Saturday, May 21, 2016

መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ያላት የሰው ድሀ ሀገር ኢትዮጵያ – ይገረም ዓለሙ

በ1982 ዓም  ኢትዮጵያ ወዴት እየሄደች እንደሆነ አይደለም የት ላይ አንዳለች አንኳን መናገር የማይቻልበት ወቅት .ከአንድ ባልንጀራየ ጋር እየሄድን እኔ ከማላውቀው የእርሱ ጓደኛ ጋር መንገድ አገናኘን፡፡ እናም ሰላምታ ተለዋውጠው  ታዲያስ አንዲት ነህ እንዴት ናችሁ ሲለው  ምን እባክህ ሰውም አለን ሰውም የለንም  ሲል መለሰለት፡፡
ሁለቱ ተለያይተው እኛ መንገድ እንደጀመርን ምንድን ነው ያለው ስል ባልንጀራየን ጠየኩት፡፡ እባክህ እሱ አመሉ ነው፡ ከርሱ ጋር ስናወራ ጓደኞቹ ሁሉ አንደተቸገርን ነው፤ በቀጥታ መናገር አይሆንለትም አለኝ፡፡ ምንድን ነው ስራው ስል ጥያቄ አከልኩ ስራው ወታደራዊ ካድሬ ፣ትውልዱ ጎንደሬ፣ፖለቲካውን በጎንደር አማርኛ እየመሰጠረ ነው የሚያስቸግረን  በማለት ባላንጀራየም እንደመራቀቅ እያደረገው መለሰልኝ፡፡ ሰው አለን ሰው የለንም  የሚለውን አባባል ምንነት ለመረዳት ከባልንጀራየ ጋር ብዙ አውርተንበታል፤ብቻየንም ብዙ ግዜ አውጥቼ አውርጄዋ
Ethiopian-Flag.jpg
ይህ በሆነ  አስር ዓመት ግድም ፕ/ር መስፍን ወልደማሪያም በጦቢያ መጽሄት ላይ ኢትዮጵያ የሰው ድሀ ካልሆነች ታዲያ የምን ድሀ ልትሆን ነው የሚል ጽሁፍ  አስነበቡን፡፡ ይህም ከሆነ አስር ዓመት ግድም (አጋጣሚው ሊገርም ይችላል)   ፕ/ር መስፍንን አግኝቻቸው  ከላይ የጠቀስኩትን ጽሁፋቸውን አስታውሼ ከ90 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ያላት፣ በተለያዩ የዓለም ሀገራት በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ተሰማርተው የሚሰሩ አንቱ የተባሉ ልጆች ያሏት በማለት ብዙ ነገር ዘረዘርኩና እንዴት የሰው ድሀ ትባላለች ስል ጠየኳቸው ፡፡ በጥሞና አዳምጠው በርጋታ የሰጡኝ ማብራሪያ ረዥምና አጥጋቢ ነበር፡፡ ከግዜው ርዝመት አንጻር ማስታወስ ቢገደኝም አንኳር ነጥቡ እነዚህ የምትላቸው ሰዎች ለራሳቸው ኖረው ሊሆን ይችላል፤ ላስተማራቸው ሀገርና ሕዝብ ምን ሰርተዋል? ከአገዛዝ አላቀውታል? ከድህነት አውጥተውታል? ሰው በሚፈለግበት ግዜና ቦታ ካልተገኘ መኖሩ ብቻ ለሀገር ምን ይጠቅማል የሚል ነበር፡፡
የርሳቸውን ማብራሪያ እያዳመጥኩ አስር ዓመት ያህል ወደ ኋላ ተመልሼ ሰው አለን ሰው የለንም ያለውን የወዳጄን ወዳጅ አስታወስኩት፡፡ የአባባሉ ምንነትና እንደዛ ለማለት ያበቃውም ምክንያት በፕ/ር ንግግር ውስጥ ግልጽ ብሎ ታየኝ፡፡ በቁጥር ብዙ ሰው አለ፤ በቁም ነገር መድረክ በተግባሩ መስክ ግን  ..ማለቱ ነበር የሰው ድሀ ማለት ይህ አይደል ታዲያ፡፡
ብቸኛው ፓርቲ ኢሰፓ ከሲቭልም ሆነ ወታደራዊ ማዕረጋቸው የሚቀድመውን ጓድ መጠሪያቸው ያደረጉ ብዙ እጅግ ብዙ አባላት ነበሩት፡፡ነገር ግን አባሉ በቁጥር በዝቶ  ቁም ነገር ያለው ግን አንሶ  አይደለም ሀገሪቱን ሲያንቆለጳጵሱዋቸው የነበሩትን መሪ ከስደት፤ ፓርቲውን ከሞት፤ ራሳቸውን ከውርደት መታደግ ሳይችሉ ቀሩ፡፡
ኢሰፓ ያልነበሩ እንደውም ኢሰፓን ተቃውመው መንግስቱን አውግዘው ሲታገሉ የነበሩ ባይታገሉም ሥርዓቱን ይቃወሙ ዴሞክራሲን ይመኙ የነበሩ በቁጥር ብዙ  ነበሩ፡፡ ግና ቁም ነገራቸው ሚዛን የሚደፋ የተግባር ሰውነታቸው እስከመስዋዕትነት የደረሰ ጥቂቶች ሆኑና ኢትዮፕያ ሰው እያላት የሰው ድሀ ሆነችና  ከወታደራዊ አገዛዝ ወደ ተጋዳላዮች አገዛዝ ለመሸጋገር በቃች፡፡
ዘመነ ወያኔንም ስናይ ከመነሻው ጀምሮ ወያኔን የሚቃወመው፣ ስለ ለውጥ  የሚደሰኩረው፣  ስለ ዴሞክራሲ  የሚሰብከው፣ ወዘተ ቁጥሩ የትየለሌ ነው፡፡ ግና ከቁም ነገሩ መድረክ ከተግባሩ ስፍራ የሚገኙት ጥቂት በጣም ጥቂት ሆኑና ወያኔ ማን አለኝ ከልካይ እያለ የሻውን እየፈጸመ ሀያ አራት ዓመታት ለመግዛት ቻለ፡፡ ሌላው ቀርቶ በቅርቡ ኢሳትና ቪዥን ኢትዮጵያ በጋራ ባዘጋጁት የውይይት መድረክ ላይ የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡትን  በተለያየ የሙያና የእውቀት ዘርፍ ከጫፍ የደረሱ ምሁራንን የተመለከተ  የእነርሱ መሰሎች ሀገር ኢትዮጵያ እንዲህ በአገዛዝ ስትማቅቅ፤፣ከዴሞክራሲ ጋር ሆድና ጀርባ ሆና ስትኖር፣ ሕዝቡ በየግዜው በረሀብ አለንጋ ሲገረፍ ሰው እያላት ሰው ያጣች ሀገር አያሰኝም ትላላችሁ!
የኢትዮጵያ የሰው ድሀነት በወያኔም ውስጥ በገሀድ ይታያል፡፡ በተለያየ መንገድ የድርጅቱ አባልም ደጋፊም የሆኑ አባልና ደጋፊም ባይሆኑ ደግሞ የማይቃወሙ በተለያየ የእውቀትና የሙያ መስክ ላይ የሚገኙ በውጪም በውስጥ ብዙ ዜጎች አሉ፡፡ነገር ግን እነርሱም ቁጥራቸው እንጂ ቁም ነገራቸው የሚታይ ባለመሆኑ ድርጅታቸው በሀገርና  በሕዝብ ላይ የሚያደርሰውን ጥፋት ማሰቆም ቀርቶ አንድ መለስ ያለእኔ ማን አለ ብለው ፓርቲም መንግሥትም ግለሰብም ሆነው ናውዘው ለሞት ሲበቁ ሊታደጉዋቸው አልቻሉም፡፡
ይህም ብቻ አይደለም ከአስር ዓመት በፊት ከአምስት ሚሊዮን በላይ አባላት አሉኝ ያለ ድርጅት በቁጥር እንጂ በቁም ነገር (ከሱ ፍላጎት አንጻር) ሚዛን የሚደፋ ሰው አጥቶ ከቦታ ቦታ የሚያገላብጣቸው የተወሰኑ ሰዎችን ነው፡፡ ሴቶችማ ለቁጥርም የሉ፡፡የአሁኑ አፈ ጉባኤ አባ ዱላ ገመዳ አንዴ ጀነራል አንዴ አቶ እየተባሉ ስንት ቦታ አንደተገለባበጡ ማስታወሱ ብቻ ለዚህ በቂ ይመስለኛል፡፡
የትውልድ ድርሻውንና የዜግነት ግዴታውን ቅንጣት ሳይከውን በሥልጣኔ ስም ሰይጥኖ ወደ ላይ አንጋጦ ትናትን የማውገዝ ድፍረት በተላበሰው ትውልድ የሚነቀፉ የሚዘለፉት አባቶቻችን በቁጥር ጥቂት ሆነው ከነዛው መካከል ግን የቁም ነገር ሰዎች ብዙም ብርቱም የነበሩ በመሆናቸው ነበር በዙሪያችን ያሉ ሀገሮች በቅኝ ግዛት ሲማቅቁ ኢትዮጵያ በነጻነት የዘለቀችው፤ ዳር ድንበሯን አስከብራ የባህር በሯን አስጠብቃ ለመኖር የቻለችው፡፡ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ተምሳሌት ሆና የኖረችው፡፡
ዛሬ ግን አንደ ቁጥራችን ብዛት ከቁም ነገር ያፋቱን፣ ከተግባር ያራቁን ችግሮቻችን በዝተው እኛ የሚናቁት የሚወገዙና የሚኮነኑት አባት እናቶቻችን የቆዩንን ሀገር፣  ዳር ድንበር፣ የባህር በር፣ወዘተ ማስከበርና መጠበቅ ሳንችል ቀረን፡፡  ከወያኔ አገዛዝ ተላቀን የምናወራለትን ዴሞክራሲ እውን ለማድረግ  መስኩ ላይ መገኘት አቃተን፡፡ በእውቀት የበለጸጉ በሙያ የተካኑ በልምድ የዳበሩ አያሌ ልጆቿ  በመላው ዓለም በተለይም በምእራቡ የዓለም ክፍል ተሰማርተው እውቀት ጉልበታቸውን ለሌላ ሀገር እየሸጡ የተደላደለ ኑሮ መኖር ቢቻላቸውም  እውቀታቸውም ሆነ ሙያቸው፣ ልምዳቸውም ሆነ ጉልበታቸው፣ ለሀገራቸው የሚፈይድ አልሆነም፡፡ አንዲህም ሆነና እናት ሀገር ኢትዮጵያ መቶ ሚሊዮን የሚሆን ሰው እያላት  የሰው ድሀ ሆና  አገዛዝ እንደተፈራረቀባት፣ ዴሞክራሲ አንደናፈቃት፣ ረሀብ ልጇን እንዳሰቃየባት ትኖራለች፡፡ ዛሬ እየሆነ ካለው በላይ  የነገው ተስፋ የለሽነት  ይብስ ይከፋል፡፡
መቼ ይሆን! ኢትዮጵያ ልጆቿ  ቁጥራችን ብቻ ሳይሆን ቁም ነገራችንም በዝቶ ሰው እያላት የሌላት የሰው ድሀ ከመሆን የምትወጣው? መቼ ይሆን! በዘር፣ በሀይማኖት፣ በአመለካከት ልዩነት ተለያይተው የመቶ ሚሊዮኖች እናት ግን የሰው ድሀ ያደረጉዋት ልጇቿ ከምንም ነገር በፊት እናታችን ብለው እውቀታቸውን አቀናጅተው ሀይላቸውን አስተባብረው  ነጻነት የሚያቀዳጇት? መቼ ይሆን! ልጆቿ ከራስ በላይ ነፋስ አስተሳሰብ ተላቀው፣ ከመጠላለፍ አዙሪት ወጥተው፣ ከቁልቁለት ጉዞ የሚያቃኑዋትና  የነበረ ዝናና ክብሯን መልሰው የሚያቀዳጁዋት? አረ መቼ ይሆን! ልጆቿ  ዴሞክራሲ እየተረገዘ የሚጨነገፍበትን ሲወለድም   በአጭር የሚቀርበትን በሽታ ተርደተው መድሀኒትም አግኝተውለት ኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊት ሀገር ለማድረግ የሚበቁት ? አረ መቼ ይሆን! ልጆቿ የመቶ ሚሊዮን ሕዝብ ሀገር የሰው ድሀ የሆነችው እነርሱ ተለያይተው በመቆማቸው፤ በስልጣን ጥም በመታወራቸው፤ ከእኔ በላይ በሚል አስተሳሰብ በመታጠራቸው፣ለራስ እንጂ ለመጪው ትውልድ የማይጨነቁ በመሆናቸው ወዘተ መሆኑን ተረድተው ከየራሳቸው ታርቀው፣ ርስ በርሳቸው ፍቅር መስርተው፣ አንደ ብዛታቸው ቁም ነገራቸውም ለሀገርና ለወገን ሲበጅ የሚታየው መ? መቼ አረ መቼ !
ተዋቂው የብእር ሰው ሎሬት ጸጋየ ገብረ መድህን  ይድረስ ከእኛ ለእኛ በሚለው ተከታታይ ግጥም ውስጥ እንዲህ ብሎ ነበር፡፡
ይድረስ ወገን ከእኛ ለኛ “እሳት አንሆን ወይ አበባ”
የነገን ራዕይ አንዳናይ ፣በሐቅ እንቅ ስንባባ
መክሊታችንም ባከነች፣ዕድሜአችንን ስናነባ፡፡
ፍቅር ፈርተን፣ሰላም ፈርተን
አንድታችንን ጠልተን ፣ተስፋችንን አጨልመን
የነፍስን አንደበት ዘጋን፣
የልጆቻንን ተስፋ ፣እምቡጥ ሕልማቸውን በላን፡፡
ሳይነጋ እየጨለመ ነው፣ተው ወንድሜ እንተማመን፣
ዓለም ባበደበት ዘመን፣የብረት ምሽግ ነው ወገን፡፡
ኢትዮጵያ ዘለዓለሚቷ፣አንድነት ነው መድኃኒቷ
ሕብረት ነው መፍትሔው ስልቷ፡፡

Friday, May 20, 2016

ቃና ቴሌቪዥን ንብረትነቱ የማን ነው? ዓላማውስ ምንድን ነው? | ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

ቃና ቴሌቪዥን (ምርዓየኩነት) እንደ ፋና ራዲዮ (ነጋሪተ ወግ) ሁሉ መቀመጫውን በዓረብ ሀገር ያደረገ ሞቢ ግሩፕ በሚባል የውጭ ድርጅት ስም የተመዘገበ የአገዛዙ ባለሥልጣናት እንደሆነ ይነገራል፡፡ አቶ ዘረሰናይ ብርሃነ፣ አቶ መሐሪ፣ አቶ ኤልያስ ሽሉዝ፣ የ251 ኮሙዩኒኬሽን ባለቤቶች አቶ ናዝራዊ ገብረ ሥላሴና አቶ አዲስ ዓለማየሁ የተባሉ ግለሰቦች ደግሞ በመሠረቱት የጋራ የሽርክና ድርጅታቸው የቴሌቪዥን ጣቢያው የሚልክላቸውን ፊልሞች (ምትርኢቶች) በተለምዶ የጃፓን አምባሳደሮች መኖሪያ ከሚባለው አካባቢ በሚገኝ ሕንፃ ላይ በተከራዩት ሦስት ፎቆች ስድስት ስቱዲዮዎችን (መከወኛ ክፍሎችን) ገንብተው ፊልሞችን (ምትርኢቶችን) እየተረጎሙ ለጣቢያው ያቀርባሉ፡፡

