Sunday, November 29, 2015

የአዲስ አበባ ህፃናት ከቆሻሻ ላይ ምግብ አንስተው ሲመገቡ የሚያሳይ ቪዲዮ | ከተሜው ከተራበ ቆይቷል


  • 165
     
    Share
ስሜነህ ከሚኒሶታ

15 ሚሊዮን ሕዝብ ተርቧል ሲባል አንዳንድ የስርዓቱ ገጽታ እንዲበላሽ የማይፈልጉ ተላላኪዎች “የተራበም በርሃብ የሞተም የለም” በሚል አይናቸውን ጨፍነው ሲከራከሩ ማየት በጣም ያማል:: በቅርቡ በቢቢሲ ላይ ወጥታ ልጇ በርሃብ የሞተባት ወ/ሮ ብርቱካን እንዴት አድርገው በመሳሪያ ሃይል አስፈራርተው ልጄ በርሃብ አልሞተም እንድትል እንዳደረጓት የቀናት ት ዝታችን ነው:: ዛሬ ከዓመት በፊት በኢትዮጵያ የተለቀቀውን ቪዲዮ ለትውስታ ያቀረብኩላችሁ እነዚሁ የ ስር ዓቱ መልካም ገጽታ ገንቢዎች እንዲያፍሩ በማሰብ ነው:: አሁን ድረስ በአዲስ አበባ ችግር ውስጥ ያሉ ህፃናት ከቆሻሻ መጣያ ምግብ እያነሱ ይመገባሉ:: የ ስር ዓቱ ተላላኪዎች እነዚህንስ ምን ይሏቸው ይሆን?
የሚያሳዝነው የስርዓቱ ደጋፊዎች ይህን እውነታ ለመደበቅ መሞከራቸው ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ይህን ለመለወጥ ሲሰሩና ሲጥሩ አላሰራ ማለታቸው ነው:: በቅርቡ በየሃገራቱ ያሉት የኢትዮጵያ ኢምባሲዎች ያወጧቸውን መግለጫዎች ይጠቅሷል::
addis ababa
- See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/48367#sthash.OBLQJPQ9.dpuf

ወይ እነሱ ወይ እኔ ኢትዮጵያዊ አይደለንም” | በ4 ፖሊሶች የተደበደበው ሰው | ከያሬድ ሹመቴ


Yared

ካዛንቺስ ቶታት ፊትለፊት ጫጫ ኮርነር የተባለ ቤት በር ላይ የፒያሳ ታክሲ ለመያዝ ከምሽቱ 3:30 ገደማ በርካታ ሰዋች መሀል ቆሜያለሁ። 4 ፖሊሶች ደግሞ አለፍ ብለው ቆመዋል።

እድሜው ወደ 30ዋቹ መጨረሻ የሚሆነው አንድ ሰው በፌስታል የተቋጠረ ነገር ይዞ አቀርቅሮ ይጓዛል። ፖሊሶቹ አጠገብ ሲደርስ በመሀላቸው አቋረጠ። ከመሀላቸው ልጅ እግር የሆነው ፖሊስ ሰውየውን ጎትቶ ወደ ኋላ መለሰው።
“አቤት?” አላቸው ሰውየው።
“ለምንድነው በመሀላችን ያቋረጥከው?” አለው።
“አላየኋችሁም ይቅርታ”
“እንዴት አላየኋችሁም ትላለህ” አለው ሌላው
“ምን አጠፋው” ብሎ መለሰ
“ፖሊሶች እኮ ነን” አለው አንዱ
“ፖሊስ ማለት ህዝብ ነው” አለ ቆፍጠን ብሎ
“አንተማ ሌላ ተልዕኮ አለህ” ልጅ እግሩ ተናገረ።
“በስህተት በመሀላችሁ በማለፌ ነው ተልዕኮ ያለኝ?”

ታክሲ ለመሳፈር የተሰበሰበው ሰው ከንፈሩን እየመጠጠ ፖሊሶቹን በትዝብት ሲመለከት አንደኛው ፖሊስ “በቃ ና” ብሎ ወደፊት ጎትቶ ሲወስደው ሁሉም ተከተሉት።
ከፊት 2 ከኋላ 2 ሆነው ሰውየውን ይዘውት ሲሄዱ ታክሲ ተራው ላይ መቅረት አላስቻለኝም። ተከተልኳቸው። ከፊት ያሉት ሁለቱ ፖሊሶች እንደ ጓደኛ እያወሩት ይሄዳሉ። ወደ ፈንድቃ ባህል ምሽት ጋር ከመታጠፋቸው በፊት አንድ የብረት ፍርግርግ አጥር ያለው ጊቢ በር ከፍተው ገቡ። ኮምዩኒቲ ፖሊሲንግ የሚባል ቢሯቸው ነው።
የቢሮውን በር ከፍተው ሶስቱ ፖሊሶች ወደ ውስጥ ይዘውት ሲገቡ አንደኛው በረንዳው ላይ ቆሞ አካባቢውን ይቃኛል። እኔም እንዳያየኝ ካንትራት ታክሲ አስቁሜ ዋጋ መደራደር ጀመርኩ። ፖሊሱ ሰው አለማየቱን አረጋግጦ ወደ ውስጥ ሲገባ፥ ታክሲውን ይቅርታ ብዬው ወደ አጥሩ ተጠጋሁ።
የጊቢው አጥር እና ቢሮው ብዙም ርቀት የሌለው በመሆኑ በድንብ ይታያል። የበረንዳው መብራት እንደበራ ሲሆን ከፍተው የገቡትን ቢሮ መብራት አላበሩትም። ጨለማው ክፍል ውስጥ ሰውየው በመስኮቱ በኩል ከውጭ በሚገባው ብርሀን ይታየኛል።
ከመቅጽበት በሩ ተከፍቶ አንደኛው ፖሊስ ወደ ውጭ ወጣ። በረንዳው ላይ ቆሞ አላፊ አግዳሚውን መቃኘት ሲጀምር እኔም ታክሲ ጠባቂ መስዬ ቆምኩ። የሰውየውን ጩኸት ሰማሁት። የዱላ ድምጽ እና የሰውየው ጩኸት መንገደውኛውን ፊቱን ቢያስዞረውም ፖሊሱ አይኑ ፈጦ ሁሉንም ሰው ያይ ስለነበር ደፍሮ የቆመ የለም።
ጨለማ ቤት ውስጥ ለሚቀጠቀጠው ምስኪን ሰው አንጀቴ አረረ። ማድረግ የምችለው ነገር ምን እንደሆነ ጠፋኝ። የሰውየውም ድምጽ እና የዱላ ውርጂብኝ እየበረታ ሲሄድ አልቻልኩም። በፍጥነት ወደ 6ተኛ ፖሊስ ጣቢያ ሮጥኩ። የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ፖሊስ መምሪያ (6ተኛ) አሁን ካለሁበት ብዙም ርቀት የሌለው በመሆኑ በፍጥነት ደረስኩ።
ጨለማ የወረሰው ግቢ ውስጥ ተረኛ ጥበቃ ፖሊሶች አግኝቼ አዛዦች ካሉ ብዬ ጠየቅኩ። “ማንም የለም ለኛ ንገረን” አሉኝ “አይ ሀላፊ ነው የምፈልገው” አልኳቸው። ሀላፊዎች የሉም ግን የመረጃ ክፍል ሄደህ ማነጋገር ትችላለህ አሉኝና ቢሮውን አመላከቱኝ።
ጨለማውን ኮሪደር አልፌ አንደኛ ፎቅ ላይ ወደሚገኘው መረጃ ክፍል ደረስኩ። አንድ ፖሊስ ብቻውን በርካታ የራዲዮ መገናኛ የድምጽ መሳሪያዎች ፊቱ ተደርድረው አንድ መዝገብ ላይ የሆነ ነገር እየፃፈ አገኘሁት።
“አስቸኳይ ጥቆማ ለመስጠት ነው” አልኩት።
“ምን ልታዘዝ” አለኝ። ፖሊሱ በጣም ትሁት ነው። የሆነውን በሙሉ ነገርኩት። ተናደደ።

