ሀገራችን መሬት ላይ እንድ ሌላ ግዙፍ የርሀብና የችጋር ዳመና እያንዣበበ ነው። አንዳንድ ቦታም ግዳይ መጣል መጀመሩን እየሰማን ነው። ይህ ችግር በሰብዓዊ ዕውቀትና ሀይል የሚፈታ ሆኖ ለምንድነው እንዲህ እየተመላለሰ የሚጎበኘን? ሌሎች ሀገሮች ተመሳሳይ የአየር ሁኔታ ችግር እየገጠማቸው እንደኛ ለአዋራጅ ጉስቁልናና ልመና አልተዳረጉም። እኛ ጋ ምን የተሰወረብን ነገር አለ? የአፍሪካ የውሀ ሰገነት የምትባልና ከማንም የማይተናነስ የተፈጥሮ ጸጋ ያላት ሀገር ይዘን ለምን እንደዚህ አይነት ሕዝብ ሆንን? በጅጉ የሚደንቅ ነገር ብቻ ሳይሆን በንዴት የሚያቃጥል ነገር ነው። እንደሚመስለኝ ችግሩን የልፈታንበት አንዱ ምክንያት ተገቢና የበሰለ ውይይት የማናካሂድ ህዝብ መሆናችንና ይህንንም ለማድረግ የመወያያና መፍትሄ ፍለጋ ሁኔታ እንዳይፈጠር መንግስታቱ ተጠያቂነትን ለማምለጥ ሲሉ የሚፈጥሩት እንቅፋትነት ይመስለኛል። እስከመቼ በዚህ ውርደት እንደምንቀጥል ባሰብኩ ቁጥር የሚያመኝን ህመም ችዬ ነው ይህን ለውይይት የሚሆን ጽሁፍ የጻፍኩት።
ከላይ በርዕሱ ላይ ያነሳኋቸውን ቃላት ብዙ ሰዎች በተለዋዋጭነት ሲጠቀሙባቸው መስማት ያልተለመደ ነገር አይደለም። ችጋርን ወይም ሰፊ መጠን ያለውን የሀገራችንን ርሀብ ድርቅ እያሉ የሚጠሩ ሰዎች ብዙ ናቸው። ርሀብና ችጋርንም እንደዚሁ የሚያደበላልቁ ሰዎች ብዙ ናቸው። ዝቅ ብዬ ለማሳየት እንደምሞክረው ድርቅ የምንለው የአየር ባህርይ ርሀብና ችጋር ብለን ከምንጠራቸው ነገሮች ጋር በመሰረቱ የመንስዔና የውጤትም ሆነ ሌላ የተፈጥሮ (structural) ተዛምዶ የለውም። ይህንን በቅጡ ለመረዳት የቃሎቹን ቀጥተኛና ቴክኒካል ትርጉም የያዙትንም ጽንሰ ሀሳብ በቅጡ መለየት ያስፈልጋል። በዚህ ላይ ይህን የሚያረጋግጡ በርካታ የአለማችንን ተመክሮ መመልከት ይጠቅማል።
ድርቅ (Drought) ባንድ አካባቢና ባንድ ወቅት ባልተለመደ ሁኔታ የሚደርስን የዝናብ መጥፋት ወይም መጠን መዛባት የሚገልጽ ቃል ነው። ከሰው ቁጥጥር ውጭ የሆነ የአየር ሁኔታንና የአየር ሁኔታን ብቻ የሚገልጽ ሀሳብ ነው ማለት ነው። ርሀብ (Hunger) በምግብ አለመብቃት ምክንያት ሰዎች የምግብ ፍላጎታቸው ሳይሟላ ቀርቶ ውሎ ለማደር ብቻ ምግብ የሚያገኙበት አልፎ አልፎም በምግብ ችግር ምክንያት ለሞት የሚዳረጉበት ሁኔታ ነው። ችጋር (Famine) ሰዎች የሚላስ የሚቀመስ ምግብና ውሀ በማጣት አካላቸው እያለቀ ሄዶ በብዙ ቁጥር (mass) ለዕልቂት የሚዳረጉበት ሁኔታ ነው። ድርቅ በመሰረቱ ከርሀብም ሆነ ከችጋር ጋር ተፈጥሮአዊ ዝምድና የለውም ብያለሁ። በሌላ አነጋገር ድርቅ የርሀብም የችጋርም የተፈጥሮ ምክንያት አይደለም። በምግብ ራስን ለመቻልና በችጋርም ሆነ በርሀብ ላለመጠቃት የግድ እህል አምራች ሀገር መሆንም ላያስፈልግ ይችላል። ሌላ ነገር ሰርተው ምግባቸውን ከውጭ ገዝተው የሚኖሩ ሀገሮች እሉ። ስለዚህ ድርቅና ኤል ኒኖ የርሀብ ምንጭ ነው የሚለው ልፈፋ ሌላ የጎላ ስሕተትና የችግሩን ዕውነተኛ መንስዔ መሸፈኛ ሆኖ እያገለገለ ነው። እንዲያ ቢሆን ኤል ኒኖና ድርቅ አገር እየመረጡ ችጋርና ርሀብ አያመጡም ነበር።
ድርቅ የተፈጥሮ ሁኔታ ስለሆነ ለመከላከልም አይቻልም። ችጋርና ርሀብ ሰው በጥረቱ ሊከላከላቸውና ሊያጠፋቸው የሚችሉ ነገሮች ናቸው። ብዙ ሀገሮች ይህን በማድረጋቸው ከኛ የበለጠ ድርቅ እየመታቸው እንኳን ችጋርም ርሀብም አይነካቸውም። እድግመዋለሁ ድርቅ የርሀብና የችጋር የተፈጥሮ ምክንያት አይደለም። ይህን የሚሉ ሰዎች ወይ አውቀው እውነተኛውን ችግር መሸፈን የሚፈልጉ ወይ አገላብጦ ማየት የተሳናቸው የዋሆች ናቸው። አንድ ሰው ናላው እስኪዞር ድረስ አልኮል ጠጥቶ ሰክሮ መኪና ሲነዳ ተጋጭቶ ወይም ገደል ገብቶ ቢሞት የሞቱን ምክንያት በደፈናው የመኪና አድጋ ነው ብሎ መሸፋፈን እውነት እንዳልሆነ ሁሉ በኛም ሀገር እየተደጋገመ የሚደርሰውን ርሀብና ችጋር በኤል ኒኖና በድርቅ ማመካኘት ዕውነት አይደለም። ሌላው ቀርቶ ችጋርንና አደገኛ ርሀብን በጊዜ በመለመን ማስቀረት ይቻላል። በሀገራችን የስከዛሬዎቹን ችጋሮች ጥፋት መቀነስ ወይም ማስወገድ ያልተቻለው መንግስታቱ ክብራቸው ወይም ሊፈጥሩ የፈለጉት ገጽታ የተበላሸ እየመሰላቸው ችግሩን በመደበቃቸውም ነው። ባሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣኖች ለርዳታ ሰጭዎች የሚያቀርቡትን አንዴ ራሳችንን ስለቻልን ራሳችን እንወጣዋለን ሌላ ጊዜ ደግሞ ርዳታ ስጡን የሚሉ የተምታቱ መልዕክቶችን አሁን ሀገሪቱ ውስጥ ግዳይ መጣል ከጀመረው ርሀብ ጋር ስናስተያየው ከዚሁ በባዶ ቤት የአክብሩኝ ባይነት የመግደርደርና የመደባበቅ ተግባር ብዙ አለመራቃችንን ያሳያል። የኢትዮጵያ ሹማምንት ነጋ ጠባ በሚቲዮር ፍጥነት ኢኮኖሚ አሳደግን ሲሉን የነበረው ፕሮፓጋንዳና ኢኮኖሚው አንድ የድርቅ ወቅት የሚያሻግር አቅም የሌለው ሆኖ መገኘት እንዳሳፈራቸው በግልጽ ይታያል። ይህ እንዳይሆን ቀድሞ ነበር ስታቲስቲክሱን አልሞ መደቆስ የነበረባቸው። ለመሆኑ አንድ አስርት ሙሉ በሚያስጎመጅና አለም እይቶት በማያውቅ መጠን ሲያድግ የነበረ ግብርና እንዴት ያንድ በልግና መኸር ዝናብ ችግር መሻገር ኣቃተው? አለም ለዚህ ጥያቄ መልስ እየፈለገ ይመስለኛል። እስካሁን ለዚህ ጥያቄ መልስ የሰጠ ሹም ግን አላየሁም።
