October 7, 2015
ክቡር ከንቲባ ‹‹በአዲሱ መንግስት›› ይዤዎታለሁ፤ የምትከተለዋን ማመልከቻዬን አጠናቀው ያንብቡልኝማ!
በኃይሉ ገ/እግዚአብሔር
ክቡር ሆይ! እንኳን ከስኬታማው ወደ ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አሸጋገርዎ! እንኳን ለአዲሱ ዓመትም አደረስዎ! ኧረ እንኳንም ‹‹ለአዲሱ መንግሥት›› አደረስዎ!
ክቡር ሆይ የቤት አከራዬን በደል እና የቤት ኪራይ ጭማሪ፤ የኑሮ ውድነቱን የምቋቋምበት አቅም አጣሁ… ልልዎ ፈለግሁና ከአፌ መለስኩት፡፡ ከ አ ፌ! …እንዲህ ማማረር ስኬታማውን ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ማሳጣት ይሆንን? ስል አሰብኩና፣ በእውነት ነው የምልዎ ከአፌ መለስኩት፡፡
ክቡር ከንቲባዬ ኮንደሚንየም ከተመዘገብኩ ስንት ዓመት ሆነኝ መሰለዎ፡፡ መጪው ግንቦት ሲመጣ አሥራ አንድ ዓመቴ፡፡ ጊዜው እንዴት ይሮጣል ክቡር ከንቲባ፡፡ ‹‹ኮንደሚኒየም ከተመዘገባችሁ ወዲህ ጠግባችኋል!›› የሚለውን የአከራዮቼን የቃላት በትር ከነቤተሰቤ ችለን መኖር ከጀመርን አሥራ አንድ ዓመት ሆነን፡፡ እግዚኦ!
ልጄ ትናንት ‹‹ምርጥ›› የሚለውን ሕልም አየ፡፡ ምን እንደሆነ ያውቃሉ? እንጀራ በሽሮ ወጥ ሲበላ፡፡
‹‹አባቴ!›› አለኝ በቀሰስተኛ ድምፁ፡፡
‹‹አቤት!›› አልኩት፡፡
‹‹እንጀራ በሽሮ ወጥ ስበላ በሕልሜ አየሁ!›› አለኝ፡፡
‹‹እንጀራው የጥቁር ጤፍ ነው የነጭ ጤፍ?››
‹‹የጥቁር ጤፍ!››
‹‹ወጡ ቅቤ አለው?›› አልኩት እኔ ራሴ በሱ ሕልም መጎምዠቴ እንዳይታወቅብኝ እየተጠነቀቅሁ፡፡
‹‹ኧረ እኔ እንጃ!›› አለ ልጄ እሱም በጉምዥት ምራቁን ወደ ጉሮሮው እየሰደደ፡፡
‹‹በደንብ ማየት ነበረብህ!›› ልለው ፈለግሁና ተውኩት፡፡
‹‹አባቴ!›› አለኝ በቀሰስተኛ ድምፁ፡፡
‹‹አቤት!›› አልኩት፡፡
‹‹እንጀራ በሽሮ ወጥ ስበላ በሕልሜ አየሁ!›› አለኝ፡፡
‹‹እንጀራው የጥቁር ጤፍ ነው የነጭ ጤፍ?››
‹‹የጥቁር ጤፍ!››
‹‹ወጡ ቅቤ አለው?›› አልኩት እኔ ራሴ በሱ ሕልም መጎምዠቴ እንዳይታወቅብኝ እየተጠነቀቅሁ፡፡
‹‹ኧረ እኔ እንጃ!›› አለ ልጄ እሱም በጉምዥት ምራቁን ወደ ጉሮሮው እየሰደደ፡፡
‹‹በደንብ ማየት ነበረብህ!›› ልለው ፈለግሁና ተውኩት፡፡
ዛሬ ቤቴ በጊዜ ብገባ ያ ሕልመኛው ልጄ፣ ዘወትር በሚተኛበት አሮጌ ሶፋ ላይ በጀርባው ተንጋሏል፡፡ ‹‹እንቅልፍ ወስዶት ይሆን?›› ብዬ ጠጋ ብዬ ሳየው ዐይኑን ጨፍኗል፡፡
‹‹ታምሩ! አንተ ታምሩ!›› ስለው ዐይኑን እንደጨፈነ፣ ‹‹አቤት!›› አለኝ፡፡ ‹‹ምነው በጊዜ ተኛህሳ!?›› ብለው፣ ‹‹አይ አባቴ የትናንትናውን እንጀራ በሽሮ ወጥ በድጋሚ ለማየት ነው!›› አለኝ፡፡
‹‹በል ተነስ! ሢሳይ የሚታየው አንዴ ነው!›› አልኩት፡፡ እንዳልሰማ ዐይኑን እንደጨፈነ ቀረ፡፡ ይቅናው! ምን አደርጋለሁ? …ክቡር ከንቲባ እንዲህ ተመሳቀቅ ያድንዎ!
