Monday, June 15, 2015

ይድረስ ስለ አንዳርጋቸው – አብዩ በለው ጌታሁን

andargachew Tisge           እነ ጀነራል ተፈራ ማሞ በመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተጠርጥረው በህወሃት የማሰቃያ ጉድጓድ ከተጣሉ እነሆ የዳግሚያ ስቅለት 6ኛ አመታቸው አለፈ ፡፡ ታዲያ በዚያን ሰሞን ነበር፡-
1ኛ. ጀነራሎቹ እንዴት በህወሃት የስለላ ወጥመድ ውስጥ ሊወድቁ ቻሉ?
2ኛ. ስህተቱ በማንና ምን ላይ ተሰራ? ከመካከላቸው ለህወሃት ያደረ ይኖር ይሆን? ወዘተ የመሳሰሉ ጥያቄዎችን ያለማቋረጥ አስተናግድ የነበረው፡፡
እነሆ ዛሬ እነዚህን መሰል ወሳኝና ፈታኝ ጥያቄዎች ለድርጅታዊ ወይም ለግልፅ ህዝባዊ ውይይት ቀርበው ምላሽ ሳያገኙና የእርምት እርምጃ ሳይወሰድባቸው ስድስት የድብት አመታት አለፉና ዛሬም ሌላ ዙር ክሽፈት፣ ሌላ ዙር አስጨናቂ ጥያቄና፣ ሌላ ዙር መራር መርዶ ለማስተናገድ የተገደድን ይመስለኛል፡፡
በአንፃሩ ደግሞ ዛሬ በህወሃት የማሰቃያ ጉድጓድ ውስጥ የተጣለው የግንቦት 7ቱ አቶ አንዳርጋቸው ባይሆን ኖሮ ከላይ የገለፅኳቸውን ተመሳሳይ ጥያቄዎች ከስድስት አመታት በኃላ ወደ ማን ይዥጎደጉዳቸው ነበር? ብዬ መጠየቄ አልቀረም፡፡ ለምን ቢሉ እነሆ ያ! ብርቱ ጠያቂዬ ዛሬ ሊጠየቅለት ተረኛ ሆኗልና ተጠያቂነቱን ለባለተራዎቹ እነሆ በረከት እላለሁ፡፡
ዛሬ ድረስ በህወሃት አረመኔያዊ የማሰቃያ ዘዴዎች ለሚሰቃዩት ለእነ ጀነራል ተፈራ ማሞ እና ጓዶቹ  መታሰቢያ ትሁንልኝ፡፡
መልካም ንባብ
ለነፃነታችን፣ ለፍትህና፣ ለዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ መገንባት ከህወሃት በተፃፃሪ ተሰልፈን ለምንታገል ሁሉ፤ መቼም ቢሆን ፀፀቱ ለማይለቀን ስህተትና ውድቀት ስንዳረግ፣ ህወሃትንና የስለላ ቡድኑን ምትሃታዊ አድርጎ ማቅረብና ውንጀላውንም ሆነ ተጠያቂነቱን ወደ አንድ ጥግ መግፋት የሚያዋጣና ከተጠያቂነት የሚያድን የብልሆች መንገድ አልመስልህ ካለኝና የ“ቀስት” መንገድ ከተኮላሸ እነሆ አስርት አመታት፤ የእነ ጀ/ል አሳምረው ፅጌ ጉዞ ከከሸፈ ደግሞ ድፍን ስድስት አመታት እንደዋዛ ነጎዱ፡፡
ፈላስፋው “ታሪክ እራሱን ደገመ፣ መጀመሪያ አሳዛኝ ቀጥሎ ቧልት በሚመስል መንገድ” እንዳለው ሁሉ የእነ ጀነራል ተፈራ ማሞ በህወሃት ወጥመድ ውስጥ የወደቁበትን አሳዛኝ እውነታ ለማወቅና የጥፋቱን ቋጠሮ ለመፍታት እንዲያ በእልህና በቁጭት ተውጦ የጥያቄ ናዳ ሲያወርድብኝ የነበረው አይታክቴው የፅጌ ልጅ ዛሬ ለህወሃት ቧልት በሚመስል መልኩ በዚያው ወጥመድ ተጠልፎ ሲሰቃይ ማየት በእጅጉ ያማል፡፡
ይህ ብርቱ ፀፀትና ህመም የሚጠግገውና የህወሃትን የጠለፋ ቡድን ከአስማተኛነት ወደ ወጀድ ጠባቂነት ማውረድ የሚቻለው፣ ከአቶ አንዳርጋቸው መጠለፍ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ውስጣዊና ውጫዊ ጉዳዮች ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው ሁኔታ በመመርመር፣ የተፈፀሙትን ስህተቶች ነቅሶ በማውጣት የማያዳግም የእርምት እርምጃ መውሰድ ሲቻል ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
ለዚህም ይረዳ ዘንድ በተለይም፡-
1ኛ. ድርጅታቸው ግንቦት 7 ለፍትህና ለዲሞክራሲ ንቅናቄ (የአሁኑ አርበኞች ግንቦት 7) ፣
2ኛ. የህዝብ አይንና ጆሮ የሆናችሁት የእኔው ኢሳት፣ አዲስ ድምፅ ሬዲዮና፣ ሁላችሁም ነፃና የህዝብ ሚዲያዎቻችን በሙሉ፣
3ኛ. የህወሃትን ሸፍጥ በማጋለጥ የምትተጉና ለእውነት ዘብ የቆማችሁ ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች፣ በተለይም ጓዴ አበበ ገላው፣
እናንተ ሁላችሁ ኃላፊነትና ተጠያቂነትን አያጣችሁምና ቅድሚያውን በመውሰድ የየበኩላችሁን ጥረትና ምርመራ በማድረግ የደረሳችሁበትን እውነት ወገኖቹን ከወያኔ መንጋጋ ነፃ ለማውጣት ሌት ከቀን ለሚባዝነው ወገናችሁ የማሳወቅና መጭውንም አደጋ ከወዲሁ የመከላከል ታላቅ ኃላፊነትና አደራ አለባችሁ የሚል ፅኑ እምነት ስለአለኝ፤
ይልቁንም አበው “ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ” እንዲሉ፡-
እግረ-መንገዳችንም ህወሃት መራሹን ዘራፊ ቡድንና የሚዲያ ተቋማቱን ከምንወቅስበት የግልፅነትና የተጠያቂነት በሽታ ይልቁንም “ከልማታዊ ጋዜጠኝነት” እራሳችንን እያፀዳንና ለዚህ ክስረት አስተዋፅኦ ያደረጉና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ አካላት የድርሻቸውን በማንሳት ለህዝባቸው ያላቸውን ታማኝነትና ተጠያቂነት ማረጋገጥ ቢችሉ እሰዬው ነው፡፡
1ኛ. አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በህወሃት የስለላ ወጥመድ ውስጥ እንዴት ሊወድቁ ቻሉ?
እርግጠኛ መሆን አይቻል እንደሆን እንጂ ይህ ጥያቄ የሁሉንም ነፃነት ናፋቂና ታጋይ ኢትዮጵያዊ ህሊና በእጅጉ የሚሞግት ይመስለኛል፡፡ በተለይም ለቀጣዩ የትግል ጉዞ ትምህርት ሊሆኑ የሚችሉ፣ የህወሃትን አስማተኛነት የሚያረክስ፣ ሁሉም በህወሃትና አጋሮቹ የስለላ መረቦች ላይ በሩን አጥብቆ እንዲዘጋ የሚረዱ ቅርቃሮች ለማግኘት በሚያግዙ ተጠየቆች ላይ ትኩረት ይሰጣል የሚል ፅኑ እምነት አለኝ፡፡
የአቶ አንዳርጋቸው የየመን ጉዞ የስህተቶች ሁሉ ድምር ውጤት መቋጫ/መዳረሻ ሊሆን ይችል እንደሆን እንጂ ዋናው ስህተትና የመጀመሪያው መጨረሻ ቀደም ብሎ እንደተሰራ መገመት አያዳግትም፡፡ ከዚህም በመነሳት የፅጌን ልጅ ለክፉው አሳልፎ ሊሰጣቸው የቻለው ስህተት የትኛው/ኞቹ ነበር/ሩ?  ብሎ መጠየቅ ተገቢና ወቅታዊ ይመስለኛል፡፡
ይልቁንም አቶ አንዳርጋቸው ከማንም በተሻለ ሁኔታ የህወሃትና የአጋሮቹን የስለላ መዋቅርና አሰራር ጠንቅቀው የሚያውቁና በተለይም የየመንን መንግስትና በወቅቱ የነበረውን የአካባቢውን ተጨባጭ ሁኔታ ተንትነው የሚያስረዱ እንደሆኑ ለማመሳከር ወደ ኢሳት ማህደር ጎራ ማለቱ ከበቂ በላይ ይመስለኛል፡፡ በተለይም ይህን የህውሃት አፋኝ ቡድን ተግባራት ጠንቅቆ የሚያውቀው የግንቦት 7 “የስለላ ክንፍ” የመሪውን እንቅስቃሴና ደህንነት እንዴት ነበር የሚከታተለው? የድርጅቱ መሪ በባላንጣው የአፈና ወጥመድ እንዴት ሊታፈኑ ቻሉ? ተቀዳሚ ጥያቄዎቼ ናቸው፡፡
2ኛ. ለመታፈናቸው እነማን አስተዋፅኦ አደረጉ? ተጠያቂዎቹስ? (የወደቀችውን የመን አንድ ብያለሁ)
