Thursday, November 12, 2015

“መልካም አስተዳደርን እውን ለማድረግ ድክመትንና ስህተትን ከመቀበል ያለፈ እርምጃን ይጠይቃል” – ሸንጎ


  • 114
     
    Share
shengo
በአለፉት ቀናቶች በልዩ ልዩ የሚዲያ ዘርፎች ሲስተናገድና ትችት ሲሰነዘርበት የከረመው ጉዳይ በቅርቡ የወያኔ/ኢሕአዴግ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ስለመልካም አስተዳደርና ተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር ለመቀራረብ ፍላጎት እንዳላቸው በሰጡት መግለጫ ዙሪያ ነበር። ትልቁ የአንድነት ሀይሎች ስብስብ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ ጉዳዩን ተከታትሎና ሊያስከትል የሚችለውን ጥቅምና ጉዳት በመመርመር የሚከተለውን አቋም ወስዷል።

በአገሪቱና በሕዝቡ ላይ የደረሰው በደል ተጠራቅሞ ወሳኝ ደረጃ ላይ በመድረሱ የተነሳ መንግስት እራሱ በአስተዳደሩ ውስጥ የሚታዩ ጉድለቶችን የሚያጠና የባለሙያዎች ቡድን ለማቋቋም ተገዷል።ሸንጎ በመንግስት የተቋቋመው ቡድን ሰፊ ጥናት አድርጎ ያቀረበውን ዘገባ ይፋ በማውጣቱ ነቀፋና ተቃውሞ ባይኖረውም የተደረሰበት ጥናትና የቀረበው ሃሳብ በተግባር መገለጽ እንዳለበት ፣ያ ካልሆነ ግን ለይስሙላና ለማደናገሪያ ብሎም ጊዜ መግዣና ተቃውሞን ለማለሳለስ የተደረገ እርምጃ ሆኖ እንደሚቀር ከወዲሁ ለማሳሰብ ይወዳል።
አሁን አገዛዙ በይፋ ያወጣው ውስጣዊ ድክመት ሸንጎና የተቃዋሚው ጎራ ላለፉት ዓመታት እያነሱና እያጋለጡ ሲታገሉበት የነበረ ፣ ሕዝቡም በአንክሮ የሚያሰማው ብሶት በመሆኑ በስልጣን ላይ ያለው አካል ጥፋቱንና ድክመቱን ከማመን ሌላ አማራጭ ስላላገኘ ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም በተወሰነ ደረጃ ያለበትን ውስጣዊ ድክመት ለመቀበል ተገዷል።እዚህ ላይ መቀበል ማለት መፍትሔ መሻትና በተግባር መግለጽ እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል።

