Saturday, May 21, 2016

መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ያላት የሰው ድሀ ሀገር ኢትዮጵያ – ይገረም ዓለሙ

በ1982 ዓም  ኢትዮጵያ ወዴት እየሄደች እንደሆነ አይደለም የት ላይ አንዳለች አንኳን መናገር የማይቻልበት ወቅት .ከአንድ ባልንጀራየ ጋር እየሄድን እኔ ከማላውቀው የእርሱ ጓደኛ ጋር መንገድ አገናኘን፡፡ እናም ሰላምታ ተለዋውጠው  ታዲያስ አንዲት ነህ እንዴት ናችሁ ሲለው  ምን እባክህ ሰውም አለን ሰውም የለንም  ሲል መለሰለት፡፡
ሁለቱ ተለያይተው እኛ መንገድ እንደጀመርን ምንድን ነው ያለው ስል ባልንጀራየን ጠየኩት፡፡ እባክህ እሱ አመሉ ነው፡ ከርሱ ጋር ስናወራ ጓደኞቹ ሁሉ አንደተቸገርን ነው፤ በቀጥታ መናገር አይሆንለትም አለኝ፡፡ ምንድን ነው ስራው ስል ጥያቄ አከልኩ ስራው ወታደራዊ ካድሬ ፣ትውልዱ ጎንደሬ፣ፖለቲካውን በጎንደር አማርኛ እየመሰጠረ ነው የሚያስቸግረን  በማለት ባላንጀራየም እንደመራቀቅ እያደረገው መለሰልኝ፡፡ ሰው አለን ሰው የለንም  የሚለውን አባባል ምንነት ለመረዳት ከባልንጀራየ ጋር ብዙ አውርተንበታል፤ብቻየንም ብዙ ግዜ አውጥቼ አውርጄዋ
Ethiopian-Flag.jpg
ይህ በሆነ  አስር ዓመት ግድም ፕ/ር መስፍን ወልደማሪያም በጦቢያ መጽሄት ላይ ኢትዮጵያ የሰው ድሀ ካልሆነች ታዲያ የምን ድሀ ልትሆን ነው የሚል ጽሁፍ  አስነበቡን፡፡ ይህም ከሆነ አስር ዓመት ግድም (አጋጣሚው ሊገርም ይችላል)   ፕ/ር መስፍንን አግኝቻቸው  ከላይ የጠቀስኩትን ጽሁፋቸውን አስታውሼ ከ90 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ያላት፣ በተለያዩ የዓለም ሀገራት በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ተሰማርተው የሚሰሩ አንቱ የተባሉ ልጆች ያሏት በማለት ብዙ ነገር ዘረዘርኩና እንዴት የሰው ድሀ ትባላለች ስል ጠየኳቸው ፡፡ በጥሞና አዳምጠው በርጋታ የሰጡኝ ማብራሪያ ረዥምና አጥጋቢ ነበር፡፡ ከግዜው ርዝመት አንጻር ማስታወስ ቢገደኝም አንኳር ነጥቡ እነዚህ የምትላቸው ሰዎች ለራሳቸው ኖረው ሊሆን ይችላል፤ ላስተማራቸው ሀገርና ሕዝብ ምን ሰርተዋል? ከአገዛዝ አላቀውታል? ከድህነት አውጥተውታል? ሰው በሚፈለግበት ግዜና ቦታ ካልተገኘ መኖሩ ብቻ ለሀገር ምን ይጠቅማል የሚል ነበር፡፡
የርሳቸውን ማብራሪያ እያዳመጥኩ አስር ዓመት ያህል ወደ ኋላ ተመልሼ ሰው አለን ሰው የለንም ያለውን የወዳጄን ወዳጅ አስታወስኩት፡፡ የአባባሉ ምንነትና እንደዛ ለማለት ያበቃውም ምክንያት በፕ/ር ንግግር ውስጥ ግልጽ ብሎ ታየኝ፡፡ በቁጥር ብዙ ሰው አለ፤ በቁም ነገር መድረክ በተግባሩ መስክ ግን  ..ማለቱ ነበር የሰው ድሀ ማለት ይህ አይደል ታዲያ፡፡
ብቸኛው ፓርቲ ኢሰፓ ከሲቭልም ሆነ ወታደራዊ ማዕረጋቸው የሚቀድመውን ጓድ መጠሪያቸው ያደረጉ ብዙ እጅግ ብዙ አባላት ነበሩት፡፡ነገር ግን አባሉ በቁጥር በዝቶ  ቁም ነገር ያለው ግን አንሶ  አይደለም ሀገሪቱን ሲያንቆለጳጵሱዋቸው የነበሩትን መሪ ከስደት፤ ፓርቲውን ከሞት፤ ራሳቸውን ከውርደት መታደግ ሳይችሉ ቀሩ፡፡
