ግቡ አልመታም፤ በኦሮሚያ አመጽ የተከናወነው የቤተ-ክርስቲያናት ቃጠሎ የአንዱዋ የፕሮቴስታንት ቸርች ብቻ  በአካባቢው ባሉ አክራሪ ሙስሊሞች የተፈጸመ ቢሆንም የእኛው ካድሬዎች የሰሩት ተልእኮ ግን በክፊል የተነቃበት ሁኔታ ነው ያለው። ሌላው የአማራውና የቅማንቱ ዘር ግጭት በብዙ ኢትዮጵያውኖች መንግስት እንዳቀነባበረው የተደረሰብት የሚመስል እምነት በህዝቡ ዘንድ እንዳለ ታማኝ ካድሬዎቻችን አድርሰውናል። ይህ ሊሆን የቻለውም  ከትግራይ ተወላጆች ውጭ ያሉት ካድሬዎቻችን በብዛት ታማኝ ሆነው ሳይሆኑ ለሆዳቸው ብቻ ብለው ግዳጅ እየፈጸሙ እንደሆነ ነው የሚያሳየው። ከጎንደሩ የአማራና ቅማንት  የዘር ግጭት ውጭ በኦሮሚያ በሚገኙ አንዳንድ አከባቢዎች በከፊል አማሮች ከደረሰው ነገር  በቀር እንዲያውም ባልጠበቅነው ሁኔታ የኦሮሞ አባቶች ከለላ የሰጡበት ሁኔታ ሁሉ ስለነበር በተግባር እንደ እቅዳችን ተሳክቷል ለማለት አያስደፍርም። እንዲህም ሆኖ ግን ኦፕሬሽኑ ፍርሀትንና ጭንቀትን፤ ውጥረት፣ አለመተባበርንና አለመተማመንን ከመፍጠር አኳያ ግን እጅግ አጥጋቢ የተባለን ውጤት አስገኝቷል። ይህም በተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች የተነሱ አመጾችን ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ከማምጣትና መንግስትን ከመዳፈር ውጭ የተበጣጠሱና ለውጥ የማያመጡ አድርጓቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ኦፕሬሽኑ ከፍተኛ በሆነ የመባነን ሰለባ ሆኗል የምንለው ደግሞ በዩኒቨርሲትዎች የደረሱት የቦንብ ፍንዳታዎችና ቃጠሎዎች በብዛት ማለት ይቻላል መንግስት እንዳደረሰው ነው ህዝቡ ካድሬዎቻችንን ሳይፈራ  በየሻይ ቤቱና መጠጥ ቤቱ በንቀት የሚያወራው፤ ይህ ለእኛ ውርደት ከመሆን በዘለለ መልኩ ህልውናችንን የሚፈታተን ነገር ነው። እይህ ድፍረትም ካድሬዎቻችን የበለጠ እንዲፈሩና የሚፈጸሙት ተልእኮ ይባስ የተባነነበት እንዲሆን ያደርገዋልና ታማኝና ቆራጥ ካድሬዎችን ለተልእኮው ማሰልፍ የግድ ይላል። ካልሆነ ግን በፍርሃታቸው እንዲህ አይነት የተንዘላዘለ የጅል አሰራር የሚሰሩ ካድሬዎች ባስቸኳይ  ሊወገዱ ይገባል።
እንደዛም ሆኖ ግን አመጹ አሁንም ቢሆን ለመንግስት ስጋት ስለሆነ ይህ ኦፕሬሽን ክፍተቶቹን በመዝጋትና  ሁኔታዎችን ባገናዘበ መልኩ በተጠናከረ መንገድ መቀጠል አለበት። ቁልፍ መርሗችን እስከሆነ ድረስ በታማኝነትና ቆራጥነት ልንወጣው ግድ ይለናል። ለምሳሌ የወልቃይት ጉዳይ ለእኛ በጣም  አሳሳቢ ደረጃ  ላይ ደርሷል። ጥያቄያቸውም ህገ-መንግስታዊ ሽፋን ያለው በመሆኑና የተለያዩ ሚዲያዎች ሽፋን ስለሰጡት በቀላሉ ለማጥቃት ቢያስቸግረንም የስልክ ኔትዎርክና የመረጃ መረቡን በመዝጋት የሚቻለንን ያህል እይደረግንን ነው። ህዝቡም በጣም እልኸኛና ቆራጥ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ህጋዊ የፌደረሽን ምክር ቤቱ ውሳኔ በትዕግስት መስማት ስለፈ ለገ ነው እንጂ ውሳኔው አይሆንም ከተባለ በቀላሉ ወደ ጦርነት ገብቶ ከፍተኛ ኪሳራ ሊያደርስብን የሚችል ህዝብ ስለሆነ የፌደርሽኑ ውሳኔ በማዘግየት ወደ ሗላ በሳል ስራዎችን ከመስራት በቀር ምንም ልናደርገው አንችልም።  ነገር ግን ይህ ኦፕሬሽን በወልቃይት ተፈጻሚ ሲሆን በዛ አካባቢ ያሉ ሙስሊምና ክርስቲያኖች በመተማመን ስለሚኖር በህዝቡ መከፋፈል ለመፍጠር  መሞከር ኪሳራ እንጂ ውጤት አያመጣም፤ ግን ደግሞ የአካባቢው ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ይህ ኦፕሬሽን ለየት ባለ መልኩ ነው ባስቸኳይ መፈጸም ያለበት።
ህዝቡ በቀላሉ የመባነን ባህሪ ስላለው በህዝቡ እማኝነት እንዲኖረው ለማድረግ አካባቢው ክርስቲያን የበዛበት እንደመሆኑ መጠን የታጠቁ  አክራሪ እስላሞች ከሰሜን ሱዳን እንዲዘልቁ በማድረግ የድንበር ችግር ያለባቸው በማስመሰል እዛ በአከባቢው ያሉ የትግራይ ተወላጆችና ባለ የመከላከያ እዝ ተመጣጣኝ ስትራተጂያዊ  ዋጋ በመክፈልና የሚዲያ ሽፋን በማሰጠት ሌላ ቋሚ መፍትሔ እስኪገኝለት ድረስ ጉዳዩ እንዲበርድ ማድረግ ይቻላል።  የህወሃት መቃብር የተቆፈረው  በመቀሌ ሳይሆን በወልቃይት እንደመሆኑ መጠን ከሁኔታው አንገብጋቢነት አንጻር  ይህ የምናወራው  ኦፕሬሽን  ባስቸኳይ መፈጸም ያለበት  በዚህ መልኩ ከሆነ ፍጹም አመርቂ የሆነ ግን ደግሞ ያለተባነነበት ሁኔታውን ያገናዘበ ኦፕሬሽን ተካሔደ ማለት ነው።
አሁንም ቢሆን  ግጭቱ በዋነኝነት በሙስሊምና  ክርስቲያኖች፣ በክርስቲያኖችና ፕሮቴስታንቶች፣ በሙስሊልምና ፕሮቴስታንቶች  እንዲሁም  በተለያዩ ብሔረስቦች መካከል ባስቸኳይ እውን መሆን አለበት። ከብሔር አንጻር  ሲታይም ግጭቱ በኦሮሞዎችና በአማሮች፤ በኦሮሞዎችና በሶማሊዎች፣ በሶማሊዎችና አፋሮች፣ በአፋሮችና የጁቡቲ ድንበር አፋሮች፣በጋምቤላና በደቡብ ሱዳን ድንበርተኞች፣ በኦሮሞዎችና ደቡቦች እንዲሁም በእነዚህ የተጠቀሱ አካባቢ ህዝቦች በውስጣቸው በተለያየ መንገድ መከፋፈልና ግጭት በሰፊው እንዲከሰት በማድረግ ጣታቸውን ከመንግስት ቅሰራ እንዲቆረጡ በማድረግ መንግስትን  ለአስታራቂነት እንዲለምኑ መደረግ አለበት። ስብሰባው ሊያልቅ ወደ 40 ደቂቃ ገደማ ሲቀረው አቶ አባይ ጸሐየ በስልክ ደዉለው በማይክሮፎፎን ላውድ ተደርጎ እጅግ በጣም በተበሳጨ ስሜት ሆኖ በቀጥታ በስልክ በተላለፈው ቀጭን ትእዛዛቸው ‘ስትነጋገሩበት የቆያችሁ አገራዊ አጀንዳ በውስጥ መስመር ሲደርሰኝ ነበር’ ካሉ ብሗላ ‘አንዳንድ ማጉረምረም በሚሰማባቸው የትግራይ አካባቢዎች ቢሆንም እንኳ ኦፕሬሽኑ ካስፈለገ ተግባራዊ ይደረግ’ ከእንግዲህ ወደሗላ ማለት የለም” ካሉ ብሗላ ሁለት ካድሬዎች በፍጥነት ሲያጨበጭቡ ሌላውም በፍርሃት እየተያየ ደማቅ ጭብጨባ አሰምቷል” ተብሏል።
በአሁኑ ስአት ስለብሔርና ስለሐይማኖት ልዩነት የሚያወሩ ሰዎች የወያኔ ካድሬ አለያም ደግሞ ወያኔ ባይሆኑም በስራቸው ተባባሪዎችመሆናቸውን አውቃችሁ እንደትጠነቀቁ በማሳሰብ አስፈላጊውን ኢትዮጵያዊ መልስ እንድተሰጧቸው አሳስባለው። በተባበረው ክንዳችን ወያኔን በፍጥነት እናስወግድ!!! ይህ ሲባል ታድያ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ስለብሔሩ ችግር አያውራ ወይንም ደግሞ አይደራጅ ማለት አይደለም። ነገር ግን ብሔርነታችን ለኢትዮጵያዊነታችን ዋስትና ሊሆነው ይገባል፤ ኢትዮጵያዊነታችንም ለብሔራችን ዋስትና ሊሆነው እስከቻለ ድረስ። ከዚህ ውጭ ግን ኢትዮጵያውያን ሆነን በሃይማኖትና በብሔር ያተኮረ ስድብና የፈጠራ ታሪክ  ነገር ሁሉ መጥፊያችን ነው። ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችሁ ጋር ይሁን።


