Wednesday, October 7, 2015

አብዱ ኪያር ዘንድሮ አንበሳ ሆኖ መጣ

ሄርሜላ አበበ ከልደታ
የራሳቸውን ግጥምና ዜማ ከሚሰሩት ጥቂት የሃገራችን ድምጻውያን ጋር በዋነኝነት ይሰለፋል:: ብዙዎች ደግሞ መድረክ ላይ ሲጫወት ልክ እንደ ሲዲው ኩልል አርጎ በመዝፈን ያደንቁታል:: ለጥቂት አመታት አዳዲስ ስራ ሰርቶ አልቀረበም ነበር :: ምክንያቱንም ሲገልጽ ትምህርት ቤት ገብቶ ሲማር በመቆየቱ እንደሆነ አስረድቷል::Abdu Kiar, New Song Anbessa (Black Lion)
በአሁኑ ሰአት ላይ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርት እራሱን አሳድጎ ሶፍትዌር ዴቨሎፐር ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል:: በቅርብ የሚያውቁት ሰዎች ስለሱ ሲናገሩ ሰው አክባሪ ግልጽ እና ጥርስ የማያስከድን በጣም ተጫዋች ሰው ነው ይሉታል:: እኔና በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከሰይፉ ፋንታሁን ጋር ያደረገውን ቆይታ በኢቢኤስ ክተመለከትን በኋላ ከለፉና ከጣሩ ምንም የማይደረስ ነገር እንደሌለ ስላሳየን ወደነዋል አክብረነዋል ልባችን ውስጥም ልዩ ቦታ ሰጥተነዋል:: ከጥበቡ ውጭ ለእውቀት እንዲህ ያለ ስፍራ በመስጠቱና ከዝና ጋር ትምህርት ቤት ሄዶ ስኬታማ በመሆኑ እጅግ በጣም አድንቀነዋል ብዙም አስተምሮናል::
ድምጻዊ አብዱ ኪያር አዲሱ ጥቁር አንበሳ የተሰኘ አልበሙን እንካችሁ ብሎናል ይህ ማለት አራተኛ ስራው መሆኑ ነው:: ያለፉት ሶስቱ አልበሞቹ መርካቶ ሰፈሬ ፍቅር በአማርኛ ና ምነው ሸዋ በህዝብ ዘንድ እጅግ ከፍ ያለ ፍቅር እና አድናቆት አስገኝተውለታል::
እንግዲህ ስለ አብዱ ኪያር ይሄን ካልኩ በኋላ ወደ አዲሱ ጥቁር አንበሳ የሙዚቃ አልበም ጽሁፌን ልቀጥል:: ሁሉንም ዘፈን ያቀናበረው አሸብር ማሞ ሲሆን ታላቁ የሙዚቃ መምህር ፈለቀ ሃይሉም ተሳትፎበታል:: ተክሉ ደምሴ ሳክስፎን ሰጠኝ አጣናው ማሲንቆ በመጫወት እዚህ ስራ ላይ ተሳትፈዋል::11 ዘፈኖች ሲኖሩት የተለያየ ሪትም አላቸው ሬጌ፣ ችክችካ፣ ዙክ… በየዘፈኖቹ ላይ የሚያነሳቸው ሃሳቦች ልዩ መሆናቸውን ዘንድሮም በብዙ ዘፈኖቹ አሳይቶናል:: በየቀኑ የምናየውን ነገር ልብ ካለማለታችን ወደ ሩቅ እንመለከታለን:: አይናችን ስር ያለ ግን ደሞ አግዝፈን የማናየውን ነገር በጥበብ ቀምሮ የሰጠንን ጥቁር አንበሳን እንመልከተው::
ስንቶቻችንን ነው በአንበሳ ነው ለካ የተከበብነው እንድንል ያደረገን? ጥቁር አንበሳ ትምህርት ቤት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የአየር መንገድ አርማ አንበሳ የአውራ ጎዳና አርማ አንበሳ የቴሌ አርማ አንበሳ ሳንቲሞቻችን አንበሳ አንበሳ አውቶቡስ አንበሳ ጫማ አንበሳ ሻይ ስንጎብዝ አንበሳ ስንበረታ አንበሳ ስናይል አንበሳ ስንቀድም አንበሳ ስንጎብዝ አንበሳ… ለባእድ እጅ አልልሰጥም በማለት ሃገራችንን ያቆዩልንን ጥቁር አንበሶችን በዚህ መልኩ በጥበብ ሲያመጣልን ተደስተናል ታላቅ ኩራትም ተሰምቶናል::Abdu Kiar's new album "anbesa"
ሆ ብሎ ሆ ከተነሳ 
ያስፈራል ጥቁር አንበሳ
