Friday, May 20, 2016

ቃና ቴሌቪዥን ንብረትነቱ የማን ነው? ዓላማውስ ምንድን ነው? | ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

ቃና ቴሌቪዥን (ምርዓየኩነት) እንደ ፋና ራዲዮ (ነጋሪተ ወግ) ሁሉ መቀመጫውን በዓረብ ሀገር ያደረገ ሞቢ ግሩፕ በሚባል የውጭ ድርጅት ስም የተመዘገበ የአገዛዙ ባለሥልጣናት እንደሆነ ይነገራል፡፡ አቶ ዘረሰናይ ብርሃነ፣ አቶ መሐሪ፣ አቶ ኤልያስ ሽሉዝ፣ የ251 ኮሙዩኒኬሽን ባለቤቶች አቶ ናዝራዊ ገብረ ሥላሴና አቶ አዲስ ዓለማየሁ የተባሉ ግለሰቦች ደግሞ በመሠረቱት የጋራ የሽርክና ድርጅታቸው የቴሌቪዥን ጣቢያው የሚልክላቸውን ፊልሞች (ምትርኢቶች) በተለምዶ የጃፓን አምባሳደሮች መኖሪያ ከሚባለው አካባቢ በሚገኝ ሕንፃ ላይ በተከራዩት ሦስት ፎቆች ስድስት ስቱዲዮዎችን (መከወኛ ክፍሎችን) ገንብተው ፊልሞችን (ምትርኢቶችን) እየተረጎሙ ለጣቢያው ያቀርባሉ፡፡

zana ana chandra

kkanaየቴሌቪዥን ጣቢያው ዋና መቀመጫው ከሀገር ውጭ እንዲሆን የተደረገውም ሆን ተብሎ ለዓላማና በምክንያት ነው፡፡ ይሄንን ጣቢያ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን የአሁኑን ኢቢሲን አስጎምጅ የማስታወቂያ ገቢ ለመውሰድ ያሰቡ የወያኔ ባለሥልጣናት ናቸው ያቋቋሙት፡፡ ይሁን እንጅ ዋና ዓላማው ግን ይሄ አይደለም፡፡
አስቀድሞ ግን የውጭ ሀገራትን ፊልሞች ወደ አማርኛ በመተርጎም ለተመልካች ለማቅረብ የአየር ሰዓት በኪራይ እንዲሰጣቸው ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ማለት ለኢቢሲ ፕሮፖሳል (ንድፈ ሥራ) ያቀረቡ ሌሎች ነበሩ፡፡ ወያኔ እንደልማዱ ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከግለሰቦች ፕሮፖዛል (ንድፈ ሥራ) ሲቀርብ ለእሱ ጠቃሚ መስሎ ከታየው ፕሮፖሳሉን ያቀረበውን ወይም ያቀረቡትን ግለሰቦች ፈንግሎ ነጥቆ ይወስድና ለራሱ ሰዎች እንዲጠቀሙበት እንደሚያደርግ ሁሉ ይሄንንም ሊጠቀሙበት ስለፈለጉ ካቀረቡት ሰዎች እጅ በመንጠቅ ለራሳቸው አገረጉት፡፡ ፕሮፖሳሉን ለኢቲቪ ያቀረቡት ግለሰቦች ግን የሚያውቁት ኢቲቪ ለጥያቄያቸው በወቅቱ ተገቢውን ምላሽ በወቅቱ ሳይሰጣቸው ጉዳያቸውን በማዘግየቱ በመጥፎ ባጋጣሚ በውጭ ድርጅት መቀደማቸውን ነው፡፡
