ኢትዮጵያ ክብሬ
ወንድማችን አቶ ኦባንግ ሜቶ ከጥቂት ቀናት በፊት የትግራይ ነጻ አውጪ ብሎ እራሱን የሚጠራውን ድርጅት ምንነት የተመርኮዘ ጽሁፍ ኢካደፍ ላይ አውጥቶ ነበር። የጽሁፉ ዋና ሀሳብ በጎሳ ተከፋፍሎ ነጻ መውጣት በጭራሽ አንደማይቻል በመጠቆም በአንድነት ለአንድነት መስራት አማራጭ የሌለው የችግራችን መፍትሄ እንደሆነ ማሳየት ነው። ይሄ የማያጠያይቅ እውነታና በጣም የሚደገፍም ሀሳብም ነው። ነገር ግን ወያኔን ያቋቋሙት ሰዎች ጫካ የገቡት የትግራይን ህዝብ ነጻ ለማውጣት ነው አሁንም አላማቸው ይሄንን ብሄረስብ መጥቀም ነው የሚለው አገላለጽ ብዙም አልተመቸኝም።
አንድ እግሩን ኢትዮጵያ አንድ እግሩን ኤርትራ አንፈራጦ በሁለት ቢላ የሚበላ ለእናቱም ይሁን ለአባቱ ሀገር ሙሉ ታማኝነት የሌለው እንደመለስና አቦይ ስብሀት አይነት ራስ ወዳድ የሚቆጣጠረው ድርጅት አላማው የትግራይን ህዝብ ጥቅም ማስጠበቅ ነው ማለት አይጥ የምትቦረቡረውን ቤት ለመሸሸጊያነት ፈልጋው ሳይሆን ቤቱን ላጠንክረው ብላ ነው ስትቆፍረው የምታድር እንደማለት ነው። ትግሬውን ከሌላው አናክሰው የራሳቸውን ጥቅም ለማግበስበስ የሚያሴሩ ለትግራይ ህዝብ ዘላቂ ጥቅም የመቆም ፍላጎቱም ይሁን ብቃቱ የላቸውም። ስለዚህ ወያኔ ለትግሬ የቆመነው የሚለውን የነአባይ ጸሀዬ ማወናበጃ ፕሮፖጋንዳ እኛም በማስተጋባት “አማራው መጣብህ፣ ኦሮሞው ሊፈጅህ ነው፣ እኛ ከስልጣን ከወረድን ወየውልህ” እያሉ የሚያስፈራሩትን ወገናችንን እኛም አስፈራርተን ወደነሱ ጉያ አንግፋው።
እርግጥ ነው ሌላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ሰብእናውንና ታሪኩን እያንቋሸሹ ትግሬውን “ወርቁ ህዝብ ጀግናው ዘር” እያሉ ሰብከዋል። ለተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ መሰረታዊ አገልግሎት እየነፈጉና የኢኮኖሚ አቅሙን እያደቀቁ ትግራይ ላይ የተሻለ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ሁኔታን ፈጥረዋል። ትግራይ ጫት እየከለከሉ ሌላውን ኢትዮጵያዊ ወጣቱ በአጉል ልማድ እየበከሉ ተስፋውን ያጨልሙበታል። ከጽዳት ሰራተኛ እስከ ከፍተኛ ሹመት ለማግኘት መመዘኛው ትግሬ መሆን ብቻ እስኪመስል ሌላውን ወገን ከስራ እያፈናቀሉ በትግራይ ተወላጆች ይተካሉ። ነባር ነጋዴውን በሰበብ አስባቡ ንብረቱን እየቀሙ ከአስመጪና ላኪ ከጅምላ እስከችርቻሮ ንግድ የኛ በሚሉት ወገን አስይዘዋል። ሌላው ኢትዮጵያዊ በኪራይ የሚኖርበት ቤት በላዩላይ እየፈረሰበት ከትግራይ ነኝ የሚለውና ከንሱ በጥቅም ጡት የተጣባ በርካታ ኮንዶሚኒየም እየተሰጠው አከራይቶ ብሩን ያጋብሳል። ኮንሶውና አኝዋኩ አንገቱና እግሩ እንደበግ በሲባጎ ታስሮ ከመሬቱ እየተፈናቀለ መሬቱ ሀገሩን ረግጠው ለማያውቁ የትግራይ ተወላጆች በነጽ ይቸራል። ይሄና ከዚህም የከፋ ብዙ አድሎአዊ ድርጊት በአለፈው 25 አመት መከናወኑ አይካድም። ነገርግን በጭራሽ ሊዘነጋ የማይገብው ነገር ይህ ድርጊታቸው ለትግራይ ህዝብ ከመቆርቆር የመነጨ ሳይሆን የትግራይ ተወላጆችን ከተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በማናከስ ለስልጣን ዘመናቸው መራዘም መስዋእት የሚሆን የትግሬ ጀሌ ጦር ለመፍጠር የተቀመረ መሰሪ ስሌት መሆኑ ነው።