ባለቤቴ በባለፈው ሣምንት ባንዱ ቀን ድንገት ተነስታ፣ ‹‹መቶ አሥር ብር ስጠኝ!›› አለቺኝ፡፡ ነደደኝ፤ እየተጠየቅሁ ያለሁት መቶ አሥር ብር እኮ ነው ክቡር ከንቲባ፡፡ በጣም ነደደኝ፡፡ ‹‹ያለ ወትሮሽ ምነዋ መቶ አሥር ብር!?›› ስላት፤ ‹‹በርበሬ ልገዛበት!›› አለችኝ፡፡ ንዴቴ ወደ ድንጋጤ ተቀየረ፤ ‹‹አንቺ ሴት ምንድነው ነገሩ? ድግስ አለብሽ? ወይስ ሆቴል ልትከፍቺ ነው? ወይስ ያ የማርያም ፅዋሽ ደረሰ!? የመቶ አሥር ብር በርበሬ ምን ሊሆንሽ ነው!?›› ስላት ተቆጥቼ፤ የሚያሳዝን የደሃ ሳቅ ሳቀችና፣ ‹‹አትቀልድ እባክህ፤ የግማሽ ኪሎ መግዣ ነው የጠየቅሁህ!›› አለቺኝ፡፡ ‹‹ኧረ ጉድ ነው እናንተ! ግማሽ ኪሎ በርበሬ መቶ አሥር ብር!›› ብዬ በቅጡ ደንግጬና ጮኼ ሳልጨርስ፣ የነምስርን፣ የእነ ሽሮ ክክን፣ ዋጋ ነግራ በሽታ ላይ ጣለቺኝ፡፡ …ኧረ ምኑ ይወራል ክቡር ከንቲባ!? ባደገች አገር ውስጥ እየኖርን የእህል መወደድን ጉዳይ አድርጎ ማጉተምተም የፀረ ሰላም ኃይሎች ተግባር ነው ብለን እንተወው እንጂ ምኑ ይወራል ብለው ነው!?
ብቻ ያልቻልኳቸው ቤት አከራዬን ነው ክቡር ከንቲባ፤ እኚህ ኪራይ ሰብሳቢ! (ባይሆን ለእርስዎ በምጽፈው ደብዳቤ ላይ እንኳ ልስደባቸው እንጂ!) ትናንት ማታ፤ ተዘጠኝ ተከራይ የሽንት ቤት ወረፋ በኋላ፣ ተራው ደርሶኝ ገብቼ አረፍ ብል፣ ከዘራቸውን እያንቋቁና እያወናጨፉ መጡ፡፡ እንደ ጨዋ የመፀዳጃ ቤቱን ደጃፍ አንኳኩ፡፡ ድምፄን በመጠራረግ ሰው እንዳለ ልነግራቸው ሞከርሁ፡፡ ደግመው አንኳኩ፤ ‹‹ሰው አለ!›› ብዬ ጮኽኩ፡፡
‹‹እ! አንተ ነህ እንዴ! ይገርማል፤ የሚበላ ስትሸምቱ አናይም፤ ሽንት ቤት ገብታችሁ ስትቀመጡ ግን አንደኛ ናችሁ፡፡ ኧረ ለበሉት ልቀቁ!›› አሉኝ፡፡ እኔ ልሙት ክቡር ከንቲባ! እንደው ተነስቼ አንገታቸውን ባንቀው ምንኛ ደስ ባለኝ!