በሬዲዮው መገናኛ የተለያዩ ኮዶችን እየጠራ የፖሊሶቹን ማንነት ለማጣራት ሞከረ። ተረኛ የጣቢያ አዛዡን ሞባይል ስልክ ቁጥር ጠይቆ ደወለ።
“ሀሎ … የት ነው ያለኸው?… 26 ያሉት ለምንድነው ሰው የሚደበድቡት?… ሰዋች በአካል መጥተው አባሎች ሰው እየደበደቡ ነው ብለው እየተናገሩ ነው። ጠቋሚ ሰዋቹ ‘በመሀላችን ለምን አለፍክ ብለው ነው የሚደበድቡት’ ነው የሚሉኝ…ፈጥነህ ድረስ…ቦታው ላይ ሂድ። ሰውየው ካለ ወደ ቤቱ የሚሄድበትን ወይም ወደ ህግ የሚሄድበት ነገር አድርግ። ህግ ከጣሰም በህግ ነው መቀጣት ያለበት እንጂ እንዴት በዱላ ይቀጣል?… እንደሰው አያስቡም እንዴ? ለምን አትነግሯቸውም? ሰው ለምን በመሀል አለፍክ ተብሎ ይደበደባል?…

…በባህላችን በሰው መሀል እንደማይታለፍ አስተምረኸው ታልፋለህ እንጂ ሰውን በዱላ ነው እንዴ የምታስተምረው?… እኔ ጋር ነው ያሉት የጠቆሙኝ ሰዋች… ምን?…ለምንድነው ወዳንተ ጋር የምልካቸው?… ወዳንተ ልኬ ደግሞ ልታስደበድባቸው ነው? ቶሎ ሂድና ያለውን ውጤት እኔ ጋር መጥተህ ንገረኝ።” ስልኩን ዘጋውና አመስግኖ አሰናበተኝ።
የሰውየው ነገር መጨረሻ አሳስቦኛል። እንደገና በሩጫ ትቼው ወደ ሄድኩት የኮምዩኒቲ ፖሊሲን ቢሮ አቅጣጫ ሄድኩኝ። መታጠፊያው አካባቢ ስደርስ ይህ ሰው እያነከሰ እና እየተንፏቀቀ ወደ እኔ አቅጣጫ ሲመጣ አየሁት። ያለቅሳል” ወይኔ” እያለ ግንባሩን ይደበድባል። “አይዞህ” አልኩት። “እባክህ ደግፈኝና 6ተኛ ፖሊስ ጣቢያ አድርሰኝ” አለኝ። የሆነውን በሙሉ እንዳየሁ ነገርኩትና ደግፌው ወደ ጣቢያው በድጋሚ ሄድኩ።
ፖሊስ ጣቢያው ጊቢ ውስጥ እንደገባን ሰውየው የቢሮው በረንዳ ላይ ተቀመጦ ለቅሶ እና የህመም ሲቃውን ቀጠለ። እኔን ያስተናገደኝ ፖሊስ እና የደወለለት ፖሊስ ተከታትለው መጡ። የሰውየውን ስም ጠየቁት “ዘላለም” አለ እያለቀሰ።
ዘላለም ብሶቱን በእንባ እና በለቅሶ መናገር ጀመረ።” “እኔ እኮ የተከተልኳቸው የናንተን ልብስ ስለለበሱ ነው። የፖሊስ ልብስ ባይለብሱ ኖሮ ጨለማ ክፍል ውስጥ ተከትያቸው እገባ ነበር? ህግ ቦታ እየወሰዱኝ ነው ብዬ ነው አምኜ የተከተልኳቸው። ምን አደረግኳቸው? ምን በደልኳቸው? አያውቁኝ! አላስቀይምኳቸው። ምን በድዬ ነው ምን አጠፋሁ ባልኩ የሚሰባብሩኝ?” እንባውን እየዘረገፈ ሲቃ እየተናነቀው ሲናገር ሀይለኛ ቁጣ እና ሀዘን ሆዴ ውስጥ ዘልቆ ገብቶ ጉሮሮዬን ሳግ ተናነቀኝ።
“ምን አድርጌ ነው። ለልጄ ልብስ እና ጫማ ገዝቼላት እንቅልፏን ሳትተኛ ልድረስ ብዬ ስሮጥ ጠልፈው ይቀጥቅጡኝ?!። እግዚአብሔር ፍርድ ይሰጣል እኔ ምንም አልልም እንባዬን እሱ ያብሰዋል። ምንም መናገር አልችልም ሌላ።”
ፖሊሶቹ የተመታውን እንዲያሳያቸው ባትሪ ወደ እግሩ አበሩ። ግራ እግሩ ክፉኛ አብጧል። እንባው እንደጎርፍ እየወረደ ለቅሶውን ቀጥሎ እያነከሰ ከተቀመጠበት ተነሳ። ፖሊሶቹ ነገ መጥተህ ክስ መስርት አሉት።
“እኔ ክሴ ለእግዜር ነው። እሱ ፍርድ ይስጥ። ብቻ ወይ እነሱ ወይ እኔ ኢትዮጵያዊ አይደለንም። አንዳችን ሀገር ክደናል። አይ ኢትዮጵያ! የፖሊስ ልብስ ለብሰዋል ብዬ ተከትዬ ስደበደብ እውነት ሀገር አለኝ እላለሁ? ነገም አልመጣም እናንተ ከሰማችሁኝ ይበቃኛል። ምን ፍርድ አገኛለሁ ብዬ ነው?” እንባውን እየጠራረገ ወደ ቤቱ ለመሄድ እያነከሰ መራመድ ጀመረ። ፖሊሶቹ ስልኩን ተቀበሉት። በነጋታው እንዲመጣ ቢለምኑትም ምንም ፍትህ ተስፋ እንደማያረግ ነግሯቸው እንባውን እያዘራ መሄድ ጀመረ። ከፖሊሶቹ ጋር ተሰናብቼ ደግፌው አብረን መሄድ ጀመርን።
ግማሽ መንገድ ሸኘሁት። “ወይ እነሱ ወይ እኔ ኢትዮጵያዊ አይደለንም” የሚለውን ቃል እየደጋገመ እንባውን እያፈሰሰ ወደ ቤቱ በእየተሳበ ሄደ።
፡።።።
ሀቀኛ ፖሊሶች ካላችሁ ልብሳችሁን አስከብሩ።
።።።።

