Tuesday, November 11, 2014

ለአስራ አራት ቀን አራስ ጥይት? – (እውነተኛ የወንጀል ታሪክ)

crime
አቶ አስጨናቂ ደስታ፤ ተሬ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ በእርሻ የሚተዳደሩ አርሶ አደር ናቸው፡፡ ትዳር መስርተው መኖር ከጀመሩ ደግሞ አስራ ሶስት ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ ባለቤታቸው ወ/ሮ ኮከብ ወርቁ ከአቶ አስጨናቂ አራት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በሰሜን ሸዋ ዞን በቀወት ወረዳ ለረጅም ዓመታት በትዳር አብረው የኖሩት ሁለቱ ጥንዶች ትዳራቸው እንዲሁም ቤተሰባቸውን እንከን ገጥሞታል፡፡ አቶ አስጨናቂ ደስታ ታታሪ ገበሬ በመሆናቸው ነው በአካባቢው የሚታወቁት፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አቶ አስጨናቂ ደስታ ርቋቸዋል፡፡ እርሳቸው እና ቤተሰባቸው በመጥፎ የስሜት ድባብ ውስጥ ሆነው ጊዜው እየነጎደ ነው፡፡ ይመሻል ይነጋል፡፡ ይህ የሆነበት ደግሞ ምክንያት አለው፡፡ አቶ አስጨናቂ በአጭር ጊዜ ውስጥ አራት በሬዎቻቸውን አጡ፡፡ የሚመኩባቸው የእርሻ በሬዎቻቸው ሳይታሰብ እየታመሙ ሞተው አለቁባቸው፡፡
የሀገራችን ገበሬዎች በበሬዎቻቸው በጣም ነው የሚመኩት፡፡ ዘር ዘርተው… አርመው… ጎልጉለው… አጭደውና ወቅተው ምርት የሚያገኙት የበሬዎቻቸውን ጉልበት በመጠቀም ነው፡፡ በሬ ለሀገራችን ገበሬዎች ከምንም በላይ እንደሆነ በአርሶ አደሮች አንደበት ጭምር ይነገራል… ይዘመራል፡፡
‹በሬ እረስልኝ…
በሬ ዙርልኝ
አጋዥ ባልደረባ
አራሽም የለኝ
በጥቋቁር በሬ…
መሬት ካላረሱ
ገንዘብ የት ይገኛል…
ቦርሳ ቢዳብሱ›
ከአርሶ አደሮች አንደበት የሚደመጡ የማሞካሻ ስነ-ቃሎች ናቸው፡፡ ለበሬ ማሞካሻ… ማሞገሻ… ውለታ መግለጫ የሚሆኑ ስነ-ቃሎች እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡
አቶ አስጨናቂ አራት ልጆቻቸውን አርሰው የሚመግቡባቸው የአራት በሬዎቻቸው ሞት ትልቅ ሀዘን እንዲሰማቸው አድርጓቸዋል፡፡ የበሬዎቻቸው ሞት ራቁታቸውን ስላስቀራቸው የኑሮ ምስቅልቅልን ፈጥሮባቸዋል፡፡
‹መሬት ያለ በሬ
ምርት ያለገበሬ› አይታሰብም የሚለው የሀገራችን ብሂል በአርሶ አደር አስጨናቂ ደርሶባቸው ዘወትር ጭንቀት ሆኖባቸዋል፡፡ በእነዚህ መጥፎ አጋጣሚዎች ውስጥ ቤተሰባቸውን እንዴት እየመሩ ነበር? ከባለቤታቸው ወ/ሮ ኮከብ ጋር ምንምን ነገሮችን ያወሩ እንደነበር ለማወቅም ወ/ሮ ኮከብን ማግኘት አልተቻለም… ለምን? ቢሉ… ምክንያቱ ወዲህ ነው፡፡
የወርሀ ሐምሌ ክረምት ወቅት ነው፡፡ ሐምሌ 4 ቀን 2001 ዓ.ም በግምት ከረፋዱ አምስት ሰዓት ላይ አቶ አስጨናቂን ‹‹ምን አስጨከናቸው?›› ያስባለ ትእይንት በመኖሪያ ቤታቸው ተከሰተ፡፡ ጎረቤትን… ዘመድ አዝማድን… የአካባቢውን ነዋሪ ያስደመመ በእጅጉ ያሳዘነ ትእይንት ነበር የተከሰተው፡፡