ኢሰፓ ያልነበሩ እንደውም ኢሰፓን ተቃውመው መንግስቱን አውግዘው ሲታገሉ የነበሩ ባይታገሉም ሥርዓቱን ይቃወሙ ዴሞክራሲን ይመኙ የነበሩ በቁጥር ብዙ  ነበሩ፡፡ ግና ቁም ነገራቸው ሚዛን የሚደፋ የተግባር ሰውነታቸው እስከመስዋዕትነት የደረሰ ጥቂቶች ሆኑና ኢትዮፕያ ሰው እያላት የሰው ድሀ ሆነችና  ከወታደራዊ አገዛዝ ወደ ተጋዳላዮች አገዛዝ ለመሸጋገር በቃች፡፡
ዘመነ ወያኔንም ስናይ ከመነሻው ጀምሮ ወያኔን የሚቃወመው፣ ስለ ለውጥ  የሚደሰኩረው፣  ስለ ዴሞክራሲ  የሚሰብከው፣ ወዘተ ቁጥሩ የትየለሌ ነው፡፡ ግና ከቁም ነገሩ መድረክ ከተግባሩ ስፍራ የሚገኙት ጥቂት በጣም ጥቂት ሆኑና ወያኔ ማን አለኝ ከልካይ እያለ የሻውን እየፈጸመ ሀያ አራት ዓመታት ለመግዛት ቻለ፡፡ ሌላው ቀርቶ በቅርቡ ኢሳትና ቪዥን ኢትዮጵያ በጋራ ባዘጋጁት የውይይት መድረክ ላይ የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡትን  በተለያየ የሙያና የእውቀት ዘርፍ ከጫፍ የደረሱ ምሁራንን የተመለከተ  የእነርሱ መሰሎች ሀገር ኢትዮጵያ እንዲህ በአገዛዝ ስትማቅቅ፤፣ከዴሞክራሲ ጋር ሆድና ጀርባ ሆና ስትኖር፣ ሕዝቡ በየግዜው በረሀብ አለንጋ ሲገረፍ ሰው እያላት ሰው ያጣች ሀገር አያሰኝም ትላላችሁ!
የኢትዮጵያ የሰው ድሀነት በወያኔም ውስጥ በገሀድ ይታያል፡፡ በተለያየ መንገድ የድርጅቱ አባልም ደጋፊም የሆኑ አባልና ደጋፊም ባይሆኑ ደግሞ የማይቃወሙ በተለያየ የእውቀትና የሙያ መስክ ላይ የሚገኙ በውጪም በውስጥ ብዙ ዜጎች አሉ፡፡ነገር ግን እነርሱም ቁጥራቸው እንጂ ቁም ነገራቸው የሚታይ ባለመሆኑ ድርጅታቸው በሀገርና  በሕዝብ ላይ የሚያደርሰውን ጥፋት ማሰቆም ቀርቶ አንድ መለስ ያለእኔ ማን አለ ብለው ፓርቲም መንግሥትም ግለሰብም ሆነው ናውዘው ለሞት ሲበቁ ሊታደጉዋቸው አልቻሉም፡፡
ይህም ብቻ አይደለም ከአስር ዓመት በፊት ከአምስት ሚሊዮን በላይ አባላት አሉኝ ያለ ድርጅት በቁጥር እንጂ በቁም ነገር (ከሱ ፍላጎት አንጻር) ሚዛን የሚደፋ ሰው አጥቶ ከቦታ ቦታ የሚያገላብጣቸው የተወሰኑ ሰዎችን ነው፡፡ ሴቶችማ ለቁጥርም የሉ፡፡የአሁኑ አፈ ጉባኤ አባ ዱላ ገመዳ አንዴ ጀነራል አንዴ አቶ እየተባሉ ስንት ቦታ አንደተገለባበጡ ማስታወሱ ብቻ ለዚህ በቂ ይመስለኛል፡፡
የትውልድ ድርሻውንና የዜግነት ግዴታውን ቅንጣት ሳይከውን በሥልጣኔ ስም ሰይጥኖ ወደ ላይ አንጋጦ ትናትን የማውገዝ ድፍረት በተላበሰው ትውልድ የሚነቀፉ የሚዘለፉት አባቶቻችን በቁጥር ጥቂት ሆነው ከነዛው መካከል ግን የቁም ነገር ሰዎች ብዙም ብርቱም የነበሩ በመሆናቸው ነበር በዙሪያችን ያሉ ሀገሮች በቅኝ ግዛት ሲማቅቁ ኢትዮጵያ በነጻነት የዘለቀችው፤ ዳር ድንበሯን አስከብራ የባህር በሯን አስጠብቃ ለመኖር የቻለችው፡፡ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ተምሳሌት ሆና የኖረችው፡፡
