Sunday, April 17, 2016

ግልጽ ደብዳቤ – ይድረስ ለቴሌና ለመብራት ኃይል (ነፃነት ዘለቀ (አዲስ አበባ)

ራሷ ሄዳ ጅብ-አይበላሽን የከለከሏት ‹ምላስ ሰምበር (በሰው) ላኩልኝ› አለች” እንደተባለው ባይሆንብኝ እዚሁ አጠገባችን ላሉ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ዘወትር እየጮኽን ያልተሣካልን ብቻ ሣይሆን እንደሕጻናት ተቆጥረን የተሾፈብን አሁን በግልጽ ደብዳቤ ምንም ነገር እንደማላመጣ አውቃለሁ፤ ቢሆንም ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ለአስተምህሮና ለስብከት ሲልክ “የምትሏቸውን ከሰሟችሁ እሰዬው፤ ባይሰሟችሁ ግን ከናንተ ይውጣ ግዴለም፡፡ ከዚያ ዐመፀኛ መንደር ግን የእግራችሁን አቧራ ሣይቀር አራግፋችሁ ምንም ነገር ሳትይዙ በቶሎ ውጡ፡፡ መርገምቱ ለራሳቸው ይሁንላቸው…” እንዳለው እኔም ትንሹ ኃጥዕ ወአባሲ ነፃነት ዘለቀ ይህን የሕዝብ መከራና ሰቆቃ ለሚያነበው ሁሉና ለታሪክ መዝገብ እንደሚከተለው አሳውቃለሁ፤( በነገራችን ላይ እዚች አካባቢ የጠቀስኩትን ክርስቶስ ለሐዋርያቱ የሰጠውን መመሪያ ለኔ በሚስማማ መልክ ለወጥ እንዳደረግሁት መጠቆም ያለብኝ ይመስለኛል፡፡)
ቴሌዎች፡-

Ethiopian Electric Power Corporation

እንደወያኔው መንግሥታችን ሁሉ እኛን ሕዝቡን የቴሌው መሥሪያ ቤት ክፉኛ ይንቀናል፡፡ የቆመበት መሠረት እኛ መሆናችንን ረስቷል፡፡ ወታደሩም፣ ፖሊሱም፣ የፀጥታና አስተዳደር ሠራተኛውም እኛ በምንከፍለው ግብርና ቀረጥ መኖሩን አያውቅም፡፡ በተለይ በዚህ ዘመን አብዛኛው የመንግሥት ተቀጣሪ የኑሮው መደላድል ሕዝብ መሆኑን የዘነጋ ይመስላል፡፡ ለነገሩ ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ማን ሊያከብረው ይችላል?
እናም ዐይንና ጆሮው የተደፈነበት የቴሌው መ/ቤት በብዙ መንገድ እየበደለን ነው፡፡
አንደኛ ከየትኛውም የዓለም ሀገር ጋር ፍጹም በማይወዳደር ከፍተኛ የተንቀሳቃሽና የቋሚ ስልክ ታሪፍ ገንዘባችንን ይዘርፋል፡፡ በኢትዮጵያ እንዳለው ያለ የቴሌና የመብራት ኃይል ዘረፋ በየትም ሀገር የለም ይባላል፡፡ አንዱ ምሥክር ዓመታዊ ወይ ወቅታዊ ትርፋቸውን ሲያሳውቁ የሚናገሩት የብር መጠን ቁጥር እስከማወቃቸው የሚያጠራጥር ነው፡፡ እንደገናም “ይህን ያህል መቶ ሚሊዮን በሩብ ዓመት አተረፍን” ሲሉ በጭራሽ አያፍሩም – “ዘረፍን! የሕዝቡን ማጅራት መታን!” ነበር ማለት የሚገባቸው፡፡ ቴሌ ነፋስ ነው የሚሸጠው – ያውም እጅግ በተጋነነ ውድ ዋጋ፤ ያ ካሡ ኢላላ የሚሉት አጋሰስ የወያኔ አሽከር ቴሌን በጥገት ላም