ርዕሰ ዜና
– ኖርዌይ የፖለቲካ ጥገኛነት የጠየቁ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው ልትልክ ነው
– የታክሲ ነጅዎች አድማ እንደገና ሊጀምር ይችላል ተባለ
– በትግራይ የቤት መስሪያ የቦታ ስፋት እንዲጨምር ተደረገ
– የሶማሊያ መንግስት 115 የአልሸባብ አባላት የተገደሉና ሌሎች 110 የተማረኩ መሆናቸውን ገለጸ
* የግብጽ የመንገደኛ አውሮፕላን ተጠለፈ
– በመከካለኛው አፍሪካ ሪፕብሊክ ተጨማሪ የተመድ የሰላም አስከባሪ አባላት በወሲብ ወንጀል ተከሰሱ
መጋቢት 20 ቀን 2008 ዓ.ም.
Ø የኖርዌይ መንግስት የፖሊቲካ ጥገኝነት የጠየቁ 800 ኢትዮጵያውያንን ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ የተዘጋጀ ሲሆን ከሚላኩት ውስጥ 60ዎቹ ህጻናት እንደሆኑ ተገልጿል። መንግስቱ ስደተኞች ያቀረቡት የፖሊቲካ ጥገኝነት ጥያቀ ተቀባይነት አላገኘም በማለት በግዳጅ ለመመልስ ይወስን እንጅ የስደተኛ ከለላ ጠባቂ የሆኑ ድርጅቶች ግን ስደተኞቹ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በአካላቸውና በመንፈሳቸው ጉዳት ከማምጣቱ በተጨማሪ ለህይወታቸው አስጊ እንደሚሆን በመጥቀሰ መንግስት ጉዳዩን እንደገና እንዲመለተው ውትወታ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በቅርቡም በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የኖርዌይን መንግስት ውሳኔ በመቃወም ኦስሎ ላይ ታላቅ የተቃውሞ ስለፍ ማድረጋቸው ይታወሳል። የወያኔ ቡድን መሪዎች በሀገር ውስጥ ሕዝብን በዘረኛ አምባገነን አገዛዝ ረግጦ መግዛት ብቻ ሳይሆን በውጭ ሀገር የሚኖሩትም ገጽታችንን ያበላሻሉ በማለት ከየቦታው ለማስወጣት ከየአገሮቹ ጋር ልዩ ልዩ ስምምነት እየፈጠሩ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከፍተና መከራና ስቃይ እየደረሰባቸው ነው።
Ø ከጥቂት ቀና በፊት በአዲስ አበባ ከተማ የታክሲ ሹፌሮችና ባለንብረቶች አዲስ የወጣውን የትራፊክ ህግ በመቃወም የሥራ ማቆም አድማ በማድረጋቸው የወያኔ መሪዎች ሕጉ እንደገና እንደሚታይና ለሶስት ወር ተግባራዊ እንደማይሆን በመግለጽ የሥራ ማቆም አድማውን ለጊዜውም ቢሆን ማስቆማቸው ይታወሳል። ሰሞኑን ውስጡን አዲሱን የተራፊክ ሕግ ተግብራዊ እያደረጉ በመምጣታቸው ምክንያት አንዳንድ የታክሲ ሹፌሮች ትናንት መጋቢት 19 ቀን 2008 ዓም ለአገልግሎት ሳይወጡ የቀሩ መሆናቸው የታየ ሲሆን በወያኔ ካድሬዎች ለታክሲዎቹ መጥፋት የገብርኤል በዓል እንደምክንያት ሲሰጥ ውሏል ። በዛሬው ዕለት መጋቢት 20 ቀን 2008 ዓም በስራ መግቢያ ሰዓት ላይ ከፍተኛ የታክሲ ዕጥረት እንደነበር ታውቋል፡፤ ይህ የታክሲ ዕጥረት የተከሰተው በርካታ አሸከርካሪዎች ለሥራ ባላመውጣታቸው መሆኑ ሲታወቅ ምናልባት የታክሲ ማኅበራቱ አጥቃላይ አድማ ሊጠሩ ይችላሉ ተብሎ ተገምቷል። አሁን ያለው የታክሲ ሥራን የማቀዝቀዝ አድማ አዲስ አበባ ከተማን ውጥረት ውስጥ ከቷል።
