Sunday, April 17, 2016

ውርደታችን ይኸው እንደቀጠለ ነው፤ በአንድ ቀን በጋምቤላ የሚኖሩ 170 ዜጎቻችን ለምን ተገደሉ?

ከብስራት ወ/ሚካኤል
የዜጎችን ደህንነት እና ሀገርን ዳንድንበር ሳያስደፍር መጠበቅ የነበረበት መከላከያ ሰራዊት፤ መሃል ሀገር ዜጎችን ለመግደልና ለማሸበር በመሰማራቱ ስራ ከበዛበት ሰነባብቷል፡፡ ዜጎችን ከመድገልና ከማሸበር የተረፈውም አንዴ ሶማሊያ ሞቃዲሾ በረሃ፣ አንዴ ሱዳን እና ላይቤሪያ ዜጎችን ሰላም ሊያስጠብቅ እንደተሰማራ እንሰማለን፡፡
ፎቶ ምንጭ: ሐና

ነገሩን መች አጣናውና፤ ወታደሮቻችን ለህወሓቶች ጥሩ የዶላር ምንዛሪና የኪስ ማደለቢያ መሆናቸውን፡፡ ሰላም አስከባሪ ወታደሮቹም ቢሆኑ ለገዥዎች ዶላር ምንዛሪ ከመሆን ውጭ የሞቱትና የተሰወሩት እንኳ ስላሉበት ሁኔታ ቤተሰብ ጋ ሳይደርስ እዛው የአሞራ ሲሳይ የሆኑትን ቤት ይቁጠረው፡፡
እጅግ በጣም የሚያሳዝነውና የሚያስቆጨው ትናንትና የጦር መሳሪያ እንደሸንበቆ ዘንግ ይዘው የሚዞሩ የደቡብ ሱዳን ዘላኖች ድንበራችንን ዘና ብለው በመሻገር በጋምቤላ 170 ንፁሃን ዜጎቻችንን በግፍ ገድለው በርካታዎችን አቁስለውና እስካሁንም ቁጥሩ በውል ያልታወቀ የቁም እንሰሳቶቻችን ዘርፈው ዘና ብለው ወደመጡበት ሄደዋል፡፡
በጅምላ ግድያ የተሰነዘረባቸው ዜጎች ለአካባቢው የጋምቤላ ክልል መንግሥትና በአካባቢው ላሉ የፖሊስና መከላከያ የድረሱልን ጥሪ ቢያቀርቡም ሚሰማቸው በማጣታቸው የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ ዜጎቻቸውን ድረሱልን በማለታቸው በተደረገ ትብብር ከ60 ያላነሱ የደቡብ ሱዳን ዘራፊና ገዳዮችን መግደላቸውንና ከዛም ወደመጡበት ሊመለሱ እንደቻሉ የጥቃቱ ሰለባዎች ይናገራሉ፡፡ ህወሓት/ኢህአዴግ ሰዎች ውርደት ክብራቸው ስለሆነ እንጂ ይህ የሀገሪቱና የዜጎች ብቻ ሳይሆን የነሱም ውርደት መሆኑ በገባቸው ነበር፡፡ ነገሩ ከሆድና ስልጣን የዘለለ ራዕይና ዓላማ ለሌለው ሰው ክብር መች ይገባዋል?
ኢትዮጵያዊ ስሜት ያለውና ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን መብትና ጥቅም የሚቆም መንግሥትና ስርዓት እስኪመጣ ግድያውም ሆነ ውርደታችን በዚህ የሚያበቃ ሊሆን አይችልም፡፡ የትናንቱ የመጀመሪያው አይደለምና፡፡ የሱዳን ነጋዴዎችና ሾፌሮች ካቅማቸው በየጊዜው ስንት ኢትዮጵያውያንን በራሳችን ምድር ገድለው መንገድ ላይ ወንዝ ዳር እየጣሉ ዘና ብለው ወደ መዲናቸው ካርቱም ይመለሱ የለ?
መቼም ያን በደል የፈፀሙት ደቡብ ሱዳናዊ ዘላኖች የእናት ጓዳ ይመስል ዘው ብለው በመግባት ነው፡፡ ይህም የሆነው ኢትዮጵያዊ እና የኢትዮጵያውያንን ደህንነትና ሰላም የሚያደፈርስ እንጂ የሚያስጠብቅ መንግሥት እንደሌለን ጠንቅቀው ስለሚያውቁ እንጂ በቅርባቸው ያሉ ኬንያና ዩጋንዳ ቢሆን እንዲህ ይዳፈሩ ነበር? ይባስ ብሎ በልሳኑ ፋናቢሲ የተገደሉ ዜጎችን ቁጥር ለመቀነስና የተለመደውን ደረቅ ፕሮፖጋንዳ ይነዛልኛል፡፡ ቲሽሽሽ!

No comments:

Post a Comment