የመሰለውም ለዚህ ነው – ቴሌ ንጹሕ አየር እየሸጠ በልቶ ለማይጠረቃው የወያኔ ቀዳዳ ካዝና ትልቅ ገቢ ስለሚያስገባ ነው ቴሌን በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ ለማንም እንደማይሰጡ ሲያብራራ እንዲያ ያለው፡፡ “ጊሎቲኖቹ” ቴሌዎች የ50 ብር ካርድ ወደስልክህ ከመጨመርህ በየሰበቡ ሲገመድሉልህ በደቂቃዎች ውስጥ ያልቃል – በውነቱ ኢትዮጵያ ውስጥ በሞባይል ስልክ ደውሎ መነጋገር በእሳት ላይ እንደመረማመድ ያህል ነው፤ አንዳንድ ሰው ስልክ እየተነጋገረ ባለበት ቅጽበት ቴሌ በየደቂቃና ሴከንዱ የሚቆነድደውን ገንዘብ ስለሚያስብ ከደወለለት ሰው ጋር በከንቱ ከመደነቋቆር ባለፈ በቅጡ አይግባባም  – ክፍያው አስደንጋጭ ነው፡፡ እኔንም እንዲህ ያለ ሁኔታ ይገጥመኛል፤ ስለምቸኩል ሳልግባባ ተደነቋቁሬ ስልኬን የምዘጋበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡
በዚያን ሰሞን ሳልጠቀምበት – አለመጠቀሜንም በማስረጃ አቅርቤ – 30 ብር ከምናምን ሣንቲም ተቆርጦብኛል፤ የተሰጠኝ መልስ ግን “በዚህ ስልክ ለሦስት ደቂቃ ውጭ ሀገር እንደተደወለበት ኮምፒውተሩ ያሳያል” የሚል ነው፡፡ ተደወለበት በተባለበት ወቅት ለሥራ መስክ ወጥቼ እልም ያለ ገጠር ውስጥ ነበርኩ – በዚያ ላይ ውጭ ሀገር ከተዛዋሪ ስልክ ውጪ እኔ የምደውልበት አቅም የለኝምና በጭራሽ ደውዬ አላውቅም – ክርስቶስ ምሥክሬ ነው፡፡ ታዲያ ኮምፒውተሩ ያን የሀሰት መረጃ ከየትአባቱ አመጣው?  ይህን ነጥብ ከዋጋው አጠቃላይ ውድነት ጋር አጣምራችሁ አንድ በሉልኝ እንግዲህ፡፡
ሁለተኛ የማንፈልገውን አጭር የጽሑፍ መልእክት በግድ ይልክብናል፡፡ የዜጎች መብት እንደኢትዮጵያ የሚጣስበት ሌላ ሀገር ካለ ይገርመኛል – ምናልባት ከሰሜን ኮሪያ በስተቀር፡፡ ቀኑን ሙሉ በሚሰዱልህ መልእክት ስልክህን ሲያስጨንቁትና አሥሬ ሲያንጫርሩት ይውላሉ፡፡ ሰዎች ሄደው ስለዚህ ጉዳይ ቢጠይቋቸው “ከፈለጋችሁ ሲሙን አውጡ እንጂ እኛ ውል የገባንበት ስለሆነ ላኩ ስንባል እንልካለን” ነው ያሉት – በሚያስደንቅ ትዕቢት፡፡ ምን ዓይነት ትምክህታዊ አስተዳደር ነው? እኔ ካልፈለግሁ እንዴት ነው ላቤን ጠብ አድርጌ በገዛሁት የግል ስልኬ ያዳሜ ኮተት የሚላክብኝ? ቲቪውን መዝጋት ስለምንችል የማንንም ቅርሻት አንጋትም – ግልግል፤ ኢቲቪም ሆነ ኢቢሲ ያው መለያው ውሸት ነው – አንዲት የቀረቻቸውን እውነትም – ሰዓትን በትክክል መናገሩን – ትተዋት በተበላሸ ሰዓት እየቆጠሩ የዜና ዕወጃ ጊዜን ስለሚያዛንፉ መድሓኒት ወሳጆችንና ጸሎተኞችን ማደናገርና ማሳሳት ጀምረዋል አሉ፡፡ ይህኛውን የቴሌን ዕብሪት ግን ምን እናድርገው?  