Ø ከምርኮኛ ወታደሮች ወያኔ በአምሳሉ ጠፍጥፎ የሰራው ኦህዴድ የመሠረተበትን 24 ኛ ዓመት አከብራለሁ ይበል እንጅ እንደታሰበውና እንደታቀደው መከበሩ አጠያያቂ እየሆነ ነው። የወያኔው ኦህዴድ በዓሉን ምክንያት በማድረግ በተዋረድ ታች ያሉትን አባላትና ደጋፊዎች ሰብስቦ ለማነጋገር ይታቀድ እንጅ ከሕዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ ከሕዝብና ከታች አባላት ጋር መገናኘቱ አስቸጋሪ እንደሚሆን ከወያኔው ኦህድዴ ጽሕፈት ቤት አካባቢ የተገኘው መረጃ አመልክቷል። ኦህዴድ ቀደም ሲል በያዘው መርሀ ግብር መሠረት የድርጅቱ ባለሥልጣናት በየቦታውና በየአዳራሹ እየተገኙ የኦህዴድን በዓል እንዲያስከብሩ የታቀደ ቢሆንም የወገኖቻችንን ደም በአግአዚ ወታድሮች እያፈሰሰ እንዴት በዓልና ፌስታ ይኖራል? ኦህዴድ የአሰገዳይና የገዳዮች ተባባሪ ሆኗል በማለት ካድሬዎቹ እርስ በርስ መነጋገራቸው የኦህዴድ በዓል መከበሩ አጠያያቂ ሆኗል። ከዚህ በዓል አካባበር ጋር በተያያዘ ዋና የተባሉ ካድሬዎች በዓሉ ከተከበረ ላለመገኘት የዓመት ፈቃድና የህክምና ፈቃድ እየጠየቁ ከስራ እየወጡ መሆናቸው ታውቋል።
Ø የወያኔ ቡድን መሪዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ለከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲያቸው እንዲያመች አድላዊና ዘረኛ አምባገነን አገዛዝን ከመሠረቱ ጊዜ ጀምሮ የትግራይ ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመነጠል የኢኮኖሚ የፖሊቲካ የወታደራዊ የትምህርት የልማትና የኢንቨስትመንት የሚዲያዎች ወዘተ ሥራዎች ለትግራይና ለትግራይ ተወላጆች ሲሰጥ መቆየቱ ይታወሳል። ሰሞኑን ደግሞ በሌላው የኢትዮጵያ ክፍል የማይታሰበውን በትግራይ አዲስ ቤት የሚሰራበትን ቦታ ስፋት በመጨመር መመሪያ አውጥቷል። በመመሪያው መሠረት ቀደም ብሎ ቤት ሰሪዎች ከ180 ካሬ ሜትር በላይ የማይፈቅድላቸው የነበረ ሲሆን አሁን ከዚያ በላይ በሆነ የቦታ ስፋት ላይ መስራት እንደሚችሉ ተፈቅዶላቸዋል። የወያኔ ቡድን መሪዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመላ ኢትዮጵያ እየተቀጣጠለ የመጣውን የተቃውሞ እሳት በትግራይ ሕዝብ ኪሳራ ለማዳፈን ትግራይ ውስጥ አንድ ግዙፍ የኬሚካል ፋብሪካ ለማቋቋም ከወስኑ ወዲህ አሁን ደግሞ የቤት ሠሪዎችን የቦታ መጠን ለማስፋት መፍቀዱ የትግራይ ሕዝብ ከጎኑ ለማሰልፍ የሚደርግ ጥረት መሆኑ ታውቋል። ብዙ ሀገር ወዳድ ዜጎች ወያኔ ከትግራይ ውጭ ባሉ ኢትዮጵያያኖች ላይ የሚፈጽመው ግድያ እስር በደልና አድልዎችን በትግራይ ሕዝብ ላይ ለለላው መጠን እንዲፈጽም ፍላጎት ባይቦራቸውም እንደ ትግራይ ግን ልማትና እንክብካቤ ቢኖራቸው እንደማይጠሉ ይናገራሉ።