ግልጽ ደብዳቤ – ይድረስ ለቴሌና ለመብራት ኃይል (ነፃነት ዘለቀ (አዲስ አበባ)

ራሷ ሄዳ ጅብ-አይበላሽን የከለከሏት ‹ምላስ ሰምበር (በሰው) ላኩልኝ› አለች” እንደተባለው ባይሆንብኝ እዚሁ አጠገባችን ላሉ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ዘወትር እየጮኽን ያልተሣካልን ብቻ ሣይሆን እንደሕጻናት ተቆጥረን የተሾፈብን አሁን በግልጽ ደብዳቤ ምንም ነገር እንደማላመጣ አውቃለሁ፤ ቢሆንም ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ለአስተምህሮና ለስብከት ሲልክ “የምትሏቸውን ከሰሟችሁ እሰዬው፤ ባይሰሟችሁ ግን ከናንተ ይውጣ ግዴለም፡፡ ከዚያ ዐመፀኛ መንደር ግን የእግራችሁን አቧራ ሣይቀር አራግፋችሁ ምንም ነገር ሳትይዙ በቶሎ ውጡ፡፡ መርገምቱ ለራሳቸው ይሁንላቸው…” እንዳለው እኔም ትንሹ ኃጥዕ ወአባሲ ነፃነት ዘለቀ ይህን የሕዝብ መከራና ሰቆቃ ለሚያነበው ሁሉና ለታሪክ መዝገብ እንደሚከተለው አሳውቃለሁ፤( በነገራችን ላይ እዚች አካባቢ የጠቀስኩትን ክርስቶስ ለሐዋርያቱ የሰጠውን መመሪያ ለኔ በሚስማማ መልክ ለወጥ እንዳደረግሁት መጠቆም ያለብኝ ይመስለኛል፡፡)
ቴሌዎች፡-