እነዚህን 4 ፖሊሶች በህግ ተጠያቂ ይሆኑ ዘንድ ይህንን መልዕክት Share በማድረግ ሀላፊነትዎን ይወጡ።
።።።።
ዘላለምን ግን ቸር አምላክ ምህረቱን ያውርድለት።

- See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/48550#sthash.7hi3bZbP.dpuf

Monday, November 16, 2015

እነሃብታሙ አያሌው ላይ የተጠየቀው ይግባኝ “ያስቀርባል” ተባለ * ፍርድ ቤት ቀርበው ሊከራከሩ ነው


  • 32
     
    Share
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
አቃቤ ህግ የሽብርተኝነት ክስ መስርቶባቸው በፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ እንዲሰናበቱ ተበይኖላቸው በነበሩት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች ላይ አቃቤ ህግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት የጠየቀው ይግባኝ ያስቀርባል ተባለ፡፡

habitamu
































ዛሬ ህዳር 6/2008 ዓ.ም ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በእነ ሀብታሙ አያሌው ላይ የተጠየቀውን ይግባኝ መዝገቡን መመርመሩን በመግለጽ ዝርዝር ሁኔታውን በንባብ ሳያሰማ በአጭሩ፣ ‹‹ይግባኙ ያስቀርባል ብለናል›› ብሏል፡፡
በመሆኑም ይግባኝ የተጠየቀባቸው ተከሳሾች ሀብታሙ አያሌው፣ የሺዋስ አሰፋ፣ አብርሃ ደስታ፣ ዳንኤል ሺበሺ እና አብርሃም ሰለሞን በቀረበባቸው ይግባኝ ላይ በአካል ቀርበው የቃል ክርክር ለማድረግ ለህዳር 29/2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል፡፡
የስር ፍርድ ቤት በነጻ እንዲሰናበቱ ቢበይንም፣ ሁሉም ተከሳሾች አሁንም ድረስ በእስር ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡

- See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/48292#sthash.3uFP26vX.dpuf

አውሮፓዊያኑ የ1.8 ቢሊዮን ዩሮ እርዳታ ስደተኛን ለመቀነስ ወይንስ ለማብዛት?