ችጋር በድርቅ ሳይሆን ሰዎች በተለይም መንግስታት አስበው መስራት ያለባቸውን ስራ በዕውቀትና በትጋት ባለመስራታቸው ወይም በተለያየ ምክንያት ትክክለኛ ፖሊሲ ለመከተል ባለመፈለጋቸው የሚመጣ አደጋ ነው። እዚህ ላይ ከባህል ጋር የተያያዙ ሌሎች ሊለወጡ የሚገባቸውና የሚችሉ ምክንያቶችን መጨመር ይቻል ይሆናል። በአለም ዙሪያ በብዙ መጠንና በተደጋጋሚ ማየት እንደምንችለው ሰዎች ምግባቸውን ባግባቡ የማያሟሉባቸው ሀገሮች የተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚገፉ ወይም አፈናና አድሎ የበዛባቸው ፣ ማናለብኝነትና አምባገነናዊ ፖለቲካ ስርዓት የሰፈነባቸው ፣ ማህበራዊ ግጭቶችን በውይይት ከመፍታት ይልቅ መጨፍለቅ በሚያበዙ ወይም ሙስና በሚፈጥረው ቀውስና ብልሹ አስተዳደር የተበከሉ የህግ ልዕልና የሌለባቸው ናቸው። እውሮፓና አሜሪካ ውስጥ ብዙ ጊዜ ትልልቅ ድርቅ ይከሰት እንጂ ሰው ተርቦ ሞተ ሲባል የማንሰማው ዴሞክራሲያዊና ግልጽነት የሰፈነበት ስርዓት ስላላቸውና መንግስት ልሒቃኑና ተቋማቱ ከነፖለቲካ ልዩነታቸው ካለምንም ይሉኝታና መፎጋገር ስለመጭው ዘመን ተጨንቀው ስለሚያስቡ ስለሚወያዩና ስለሚያቅዱ ነው።
የኢትዮጵያ ባለስልጣኖች የቀድሞዎቹም ያሁኖችም ድርቅን የርሀብና የችጋር ምክንያት አድርገው ራሳቸውን ነጻ ለማድረግ በሚያደርጉት ሀሰተኛ ጥረት በጣም ይመሳሰላሉ። የቀድሞዎቹን መንግስታት ህዝብ በማስራብና ለችጋር በመዳረግ የሚከሱት የዛሬዎቹ መሪዎች አሁን ሀገሪቱን የገጠማትን የርሃብና የችጋር አደጋ ልክ እንደቀድሞዎቹ በድርቅ በተለይ በፈረደበት ኤል ኒኖ ማመካኘቱን ተያይዘውታል። ኤል ኒኖ ከችጋር ጋር ዝምድና ያለው ስራቸውን ባግባቡ ባልሰሩ ሀገሮች እንደሆነ እንድናውቅ አይፈልጉም። በነሱ ቤት አንድም የፖሊሲም ሆነ የሀገር አስተዳደር ምክንያት የለበትም። የችግሩ መንስዔ የግብርና ፖሊሲ ፣ ያጠቃላይ የኢኮኖሚ ወይም የመሬት ይዞታ ፖሊሲ ወይስ የዴሞክራሲ ችግር ብሎ ሰው እንዲጠይቅና መልስ እንዲፈልግ አይፈልጉም።
አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ አንድ የዲያስፖራዎች (ይህ ዲያስፖራ የሚል ቃል ሲያስጠላኝ) ነው በተባለ ስብሰባ ላይ በድርቅ ምክንያት ካሊፎርኒያና አውስትራሊያም እየተሰቃዩ ነው ሲሉ ወዶ አይስቁ ሳቅ እየሳኩ ስምቻቸዋለሁ። እኛ ሀገር ላይ የተለየ ነገር አልመጣም እያሉ መዋሸታቸው ነበር። እኝህ ሰውዬ እንዴት ምስክር አይኖርም ብለው እንደገመቱ በጣም ነው የገረመኝ። እኔ ራሴ ድርቁ በገነነበት ባለፈው ስፕሪንግ ካሊፎርኒያ ሳን ፍራንሲስኮ ኦክላንድና ሳን ሆዜ አካባቢ ነበርኩ። ጆግራፈር ስለሆንኩ ለንደዚህ አይነት ጆግራፊያዊ ክስተት መመልከቻ ትልቅ አይን አለኝ። ሁኔታውን ስራዬ ብዬ ነበር ለማየት የሞከርኩት። ብዙ የደረቀ ሳርና ቅጠል ብዙ ቦታ አይቻለሁ። አፈሩም ብዙ ርጥበት እንዳልነበረው አይቻለሁ። አቶ ሀይለማሪያም የሚያወሩት ስቃይ ግን በቦታው አልነበረም። ለመኪና ማጠቢያ ውሀ አራርቆ መጠቀምን ፥ የጓሮ አትከልት ዉሀ ቆጥቦ ማጠጣትን ፥ ቧንቧ የሚያወርደው ውሀ ቀጠን እንዲል ማድረግንና ሌሎች የውሀ ቁጠባ ስራዎችን ሰቃይ ነው ካላሉ በስተቀር ስቃይ አልነበረም። ብዙ ያካበቢው ነዋሪ ድርቅ መኖሩን እንኩዋን የማያውቅ አለ። ካለኝ መረጃ አውስትራሊያም ስቃይ ሊባል የሚችል ነገር አልነበረም። በነገራችን ላይ አቶ ሀይለማሪያም ስለ ካሊፎርኒያና አውስትራሊያም በድርቅ መሰቃየት ሲናገሩ ያጨበጨቡት ዲያስፖራዎች በጅጉ አስገርመውኛል። ጭብጨባቸውን ስሰማ አቅለሽልሾኝ ነበር ብዬ ዕውነቱን ልናገር መሰለኝ። ቪዲዮውን ያላያችሁ እዩትና የገባችሁ ካላችሁ የጭብጨባውን ትርጉም ንገሩኝ። የድርቅ ስቃያችን ከካሊፎርኒያና ከአውስትራሊያ ጋር ይመሳሰላል ስለተባለ ሀገራችን እኩል ሆነች ብለው መደሰታቸው ይሆን? ቁጥሩ ይህን የሚያህል ገልቱ ዲያስፖራ ያለ አይመስለኝም ነበር።
ወደተነሳሁበት ነገር ልመለስ። ድርቅ የምክንያት ርሀብና ችጋር የውጤት ግንኙነት እንዳላቸው እያደረግን የምንለፍፈው ወሬ ከደረቅ ውሸትነቱ አለፎ ለስንፍና የሚዳርግ አደገኛ ነገርም ነው። ተፈጥሮን (ድርቅን) መቆጣጠር ስለማንችል ድርቅ በመጣ ቁጥር ለሚመጣው ርሐብና ችጋር እጅ እየሰጠንና እየለመንን ከመኖር ሌላ ምርጫ የለንም ወደሚል አደገኛ ድምዳሜ ይወስደናል። ለሀገሩ የሚቆረቆር ማንኛውም ቅን ኢትዮጵያዊ የሀገራችን የርሀብ ምንጭ ድርቅና ኤል ኒኖ ነው የሚለውን ሀሰት የማታለያ ፕሮፓጋንዳ መቀበል ቀርቶ ለመስማት ፈቃደኛ ሊሆን አይገባም። ባለስልጣናትም ይህን ውሸት በመደጋገም ካለባቸው ሀላፊነት እንዲሸሹ ልንፈቅድላቸው አይገባም። ይህ የችግሩ መፍቻ የመጀመሪያ ርማጃ ይመስላኛል።