Ethiopian Electric Power Corporation

እንደወያኔው መንግሥታችን ሁሉ እኛን ሕዝቡን የቴሌው መሥሪያ ቤት ክፉኛ ይንቀናል፡፡ የቆመበት መሠረት እኛ መሆናችንን ረስቷል፡፡ ወታደሩም፣ ፖሊሱም፣ የፀጥታና አስተዳደር ሠራተኛውም እኛ በምንከፍለው ግብርና ቀረጥ መኖሩን አያውቅም፡፡ በተለይ በዚህ ዘመን አብዛኛው የመንግሥት ተቀጣሪ የኑሮው መደላድል ሕዝብ መሆኑን የዘነጋ ይመስላል፡፡ ለነገሩ ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ማን ሊያከብረው ይችላል?
እናም ዐይንና ጆሮው የተደፈነበት የቴሌው መ/ቤት በብዙ መንገድ እየበደለን ነው፡፡
አንደኛ ከየትኛውም የዓለም ሀገር ጋር ፍጹም በማይወዳደር ከፍተኛ የተንቀሳቃሽና የቋሚ ስልክ ታሪፍ ገንዘባችንን ይዘርፋል፡፡ በኢትዮጵያ እንዳለው ያለ የቴሌና የመብራት ኃይል ዘረፋ በየትም ሀገር የለም ይባላል፡፡ አንዱ ምሥክር ዓመታዊ ወይ ወቅታዊ ትርፋቸውን ሲያሳውቁ የሚናገሩት የብር መጠን ቁጥር እስከማወቃቸው የሚያጠራጥር ነው፡፡ እንደገናም “ይህን ያህል መቶ ሚሊዮን በሩብ ዓመት አተረፍን” ሲሉ በጭራሽ አያፍሩም – “ዘረፍን! የሕዝቡን ማጅራት መታን!” ነበር ማለት የሚገባቸው፡፡ ቴሌ ነፋስ ነው የሚሸጠው – ያውም እጅግ በተጋነነ ውድ ዋጋ፤ ያ ካሡ ኢላላ የሚሉት አጋሰስ የወያኔ አሽከር ቴሌን በጥገት ላም የመሰለውም ለዚህ ነው – ቴሌ ንጹሕ አየር እየሸጠ በልቶ ለማይጠረቃው የወያኔ ቀዳዳ ካዝና ትልቅ ገቢ ስለሚያስገባ ነው ቴሌን በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ ለማንም እንደማይሰጡ ሲያብራራ እንዲያ ያለው፡፡ “ጊሎቲኖቹ” ቴሌዎች የ50 ብር ካርድ ወደስልክህ ከመጨመርህ በየሰበቡ ሲገመድሉልህ በደቂቃዎች ውስጥ ያልቃል – በውነቱ ኢትዮጵያ ውስጥ በሞባይል ስልክ ደውሎ መነጋገር በእሳት ላይ እንደመረማመድ ያህል ነው፤ አንዳንድ ሰው ስልክ እየተነጋገረ ባለበት ቅጽበት ቴሌ በየደቂቃና ሴከንዱ የሚቆነድደውን ገንዘብ ስለሚያስብ ከደወለለት ሰው ጋር በከንቱ ከመደነቋቆር ባለፈ በቅጡ አይግባባም  – ክፍያው አስደንጋጭ ነው፡፡ እኔንም እንዲህ ያለ ሁኔታ ይገጥመኛል፤ ስለምቸኩል ሳልግባባ ተደነቋቁሬ ስልኬን የምዘጋበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡
በዚያን ሰሞን ሳልጠቀምበት – አለመጠቀሜንም በማስረጃ አቅርቤ – 30 ብር ከምናምን ሣንቲም ተቆርጦብኛል፤ የተሰጠኝ መልስ ግን “በዚህ ስልክ ለሦስት ደቂቃ ውጭ ሀገር እንደተደወለበት ኮምፒውተሩ ያሳያል” የሚል ነው፡፡ ተደወለበት በተባለበት ወቅት ለሥራ መስክ ወጥቼ እልም ያለ ገጠር ውስጥ ነበርኩ – በዚያ ላይ ውጭ ሀገር ከተዛዋሪ ስልክ ውጪ እኔ የምደውልበት አቅም የለኝምና በጭራሽ ደውዬ አላውቅም – ክርስቶስ ምሥክሬ ነው፡፡ ታዲያ ኮምፒውተሩ ያን የሀሰት መረጃ ከየትአባቱ አመጣው?  ይህን ነጥብ ከዋጋው አጠቃላይ ውድነት ጋር አጣምራችሁ አንድ በሉልኝ እንግዲህ፡፡
ሁለተኛ የማንፈልገውን አጭር የጽሑፍ መልእክት በግድ ይልክብናል፡፡ የዜጎች መብት እንደኢትዮጵያ የሚጣስበት ሌላ ሀገር ካለ ይገርመኛል – ምናልባት ከሰሜን ኮሪያ በስተቀር፡፡ ቀኑን ሙሉ በሚሰዱልህ መልእክት ስልክህን ሲያስጨንቁትና አሥሬ ሲያንጫርሩት ይውላሉ፡፡ ሰዎች ሄደው ስለዚህ ጉዳይ ቢጠይቋቸው “ከፈለጋችሁ ሲሙን አውጡ እንጂ እኛ ውል የገባንበት ስለሆነ ላኩ ስንባል እንልካለን” ነው ያሉት – በሚያስደንቅ ትዕቢት፡፡ ምን ዓይነት ትምክህታዊ አስተዳደር ነው? እኔ ካልፈለግሁ እንዴት ነው ላቤን ጠብ አድርጌ በገዛሁት የግል ስልኬ ያዳሜ ኮተት የሚላክብኝ? ቲቪውን መዝጋት ስለምንችል የማንንም ቅርሻት አንጋትም – ግልግል፤ ኢቲቪም ሆነ ኢቢሲ ያው መለያው ውሸት ነው – አንዲት የቀረቻቸውን እውነትም – ሰዓትን በትክክል መናገሩን – ትተዋት በተበላሸ ሰዓት እየቆጠሩ የዜና ዕወጃ ጊዜን ስለሚያዛንፉ መድሓኒት ወሳጆችንና ጸሎተኞችን ማደናገርና ማሳሳት ጀምረዋል አሉ፡፡ ይህኛውን የቴሌን ዕብሪት ግን ምን እናድርገው?  