Ø ሰሞኑን በሰሜን ሶማሊያ በአልሸባብና መንግስቱን በሚደግፉ ወታድሮች መካከል በተካሄደ ውጊያ 115 የአልሸባብ ወታድሮች መገደላቸውን የሶማሊያ መንግስት ቃል አቀባይ አስታውቋል። 110 የአልሸባብ ታጣቂዎች መማረካቸንና ሌሎች ወደ ገጠር ማምለጣቸውን መግለጫው ጨምሮ ገልጿል። ታጣቂዎቹ ሽንፈት የገጠማቸው ለአራት ተከታታይ ቀኖች በተደረገ ጦርነት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን የሶማሊያ መንግስት በውጊያ ስለደረሰበት ጉዳይ የሰጠውም መግለጫ የለም።ይህ የመንግስት መግለጫ በሌላ በሶስተኛ ወገን አልተረጋገጠም። አልሸባብ በደቡብ ሶማሊያ በርካታ ሽንፈት ስለገጠመው በሰሜን የጦር ሰፈር ለመመስረት እየሞከረ ነው ተብሏል። 22000 የሚደርሱ የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል በሱማሊያ የሚገኝ ሲሆን የሶማሊያ መንግስትን አልሸባብን ለመደምሰስ የቆረጠ መሆኑን በተደጋጋሚ ቢዝትም የቡድኑ እንቅስቃሴ ጎላ እያለ መምጣቱን ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ሰዎች ይጠቁማሉ
Ø አሌክሳንድሪያ ከምትባለው የወደብ ከተማ ወደ ካይሮ ሲበር የነበረው የግብጽ የመንገደኛ አውሮፕላን ተጠልፎ ወደ ቆፕሮስ (ሳይፕረስ) መወሰዱ ተነገረ። ጠለፋው ከሽብረተኛነት ጋር የተያያዘ አይደለም የተባለ ሲሆን አውሮፕላኑ በቆፕሮስ አውሮፕላን ማረፊያ እንዳረፈ ተሳፋሪዎቹ በሙሉ ተለቀዋል። በአውሮፕላኑ ውስጥ ከነበሩት 55 መንገደኞች መካከል 21 ዱ የውጭ አገር ሰዎች መሆናቸው ተገልጿል። ጠላፊው በእጁ ላይ የያዘው ምንም ዓይነት ፈንጅ ወይም መሳሪያ ያልተገኘ ሲሆን ጠለፋውን ለመፈጸም ያስገደደው በቆፕሮስ የምትኖረውን ፍቅረኛውን ለማይት መሆኑን ገልጿል። ጠላፊው በቁጥጥር የተደረገ ሲሆን በቆፕሮስ የፖሊቲካ ጥገኛነት ጠይቋል።
Ø በአይቮሪ ኮስት ሰሜናዊ ግዛት ባለፈው ሳምንት ረቡዕ መጋቢት 14 ቀን 2008 በአርብቶ አደሮችና በአካባቢው ገበሬዎች መካከል በግጦሽ ምክንያት በተነሳ የእርስ በርስ ግጭት የአስራ ሰባት ሰዎች ህይወት የጠፋ ሲሆን ከ 1300 የሚሆኑ ሰዎች በላይ የሆኑ ሸሽተው ወደ ቡርኪና ፋሶ የገቡ መሆናቸው ተገልጿል። ከተሰደዱት መካከል አብዛኞቹ ሴቶችና ህጻናት ናቸው። በአይቮሪ ኮስት በዘላኑ ህብረተሰብ እና በገበሬዎች መካከል በግጦሽና በውሃ አጠቃቀም ብዙ ግጮት ሲደደሩ የቆዩ ቢሆንም የአሁኑ ከፍተኛ የነበረ መሆኖ ተገልጿል።
Ø በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፕብሊክ የሚገኙ ሁለት የተመድ የሰላም አስከባሪ ኃይል አባላት በወሲብ ወንጀል የተከሰሱ መሆናቸውን የተመድ ቃል አቀባይ ሰኞ መጋቢት 19 ቀን ለጋዘጠኞች በሰጡት መግለጫ ገለጹ። ተጠርጣሪዎቹ አንዱ የብሩንዲ ሌላው የሞሮኮ ወታደሮች ሲሆኑ በማዕካለአዊ አፍሪካ ሪፕብሊክ ሴቶችን አስገድዶ በመድፈር ክስ የተመሰረተባችደውን የተመድ የሰላም አስከባሪ ኃይል አባላት ቁጥር ወደ 25 ከፍ አድርጎታል። በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ውስጥ ብሩንዲ 1128 ወታድሮች ሞሮኮ ደግሞ 741 ወታድሮች ሲኖሯቸው ሞሮኮ በወታደሩ ላይ የተሰነዘረውን ክስ የምትመረምር መሆኗን ገልጻለች። ባለፈው ሳምንት አስፈላጊ ከሆነ በቻድ ውስጥ የሚገኘው ወደ 12 000 የሚደረሰው የተመድ የሰላም አስከባሪ ኃይል በሙሉ በለላ ኃይል ሊለውጥ እንደሚችል የተመድ ዋና ጸሀፊ ባንኪ ሙን መግለጻቸውና ይህንን አስመልክቶ በመጋቢት 2 ቀን 2008 ዓም ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል፡
Ø በምግብ እጥረት ምክንያት ከደቡብ ሱዳን ወደ ሱዳን የሚሰደደው ሕዝብ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መሄዱ ተነገረ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 20 ቀን 2008 ዓም እንዳስታወቀው በደቡብ ሱዳን ውስጥ በሰሜን ምዕራብ ግዛቶች ብቻ 38000 ሺ የሚሆኑ ስደተኛች ወደ ምስራቅና ደቡብ ዳርፉር ግዛት የተሰደዱ መሆናቸውን ገልጿል። ኮሚሽኑ የስደተኞቹ ሁኔታ በጣም አሳሳቢ እንደሆነ ገልጾ ልጆች ከወላጆቻቸው የተለዩ መሆናቸውንና ከፍተኛ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው መሆኑ አብራርቷል። ባለፉት ሶስት ዓመታት በደቡብ ሱዳን በተከሰተው የእርስ በርስ ጦርነት 2.3 ሚሊዮን የሚሆን የደቡብ ሱዳን ዜጋ ከሚኖርበት ተነቅሎ ወደ ሌሎች ቦታዎች የተሰደደ መሆኑ ይታወቃል።
Ø በደቡብ አፍሪካ በጆሃንስበርግ ከተማ የኖርዝ ዌስት ዩኒቨርስቲ ለአንድ ወር ያህል ከተዘጋ በኋላ እንደገና መከፈቱ ተነገረ። ከጥቂት ወራት በፊት በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የትምህርቱ ክፍያ እንዲቀንስ፤ የኖሮ ሁኔታ እንዲሻሻልና ለነጮች ፍላጎት የተዘጋጀው የትምህርት ሥርዓት እንዲሻሻል በመጠየቅ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሲካሄድ መቆየቱ የሚታወቅ ሲሆን ባለፈው ወር የኖርዝ ወስት ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ባደረጉት ተቃውሞ የአስተዳድሩን ቢሮና የሳይንስ ማዕከሉን ማቃጠላቸው ይታወሳል። ሁኔታው ተረጋግቶ በዛሬው ዕለት ትምህርት መጀመሩ ተነግሯል።
Ø የአዲስ አበባን አጎራባች ከተሞችን ወደ አዲስ አበባ ለመጠቅለል የወጣውን ማስተር ፕላን በመቃወም በተለያዩ ቦታዎች ሕዝባዊ ተቃውሞ ሲካሄድ የቆየ መሆኑ ይታወቃል። ለዚህ ሕዝባዊ ተቃውሞ አስፈላጊውን እርምጃ አልወሰዳችሁም፤ ተባባሪ ነበራችሁ በማለት ከወያኔ መሪዎች በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ኦህዴድ ከፍተኛ ባለስልጣኖችን ከፓርቲው የኃላፊነት ቦታ ማባረሩም ይታወሳል። ሰሞኑን ከሚደመጡና ከሚነበቡ ሪፖርቶች ደግሞ የወያኔው ፓርላማ አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳና የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የተባለው ዲሪባ ኩማ እንቅስቃሴያቸው በወያኔ ደህንነት ራዳር ስር መውደቁ ተዘግቧል። ሁለት ከፍተኛ የአገዛዙ ባላሥልጣናትና የወያኔ ኦህዴድ መሪዎች ከተነሳው ሕዝባዊ ተቃውሞና ቁጣ ጋር በተያያዘ በዓይነ ቁራኛ ውስጥ እንዲወድቁ መደረጉ ሲታወቅ ወደ ውጭ ሀገራም እንዳይወጡ ፓስፖርታቸውን መነጠቃቸው ተገልጿል። የወያኔ መሪዎች ላጠፉት ህይወትና ላወደሙት ንብረት አገልጋዮችና አሽከሮች የሆኑትን ከፍተኛ የኦህዴድ ካድሬዎችና መሪዎች ጭዳ ለማድረግ መዘጋጀታቸው ቀደም ሲል መገለጹ ይታወሳል።
Ø የወያኔ መሪዎች የሥልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም እንዲያስችላቸው በውጭ ሀገራት የማግባቢያ ሥራ (የሎቢ ሥራ) ለሚሰሩላቸው ኩባንያዎች የአገሪቱን ሀብት ማዕድኗን እንዲበዘብዙ መንገዶችን ሲያመቻቹ መቆየታቸው ይታወቃል። ከአፋር ግዛት ከሰመራ የሚመጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከአስር ዓመት በፊት ለቀድሞ የወያኔ መሪና ጠቅላይ ሚኒስትር ለመለሰ ዜናዊ ሽልማት የሰጠው ያራ የተባለው የኖርዌይ የማዳበርያ አምራች ድርጅት በአፋር ዳሎል የሚገኘውን የፖታሽ ክምችት እንዲያወጣ ፈቃድ ተሰጥቶታል። ከኖርዌይ ያራ በተጨማሪ አንድ የእንግሊዝ የማዕድን ኩባንያም ይህንኑ የአፋር ማዕድን እንያወጣ ተፈቅዶለታል። ኢትዮጵያ በከርሰ ምድሯ ያላትን ሃብት የወያኔ መሪዎች ከንግድ ሸሪኮቻቸውና ከባለውለታና አጋር ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር በመሆን እየበዘበዙና በባዕድ ሀገርም ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብትና ንብረት እያከማቹ መሆናቸው ይታወቃል። የኖርዌይና የእንግሊዙ ማዕድን አውጭዎች በቅርብ ጊዜ ወደ ማዕድን ቁፋሮ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
Ø ከጎንደር የሚመጡ ሪፖርቶችና መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ የጎንደር ሕዝብ የወልቃይት ጠገዴ ነዋሪ ያነሳውን የማንነት ጥያቄ በመደገን ለወያኔ አገዛዝ ያለውን ተቃውሞ ባገኘው አጋጣሚና ሁኔታ እየገለጸ መሆኑ ታውቋል። መጋቢት 18 ቀን 2008 ዓም በጎንደር ከተማ በጎንደር ስታዲዩም ለብሔራዊ ሊግ በጎንደር ከነማና በአዲግራቱ ውልዋሎ ክለብ መሃል የእግር ኳስ ግጥሚያ በሚደረግበት ሰዓት የስታዲየሙ ተመልካች በቦታው መሰብሰቡን እንደ አጋጣሚ በመጠቅም ተቃውሞን ሲያሰማ፤ ብሶቱን ሲገልጽ ቁጣውን ሲያሳይ ውሏል። በዕለቱ በስታዲየሙ የነበረው ተመልካች “የወያኔ ኖር ይለያል ዘንድሮ”፤ “ወልቃት ይመለስ”፤ “አማራ ነን”፤ “የትግራይ የበላይነት ያብቃ”፤ “አፈና ይቁም” የሚሉትን መፈክሮችና ልዩ ልዩ የተቃውሞ መዝሙሮችን ሲያሰሙ ውለዋል። ወያኔ ህዝብ እንዳይሰበሰብና ተቃውሞውን እንዳይገልጽ ቢገድብም በስፖርት ሜዳና በጸሎት ቦታ ሳይቀር ሕዝብ ሲሰባሰብ ብሶቱን መግለጽ መጀምሩ ምናልባት ነገ ተሰባስቦ አደባባይ መውጣቱ የማይቀር ነው የሚሉ ታዛቢዎች አሉ።
