Tuesday, October 27, 2015

በአማራ ሕዝብ ስም ሌሎችን መዝለፍ የሚወገዝ ነው

ይህን አቅዋም ማስተጋባቱ የግድ የሆነብን አማራው ህዝብ ተበደለ በሚል ጸያፍ ዘመቻዎች በሌሎች ህዝባችን ላይ መካሄዱ ስለቀጠለ ነው። ዝምታ ሕዝብን ለጥቃት አሳልፎ መስጠት በመሆኑ ግዳጅና ሀላፊነትን መካድ ይሆንብናል። በሰሞኑ አማራው ህዝብ ከቤኒ ሻንጉል ተፈናቀለ በሚል ለዚህ ዋናውን ተጠያቂ ወያኔን በማውገዝ ፈንታ በጉምዝ ሕዝብ ላይ የተከፈተው ጸያፍ ዘመቻ የአማራን ሕዝብ ተገን አድርጎ በመሆኑ ሊወገዝ የሚገባው ነው። በመጀመሪያ ደረጃ አማራው ከጉምዝና ቤኒ ሻንጉል አካባቢዎች መፈናቀል የጀመረው ወያኔ ኢሕአፓን አጥቅቶ ቦታውን ከተቆጣጣውረ ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ ነው። ደርግ በጣና በለስ አካባቢ አስፍሯቸው የነበሩ ዜጎች የዚህ ወያኔያዊ ዘመቻ ሰለባ ነበሩ፡፡ ቀደም ሲል ደርግ ያደረሰባቸው በደልና ይህንንም በመቃወም ድርጅቱ ያደረጋቸውን ጥረቶች ለታሪክ ትተን ወያኔ ስልጣን ሲይዝ በቦታው በነበሩ የአማራ ተወላጆች ላይ እርምጃ ሲወስድ ያኔ ከኢሕአፓ ሌላ በጉዳዩ ቁጭትም ያሰማ ትችትም ያቀረበ አልነበረም። አሌ ከተባለ በመረጃ መርታት ይቻላል። ከቤኒ ሻንጉልም፤ ከምስራቅ ወለጋም፤ ከደቡብ ኢትዮጵያም ወዘተ አማሮች ላይ የማፈናቀሉ ዘመቻ ምንጩ ወያኔ ነው። የወያኔ ተለጣፊዎች ናቸው:: በአሶሳ፤ በደኖ፤ አርባጉጉ ከወያኔ ያበሩ የኦሮሞ ድርጅቶች ለደረሰው ወንጀል ተጠያቂነታቸው የሚካድ አይደለም። የነሺፈራው ሽጉጤና ሃይለ ማርያም ደሳለኝም ወንጀል ወያኔ በሚል የሚሸፈን አይደለም። ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ንጹህ ሕዝብን በጸያፉ መወንጀልና መክሰስ ብልግና ነው። የጉምዝ ሕዝብ/ቤኒ ሻንጉሎች አማራውን ገድለው ጉበቱን፤ ኩላሊቱን፤ የታፋ ስጋውን በሉ ብሎ ዓይንን በጨው አጥቦ ሕዝብን መዝለፍ አፍሪካን ከሚጠሉ ነጮች የሚጠበቅ እንጂ ለአማራው ተቆረቆርን ባዮች ሊሰማ የሚገባው አይደለም። ያሳፍራል ይህ ሲደመጥ። ሊደመጥ የማይገባውን ትምክህትንም አንጸባራቂ ነው። ሕዝባችን የትም ቢሆን የት ሰው አይበላም:: ይህን ውሸት ማሰራጨት ኢትዮጵያ ላይ መዝመት ነው። የሚከሰሱት አህዛብ ናቸው፤ ሀይማኖት የላቸውም፣ ስለዚህም ሰው የሚበሉ አረመኔዎች ናቸው ብሎ ልፈፋም አማራ ነን ባዮቹ ምንኛ ኋላ ቀርና የሀገርን ስምና የአንድነት መሰረት አውዳሚ እንደሆኑ ያሳያል። ሁሉም ሕዝብ የራሱ እምነት አለውና መከበር ይገባዋል ከማለታችን በተጨማሪ “ሰው ብላ!” የሚል እምነት በኢትዮጵያ አለ ብሎ መነሳት ሀገራችንን ማዋረድ ነው። ኢትዮጵያዊያን ግፍ አይፈጽሙም ስንል ቆይተን የደርግ አረመኔዎች (አሁን ሰው ተበላ ባዮች አንዳንዶቹ እነዚሁ ናቸው ) የኢሕአፓን አባላት ስጋ እየቆረጡ ብሉ ሲሉ ታዝበናል። እነዚህ ከይሲዎች ዛሬ በየተቃዋሚው ድርጅት ተሰግስገው እንዳሉም እናውቃለን። በየፓል ቶኩ የሚባልጉት እነዚሁ ናቸው። ይህ የአማራው ስጋ ተበላ የሚል መረጃ አልባ ልፈፋ ተወደደም ተጠላም ወያኔን የሚጠቅምና ተከሳሹን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን መላ ኢትዮጵያን ሕዝብ መብትና ክብር የሚጥስም የሚያክቸለችልም ነው፡፡የጉምዝ ቤኒሻንጉልን ሕዝብ በጸያፍ ውንጀላ የከሰሱት ሁሉ ህዝብን ይቅርታ መጠየቅ ይገባቸዋል። አፍሪካዊያኖች አረመኔዎች ናቸው ብለው ሊያጣጥሉን ለሚጥሩ ባዕዳንም ወፍጮ እህል በማቅረባችው የሚወገዙ ናቸው። ኢትዮጵያን ሲጎዳ የቆየውን ትምክህት በማናፈሳቸውም በህዝብ መከፋፈል ልክ እንደ ወያኔም ሊከሰሱ ይገባቸዋል። እውነቱ ተነግሮ ሳያልቅ ወደ ሀሰቱ መጓዝስ ለምን አስፈለገ? ወያኔ አማራውን ከየቦታው ያፈናቅላል? እውነት። ከቤኒ ሻንጉልና ሌሎች ቦታዎች አማራው ተፈናቅሏል? እውነት። መፈናቀሉ በደልንም አዘል ነበር? አዎ:: የተገደሉ አማራዎች አሉ? ትክክል። ሬሳቸው ቅርጫ ገብቶ ተበልቷል? አሳፋሪና ጸያፍ ውሸት። ይህን ውሸት ማራገቡ ጠቃሚ ነው ብለው የተነሱ ክፍሎች ፖለቲካዊ መሃይምነታቸውን ተገንዝበው እንዲያቆሙ ሊደረጉ ይገባል። የጉምዝና ቤኒ ሻንጉል ሕዝብ ኢትዮጵያዊነትን በጥያቄ ማስገባት ራሱ አሳዛኝ ከመሆኑ ባሻገር ግን ሬሳ በላ ብሎ መወንጀሉ አሳፋሪ፤ ትምክህተኛና የኢትዮጵያን የአንድነት መሰረት ጎጂ ነው። የተወነጀለው ሕዝብ አያሌ መሀይሞችና ትምክህተኞች አሁንም እንዳሉ ተገንዝቦ ቅሬታ እንዳይኖረው ጥሪ ማድረግን እንፈልጋለን።

No comments:

Post a Comment