የወያኔ ባለሥልጣናት ቃና ቴሌቪዥንን (ምርዓየኩነትን) ያቋቋሙበት ዓላማ አንደኛው ከላይ እንደጠቆምኩት ለጥቅም ማለትም ከማስታወቂያ የሚገኘውን ከፍተኛ ገቢ በግል ለማግኘት ሲሆን፡፡ ዋናው ጥቅምና ዓላማ ግን የሕዝብን ትኩረት በመያዝና ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዳይሔድ በማቀብ ተቆጣጥሮ በመያዝ አገዛዙ ከሚፈጥረው ከወቅታዊና ነባራዊ ችግሮች የሚነሣን የሚቀሰቀስን ሕዝባዊ ዐመፅን አለመረጋጋትንና እንቢጠኝነትን ከሩቁ ለመከላከል ነው፡፡ ዓላማው ይሄ ይሁን እንጅ “በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ” እንዲሉ ቃና ለወያኔ የሚሰጠው ጥቅም ከሁለት ወፍም በላይ በርካታ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የሚፈልገውን የጥፋት ውጤት ለማምጣት ብዙ ሲደክምበት የቆየውን ነግር ሁሉ በአቋራጭ በአጭር ጊዜ እያመጣለት ነው፡፡ ወደ ኋላ እንመለስበታለን፡፡
ቃና ቲቪን ለመክፈት ባለሙያ ለማሠልጠን ብቻ ከሁለት ዓመታት በላይ ጊዜ ወስዷል፡፡ በቅድሚያ ኢ.ቢ.ኤስ. የተባለው ጣቢያ እንዲከፈት የተደረገው ለማላመጃ ነው፡፡ ስለ ኢ.ቢ.ኤስ. አገልግሎትና ዓላማ ከዓመታት በፊት “ቶክ ሾው (ትዕይንተ-ወግ) ከያኔያንና ጥበብ በሀገራችን” በተሰኘው ጽሑፍ ላይ መግለጤ ይታወሳል፡፡
ታስታውሱ እንደሆነ የሀገሪቱ ብቸኛው ቴሌቪዥን (ምርዓኩነት) ኢቲቪ የአሁኑ ኢቢሲ ለረጅም ዓመታት ድራማን (ትውንተ ኩነትን) ጨምሮ ለመዝናኛ ዝግጅቶች ትኩረት ነፍጎ ቆይቶ ነበር፡፡ የጣቢያው ሙሉ ትኩረትና ሥራ ፕሮፖጋንዳ (ልፈፋ) ብቻ ሆኖ እጅግ አሰልቺ በሆነ መንገድ የወያኔን አደንቋሪ ልፈፋዎችንና ሐሰተኛ ወሬዎችን ማስተላለፍ ብቻ ሆኖ ቆይቶ ነበር ሥራው፡፡ በዚህ ረጅም ወቅት ጣቢያው የነበረውን ክብር ተአማኒነትና መወደድ ለማጣት ተገዷል፡፡
ከምርጫ 97ዓ.ም. በኋላ ወያኔ የደረሰበትን ኪሳራ ለመቀልበስ ከነደፋቸው አቅዶች አንዱ አስቀድሞ ሕዝቡን መዝናኛ ዝግጅቶችን ነፍጎ ያላ አማራጭ የራሱን አደንቋሪ አሰልቺ አስቀያሚና አስጠሊታ ልፈፋ ብቻ እንዲሰማ ማስገደዱ ሕዝቡን ምሬቱና መታፈኑ እንዲሰማው እንዲታወቀውና አሻፈረኝ እንዲል እንዳደረገው በመረዳቱ ጨርሶ ትኩረት ነፍጎት የነበረውን የመዝናኛ ዝግጅት ከፍተኛ ትኩረት ሰጠውና በተለይ ድራማዎችን (ትውንተ ኩነቶችን) በገፍ እንዲቀርቡ በማድረጉ ከሀገር ውስጥ እስከ በባዕዳን ሀገራት በስደት እስካለው ወገን ድረስ ሕዝቡ የወሬው የወጉ የጫወታው ርእስ እየቀረቡ ያሉት ድራማዎች (ትውንተ ኩነቶች) ሆነው ሲያይና በዚህም ምን ያህል ትኩረት ማስቀየስና መያዝ እንደቻለ እንደተጠቀመም ሲረዳ በዚህ ጉዳይ ላይ የበለጠ ቢሠራበት ሕዝብን ማዘናጋትና ትኩረቱን ወደሌላ ሳያደርግ መያዝ እንደሚችል በማመኑ የበለጠ ሊሠራበት የሚችልበትን መንገድ በሚያሰላስልበት ወቅት ነው የእነዚያ ሰዎች ንድፈ ሥራ (ፕሮፖዛል) በእጁ የገባው፡፡