Ø የወያኔ አጃቢና ሻማ ያዥ የሆኑት የፖሊቲካ ፓርቲ መሪ የተባለት ግለሰቦች ከወያኔ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር መነጋገራቸውን ወያኔ አስታውቋል። ይህ በወያኔ መሪዎች ትዕዛዝ በኃይለማርያም ደሳለኝ ፈጻሚነት የተካሄደው የብሔራዊ መግባባት የተባለለት ስብሰባ ከፕሮፓጋንዳ ወፍጮነት ባለፈ እንደ ስሙና አጀንዳው ምንም የተግባር ምላሽ ያልሰጠና ይልቁንም በወያኔ የምርጫ ድራማ ወቅት ስለሚከፈላቸው የገንዘብ መጠን የተጨነቀ ንግግር ሲያደርጉ መዋላቸው ታውቋል። የወያኔ ፕሮፓጋንዳ መሳሪያ ግን ለመልካም አስተዳድር ችግር ብሔራዊ መግባባት ዋና መሳሪያ ስለሆነ ከተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ጋር ውይይት ተደረገ ቀጥሎ ከሕዝብ ጋር ይሆናል በማለት ሲያናፉ ሰንብተዋል። የፓለቲካ ታዛቢዎች ወያኔ በአራቱም ማዕዘና የተነሳበትን ተቃውሞና አገዛዙ በቃን በማለት ሕዝብ እያካሄደ ያለውን የአመጽ እንቅስቃሴ ለማዳካም አንዴ ይቅርታ ተጠየቀ ሌላ ጊዜ ስለ መግባባት ንግግር ተደረገ በማለት ለማወናበድና ዕድሜ ለማስረዘም የሚያደርገው ጥረት አካል መሆኑን ይጠቅሳሉ። የወያኔ መሪዎች የሰላምና የዕርቅ ብሩን ከዘጉ ዓመታት ማስቆጠራቸውን ገልጸው በአሁኑ ወቅት የተባለው የብሔራዊ መግባባት ንግግር የተደረገው የወያኔ አጃቢና ሻማ ያዥ ፓርቲዎችን ከቀውሱ ጀርባ የቤት ስራ ሊሰጣቸው ታስቦ መሆኑን ሕዝቡ ይገነዘባል በማለት ተጨማሪ አስተያየት ይሰጣሉ።
Ø ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ አገሮች ለመሰደድ ሙክራ ሲያደርጉ የነበሩት 600 ስደተኞች በየሊቢያ የወደብ ጠባቂዎች የታገዱ መሆናቸው ታወቀ። ስደተኞቹ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የመጡ ሲሆን ህጻናትና እርጉዝ ሴቶች እንደሚገኙባችውም ተነግሯል። መቀመጫው ትሪፖሊ የሆነውና የዓለም አቀፍ እውቅና ባያገኝም ራሱን መንግስት ብሎ የሚጠራው አካል ስር የሚገኘው የሊቢያ ባህር ኃይል ስደተኞችን ያገተው ከትሪፖሊ ምዕራብ 70 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሳብራታ በምትባለው ወደብ ነው። ሊቢያ ውስጥ ከ800 000 በላይ ስደተኞች እንደሚገኙ ቀደም ብሎ በፈረንሳዩ የመከላከያ ሚኒስትር የተሰጠውን መረጃ የሊቢያ ባለስልጣኖች የተጋነነ ነው በማለት ውድቅ ቢያደርጉትም ባለፉት ሶስት ዓመታ እስከ 300 000 ስደተኞች ሊቢያ መግባታቸውን አልካዱም። ከአምስት አመት በፊት የጋዳፊ መንግስት ተገርስሶ ሊቢያ ውስጥ ቀውስ ከተፈጠረ ጀምሮ ከፍተኛ ገንዘብ በማስከፈል ስደተኞች ከቦታ ወደ ቦታ የማስተላለፍ ስራ በጣም አትራፊ የሆነ የንግድ ስራ መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ።፡