zana ana chandra

kkanaየቴሌቪዥን ጣቢያው ዋና መቀመጫው ከሀገር ውጭ እንዲሆን የተደረገውም ሆን ተብሎ ለዓላማና በምክንያት ነው፡፡ ይሄንን ጣቢያ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን የአሁኑን ኢቢሲን አስጎምጅ የማስታወቂያ ገቢ ለመውሰድ ያሰቡ የወያኔ ባለሥልጣናት ናቸው ያቋቋሙት፡፡ ይሁን እንጅ ዋና ዓላማው ግን ይሄ አይደለም፡፡
አስቀድሞ ግን የውጭ ሀገራትን ፊልሞች ወደ አማርኛ በመተርጎም ለተመልካች ለማቅረብ የአየር ሰዓት በኪራይ እንዲሰጣቸው ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ማለት ለኢቢሲ ፕሮፖሳል (ንድፈ ሥራ) ያቀረቡ ሌሎች ነበሩ፡፡ ወያኔ እንደልማዱ ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከግለሰቦች ፕሮፖዛል (ንድፈ ሥራ) ሲቀርብ ለእሱ ጠቃሚ መስሎ ከታየው ፕሮፖሳሉን ያቀረበውን ወይም ያቀረቡትን ግለሰቦች ፈንግሎ ነጥቆ ይወስድና ለራሱ ሰዎች እንዲጠቀሙበት እንደሚያደርግ ሁሉ ይሄንንም ሊጠቀሙበት ስለፈለጉ ካቀረቡት ሰዎች እጅ በመንጠቅ ለራሳቸው አገረጉት፡፡ ፕሮፖሳሉን ለኢቲቪ ያቀረቡት ግለሰቦች ግን የሚያውቁት ኢቲቪ ለጥያቄያቸው በወቅቱ ተገቢውን ምላሽ በወቅቱ ሳይሰጣቸው ጉዳያቸውን በማዘግየቱ በመጥፎ ባጋጣሚ በውጭ ድርጅት መቀደማቸውን ነው፡፡
የወያኔ ባለሥልጣናት ቃና ቴሌቪዥንን (ምርዓየኩነትን) ያቋቋሙበት ዓላማ አንደኛው ከላይ እንደጠቆምኩት ለጥቅም ማለትም ከማስታወቂያ የሚገኘውን ከፍተኛ ገቢ በግል ለማግኘት ሲሆን፡፡ ዋናው ጥቅምና ዓላማ ግን የሕዝብን ትኩረት በመያዝና ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዳይሔድ በማቀብ ተቆጣጥሮ በመያዝ አገዛዙ ከሚፈጥረው ከወቅታዊና ነባራዊ ችግሮች የሚነሣን የሚቀሰቀስን ሕዝባዊ ዐመፅን አለመረጋጋትንና እንቢጠኝነትን ከሩቁ ለመከላከል ነው፡፡ ዓላማው ይሄ ይሁን እንጅ “በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ” እንዲሉ ቃና ለወያኔ የሚሰጠው ጥቅም ከሁለት ወፍም በላይ በርካታ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የሚፈልገውን የጥፋት ውጤት ለማምጣት ብዙ ሲደክምበት የቆየውን ነግር ሁሉ በአቋራጭ በአጭር ጊዜ እያመጣለት ነው፡፡ ወደ ኋላ እንመለስበታለን፡፡
ቃና ቲቪን ለመክፈት ባለሙያ ለማሠልጠን ብቻ ከሁለት ዓመታት በላይ ጊዜ ወስዷል፡፡ በቅድሚያ ኢ.ቢ.ኤስ. የተባለው ጣቢያ እንዲከፈት የተደረገው ለማላመጃ ነው፡፡ ስለ ኢ.ቢ.ኤስ. አገልግሎትና ዓላማ ከዓመታት በፊት “ቶክ ሾው (ትዕይንተ-ወግ) ከያኔያንና ጥበብ በሀገራችን” በተሰኘው ጽሑፍ ላይ መግለጤ ይታወሳል፡፡
ታስታውሱ እንደሆነ የሀገሪቱ ብቸኛው ቴሌቪዥን (ምርዓኩነት) ኢቲቪ የአሁኑ ኢቢሲ ለረጅም ዓመታት ድራማን (ትውንተ ኩነትን) ጨምሮ ለመዝናኛ ዝግጅቶች ትኩረት ነፍጎ ቆይቶ ነበር፡፡ የጣቢያው ሙሉ ትኩረትና ሥራ ፕሮፖጋንዳ (ልፈፋ) ብቻ ሆኖ እጅግ አሰልቺ በሆነ መንገድ የወያኔን አደንቋሪ ልፈፋዎችንና ሐሰተኛ ወሬዎችን ማስተላለፍ ብቻ ሆኖ ቆይቶ ነበር ሥራው፡፡ በዚህ ረጅም ወቅት ጣቢያው የነበረውን ክብር ተአማኒነትና መወደድ ለማጣት ተገዷል፡፡
ከምርጫ 97ዓ.ም. በኋላ ወያኔ የደረሰበትን ኪሳራ ለመቀልበስ ከነደፋቸው አቅዶች አንዱ አስቀድሞ ሕዝቡን መዝናኛ ዝግጅቶችን ነፍጎ ያላ አማራጭ የራሱን አደንቋሪ አሰልቺ አስቀያሚና አስጠሊታ ልፈፋ ብቻ እንዲሰማ ማስገደዱ ሕዝቡን ምሬቱና መታፈኑ እንዲሰማው እንዲታወቀውና አሻፈረኝ እንዲል እንዳደረገው በመረዳቱ ጨርሶ ትኩረት ነፍጎት የነበረውን የመዝናኛ ዝግጅት ከፍተኛ ትኩረት ሰጠውና በተለይ ድራማዎችን (ትውንተ ኩነቶችን) በገፍ እንዲቀርቡ በማድረጉ ከሀገር ውስጥ እስከ በባዕዳን ሀገራት በስደት እስካለው ወገን ድረስ ሕዝቡ የወሬው የወጉ የጫወታው ርእስ እየቀረቡ ያሉት ድራማዎች (ትውንተ ኩነቶች) ሆነው ሲያይና በዚህም ምን ያህል ትኩረት ማስቀየስና መያዝ እንደቻለ እንደተጠቀመም ሲረዳ በዚህ ጉዳይ ላይ የበለጠ ቢሠራበት ሕዝብን ማዘናጋትና ትኩረቱን ወደሌላ ሳያደርግ መያዝ እንደሚችል በማመኑ የበለጠ ሊሠራበት የሚችልበትን መንገድ በሚያሰላስልበት ወቅት ነው የእነዚያ ሰዎች ንድፈ ሥራ (ፕሮፖዛል) በእጁ የገባው፡፡
ፕሮፖሳሉ (ንድፈ ሥራው) በእኛው ባለሙያዎች እየተዘጋጁ የሚቀርቡት ድራማዎች (ትውንተ ኩነቶች) ከሚጠይቁት ወጭና ተጓዳኝ ሁኔታዎች አንጻር የውጪ ፊልሞችን (ምትርኢቶችን) ተርጉሞ ማቅረብ በጣም በቀላል ወጭ የሚከወንና እጅግ በጣም ወጭ ቆጣቢ አትራፊም መሆኑን በመረዳት ከዚህ ዝግጅት የሚገኘውን ፖለቲካዊ ጥቅም ከፍተኛ ለማድረግ በኢቲቪ አጭር ሰዓታትን ሰጥቶ ከማስተናገድ ይልቅ 24 ሰዓታት የሚተላለፍበትን የራሱን መስመር በመክፈት ዝግጅቱ እንዲተላለፍ ቢደረግ ጥቅማቸው ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ስለተረዱ ባለቤቶቹ እነሱ እንደሆኑ እንዳይታወቅ በከፍተኛ ምሥጢር ተይዞ መቀመጫውንም ከሀገር ውጭ በማድረግ ሥራውን እንዲሠራ ተደረገ፡፡
ይሄው እያየለው እንዳለውም ሕዝብ ትኩረቱን ወደሌላ እንዳያዞርና ባሉበት በተጋፈጣቸውም በችግሮቹ ላይ አተኩሮ መፍትሔ እንዳይሻ እንዳያፈላልግ፣ ችግር እንዳይፈጥር ተቆጣጥሮ ከመያዝ አኳያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከጠበቁት በላይ እጅግ አመርቂ ውጤት ሊያስመዘግብላቸው ችሏል፡፡ ያስገኘው ውጤት የሕዝቡን ትኩረት ቀፍድዶ ይዞ በችግሮቹ ላይ እንዳያተኩርና መፍትሔም እንዳይሻ እንዳያፈላልግ ሌላ ነገር እንዳያስብ ከማድረግም ተሻግሮ ትምህርትንና ሥራንም ጨርሶ ማስረሳቱ ማዘንጋቱ ነው አስገራሚውና ከሀገርና ከሕዝብ ጥቅም አንጻር ሌላው ተጨማሪ እጅግ አደገኛና አሳሳቢ ጉዳቱ፡፡
በቃና የሚተላለፉ የሚከታተሏቸውን ፊልሞችን (ምትርኢቶችን) እንዲያልፏቸው እንዲያመልጧቸው ካለመፈለግ የተነሣ ተማሪዎች እንኳንና ጥናት ሊያጠኑ ቀርቶ ከትምህርት ቤት የተሰጣቸውን የቤት ሥራዎች እንኳን ሳይሠሩ ወደ ትምህርት ቤት ለመሔድ ተገደዋል፣ ክፍል ውስጥ ወሬያቸው ሁሉ በቃና የሚቀርቡ ምትርኢቶች ሆነዋል፣ ከትምህርት ገበታቸው እየቀሩ ወይም አቋርጠው እየወጡም የቃና ፊልሞችን (ምትርኢቶችን) በመመልክት በሕይዎታቸው ላይ የሚቀልዱ ሆነዋል፡፡