  • 540
     
    Share
ከተማ ዋቅጅራ 
የአውሮፓ ህብረት በማልታ ቫልታ ከተማ ላይ በስደተኛ ዙሪያ ከአፍሪካ መሪዎች ጋር ስብሰባ አድርገው ነበረ። አውሮፓዊያኑ በያዝነው አመት ታይቶ  በማይታወቅ ሁኔታ በስደተኞች በመጥለቅለቃቸው ስጋት የፈጠረባቸው ጉዳይ በመሆኑ ከአፍሪካ መንግስታት ጋር በስደተኛ ዙሪያ ተወያይተው ነበረ። እውን የአውሮፓ ህብረት መንግስታቶች እንዳሰቡት ለአንባ ገነኖች ለአፍሪካ መሪዎች የገንዘብ እርዳታ በማድረጋቸው ስደተኛን ወደ አውሮፓ መፍለሱን ያስቆሙት ይሆንን?
video-migrant-boat-capsizes-near-italy-leaving-200-people-in-the-sea
የአውሮፓ ህብረት 1.8 ቢሊዮን ብር ወጪ እናደርጋለን በማለታቸው ለአፍሪካ መሪዎች ልገሳ በማድረግ ስደተኞችን እናስቆማለን ብለው የተናገሩት ሃሳብ የአፍሪካ መሪዎች ወደግል ካዝናቸው በመክተት እና የጦር መሳሪያ በመግዛት ለአፈና ስራ በማዋል ስደተኛው የበለጠ እንዲሰደድ ከማድረግ ውጪ የሚፈይደው  አንዳች ነገር እንደሌለ ጠንቅቀን እናውቀዋለን። ለግዜው ስለ ሌሎች አፍሪካ አገር ተወት እናድርገውና በአውሮፓ ህብረቱ ስብሰባ እና የገንዘብ እርዳታ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ስላለው አንድምታ እንመልከት። የኢትዮጵያ ችግር የተወሳሰበ ነው። ያወሳሰበውም ወያኔ ነው። የአውሮፓ መንግስታትም ሆኑ የአሜሪካ  እንዲሁም ያደጉት አገራት የሚባሉት ሊያዩት ያልቻሉት ከፍተኛ የሆነ ችግር በኢትዮጵያ ውስጥ አለ። ይሄንን ግፍና ችግር በኢትዮጵያኑ ላይ የሚደርስ ስለሆነ በአገራችን መኖር ባለመቻላችን ለስደት እንዳረጋለ። ይሄም የወያኔ አንባ ገነን ገዢዎች  የሚፈጥሩት የከፋ ችግር ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት ስለ ዲሞክራሲአዊ አሰራር ሰርቶ አያውቅም። ስለ ህዝብ ነጻነት ሰርቶ አያውቅም። ስለ አገር አንድነት እና ሰላም ሰርቶም አያውቅም። ለምዕራባዊያኖቹ ፎቆችን እና መንገዶችን እንዲሁም አንድ አንድ ነገሮችን በማሳየት በዲሞክራሲ መንገድ እየሰራው ስለሆነ ኢትዮጵያ እያደገች እንደሆነች በማስመሰል ምዕራባዊያኑን ቢያታልላቸውም ቅሉ ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ በጥቂት የወያኔ ጉሩፖች ተይዘው ህዝባችንን ለከፋ ችግር እያጋለጡ እንደሆነ አልተረዱትም። ለዚህም የአውሮፓዊያኑ መንግስታት የኢትዮጵያን ህዝብ ችግር ከማስወገድ ይልቅ ከችግር ፈጣሪ አንባ ገነን መሪዎች ጋር በመስራት አቅማቸውን በማሳደግ አንባ ገነኖቹ ወደ ከፋ  አንባ ገነንነት ስለሚሸጋገሩ በደሉን እና ግፉን መቋቋም የማይችለው ህዝብ ለስደት የሚዳረጉት በእጥፍ ከማሳደግ ውጪ የሚፈይደው ነገር እንደሌላ እናውቃለን።
ሁሉም ሰው በአገሩ በሰላም መስራት እና መኖር ከቻለ ስደትን የሚመርጥ አለ ብዬ መናገር አልችልም። እንደ ስደት በጣም አስቀያሚ ነገር የለም። ሁሉም ነገር በተወለድክበት በኖርክበት በአገር ሲሆን ደስ ይላል። አንባ ገነኖች በሚፈጥሩት ግፍ ግን ሳንወድ በግድ ስደትን እንመርጣለን። ስደተኛ ርሃብተኛ አይደለም። ስደተኛ ያልተማረ  አይደለም። ስደተኛ መኖሪያ የሌለው ቤት አልባም አይደለም። ስደተኛው ሁሉ ነገር ኖሮትና ተርፎት በአገሩ በሰላም መኖር የሚያስችል መንግስት ባለመኖሩ ሰላምዊ ኑሮን ፍለጋ የተሰደደ እንጂ።
ዛሬ ስደተኛ ብለን የናቅናቸው እና በግድ እንመልሳቸው እና ለንባ ገነን መሪዎች አሳልፈን እንስጥ ብላችሁ ስብሰባ የተሰበሰባችሁባቸው እኮ ትላንትና የአፍሪካው አባት የሚባሉት እና የአለም የኖቤል ሽልማት ተሸላሚ የሆኑት ኔልሰን ማንዴላ ስደተኘ ነበሩ። ትላንትና እኮ  በአለም ህብረተሰብ ተወዳጅ ተቀባይነት የነበራቸው ኖርዌይን በመርዳት የሚታወቁት ጀርመንን በመርዳት የሚታወቁት ጀማይካኖች በፍቅር የሚወዷቸው የአፍሪካ ህብረትን መስራች የሆኑት ኢትዮጵያዊው መሪ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስደተኛ ነበሩ። በአለማችን ላይ ተጽእኖ ፈጣሪ እና በእውቀጣቸው ከአለም ጥቂት ሰዎች መሃል የነበረው በአለም መንግስታት ዘንድ ቁጥር አንድ ተፈላጊ የነበረው በናሳ ሳይንቲስት ዘርፍ ከፍተኛ ስልጣን የነበረው ኢትዮጵያዊው ሳይንቲስት ቅጣው እጅጉ ስደተኛ ነበረ። ዛሬም በአለማችን ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ እንዲሁም አለማችንን ወደ ተሻለ አቅጣጫ ሊለውጧት ይችላሉ ከተባሉት አስር የአለማችን ተመራማሪዎች ሁለቱ ኢትዮጵያዊ ወንድማማቾች ስደተኞች ናቸው። በስደት ያሉት ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያን ለውጠው ከአገር አልፈው አለምን ጉድ ሊያሰኙ የሚችሉ ልጆች እንዳላት እናውቃለን። ኢትዮጵያን በአጭር ግዜ ውስጥ መለወጥ የሚችሉ የኢትዮጵያ ልጆች ግን በአንባ ገነን መሪ ጫና በሰላም መኖር ስላልቻሉ ብቻ ከአገር ተሰደው ይኖራሉ። በአገር መኖርን ጠልተው አልያም የኢኮኖሚ ስደተኞች ሆነው ሳይሆን ሰላምን ባለማግኘታቸው ነው የተሰደዱት። ዛሬም አገራቸውን እየናፈቁ እርቀው ያሉ በመቶ  ሺ የሚቆጠሩ ሙህራኖች አሏት ሳይንቲስቶች፣ ፕሮፌሰሮች፣ ዶክተሮች፣ ኢንጅነሮች፣ ወዘተ….።
Mediterranean-troubles
የኢትዮጵያ መንግስት ከአውሮፓ መንግስታት በሚረዳው ገንዘብ የህዝቡን ኑሮ  የመለወጥ ስራ የሚሰራ ሳይሆን  በንግስናው  የሚቆይበትን ነገር በመቀየስ ህዝባችንን የሚያፍንበት  የጦር መሳሪያ በመግዛት ወታደራዊ ኃይሉን እያደራጀ ህዝብን በማፈን ዲሞክራሲ የሚባል ነገር ከአገር ወደ ማጥፋቱ ተግባር እየሄደ ባለበት ሰዓት የአውሮፓዊያኑ መንግስታት ለእንደዚ አይነቱ አንባ ገነን መንግስት ብር መርዳት ማለት የኢትዮጵያን ዘጠና ሚሊዮን ህዝብ ለስደት መዳረግ እንዳይሆንባቸው በጥልቀት ቢያስቡ መልካም ይመስለኛል።
አውሮፓዊያኑ ማድረግ ያለባቸው ከአንባ ገነኖች ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማቋረጥ ጥቂት በስልጣን ላይ ላሉ ሰዎች እርዳታን ከመርዳት ይልቅ ዘላቂ መፍትሄ የሚኖረው የህብረተሰቡን የሰላም ጥያቄ ሊመለስ በሚችልበት ጉዳይ ላይ ቢያተኩሩ ኢትዮጵያ  ብሎም አፍሪካ ወደ ሰላም እና ወደ እድገት ጎዳና በማምጣት ህዝቦቿን በሰላም እጦት ከመሰደድ ሊታደጓቸው ይችሉ ነበር።
ስደተኖችን በግድ አሳልፎ  ለአንባ ገነኖች መሪ መስጠት ክቡር በሆነው በሰው ህይወት ላይ ቁማር እንደመጫወት ይቆጠራል። ስለዚህ በታላላቅ ቦታ ያላችሁ የኢትዮጵያ ልጆች በግድ ለወያኔ መንግስት ተላልፎ የሚሰጠው ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ህይወቱ አደጋ ላይ እንዳለ አውቃችሁ የበኩላችሁን ነገር እንድታደርጉ አሳስባለው።
ሌላው እና ወሳኙ ሁኔታ  አውሮፓዊያኑ ጥሬ ገንዘብ ለአንባ ገነኖች ከመርዳት ይልቅ ልትረዱት ባሰባችሁት የብር መጠን ሃምሳ ሺ ይሁን መቶ  ሺ ሰው ሃይል ሊሰራበት የሚችልበትን ፋብሪካ ብትከፍበት ህዝባችንን ልትጠቅሙት ትችሉ ይሆናል እንጂ በጥሬ ገንዘብ የምትሰጡት እርዳታ  የኢትዮጵያን ህዝብ ጭቆናው እንዲበዛበት በማድረግ ሃገሩን ጥሎ  የሚሰደደው ህዝብ ከእጥፍ በላይ ታበዙታላችሁ።
- See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/48262#sthash.6DJZ3Dpg.dpuf