ፕሮፖሳሉ (ንድፈ ሥራው) በእኛው ባለሙያዎች እየተዘጋጁ የሚቀርቡት ድራማዎች (ትውንተ ኩነቶች) ከሚጠይቁት ወጭና ተጓዳኝ ሁኔታዎች አንጻር የውጪ ፊልሞችን (ምትርኢቶችን) ተርጉሞ ማቅረብ በጣም በቀላል ወጭ የሚከወንና እጅግ በጣም ወጭ ቆጣቢ አትራፊም መሆኑን በመረዳት ከዚህ ዝግጅት የሚገኘውን ፖለቲካዊ ጥቅም ከፍተኛ ለማድረግ በኢቲቪ አጭር ሰዓታትን ሰጥቶ ከማስተናገድ ይልቅ 24 ሰዓታት የሚተላለፍበትን የራሱን መስመር በመክፈት ዝግጅቱ እንዲተላለፍ ቢደረግ ጥቅማቸው ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ስለተረዱ ባለቤቶቹ እነሱ እንደሆኑ እንዳይታወቅ በከፍተኛ ምሥጢር ተይዞ መቀመጫውንም ከሀገር ውጭ በማድረግ ሥራውን እንዲሠራ ተደረገ፡፡
ይሄው እያየለው እንዳለውም ሕዝብ ትኩረቱን ወደሌላ እንዳያዞርና ባሉበት በተጋፈጣቸውም በችግሮቹ ላይ አተኩሮ መፍትሔ እንዳይሻ እንዳያፈላልግ፣ ችግር እንዳይፈጥር ተቆጣጥሮ ከመያዝ አኳያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከጠበቁት በላይ እጅግ አመርቂ ውጤት ሊያስመዘግብላቸው ችሏል፡፡ ያስገኘው ውጤት የሕዝቡን ትኩረት ቀፍድዶ ይዞ በችግሮቹ ላይ እንዳያተኩርና መፍትሔም እንዳይሻ እንዳያፈላልግ ሌላ ነገር እንዳያስብ ከማድረግም ተሻግሮ ትምህርትንና ሥራንም ጨርሶ ማስረሳቱ ማዘንጋቱ ነው አስገራሚውና ከሀገርና ከሕዝብ ጥቅም አንጻር ሌላው ተጨማሪ እጅግ አደገኛና አሳሳቢ ጉዳቱ፡፡
በቃና የሚተላለፉ የሚከታተሏቸውን ፊልሞችን (ምትርኢቶችን) እንዲያልፏቸው እንዲያመልጧቸው ካለመፈለግ የተነሣ ተማሪዎች እንኳንና ጥናት ሊያጠኑ ቀርቶ ከትምህርት ቤት የተሰጣቸውን የቤት ሥራዎች እንኳን ሳይሠሩ ወደ ትምህርት ቤት ለመሔድ ተገደዋል፣ ክፍል ውስጥ ወሬያቸው ሁሉ በቃና የሚቀርቡ ምትርኢቶች ሆነዋል፣ ከትምህርት ገበታቸው እየቀሩ ወይም አቋርጠው እየወጡም የቃና ፊልሞችን (ምትርኢቶችን) በመመልክት በሕይዎታቸው ላይ የሚቀልዱ ሆነዋል፡፡

ይህ ምን ማለት እንደሆነና ውጤቱ ትውልዱን እንኩቶ ገለባ አድርጎ ሀገርን ሊገለጽ ከሚችለው በላይ ከባድ ኪሳራ ላይ ሊዘፍቃት የሚችል አደጋ እንደሆነ፣ ሕዝባችን አሁን ካለበት የድህነት ወለል በታች ቦታው ጭራሽኑ ወደ መቀመቁ የድህነት ደረጃ ቁልቁል የሚወረውረው መሆኑን መረዳት የማይችል ዜጋ ካለ የተሸከመው የሰው ጭንቅላት ሳይሆን ድንጋይ እንደሆነ የትም ቦታ ሔዶ ማረጋገጥ ሳያስፈልገው እርግጠኛ ሊሆን ይችላል፡፡