ይህ ምን ማለት እንደሆነና ውጤቱ ትውልዱን እንኩቶ ገለባ አድርጎ ሀገርን ሊገለጽ ከሚችለው በላይ ከባድ ኪሳራ ላይ ሊዘፍቃት የሚችል አደጋ እንደሆነ፣ ሕዝባችን አሁን ካለበት የድህነት ወለል በታች ቦታው ጭራሽኑ ወደ መቀመቁ የድህነት ደረጃ ቁልቁል የሚወረውረው መሆኑን መረዳት የማይችል ዜጋ ካለ የተሸከመው የሰው ጭንቅላት ሳይሆን ድንጋይ እንደሆነ የትም ቦታ ሔዶ ማረጋገጥ ሳያስፈልገው እርግጠኛ ሊሆን ይችላል፡፡
በሥራ ቦታዎች ያለው ሁኔታም ተመሳሳይ ነው፡፡ ይሄ እንግዲህ በዚህ ቴሌቪዥን (ምርዓየኩነት) የሚቀርቡ የባዕዳን ምትርኢቶች በሚያደርሱት አሉታዊ ተጽእኖ ሕዝቡን ለባሕል ወረራ ጥቃት አጋልጦት ማንነቱን ሊበርዙበት ከማንነቱ ሊያራርቁት ሊያቆራርጡት ብሎም ማንነቱን ሊያጠፉት የሚችል መሆኑን ትተን ከዚህ በመለስ ያስከተለውንና እያስከተለ ያለውን ጉዳት ብቻ ስንመለከት ነው፡፡
ጣቢያው በዚህ ዘርፍ በተሠማሩ ዜጎች እንጀራ ላይ እንደመምጣቱም ምንም እንኳ በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች ወያኔ ገበያውን በሕገወጥ ቅጅ የሚያጥለቀልቁ ግለሰቦችን አደራጅቶ በማሰማራት ሥነኪንን (በዘልማድ ሥነ ጥበብን) ከማሽመድመዱና ሥነኪን ሀገርንና ሕዝብን ለማገልገል ከተጣለባት ተፈጥሯዊ ኃላፊነት አኳያ ወያኔ እንድትንቀሳቀስ ፈጽሞ ስለማይፈቅድ በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች ሥነ ኪን የሚጠበቅባትን ተግባርና ኃላፊነት እንድትወጣ ባያደርጉም ቃና ቲቪ በእነዚሁ ሁኔታውና አቅማቸው የፈቀደላቸውን ያህል እየተንቀሳቀሱ ባሉት ባለሙያዎች ባለድርሻ አካላትና በስራቸው በሚያስተዳድሯቸው ቤተሰቦች ላይ ሊያስከትል የሚችለው ጉዳትም እንዲሁ አሳሳቢ ነው፡፡ የአገሪቱ የባሕል ፖሊሲ (መመሪያ) ግን ለአገርኛ የጥበብ ሥራዎች መደረግ ስላለበት ድጋፍ ያትታል፡፡ “ጽድቁ ቀርቶ” አሉ! ድጋፉ ቀርቶ ማደናቀፉን ማሰናከሉን ክልከላውን አፈናውን ቢተው ድጋፉ ሳያስፈልግ ሥነኪናችን የት በደረሰ ነበር፡፡

የፊልም (የምትርኢት) እና የቲያትር (የተውኔት) ተመልካቹ አይደለም ከምትርኢትና ተውኔት ቤቶች ከትምህርት በመቅረትና ሥራን በማስተጓጎል ቃና ላይ ተጥዶ እየዋለና እያመሸ ነውና ለቃና ብሎ ትምህርቱንና ሥራውን የበደለ ገንዘብ አውጥቶ ከሚመለከትበት ከፊልም (ከምትርኢት) እና ከቲያትር (ከተውኔት) ቤቶችማ የሚቀር የሚርቅ መሆኑ ምንም የሚያጠራጥር አይሆንም፡፡
“እንዲህ ዓይነት የቴሌቪዥን ጣቢያ ስርጭቶች በተማሪዎችና በሠራተኞች ላይ የተገለጸውን ዓይነት ችግር የሚያስከትል ከሆነ እንዴት ታዲያ ባደጉ ሀገራት ባሉ ማኅበረሰቦች ላይ ተመሳሳይ ችግር ፈጥሮ ሀገሮቻቸውን ሳይጎዳ ቀረ?” የሚል ጥያቄ ይነሣ ይሆናል፡፡ በምእራቡ ሀገራት ተሰዶ የሚኖር ዘመድ ካላቹህ እሱ በሚኖርበት ሀገር እንኳን እንዲህ እኛ እንደምናደርገው ትምህርቱንና የሥራ ሰዓቱን በእጅጉ እየጎዳ በራሱ ላይ በሕይዎቱ ሊቀልድ ይቅርና ኑሮን ለመግፋት እንኳ ያለውን 24 ሰዓት ከስንት በጣጥሶ ስንት ሥራ እየሠራና እየተማረ በቀን ውስጥ ለሁለትና ቢበዛም ለአራት ሰዓታት ብቻ እየተኛ ሕይዎቱን እንዴት አድርጎ እንደሚገፋ ኑሮን እንዴት እንደሚኖር እየጠቃቀሰ ቢነግራቹህ አጥጋቢ ምላሽ ባገኛቹህ ነበር፡፡