የኔን ስልክ አሁን ባነብላችሁ ጉድ ትላላችሁ፡፡ በየሰዓቱ እየላኩ በአሰስ ገሰስ ስልኬን እንዳለ አጭቀውታል፡፡ ጥቂቶቹን መልእክት መላኪያ ቁጥሮች ልንገራችሁማ ፡- 8100፣ 8400፣824፣8852፣ 8851፣ 251994፣ +251994፣ 994፣ Red Cross, ethio tel,፣ ብርሃኑ ዘገዬ (አይ፣ ይሄኛውስ የጓደኛየ ነው ተውት) … ብቻ ማንም የፈለገ ነጋዴም ይሁን የመንግሥት መሥሪያ ቤትና ባለሥልጣን በነሸጠው ቁጥር ይነሣና ከቴሌ ጋር በመሻረክ ዘባዘቦ ማስታወቂያውን ይልክብሃል፡፡ ስልክህ ምርጫ የለውምና ካልዘጋኸው ወይ ድምጹን ካላጠፋኸው በስተቀር ይረብሽሃል – ይህ ሰውን የመናቅ ጠባይ ትልቅ ነውር ይመስለኛል፤ የአክሲዮንና መሰል የስብሰባና ጉባኤ ጥሪዎች ለአባላት በዚህ መልክ መነገሩ ዘመናዊነት ነውና – ጥሩ ነው፡፡ ባልተገባ አኳኋን ሁሉን ዜጋ በማይመለከተው መልእክት ማስጨነቅ ግን ወንጀል ነው፡፡ እንዲህ ያለ ብልግናና ጥጋብ በሌሎች ሀገራት ይኖር ይሆን?  እስኪ ንገሩን፡፡
በዚያ ላይ ቫት ያስከፍላሉ፡፡ ለወሬ ደግሞ ቫት ለምን ይከፈላል?(እነዚህ መሥሪያ ቤቶች ዋና የሙስና ማዕከላት ስለመሆናቸው፣ በውጪ ሀገራት የሥራ ዘመናቸውን ጨርሰው አርጅተው በተቀየሩ ውድቅዳቂ ዕቃዎች ኢትዮጵያን የሚያጥለቀልቁ ስለመሆናቸው፣ ለመናኛ ዕቃዎች (ከነሙስናው) ብዙ ብር እያወጡ ዕቃዎቹ ሳይገጠሙ ሣር በቅሎባው እንደሚቀር፣ ቢገጠሙም ወዲያው እየፈነዱ አገልግሎት እንደማይሰጡ… አሁን ጊዜ ስለሌለን ሌላ ቦታ አንብቡ፡፡)
መብራት ኃይል፡-
ከቴሌና ጅምሩክ ቀጥሎ አንዱ የወያኔ ጅብ ይህ መሥሪያ ቤት ነው፡፡ ብቸኛ ሥራው ገፈፋ ነው – ቆዳህን ከነአጥንትና ሥጋህ ነው የሚገፍህ ደግሞ፤ ርህራሄ የሚባል የላቸውም፡፡ እኛ ዜጎች ከጨረቃ ወይ ከማርስ የመጣን ሳንመስላቸው አንቀርም፡፡ ይህን ምሥኪን ሕዝብ ከቴሌ ጋር ተባብረው ይግጡታል፡፡ እንደመስቀል ወፍ ሲያሰኘው የሚመጣውን መብራት ለማስገባት ያለው ውጣ ውረድ እንዳለ ሆኖ ክፍያው ደግሞ ስትሰማው ገና ለጆሮም ይሰቀጥጣል፡፡ ባለፈው ተጨማሪ ቆጣሪ ፈልጌ ሄድኩና ስጠይቅ 16 ሺህ ብር ወዲህ በል አለኝ፡፡ “እኔ እኮ የጠየቅኋችሁ ለመንደሩ በሙሉ አይደለም፡፡ የመንደሬ ነዋሪዎችማ ሁሉም መብራት አስገብተዋል፡፡ ለኔ ብቻ ነው – ሊያውም ሁለተኛ ቀጣሪ ስላስፈለገኝ ነው፡፡ ምሰሦ አያስፈልግም፤ ገመድም በጣም አጭር ነው የሚያስፈልገው” አልኳቸው፡፡ እነሱ ግን ሣቁብኝ፡፡ “ተጨማሪ ቆጣሪ የሚፈልግ ሰው የሚከፍለው  ሒሳብ ይህን ነው፤ ደምብ ደምብ ነው፣ መመሪያም መመሪያ ነው” አሉና – እንደኢንጂነር ባንጃው – ከቢሯቸው እንድወጣላቸው ገላመጡኝ፤ ሀገርህ ሰው እንደውሻ የሚታይባት ሆናለች – እንደሰሃራ በታች ውሻ ማለቴ እንጂ የአውሮፓውማ በፊልም እንደምናየው ከሆነ ከሰው እኩል ጠረጴዛ ላይ ቂብ ብሎ ምግቡን ይበላ የለም?  አሁንስ ሳስበው የወረደብን እርግማን ለከት አጣ፡፡ መንግሥት የሚሉት የዱርዬዎች ጥርቃሞ አያከብረንም፤ የርሱው ቅጥር ሠራተኞችም እሱን እያዩ ከርሱው ባልተናነሰ ሁኔታ ያዋርዱናል፡፡ ምን ይዋጠን? እንዴ፣ ዙሪያ ገባው ጨለማ ሆነ እኮ!  የሕዝብን የልብ ትርታ የሚያዳምጥ እንዴት አንድ ተቋምና  አንድ ሠራተኛ እንኳን ይጥፋ?  እንዴት ነው ሁሉም ተያይዞ ድንጋይ ልብ የሆነው? እንዴት ያለ ንፋስ ቢነፍስብን ነው ሁሉም በጥቅም ተሳስሮ የጥፋት ሠራዊት አባል ሊሆን የቻለው? ይህ ሁሉ ውርጅብኝ በዚህች ሀገር ላይ የወረደው ፈጣሪዋን ምን በድላ ይሆን?