ወ/ሮ ኮከብ ወርቁ በትዳር ሕይወታቸው አራተኛ ልጃቸውን ከወለዱ ገና አስራ አራተኛ ቀናቸው ነው፡፡ ወገባቸው ያልጠነከረ አራስ ናቸው፡፡ በአራስ ቤት ውስጥ ሁለተኛ ሳምንታቸውን ገና አልደፈኑም፡፡ በመጫቷ ወ/ሮ ኮከብ ላይ የተፈፀመው ግን ‹‹መታረስ ነው የሚገባቸው ወይንስ ሌላ?›› የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ …ጥያቄው ደግሞ የሁሉም ሰው ነው፡፡ አቶ አስጨናቂ የአራት ልጆቻቸውን እናትና ባለቤታቸውን ‹‹…እንደ ቤታችን ምን ላቅርብልሽ?›› ብለው አልጠየቁም፡፡ በእዚህ ምትክ የሰጧቸው ጥይት ነበር፡፡ የአራት ልጆቻቸው እናት እና አራሷ ወ/ሮ ከባለቤታቸው በተተኮሰባቸው ጥይት ተመተው እስከ ወዲያኛው አሸለቡ፡፡
ለጥፋት የተዘረጋው የአቶ አስጨናቂ የጭካኔ እጅ በእዚሁ አላበቃም፡፡ ጭካኔያቸው ቀጥሏል፡፡ የሰባት ዓመት ሴት ልጃቸውንም እናቷን እንድትከተል አድረጓት፡፡ አባወራው ባለቤታቸውንና የሰባት ዓመት ሴት ልጃቸውን ጨክነው በጥይት መትተው የህይወት እስትንፋሳቸው እንዲቆም አደረጉ፡፡
ተግባራቸውን ያየ… የሰማ ሁሉ ‹‹ምንድን ነው ይህንን ያህል ጭካኔ?›› ብሎ እንዲጠይቅና እንዲወያይ አደረገው፡፡ እውነት በሬዎቻቸው ስለሞቱባቸው ተስፋ ቆርጠው ይሆን? ይህ የእኛ ጥያቄ ነው፡፡ ጎረቤቶች ግን የሚሉት አራት በሬዎችን በአንድ ጊዜ በሞት በማጣታቸው ተስፋ ቆርጠው ነው ብለዋል፡፡ ፖሊስ ጉዳዩን በማጣራት ላይ ነው፡፡ በእንስሳት ሞት የቤተሰብን ህይወት ማጥፋት ለምን አሰፈለገ? የሚለው የፖሊስም ጥያቄ በመሆኑ ምርመራው እንደተጠናቀቀ የሚታወቅ ነው የሚሆነው፡፡
አሁን አቶ አስጨናቂም በህይወት የሉም፡፡ ምክንያቱም በዕለቱ በባለቤታቸውና በሰባት ዓመት ሴት ልጃቸው ላይ ግድያውን ከፈፀሙ በኋላ በራሳቸው ላይ ፈረዱ፡፡ ራሳቸውን አጠፉ፡፡ በአራት በሬዎች ሞት የሦስት ሰዎች ህይወት መጥፋቱ ሁሉንም ያሳዘነ እንደሆነ የአካባቢው ሰዎች ይናገራሉ፡፡
ቤት ባዶ ቀረ፡፡ ሦስት ልጆችም ያለ አሳዳጊ ቀሩ፡፡ እናታቸውን፣ አባታቸውንና እህታቸውን አጡ፡፡ የወረዳው ፖሊስ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አህመድ መሐመድ እንደገለፁት የልጆቹን ህይወት ለመታደግ በአራስ ቤት ያለው ህፃን ወደ ሸዋሮቢት ከተማ አስተዳደር የህፃናት እንክብካቤ ተቋም በመወሰድ ተገቢውን እንክብካቤ እንዲደረግለት ተደርጓል፡፡ ቀሪዎቹ ሁለት ልጆች ደግሞ ያለ አሳዳጊ እንዳይቀሩ አሳዳጊ እንዲያገኙ ፖሊስ በጥረት ላይ ነው፡፡ የፖሊስ ጥረት ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ሁለቱን ህጻናት ለመታደግ ግለሰቦች፣ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ መንግስትና ሌሎችም እጃቸውን ማስገባት ቢችሉ በጎ ተግባር ነውና ሁላችሁም የበኩላችሁን አበርክቱ የሚለው የዝግጅት ክፍላችን መልእክት ነው

No comments:

Post a Comment