የኔን ስልክ አሁን ባነብላችሁ ጉድ ትላላችሁ፡፡ በየሰዓቱ እየላኩ በአሰስ ገሰስ ስልኬን እንዳለ አጭቀውታል፡፡ ጥቂቶቹን መልእክት መላኪያ ቁጥሮች ልንገራችሁማ ፡- 8100፣ 8400፣824፣8852፣ 8851፣ 251994፣ +251994፣ 994፣ Red Cross, ethio tel,፣ ብርሃኑ ዘገዬ (አይ፣ ይሄኛውስ የጓደኛየ ነው ተውት) … ብቻ ማንም የፈለገ ነጋዴም ይሁን የመንግሥት መሥሪያ ቤትና ባለሥልጣን በነሸጠው ቁጥር ይነሣና ከቴሌ ጋር በመሻረክ ዘባዘቦ ማስታወቂያውን ይልክብሃል፡፡ ስልክህ ምርጫ የለውምና ካልዘጋኸው ወይ ድምጹን ካላጠፋኸው በስተቀር ይረብሽሃል – ይህ ሰውን የመናቅ ጠባይ ትልቅ ነውር ይመስለኛል፤ የአክሲዮንና መሰል የስብሰባና ጉባኤ ጥሪዎች ለአባላት በዚህ መልክ መነገሩ ዘመናዊነት ነውና – ጥሩ ነው፡፡ ባልተገባ አኳኋን ሁሉን ዜጋ በማይመለከተው መልእክት ማስጨነቅ ግን ወንጀል ነው፡፡ እንዲህ ያለ ብልግናና ጥጋብ በሌሎች ሀገራት ይኖር ይሆን?  እስኪ ንገሩን፡፡
በዚያ ላይ ቫት ያስከፍላሉ፡፡ ለወሬ ደግሞ ቫት ለምን ይከፈላል?(እነዚህ መሥሪያ ቤቶች ዋና የሙስና ማዕከላት ስለመሆናቸው፣ በውጪ ሀገራት የሥራ ዘመናቸውን ጨርሰው አርጅተው በተቀየሩ ውድቅዳቂ ዕቃዎች ኢትዮጵያን የሚያጥለቀልቁ ስለመሆናቸው፣ ለመናኛ ዕቃዎች (ከነሙስናው) ብዙ ብር እያወጡ ዕቃዎቹ ሳይገጠሙ ሣር በቅሎባው እንደሚቀር፣ ቢገጠሙም ወዲያው እየፈነዱ አገልግሎት እንደማይሰጡ… አሁን ጊዜ ስለሌለን ሌላ ቦታ አንብቡ፡፡)
መብራት ኃይል፡-
ከቴሌና ጅምሩክ ቀጥሎ አንዱ የወያኔ ጅብ ይህ መሥሪያ ቤት ነው፡፡ ብቸኛ ሥራው ገፈፋ ነው – ቆዳህን ከነአጥንትና ሥጋህ ነው የሚገፍህ ደግሞ፤ ርህራሄ የሚባል የላቸውም፡፡ እኛ ዜጎች ከጨረቃ ወይ ከማርስ የመጣን ሳንመስላቸው አንቀርም፡፡ ይህን ምሥኪን ሕዝብ ከቴሌ ጋር ተባብረው ይግጡታል፡፡ እንደመስቀል ወፍ ሲያሰኘው የሚመጣውን መብራት ለማስገባት ያለው ውጣ ውረድ እንዳለ ሆኖ ክፍያው ደግሞ ስትሰማው ገና ለጆሮም ይሰቀጥጣል፡፡ ባለፈው ተጨማሪ ቆጣሪ ፈልጌ ሄድኩና ስጠይቅ 16 ሺህ ብር ወዲህ በል አለኝ፡፡ “እኔ እኮ የጠየቅኋችሁ ለመንደሩ በሙሉ አይደለም፡፡ የመንደሬ ነዋሪዎችማ ሁሉም መብራት አስገብተዋል፡፡ ለኔ ብቻ ነው – ሊያውም ሁለተኛ ቀጣሪ ስላስፈለገኝ ነው፡፡ ምሰሦ አያስፈልግም፤ ገመድም በጣም አጭር ነው የሚያስፈልገው” አልኳቸው፡፡ እነሱ ግን ሣቁብኝ፡፡ “ተጨማሪ ቆጣሪ የሚፈልግ ሰው የሚከፍለው  ሒሳብ ይህን ነው፤ ደምብ ደምብ ነው፣ መመሪያም መመሪያ ነው” አሉና – እንደኢንጂነር ባንጃው – ከቢሯቸው እንድወጣላቸው ገላመጡኝ፤ ሀገርህ ሰው እንደውሻ የሚታይባት ሆናለች – እንደሰሃራ በታች ውሻ ማለቴ እንጂ የአውሮፓውማ በፊልም እንደምናየው ከሆነ ከሰው እኩል ጠረጴዛ ላይ ቂብ ብሎ ምግቡን ይበላ የለም?  አሁንስ ሳስበው የወረደብን እርግማን ለከት አጣ፡፡ መንግሥት የሚሉት የዱርዬዎች ጥርቃሞ አያከብረንም፤ የርሱው ቅጥር ሠራተኞችም እሱን እያዩ ከርሱው ባልተናነሰ ሁኔታ ያዋርዱናል፡፡ ምን ይዋጠን? እንዴ፣ ዙሪያ ገባው ጨለማ ሆነ እኮ!  የሕዝብን የልብ ትርታ የሚያዳምጥ እንዴት አንድ ተቋምና  አንድ ሠራተኛ እንኳን ይጥፋ?  እንዴት ነው ሁሉም ተያይዞ ድንጋይ ልብ የሆነው? እንዴት ያለ ንፋስ ቢነፍስብን ነው ሁሉም በጥቅም ተሳስሮ የጥፋት ሠራዊት አባል ሊሆን የቻለው? ይህ ሁሉ ውርጅብኝ በዚህች ሀገር ላይ የወረደው ፈጣሪዋን ምን በድላ ይሆን?
ዱሮ በ90 ብር የሚገባ አዲስ መብራት ዛሬ ከ6 ሺህ በላይ ነው፡፡ ይህ ዕድገትን ነው ወይንስ ከፍ ሲል እንዳልኩት ከቁጥር ዕውቀት ነፃ መሆንን የሚያመለክት የድንቁርና ውጤት ነው? በየቦታው ሂዳችሁ ስለዕቃና አገልግሎት ክፍያ ስትጠይቁ የምትሰሙት የገንዘብ መጠን የማይታመን ነው – የአብዛኛውን ዜጋ የገቢ መጠንና የኑሮ ዘይቤ ግምት ውስጥ ያላስገባ አሠራር ተዘርግቶ ሕዝብ በሁሉም አቅጣጫ እየተገረፈና ምርጫም በማጣቱ ወደላይ ወደፈጣሪ እያለቀሰ ነው – እግዜሩስ እንዲህ እንደጨከነ ይቀር ይሆን? ዕድሜ የሰጠው መጨረሻውን ያየዋል፡፡ የአብዛኛውን ዜጋ የወር ደሞዝ ስትመለከቱ ከጥንቱ ብዙም ፈቀቅ አላለም – ሌብነትና ውንብድና የተስፋፋውም መደበኛ ገቢ ከኑሮ ጋር ባለመጣጣሙ ምክንያት ነው – ለምሣሌ አንድ የት/ቤት ዘበኛ አምፖል አውልቆ ቢሸጥ፣ ጽዳቷ ባልዲና መጥረጊያ አውጥታ በመሸጥ ለሣሙና መግዣ ብታውለው ማን ምን ሊፈርድባቸው ይችላል? መንግሥት ሌባ፣ የሃይማኖት መሪው ሌባ፣ ፖሊሱ ሌባ፣ ዳኛው ሌባ …ከሞላ ጎደል ሁሉም ሌባና ቀማኛ የሆነበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነው ያለ፡፡ ደግሞም “መልካም አስተዳደር እናሠፍናለን!” ይባልልኛል፡፡ መልካም አስተዳደር በምኞት ይሠፍናል እንዴ? ከግርጌ እስከራስጌ በሙስናና በንቅዘት በገማ ሥርዓት ውስጥ ማን ከማን ተሸሎስ ነው በሙስና ምክንያት አንዱ አሣሪ ሌላው ታሣሪ የሚሆነው?? ወግ ነው አሉ ሲዳሩ ማልቀስ! ኢትዮጵያ ውስጥ ሙስና ብትሞት አንድም ባለሥልጣን አይተርፍመ – ሁሉም እስትንፋሱ ይዘጋል፡፡ ለመሆኑ ባለሥልጣኖቻችን ደሞዛቸውን ያውቁታል? ለይምሰል ያህል በገንዘብ ከፋዮችና በጓደኞቻቸው ተለምነውና ተንቀባርረው ይቀበሉታል እንጂ ለጫማ ማስጠረጊያ እንኳን የማይበቃቸውን ያን ደመወዝ ተብዬ ከነመጠኑ ጭምር ያውቁታል ብዬ አልገምትም፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ሁሉም ነገር ዕንቆቅልሽ ነው፡፡ ሀገሪቱ ግን አድጋለች እየተባለ ነው የሚወራው፤ ታዲያ ያደገው ማን ነው?  