ዱሮ በ90 ብር የሚገባ አዲስ መብራት ዛሬ ከ6 ሺህ በላይ ነው፡፡ ይህ ዕድገትን ነው ወይንስ ከፍ ሲል እንዳልኩት ከቁጥር ዕውቀት ነፃ መሆንን የሚያመለክት የድንቁርና ውጤት ነው? በየቦታው ሂዳችሁ ስለዕቃና አገልግሎት ክፍያ ስትጠይቁ የምትሰሙት የገንዘብ መጠን የማይታመን ነው – የአብዛኛውን ዜጋ የገቢ መጠንና የኑሮ ዘይቤ ግምት ውስጥ ያላስገባ አሠራር ተዘርግቶ ሕዝብ በሁሉም አቅጣጫ እየተገረፈና ምርጫም በማጣቱ ወደላይ ወደፈጣሪ እያለቀሰ ነው – እግዜሩስ እንዲህ እንደጨከነ ይቀር ይሆን? ዕድሜ የሰጠው መጨረሻውን ያየዋል፡፡ የአብዛኛውን ዜጋ የወር ደሞዝ ስትመለከቱ ከጥንቱ ብዙም ፈቀቅ አላለም – ሌብነትና ውንብድና የተስፋፋውም መደበኛ ገቢ ከኑሮ ጋር ባለመጣጣሙ ምክንያት ነው – ለምሣሌ አንድ የት/ቤት ዘበኛ አምፖል አውልቆ ቢሸጥ፣ ጽዳቷ ባልዲና መጥረጊያ አውጥታ በመሸጥ ለሣሙና መግዣ ብታውለው ማን ምን ሊፈርድባቸው ይችላል? መንግሥት ሌባ፣ የሃይማኖት መሪው ሌባ፣ ፖሊሱ ሌባ፣ ዳኛው ሌባ …ከሞላ ጎደል ሁሉም ሌባና ቀማኛ የሆነበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነው ያለ፡፡ ደግሞም “መልካም አስተዳደር እናሠፍናለን!” ይባልልኛል፡፡ መልካም አስተዳደር በምኞት ይሠፍናል እንዴ? ከግርጌ እስከራስጌ በሙስናና በንቅዘት በገማ ሥርዓት ውስጥ ማን ከማን ተሸሎስ ነው በሙስና ምክንያት አንዱ አሣሪ ሌላው ታሣሪ የሚሆነው?? ወግ ነው አሉ ሲዳሩ ማልቀስ! ኢትዮጵያ ውስጥ ሙስና ብትሞት አንድም ባለሥልጣን አይተርፍመ – ሁሉም እስትንፋሱ ይዘጋል፡፡ ለመሆኑ ባለሥልጣኖቻችን ደሞዛቸውን ያውቁታል? ለይምሰል ያህል በገንዘብ ከፋዮችና በጓደኞቻቸው ተለምነውና ተንቀባርረው ይቀበሉታል እንጂ ለጫማ ማስጠረጊያ እንኳን የማይበቃቸውን ያን ደመወዝ ተብዬ ከነመጠኑ ጭምር ያውቁታል ብዬ አልገምትም፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ሁሉም ነገር ዕንቆቅልሽ ነው፡፡ ሀገሪቱ ግን አድጋለች እየተባለ ነው የሚወራው፤ ታዲያ ያደገው ማን ነው?  በዚህች ሀገር ውስጥ ስንት ዓይነት ዜጋስ አለ? ተራው ዜጋ የት ይሂድ?  በሙስናም ይሁን በድጎማ ተጨማሪ ገንዘብ ለማያገኘው ለመምህሩ፣ ለዘበኛው፣ ለጽዳቱ፣ ለወታደሩ፣ ለቢሮ ሠራተኛው፣ ለወዛደሩ፣ ለገበሬው፣ ለሥራ አጡ፣ ለጡረተኛው፣ ለተማሪው፣… ማን ይድረስለት? ሀገራችን ውስጥ ምን እየሆነ፣ ምንስ እየተካሄደ ነው ያለው? ወገኖቼ እስኪ ቆም ብለን እናስበው፡፡ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ያላችሁ የሥራ ኃላፊዎችም ቆም ብላችሁ “ሕዝባችሁ”ን አስቡት፡፡ ሕዝቡ በየቢሮክራሲው በተሰገሰጉ ደንታቢስ ትኋኖችና ተምቾች እስከመቅኒው ድረስ በሚዘልቅ ጭካኔ ያለችውን አነስተኛ ጥሪት እንዴት እየተገሸለጠ እንደሆነ ይታያችሁ – እናንተም ራሩለትና ፋታ የሚያገኝበትን ሁኔታ ፍጠሩለት፡፡ ነገሩ ሁሉ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ሆኗል፡፡ የተናጠል ሩጫ ገኗል፤ የዚህ ሁሉ መጨረሻ ግን በርግጠኝነት አያምርም፡፡ ሊቢያና ሦርያ ውስጥ የተከፈተችው የ“ፓንዶራ ሣጥን”(Pandora’s Box) ለ42 ዓመታት ግድም እንደሽሮ ስትንተከተክ ከቆየች በኋላ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ አሁን ሕዝቡ ምርር ብሎናል፤ ቀጭን ሰበብ ነው የምንፈልገው፡፡ እኔ ራሴ ምርርርር… ብሎኛል – ደፍርሶ ይጥራ የምልበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነው ያለ – ያልተፈጠረ ሁኔታ የለም ወገኖቼ፡፡ ሰሞኑን ብታዩኝ ሲናገሩኝ በቀላሉ ሆደ በሻ እየሆንኩ ሰውን ተማታ ተማታ የሚለኝ መጥፎ መንፈስ ተፈጥሮ ያለበት ሁኔታ ላይ ነው የምገኘው – ይቺ የወያኔ አማርኛ አበላሸችኝ መሰለኝ ጎበዝ፤ “ካለበት የተጋባበት”ይባል የለም?  ለማንኛውም ሁሉም ሰው ሆድ ብሶታል፤ ሁሉም መነጫነጭ ይዟል፡፡ የኔን በተመለከተ ግን ለጊዜው  ከባለቤቴ ከማንጠግቦሽ ውጪ የማሸንፈው አጥቼ ተቸገርኩ እንጂ ደፋር ተነስቶ ና ተከተለኝ ቢለኝ ቢያንስ በመጮህ ለመተባበር ዝግጁ ነኝ – ኢያሪኮም የጠፋችው በመጮህ ነው ይባላልና ጩኸቴን አሳንሳችሁ እንዳትገምቱት ታዲያ፡፡ … በቃኝ ወንድሜ፤ ሀበሻ በያለህበት ደኅና ዋልልኝ ወይም እደርልኝ፡፡
ደኅናውን ቀን ያምጣልን፤ አሜን፡፡