በሥራ ቦታዎች ያለው ሁኔታም ተመሳሳይ ነው፡፡ ይሄ እንግዲህ በዚህ ቴሌቪዥን (ምርዓየኩነት) የሚቀርቡ የባዕዳን ምትርኢቶች በሚያደርሱት አሉታዊ ተጽእኖ ሕዝቡን ለባሕል ወረራ ጥቃት አጋልጦት ማንነቱን ሊበርዙበት ከማንነቱ ሊያራርቁት ሊያቆራርጡት ብሎም ማንነቱን ሊያጠፉት የሚችል መሆኑን ትተን ከዚህ በመለስ ያስከተለውንና እያስከተለ ያለውን ጉዳት ብቻ ስንመለከት ነው፡፡
ጣቢያው በዚህ ዘርፍ በተሠማሩ ዜጎች እንጀራ ላይ እንደመምጣቱም ምንም እንኳ በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች ወያኔ ገበያውን በሕገወጥ ቅጅ የሚያጥለቀልቁ ግለሰቦችን አደራጅቶ በማሰማራት ሥነኪንን (በዘልማድ ሥነ ጥበብን) ከማሽመድመዱና ሥነኪን ሀገርንና ሕዝብን ለማገልገል ከተጣለባት ተፈጥሯዊ ኃላፊነት አኳያ ወያኔ እንድትንቀሳቀስ ፈጽሞ ስለማይፈቅድ በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች ሥነ ኪን የሚጠበቅባትን ተግባርና ኃላፊነት እንድትወጣ ባያደርጉም ቃና ቲቪ በእነዚሁ ሁኔታውና አቅማቸው የፈቀደላቸውን ያህል እየተንቀሳቀሱ ባሉት ባለሙያዎች ባለድርሻ አካላትና በስራቸው በሚያስተዳድሯቸው ቤተሰቦች ላይ ሊያስከትል የሚችለው ጉዳትም እንዲሁ አሳሳቢ ነው፡፡ የአገሪቱ የባሕል ፖሊሲ (መመሪያ) ግን ለአገርኛ የጥበብ ሥራዎች መደረግ ስላለበት ድጋፍ ያትታል፡፡ “ጽድቁ ቀርቶ” አሉ! ድጋፉ ቀርቶ ማደናቀፉን ማሰናከሉን ክልከላውን አፈናውን ቢተው ድጋፉ ሳያስፈልግ ሥነኪናችን የት በደረሰ ነበር፡፡

የፊልም (የምትርኢት) እና የቲያትር (የተውኔት) ተመልካቹ አይደለም ከምትርኢትና ተውኔት ቤቶች ከትምህርት በመቅረትና ሥራን በማስተጓጎል ቃና ላይ ተጥዶ እየዋለና እያመሸ ነውና ለቃና ብሎ ትምህርቱንና ሥራውን የበደለ ገንዘብ አውጥቶ ከሚመለከትበት ከፊልም (ከምትርኢት) እና ከቲያትር (ከተውኔት) ቤቶችማ የሚቀር የሚርቅ መሆኑ ምንም የሚያጠራጥር አይሆንም፡፡
“እንዲህ ዓይነት የቴሌቪዥን ጣቢያ ስርጭቶች በተማሪዎችና በሠራተኞች ላይ የተገለጸውን ዓይነት ችግር የሚያስከትል ከሆነ እንዴት ታዲያ ባደጉ ሀገራት ባሉ ማኅበረሰቦች ላይ ተመሳሳይ ችግር ፈጥሮ ሀገሮቻቸውን ሳይጎዳ ቀረ?” የሚል ጥያቄ ይነሣ ይሆናል፡፡ በምእራቡ ሀገራት ተሰዶ የሚኖር ዘመድ ካላቹህ እሱ በሚኖርበት ሀገር እንኳን እንዲህ እኛ እንደምናደርገው ትምህርቱንና የሥራ ሰዓቱን በእጅጉ እየጎዳ በራሱ ላይ በሕይዎቱ ሊቀልድ ይቅርና ኑሮን ለመግፋት እንኳ ያለውን 24 ሰዓት ከስንት በጣጥሶ ስንት ሥራ እየሠራና እየተማረ በቀን ውስጥ ለሁለትና ቢበዛም ለአራት ሰዓታት ብቻ እየተኛ ሕይዎቱን እንዴት አድርጎ እንደሚገፋ ኑሮን እንዴት እንደሚኖር እየጠቃቀሰ ቢነግራቹህ አጥጋቢ ምላሽ ባገኛቹህ ነበር፡፡