በእኔ እምነት ሁሉም በጎ ነገር ለትግሬዎች እያለ የሚጮኽው የወያኔዎች ፖሊሲ አላማው ትግሬውን ከተቀረው ወገኑ ካናከሱት በኋላ በፍርሀት ሰንሰለት አስረው ሲያበቁ የነአባይ ወልዱ ትንሽ የትግራይ ቤተመንግስት ዘበኛ ማድረግ ነው ምኞታቸው። አላማቸው ያ ባይሆን ኖሮ በእነሱ እኩይ ስራ ምክንያት “የኛ ወርቅ ህዝብ” የሚሉትን ህብረተሰብ በመላው ኢትዮጵያዊ ሰብሉን እንደሚያጠፋበት ተምች እንዲጠላ የሚያደርግ ለከት ያጣ የዘረኝነት ፖሊሲ አያላራምዱም ነበር። ይህ ድርጊታቸው ትግሬ ወገኖቻችን በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል በሰላም ተንቀሳቅሰው እንዳይሰሩና በሰላም እንዳይኖሩ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ጥርጣሬ የለኝም። ለዚህ ነው እነሲዩም መስፍንና አቦይ ስብሀት ጫካ የገቡትም ሆነ ከጫካ መልስ ኢትዮጵያ ላይ የሚያኪያሂዱት ጦርነት ጸረ ትግሬ እንጂ የትግሬን ዘላቂ ጥቅም የሚያስጠብቅ አይለም የምለው። የወያኔ መሪዎች በኢትዮጵያ ህዝብ ትግል የግፋቸው ዘመን ማለቁ እንድማይቀር ጠንቅቀው ያውቃሉ። ታዲያ ያቺ ለህዝቡ መልካም ለእነሱ ክፉ የሆነች ቀን መምጣት የሚያደርጉት ዝግጅት አንዱ አካል የሆነው ትግራይ የምትባል የግዞት ሀገር በመፍጠር እንደ ቤት ሰርሳሪዋ አይጥ የዘረፉትን ሀብት እየበሉ የሚሞቱበት መደበቂያ ጉድጓድ ነው መማስ ነው። ይሄ ጉድጓድ ለረጅም ጊዜ መብቱን በተገፈፈውና ንብረቱን በገፍና በግፍ በተዘረፈው ህዝብ አመጽ ሲደረመስ ለአንድ ጎሳ አባልነቱና ለጊዜያዊ ጥቅም ሲል ሀገሩንና ወገኑን በመክዳት ለወያኔ ባለሀብቶች ጠባቂነት የተደረደረውን ደሀ ጀሌ ሁሉ ጠራርጎ ይፈጀዋል። የእኛ ስራ መሆን ያለበት ይሄ መአት እውን እንዳይሆን የትግራይ ተወላጆችም በጭፍን የወያኔ ደጋፊ ከመሆን እንዲቆጠቡ መምከር እኛም ሁልም ትግሬ በፈቃዱ የወያኔ ክፉ ሥራ ተጠቃሚ ነው ብለን ከማሰብ መቆጠብ ነው።
ሌላው የእነ አቦይ ስብሀትና አርከበ እቁባይ ከስልጣን በኋላ እቅድ ከደሀው ጉሮሮ ሲዘርፉት የኖረውን ሀብት በባእድ ሀገር መደበቅ ነው። ለዚህ በዝርፊያ ላካበቱት ሀብት አንዱ ምንጭ በትግሬ ማቋቋሚይ ስም ያላቸውና አንድም ቀን ሂሳቡ ተመርምር የማያውቀው ኤፈርት ነው። እነኚህ ባለስልጣኖች እውን ለትግራይ ህዝብ የቆሙ ቢሆን እነአዜብ ጎላና ሲዩም መስፍን የግል ንብረታቸው ያደረጉት ድርጅት ንብረት ለትግራይ ህዝብ ግልጽ በሆነ ነበር። ደግሞስ ትግራይ እስከመቼ ነው በተቀረው ኢትዮጵያዊ ህዝብ አጥንት መልሳ የምትቋቋመው?