ሰውን ከሰው እኩል ያደረገው መቃብር እና ሽንት ቤት አይደለምን? እንዴት እንዲህ ይባላል ክቡር ከንቲባ!? ከሳም ወፈረም፤ አገኘም አጣም ሰው ሁሉ ወደ ሞት መሄዱ አይቀርም፡፡ ቆሎ ቆረጠመም፣ ጮማ ቆረጠም ከመፀዳጃ ቤትስ የሚቀር አለ? የለም፡፡ ሁሉም የአቅሙን ለመጣል ይቀመጣል፡፡ እንዴት እንዲህ ይሉኛል?
የቤት ኪራይ ጭማሪው፣ የእኔን እና የሚስቴን ደም ብዛት ይኸው እንደጨመረው አለ፡፡ (ጉድ ነው፤ ደም እንዳለው ሰው!) ከዚህም አልፎ ንጭንጫቸው፡፡ ባለፈው ወር፣ ‹‹ሁለት ቀን መብራት ሳታጠፉ ሥራ ሄዳችሁ›› ብለው የቤት ኪራይ ላይ ሃምሳ ብር ጨመሩ፡፡ ‹‹ኧረ ጋሼ! መብራቱ መች ነበረና!›› ብላቸው፤ ‹‹መብራቱ ቢኖርማ ኖሮ መቶ ብር ነበር ጭማሪው!›› አሉኝ፡፡ ኧረ በደል በዛ፤ ኧረ ስቃይ በዛ ክቡር ከንቲባ! ኧረ ይሄ የቤት ኪራይ ነገር አንገፈገፈኝ ክቡር ሆይ! ኧረ አንገፈገፈኝ!!
‹‹ምነው እማዬ እኛ እየከሳን ስንሄድ ትልቁ አሣ ይበልጥ ትልቅ እየሆነ ሄደሳ!?›› አለች አሉ ትንሺቱ አሣ ለእናቷ፤ እናቲቱም እንዲህ አለች አሉ፤ ‹‹አዬ ልጄ እኛን የመሰሉ ደካማ አሦችን እየበላ ይሆናላ!››
ወደ ጉዳዬ ስመጣ ጥያቄዬ ቤት የመገንቢያ ቦታ እንዲሰጠኝ ነው ክቡር ከንቲባ፡፡ አውቃለሁ፤ ኮንደሚኒየሙ አንድ ቀን ይደርሰኝ ይሆናል፡፡ ይህ ቀን ግን የምፅአት ቀን ሆኖብኛል፡፡ ለነገሩ ቢመጣስ የምከፍለው ገንዘብ ከየት አገኝና! ስለዚህ ክቡር ከንቲባ እንደአቅሜ ቤት የምሠራበት ቦታ እንዲሰጠኝ ነው ጥያቄዬ፡፡
መቼም ክቡር ከንቲባ፣ ‹‹ዞሮ ዞሮ ከቤት፣ ኑሮ ኑሮ ከመሬት›› እንዲሉ አባቶች ያ የቁርጥ ቀን ሲመጣ አፈር መቅመሴ አይቀርም፡፡ እኔ ብቻም ሳልሆን ቤተሰቦቼም ጭምር፡፡ ስለሆነም ያቺ የመቀበሪያችን ቦታ ተሰልታ ትሰጠንና የመኖሪያ ቤት ግንባታ እንድናካሂድባት ይፈቀድልን ስንል ‹‹በአዲሱ መንግስት›› እንዲሁም በሰላምና በዴሞክራሲ ስም አጥብቄ እጠይቃለሁ፡፡
No comments:
Post a Comment