Sunday, April 17, 2016

ከኢሳት ሬዲዮና ቴሌቪዥን የተሰጠ የሀዘን መግለጫ


“ጋምቤላ” የሚለውን ስም ካወቅነው ድፍን ሃያ ስምንት ዓመታት ሆኖታል፡፡ ከስሙ ጋር የተዋወቅንበት አጋጣሚ ደግሞ የሚረሳ አይደለም፡፡ እንዲህ ነው!!
የአራተኛ ክፍል የህብረተሰብ ትምህርትን ታስተውሱታላችሁ… አዎን! ህብረተሰብ በፍቅር ከምንማራቸው ጥቂት የትምህርት ዓይነቶች አንዱ ነው፡፡ ትምህርቱ “ህብረተሰብ” ቢባልም ጂኦግራፊን፣ ታሪክንና ሶስዮሎጂን የሚያካትት ዓይነት ነበር፡፡ የመማሪያ መጽሐፋችን በጣም ግሩም ነበር፡፡ ከርሱ በተጨማሪ በሬድዮ የሚሰጠው የአንድ ፔሬድ (ክፍለ ጊዜ) የማጠናከሪያ ትምህርት በመጽሐፉ የሌሉ በርካታ ቁም ነገሮችን የሚያስጨብጥ ነበር፡፡


Gambella4

ታዲያ በገጠር የምትኖር አያቴ ሞታ ለሀዘኗ ስል ለአንድ ሳምንት ከክፍል ጠፋሁ፡፡ ሀዘኑ ተጠናቆ ወደ ከተማ በተመለከስኩበት በሁለተኛው ቀን የህብረተሰብ ትምህርት አስተማሪያችን የሙከራ ፈተና (“ቴስት” የሚባለው) ሰጠን፡፡ ከአስር ጥያቄዎች ዘጠኙን መለስኩ፡፡ አንደኛው ግን አቃተኝና ባዶውን ተውኩት፡፡ የሚገርመው ነገር አብዛኛው ተማሪ የመለሰው ጥያቄ ነበር የከበደኝ፡፡ እንዲህ ይላል፡፡
“በኢትዮጵያ በዱር አራዊት ሃብቱ አንደኛ የሆነው አውራጃ የትኛው ነው”
አስተማሪያችን (ጸጋ መለሰ ይባላል) ጠራኝና “ሁሉንም መልሰህ ይሄ ጥያቄ ብቻ እንዴት ከበደህ አለኝ” በማለት ጠየቀኝ፡፡ በህብረተሰብ መማሪያ መጽሐፋችን ላይ እንዲህ የሚል መረጃ እንደሌለ ነገርኩት፡፡ “ባለፈው ሳምንት” ትምህርት በሬድዮ አልተከታተልክም” በማለት ጠየቀኝ፡፡ ፈቃድ ወስጄ ገጠር እንደሄድኩ ነገርኩት፡፡ መምህራችን የተሸወድኩበትን ምክንያት አወቀ፡፡ እናም የጥያቄውን መልስ እንዲህ በማለት መለሰልኝ፡፡