መዘንጋት የሌለብን ሌላው ሀቅ እንመለስ ዜናዊ የደረሱበት የስልጣንና ሀብት ደረጃ የደረሱት በርካታ አብረዋቸው ጫካ የነበሩትን “ታጋይ” ትግሬዎች በለሊት አሳርደውና ከነህይወታቸው ጉድጓድ ውስጥ ቀብረው በመግደል መሆኑን ነው። የውጪ ድጋፍ ለማግኘት ሲሉም ሀውዜን ላይ የራሳቸውን ህዝብ በቦንብ አሰድብድበዋል። በተራበው ህዝብ ስም የሚመጣላቸው ገንዘብና እህል መጠኑ እንዲጨምር በመፈለግ ብቻ ረሀብተኛው ድጋፍ ወደሚያገኝበት ስፍራ እንዳይሄድ አግተውት ስንቱን ለመከራና ሞት ዳርገውታል። በብዙ ሺህ የሚቆጥር የትግራይ ተወላጅ በጠኔ ሲረግፍ በእነሱ ስም በተሰበሰብ ገንዘብ የወያኔ ባለሟሎች ስንቴ ድል ያለ ፓርቲ ደግሰው በውስኪ ተራጭተዋል። ስንቱን ከወያኔ በአስተሳሰብ የተለየ ትግሬ ደርግ ውስጥ አሰርገው ባስገቧቸው ካድሬዎቻቸው አማካኝነት ለነሀምሳ አለቃ ለገሰ አስፋውና ለደህንነቱ ተስፋዬ ወልደስላሴ ሀገር ከሀዲዎች ናቸው እያሉ በመንገር አሳስረዋል አስገድለዋል። መሀል ሀገር ከገቡስ በኋላ በደም በአጥንታቸው ወያኔን ተሸክመው አዲስ አበባ ያስገቡ ስንት አካለ ስንኩላን የወያኔ ወታደሮች እንደቆሻሻ ተጠራርገው ተሸኝተዋል። ስንቱስ ተገድሏል። ሌላው ይቅር መለስን ሳይቀር ጠመንጃ አያያዝ ያስተማሩት አቶ አሰግድ ገብረሰላሴ ከነመለስ የተልየ አስተሳሰብ ስላላቸው አይደል የወያኔን ጭካኔ መቀበል ከሳቸው አልፎ ለልጆቻቸው የተርፈው። እንዲህ አይነት በርካታ ምሳሌዎችን ስናስታውስ የወያኔ ባልስልጣናት ከራሳቸው ባሻገር ለማንም ጥቅም አለመቆማቸው ፍንትው ብሎ ይታየናል። ሌላውን ተጠቃሚ ካደረጉም የእንሱን የስልጣንና ዘረፋ ዘመን እንዲራዘም በማድረግ እንዲያግዟቸው በማሰብ ብቻ ነው።
በአለም አቀፍ ደርጃ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩትም በአብዛኛው ብሶት አለብን ብለው በጎሳና ሀይማኖቶ ጥላ ስር የሚነሱ ስብስቦች መሰረታዊ አላማቸው በህብረተሰብ ላይ የሚደርስን በደል መቅረፍ ሳይሆን የራሳቸውን ስግብግብነት ማርካት እንደሆነ ነው። ሴራሊዮንን ብንመለከት የኮንጎ ሪፕብሊክን ብንቃኝ አሁን ደግሞ በእስልምና ስም የተሰባሰቡትን ቦኮ ሃራምም ይሁን አይስስ ቡድኖች ብናይ ድጋፍ ለማሰባሰብ ይረዳቸው ዘንድ የሌላ ሀይማኖት ተከታዮችን ሲገድሉ ቢታዩም ከማንም በላይ በብዛት የሚያሰቃዩት፣የሚያርዱትና በታንክ የሚደፈጥጡት ሀይማኖታችሁን ለማስከበር ነው የቆምነው የሚሏቸውን እስላሞች ነው ።
ለምሳሌ ሴራሊዮን ውስጥ ከሰባ አምስት ሺህ ሰው በላይ የሞተበትና ከግማሽ ሚሊዮን የማያንስ ሰው ስደተኛ ሲሆን የሀገሪቱ ህዝብ ግማሽ የተፈናቀለበት ጦርነት ዋና ተዋናይ እራሱን የተባበሩ አብዮታዊ ግንባር ብሎ የሰየመየው ሀገርበቀል አማጺ ቡድን ነበር። ይህ ቡድን ነበር ህጻናትን ሳይቀር በሱሰኛ እጽ እየበከለ የራሳቸውን ቤተሰቦች ጭምር እጅ በቆንጨራ እየቆረጡ አዛውንትና ህጻናት ሴቶችን እንዲደፍሩና እንዲገድሉ ያደረጉት። ይህን ሲያደርጉ ዋና አላማቸው ልጆቹ የራሳቸውን ቤተሰብ ካዋረዱን ከገደሉ ብኋል የሚሸሹበት ስለማይኖራቸው የአረመኔዎቹ የሽፍታ መሪዎች ታማኝ አገልጋይ እንዲሆኑ ማድረግ ነው። የመሪዎቹ የነፎዴ ሳንኮህ ብቸኛ አላማቸውም የሀገሪቱን የአልማዝ ሀብት መቆጣጠር ነበር። ይህን አላማቸውን ለማሳካት ሲሉ ስፍር ቁጥር የሌለው ወገናቸውን ለስቃይና ለሞትና ስደት ዳርገዋል። ወያነዎችም ትግሬውን ከተቀረው ህዝብ የሚያጣሉት የምሸሽበት የለኝም ብሎ እነሱ ግደል ሲሉት የሚገድል ዘበኛ እንዲሆን ለማድረግ ነው።
ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎንና ደቡብ ሱዳንን እንደ ተጨማሪ ምሳሌ ብንመለከት ወገን በወገኑ ላይ ጠብመንጃና ቆንጮራ አንስቶ እንዲተላለቅ የሚቀሰቅሱትና የሚያናፍሱት አላማችን የህዝባችንን ጥቅም ማስጠበቅ ነው ይላሉ እንጂ እውነተኛ ፍላጎታቸው የሀገራቸውን ጥሬ ሀብት መቆጣጠር መሆኑን አይናገሩም። ያንን ከተናገሩ ብዙ ድጋፍ ስለማያገኙ። የትግራይ ነጻ አውጭ ድርጅት ባህሪይም ከዚህ የተለይ አይደለም።
የወያኔና ኢሀዴግ አባላት እያንዳንዳቸው የቆሙት ለራሳቸው የግል ጥቅም ብቻ ነው። ወገን የሚሉት የላቸውም። ለዚህም ነው የተለያየው ብሄር ተጠሪ ነኝ የሚለው የወያኔ ጀሌ በሙሉ ጨካኙን አጋዚ መንገድ እየመራ ወዳጅ መስሎ በዘር የሱ ወገን የሆነዉን ሁሉ የሚያስፈጀው። የወያኔ ስርአት ለማንም ደህንነት የማይጨነቅና ስልጣን ላይ ያሉትን ብቻ በሀብትና ዝና ለማግነን የሚሰራ የዘራፊ ቡድን እንጂ የየትኛውንም ብሄረሰብ ዘላቅ ጥቅም አስጠባቂ አይደለም።
ይሄ የወያኔ ተፈጥሮና ባህሪይ ለኛ የሚሰጠን ግንዛቤ ማንኛውም በዘርም ይሁን በሀይማኖት አመካኝቶ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭ ቡድን አላማው ህዝባዊ ሳይሆን ግላዊ መሆኑን ነው። ሁሉም ሰው የሚፈልገው በተረጋጋ ሰላም ያለፍርሀት ሰርቶ በደስታ መኖርን ነው። ከጎረቤቱ ጋር የጎሪጥ እየተያየ ሳይቀድመኝ ልቅደመው በሚል የፍርሀት መንፈስ ተውጦ ደስታና ብልጽግናን ማግነት ከቶውንም አያልም። ስለዚህ ለህዝብ ጥቅም ቆመናል የሚል ማንኛውም ስብስ አንድን ህብረተሰብ ከሌላው ጋር በዘርና ሀይማኖት ሰበብ ማናከስ አላማው ሊሆን አይገባም። ይህ ማለት የባህልና የቋንቋ ልዩነታችን ይከበር ብሎ መጠየቅ መጥፎ ነው ለማለት አይደልም። ልዩነታችን ለጸብ ሳይሆን ለፍቅርና ለመደጋገፍ እንዲረዳን ልንጠቀምበት እንችላላን። ከነልዩነታችን ተከባብረን በአንድነት መኖር እንችላላን።
በመጨረሻም ከልምድ ጠንቅቀን የምናውቀው የአንድ እናትና አባት ልጆች ጠላት ሁነው ሲጋደሉ ፍጹም ባእድ የሆነው ሰው በሰው ልጅነቱ ብቻ አዝኖ ሌላውን ለመርዳት እራሱን እንደሚሰዋ እናውቃለን። በአጭሩ የአንድ ጎሳ ወይንም ሀይማኖት አባል መሆን ብቻውን ለወዳጅነት ለመታመንም መሰረት ሊሆን አይችልም። በደም ግማሽ ኤርትራዊ በአንዳንድ ድርጊቱ ከኤርትራዊያን በላይ ኤርትራዊ ይባል የነበረውና ወላጅ እናቱም ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንደትገነጠል ድምጻቸውን የሰጡት ባለራዕዩ መለሰ ዜናዊ “የአይናችሁ ቀለም ካላማረኝስ” እያለ ኤርትራዊያንን ከኢትዮጵያ በአንድ ጀንበር ሲያባርር ተባራሪዎቹን እያለቀሱ የሸኙትና ንብረታቸውን በአደራ የጠበቁላቸው የተለያየ ጎሳ አባል የሆኑ ኢትዮጵያውያን ናቸው።
No comments:
Post a Comment