Saturday, April 16, 2016

ጋምቤላ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ140 በላይ ሰዎች ማንነታቸው ባልታወቀ ታጣቂዎች ተገደሉ።



ጋምቤላ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ140 በላይ ሰዎች ዐርብ ሚያዝያ 7 ቀን፣ 2008 ዓ.ም. ማንነታቸው ባልታወቀ ታጣቂዎች ተገደሉ።
የኑዌር ጎሳ አባላት የመኖሪያ መንደሮች ላይ ባነጣጠረው ጥቃት የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ከ221 በላይ መሆኑን ሱዳን ትሪቡዩን ዘግቧል።
ሱዳን ትሪቢዩን የደቡብ ሱዳን ጦር መለዮ የለበሱ እና የታጠቁ በሺዎች የሚቆጠሩ የተደራጁ ታጣቂዎች የኢትዮጵያን ድንበር በማቋረጥ በዐሥር መንደሮች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ዘግቧል። ጥቃት ፈጻሚዎቹ በደቡብ ሱዳን የቡማ ወይም ጆንጊሌ ግዛት የሚገኙት የሙርሌ ጎሳ አባላት መሆናቸውንም አትቷል።
በጥቃቱ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር 221 መድረሱን የዘገበው ሱዳን ትሪቢዩን 170 የኔዌር ጎሳ አባላት እና 51 የሙርሌ ጎሳ አባላት መገደላቸውን አትቷል።
ለኢትዮጵያ መንግስት ቅርበት ያላቸው መገናኛ ብዙሃን የታጣቂዎቹ ማንነት እንደማይታወቅ እና «መከላከያ ሰራዊት ጭፍጨፋውን የፈጸመው ቡድን ላይ ተከታትሎ አርምጃ እየወሰደ መሆኑን ዘግበዋል።

“የአቶ አባይ ወልዱን የእርስ በእርስ ጦርነት አዋጅና በጎንደር ሕዝብ ላይ የተቃጣውን ጥቃት እንጋፈጣለን” | የጎንደር ሕብረት ማሳሰቢያ




abay weldu 2

የትግራይ ነጻ አዉጭ ግንባር ብሎ እራሱን የሚጠራዉ ድርጅት መሪ አቶ አባ ወልዱ እና የክልሉ የፀጥታና የአስተዳደር ኃላፊ አቶ ሐድስ ዘነበ ከዘራፊ ካድሬወቻቸው ጋር በመሰባሰብ፤ በወልቃይት፤ በጠገዴ እና በጠለምት ህዝብ ላይ የማያዳግም ጦርነት ለማካሄድ የጦር ነጋሪት እየደለቁ በማስፈራራት ላይ ይገኛሉ። ጦርነቱን በሚፈልጉት መንገድ በድል ለመወጣት እየተጠቀሙበት ያለው የሞራል መምቻ ደግሞ፤ ህብረተሰቡን፤ በገብያ፤ በቤተክርስቲያን እና ቤት ለቤት በማደን እያስፈራሩ ወደፖሊስ ጣቢ እየወሰዱ፤ ወልቃይት የትግራይ ክልል እንደሆነች እንድትቀጥል እንደሚፈልጉ በማሥመሰል በማሥገደድ እያስፈረሙ ናቸው።