ፎቶ ምንጭ: ሪፖርተር ጋዜጣ
ፎቶ ምንጭ: ሪፖርተር ጋዜጣ
ሆኖም ግን አይኔን ግንባር ያድርገው ወይም የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ ከሚለው የተለመደ የክህደት አቋም የተለዬ በመሆኑ አንድ እርምጃ ወደፊት የመሄድ ያህል ይቆጠራል።ጥናቱ ሁሉንም ከመልካም አስተዳደር ጋር የተዛመደ ጉዳይ በተለይም በፖለቲካው ዙሪያ ያለውን መጠነ ሰፊና ዘግናኝ በደል የሚያነሳ ባይሆንም በአገልግሎት ዘርፍ፣በኢንቨስትመንት በመሬት ይዞታና ስርጭት፣በቀረጥና ግብር አሰባሰብ ዙሪያ ስርአቱ የሚስተናገደውንና ከላይ እስከታች የተንሰራፋውን የሙስና ሰንሰለትና ንቅዘት የሚያጋልጥ ነው።
በፍትህና አስተዳደር ዙሪያም ላይ ያሉትን ድክመቶች እጅግ በተወሰነ መልኩ ነካ ነካ አድርጓል።ጥናቱ ተጠናቆ የመንግስት ተጠሪዎች ጋር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባካሄዱት ውይይት ላይ እንደታየው የጥናቱ ደጋፊዎች የቀረበው ጥናት ሁሉንም ያካተተ አለመሆኑንና እንደውቅያኖስ ጥልቀትና ስፋት ካለው ችግርና የመንግስት አሰራር ጉድለት ውስጥ በማንኪያ የተጨለፈ ነው በማለት ይበልጥ በቀሩት ጉዳዮች ላይ ጥናቱ እንዲቀጥል ሲናገሩ አንዳንዶቹ ደግሞ የጥናቱ ሰለባ የመሆን እድል የሸተታቸው ይመስላሉ የቀረበው ጥናት በማስረጃ የተደገፈ አይደለም በማለት ለማጣጣልና ደግሞ እንደተለመደው ሁሉ ለመሸፋፈን ሲሞክሩ ተሰምተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመደምደሚያ ሃሳባቸው እያንዳንዳቸው የመንግስት ባለስልጣኖች የችግሩ ምንጭና ባለቤቶች መሆናቸውን ”ችግሩን የፈጠርነው እኛው ነን፤እራሳችን ልዩ ልዩ የጥቅም ሰንሰለቶች ስላሉን እነሱ እንዳይፈርሱብን ወይም እንዳይነኩ አሁን በስብሰባ ላይ የተነጋገርነውንና የተስማማንበትን ጉዳይ ከስብሰባው ስንወጣ በተግባር እንዳይገለጽ አናደርጋለን” በማለት ስርዓቱና የስርዓቱ ተጠሪዎች ለደረሰው ጥፋትና ውድቀት ተጠያቂ መሆናቸውን አምነዋል።አቶ ሃይለማርያም እንዳሉት ባለስልጣኖቹ በተለመደው አሰራራቸውና የግል ጥቅማቸው ውድድር ከቀጠሉበት አንድ ቀርቶ አስር ጥናት ቢካሄድ ለውጥ አይመጣም። ይህ ደግሞ የሀገራችንን ሀብት የጥቂቶች መደለቢያ ከማድረግም አልፎ ሀገራችን፤ ህዝባችንና መጭውም ትውልድ ለዘመናት ወደማይወጡት አዘቅት እንዲያመሩ ያደርጋል።
ከተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመስራትም ያለው ፍላጎት ከቃላት አልፎ እውነት የሚሆነው በስበብ ባስባቡ ካለምንም ማስረጃ በእስርቤት የታጎሩት ጋዜጠኞች፣የፖለቲካ ድርጅት ተጠሪዎችና ደጋፊዎች ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ተለቀው በፖለቲካ እንቅስቃሴያቸው፣እምነታቸውና በሙያቸው ላይ ካለምንም ተጽእኖ ለመስራት የሚችሉበት ሁኔታ ሲፈጠር ነው።ያ በተግባር ሳይታይ፣ሕዝብ የሚያምናቸውና የሚከተላቸው እውነተኛ የተቃዋሚ ድርጅቶችን ጠፍንጎና አሸብሮ፣በሰርጎ ገብ አዳክሞ፣ በቃላት ብቻ ከተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር ሰላም እፈጥራለሁ፣ለለውጥ ተዘጋጅቻለሁ ብሎ መናገርና ጥናት ማዥጎድጎድ፣ በተቃዋሚ ድርጅቶች ስም ለስርዓቱ ቅርበትና አድናቆት ያላቸውን ቡድኖች ሰብስቦ መወያየትም የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት አይደለም። አንድ እርምጃ ወደፊት ሁለት እርምጃ ወደዃላ ይሆንና በጥፋት ላይ ጥፋት እየተቆለለ አገር አፍራሽ ሱናሚ ይሆናል።
