Thursday, January 22, 2015

ብርቱካን ተናገረች፣ ብርቱካን አሁንም ያቺው ብርቱካን ነች

የብርቱካንን ሙሉ ቃል በድምጽ የተደመጠውን ለማዳመጥ እድል ለማያገኙ፣ ድምጿንም፣ መልእክቷንም ሲናፈቁ ለነበሩ ዜጎች መልእክቱ እንዲደርሳቸው በማሰብ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ መወያያ መድረክ ንግግሯን እንዳለ በጽሑፍ ከዚህ እንደሚከተለው ያቀርባል::
Birtukan Mideksa, Washington D.C. Speech
ንግግሯን ከማቅረባችን በፊት ግን አንባቢያን በአይነ ህሊናችሁ ሁኔታውን ለመቃኘት ያመቻችሁ ዘንድ ጥቂት ማለት እንፈልጋለን።
“መሪ ይፈጠራል እንጂ አይወለድም” ፍጡር ደግሞ አስትንፋሱ እስክትቋረጥ ድረስ ያው ፍጡር ነውና በህያውነት የተፈጠረበትን ተግባር ማከናወን ይቀጥላል:
ብርቱካን መሪ ሆና ተፈጥራለች፣ በመሪነት ተቀጥላለች።
በባህላችን ጀግና ይፈጠራል እንጂ መሪ ይፈጠራል የሚል አባባል የተለመደ አደለም: ገዥ እንጂ መሪ ኖሮን ስለማያውቅ ይሆን? ወይስ መሪነት ከእግዚአብሄር ተቀበቶ የሚሰጥ ጸጋ ስለሆነ፣ ወይም ታሪክ ሓላፊነት የሚጥልበት ስለሆነ? አለዚያም መሪነት የሚገኘው በትግል አሸንፎ ነው ስለሚባል?
መልሱን አንባቢያን እንዲያሰላስሉት እንለፈውና ወደ ተነሳንበት አንኳር ጉዳይ እንመለስ። ብርቱካን ተናገረች ንግግሯ አጭር ነው፣ በሕጻናት ቡረቃና ጫወታ የታጀበ ነበር፣ የነገ ተረካቢዎች ናቸውና እሰየው የሚያሰኝ ነው: ከንግግሯ የበለጠ ግን አካላዊ ቋንቋዋ (body language) የበለጠ ጮሆ ይደመጥ ነበር: በእስር ቤት በነበረችበት ጊዜ በአገር ቤት እና በመላው አለም ተበትነው የሚገኙ ወገኖቿ ላደረጉላት ሞራላዊም ሆነ ቁሳዊ ደጋፍ ስታመሰግን፣ አሁንም ወገኖችዋ እያሳዩአት ያለው ፍቅር እንክብካቤ ስትገልጽ በታላቅ ትህትና ከአንገቷ አጎንበሳ ሳይሆን ለጥ ብላ እጅ ነስታ ነበር:: ለህዝብ ያላትን አክብሮት፣ ፍቅር ለመግለጽ ተቸግራ ጭንቅ ጥብብ ስትል ማየት የህዝብ ፍቅር ልክፍት መሆኑን መረዳት ይቻላል::
ከምስጋና ቀጥላ ወደ እለቱ በዓል አላማ ነበር የገባችው: የዛሬው በዓል አላማ ኢትዮጵያዊነትን እናክብር፣ “ሰለብሬት” እናድርግ የሚል ነው: ግን እትዮጵያዊነት መከበር ያለበት ጊዜ ላይ ነን ወይ የሚለውን ጥያቄ ራሷ አንስታ ስትመልሰው፣ ከቃላቶቿ በላይ ፊቷ ላይ ያንዣበበው የሐዘን ዳመና ከውሰጧ ማዕበል የሚንጣት መሆኑን ፍንትው አርጎ ያሳይ ነበር።