ዛሬ ግን አንደ ቁጥራችን ብዛት ከቁም ነገር ያፋቱን፣ ከተግባር ያራቁን ችግሮቻችን በዝተው እኛ የሚናቁት የሚወገዙና የሚኮነኑት አባት እናቶቻችን የቆዩንን ሀገር፣  ዳር ድንበር፣ የባህር በር፣ወዘተ ማስከበርና መጠበቅ ሳንችል ቀረን፡፡  ከወያኔ አገዛዝ ተላቀን የምናወራለትን ዴሞክራሲ እውን ለማድረግ  መስኩ ላይ መገኘት አቃተን፡፡ በእውቀት የበለጸጉ በሙያ የተካኑ በልምድ የዳበሩ አያሌ ልጆቿ  በመላው ዓለም በተለይም በምእራቡ የዓለም ክፍል ተሰማርተው እውቀት ጉልበታቸውን ለሌላ ሀገር እየሸጡ የተደላደለ ኑሮ መኖር ቢቻላቸውም  እውቀታቸውም ሆነ ሙያቸው፣ ልምዳቸውም ሆነ ጉልበታቸው፣ ለሀገራቸው የሚፈይድ አልሆነም፡፡ አንዲህም ሆነና እናት ሀገር ኢትዮጵያ መቶ ሚሊዮን የሚሆን ሰው እያላት  የሰው ድሀ ሆና  አገዛዝ እንደተፈራረቀባት፣ ዴሞክራሲ አንደናፈቃት፣ ረሀብ ልጇን እንዳሰቃየባት ትኖራለች፡፡ ዛሬ እየሆነ ካለው በላይ  የነገው ተስፋ የለሽነት  ይብስ ይከፋል፡፡
መቼ ይሆን! ኢትዮጵያ ልጆቿ  ቁጥራችን ብቻ ሳይሆን ቁም ነገራችንም በዝቶ ሰው እያላት የሌላት የሰው ድሀ ከመሆን የምትወጣው? መቼ ይሆን! በዘር፣ በሀይማኖት፣ በአመለካከት ልዩነት ተለያይተው የመቶ ሚሊዮኖች እናት ግን የሰው ድሀ ያደረጉዋት ልጇቿ ከምንም ነገር በፊት እናታችን ብለው እውቀታቸውን አቀናጅተው ሀይላቸውን አስተባብረው  ነጻነት የሚያቀዳጇት? መቼ ይሆን! ልጆቿ ከራስ በላይ ነፋስ አስተሳሰብ ተላቀው፣ ከመጠላለፍ አዙሪት ወጥተው፣ ከቁልቁለት ጉዞ የሚያቃኑዋትና  የነበረ ዝናና ክብሯን መልሰው የሚያቀዳጁዋት? አረ መቼ ይሆን! ልጆቿ  ዴሞክራሲ እየተረገዘ የሚጨነገፍበትን ሲወለድም   በአጭር የሚቀርበትን በሽታ ተርደተው መድሀኒትም አግኝተውለት ኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊት ሀገር ለማድረግ የሚበቁት ? አረ መቼ ይሆን! ልጆቿ የመቶ ሚሊዮን ሕዝብ ሀገር የሰው ድሀ የሆነችው እነርሱ ተለያይተው በመቆማቸው፤ በስልጣን ጥም በመታወራቸው፤ ከእኔ በላይ በሚል አስተሳሰብ በመታጠራቸው፣ለራስ እንጂ ለመጪው ትውልድ የማይጨነቁ በመሆናቸው ወዘተ መሆኑን ተረድተው ከየራሳቸው ታርቀው፣ ርስ በርሳቸው ፍቅር መስርተው፣ አንደ ብዛታቸው ቁም ነገራቸውም ለሀገርና ለወገን ሲበጅ የሚታየው መ? መቼ አረ መቼ !
ተዋቂው የብእር ሰው ሎሬት ጸጋየ ገብረ መድህን  ይድረስ ከእኛ ለእኛ በሚለው ተከታታይ ግጥም ውስጥ እንዲህ ብሎ ነበር፡፡
ይድረስ ወገን ከእኛ ለኛ “እሳት አንሆን ወይ አበባ”
የነገን ራዕይ አንዳናይ ፣በሐቅ እንቅ ስንባባ
መክሊታችንም ባከነች፣ዕድሜአችንን ስናነባ፡፡
ፍቅር ፈርተን፣ሰላም ፈርተን
አንድታችንን ጠልተን ፣ተስፋችንን አጨልመን
የነፍስን አንደበት ዘጋን፣
የልጆቻንን ተስፋ ፣እምቡጥ ሕልማቸውን በላን፡፡
ሳይነጋ እየጨለመ ነው፣ተው ወንድሜ እንተማመን፣
ዓለም ባበደበት ዘመን፣የብረት ምሽግ ነው ወገን፡፡
ኢትዮጵያ ዘለዓለሚቷ፣አንድነት ነው መድኃኒቷ
ሕብረት ነው መፍትሔው ስልቷ፡፡

No comments:

Post a Comment