ሸንጎ አሁን በአገሪቱ ውስጥ የሚታየው መጠነ ሰፊ ስብራት፣በመንግስት ባለስልጣኖች ዙሪያ የሚታየው አይን ያወጣ ዘረፋ፣ የጥቅም ሽኩቻና የእርስ በርስ አለመተማመን የአጠቃላዩ የስርዓቱ ብልሽት ውጤት እንደሆነ ያምናል።ይህም በአገሪቱና በሕዝቡ ላይ የደረሰው ችግርና ስብራት ለዘለቄታው ሊወገድ የሚችለው የጥፋቱ ተጠያቂ የሆነው መንግስት አንዳንድ ለውጥ አድርጎ በስልጣን ላይ በመቆየቱ ሳይሆን፤ የፖለቲካ ምህዳሩ ሰፍቶ በልዩልዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ተሳትፎና ነጻ የሕዝብ ምርጫ የመንግስት ለውጥ ሲመጣ ብቻ ነው። ወደዚህ የሚወስደውን ጎዳና ለማመቻቸት ደግሞ እስካሁን እንቅፋት የሆኑትን ጉዳዮች ነቅሶ በማውጣት እንዳይደገሙ ለማድረግ የሚያስችል ግልጽና ሰፊ አገራዊ መግባባትንና ብሄራዊ እርቅን ተጋባራዊ ማድረግን ይጠይቃል። ለዚያም ሸንጎ ይታገላል።
በአገሪቱ የሚታየው የመልካም አስተዳደር እጦት በአገልግሎትና በመሬት ባለቤትነትና በሀብት ዝርፊያ ዙሪያ ላይ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በሰባዊ ና ዴሞክራሲ መብቶች ፣ በአገሪቱ አንድነትና በሕግ የበላይነት፣በተቃዋሚ ሃይሎች ድርሻ፣ የተሳትፎና የመንቀሳቀስ መብት ዙሪያ ጭምር ነው። መልካም አስተዳደርን እውን ለማድረግ ከቃላት አልፎ የሚታየው የመንግስት እረገጣ ተወግዶ በተግባር መታየት ይኖርበታል።
መልካም አስተዳደርን እውን ለማድረግ የፍትህ አካሉ ከመንግስት ጫና ነፃ መሆን ይኖርበታል። ለህዝብ መብት ተሟጋች የሆኑ የሲቪክ ድርጅቶችን ለማፈንና ለማገድ የወጣው ህግና የአሸባሪነት ህግ ህዝቡ እንዳይናገርና እንዳይደራጅ የሚያግዱ በመሆናቸው መሰረዝ አለባቸው። ያለ ህዝብና ሲቪክ ድርጅቶች ነፃ ተሳትፎ የኢህአዴግን ያህል በሙስና የነቀዘና በጎሳ የተዋቀረ ስርዓት ማስተካከልና ድክመቶቹን ማስወገድ በፍፁም አይቻልም። ይህን ሁሉ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ሙሉ ለሙሉ ይፈጽመዋል ባይባልም በውስጡ ያሉና የያዙት መንገድ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ የተረዱ ባለስልጣኖችና ደጋፊዎች ሰልፋቸውን ከሕዝቡ ጋር እንዲያስተካክሉ ሸንጎ ጥሪና ምክር ያቀርብላቸዋል።
የተለያዩ ተቃዋሚ ድርጅቶችም መንግስት አምኖ የተቀበለውን ጥፋትና ድክመት ተሸክሞ እንዳይቀጥልበት ሃይላቸውን አስተባብረው በሀገራችን አንድነት ስር ለስርዓት ለውጥ ሕዝቡን ለማደራጀት ቆርጠው መነሳት ይኖርባቸዋል። የለውጥ መስኮት ከተከፈተ ያንን ቀዳዳ በር ለማድረግ አንድ ላይ ተባብረው ሊታገሉ ይገባል። በመንግስት አካሄድና ስልት ላይ በጋራ መወያየትና መልስ ሊሰጡበት ይገባል።እንዳለፈው ጊዜ በራሳቸው ጠባብ ድንኳን ወይም የፖለቲካ ገዳም ውስጥ መሽጎ መቀመጥን ከመረጡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የችግሩ ተጠያቂዎች ይሆናሉ። ላለውም ስርዓት ቀጣይነት አስተዋጽኦ ማድረግ ይሆናል። ስለሆነም በተከሰተው ሁኔታና በአገሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ ከሁሉም ያገባኛል ባይ ድርጅት ግለሰብና ስብስብ ጋር በየትኛውም ቦታና ወቅት ለመወያየት ሸንጎ ዝግጁና ፈቃደኛ መሆኑን ይገልጻል።
ለሰላማዊ ሕዝባዊ የትግል እንቅስቃሴና ለውጥ እንነሳ!
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ

- See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/48192#sthash.nK7ZUwCx.dpuf

No comments:

Post a Comment