Saturday, November 29, 2014

የነዳጅ ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቢቀንስም የኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን የችርቻሮ ዋጋን አልቀነሰም

ለአመት ያህል በበርሜር ወደ 110 ዶላር ንሮ የቆየው የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ፤ ካለፈው ሐምሌ ወዲህ እየወረደ በያዝነው ሳምንት ከ75 ዶላር በታች የደረሰ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋ ላይ መንግስት እስካሁን ቅናሽ አላደረገም።
በአመት በአማካይ ከሰባት በመቶ በላይ እየጨመረ የመጣው የኢትዮጵያ የነዳጅ ፍጆታ፣ ባለፈው አመት 3.4 ቢሊዮን ዶላር (ከ65 ቢሊዮን ብር በላይ) ወጪ እንዳስከተለ ታውቋል። ሸቀጦች ወደ ተለያዩ አገራት በመላክ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ ባለፉት አራት አመታት እድገት ባለማሳየቱ አመታዊው ገቢ ከሶስት ቢሊዮን ዶላር ገደማ ብዙም ፈቅ ባለማለቱ፣ የነዳጅ ግዢን እንኳ ለመሸፈን የማይበቃ ሆኗል።
news
በአለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ ባለፈው አመት በነበረበት ቢቀጥል ኖሮ፣ በቀጣዩ አመት ኢትዮጵያ ሩብ ቢሊዮን ዶላር (5 ቢሊዮን ብር) ተጨማሪ ገንዘብ ለነዳጅ ግዢ ለማውጣት መገደዷ አይቀርም ነበር። ይሁን እንጂ፣ ያለማቋረጥ እየወረደ የመጣው የነዳጅ አለማቀፍ ዋጋ በስድስት ወራት ውስጥ ሲሶ ያህል ስለቀነሰ፣ ኢትዮጵያ ለነዳጅ ግዢ የምታውለው የውጭ ምንዛሬ ዘንድሮ እንደማያሻቅብ ተገምቷል።
እንዲያውም የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በበርሜል ከ80 ዶላር በታች ሆኖ ከቀጠለ፣ የአንድ ቢሊዮን ዶላር (የ20 ቢሊዮን ብር ወጪ ቅናሽ ያስገኛል፡፡) በርካታ ነዳጅ አምራች አገራትን የሚቆጣጠሩ መንግስታት በአባልነት የተካተቱበት ኦፔክ የተሰኘው ማህበር፣ ሰሞኑን በነዳጅ ዋጋ ዙሪያ የተወያየ ቢሆንም፣ ውይይታቸው በአለም የነዳጅ ዋጋ ላይ ለውጥ እንደማያስከትል ትናንት ቢቢሲ ዘግቧል። እየወረደ የመጣው የነዳጅ ዋጋ፣ የበርካታዎቹን መንግስታት ገቢ እንደሸረሸረ የገለፀው ቢቢሲ፣ ከፍተኛ የበጀት ጉድለት ያጋጥማቸዋል ብሏል። “ዋጋ እንዲያንሰራራ የነዳጅ ምርት መቀነስ አለብን” የሚል ጥያቄ ከሁለት መንግስታት በኩል እንደቀረበ ዘገባው ጠቅሶ፣ ጥያቄው በአብዛኞቹ መንግስታት ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱን አመልክቷል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የነዳጅ ዋጋ መውረድ የጀመረው፣ በከፊል ከአለም ኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ጋር በተያያዘ ምክንያት ቢሆንም፣ ዋናው ምክንያት ግን የአሜሪካ ኩባንያዎች ከፍተኛ የነዳጅ ምርትን የሚያስገኝ አዲስ ዘዴ በመፍጠራቸውና ተጨማሪ ነዳጅ ማምረት በመጀመራቸው እንደሆነ ፎርብስ መፅሔት ዘግቧል።
ከአለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ ውጣ ውረድ ጋር፣ የኢትዮጵያ መንግስት በንግድ ሚኒስቴር በኩል በየወሩ የነዳጅ ዋጋ ተመን የሚያወጣ ሲሆን፣ ከጥቂት ጊዜያት በስተቀር አብዛኛውን ጊዜ የዋጋ ተመኑ በነበረበት እንዲቀጥል አልያም የአለም ገበያን ተከትሎ እንዲጨምር ሲወስን መቆየቱ ይታወሳል።
ባለፉት ስድስት ወራትም እንዲሁ፣ በአለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ በፍጥነት እየወረደ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ግን የችርቻሮ ዋጋ በነበረበት ደረጃ እንዲቀጥል አልያም እንዲጨምር የተደረገ ሲሆን፣ በያዝነው ወር መጨረሻ የዋጋ ተመኑ ላይ ምን አይነት ለውጥ እንደሚደረግበት ገና አልታወቀም። በተለመደው የመንግስት አሰራር፣ የዋጋ ተመን ውሳኔው በይፋ እስከሚገለፅበት እለትና ሰዓት ድረስ በሚስጥር ተጠብቆ ነው የሚቆየው።

ምንጭ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ዛሬ በአዲስ አበባ ታትሞ የወጣ

No comments:

Post a Comment