“በኢሉባቦር ክፍለ ሀገር ጋምቤላ አውራጃ”
አዎን! “ጋምቤላ” የሚለውን ስም ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት በዚያች አጋጣሚ ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ስለርሱ ክፉና ደጉን እየሰማን እስከ አሁን ድረስ አለን፡፡ በተለይም ስለጋምቤላ ከሚታወሱኝ መካከል በ1981 የጋምቤላ ተወላጅ የሆነው ታዋቂው ጊታሪስ ኩት ኡጁሉ የሚገኝበት የኪነት ቡድን ወደ ከተማችን መምጣቱ (ነዋይ ደበበ፣ ሂሩት በቀለና ሐመልማል አባተም በቡድኑ ውስጥ ነበሩ)፣ በተመሳሳይ ዓመት ጋምቤላ ከኢሉባቦር ስር ወጥቶ ራሱን የቻለ የአስተዳደር አካባቢ መሆኑ እንዲሁም አሜሪካዊው ኮንግረስማን ሚኪ ሌላንድ “ፑኝዶ” በተባለችው የጋምቤላ መንደር የሰፈሩትን የደቡብ ሱዳን ስደተኞችን ለመጎብኘት ሲጓዙ ደብዛቸው መጥፋቱና ከሁለት ወር ፍለጋ በኋላ አውሮፕላናቸው መገኘቷ ወዘተ…. ከማይረሱኝ ጋምቤላ ተኮር የደርግ ዘመን ትዝታዎቼ መካከል ናቸው፡፡
——–
በዘመነ ኢህአዴግ ደግሞ ጋምቤላ ወደ ክልል አደገ፡፡ በዚህ ዘመን በደምብ ከሚታወሱን ትዕይንቶች መካከል ቀዳሚ ሆኖ የሚወሳው በተከታታይ የተሾሙ ሶስት የክልሉ ፕሬዚዳንቶች “ኦኬሎ” የሚል ስም የነበራቸው መሆኑ ነው፡፡ ይህ የስም መመሳሰል ብዙዎችን ሲያነጋግር እንደነበረ አስታውሳለሁ፡፡ ከዚያ በፊት ደግሞ በጋምቤላ በመምህርነት የተመደበው “ቶማስ መንግሥቱ” የተባለ የገለምሶ ተወላጅ የተማሪዎቹን የስም መመሳሰል እንደ ትንግርት ሲያወራ እንደነበረ ከአንድ አጎቴ አንደበት ሰምቻለሁ፡፡

ከዚህ የስም መመሳሰል ጀርባ ያለው ሚስጢር የተገለጸልን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በ1992 በአሶሳ ከተማ አንድ ልዩ ዝግጅት ባቀረበበት ወቅት ነው፡፡ በዝግጅቱ ላይ የተገኙ ሽማግሌዎች የልዩ ልዩ ብሄረሰቦችን የስም አወጣጥ ሲናገሩ የጋምቤላው የአኙዋክ ብሄረሰብ እንደምሳሌ ተጠቃሽ ሆኖ ቀረበ፡፡ ሽማግሌዎቹ እንደተናገሩት በአኙዋክ ብሄረሰብ ደምብ መሠረት የመጀመሪያ ልጅ ምንጊዜም ቢሆን “ኦኬሎ” ተብሎ ነው የሚጠራው፡፡ ሁለተኛ ልጅ ደግሞ “ኡጁሉ” የሚል ስም ይሰጠዋል፡፡ የመጀመሪያ ልጅ ሴት ከሆነች ደግሞ “አሪየት” ተብላ ትጠራለች (ሁለተኛዋ ልጅ የምትጠራበትን ስም ረስቼዋለሁ፤ የምታስታውሱ ንግሩን)፡፡ በዚያው ዓመት አንድ የናሽናል ጂኦግራፊ ጋዜጠኛ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ ዘመን ፎቶዋን አንስቶ በዓለም ላይ ያስተዋወቃት የጋምቤላዋ ኮረዳ ትልቅ ሴት ሆና ለጋዜጣ ኢንተርቪው ቀርባ አንብበናታል፡፡
በዚህ ክልል በጥሩነታቸው ከሚታወሱት ዜናዎች አንዱ ነዳጅ ተገኘ መባሉ ነው፡፡ ነገር ግን ነዳጁ እስከዛሬ ድረስ አልወጣ ብሏል፡፡ ወሬው ብቻ በየጊዜው ይመላለሳል፡፡ ግምባታ ተካሂዷል፣ ዩኒቨርሲቲ ተከፍቷልም ይባላል፡፡ ይሁንና ከክልሉ የሚመነጩት ዜናዎች በአብዛኛው ጥሩ አልነበሩም፡፡ የትናንቱን ዓይነት ልብ ሰባሪ ወሬ ነው በአብዛኛው የምንሰማው፡፡ ጋምቤላዎች ሁሌም ሐዘንተኞች ናቸው፡፡ ያሳዝናል!!
የሞቱትን ነፍስ ይማር!!

No comments:

Post a Comment