በዚህች ሀገር ውስጥ ስንት ዓይነት ዜጋስ አለ? ተራው ዜጋ የት ይሂድ?  በሙስናም ይሁን በድጎማ ተጨማሪ ገንዘብ ለማያገኘው ለመምህሩ፣ ለዘበኛው፣ ለጽዳቱ፣ ለወታደሩ፣ ለቢሮ ሠራተኛው፣ ለወዛደሩ፣ ለገበሬው፣ ለሥራ አጡ፣ ለጡረተኛው፣ ለተማሪው፣… ማን ይድረስለት? ሀገራችን ውስጥ ምን እየሆነ፣ ምንስ እየተካሄደ ነው ያለው? ወገኖቼ እስኪ ቆም ብለን እናስበው፡፡ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ያላችሁ የሥራ ኃላፊዎችም ቆም ብላችሁ “ሕዝባችሁ”ን አስቡት፡፡ ሕዝቡ በየቢሮክራሲው በተሰገሰጉ ደንታቢስ ትኋኖችና ተምቾች እስከመቅኒው ድረስ በሚዘልቅ ጭካኔ ያለችውን አነስተኛ ጥሪት እንዴት እየተገሸለጠ እንደሆነ ይታያችሁ – እናንተም ራሩለትና ፋታ የሚያገኝበትን ሁኔታ ፍጠሩለት፡፡ ነገሩ ሁሉ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ሆኗል፡፡ የተናጠል ሩጫ ገኗል፤ የዚህ ሁሉ መጨረሻ ግን በርግጠኝነት አያምርም፡፡ ሊቢያና ሦርያ ውስጥ የተከፈተችው የ“ፓንዶራ ሣጥን”(Pandora’s Box) ለ42 ዓመታት ግድም እንደሽሮ ስትንተከተክ ከቆየች በኋላ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ አሁን ሕዝቡ ምርር ብሎናል፤ ቀጭን ሰበብ ነው የምንፈልገው፡፡ እኔ ራሴ ምርርርር… ብሎኛል – ደፍርሶ ይጥራ የምልበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነው ያለ – ያልተፈጠረ ሁኔታ የለም ወገኖቼ፡፡ ሰሞኑን ብታዩኝ ሲናገሩኝ በቀላሉ ሆደ በሻ እየሆንኩ ሰውን ተማታ ተማታ የሚለኝ መጥፎ መንፈስ ተፈጥሮ ያለበት ሁኔታ ላይ ነው የምገኘው – ይቺ የወያኔ አማርኛ አበላሸችኝ መሰለኝ ጎበዝ፤ “ካለበት የተጋባበት”ይባል የለም?  ለማንኛውም ሁሉም ሰው ሆድ ብሶታል፤ ሁሉም መነጫነጭ ይዟል፡፡ የኔን በተመለከተ ግን ለጊዜው  ከባለቤቴ ከማንጠግቦሽ ውጪ የማሸንፈው አጥቼ ተቸገርኩ እንጂ ደፋር ተነስቶ ና ተከተለኝ ቢለኝ ቢያንስ በመጮህ ለመተባበር ዝግጁ ነኝ – ኢያሪኮም የጠፋችው በመጮህ ነው ይባላልና ጩኸቴን አሳንሳችሁ እንዳትገምቱት ታዲያ፡፡ … በቃኝ ወንድሜ፤ ሀበሻ በያለህበት ደኅና ዋልልኝ ወይም እደርልኝ፡፡
ደኅናውን ቀን ያምጣልን፤ አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment