Tuesday, June 16, 2015

ምርጫ ማላገጫ (ሰኔ 2007 ዘሀበሻ) – ይገረም አለሙ

      በቅድሚያ የወያኔን ሕገ ወጥና ሞራለ ቢስ እንዲሁም ወራዳና እኩይ ተግባር ሁሉ ተቋቁመው እዚህ በሀገር ቤት ሰላም በሌለበት ሰላማዊ ብለው የህግ የበላይነት በሌለበት ራሳቸውን ህጋዊ አድርገው ለሚታገሉት ፖለቲከኞች አክብሮትም አድናቆትም ያለኝ መሆኑን እገልጻለሁ፡፡ይህ ስሜት ግን ድክመታቸውን ለማየት ስህተታቸውን ለመተቸት የሚጋርድና የሚከለክል መሆን የለበትም፡፡ የሚወዱትና የሚደግፉት ይበልጥ እንዲጎለብት በግልጽና በድፍረት መተቸት፣ ድክመት ስህተትን ማሳየት ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም፡፡ የሚያሳዝነው ለዚህም አልታደልን፡ ከሚጥመን ውጪ ሌላ ለመቀበል ቀርቶ ለመስማት ፍላጎቱ ብዙም የለንም፡፡ ምርጫ አንድም ሕዝብ በድምጹ ያሻውን መርጦ የሥልጣን ባለቤትነቱን የሚያረጋግጥበት፣ አንድም አምባገነኖች ለሕገ ወጥ ሥልጣናቸው ሕጋዊ ካባ የሚያላብሱበት ክንውን ነው፡፡ ምርጫ አስፈጻሚ ተቋም ተቋቁሞ ተወዳዳሪዎች ተሰይመው መራጭ ተመዝግቦ ካርድ ኮሮጆ ውስጥ መክተቱ ብቻ አይደለም የምርጫን እንዴትነት የሚወስነውና ምንነቱን የሚያሳየው፡፡ ከመነሻው የሥልጣን ባለቤቱ ሕዝብ መሆኑን አምኖ፣ የሥልጣን መያዣው አንድና ትክክለኛ መንገድ ምርጫ መሆኑን ተቀብሎ፣ በሕዝብ ውሳኔ ለመገዛት ራስን አዘጋጅቶ፣ የሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር ነጻ ተአማኒና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል እንዲሆን ከማድረግ ነው የሕዝብን የሥልጣን ባለቤትነት የሚያረጋግጥ ትክክለኛ ምርጫ የሚጀምርው፡፡ ወያኔ ከደደቢት ተነስቶ ለአስራ ሰባት ዓመታት ገድሎና ሞቶ ለምኒልክ ቤተ መንግሥት ከበቃ እነሆ ዘንድሮ አምስተኛውን ምርጫ አካሂዷል፡፡ በ1997 ዓም ከተካሄደው ሶስተኛ ምርጫ በስተቀር ሌሎቹ ለውጥ ሊታይባቸው ቀርቶ በሰው አዕምሮ ውስጥ ጥለውት ያለፉት ትውስታ የለም፡፡ አለ ከተባለ የ2002ቱ 99.6 በመቶ ወያኔ አሸናፊ መሆኑ በአንጻሩ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ 20 ዓመት ወደ ኋላ መመለሱ ነው፡፡ እንደ ወያኔ በሁለንተናዊ ተግባሩ የህዝብ ድጋፍ የተለየው ፓርቲ ቀርቶ ከፊል የህዝብ ድጋፍ ያለው ፓርቲ እንኳን ቢሆን በተከታታይ አምስት ምርጫ ሊያሸንፍ አይችልም፡፡ የሰው ልጅ ለውጥ መፈለጉ የተፈጥሮ ህግ ነውና የጎደለው እንዲሟላለት፣ ቅር የተሰኘበት እንዲስተካከልለት አለያም በስልጣን ላይ የቆየው ፓርቲ ተምሮ ለወደፊት የተሻለ ሆኖ እንዲቀርብ ወዘተ ሌላ ይመርጣል፡፡ እናም በዴሞክራሲያዊ ሀገራት ሕዝቡ በሚያዝበት የሥልጣን ወንበር ላይ አንዱን ከአንዱ እያፈራረቀ ያያል ይፈትናል፡፡ በኢትዮጵያ ግን ይህ የለም፤ብሎ ብሎ የዘንድሮው ውጤት መቶ በመቶ ወያኔ አሸናፊ የተባለበት ሆኗል፡የሚገርመው በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች የወያኔ ተወዳዳሪ ሙሉ ድምጽ አገኘ ሲባል ለሌሎቹ ተወዳዳሪዎች አገኙት ተብሎ የተገለጸው የእያንዳንዳቸው ውጤት ዜሮ በድፍረት ተጽፎ መገለጹ ነው፡፡ ተወዳዳሪዎቹ ራሳቸውን አልመረጡም ?