ድርቅ ርሃብና ችጋር ምንና ምን ናቸው? ኢትዮጵያስ ለምን የርሀብ ሀገር ሆነች? | ፈቃደ ሸዋቀና


  • 95
     
    Share
ሀገራችን መሬት ላይ እንድ ሌላ ግዙፍ የርሀብና የችጋር ዳመና እያንዣበበ ነው። አንዳንድ ቦታም ግዳይ መጣል መጀመሩን እየሰማን ነው። ይህ ችግር በሰብዓዊ ዕውቀትና ሀይል የሚፈታ ሆኖ ለምንድነው እንዲህ እየተመላለሰ የሚጎበኘን? ሌሎች ሀገሮች ተመሳሳይ የአየር ሁኔታ ችግር እየገጠማቸው እንደኛ ለአዋራጅ ጉስቁልናና ልመና አልተዳረጉም። እኛ ጋ ምን የተሰወረብን ነገር አለ? የአፍሪካ የውሀ ሰገነት የምትባልና ከማንም የማይተናነስ የተፈጥሮ ጸጋ ያላት ሀገር ይዘን ለምን እንደዚህ አይነት ሕዝብ ሆንን? በጅጉ የሚደንቅ ነገር ብቻ ሳይሆን በንዴት የሚያቃጥል ነገር ነው። እንደሚመስለኝ ችግሩን የልፈታንበት አንዱ ምክንያት ተገቢና የበሰለ ውይይት የማናካሂድ ህዝብ መሆናችንና ይህንንም ለማድረግ የመወያያና መፍትሄ ፍለጋ ሁኔታ እንዳይፈጠር መንግስታቱ ተጠያቂነትን ለማምለጥ ሲሉ የሚፈጥሩት እንቅፋትነት ይመስለኛል። እስከመቼ በዚህ ውርደት እንደምንቀጥል ባሰብኩ ቁጥር የሚያመኝን ህመም ችዬ ነው ይህን ለውይይት የሚሆን ጽሁፍ የጻፍኩት። 
fekade shewakena
ከላይ በርዕሱ ላይ ያነሳኋቸውን ቃላት ብዙ ሰዎች በተለዋዋጭነት ሲጠቀሙባቸው መስማት ያልተለመደ ነገር አይደለም። ችጋርን ወይም ሰፊ መጠን ያለውን የሀገራችንን ርሀብ ድርቅ እያሉ የሚጠሩ ሰዎች ብዙ ናቸው። ርሀብና ችጋርንም እንደዚሁ የሚያደበላልቁ ሰዎች ብዙ ናቸው። ዝቅ ብዬ ለማሳየት እንደምሞክረው ድርቅ የምንለው የአየር ባህርይ ርሀብና ችጋር ብለን ከምንጠራቸው ነገሮች ጋር በመሰረቱ የመንስዔና የውጤትም ሆነ ሌላ የተፈጥሮ (structural) ተዛምዶ የለውም። ይህንን በቅጡ ለመረዳት የቃሎቹን ቀጥተኛና ቴክኒካል ትርጉም የያዙትንም ጽንሰ ሀሳብ በቅጡ መለየት ያስፈልጋል። በዚህ ላይ ይህን የሚያረጋግጡ በርካታ የአለማችንን ተመክሮ መመልከት ይጠቅማል።
ድርቅ (Drought) ባንድ አካባቢና ባንድ ወቅት ባልተለመደ ሁኔታ የሚደርስን የዝናብ መጥፋት ወይም መጠን መዛባት የሚገልጽ ቃል ነው። ከሰው ቁጥጥር ውጭ የሆነ የአየር ሁኔታንና የአየር ሁኔታን ብቻ የሚገልጽ ሀሳብ ነው ማለት ነው። ርሀብ (Hunger) በምግብ አለመብቃት ምክንያት ሰዎች የምግብ ፍላጎታቸው ሳይሟላ ቀርቶ ውሎ ለማደር ብቻ ምግብ የሚያገኙበት አልፎ አልፎም በምግብ ችግር ምክንያት ለሞት የሚዳረጉበት ሁኔታ ነው። ችጋር (Famine) ሰዎች የሚላስ የሚቀመስ ምግብና ውሀ በማጣት አካላቸው እያለቀ ሄዶ በብዙ ቁጥር (mass) ለዕልቂት የሚዳረጉበት ሁኔታ ነው። ድርቅ በመሰረቱ ከርሀብም ሆነ ከችጋር ጋር ተፈጥሮአዊ ዝምድና  የለውም ብያለሁ።  በሌላ አነጋገር ድርቅ የርሀብም የችጋርም የተፈጥሮ ምክንያት አይደለም።  በምግብ ራስን ለመቻልና በችጋርም ሆነ በርሀብ ላለመጠቃት የግድ እህል አምራች ሀገር መሆንም ላያስፈልግ ይችላል። ሌላ ነገር ሰርተው ምግባቸውን ከውጭ ገዝተው የሚኖሩ ሀገሮች እሉ። ስለዚህ ድርቅና ኤል ኒኖ የርሀብ ምንጭ ነው የሚለው ልፈፋ ሌላ የጎላ ስሕተትና የችግሩን ዕውነተኛ መንስዔ መሸፈኛ ሆኖ እያገለገለ ነው።  እንዲያ ቢሆን ኤል ኒኖና ድርቅ አገር እየመረጡ ችጋርና ርሀብ አያመጡም ነበር።
