Thursday, June 18, 2015

ለእውነት እንዳንታገል አዚም የሆነብን ምንድር ነው? – ዘጠኙ ምክንያቶችን እንሆ -(በይበልጣል ጋሹ -

ስለ እውነት በተግባር እንጂ በቃል ደረጃ ብዙ ማለት ከባድ ቢሆንም ብዙዎች ብዙ ጽፈዋል ተናግረዋል። እውነት ማለት ያዩትን፣ የሰሙትን፣ የሚያውቁትን፣ የተረዱትን፣ የሆኑትን እና የሚያምኑበትን ነገር ሳይጨምሩ ሳይቀንሱ በግልም ሆነ በአደባባይ በይፋ መናገርና መመስከር መቻል እንደሆነ የዘርፉ ሙህራን ያስረዳሉ። በሌላ መልኩ ደግሞ ያላዩትን፣የማያውቁትን፣ ያልሰሙትን፣ ያልሆነን ነገር ሳያረጋግጡ እና የማያምኑበትን ጉዳይ አለመናገር ማለት እንደሆነም አክለው ያስረዳሉ፡፡ በአጭሩ እውነት የሀሰት ተቃራኒ ነው። እውነት ለመናገር፣ ስለ እውነት ለመመስከር በመጀመርያ ሀሰትን መቃወም ይኖርብናል። ስለ እውነት ለመናገር ያልቆሸሸ ንጹህ ሕሊና ሊኖረን ይገባል። ንጹህ ሕሊና እውነተኛ ዳኛ ነውና። ያልተበረዘ፣ያልቆሸሸ እና ንጽህ ሕሊና ሀሰትን የማስተናገድ ባህሪ የለውም።
Tensaye
ሀቀኝነት፣ ታማኝነት፣ እርግጠኛነት፣ ትክክለኛነት፣ ተጠያቂነትን መቀበል እና ሀላፊነትን መወጣት የእውነት መገለጫ ባህሪያት ናቸው። በሌላ አነጋገር እውነት ማለት ጽድቅን ማድረግ፣ መልካም ሥነ ምግባርን መላበስ እና ለነጻነት፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ግንባታ መታገል ማለት ነው። እውነት ማለት ሀገር፣ ታሪክ፣ ባህል እና ማንነት ነው። እውነት አድሎ የማይታይበት፣ ርህራሄና ቸርነት በተሞላበት ለሰው ልጅ ሁሉ መልካም ነገር እንዲያገኝ መመኘትና በጎ ተግባራትን ማከናወን ነው። እውነት የሰው ልጅ ዘላቂ ሰላም እና የተረጋጋ ህይወት እንዲያገኝ ከፍተኛ አስትዋጾ ያደርጋል።

ቀደምት አባቶቻችን ስለእውነት ሲሉ ውድ ህይወታቸውን በሰማዕትነት አሳልፈው ሰጠዋል፤ ብዙ መከራና ስቃይ ተቀብለዋል። ለእውነት ሲሉ ከጊዜያዊ ጥቅም ታቅበዋል። ዛሬም ለእውነት ሲሉ ዋጋ እየከፈሉ የሚገኙ እውነተኛ የእውነት ምስክሮች በብዙ ስቃይና መከራ ውስጥ ይገኛሉ። በብዙ ውጣ ውረድ እውነትን መናገር እጅግ መልካምና ልብን የሚያስደስት ቢሆንም እውነትን የሚወዷትን ያህል የሚፈሯትና ከቻሉም በሀሰት ለውጠው ለማጥፋት የሚመኙ ብዙዎች ናቸው፡፡ በተለይ ጥቅምና ስልጣን ፈላጊዎች እንዲሁም አምባገነን መሪዎች በዋናነት ለእውነት መጥፋት ዋነኛ ተዋናኞች ናቸው፡፡
አምባገነን መሪዎች እውነትን መከተልም ሆነ መስማት አይፈልጉም። መነሻቸውና ግብራቸው ሀሰት ስለሆነ እውነትን ፈጽመው አያውቋትም። እርግጥ ነው እውነት ለእነሱ ጠላት ናት፤ ታጠፋቸዋለች። እነርሱ የሀገር መጥፋት፣ የታሪክ መዛባት፣ የህዝብ ሰላምና ደህንነት አያስጨንቃቸውም። ለሥልጣን ማራዘሚያ ሀገር ይሸጣሉ፣ ህዝብን ይጨቁናሉ፣ ይገድላሉም።
በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ ስለ ነጻነት፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ማውራትና መስበክ ወንጀል ከሆነ ዘመናትን አስቆጥሯል። በዚህ ዙርያም ለምን እና እንዴት ብለው የሚጠይቁ ዜጎች እጣ ፈንታቸው እስር፣ እንግልትና ሞት ሆኗል። በኢትዮጵያም ያለው ይህ እውነትን የሚፈራ እና ከእውነት ፈጽሞ የተጣላ የህወሓት አገዛዝ ለሀቅ፣ ለእውነት የቆሙትንና ሕዝብ እውነትን ያውቅ ዘንድ ያለመታከት እየሰሩ የሚገኙ ጋዜጠኞችን፣ ጦማርያንን፣ የፖለቲካ መሪዎችን እና ንጹሃን ዜጎችን ማሳደድና ማሰር ቀጥሎበታል፡፡ በአጠቃላይ ለነጻነት፣ፍትህና ዲሞክራሲ የሚታገሉ ውድ ኢትዮጵያውያንን ወያኔ ማንኛውንም ዋጋ ከፍሎ ወደ ግዞት እንዲወረወሩ ማድረግ፣ መግደልና ማሰቃየት የሥርዓቱ ተቀዳሚ ተግባር አድርጎታል። ወያኔዎች ሰባዊነት የሚባል በውስጣቸው ቅንጣት ስለሌላቸው በነጻነት ታጋይ ኢትዮጵያውያን ላይ የአካልና የሥነ ልቦና አሰቃቂ እና ኢ_ሰባዊ ድርጊት ካለ ምንም ርህራሄ ይፈጽማሉ፤ ዛሬም በመፈጸም ላይ ይገኛሉ።

የወያኔ ፈላጭ ቆራጭ፣ ዘረኛና አምባገነን አገዛዝ በህብረተሰቡ ላይ የሚያደርሰው ግፍና ሰቆቃ ከመብዛቱ የተነሳ ለእውነት እንዳንቆም እንቅፋት ሆኖብናል። ብዙዎች እውነት መናገር ቢፈልጉም እንዳይናገሩ የተለያዩ አመክንዮ ይሰጣሉ። ከፊሎችም በወያኔ አምባገነን አገዛዝ ተጠልፈው የሥርዓቱ ከዳሚና ደንገጡር በመሆን ከእውነትና ከእራሳቸው ጋር ተጣልተው የሕሊና እስረኞች ሆነው መኖር ጀምረዋል። አብዛኛው ህዝብ ደግሞ ከእውነት ጋር ለመቆም፣ ለእውነት ለመታገል ጊዜና ወቅት በመጣባበቅ ላይ ይገኛል። ብዙ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የወያኔን የውንብድና አገዛዝ ተቋቁመው ለእውነት ሲሉ ሰማዕትነትን እየተቀበሉ ይገኛሉ። እውነት ዘላለማዊ ሰላም የምታጎናጽፍ ከመሆኗም በላይ ድልን የምታቀናጅ አሸናፊ ናትና።
- See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/44426#sthash.8JwkWRYC.dpuf

No comments:

Post a Comment