ሌላ የዚህ ሳምንት አስገራሚዉ የወያኔ ቲያትር ደግሞ፤ ከስህተት ላይ ሥተት በመደራረብ ህዝብና ህዝብን ለማጋጨት የትግራይ ተወላጆችን ስልፍ አሰልፎ በጉልበት ይዞት የቆየዉን መሬት የትግራ ነዉ እያለ ማስጨፈሩ ነዉ። ወያኔ በመላዉ ኢትዮጵያ ሰልፍ ከልክሎ ሰላማዊ ሰልፈኞችን በታንክና መትረየስ እዬጨፈጨፈ፤ ጎንድር መሪ የሌለዉ መሆኑን የተረዳዉ ወያኔ ወገራ አዉራጃ ላይ የትግራይ ተወላጆችን ከጎንደር ህዝብ ጋር ቂም ለመትከል የዉሸት ሰልፉን አቀነባብሮ ያስጨፍራል። የተቃዉሞ ስሜትን በአደባባይ መግለጽ ከሆነማ ይህ አይነቱ ወልቃይት ጠገዴ እና ጠለምት ብሎም ለመላዉ ጎንደር/ አማራ ህዝብ መፈቀድ የግድ ይላል።
ጦረኛ ቡድን በአሁኑ ሰዓት ሌላ ወንጀል እና ደባ ከመፈጸም ይልቅ፤ መደረግ የነበረበት፤ የወልቃይት፤ የጠገዴ እና የጠለምትን ህዝብ ባለፉት 25 ዓመታት በተፈጸመበት ግፍና በደል ይቅርታ መጠየቅ ነበር እንጂ አድሮ ጥጃ የሆነዉ የትግራይ ነፃ አዉጭ ግንባር የአማራን መሬት በሰፊዉ ለመቆጣጠር የጦርነት ክተት አዋጅ ነጋሪት መደለቅ እና በቴለቭዥን መስኮት ውሸት መርጨት አልነበረበትም። ይህ ድርጊት ታሪክ ይቅር የማይለው አሳዛኝ ተግባር ነው። ለዚህ ሰይጣናዊ ስራው የሚገጥመዉ ምላሽም በጣም የከፋ ሊሆን ስለሚችል ለጥፋት ብቻ ትግራይ መሬት ላይ የተቀመጠዉ አቶ አባይ ወልዱ በጊዜው የያዘውን ሥልጣን እና ያስታጠቀውን ሚሊሺያ ሌላ ሊበግረው የሚችል ሃይል መሥሎት በትቢት ወይም በድንቁርና ከአንድ ጥፋት ወደ ሌላ ጥፋት መሸጋገሩ ትልቅ አደጋ ነዉ። በመላው አገሪቱ በዜግነታቸው ኮርተው፤ የሚኖሩበትን ህብረተሰብ አምነው እና ተዋደው የሚኖሩትን የትግራይ ተወላጆች በወልቃይት ጠገዴ የግፍ እሳት ላለማቃጠል ቆም ብሎ እንዲያስብ እጅግ እናሳስባለን።
ላለፉት 30 ዓመታት የቃፍቲያ ሁመራ፤ ወልቃይት ጠገዴ/ጠለምት ህዝብ የአማራ ምንነቱን ተነጥቆ፤ አማራም ጎንደሬም አይደለህም ተብሎ፤ የዘር ማጽዳት ድርጊት ተፈጽሞበታል። ለዘመናት ከኖረበት መሬት ተፈናቅሎ ብዙ ትዉልድ ለስደት ተዳርጓል። ላለመሰደድ በቀየው መሞትን የመረጠ ተወላጅ፤ እጣ ፈንታው ለዘመናት ፀሐይን እንዳያይ ተወስኖበት እስር የሚማቅቀዉን ብዛት፤ የትግራ እስር ቤቶች ይቁጥሩት። በጀምላ የተቀበረዉን ደግሞ፤ ጊዜ እያወጣዉ ነዉ፤ ክቡር ገረመድን አራያ ይናገራሉ።
የዚህን አካባቢ ህዝብ ከገደለ እና ካፈናቀለ በኋላ፤ ብዛት ያላቸውን የትግራይ ተወላጅ የወያኔ ደጋፊዎቹን ተከዜን አሻግሮ አስፍሯል። በአሁኑ ሰዓት ደግሞ ይህን ሁሉ ግፍ እና በደል ከፈጸመ በኃላ፤ በአካባቢው ለህዝበ ውሳኔ ለማቅረብ የማጥቂያ ስልት ነድፎ ተነስቷል። በቂ የወልቃይት ተወላጆች የሉምና እኔ ያሰፈርኳቸውና አንዳንድ ሆዳሞች በድምጽ ብልጫ ለኔ ድምጽ ሊሰጡ ይችላሉ ብሎ በማመን፤ የዘወትር ዉሸትና ብልጥነቱን በማጠናከር እራሱ ፌደራል ብሎ በሰየመዉ ምክር ቤት ህዝቡ ተጠይቆ ምክር ቤት ይወስናል የሚል አጀንዳ ይዞ ብቅ ለማለት እየተዘጋጀ ነዉ። ከአሁን በኋላ፤ የወልቃይት አማራም፤ ጎንደሬም የመሆን ውሳኔ የሚጸናው፤ በወልቃይት መሬት በሰፈሩ ተከዜ ተሻጋሪ የትግራይ ተወላጆች ሳይሆን፤ የመላው ጎንደር ሕዝብ ውሳኔ ነው።

ይህ የማንነት ውሳኔ ደግሞ፤ በወያኔ መሪዎች በነ አባይ ወልዱ ችሮታ የሚለገስ ሳይሆን፤ በቆራጥነት፤ እነሱ የረገጡትን ጀግንነታችን አሥመስክረን በምንጎናፀፈው ነፃነት ብቻ ነዉ።። በዚህ መልክ ቆርጠን ስንነሳ ነው፤ የጎንደር ታሪካዊ መሬት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ወደነበረዉ ወደጥንቱ ጎንደር ክፍለ ሃገር በአስቸኳይ ሊመለስ የሚችለው ብሎ የጎንደር ሕብረት አጥብቆ ያምናል። ይህ እንደሚመጣ ወያኔ አስቀድሞ በማወቁ፤ መላ የትግራይን ወንድ ልጅ ከመንግሥት ካዝና እየዘረፈ ሙሉ በሙሉ አስታጥቋል። ይን ለመመከት፤ ካሁን በፊት ደግመን ደጋግመን እንዳስጠነቀቅነው፤ ዛሬም እንዳለፈው፤ ለአቅመ አዳም የደረሰ ጎንደሬ በሙሉ መታጠቅ አለበት። የወልቃይት ጉዳይ፤ ከአዲስ አበባው ማስተር ፕላን በላይ በዜጎች ማንነት ላይ እዬተፈጸመ ያለ አስከፊ በደል ነው። በመሆኑም በቆራጥነት መስዋዕትነትን መክፈል፤ የማንነትም፤ የተወላጅ ባለቤትነትም፤ የዜግነት ግዴታ ነው።
ከዚያም በላይ! በጎንደር ህብረት አቋም እና እምነት ደግሞ፤ ይህ በጎንደር ህዝብ ላይ፤ ብሎም በሰፊዉ አማራ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ የወያኔ ቱባ መሪ አባይ ወልዱ የክተት አዋጅ ወያኔ እራሱን እንደማነቅ ሲሆን፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ አፍኖ የሚመራዉ ስርዓትም የመጨረሻዉ የሞት ጣር እና ኑዛዜ ከመሆን እንደማያልፍ እርግጠኛ ሁነን እንናገራለን። ታላቁን የአማራ እና የትግራይን ህዝብ ለማዳማት በፈጸሙት የአርባ አመታት የጭፈጨፋ እና የጥላቻ ዘመቻ በኪሳራ ስሌት እየገፋ የሁለቱ ማህበረሰብ እስከ አሁኑ ድረስ ችግርም ሆነ ደስታዉን የወያኔን ከፋፋይ መርዝ ተቋቁሞ በጋራ ህይወቱን እየገፋ ይገኛል። ይህ እንዳይደፈረስ ከታሰበ፤ “የትግራይ ህዝብ የጎንደርን መሬት በጉልበት እንድንገዛ ድጋፍ ሰቶናል” እያሉ የሥራዓቱ ሙስና እጃቸዉ የነካ ግለሰቦችን በማናገር በቴሌቢዥን መስኮት የሚያካሂዱት ቅስቀሳ በአስቸኳይ መቆም አለበት።
ሰፊዉ የኢትዮጵያ ህዝብም የአቶ አባይ ወልዱን የእርስ በእርስ ጦርነት አዋጅን በመቃወም በጎንደር ሕዝብ ላይ የተቃጣዉን ጥቃት ለመጋፈጥ አጋርነታችሁን እንድታሳዩ በአክብሮት እንጠይቃለን። እንዲሁም የብሔረ አማራ ዲሞክራሲ ንቅናቄ (ብአዴን)ብሎ የሚጠራዉ፤ የአማራን ህዝ እወክላለሁ የሚለዉ የወያኔ አጋር ድርጅት፤ የወያኔ መጠቀሚያ መሳሪያ የመሆን የባዶ ጨዋታ ዘመን አክትሞ የትግራይ ነጻ አዉጭ ግንባር የሚያካሂደዉን የመስፋፋት ዘመቻ እንቅስቃሴ ህዝቡ ተቃዉሞዉን በመግለጽ ምላሽ ለመስጠት በሚዘጋጅበት ሁኔታ ሁሉ ጣልቃ ገብቶ ተጽዕኖ ከማድረግ እንዲቆጠብ በጥብቅ እናሳስባለን።
በመጨረሻም፤ ከህዝብ አብራክ የወጣዉ ሰራዊትም የአገሩን ዳር ድንበር ከማስከበር ዉጭ የወያኔ ታዛዥ ሁኖ በዘረኛ መንግስት የተበደለ ወገኑን ተኩሶ ከመግድል እንዲቆጠብ እናሳስባለን።፤ በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን አረመኒያዊ የግፍ ሥራዓት ሊሸከም ባለመቻሉ፤ በእምቢተኝነት እየተነሳሳ ያለውን ወገንህን፤ በተለይም በሽዋ፤ በወለጋ፤ በአርሲ፤ በሃረር በጋምቤላ፤ የሚያካሄደዉን ጭፍጨፋ በአስቸኳይ እንዲቆም ወገናዊ ጥሪያችን እናስተላልፋለን። እንዲሁም፤ የወያኔ መንግስትም ብዙ ደም ሳይፈስ ስልጣን ለቆ አገሪቱን የሚያድን፤ ህዝቡን የሚያረጋጋ፤ ሁሉን ያካተተ በሕዝብ የተመረጥ መንግስት በአስቸኳይ እንዲቋቋም በጥብቅ እናሳስባለን።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