ግጥጥ ያለው ዕውነት ግን እንዲህ ነው። የኖቤል ሎሬቱን አመርትያ ሴንን የመሳሰሉ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች እንደሚነግሩን ዴሞክራሲ ባለበት ቦታ ሁሉ ርሀብና ችጋር የለም። ችጋርና ሰፊ ህዝብ የሚሸፍን ርሀብ በአንድ ሀገር ውስጥ የዴሞክራሲና ነጻ ማህበረሰብ አለመኖር ውጤት ናቸው። ዴሞክራሲ ባለበት ሀገር እንደልብ በሚካሄድ ክርክር የሀሳብ አማራጮች ይፈልቃሉ። አምባገነኖች ህዝብ የሚጠቅምና ርሀብ ጭራሽ የሚያስወግድም ቢሆን እንኳን ስልጣናቸውን የሚፈታተን ከሆነ ርሃብና ችጋሩን ይመርጣሉ። ነጻ ውይይትና ክርክር ስልጣንና ፖሊሲ የሚጠይቅ ስለሆነ ይህንን እንድንወያይ አይፈልጉም። በኢትዮጵያ የመሬት ይዞታን ፖሊሲ ህዝብ አይከራከርበትም። ሀገሬውን የመንግስት ጭሰኛ ያደረገ ፖሊሲ በኔ እምነት ርሀብተኛ ሀገር ለመሆናችን አንድ ምክንያት ይመስለኛል። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ይህ ነገር ከተቀየረ የሚቀየረው በመቃብራችን ላይ ነው ነበር ያሉት። የገበሬው የይዞታ ባለቤትነት ርግጠኝነት አለመኖር ፣ የግለሰብ ይዞታዎች ከጊዜ ጊዜ እየተቆራረሱ ማነስ ፣ በርሻ መሬት ላይ ያለውን የሰው ብዛትና ግፊት ለመቀነስ የሚያስችል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ባግባቡ አለመዘርጋት ከብዙ ጥቂቶቹ የሀገራችን የርሀብና የችጋር ምክንያቶች ይመስሉኛል። ተገቢና ስራ ላይ ባግባቡ መዋል የነበረበትን የብሔረሰቦች የእኩልነት ጥያቄ ወደ በለጠ ልዩነትና ሰዎችና ካፒታል ብሄረሰብ ሳይመርጡ እንዳይዘዋወሩ የሚያደርገው ፖለቲካ ሁኔታ ችጋር ይፈለፍል እንደሆነ እንጂ ብልጽግና አያመጣም። አነስተኛ ገበሬዎችን በገፍ እያፈናቀሉ ለውጭ ሀገር ቱጃር መሬት መሸንሸን ችግርና ርሀብ ያፈላ እንደሆን እንጂ የማንንም ችግር ሲያስወግድ አልታየም። ሀገርን ለዜጎቿ ሳይሆን ለባዕዳን መስሕብ በማድረግ የዳበረና ችግር ያስወገደ ሀገር የለም። ይህን ማረም የማይችል መንግስት ርሃባችንን በኤል ኒኖ ሲያመካኝ ማፈር አለበት። በነዚህና እነዚህን በመሳሰሉ ማነቆዎች ላይ በግልጽና በቅንነት ተወያይተን መፍትሄ ካላበጀን ርሀብና ችጋር በየጊዜው የሚጎበኙን የውርደት ሀገር ሆነን መኖራችን ይቀጥላል።