እዚያ እንኳንና መሀከለኛና ዝቅተኛ ኗሪው የኅብረተሰብ ክፍል ቀርቶ ሀብታሞቹም እንኳ እረፍት አያውቁም፡፡ እረፍት ካላቸው የአጭር ጊዜ ቆይታ ሆና በእቅድ የምትስተናገድ ናት፡፡ ከትልቅ እስከ ትንሽ ከተማሪ እስከ ሠራተኛ ጊዜ እንደ ቁምጣ ያጠረውና ሕይዎቱ የሩጫ ነው፡፡ ሁሉም ዜጋ የጊዜ አጠቃቀምን (Time management) ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ምእራባዊያኑ ሕዝባቸው በእንደዚህ ዓይነት አዘናጊ ነገሮች ሕዝባቸው እንዳይዘነጋ ማድረግ የሚችል የሕይዎት ሥርዓት (System) አላቸው፡፡ በዚህ ሥርዓት የማይመራና የማይሯሯጥ ሰው ቢኖር ሥርዓቱ ራሱ ይተፋዋል፡፡ የፈጠሩት ሥርዓት አንድ ዜጋ በራሱ ስንፍናና መጃጃል ምክንያት ተተፍቶ ሲወድቅ የሱ መውደቅ ጉዳቱ የራሱ እንጅ የሀገርም እንዳይሆን ወይም ለሀገር የሚደርሳት ጉዳት በጣም አነስተኛ እንዲሆን ማድረግ እስከሚችል ድረስ ነው ሥርዓቱን የገነቡት፡፡ በዚህም ምክንያት እንደዚህ ዓይነት የ24 ሰዓታት ዝግጅቶች በእኛ ላይ ማኅበራዊ ቀውስና ምጣኔ ሀብታዊ (ኢኮኖሚያዊ) አደጋ ማድረስ የሚችሉበትን ያህል ከባድ ጉልበትና አቅም በእነሱ ላይ ጨርሶ የላቸውም፡፡ የደረሱበት ሥልጣኔ ለዚህ በእጅጉ ረድቷቸዋል፡፡
ወደ እኛ ስንመጣ ግን ያለው ነገር ሁሉ ከእነሱ በእጅጉ የተለየ ነው፡፡ ሕይዎትን እንመራታለን እንጅ እንደነሱ ሕይዎት አትመራንም፡፡ ስለሆነም እነሱ ላይ አደጋ አልፈጠረምና እኛ ላይም አይፈጥርም ማለት አንችልም፡፡ ሥርዓቱ አልተገነባማ! የለማ! አልሠለጠንማ! ጊዜን በአግባቡ አንጠቀምማ! በዚህም ምክንያት ነው በርካታ በራሳችን በሕይዎታችን የመቀለጃ ጊዜያት ያሉን፡፡ ሥራችንን ሠርተን ትምህርታችንን ተምረን ትርፍና የእረፍት ጊዜ በምንለው ረጅም ጊዜያችን እንኳን ባላገጥን ምንም ባልነበር፡፡ እኛ እኮ በትምህርትና በሥራ ጊዜ በመቀለድ ዋናውንም ውድ የሕይዎት ጊዜ ነው እየበላን እየቀለድን እየተጫወትንበት ያለነው፡፡
የወያኔ ባለሥልጣናት እንዲህ ዓይነት አደጋና መቅሰፍት በሀገር ላይ እያወረደና ሊያወርድ ያለው ይህ ጣቢያ “የእኛ አይደለም!” ብለው ሸምጥጠው በመካድ ለትርፍ የሚሠራ የባዕዳን የግል ድርጅት ነው የሚሉ ከሆነና ይህ ሁሉ መዓት በዚህች ሀገርና በሕዝቧ ላይ እንዳይደርስ የሚፈልጉ ከሆነ ይሄንን ጣቢያ በቀላሉ መዝጋት የሚችሉበት መንገድ አለ፡፡ ጣቢያው መቀመጫው ከሀገር ውጭ ይሁን እንጅ ኢትዮጵያ ውስጥ ፈቃድ ተሰጥቶት አጋርና ወኪል ድርጅቶች መሥሪያ ቤት ከፍተው ፊልሞቹን (ምትርኢቶችን) ተርጎሞ ከማዘጋጀት አንሥቶ የንግድ ማስታወቂያዎችን እየተቀበሉ በማስተናገድ ላይ ያሉ ድርጅት እንደመሆናቸው ቃና ቴሌቪዥንን ማዘጋት ቢፈለግ ለሕዝብና ሀገር ህልውናና ደህንነት አደጋ የጋረጠ በመሆኑ በሕገ ወጥነት ፈርጆ እዚህ ያለውን ወኪልና አጋር ድርጅቶች የሥራ ፈቃድ ሰርዞ ቢዘጋው እንበልና ድርጅቱ ሌላ ዓላማ ሳይኖረው ለትርፍ የሚሠራ የግል ድርጅት ከሆነ ትርፍ የሚያገኝባቸውን የንግድ ማስታወቂያዎች ማግኘት አይችልምና ወዲያውኑ ራሱን ለመዝጋት እንዲገደድና እንዲዘጋ ማድረግ ይቻላል፡፡
ለትርፍ የተቋቋመ የግል ድርጅት ነው እየተባለ በሀገር ውስጥ እንዲዘጋ ተደርጎ ማስታዎቂያዎችን ሳያገኝ ያለትርፍ በኪሳራ ከሆነ አካል እየተደጎመ ስርጭቱን የሚቀጥል ሆኖ ከተገኘ ያኔ ዓላማው በግልጽ የሚታወቅ ይሆናል፡፡ ውጊያውም ግልጥ በግልጥ ይሆንልናል፡፡ ስርጭቱንም ለማስቆም የሚወሰደው እርምጃ ሌላ ይሆናል፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን ይሄ ሁሉ በሚያሳዝን ሁኔታ ከንቱና የማይሆን ምኞት ነው፡፡ ያሉ ነገሮች ግልጽና የታወቁ እንደመሆናቸው የተጀመረው የጥፋት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል እንጅ የተለየ እርምጃ ሊወሰድ የሚችልበት ዕድል እንደማይኖር ሳረዳቹህ በታላቅ ሐዘን ነው፡፡
የሚመለከታቸው የአገዛዙ ሹማምንት ጉዳዩን “ሕዝብ ይወስንበት! አይጠቅመኝም ካለ እራሱ ወይም ገበያው ይጣለው!” በማለት በሕዝብ ላይ ሲቀልዱ ተደምጠዋል፡፡ ነው እንዴ! ጨዋታው እንዲያ ከሆነ ታዲያ ምነዋ ኢሳትን እንዲያ እየወደድነው እየናፈቅነው ቤታችን ድርሽ እንዳይል አድርጋቹህ ካለበት የምታስቀሩብን ለምንድን ነው? “ለማያውቅሽ ታጠኝ” አለ ያገሬ ሰው፡፡
ይሄንን እያሉ ያሉ የወያኔ ሹማምንት በእርግጠኝነት የተሰጣቸውን ኃላፊነት ፈጽሞ የማያውቁ ናቸው፡፡ ይህ ጉዳይ “ሕዝብ ወይም ገበያው ይጣለው!” በመባል የሚታይ ከሆነ ለእነኝህ ደናቁርት ባለሥልጣናት ልጠይቀው የምፈልገው ጥያቄ ቢኖር፡- አደንዛዥ ዕፆች ምንም እንኳን ጎጂ መሆናቸው ቢታወቅም ተጠቃሚዎቹ ግን ይጠቅመናል እስካሉ ጊዜ ድረስ ለምንድነው ታዲያ እንዲጠቀሙና እንዲያዘዋውሩም ሕግ የማይፈቅድላቸው? እንዲህ እንዲህ እያልን በሕግ የተከለከሉ በርካታ ነገሮችን በመጥቀስ ጎጅነት እንዳለው እየታወቀ ይጠቅመናል ይሆነናል የሚሉ ወገኖች እስካሉ ጊዜ ድረስ ብቻ ፈቃድ እንደማያገኙ እንደሚከለከሉ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