ድርቅ የተፈጥሮ ሁኔታ ስለሆነ ለመከላከልም አይቻልም።  ችጋርና ርሀብ ሰው በጥረቱ ሊከላከላቸውና ሊያጠፋቸው የሚችሉ ነገሮች ናቸው። ብዙ ሀገሮች ይህን በማድረጋቸው ከኛ የበለጠ ድርቅ እየመታቸው እንኳን ችጋርም ርሀብም አይነካቸውም። እድግመዋለሁ ድርቅ የርሀብና የችጋር የተፈጥሮ ምክንያት አይደለም። ይህን የሚሉ ሰዎች ወይ አውቀው እውነተኛውን ችግር መሸፈን የሚፈልጉ ወይ አገላብጦ ማየት የተሳናቸው የዋሆች ናቸው። አንድ ሰው ናላው እስኪዞር ድረስ አልኮል ጠጥቶ ሰክሮ መኪና ሲነዳ ተጋጭቶ ወይም ገደል ገብቶ ቢሞት የሞቱን ምክንያት በደፈናው የመኪና አድጋ ነው ብሎ መሸፋፈን እውነት እንዳልሆነ ሁሉ በኛም ሀገር እየተደጋገመ የሚደርሰውን ርሀብና ችጋር በኤል ኒኖና በድርቅ ማመካኘት ዕውነት አይደለም። ሌላው ቀርቶ ችጋርንና አደገኛ ርሀብን በጊዜ በመለመን ማስቀረት ይቻላል።    በሀገራችን የስከዛሬዎቹን ችጋሮች ጥፋት መቀነስ ወይም ማስወገድ ያልተቻለው መንግስታቱ ክብራቸው ወይም ሊፈጥሩ የፈለጉት ገጽታ የተበላሸ እየመሰላቸው ችግሩን በመደበቃቸውም  ነው። ባሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣኖች ለርዳታ ሰጭዎች የሚያቀርቡትን አንዴ ራሳችንን ስለቻልን ራሳችን እንወጣዋለን ሌላ ጊዜ ደግሞ ርዳታ ስጡን የሚሉ የተምታቱ መልዕክቶችን አሁን ሀገሪቱ ውስጥ ግዳይ መጣል ከጀመረው ርሀብ ጋር ስናስተያየው ከዚሁ በባዶ ቤት የአክብሩኝ ባይነት የመግደርደርና የመደባበቅ ተግባር ብዙ አለመራቃችንን ያሳያል። የኢትዮጵያ ሹማምንት ነጋ ጠባ በሚቲዮር ፍጥነት ኢኮኖሚ አሳደግን ሲሉን የነበረው ፕሮፓጋንዳና ኢኮኖሚው አንድ የድርቅ ወቅት የሚያሻግር አቅም የሌለው  ሆኖ መገኘት እንዳሳፈራቸው በግልጽ ይታያል። ይህ እንዳይሆን ቀድሞ ነበር ስታቲስቲክሱን አልሞ መደቆስ የነበረባቸው።  ለመሆኑ አንድ አስርት ሙሉ በሚያስጎመጅና አለም እይቶት በማያውቅ መጠን ሲያድግ የነበረ ግብርና እንዴት ያንድ በልግና መኸር ዝናብ ችግር መሻገር ኣቃተው? አለም ለዚህ ጥያቄ መልስ እየፈለገ ይመስለኛል። እስካሁን ለዚህ ጥያቄ መልስ የሰጠ ሹም ግን አላየሁም።
ችጋር በድርቅ ሳይሆን ሰዎች በተለይም መንግስታት አስበው መስራት ያለባቸውን ስራ በዕውቀትና በትጋት ባለመስራታቸው ወይም በተለያየ ምክንያት ትክክለኛ ፖሊሲ ለመከተል ባለመፈለጋቸው  የሚመጣ አደጋ ነው።  እዚህ ላይ ከባህል ጋር የተያያዙ ሌሎች ሊለወጡ የሚገባቸውና የሚችሉ ምክንያቶችን መጨመር ይቻል ይሆናል። በአለም ዙሪያ በብዙ መጠንና በተደጋጋሚ ማየት እንደምንችለው ሰዎች  ምግባቸውን ባግባቡ የማያሟሉባቸው ሀገሮች  የተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚገፉ ወይም አፈናና አድሎ የበዛባቸው ፣ ማናለብኝነትና አምባገነናዊ ፖለቲካ ስርዓት የሰፈነባቸው ፣ ማህበራዊ ግጭቶችን በውይይት ከመፍታት ይልቅ መጨፍለቅ በሚያበዙ ወይም ሙስና በሚፈጥረው ቀውስና ብልሹ አስተዳደር የተበከሉ የህግ ልዕልና የሌለባቸው ናቸው። እውሮፓና አሜሪካ ውስጥ ብዙ ጊዜ ትልልቅ ድርቅ ይከሰት እንጂ  ሰው ተርቦ ሞተ ሲባል የማንሰማው ዴሞክራሲያዊና ግልጽነት የሰፈነበት ስርዓት ስላላቸውና መንግስት ልሒቃኑና  ተቋማቱ ከነፖለቲካ ልዩነታቸው ካለምንም ይሉኝታና መፎጋገር ስለመጭው ዘመን ተጨንቀው ስለሚያስቡ ስለሚወያዩና ስለሚያቅዱ ነው።
የኢትዮጵያ ባለስልጣኖች የቀድሞዎቹም ያሁኖችም ድርቅን የርሀብና የችጋር ምክንያት አድርገው ራሳቸውን ነጻ ለማድረግ በሚያደርጉት ሀሰተኛ  ጥረት በጣም ይመሳሰላሉ።  የቀድሞዎቹን መንግስታት ህዝብ በማስራብና ለችጋር በመዳረግ የሚከሱት የዛሬዎቹ መሪዎች አሁን ሀገሪቱን የገጠማትን የርሃብና የችጋር አደጋ ልክ እንደቀድሞዎቹ በድርቅ በተለይ በፈረደበት ኤል ኒኖ ማመካኘቱን ተያይዘውታል። ኤል ኒኖ ከችጋር ጋር ዝምድና ያለው ስራቸውን ባግባቡ ባልሰሩ ሀገሮች እንደሆነ እንድናውቅ አይፈልጉም። በነሱ ቤት አንድም የፖሊሲም ሆነ የሀገር አስተዳደር ምክንያት የለበትም። የችግሩ መንስዔ የግብርና ፖሊሲ ፣ ያጠቃላይ የኢኮኖሚ ወይም የመሬት ይዞታ ፖሊሲ ወይስ የዴሞክራሲ ችግር  ብሎ ሰው እንዲጠይቅና መልስ እንዲፈልግ አይፈልጉም።
አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ አንድ የዲያስፖራዎች (ይህ ዲያስፖራ የሚል ቃል ሲያስጠላኝ) ነው በተባለ ስብሰባ ላይ በድርቅ ምክንያት ካሊፎርኒያና አውስትራሊያም እየተሰቃዩ ነው ሲሉ ወዶ አይስቁ ሳቅ እየሳኩ ስምቻቸዋለሁ። እኛ ሀገር ላይ የተለየ ነገር አልመጣም እያሉ መዋሸታቸው ነበር። እኝህ ሰውዬ እንዴት ምስክር አይኖርም ብለው እንደገመቱ በጣም ነው የገረመኝ። እኔ ራሴ  ድርቁ በገነነበት ባለፈው ስፕሪንግ ካሊፎርኒያ  ሳን  ፍራንሲስኮ ኦክላንድና ሳን ሆዜ አካባቢ ነበርኩ።  ጆግራፈር ስለሆንኩ ለንደዚህ አይነት ጆግራፊያዊ ክስተት መመልከቻ ትልቅ አይን አለኝ። ሁኔታውን  ስራዬ ብዬ ነበር ለማየት የሞከርኩት። ብዙ የደረቀ ሳርና ቅጠል ብዙ ቦታ አይቻለሁ።  አፈሩም ብዙ ርጥበት እንዳልነበረው አይቻለሁ።  አቶ ሀይለማሪያም የሚያወሩት ስቃይ ግን በቦታው አልነበረም። ለመኪና ማጠቢያ ውሀ አራርቆ መጠቀምን ፥ የጓሮ አትከልት ዉሀ ቆጥቦ ማጠጣትን ፥ ቧንቧ የሚያወርደው ውሀ ቀጠን እንዲል ማድረግንና ሌሎች የውሀ ቁጠባ ስራዎችን ሰቃይ ነው ካላሉ በስተቀር ስቃይ አልነበረም። ብዙ ያካበቢው ነዋሪ ድርቅ መኖሩን እንኩዋን የማያውቅ አለ። ካለኝ መረጃ አውስትራሊያም  ስቃይ ሊባል የሚችል ነገር አልነበረም። በነገራችን ላይ አቶ ሀይለማሪያም ስለ ካሊፎርኒያና አውስትራሊያም በድርቅ መሰቃየት ሲናገሩ ያጨበጨቡት ዲያስፖራዎች በጅጉ አስገርመውኛል። ጭብጨባቸውን ስሰማ አቅለሽልሾኝ ነበር ብዬ ዕውነቱን ልናገር መሰለኝ። ቪዲዮውን ያላያችሁ እዩትና የገባችሁ ካላችሁ የጭብጨባውን ትርጉም ንገሩኝ። የድርቅ ስቃያችን ከካሊፎርኒያና ከአውስትራሊያ ጋር ይመሳሰላል ስለተባለ ሀገራችን እኩል ሆነች ብለው መደሰታቸው ይሆን? ቁጥሩ ይህን የሚያህል ገልቱ ዲያስፖራ ያለ አይመስለኝም ነበር።
ወደተነሳሁበት ነገር ልመለስ። ድርቅ የምክንያት ርሀብና ችጋር  የውጤት ግንኙነት እንዳላቸው እያደረግን የምንለፍፈው ወሬ ከደረቅ ውሸትነቱ አለፎ ለስንፍና የሚዳርግ አደገኛ  ነገርም ነው። ተፈጥሮን (ድርቅን) መቆጣጠር ስለማንችል ድርቅ በመጣ ቁጥር ለሚመጣው ርሐብና ችጋር እጅ እየሰጠንና እየለመንን ከመኖር ሌላ ምርጫ የለንም ወደሚል አደገኛ ድምዳሜ ይወስደናል። ለሀገሩ የሚቆረቆር ማንኛውም ቅን ኢትዮጵያዊ የሀገራችን የርሀብ ምንጭ ድርቅና ኤል ኒኖ ነው  የሚለውን ሀሰት የማታለያ ፕሮፓጋንዳ መቀበል ቀርቶ ለመስማት ፈቃደኛ ሊሆን አይገባም። ባለስልጣናትም ይህን ውሸት በመደጋገም ካለባቸው ሀላፊነት እንዲሸሹ ልንፈቅድላቸው አይገባም። ይህ የችግሩ መፍቻ የመጀመሪያ ርማጃ ይመስላኛል።
ግጥጥ ያለው ዕውነት ግን እንዲህ ነው። የኖቤል ሎሬቱን አመርትያ ሴንን የመሳሰሉ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች እንደሚነግሩን ዴሞክራሲ ባለበት ቦታ ሁሉ ርሀብና ችጋር የለም። ችጋርና ሰፊ ህዝብ የሚሸፍን ርሀብ በአንድ ሀገር ውስጥ የዴሞክራሲና ነጻ ማህበረሰብ አለመኖር ውጤት ናቸው። ዴሞክራሲ ባለበት ሀገር እንደልብ በሚካሄድ ክርክር የሀሳብ አማራጮች ይፈልቃሉ። አምባገነኖች ህዝብ የሚጠቅምና ርሀብ ጭራሽ የሚያስወግድም ቢሆን እንኳን ስልጣናቸውን የሚፈታተን ከሆነ ርሃብና ችጋሩን ይመርጣሉ። ነጻ ውይይትና ክርክር ስልጣንና ፖሊሲ የሚጠይቅ ስለሆነ ይህንን እንድንወያይ አይፈልጉም። በኢትዮጵያ የመሬት ይዞታን ፖሊሲ ህዝብ አይከራከርበትም። ሀገሬውን የመንግስት ጭሰኛ ያደረገ ፖሊሲ በኔ እምነት ርሀብተኛ ሀገር ለመሆናችን አንድ ምክንያት ይመስለኛል። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ይህ ነገር ከተቀየረ የሚቀየረው በመቃብራችን ላይ ነው ነበር ያሉት። የገበሬው የይዞታ ባለቤትነት ርግጠኝነት አለመኖር ፣ የግለሰብ ይዞታዎች ከጊዜ ጊዜ እየተቆራረሱ ማነስ ፣ በርሻ መሬት ላይ ያለውን የሰው ብዛትና ግፊት ለመቀነስ የሚያስችል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ባግባቡ አለመዘርጋት ከብዙ ጥቂቶቹ የሀገራችን የርሀብና የችጋር ምክንያቶች ይመስሉኛል። ተገቢና ስራ ላይ ባግባቡ መዋል የነበረበትን የብሔረሰቦች የእኩልነት ጥያቄ ወደ በለጠ ልዩነትና ሰዎችና ካፒታል ብሄረሰብ ሳይመርጡ እንዳይዘዋወሩ የሚያደርገው ፖለቲካ ሁኔታ ችጋር ይፈለፍል እንደሆነ እንጂ ብልጽግና አያመጣም። አነስተኛ ገበሬዎችን በገፍ እያፈናቀሉ ለውጭ ሀገር ቱጃር መሬት መሸንሸን ችግርና ርሀብ ያፈላ እንደሆን እንጂ የማንንም ችግር ሲያስወግድ አልታየም። ሀገርን ለዜጎቿ ሳይሆን ለባዕዳን መስሕብ በማድረግ የዳበረና ችግር ያስወገደ ሀገር የለም። ይህን ማረም የማይችል መንግስት ርሃባችንን በኤል ኒኖ ሲያመካኝ ማፈር አለበት።  በነዚህና እነዚህን በመሳሰሉ ማነቆዎች ላይ በግልጽና በቅንነት ተወያይተን መፍትሄ ካላበጀን ርሀብና ችጋር በየጊዜው የሚጎበኙን የውርደት ሀገር ሆነን መኖራችን ይቀጥላል።
የሀገራችንን ባለስልጣኖች አስመልክቶ በጣም የሚያስተዛዝበው የርሀቡ ደረጃ ለምን ባደባባይ ተዘገበ በማለት ባለማቀፍ ሚዲያዎች ላይ  የሚያካሂዱት ቡራ ከረዩ ነው።  የሚዲያው የርሀቡን አስከፊነት በስፋት መዘገብ ልመና ለማቀላጠፍ ይረዳ እንደሆን እንጂ ጉዳት የለውም። ቡራ ከረዩው ሀገርና ህዝብ ተጎዳ በሚል ሳይሆን በብዙ  ቅባት ያሳመርነው ገጽታ ለምን ይነካል ነው።  ሰሞኑን ቢቢሲ ያቀረበውን ዘገባ አስመልክቶ የመንግስት ሹሞችና ደጋፊዎች የሚያደርጉት ያዙኝ ልቀቁኝ በጣም አስገራሚም አስተዛዛቢም ነው። በካሜራ ላይ ሰለባዎች እየተናገሩ ያካሄዱትን ዘገባ በምን ምክንያት ነው የምናወግዘው? ለንደን ያለው ኤምባሲ የሚለው ቢያጣ የርሀቡን አስከፊነት አስመልክቶ ቢቢሲ ባቀረበው ዘገባ ላይ በሰጠው የተቃውሞ መልስ ቢቢሲ ርሀቡን ያመጣው ኤል ኒኖ ነው የሚለውን የመንግስት ውሸት ደግሞ ባለማለቱ አጥብቆ ይከሳል። እንዲህ ይላል። “The report also failed to give perspective on the drought situation currently unfolding in Ethiopia and around the world and how it is triggered by the El Nino phenomenon”. የዚች አረፍተ ነገር ቁም ነገር ችግሩን ያመጣብን ኤል ኔኖ ስለሆነ ምንግስታችን አይጠየቅም የምትል ነች። ተጠያቂነትን ማምለጫ ብልጠት መሆኗ ነው። ኤል ኒኖ ሀገር እየለየ ነው እንዴ ጥቃት የሚያደርሰው? አስር ዐመት ሙሉ ግብርና ከሁለት ዲጂት በላይ ያደገባትን ሀገር ከቀርፋፋዎቹ እንዴት እድርጎ እንደመረጣት ግራ የገባው ታዛቢ ታዲያ ምን ይበል?
በኔ አመለካከት ከዚህ በአለም ፊት በተደጋጋሚ ካዋረደንና እያዋረደን ካለ ርሀብና ችጋር መገላገል የምንችለው በችግሩ ዙሪያ በግልጽ በመወያየት ነው። የስካሁኑን ተመክሯችንና መረጃዎቻችንን ይዘን በግልጽ እንወያይ። ይህ የወገንተኛ ፖለቲካ ጉዳይ አይደለም። የህልውና ጉዳይ ነው። ወደ ዝርዝር ምክንያቱ እንግባ ካልን በመንግስት ላይ ብቻ በማመካኘት የምንገላገለውም አይደለም። እንደ ህዝብ ያሉብንም ባህላችን ውስጥ የተዋቀሩና ለችግሩ የዳረጉን ብዙ ችግሮች አሉ። በሀገራችን ይህን ሁላችንም የምንወያይበት ዴሞክራሲያዊ መድረክ ያስፈልገናል። ለመፍትሄውም ፍለጋ ሆነ ያገኘነውን የመፍትሔ ሀሳብ ስራ ላይ ለማዋል ዲሞክራሲ የግድ እንደሚያስፈልገን ግን ብዙ መከራከር ያለብን አይመስለኝም። ይህን ማድረግ ካልቻልን የሚቀጥለው ቸነፈር ጊዜም ይህንኑ እያወራን በውርደታችን ለመቀጠል ተስማምተናል ማለት ነው።
- See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/48281#sthash.IqzUP3RP.dpuf