Friday, April 15, 2016

በአንድ ግዜ ብዛት ያላቸውን ኢሜይሎች መላክ በኢትዮጵያ ወንጀል ሆኖ ሊመዘገብ ነው


email

(ሳተናው) ባሳለፍነው ማክሰኞ ሚያዚያ 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ለፓርላማው የቀረበው ባለ 53 ገጹ የኮምፒዩተር ወንጀል ረቂቅ አዋጅ ማብራሪያ እንደሚያስረዳው፣ ብዛት ያላቸውን ኢሜይሎች በአንድ ጊዜ ለአንድ ሰውም ይሁን ለብዙዎች የኢሜይል ተጠቃሚዎች መላክ በወንጀል የሚያስጠይቅ በመሆን ለቅጣት ይዳርጋል  ፡፡
በሰዎች የነፃነትና ክብር ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች በሚል ንዑስ ርዕስ በአንቀጽ 13 ላይ የኮምፒዩተር ሥርዓትን በመጠቀም በሚሠራጭ ጽሑፍ፣ ንግግር፣ ቪዲዮ ወይም ሥዕል አማካይነት በሌላ ሰው ወይም በተጐጂው ቤተሰቦች ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ ያስፈራራ ወይም የዛተ ከሦስት እስከ አምስት ዓመት ጽኑ እስራት ያስቀጣል፡፡
በሕዝብ ደኅንነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች በሚለው በረቂቁ አንቀጽ 14 ላይ፣ ‹‹ማንኛውም ሰው በኅብረተሰቡ መካከል የፍርኃት ስሜት፣ አመፅ፣ ሁከት፣ ወይም ግጭት እንዲፈጠር የሚያነሳሳ ጽሑፍ፣ ተንቀሳቃሽ ምሥል፣ ድምፅ ወይም ማንኛውም ሌላ ምሥል በኮምፒዩተር ሥርዓት አማካይነት ያሠራጨ እንደሆነ ከሦስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራት ያስቀጣል፤›› ይላል፡፡
የ‹ስፓም› (የተቀባዩን ፈቃደኝነት ሳይጠይቁ ተደጋጋሚ ኢሜይሎችን መላክ) መልዕክቶችን ስለማሠራጨት በሚለው የረቂቁ አንቀጽ 15 ድንጋጌ መሠረት ማንኛውም ሰው ምርትን ወይም አገልግሎትን ለማስተዋወቅ ወይም ለሽያጭ ለማቅረብ፣ መልዕክቶችን በአንድ ጊዜ ወደ በርካታ ኢሜል አድራሻዎች ያሠራጨ እንደሆነ ከሦስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት መቀጮ ያስቀጣል፡፡ ወንጀሉ ከባድ በሆነ ጊዜ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራትና ከ50,000 ብር በማይበልጥ መቀጮ ያስቀጣል፡፡ ረቂቁን የተመለከተው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለዝርዝር ዕይታ ለሕግና ፍትሕ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል፡፡
የስፓም መልእክቶችን በተመለከተ የተለያዩ አገራት የተለያዩ የቁጥጥር አዋጆችን ያወጡ ሲሆን እንግሊዝ የገንዘብ ቅጣት በመጣል መልእክቶቹን ለመቆጣጠር ስትሞክር ጣልያን ደግሞ የሶስት አመት እስራት እንደምትፈርድ አስታውቃለች፡፡የስፓም መልእክቶች በአብዛኛው ንግድን ለማስተዋወቅና ህገ ወጥ ፊልሞችን ፣እንደ ቪያግራ ያሉ መድኃኒቶችን ለመሸጥ የሚቀሰቅሱ መሆናቸውን ብዘዎች ይገልጻሉ፡፡

No comments:

Post a Comment