Wednesday, May 18, 2016

በቦሌ ቡልቡላ ቤታችን አይፈርስም ያሉ ወገኖች የፌደራል ፖሊሶች ጥይት ራት ሆኑ

(ዘ-ሐበሻ) በአዲስ አበባ ከተማ ወረዳ 12 በተለምዶው ቦሌ ቡልቡላ በተሰኘው አካባቢ በሕገወጥ መንገድ ተሰርተዋል በሚል የፌደራል ፖሊሶች እና የአካባቢው አፍራሽ ግብረሃይል ዛሬ ጠዋት ቤቶችን ለማፍረስ ሲንቀሳቀሱ ከአካባቢው ሕዝብ ጋር በተነሳ ግጭት በርካቶች መቁሰላቸውና ህጻናት ሳይቀሩ መሞታቸው ተዘገበ::


ቦሌ ቡልቡላ (ፎቶ ከፋይል)

ከስፍራው የሚመጡ መረጃዎች እንደሚያመለከቱት “ከቤታችን ወዴት እንሂድ?” ያሉ የአካባቢው ነዋሪዎች በፌደራል ፖሊሶች እና በአፍራሽ ግብረሃይሉ ቤታቸው ሊፈርስባቸው ሲዘጋጁ ግጭቱ ጀምሯል:: ከዚያም የፌደራል ፖሊሶች ወደሕዝቡ የተኮሱ ሲሆን እስካሆን በግምት 9 ወይም 10 የሚሆኑ ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉና ሌሎችም በርካቶች መቁሰላቸው ተሰምቷል:: ቤቶችም መፍረሳቸውን ቀጥለዋል::
ምንጮች እንደሚሉት በኦሮሚያ ሕዝባዊው አመጽ ከተነሳ በኋላ ፌደራል ፖሊሶች ለህዝብ ተቃውሞ ምንም ዓይነት ሰላማዊ ምላሽ መስጠት አቁመዋል:: በቀጥታ ወደ ሕዝብ መተኮስ የጀመሩ ሲሆን ዛሬም ቤታችንን አታፍርስ; እኛን አፈናቅላችሁ መሬቱን አትሽጡ ባሉ ወገኖች ላይ ምላሹ ጥይት መሆኑ ብዙዎችን አሳዝኗል::
ይህ በ እንዲህ እንዳለ ሕዝቡ በፌደራል ፖሊሶቹ ላይም ጥቃት ማድረሱን መረጃዎች የሚጠቁሙ ሲሆን ዘ-ሐበሻ ምን ዓይነት ጉዳት በፖሊሶቹና አፍራሽ ግብረሃይሉ ላይ እንደደረሰ ለማጣራት ያደረገችው ጥረት አልተሳካም::
በአካባቢው ያለው ውጥረት ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ እንዳየለ ነው:: ጉዳዩን ተከታትለን ለመዘገብ እንሞክራለን::

No comments:

Post a Comment