ሁሌም እንደሚባለውና እንደሚታመነው፣ ለህወሃት መራሹ ዘራፊ ቡድን ጡንቻ መፈርጠምና እድሜ መራዘም ከእራሱ ከህወሃትና ከግብረ-አበሮቹ ጥንካሬ ይልቅ ለነፃነት፣ ለአንድነትና፣ ለዲሞክራሲ መከበር የምንታገል ግለሰቦችና ሃይላት ድክመት ትልቁንና ዋናውን ድርሻ እንደሚይዝ ተብሎ ተብሎ ያለቀለት ጉዳይ ነው፡፡
በተለይም ተጠያቂነትንና ግልፅነትንም በተመለከተ ህወሃት ከበርሃ ጀምሮ ለሚፈፅማቸው መራር ግፍና ወንጀሎች እነሆ ዛሬም ይከሰሳል፡፡ ይወቀሳል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ባለፉት 24 ዓመታት ብቻ ለተለያዩ ድርጅቶች፣ ጥምረቶች፣ ህብረቶችና፣ ቅንጅቶች መፍረስ፣ ለታጋዩ መበታተንና፣ ለነፃነት ናፋቂ ወገናችን ቅስም መሰበር አስተዋፅኦ ያደረጉና ሂደቱንም የመሩ ሁሉ ግልፅ በሆነ መንገድ ሂሳባቸውን ሳያወራርዱና ይመሩት ለነበረው ድርጅትና ህዝብ ያላቸውን ተጠያቂነት ሳያረጋግጡ ከአንዱ ወደ ሌላኛው መገለባበጣቸው ምን ያህል ትግሉን እንደጎዳውና ህወሃትን እንዳፈረጠመው በተግባር አሳይቶናል፡፡
ዛሬ ዛሬ በነፃነት ታጋዩ በኩል ለሚፈፀሙ ተመሳሳይ ክህደቶች፣ ወንጀሎችና፣ ጥፋቶች እንደ አይነታቸውና መጠናቸው ተጠያቂው አካል ተለይቶ ሊታወቅ፣ ተገቢውን የእርምት እርምጃም በወቅቱ ሊወሰድና፣ ውጤቱ እንደ አስፈላጊነቱ ለታጋዩና ለሰፊው ህዝብ ሊገለጥ ይገባል የሚለው አስተሳሰብና እምነት ገዥ ሃሳብ እየሆነ የመጣ ይመስለኛል፡፡ የመሻላችን አንዱና ዋነኛው መገለጫ ግልፅነትና ተጠያቂነት ካልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? ደርግ ክፍል ሶስትን በላያችን ላይ ለማንገስ?
ይልቁንም በሃገርቤት በሰላማዊ መንገድ ለመታገል የቆረጡትን ንፁሃን ታጋዮች በማን አለብኝነት እያፈነ፣ በውስጡ ሆነው የተቃወሙትንና ለህሊናቸው ለመቆም የተውተረተሩትን መዋጥ ስላልበቃው፤ ይኃው የሞተው እባብ እኛው ባፈረጠምናቸው ክንዶቹ ባህር ተሻግሮና ድንበሮችን አቆራርጦ በሱደንና በኬንያ ስንገረም የመን ደርሷል፡፡
ህወሃት የመን ድረስ ተጉዞ አቶ አንዳርጋቸውን ሲያፍን በወቅቱ የነበረው የየመን ብልሹና የተፍረከረከ አስተዳደር ያደረጉት አስተዋፅኦ የሚታወቅና ግልፅ ነው፡፡ ነገር ግን ሌሎች አካላት አስተዋፅኦ አላደረጉም ብሎ ማሰብ ግን ለእኔ አልተቻለኝም፡፡ ጥፋቱንም ሁሉ ህወሃትና የመን ላይ የሚጠፈጥፍ ግለሰብም ሆነ ተቋም ካለ፣ እርሱ በቀደመውና ህወሃት በመጣበት ሁሉንም ጥፋት “አማራ”ና “ደርግ” ላይ የመለጠፍ የሸፍጥና የማንአለብኝነት ጎዳና መሄድን የመረጠ ብቻ ይመስለኛል፡፡
ስለዚህም፡-
ለአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በህወሃት የአፈና ቡድን መጠለፍ አስተዋፅኦ ያደረጉ ሁኔታዎች ምንና ምን ናቸው? ተጠያቂ አካላትስ እነማን ናቸው? ድርጅታቸው ግንቦት 7 እና አመራሩስ ምን ያህሉን ድርሻ ይወስዳሉ? የኤርትራው ሰውዬስ አይመለከታቸው ይሆን? ወዘተ  . . . በማለት አቶ አንዳርጋቸውን አክዬ ስለ አቶ አንዳርጋቸው ድምፄን ከፍ አድርጌ ለመጠየቅ እገደዳለሁ፡፡
- See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/44270#sthash.TZXqgkhK.dpuf

No comments:

Post a Comment