እናት አገራችን ኢትዮጵያ ሆ ብሎ ሲነሳ የሚያስፈራ ህዝብ እንዳላት እናቴን እንዳትነኩ ብሎ ሁሉም እንደ አንበሳ የሚቆጣ ህዝብ እንደሆነ በጥበብ ሲነገረን ያውም በዘፈን ኩራታችን ጨምሯል:: ሌላው የድሮውንና የወደፊቱን የገለጸበት ጥበብ ነው:: የጥንቱን ታላቅነት አሁንም የሚደረገውን አድርገን መመለስ እንዳለብን በግልጽ የሚናገር ግጥም በመሆኑ ሊሰመርበት የሚገባ የዘላለም ጥቅስ ነው::
በራስ መተማመን በውርስ ያቀበለን
ለመስሪ ለፓሻ ለሶልዳቶ ያልጣለን
ጀግና አገር አክባሪ አንበሳ አያት አለን
ታላቅ እንደነበርን ታላቅ እንሆናለን!!!!!!!!
መስሪ ማለት የግብጽ ሰው ማለት ሲሆን ፓሻ ማለት ደግሞ የቱርክ የውትድርና ማዕረግ ስም ነው:: ሶልዳቶ ማለት በጣሊያንኛ ወታደር ማለት ሲሆን አብዱ ኪያር ይሄን ዘፈን ሲሰራ ምን ያህል እንደተመራመረና እንደተጨነቀበት ጽሁፍ የሚችል ያውቀዋል::
አሁን ደግሞ በታላቁ የኢትዮጵያ ቅኝት በአንች ሆዬ መልካም አመት በዓል ብሎ በሰራው ዘፈን ላይ ትንሽ ልበል:: በበአሉ ለሁሉም መልካም ምኞትን ሲገልጽ ቤተሰብ ወዳጅ ጓደኛን ብቻ አይደለም ያነሳው:: በኢትዮጵያ የዘፈን ግጥም ውስጥ ተብሎና ተነግሮ በማያውቅ መልኩ ለተሰደዱ በህመም ለተሰቃዩ እንዲሁም ወህኒ እና እስር ቤት የሚገኙትን ኢትዮጵያውያን በሙሉ መልካም አመት በዓል ብሎበታል::
ከአገር ርቀው ለተሰደዱት
በህመም በስቃይ ካልጋ ለዋሉት
በህግ ተይዘው እስር ቤት ላሉት
ያድርግላቸው እንደሚመኙት
ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚያስማማ እና ብሩህ የሆነ የመልካም ምኞት ስለሆነ በጣም ኮርኩሮኛል:: እዛው ዘፈን ላይ ሌላ እጅግ የሚደንቀው ግጥም ደግሞ ያለፈው ታሪካችን እንዴት እንደሚያኮራና ከየትና የት ሰው እንደተቀበልን የሚያሳይ ነው::
ከእየሩሳሌም ደግሞም ከመካ
እኛን አክብሮ ከሩቅ ጃማይካ
ኢትዮጵያን ብሎ በኛ ሲመካ 
ተቀብለናል ትመስክር አፍሪካ
ተቀብለናል ትመስክር አፍሪካ
አብዱ ኪያርን በዚህ ግጥሙ ኢትዮጵያውያን ምን ያህል በሃይማኖት የተለያዩ ቢሆኑም ወንድማማች እና ደራሽ ወገን መሆናቸውን አሳይቷል:: በዚህ በአሁኑ ዘመን የሃይማኖት አክራሪዎች የሚያደርጉትን እያየን እና እየተመለከትን ባለንበት ዘመን አብዱ ኪያር ይሄን የመሰለ አገራዊ ቅኝት በፍቅርና በወገን ደራሽ ስሜት ሲያንቆረቁረው ልቤን ነክቶኛል ሰውነቴን ውርር እስኪያረገኝ ድረስ በአገር ፍቅር አጥምቆኛል::
እንዲሁ እንዳለን እንዳይለየን
የወንጌሉ ሰው ላገሬ እስላሙ 
ወገኑ አይደል ወይ ደራሽ ወንድሙ
የቁርአኑ ሰው ለክርስቲያኑ 
ወንድሙ አይደል ወይ ደራሽ ወገኑ
ረመዳን ስፆም በርታ የሚል ጓዴ 
አይዞህ የምለው ሲሆን ኩዳዴ 
የኔና የሱን ታላቁን ፍቅር 
ኢትዮጵያን ያየ ወጥቶ ይመስክር
አብዱ ኪያር ኑርልን ከክፉ ይጠብቅህ ታላቅ አገራዊ ክብር ይገባሃል:: ይህ ዘፈን ምን ያህል ጥልቀት እንዳለው ለማወቅ ቅኝቱን ማወቅ ያስፈልጋል አንቺ ሆየን::
ብዙዎቹ የአንቺ ሆየ ዘፈኖች የኢትዮጵያ የሰርግ ዘፈኖች ናቸው ብዙ ጊዜም አዳዲስ ዘፈኖች በዚህ ቅኝት አይሰሩም:: አብዱ ኪያር ሂፕ ሃፕ ሬጌ ዳንስ ሆል ስታይል ዘፈኖችን እየዘፈነ ያደገ የመርካቶ የአራዳ ልጅ ሲሆን በዚህ ቅኝት ዘፍኖ ግን ድፍን የኢትዮጵያን ህዝብ አስደስቷል:: አራዳ ማለት እንዲህ ወደ ውስጣዊ ማንነቱ በጥልቀት የሚያይ መሆኑንም አስመስክሯል አንዳንድ ቅላጼው ላይም ለማ ገብረህይወትን እጅግ በጣም አስታውሶኛል:: በሚቀጥለው ክፍል ስለ አልተነጣጠልንም ስለ ዳኛው እና ስለ ሌሎቹ ዘፈኖች በስፋት እሞነጭራለሁ:: ሰላም ቆዩልኝ::

No comments:

Post a Comment