እዚያ እንኳንና መሀከለኛና ዝቅተኛ ኗሪው የኅብረተሰብ ክፍል ቀርቶ ሀብታሞቹም እንኳ እረፍት አያውቁም፡፡ እረፍት ካላቸው የአጭር ጊዜ ቆይታ ሆና በእቅድ የምትስተናገድ ናት፡፡ ከትልቅ እስከ ትንሽ ከተማሪ እስከ ሠራተኛ ጊዜ እንደ ቁምጣ ያጠረውና ሕይዎቱ የሩጫ ነው፡፡ ሁሉም ዜጋ የጊዜ አጠቃቀምን (Time management) ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ምእራባዊያኑ ሕዝባቸው በእንደዚህ ዓይነት አዘናጊ ነገሮች ሕዝባቸው እንዳይዘነጋ ማድረግ የሚችል የሕይዎት ሥርዓት (System) አላቸው፡፡ በዚህ ሥርዓት የማይመራና የማይሯሯጥ ሰው ቢኖር ሥርዓቱ ራሱ ይተፋዋል፡፡ የፈጠሩት ሥርዓት አንድ ዜጋ በራሱ ስንፍናና መጃጃል ምክንያት ተተፍቶ ሲወድቅ የሱ መውደቅ ጉዳቱ የራሱ እንጅ የሀገርም እንዳይሆን ወይም ለሀገር የሚደርሳት ጉዳት በጣም አነስተኛ እንዲሆን ማድረግ እስከሚችል ድረስ ነው ሥርዓቱን የገነቡት፡፡ በዚህም ምክንያት እንደዚህ ዓይነት የ24 ሰዓታት ዝግጅቶች በእኛ ላይ ማኅበራዊ ቀውስና ምጣኔ ሀብታዊ (ኢኮኖሚያዊ) አደጋ ማድረስ የሚችሉበትን ያህል ከባድ ጉልበትና አቅም በእነሱ ላይ ጨርሶ የላቸውም፡፡ የደረሱበት ሥልጣኔ ለዚህ በእጅጉ ረድቷቸዋል፡፡
ወደ እኛ ስንመጣ ግን ያለው ነገር ሁሉ ከእነሱ በእጅጉ የተለየ ነው፡፡ ሕይዎትን እንመራታለን እንጅ እንደነሱ ሕይዎት አትመራንም፡፡ ስለሆነም እነሱ ላይ አደጋ አልፈጠረምና እኛ ላይም አይፈጥርም ማለት አንችልም፡፡ ሥርዓቱ አልተገነባማ! የለማ! አልሠለጠንማ! ጊዜን በአግባቡ አንጠቀምማ! በዚህም ምክንያት ነው በርካታ በራሳችን በሕይዎታችን የመቀለጃ ጊዜያት ያሉን፡፡ ሥራችንን ሠርተን ትምህርታችንን ተምረን ትርፍና የእረፍት ጊዜ በምንለው ረጅም ጊዜያችን እንኳን ባላገጥን ምንም ባልነበር፡፡ እኛ እኮ በትምህርትና በሥራ ጊዜ በመቀለድ ዋናውንም ውድ የሕይዎት ጊዜ ነው እየበላን እየቀለድን እየተጫወትንበት ያለነው፡፡
የወያኔ ባለሥልጣናት እንዲህ ዓይነት አደጋና መቅሰፍት በሀገር ላይ እያወረደና ሊያወርድ ያለው ይህ ጣቢያ “የእኛ አይደለም!” ብለው ሸምጥጠው በመካድ ለትርፍ የሚሠራ የባዕዳን የግል ድርጅት ነው የሚሉ ከሆነና ይህ ሁሉ መዓት በዚህች ሀገርና በሕዝቧ ላይ እንዳይደርስ የሚፈልጉ ከሆነ ይሄንን ጣቢያ በቀላሉ መዝጋት የሚችሉበት መንገድ አለ፡፡ ጣቢያው መቀመጫው ከሀገር ውጭ ይሁን እንጅ ኢትዮጵያ ውስጥ ፈቃድ ተሰጥቶት አጋርና ወኪል ድርጅቶች መሥሪያ ቤት ከፍተው ፊልሞቹን (ምትርኢቶችን) ተርጎሞ ከማዘጋጀት አንሥቶ የንግድ ማስታወቂያዎችን እየተቀበሉ በማስተናገድ ላይ ያሉ ድርጅት እንደመሆናቸው ቃና ቴሌቪዥንን ማዘጋት ቢፈለግ ለሕዝብና ሀገር ህልውናና ደህንነት አደጋ የጋረጠ በመሆኑ በሕገ ወጥነት ፈርጆ እዚህ ያለውን ወኪልና አጋር ድርጅቶች የሥራ ፈቃድ ሰርዞ ቢዘጋው እንበልና ድርጅቱ ሌላ ዓላማ ሳይኖረው ለትርፍ የሚሠራ የግል ድርጅት ከሆነ ትርፍ የሚያገኝባቸውን የንግድ ማስታወቂያዎች ማግኘት አይችልምና ወዲያውኑ ራሱን ለመዝጋት እንዲገደድና እንዲዘጋ ማድረግ ይቻላል፡፡
ለትርፍ የተቋቋመ የግል ድርጅት ነው እየተባለ በሀገር ውስጥ እንዲዘጋ ተደርጎ ማስታዎቂያዎችን ሳያገኝ ያለትርፍ በኪሳራ ከሆነ አካል እየተደጎመ ስርጭቱን የሚቀጥል ሆኖ ከተገኘ ያኔ ዓላማው በግልጽ የሚታወቅ ይሆናል፡፡ ውጊያውም ግልጥ በግልጥ ይሆንልናል፡፡ ስርጭቱንም ለማስቆም የሚወሰደው እርምጃ ሌላ ይሆናል፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን ይሄ ሁሉ በሚያሳዝን ሁኔታ ከንቱና የማይሆን ምኞት ነው፡፡ ያሉ ነገሮች ግልጽና የታወቁ እንደመሆናቸው የተጀመረው የጥፋት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል እንጅ የተለየ እርምጃ ሊወሰድ የሚችልበት ዕድል እንደማይኖር ሳረዳቹህ በታላቅ ሐዘን ነው፡፡
የሚመለከታቸው የአገዛዙ ሹማምንት ጉዳዩን “ሕዝብ ይወስንበት! አይጠቅመኝም ካለ እራሱ ወይም ገበያው ይጣለው!” በማለት በሕዝብ ላይ ሲቀልዱ ተደምጠዋል፡፡ ነው እንዴ! ጨዋታው እንዲያ ከሆነ ታዲያ ምነዋ ኢሳትን እንዲያ እየወደድነው እየናፈቅነው ቤታችን ድርሽ እንዳይል አድርጋቹህ ካለበት የምታስቀሩብን ለምንድን ነው? “ለማያውቅሽ ታጠኝ” አለ ያገሬ ሰው፡፡
ይሄንን እያሉ ያሉ የወያኔ ሹማምንት በእርግጠኝነት የተሰጣቸውን ኃላፊነት ፈጽሞ የማያውቁ ናቸው፡፡ ይህ ጉዳይ “ሕዝብ ወይም ገበያው ይጣለው!” በመባል የሚታይ ከሆነ ለእነኝህ ደናቁርት ባለሥልጣናት ልጠይቀው የምፈልገው ጥያቄ ቢኖር፡- አደንዛዥ ዕፆች ምንም እንኳን ጎጂ መሆናቸው ቢታወቅም ተጠቃሚዎቹ ግን ይጠቅመናል እስካሉ ጊዜ ድረስ ለምንድነው ታዲያ እንዲጠቀሙና እንዲያዘዋውሩም ሕግ የማይፈቅድላቸው? እንዲህ እንዲህ እያልን በሕግ የተከለከሉ በርካታ ነገሮችን በመጥቀስ ጎጅነት እንዳለው እየታወቀ ይጠቅመናል ይሆነናል የሚሉ ወገኖች እስካሉ ጊዜ ድረስ ብቻ ፈቃድ እንደማያገኙ እንደሚከለከሉ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

አንዳች ተንኮል ከሌለው በስተቀር “ሕዝቡ ይወስን! ገበያው ይጣለው!” ልንባል አይገባም፡፡ ማኅበረሰባችን የመዝናኛ ዝግጅቶች ባላቸው ከፍተኛ የመማረክ ጉልበትና ኃይል ስለተሸነፈ እንጅ በብዙ መልኩ እንደሚጎዳው እንደሚያዘናጋው ሳያውቅ ሳይረዳ ቀርቶ አይደለም በዚህ መልኩ እራሱን እያጃጃለና እየጎዳ ያለው፡፡ ይህ የወያኔ ባለሥልጣናት አባባል ሕዝባችን ከመጃጃሉ የተነሳ “ይቅርብኝ! ይዘጋ!” ብሎ እንደማይወስን በማወቃቸው የሚሰነዝሩት ንቀት የተሞላበት አነጋገር ነው፡፡
ወያኔ አንዴ በማያገባን በማናውቃቸው ኪሳራ እንጅ በሕይዎታችን አንዳችም የሚጨምርልን ትርፍ በሌለው የአውሮፓ ሀገራት እግር ኳስ፣ ሌላ ጊዜ በጫትና በሺሻ ሱስ፣ ሌላ ጊዜ በድራማ (ትውንተ ኩነት) እና በፊልም (ምትርኢት) ወዘተረፈ. አንተን በጊዜህ በሕይዎትህ ቀልደህ አረንቋ ውስጥ እንድትሰምጥ ለማድረግ የፈለገውን ያህል ሴራ ቢሸርብ እኛ ነቅተን አንሰማም! አንመለከትም! አንዘናጋም! አንጃጃልም! ብንል ሴራው ምን ይፈይድለት እሱስ የት ይደርስ ነበር? የትም!
ወያኔ ለምንና እንዴት ትውልድን መቀመቅ ውስጥ ለማስጠም ሆን ብሎ ይሄንን እንደሚያደርግ ከዓመታት በፊት “ሱስ ትውልድና ሀገር” በሚል ርእስ የጻፍኩትን ጽሑፍ ጎግል አድርገህ በመመልከት ማረጋገጥ ትችላለህ፡፡
እርግጥ ነው ሆንብሎ ለማጥፋት ትውልድን መቀመቅ ለማስመጥ ተግቶ የሚሠራ በመንግሥት ቦታ ያለ የጥፋ ኃይል ባለበት ሁኔታ ምን ብታደርግ ከወጥመዱ አመልጣለሁ ማለት ዘበት ሊሆን ይችላል፡፡ እንግዲህ ታዲያ ምን ይዋጥህ ወገን? ወያኔ እንደ አህያነቱ በ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” አስተሳሰቡ ለግል ጥቅሙ ሲል ሀገርንና ሕዝብን የሚጎዱ ተግባራትን በመሸረብ መጠመዱ ግራ የሚያጋባው፣ የሚደንቀው፣ የሚገርመው ዜጋ ይኖር ይሆን? ወያኔ ነኝ ብሎ ማንነቱን በራሱ አንደበት በግልጽ እየተናገረ የጠላትነት ስሜት ተሞልቶ፣ ጥፋት ተጭኖ ከመጣ ጠባብና ደንቆሮ የወሮበላ ቡድን ታዲያ ከዚህ የተለየ ምን ይጠበቅና ነው ግራ የሚገባው? የሚገርመው? የሚደንቀው? እያንዳንድሽ አርፈሽ ጸጥ ብለሽ መቀመቅሽን ውረጅ! በፊትስ እሽ ሳታውቂው ቀርተሽ ይባል በኋላ ላይ ግን የወያኔን ማንነት ከተግባሮቹ ካወቅሽ በኋላ እያንዳንድሽ ላለመበላት፣ ላለመታረድ፣ ላለመነቀል፣ መቀመቅ ላመውረድ ምን ያደረግሽው ነገር አለ? ምንም! ስለዚህ አርፈሽ ዝም ብለሽ ተጋድመሽ ታረጅ!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com