ቤተሰብ ወዳጅ ዘመድ የላቸውም? ወያኔ ሀፍረት ብሎ ነገር አያወቅም እንጂ ይህ ማስተዋል የሌለበት አሳፋሪ የድንቁርና ስራ ነው፡፡ ሲዋሽ ትንሽ እውነት ይዞ ማጭበርበር ሲፈጽም ትንሽ ትንሽ እያስመሰሉ እንጂ እንዲህ ግልጽ ሆኖ የሚታይ እኩይ ስራ አይሰራም፡፡ አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ምርጫ ቦርድን ያመሰገኑት በዚህና ለዚህ ተግባሩ ነው፡፡ እስካሁን የተደረጉትን ምርጫዎች (ምርጫ 97ን ትተን) ብንፈትሽ የምናገኘው ምርጫ ማላጋጫ መሆኑን ነው፡፡ ቅንጅቶች በምርጫ 97 ወያኔ የሚያላግጥበትን ምርጫ የምር ምርጫ ለማድረግ በመቻላቸው ሕዝብ የለውጥ ፍላጎቱን በምርጫ ካርዱ አሳይቶ  ወያኔን ላልተዘጋጀበት አይደለም ፈጽሞ ላላሰበው ሽንፈት ሲዳርጉት ብዙዎቹ የወያኔ ሹማምንት ለጭንቅላት በሽታ እንደተዳረጉ ከራሳቸው ጭምር ሰምተናል፡፡ ምርጫ ቃሉን እንኳን ሲሰሙ ያ በሽታቸው ስለሚነሳባቸው ነው በምርጫ ወቅት የሚያቀበጠብጣቸው፡፡ በዛ ታሪካዊ ምርጫ ወያኔ  በእውር ድንብር ህገ ወጥ ተግባር ጉልበት ከሥርዓት ተጠቅሞ በፈጸመው ድርጊት “ሥልጣን ወይም ሞት፣ በጠመንጃ የተገኘ ስልጣን በምርጫ አይነጠቅም፣ በዮሀንስ ዘመን የተፈጸመው የሥልጣን ንጥቂያ በእኛ ዘመን አይደገምም”ወዘተ የሚልና እሱን ከስልጣን ለማንሳት የሚደረገውም ትግል ከባድ መስዋእትነት የሚያስከፍል መሆኑን አሳይቷል፡፡ በጠመንጃ ኃይል ሽንፈቱን ቀልብሶ አሸናፊዎቹን አስሮ ሥልጣኑን ካረጋገጠ በኋላ   ሽንፈት ብሎ ነገር ከዛ በኋላ ላለማየት ለሽንፈት የበቃበትን ምክንያትና መንገድ መርምሮ ምክንያቶቹን አስወግዷል፣ መንገዶቹንም ዘግቷል፡፡ ይህን የማያውቅ ፖለቲከኛ የለም ሊኖርም አይችልም፡፡ ስለሆነም በዚህ ሁኔታ ውስጥ ወያኔ የሚያካሂደው ምርጫ ማላጋጫ ከመሆን ያለፈ ፋይዳ ሊኖረው የሚችለው ተፎካካሪ ፖለቲከኞቹ የተዘጋውን አስከፍተው፣ የጠበበውን አስፍተው፣ የተከላውን መልሰው፣ ለእድሜ ማራዘሚያ የሚያዘጋጀውን ምርጫ ለሥልጣን ዘመኑ ማክተሚያ እንዲሆን ለማስቻል በየግል ጠንክረው በጋራም ተባብረው መቅረብ ሲችሉ ብቻ ነው፡፡ ወያኔ ለአሯሯጭነትና ለአጨብጫቢነት የፈጠራቸውንና ምርጫ ቦርድም ይህን ያህል ፓርቲ ተወዳድሯል ለማለት እንዲያስችለው የፓርቲነት መስፈርት ሳያሟሉ(አቶ በረከት በመጽኃፉ የቤተሰብ ፓርቲ ያላቸው) ፓርቲ እያለ እየደገፈ ያስቀመጣቸውንና ወያኔ እስትንፋስ የሚሰጣቸውን ትተን  ሕዝብ የሚያውቃቸውና እውቅና የሰጣቸውን ፓርቲዎች ብንወስድ በዘንድሮው ምርጫ አንዳቸውም ለሥልጣን የሚያበቃ የዕጩ ተወዳዳሪ ብዛት አላቀረቡም፡፡ይህን ሲያውቁ የአቅማቸውን ውስንነት ሲረዱ ደግሞ ተመካክረውና ተጋግዘው ሊቀርቡ ሲገባ ይህንንም ማድረግ አልቻሉም፡፡ እንደውም በተግባር የሚታየው  እያንዳንዳቸው ከወያኔ ጋር ከሚፎካከሩት በላይ ርስ በርሳቸው የሚፎካከሩ መሆኑ ነው፡፡ የምኒልክን ቤተ መንግሥት ሁሉም ይመኙታል ግን ሁሉም ያጡታል፡፡ ከዚህ አንጻር ካየነውና ከማለባበስ ወጥተን በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን ምርጫውን ማላገጫ ያደረገው ወያኔ ብቻ ሳይሆን አጅበው ያዘለቁት  ተዋሚዎችም ናቸው ለማለት ያሰደፍራል፡፡ በምርጫ መወዳደር በራሱ ግብ አይደለም፡፡ የምርጫ ሰሞን ብቅ ብሎ ሆይ ሆይ ማለትም በቂ የፖለቲካ ሥራ አይደለም፡፡ የፖለቲካ ስራውም ሆነ የምርጫ ውድድሩ ምርጫን ምርጫ ለማድረግና አሸንፎ የመንግሥትን ሥልጣን ለመረከብ ካልሆነም በቂ ወንበር አግኝቶ ፓርላማውን የአንድ ፓርቲ መፈንጫ ከመሆን ለማላቀቅ የሚያስችል መሆን ይኖርበታል፡፡ 547 መቀመጫ ላለው የተወካዮች ምክር ቤት ቁጥራቸው ከ200 ያልዘለለ ዕጩዎችን ይዞ ምርጫ መግባትና እናሸንፋለን ብሎ መፎከር አለያም የምርጫው ውጤት አስቀድሞ የታወቀ ነው እያሉ ማላዘን  ምርጫን ማላገጫ ማድረግ እንጂ ምን ይባላል፡፡ እንግዲህ ልብ እንበል፣በየግል ተወዳድሮ ለማሸነፍ የሚያስችል አቅም የላቸውም፡፡ይህን ተረድተው ከግል የሥልጣን ጥም ተላቀው ተባብረው ለምርጫ የሚቀርቡ አይደሉም፡፡ የሥልጣን መና ቢወርድላቸው ተስማምተው ይሄ ለአንተ ይሄ ለእኔ ብለው ስልጣን ተጋርተው መንግስት ለመመስረት የሚያስችል ቁመናም ባህርይም አይታይባቸውም፡፡ታዲያ ምን ሊሆኑ ወደ ምርጫ ገቡ? እነርሱም እንደ ወያኔ በምርጫው ሊያላግጡ? የሚያሳዝነው የፖለቲካ መሪዎቹ በሚያላግጡበት ምርጫ ለእስር ለስደት ለሞትና ለእንግልት የሚዳረገው ዜጋ ነው፡፡ ወያኔ በሥልጣን ከሚቀጥል የምንችለውን ሁሉ እናድርግ ብለው ከልብ ወስነው በቁርጠኝነት ቢነሱ ምርጫ የወያኔ ማላገጫ እንዳይሆን ማድረግ በቻሉ ነበር፡፡ እያንዳንዱን የወያኔ ሴራ እያጋለጡና የተንኮል ስራውን እያመከኑ ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማንበርከክ ባይቻላቻው ከማን አለብኝነት አይን አውጣ ስራ ሊያቅቡት በተቻላቸው ነበር፡፡ አንዱ ሲጠቃ ሌላው እልል እያለ፤አንዱ ከጨዋታ ውጪ ሲደረግ ሌላው ሜዳው የሰፋለት ያህል እየቆጠረ፣የአንዱ ዕጩ ሲሰረዝ ሌላው እሰይ እያለ ወዘተ ወያኔ የሚያላግጥበትን ምርጫ የምር ምርጫ ማድረግ አይቻልም፡፡ በሌላ በሌላው መተባበር ቢቀር ምርጫው የወያኔ ማላገጫ እንዳይሆን ለማድረግ  የጋራ እቅድ ነድፎ ተባብሮ መስራት ይጠይቃል ፡፡ ከፖለቲከኞቻችን አድራጎት የምናያውና ከየንግግራቸው የምንረዳው ግን ከእነርሱ ሌላ ተቀዋሚ ከሚያሸንፍ ወያኔ ቢቀጥል የሚመርጡ መሆናቸውን