ከሐዘኗ መልስ ግን የኢትዮጵያን ታላቅነት ገልጻ፣ ተሰፋን ከራሷ እንድንማር ስትመክር: ካመት በፊት የነበረችባትን ጠባብ ሽንት ቤት አይሏት ባኞ ቤት አስቃኝታን፣ ጥላሁን ሲሞት የደረሰባትን አስታውሳ “ሀዘንም ከሰው ጋር ነው” “የሚሉትን ባላውቀዉም ዋርድያዎቹ ሲነጋገሩ ስሰማ ቀለል ይለኝ ነበር” እነዚህ ቃላቶች ከፊቷ ገጽታ መለዋወጥ ጋር ሲሰሙ አጥንት ድረስ ዘልቆ የመግባት ሓይል ነበራቸው።
በመጨረሻም “አሁንም ተሰፋ አረጋለሁ፣ አሁንም አልማለሁ” ስትል ጸዳሏ እንደገና ፈክቶ ነበር።
አሁን ቀጥታ ወደ ንግግሯ
“ስቴዲየሙ ይዘጋል ብለው በጣም አስፈራርተውኛል! ነገር አላበዛም: እኔ ሁለት  ነገር ነው ማለት የምፈልገው:ከሁሉ አሰቀድሞ ቅድምም ለመናገር እንደፈለኩት የዚህን ፐሮግራም አዘጋጆች በጣም አመሰግናለሁ: እግዚአብሄር ያክብርልኝ ስላከበራችሁኝ እላለሁ: ከዚያ በላይ ደግሞ እናንተ ሁላችሁም እዚህ የተገኛችሁም፣ ያልተገኛችሁም ኢትዮጵያውያን ደርሶብኝ በነበረው ችግር ከጎኔ ስለቆማችሁ፣ የማቴሪያል የሞራል እርዳታ ስላርጋችሁልኝ በጣም፣ በጣም፣ በጣም፣ ከልብ፣ ከልብ ላመሰግናችሁ አወዳለሁ።
እውነቴን ነው ለስሜት መግለጫ ሌላ ነገር፣ ልላ ቃላት ቢኖር ጥሩ ነበረ፣ ..ከተፈታሁበት ጊዜ ጀምሮ አገር ውስጥ ያሉ ወገኖቼ፣ በየቦታው አገር ቤትም እያለሁ  እዚህም ድረስ መጥተው ያላቸውን ስሜት፣ ለኔ የነበራቸውን ሃዘኔታ፣የጸለዩትን ጸሎት ያደረጉትን ድጋፍ ሲገልጹ እኔም በጣም የሚከብደኝ ነገር ነበረ: እዚህም  በናንተ መሃል ተገኝቼ ይህንኑ ነው የተረዳሁት: እኔም ባልነበርኩበት ጊዜ የሆነውን ሁሉን ነገር አውቃለሁ: ዛሬ ሻምበል እኔ ባለሁበት በመዝፈኑ የተሰማውን ስሜት መገመት እችላለሁ ምክንያቱም እያለቀሰ ዘፍኖታል ይህንን ዘፈን: ዘፈኑን መስማት ግን ለኔ በጣም ይከብደኛል ከሚገባኝ በጣም የሚያለፍ ነው ብዬ የምር ስለማምን ነው: አና ሁላችሁም ያደረጋችሁልኝ ፍቅር ያሳያችሁኝ መልካም ስሜት ለኔ ከሚገባኝ በላይ ነው ብዬ ነው የማምነው አሁንም ደግሜ ሁላችሁንም እግዚአብሄር ያክብርልኝ::
ልላ አንድ ነገር መናገር የምፈልገው የዚህ ፕሮግራም ዋና አላማ እንደገባኝ ከሆነ ኢትዮጵያዊነትን ማወደስ የሚል አላማ ያለው ነው: እያሰብኩ ነበረ፣ ኢትዮጵያዊነት ዛሬ ኢትዮጵያ የምትወደስ ነች ወይ? አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት እኛ ያለንበት ሁኔታ የሚወደስ ነገር