የሀገራችንን ባለስልጣኖች አስመልክቶ በጣም የሚያስተዛዝበው የርሀቡ ደረጃ ለምን ባደባባይ ተዘገበ በማለት ባለማቀፍ ሚዲያዎች ላይ የሚያካሂዱት ቡራ ከረዩ ነው። የሚዲያው የርሀቡን አስከፊነት በስፋት መዘገብ ልመና ለማቀላጠፍ ይረዳ እንደሆን እንጂ ጉዳት የለውም። ቡራ ከረዩው ሀገርና ህዝብ ተጎዳ በሚል ሳይሆን በብዙ ቅባት ያሳመርነው ገጽታ ለምን ይነካል ነው። ሰሞኑን ቢቢሲ ያቀረበውን ዘገባ አስመልክቶ የመንግስት ሹሞችና ደጋፊዎች የሚያደርጉት ያዙኝ ልቀቁኝ በጣም አስገራሚም አስተዛዛቢም ነው። በካሜራ ላይ ሰለባዎች እየተናገሩ ያካሄዱትን ዘገባ በምን ምክንያት ነው የምናወግዘው? ለንደን ያለው ኤምባሲ የሚለው ቢያጣ የርሀቡን አስከፊነት አስመልክቶ ቢቢሲ ባቀረበው ዘገባ ላይ በሰጠው የተቃውሞ መልስ ቢቢሲ ርሀቡን ያመጣው ኤል ኒኖ ነው የሚለውን የመንግስት ውሸት ደግሞ ባለማለቱ አጥብቆ ይከሳል። እንዲህ ይላል። “The report also failed to give perspective on the drought situation currently unfolding in Ethiopia and around the world and how it is triggered by the El Nino phenomenon”. የዚች አረፍተ ነገር ቁም ነገር ችግሩን ያመጣብን ኤል ኔኖ ስለሆነ ምንግስታችን አይጠየቅም የምትል ነች። ተጠያቂነትን ማምለጫ ብልጠት መሆኗ ነው። ኤል ኒኖ ሀገር እየለየ ነው እንዴ ጥቃት የሚያደርሰው? አስር ዐመት ሙሉ ግብርና ከሁለት ዲጂት በላይ ያደገባትን ሀገር ከቀርፋፋዎቹ እንዴት እድርጎ እንደመረጣት ግራ የገባው ታዛቢ ታዲያ ምን ይበል?
በኔ አመለካከት ከዚህ በአለም ፊት በተደጋጋሚ ካዋረደንና እያዋረደን ካለ ርሀብና ችጋር መገላገል የምንችለው በችግሩ ዙሪያ በግልጽ በመወያየት ነው። የስካሁኑን ተመክሯችንና መረጃዎቻችንን ይዘን በግልጽ እንወያይ። ይህ የወገንተኛ ፖለቲካ ጉዳይ አይደለም። የህልውና ጉዳይ ነው። ወደ ዝርዝር ምክንያቱ እንግባ ካልን በመንግስት ላይ ብቻ በማመካኘት የምንገላገለውም አይደለም። እንደ ህዝብ ያሉብንም ባህላችን ውስጥ የተዋቀሩና ለችግሩ የዳረጉን ብዙ ችግሮች አሉ። በሀገራችን ይህን ሁላችንም የምንወያይበት ዴሞክራሲያዊ መድረክ ያስፈልገናል። ለመፍትሄውም ፍለጋ ሆነ ያገኘነውን የመፍትሔ ሀሳብ ስራ ላይ ለማዋል ዲሞክራሲ የግድ እንደሚያስፈልገን ግን ብዙ መከራከር ያለብን አይመስለኝም። ይህን ማድረግ ካልቻልን የሚቀጥለው ቸነፈር ጊዜም ይህንኑ እያወራን በውርደታችን ለመቀጠል ተስማምተናል ማለት ነው።
- See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/48281#sthash.IqzUP3RP.dpuf
No comments:
Post a Comment