Ø የሩዋንዳ መንግስት ያለፈበትን የሰው እልቂት ወደ ብሩንዲ በመላክ የአገሪቱ ዜጎች እርስ በርስ እንዲጫረሱ በማድረግ ላይ ነው በማለት የብሩንዲ የገዥው ፓርቲ መሪ ከሰሱ። የፓርቲው ፕሬዚዳንት ፓስካል ንያቤንዳ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ለተባለው የዜና ወኪል በጽሁፍ በላኩት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጹት የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት የብሩንዲን ዜጎች በወታደራዊ ትምህርት አሰልጥነው ወንድሞቻቸውን እንዲገድሉ ወደ ብሩንዲ ይልካሉ የሚል ክስ ከሰነዘሩ በኋላ የአውሮፓ አገሮችም መሳሪያና ገንዘብ በመስጠት እየተባበሩ ነው ብለዋል። በቅርቡ በሩዋንዳ እና በብሩንዲ መንግስታት መካከል የእርቅ ውይይት እንዲካሄድ ግፊት ስታደርግ የነበረችው የካቶሊክ ቤተክርሲያን ከወቀሳው ያልዳነች ስትሆን የፓርቲው መሪ አሸባሪዎች የሚሏቸውን የአማጽያንን ዓላማ በማራገብ የሀሰት ዜና ያስፋፋሉ በማለት በውጭ ጋዜጠኞች ላይም የከረረ ሂስ ሰንዝረዋል። በብሩንዲ የፖሊቲካ ቀውስ መከሰት ከጀመረ ወደ አንድ ዓመት ገደማ እየተጠጋ ሲሆን እየተካሄደ ባለው የእርስ በርስ ግጭት ከ400 ሰዎች በላይ መገደላቸውና ከ250 000 ሰዎች በላይ ቤት ንብረታቸውን ጥለው መሰደዳቸው አይዘነጋም።
Ø የጣሊያን ዜጋ የሆነውን ወጣት ገዳዮች ናቸው ተብለው የተጠሩ የቡድን አባሎች በአሰሳ ተገድለዋል በማለት የግብጽ መንግስት መግለጫ መስጠቱ የሚታወቅ ሲሆን በወጣቱ ግድያ ላይ የግብጽ ባለስልጣኖች ያሉበት መሆኑን የሚጠረጥረው የጣሊያን መንግስት የግብጽ ባለስልጣኖችን መግለጫ ያልተቀበለ ከመሆኑም ሌላ በጉዳዩ ላይ የጣሊያን መርማሪዎች በሚገኙበት የምርመራ ቡድን ተመስርቶ ምርመራው እንዲቀጥል የጠየቀ መሆኑ ታውቋል። የግብጽ መንግስት በጣሊያን መንግስት ግፊት ወንጀለኞቹ ተገድለዋል ካለ በኋላ ምርመራው የቀጠለ መሆኑን እንዲሁም ሌሎች ተባባሪዎች መያዛቸውን የሚገልጽ መግለጫ ቢሰጥም የጣሊያን መርማሪዎች ምርመራ ውስጥ ይሳተፉ ለሚለው ጥያቄ ገና መልስ ያልሰጠ መሆኑ ተነግሯል።
Ø ከጥቂት ቀናት በፊት በአይቮሪ ኮስት የወደብ መዝናኚያ ከተማ ለ19 ሰዎች መገደል ምክንያት የሆነው የሽብር ጥቃት ውስጥ ተሳትፈዋል የተባሉ ሁለት የእስላማውያን አክራሪ ድርጅት አባላት በማሊ ውስጥ የተያዙ መሆናቸውን የማሊ የስለላና የጸጥታ ክፍል ባለስልጣኖች ገለጸዋል። ከተያዙት መካከል አንደኛው ሾፌር በመሆን ጥቃቱን ለፈጸሙት ግለሰቦች የትራንስፖርት አገልግሎት የሰጠ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የእርሱ ተባባሪ መሆኑ ተነግሯል። ግንቦት አራት ቀን ግራንድ ባሳም በተባለው የአይቮሪ ኮስት የቱሪስት መዝናኚያ ቦታ ላይ የተካሄደው የሽብር ጥቃት በጥቂት ወራት ውስጥ ከተካሄዱት መካከል ሶስተኛው ሲሆን በሰሜን አፍሪካ የአልቃይዳ ቅርንጫፍ ለጥቃቱ ኃላፊነቱን መውሰዱ ይታወቃል።