ግርግዳ የሌለው ቤት በሩ ይቆለፋል ወይ? | ከመኳንንት ታዬ (መ..ታ )


ethiopia
የምንኖርባት አለም ሰዎች የሚተዳደሩባት የሚያስተዳድሩባትም ፤ ብበሎም  ገዢና ተገዢ ሃብታም እና ደሃ ፤እያለ ይቀጥላል ።እንዲህ ባለው ስርአት ውስጥ  የተፈቀደልንን መስመር እየረገጥን እንኖራል።በዚህ ሄደት  አንዳንዶች ቆዳቸው ሲሰፋቸውና ጫማቸው ሲያድግባቸው  እሰው መስመር ልኬት ገብተው በመርገጥ ፉርሽ ነው ይሉናል ። የረገጥነው የተፈቀደልንን መሆኑን ስናቅ ፤የለም በልኬ ነው ያለሁት ባልን ግዜ  ያልተገቡ ረጋጮች  ይጣሉን ይጀምራሉ።በዚህን ግዜ በንኪኪ የሚመጣ ጥል ይፈጠርና በቅርብ በሚያስቡና በሚያዩ ዘንድ  ጥፋተኛነታችን ሲነገረን ይኖራል።አርግጥ በዚህ ምሃል ግጭት የመነሳቱ ሁነት  አውነት ነው ። አሸናፊው  እንደ አያያዙ  ይሆናል። አብዛኛውን ግዜ እራስ ወዳዶች  ጫማቸውም  የራስ ቅላቸውም ሰፊ ስለሆነ  የሰው መስመር መርገጥ ይቀናቸዋል ።እንዲህ ካለ ስርአት እያደገ ሄዶ ሐገር ጥግ ሲደርስ  የራሳቸውንም የሰውንም መስመር መርገጥ የሚቀናቸው አስተዳዳደሪዎች ይፈጠራሉ። የዛኔ ሃገርም ፤መኖሪያ ሰፈርም ፤መኖሪያ ቤትም ፤በልኩ የሚረግጡ ሰዎች ባለቤቷ አይሆኑም ።ምክንያት ከላይ ሲውርድ እንደመጣው አይነት የእድገት ደረጃ  ባለቤቱ  ሆኖ የተፈጠረው ግለሰብ ነውና ።
ለመንደርደሪያ ታህል ይህን ካልን ግርግዳ የሌለው  ቤት በሩ ይቆለፋል ውይ ? ወደሚለው ርእስ  እንዲህ እንዝግም። በዚህ ርእስ ሰንሰለት  አጥርና በር ብሎም ግርግዳ የሌላት ሃገራችንን እናስታውስና እንዲህ እንበል። መሪዎቻችን ሊያኖሩን አልያም እየቆጠሩ ህዝብ አለ ሊሰኙበት ሃገሪቷን ከተረከቡ  ብዙ ዘመን አለፈ።ቁጥሩን መጥቀስ አስፈላጊነቱ አላመንኩበትም። ለማውራት የፈለኩት ከታች ጀምሮ ከሆነ እለቀ መሳፍርት  ወረቀት አይበቃም። ስለዚህ በቅርብ ከተፈጠረው  ከጋንቤላ እንነሳ ።መገደል ብርቃችን አደለም ።ምን እሱ ብቻ ገዳዮቻችንንም  መቃወም ያስገድላል።ይህ አይነት አስተዳደር ለማንኛውም  አለም ላይ ለሚገኝ ፍጡር  ያማል ።በር የሌላት ሃገር፤ህዝቦቿ በሄዱበት እየተዋረዱ  የሚሸማቀቁባት ሃገር ፤ ሃገር ፤ሀገር ……፤እያለ በየማዝናቱ አሳፋሪና አስፈሪ ነገሮች ባለቤት የሆኑ ህዝቦች ፤ስሟ  ኢትዮጲያ በተባለ ሃገር እንኖራለን። በዚህ ምክንያት  ሃገር ስም  የያዙትስ ትልቅናቸውና  ትንሽ ልብ ባለው  መንግስት  ከቶ ይፈሩ ይሆናል ።እንዴት  የአንድ ብሔረስብ ወሮ በላ ጎሳውች የአንድን ሐገር  ህዝብ ገድለውና ልጆ ቻቸውን ከብቶቻቸውን  ወስደው ሲያበቁ  በድርድር ለማስመለስ በሚል ደካማ ሃሳብ ይኖራል ። አረ እንደውም  የጋምቤላው አስተዳዳሪ እንዳሉት ልጆቹ ይመለሱ እንጂ ከነኚ ጋር ማን ይነጋገራል አይነት ነው። በቃ ኢትዮጲያዊ እንዲህ ነው ።አለቀ ።ይህ በርግጥ ከሙት ባህር አጠገብ  የተቀመጠ ሙት አስተዳደር ነው እንጂ፤ በእውነቱ ስም ያላት ሀገርን የሚያስተዳደር መንግስት  ከቶ ሊዋጥለት አያስፈልግም።አስከመቼስ  የታጠቀውን መሳሪያ  የገዛ ህዝቡን የሚያስፈራራበት ይሆናል ።ለሚቃወሙተስ ስንት አስር ቤት? ስንት አሳሪ ፖሊስ?  ስንት ፈራጅ ዳኛ? ስን ስንት ስንት ያስፈልጋል። በአገዛዝ ደረጃ  ለተቀመጡት  ባለዱላዎቸስ በስልጣን   የተቀመጡ መሪዎች ጉልበታችሁን እንዴት አሳንሰው እንደሚመለከቱት  አለመገንዘባችሁ ምን ቢጠፋችሁ ወይስ ምን ብታጡ ነው።ትልቅነት ነገን  ማየት እንጂ  ዛሬ ላይ በድንግዝግዝ እየኖሩ በዳበሳ መሄድ አደለም።
ማንነታችን እኛነታችንን የምናፅበት መስመር የተሰራልን ያለሙግት  የምንኖርባት ሐገር ባለቤቶች ነን።ትልቅነታችን ሲያስመሰግነንና ሲያስከብረን ኖረን የእኛ ባማይሏት ገዢዎች መስመሯን ስታ  የነገ ባለ እራቁት ሐገር ለማድረግ ደርሻዬ ከሚሉት ባለፈ ሐገርን በገፈፋ እና በብትር ለማስተዳደር መሞከር ክብሩ ምን ያህል ነው?።ሕዝቦች መሪዬ የሚሉት ሲጠፋ እንደመንደር ሰው እየተከተሉ የሚሰድቡት ባለስልጣን ማየት የ25 አመቱ የመልካም አስተዳር  ውጤት  አማራጭ የሌለው አድገት  መሆኑን የተቀረው አለም እንዴት የሚያው ይመስላቸውኋል?።ህዝቦች ብዙዎች ናቸው ያስፈራሉ።የመንግስት ባለስልጣናት ጥቂቶች ናቸው ይፈራሉ።ምክንያቱም የኔ የሚሉት  ሀገር በስማቸው አለችና ነው።ከሀገሩ ክብር  የሸሸ ባለስልጣን ከሚመራው ህዝብ ለሱ ብሎ የተቀመጠ ባለሞኖሩ ዛሬ የምናነየውን  አሰዛዥ  እጣ ፋንታ  ሁሉም በየተሰለፈበት መስመር ሲፈፅም ማየት ነው ።ከወንበሩ በስተቀር በስፋት  የተለየ ነገር  ባለመኖሩ ወደታች በመውረድ በትልቅ ደረጃ አሰራር ያለት ሐገር ግለሰቦች  ከሀገር እንዳይወጡ ፓስፖርታቸው  ዘይት ነካው በሚል ጎስቋላ ምክንያት  ብሎም  በየአይሮፕላን ጣቢያ ተቀምጦ ግለሰቦችን ከስራቸው በማጎሳቆል  ማሰቃየት  ይህ የወንበርን ስፋት ከማየት የመጣ የአንቶ ፈንቶ አስተዳደር  ስርአት  ነው። የሚያሳዝነው  ወደፊት ለመሄድ ከኋላ ስንት ሜትር እንዳለፉ አለማስታወሳችሁ ነው። ዛሬን  በዚህ ስርአትና ውርደት ለመኖር ከሆነ ትላንት የታገላችሁት ሃሰባችሁ ረፍዶበታል ።አልተኛችሁም ለማለት ከሚመጣው  የጋራ ክፉ ነገር  ወንበራችሁ  ላይ  እንዳይነጋ የማታዋን ፀሃይ ተጠቅሞ  ከግርግር መንግስት  የሽግግር መንግስት ብታቋቁሙ ለቤቱ ግርግዳ  ለመዝጊያውም በር  ከህዝቡ ጋር ሆናችሁ ትሰራላችሁ ማለት ነው ።
ቸር እንሰንብተ