አንዳች ተንኮል ከሌለው በስተቀር “ሕዝቡ ይወስን! ገበያው ይጣለው!” ልንባል አይገባም፡፡ ማኅበረሰባችን የመዝናኛ ዝግጅቶች ባላቸው ከፍተኛ የመማረክ ጉልበትና ኃይል ስለተሸነፈ እንጅ በብዙ መልኩ እንደሚጎዳው እንደሚያዘናጋው ሳያውቅ ሳይረዳ ቀርቶ አይደለም በዚህ መልኩ እራሱን እያጃጃለና እየጎዳ ያለው፡፡ ይህ የወያኔ ባለሥልጣናት አባባል ሕዝባችን ከመጃጃሉ የተነሳ “ይቅርብኝ! ይዘጋ!” ብሎ እንደማይወስን በማወቃቸው የሚሰነዝሩት ንቀት የተሞላበት አነጋገር ነው፡፡
ወያኔ አንዴ በማያገባን በማናውቃቸው ኪሳራ እንጅ በሕይዎታችን አንዳችም የሚጨምርልን ትርፍ በሌለው የአውሮፓ ሀገራት እግር ኳስ፣ ሌላ ጊዜ በጫትና በሺሻ ሱስ፣ ሌላ ጊዜ በድራማ (ትውንተ ኩነት) እና በፊልም (ምትርኢት) ወዘተረፈ. አንተን በጊዜህ በሕይዎትህ ቀልደህ አረንቋ ውስጥ እንድትሰምጥ ለማድረግ የፈለገውን ያህል ሴራ ቢሸርብ እኛ ነቅተን አንሰማም! አንመለከትም! አንዘናጋም! አንጃጃልም! ብንል ሴራው ምን ይፈይድለት እሱስ የት ይደርስ ነበር? የትም!
ወያኔ ለምንና እንዴት ትውልድን መቀመቅ ውስጥ ለማስጠም ሆን ብሎ ይሄንን እንደሚያደርግ ከዓመታት በፊት “ሱስ ትውልድና ሀገር” በሚል ርእስ የጻፍኩትን ጽሑፍ ጎግል አድርገህ በመመልከት ማረጋገጥ ትችላለህ፡፡
እርግጥ ነው ሆንብሎ ለማጥፋት ትውልድን መቀመቅ ለማስመጥ ተግቶ የሚሠራ በመንግሥት ቦታ ያለ የጥፋ ኃይል ባለበት ሁኔታ ምን ብታደርግ ከወጥመዱ አመልጣለሁ ማለት ዘበት ሊሆን ይችላል፡፡ እንግዲህ ታዲያ ምን ይዋጥህ ወገን? ወያኔ እንደ አህያነቱ በ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” አስተሳሰቡ ለግል ጥቅሙ ሲል ሀገርንና ሕዝብን የሚጎዱ ተግባራትን በመሸረብ መጠመዱ ግራ የሚያጋባው፣ የሚደንቀው፣ የሚገርመው ዜጋ ይኖር ይሆን? ወያኔ ነኝ ብሎ ማንነቱን በራሱ አንደበት በግልጽ እየተናገረ የጠላትነት ስሜት ተሞልቶ፣ ጥፋት ተጭኖ ከመጣ ጠባብና ደንቆሮ የወሮበላ ቡድን ታዲያ ከዚህ የተለየ ምን ይጠበቅና ነው ግራ የሚገባው? የሚገርመው? የሚደንቀው? እያንዳንድሽ አርፈሽ ጸጥ ብለሽ መቀመቅሽን ውረጅ! በፊትስ እሽ ሳታውቂው ቀርተሽ ይባል በኋላ ላይ ግን የወያኔን ማንነት ከተግባሮቹ ካወቅሽ በኋላ እያንዳንድሽ ላለመበላት፣ ላለመታረድ፣ ላለመነቀል፣ መቀመቅ ላመውረድ ምን ያደረግሽው ነገር አለ? ምንም! ስለዚህ አርፈሽ ዝም ብለሽ ተጋድመሽ ታረጅ!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com


No comments:

Post a Comment