Friday, April 15, 2016

በአንድ ግዜ ብዛት ያላቸውን ኢሜይሎች መላክ በኢትዮጵያ ወንጀል ሆኖ ሊመዘገብ ነው


email

(ሳተናው) ባሳለፍነው ማክሰኞ ሚያዚያ 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ለፓርላማው የቀረበው ባለ 53 ገጹ የኮምፒዩተር ወንጀል ረቂቅ አዋጅ ማብራሪያ እንደሚያስረዳው፣ ብዛት ያላቸውን ኢሜይሎች በአንድ ጊዜ ለአንድ ሰውም ይሁን ለብዙዎች የኢሜይል ተጠቃሚዎች መላክ በወንጀል የሚያስጠይቅ በመሆን ለቅጣት ይዳርጋል  ፡፡
በሰዎች የነፃነትና ክብር ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች በሚል ንዑስ ርዕስ በአንቀጽ 13 ላይ የኮምፒዩተር ሥርዓትን በመጠቀም በሚሠራጭ ጽሑፍ፣ ንግግር፣ ቪዲዮ ወይም ሥዕል አማካይነት በሌላ ሰው ወይም በተጐጂው ቤተሰቦች ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ ያስፈራራ ወይም የዛተ ከሦስት እስከ አምስት ዓመት ጽኑ እስራት ያስቀጣል፡፡
በሕዝብ ደኅንነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች በሚለው በረቂቁ አንቀጽ 14 ላይ፣ ‹‹ማንኛውም ሰው በኅብረተሰቡ መካከል የፍርኃት ስሜት፣ አመፅ፣ ሁከት፣ ወይም ግጭት እንዲፈጠር የሚያነሳሳ ጽሑፍ፣ ተንቀሳቃሽ ምሥል፣ ድምፅ ወይም ማንኛውም ሌላ ምሥል በኮምፒዩተር ሥርዓት አማካይነት ያሠራጨ እንደሆነ ከሦስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራት ያስቀጣል፤›› ይላል፡፡
የ‹ስፓም› (የተቀባዩን ፈቃደኝነት ሳይጠይቁ ተደጋጋሚ ኢሜይሎችን መላክ) መልዕክቶችን ስለማሠራጨት በሚለው የረቂቁ አንቀጽ 15 ድንጋጌ መሠረት ማንኛውም ሰው ምርትን ወይም አገልግሎትን ለማስተዋወቅ ወይም ለሽያጭ ለማቅረብ፣ መልዕክቶችን በአንድ ጊዜ ወደ በርካታ ኢሜል አድራሻዎች ያሠራጨ እንደሆነ ከሦስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት መቀጮ ያስቀጣል፡፡ ወንጀሉ ከባድ በሆነ ጊዜ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራትና ከ50,000 ብር በማይበልጥ መቀጮ ያስቀጣል፡፡ ረቂቁን የተመለከተው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለዝርዝር ዕይታ ለሕግና ፍትሕ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል፡፡
የስፓም መልእክቶችን በተመለከተ የተለያዩ አገራት የተለያዩ የቁጥጥር አዋጆችን ያወጡ ሲሆን እንግሊዝ የገንዘብ ቅጣት በመጣል መልእክቶቹን ለመቆጣጠር ስትሞክር ጣልያን ደግሞ የሶስት አመት እስራት እንደምትፈርድ አስታውቃለች፡፡የስፓም መልእክቶች በአብዛኛው ንግድን ለማስተዋወቅና ህገ ወጥ ፊልሞችን ፣እንደ ቪያግራ ያሉ መድኃኒቶችን ለመሸጥ የሚቀሰቅሱ መሆናቸውን ብዘዎች ይገልጻሉ፡፡