ነው፡፡ ታዲያ እነዚህ ከወያኔ ባልተናነሰ ምርጫን ማላገጫ ያደረጉ ናቸው ቢባል እውነትን ላለመቀበል ማንገራገር ካልሆነ በስተቀር የሚያከራክር ይሆናል? የተቃውሞ ፖለቲካ መሪነት ሥልጣን ሆኖ በውስጣቸው ርስ በርስ ይታመሳሉ፤ፓርቲ ከፓርቲ ይናቆራሉ፤ባይናቆሩም ፍቅር የላቸውም፤አብረው ሲሆኑም ሆነ ተለያይተው በቃላት ሲሸናቆጡ በቂ ምክንያት የላቸውም፡፡ በዚህ አቋምና ቁመናቸው ምርጫ እያሉ ከወያኔ ባልተናነሰ በምርጫ ያላግጣሉ፡፡ምንግዜም የማይረሳውን ምርጫ 97 ብንወስድ አራት ፓርቲዎች ቅንጅት ፈጥረው አንድ ሆነው ለምርጫ ቀረቡ፡፡ እኛ ስንዋደድ እግዜሩም ይረዳልና ያልታሰበ የምርጫ ምልክት ሁለት ጣት ሰጣቸው፤ልጅ አዋቂ ሳይል የቅንጅት መንፈስ ሰረጸበት፡፡ ምርጫ ቦርድ ሰባ ሰማኒያ ፓርቲዎች አሉ ሲል ሕዝብ በድምጹ የሚጠራው በምልክት የሚያሳየው ቅንጅትን ብቻ ሆነ፡፡ከዛ ቀጥሎ በተለይ በኦሮሚያና በደቡብ አንዳንድ ቦታዎች ህብረት፡፡ እነዚህ ሁለቱ ፓርቲዎች ደግሞ የምርጫ ሂደታቸውን አቀናጅተው በጋራ መግለጫ ከመስጠት አድማ እስከ መጥራት ደረሱ፡፡ እናም ምርጫውን ከወያኔ ማላገጫነት ወደ ትክክለኛ ምርጫነት ቀይረው ለአሸናፊነት በቁ፡፡ መጨረሻው አሳዛኝና አሳፋሪ ቢሆንም፡፡ ዛሬ መተባበሩ ቀርቶ የምርጫውን እንከን ለማሳየት እንኳን በጋራ መግለጫ መስጠት የሚችሉ ፓርቲዎች አላየንም፣ አልሰማንም፡፡ ታዲያ በየግል በቂ ዝግጅት አድርገው በበቂ ቁጥር ዕጩ አቅርበው ታዛቢ አዘጋጅተው የወያኔን ማጭበርበሪያ መንገዶች ለመዝጋት ወይንም በአቋራጭ ለማለፍ ስልት ነድፈው ለውድድር ካልቀረቡ፤ወይ ደግሞ አቅማቸውን ገምተው ከአንድ ብርቱ ሁለት መድሀኒቱ ብለው ተባብረው ካልሰሩ፡ምርጫ ስለተባለ ብቻ ወደ ምርጫ በመግባት የወያኔ አድማቂ ከመሆን ያለፈ ፋይዳ ከሌላቸው ምርጫውን ከወያኔ ባልተናነሰ ማላገጫ አድርገውታል ከማለት ሌላ ምን ሊባል ይቻላል፡፡ ሕዝቡ በወያኔ አገዛዝ ተማሯል፣እናም ለውጥ ይፈልጋል፣ይህንንም አሳይቷል፡፡ወያኔ በሕግና በሥርዓት አይደለም በጠመንጃም መግዛት የማይችልበት ደረጃ ቢደርስም ምርጫ 97ን እያስታወሰና እየቃዠ የዴሞክራሲያዊ ምርጫ መንገዶችን ሁሉ ዘግቶ  በስመ ምርጫ   የአገዛዝ ዘመኑን እያደሰ ቀጥሏል፡፡ ተቀዋሚዎች ደግሞ በተናጠል አይጠነክሩ ወይ ተባብረው አይሰሩ የወያኔን የማላገጫ ምርጫ እያደመቁ ለአገዛዝ ዘመኑ መራዘም ቡራኬ ይሰጣሉ፡፡ ከሁለት ያጣ የሆነው ሕዝቡ ነው፤ የሥልጣን ባለቤትነቱን የሚያረጋግጥለት ቀርቶ ሰዋዊ ክብሩን የሚያከብር የሚያስከብርለት መንግሥት አላገኘ፤ወይንም ከአምባገነን አገዛዝ የሚያላቅቀው ታግሎ የሚያታግለው መርቶ ወደ ለድል የሚያበቃው ተቀዋሚ/ተቀዋሚዎች አላገኘ ፡፡ - See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/44405#sthash.pkH02yvd.dpuf






election

No comments:

Post a Comment