Thursday, May 19, 2016

የቤኒሻንጉል ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አህመድ ናስር አረፉ

ahmed


(ዘ ሐበሻ) የቤኒሻንጉል ክልልን ከ2001 ጀምሮ በፕሬዚዳንትነት ሲመሩ የቆዩትእና የአማራን ሕዝብ ለይተው ከቤንሻንጉል በማፈናቀል ቤት እና ንብረታቸውን እንዲያጡ በማድረግ ወንጀል ከሚጠየቁ ባለስልጣናት መካከል አንዱ የነበሩት አቶ አህመድ ናስር ሕይወታቸው ማለፉ ተሰማ::

ከሃገር ቤት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙትና የመንግስት ሚዲያዎችም እንደዘገቡት የርዕሰ መስተዳደሩ የቀብር ስነስርዓት አሶሳ ከተማ ውስጥ ይፈጸማል::
የኢህ አዴግ ተለጣፊ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆኖእው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲዊ ፓርቲ (ቤጉህዴፓ) በምክትል ሊቀመንበር የነበሩት አቶ አህመድ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ በእርሻ ምህንድስና፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በቻይና ሆሃ ዩኒቨርሲቲ በውሃ ምህንድስና የተከታተሉት አቶ አህመድ ናስር በአሁኑ ወቅት የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር በቀድሞው ግብርና ገጠር ልማት ሚኒስትር ዴኤታነት ማገልገላቸውን የመንግስት ሚድያዎች ዘግበዋል::
የበሽታው ዓይነት ባይገለጽም አቶ አህመድ ለረዥም ጊዜ በውጭ እና በሃገር ቤት ህክምና ሲከታተሉ መቆየታቸው ሲሰማ ሕይወታቸው ሲያልፍም የ51 ዓመት ጎልማሳ እንደነበሩ የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል::
በ1957 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ፈንታሌ ወረዳ ጠዴቻ መልካ ቀበሌ የተወለዱት አቶ ናስር የአንድ ልጅ አባት ነበሩ ተብሏል::
አህመድ ናስር ከ2 ሺህ በላይ አማሮች ከቤንሻንጉል ክልል እንዲፈናቀሉ ካደረጉ በኋላ መጨረሻ ላይም “እነዚህን አማሮች ያፈናቀልነው በስህተት ነውና ወደ ክልላችን ይመለሱ:: አማሮቹ እንዲወጡ የተደረገው በበታች ባለስልጣናት ግብታዊነት ነው” በማለት ይቅርታ መጠየቃቸው በወቅቱ በዘ-ሐበሻ በኩል መዘገቡ አይዘነጋም:

Wednesday, May 18, 2016

በቅርቡ ከእስር የተፈቱት መምህር ግርማ በድርቅ ለተጎዱት ወገኖች ከሚሊዮን ብር በላይ ረዱ

memihir grma

(ዘ-ሐበሻ) በቅርቡ ከተከሰሱባቸው ክሶች በዋስትና የተፈቱት መልዐከ መንክራት ግርማ ወንድሙ በድርቅ ለተጎዱት ወገኖች መርጃ የሚሆን ገንዘብ በ እርዳታ መልክ ሰጡ::
መምህሩ በኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ በኩል ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ሁለት ሚሊዮን አርባ ስምንት ሺህ ስምንት መቶ ዘጠና ሁለት ብር ከሃምሳ ዘጠኝ ሳንቲም (2,048,892.59) ዛሬ ገቢ አድርገዋል::

በቦሌ ቡልቡላ ቤታችን አይፈርስም ያሉ ወገኖች የፌደራል ፖሊሶች ጥይት ራት ሆኑ

(ዘ-ሐበሻ) በአዲስ አበባ ከተማ ወረዳ 12 በተለምዶው ቦሌ ቡልቡላ በተሰኘው አካባቢ በሕገወጥ መንገድ ተሰርተዋል በሚል የፌደራል ፖሊሶች እና የአካባቢው አፍራሽ ግብረሃይል ዛሬ ጠዋት ቤቶችን ለማፍረስ ሲንቀሳቀሱ ከአካባቢው ሕዝብ ጋር በተነሳ ግጭት በርካቶች መቁሰላቸውና ህጻናት ሳይቀሩ መሞታቸው ተዘገበ::


ቦሌ ቡልቡላ (ፎቶ ከፋይል)

ከስፍራው የሚመጡ መረጃዎች እንደሚያመለከቱት “ከቤታችን ወዴት እንሂድ?” ያሉ የአካባቢው ነዋሪዎች በፌደራል ፖሊሶች እና በአፍራሽ ግብረሃይሉ ቤታቸው ሊፈርስባቸው ሲዘጋጁ ግጭቱ ጀምሯል:: ከዚያም የፌደራል ፖሊሶች ወደሕዝቡ የተኮሱ ሲሆን እስካሆን በግምት 9 ወይም 10 የሚሆኑ ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉና ሌሎችም በርካቶች መቁሰላቸው ተሰምቷል:: ቤቶችም መፍረሳቸውን ቀጥለዋል::
ምንጮች እንደሚሉት በኦሮሚያ ሕዝባዊው አመጽ ከተነሳ በኋላ ፌደራል ፖሊሶች ለህዝብ ተቃውሞ ምንም ዓይነት ሰላማዊ ምላሽ መስጠት አቁመዋል:: በቀጥታ ወደ ሕዝብ መተኮስ የጀመሩ ሲሆን ዛሬም ቤታችንን አታፍርስ; እኛን አፈናቅላችሁ መሬቱን አትሽጡ ባሉ ወገኖች ላይ ምላሹ ጥይት መሆኑ ብዙዎችን አሳዝኗል::
ይህ በ እንዲህ እንዳለ ሕዝቡ በፌደራል ፖሊሶቹ ላይም ጥቃት ማድረሱን መረጃዎች የሚጠቁሙ ሲሆን ዘ-ሐበሻ ምን ዓይነት ጉዳት በፖሊሶቹና አፍራሽ ግብረሃይሉ ላይ እንደደረሰ ለማጣራት ያደረገችው ጥረት አልተሳካም::
በአካባቢው ያለው ውጥረት ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ እንዳየለ ነው:: ጉዳዩን ተከታትለን ለመዘገብ እንሞክራለን::

“የትግላችን መሰረት ህዝባችን ነው እና ህዝባችንን ተደራሽ ለማድረግ የምናደገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል!” – ድምጻችን ይሰማ


ረቡእ ግንቦት 10/2008
ትግል ክስተት ሳይሆን ሂደት ነው፡፡ ይህን ሂደት የሚፈጥሩትም ሆነ ከዳር የሚያደርሱት ደግሞ የትግሉ ባለቤት የሆኑት ህዝቦች ናቸው፡፡ እንደአገራችን ባሉ ዲሞክራሲ ባልዳበረባቸው አገራትና አሁን ባለው አለም አቀፍ ተለዋዋጭ ፓለቲካ የትግል ሂደት እንደ ሜዳ ለጥ ያለና የተደላደለ አይደለም፡፡ እንቅፋትና አሜኬላ የበዛበት፣ በዳገትና ቁልቁለት የተሞላ ነው፡፡ የትግሉ ባለቤቶች በእነዚህ የትግል ተፈጥሯዊ ሂደቶች ውስጥ ሲያልፉ የሚኖራቸው ምላሽ እንደግለሰባዊ ጥንካሬያቸው፣ ለትግሉ እንዳላቸው እምነት፣ እንደ ልምድና እንደተሞክሯቸው ይለያያል፡፡ ጥቂት ነገሮች ውዥንብር የሚፈጥርባቸው እንዳሉ ሁሉ በፕሮፓጋንዳ እና በአሉባልታ ቀርቶ በኃይልም የማይፈቱ ቆራጥ ታጋዮች በርካቶች ናቸው፡




zehabesha-muslim.jpg


የአንድ የትግል ሂደት ከሚገጥሙት ተግዳሮቶች መካከል የብዙሀኑን ህዝብ ስሜት ከነባራዊው ሁኔታ ጋር በማጣጣም ትግሉን ስኬታማ የሚያደርግ የትግል አቅጣጫ መንደፍ ነው፡፡ ይህን የትግል አቅጣጫም የትግሉ ባልተቤት የሆነው ህዝብ በሚገባ ሊረዳው ይገባል። የትግሉን አቅጣጫ ህዝብ በትክክል ካልተረዳው ትግሉን ከዳር ማድረስ አስቸጋሪ ይሆናል። የትግሉ አቅጣጫ በትክክል ለህዝብ ባልደረሰበት ሁኔታ በትግሉ እና በደል በሚፈጥረው ህዝባዊ ቁጭት፣ ይህም በተራው በሚወልደው የህዝብ ስሜት መካከል ክፍተት ይፈጠራል፡፡ አንድ ህዝባዊ ትግል በቀዳሚነት ከሚይዛቸው ተግባራት መካከል የትግልን ሂደት እና አቅጣጫ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ታጋዩ ህዝብ ዘንድ ማድረስ እና ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ማከናወን እና ህዝባዊ መነቃቃትንም መፍጠር አንዱ እና ወሳኙ ጉዳይ ነው። በተለይም ትግሉ የረጅም ጊዜ ትግል በሆነበት ተጨባጭ ከህዝብ ልብ ውስጥ አስጠብቆ ማቆየት እና የህዝብን ወኔ በበዳዮች ብትር ብዛት እንዳይሰበር ተከታታይ እና ቋሚ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራን መስራት የትግሉን ህልውና ማስጠበቂያ አንዱ መሳሪያ ተደርጎ ሊታይ ይችላል።
ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች በመንግስት የተጫነብንን ብሄራዊ ጭቆና በዘላቂነት ለማስወገድ የሚያስችል የትግል አቅጣጫ አስምረን እንገኛለን። ይህ ትግላችን ጨቋኙ ስርዓት ትግስታችን እንዲሟጠጥ፣ ወኔያችን እንዲሰበር በማቀድ በሚከፍታቸው በሮች ውስጥ የሚያስገባ፣ ከተመከረበትና ከታሰበበት የትግል መስመር ወጥተን ግብታዊነትን ወይም ስሜታዊነትን እንድንከተል የሚያደርግ፣ ሁሉን አቀፍ በሆነ መብት የማስከበር ትግል ፋንታ ጥቃቅን ቀዳዳዎችን ብቻ በሚደፍኑ ጊዜያዊ የትግል ስልቶች ተሸብበን እንድንቀር የሚያደርግ ሂደትን የሚከተል አይደለም። ትግላችን የህዝብን ፍላጎት የተረዳ፣ ተለዋዋጭ ስሜትን ከነባራዊ ሁኔታው ጋር በማዛመድ እና ሚዛኑን በመጠበቅ ከጊዜያዊ ክስተቶች ይልቅ መርሆች ላይ የተመረኮዘ ነው። ትግላችን ወቅታዊ እና ተጫባጩን የሚያውቅ፣ የግንዛቤ አድማሱ ሰፊ የሆነ፣ የሚጠበቅበትን የተገነዘበ፣ የትግሉን ሂደትና ፍሰት በሚገባ የተረዳ፣ የአገሩን እና የማህበረሰቡን አብይ ችግሮች በመለየት ለችግሮቹ ተጨባጭ መፍትሄ የማስቀመጥ አቅም ያለው፣ እምነቱን በትክክል ተረድቶ ተግባራዊ የሆነ እና የሰለጠነ ማህበረሰብ በመፍጠር ሙሉ መብታችንን የምንጎናፀፍበት እና ይህንም በዘላቂነት የምናስጠብቅበት ትግል ነውና አቋራጭ መንገድ የለውም!

muslim a

የትግል አቅጣጫችን ራሳችንን በማጎልበት እና በመንግስት ላይ ጫና ሊፈጥሩ የሚችሉ ተለዋዋጭ ስልቶችን ቀርፆ ተግባራዊ ከማድረግ ባልተናነሰ የህዝቡን ግንዛቤ ከትግሉ አቅጣጫ ጋር ተመቻማች እንዲሆን ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ መስራት አለበት። ለትግላችን ስኬታማነት የተነደፈው የትግል አቅጣጫ ብቻውን በቂ አይደለም። ይህንን የትግል አቅጣጫ ተግባራዊ የሚያደርገው ህዝብ አቅጣጫውን በትክክል ተረድቶ፣ ይህንንም ጠብቆ እና አስጠብቆ በሚያደርገው የትግል እንቅስቃሴ ጭምር መሆኑንም በትክክል እንረዳለን።
በቀጣይ የትግል አቅጣጫችን እና ከህብረተሰባችን የሚጠበቀውን አስተዋጾ በተመለከተ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ እነዚህን ስራዎች ህዝብ ጋር ለማድረስ ያሉን አማራጮች ውስን በመሆናቸው ማህበራዊ ድህረ-ገፅን በጊዜያዊ አማራጭነት ለመጠቀም ተገደናል። በዚህም ምክንያት አስፈላጊ የሆኑ ርእሶች በፅሁፍ ሲዳሰሱ ቆይተዋል። ይህ ግን ብዙሃኑን ህዝብ ለመድረስ አላስቻለንም። ችግሩ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ቁጥር አናሳነት ብቻ እንዳለመሆኑ መጠን ማህበራዊ ሚዲያ ለመጠቀም እድሉ ያለው ህብረተሰባችንም መልእክቱን ሊያገኝ የሚችልባቸውን መንገዶችን ማመቻቸት እና አማራጮችንም ማቅረብ ያስፈልጋል። በዚህ ዙሪያ በቀጣይ ሰፊ ስራ ይጠብቀናል። በመሆኑም እስካሁን ከምናስተላልፋቸው የፅሁፍ መልዕክቶች ባሻገር በተለያዩ ርዕሶችና የትግል አቅጣጫችን ዙሪያ ሳምንታዊ የድምፅ መልዕክቶችን መጀመር ቀዳሚ አማራጭ እና ለቀጣይ ስራ አጋዥ ተደርጎ ተወስዷል። ከዚህ አንጻር እስካሁን በጽሁፍ የተለቀቁ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ጨምሮ ተከታታይ መልእክቶችን በቅርቡ በአላህ ፍቃድ በድምጽም የምናደርስ ይሆናል። ይህ ጅምር በሙያው ችሎታ እና ፍላጎት ያላቸው እህትና ወንድሞች ለትግሉ ቀጥተኛ አስተዋጾ ለማድረግ የሚያስችል አንድ በር ነው እና ይህን ሀላፊነታችንን ሁላችንም እንወጣ ዘንድ በአጽንኦት እንጠይቃለን።
ትግላችን በተጠናከረ መልኩ ሁሉን አሳታፊ ሆኖ ይቀጥላል!
ብሄራዊ ጭቆናን አንሽከምም!
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማል!
አላሁ አክበር