ነወይ? የሚከበር ነገር ነው ወይ? የሚለውን ነገር ሁላችንም ብንጠይቅ መለሱ አሉታዊ  ነው ብዬ አምናለሁ: ምክንያቱም  ኢትዮጵያ የነጻነት አገር አደለችም፣ ኢትዮጵያ የፍትህ አገር አደለችም: ኢትዮጵያ አሁንም ዜጎቿ ከድህነት ጋር የሚኖሩባት፣ በእፍረት የሚያቀረቅሩባት፣ እንደናንተ እንደብዙዎቻችሁ በስደት የሚሸሹባት አገር ነች: ስለዚህ አናወድሳት ወይ? ብለን ብንጠይቅ አይ ማወደስስ አለብን ነው መልሱ: ስናወድሳት ግን ምንን አስበን ነው? ኢትዮጵያ ታላቅ ሐገር ነበረች ስለሱ እኔ የምናገረው ነገር አደለም ታሪክ ያሰተምረናል: ግን ኢትዮጵያ ታላቅም  ትሆናለች ብለን ማመን እንችላለን ማመንም አለብን በዬ በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ መወደስ አለባት።
ተሰፋ ማድረግ በጣም አሰቸጋሪ እንደሆነ ግን አውቃለሁ: ብዙዎቻችን ፖለቲካ ውስጥ ያለንም የሌለንም፣ ያገራችን ጉዳይ ግድ የሚለን ዜጎች በሙሉ ያየናቸው፣  ያጋጠሙን ነገሮች አገራችን ያለችበትን ሁኔታ ስናይ፣ ስንገመግም የምናገኘው ነገር ተስፋ ለማድረግ በጣም አሰቸጋሪ መሆኑን አውቃለሁ:: ቅድም ክሪስ እዚህ ስለ ሌሎች አገሮች ሲነግራችሁ ነበረ: ብዙ ምሳሌዎች  ማነሳት ይቻላል ተሰፋ ለማረግ ምክንያቶች: የሰው ልጆች በታሪክ ውስጥ ያሸነፏቸው ተግባራቶች ማንሳት ይቻላል:
እኔ ግን ተሰፋ ለማረግ እኔን እዩ እላለሁ!  ከዛሬ አመት በፊት  በጣም ጠባብ የሆነች ክፍል ውስጥ ለብቻዬ ተቀምጬ በብቸኝነት እሰቃይ ነበር:  ስቃዩ ደግሞ ዘሬ ስናወራው ሊቀል ይችላል ግን በጣም፣ በጣም ጥልቀት ያለው ስቃይ ነበር: አልረሳውም አንድ ጋዜጠኛ እዚህ እየጠየቀኝ ነበር ስለ ጥላሁን ምን ሃሳብ አለሽ? የሞተ ጊዜ የት ነበርሽ? አለኝ: የሞተ ጊዜማ ባዶ ቤት ነበርኩ፣ የሚያናግረኝ ስው አጥቼ ለማን እንደምተነፍሰው፣ ስለስራው ምን እንደምል? የተሰማኝን ሰሜት ለማ እንደምናገረው ግራ ገብቶኝ ፖሊስ መጥቶ በሬን አስከሚከፍት እጠብቅ ነበር: መቶ በሬን ሲከፍተው ሞተ አደል? ሰማችሁ አደል? ሰማሽ አደል? ስላት ቆልፋብኝ ሄደች: ሀዘንን እንኳ ማዘን የሚቻለው የሚጋራህ ሰው ሲገኝ ነው!  እውነቴን ነው የምላችሁ በዚያን ሁኔታ ውስጥ ቁጭ ብዬ የነበረኩበት ነገር ለዘላለም ሊቀጥል እንደሚችል በጣም ብዙ ቀን አሰቤያለሁ: ለብዙ ጊዜ የማያቸው ነገሮች ግድግዳዎች፣  መታጠቢያ ቤት በሉት ሽንት ቤት በሉት በጣም አነስተኛ ነገር አለ: በቆርቆሮ ነው የታጠረው: ያ ቆርቆሮ፣ ከዚያ ደግሞ አልፎ የሚሰማው የዋርድያዎች ድምጽ ዛሬ ስለዋርድያዎች ድምጽ ግን ሳነሳ እንደቅሬታ ሊሆን ይችላል የኔ ግን ትንሽ ያስደስተኝ ነበር: ከጸጥታ የነሱ ድምጽ ይሻለኝ ነበር ምን እንደሚሉ እንኳ ባይገባኝ:
ምን ልላችሁ ነው? ከዛ መከራ ከዛ ብቸኝነት ወጥቼ ዛሬ አንድ ብቻ የነበርኩት በጣም ብዙ በሚወዱኝ ሰዎች መሃከል ተከብቤ እገኛለሁ: ዛሬም ተስፋ አረጋለሁ ስላገሬ፣ ዛሬም ህልም አልማለሁ፣ አጠንከሬ አልማለሁ፣ በናንተ አምናለሁ፣ በራሴ አምናለሁ፣ በልጄ አምናለሁ፣ በሚመጡት የልጅ ልጆች ሁሉ አምናለሁ: ስለዚህ ኢትዮጵያ ታላቅ ነች እላለሁ: ልትወደስ ይገባታል እላለሁ:  እናንተም በዚህ ሃሳብ እንደምትስማሙ አምናለሁ: መልክቴ ይኸው ነው: ኢትዮጵያ ልትወደስ የሚገባት ታላቅ ሐገር ነች: ታላቅነቷን ለማየት ግን ሁሌም ተስፋ ይኑረን፣ ሁሌም ባንድነት እንቁም: አንድነታችን ሁሉንም የሚያቅፍ፣ ሁሉንም የሚያሰባስብ፣ የኢትዮጵያን የጋራ መኖሪያነት የሚያወድስ ይሁን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

የዲሞክራሲ ለውጥ ድጋፍ ድርጅት በኖርዌይ ጉባኤ አዘጋጅቷል

የዲሞክራሲ ለውጥ ድጋፍ ድርጅት በኖርዌይ የ3ኛና 4ኛ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ክንውን የሚቀርብበትና ለወደፊት ሊሰሩ የሚገባቸውን ተግባራት ለመወሰንበህገ ደንባችን መሰረት ምልዓተ ጉባኤ ማዘጋጀት አስፈልጓል። ስለዚህ የድርጅቱ አባላት በሙሉ በፌብሯሪ 14/2015 ከቀኑ 13፡00 እስከ 16፡00 ስዓትእንድትገኙ በጥብቅ እናሳስባለን!ከዚህበመቀጠልም
የአርበኛው አቶ አንዳርጋቸው ፷ኛ ዓመት የልደት በዓል!
ለኢትዮጵያ አገራችን ነጻነትና ፍትህ ለማስፈን የህይወት መስዋትነትን እስከ መክፈል ድረስ እየታገለ የሚገኘውን የነጻነት ተምሳሌት የጀግናው አንዳርጋቸው ጽጌ ፷ኛ ዓመት የልደት በዓልን በዓለም አቀፍ ደረጃ በደማቅ ሁኔታ ይከበራል። ስለዚህ በኖርዌይ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ፌብሯሪ 14/2015 ከ16፡00እስከ 22፡00 ስዓት በልደት በዓሉ ላይ ተገኝተታችሁ የአላችሁን አክብሮት ትገልጹ ዘንድ ተጋብዛችኋል።
የዝግጅት ቦታ፡ በቅርብ ቀን እናሳውቃለን
DEMOCRATIC CHANGE ETHIOPIA SUPPORT ORGANIZATION NORWAY

ሰበር ዜና – የመን እየታመሰች ነው፣ የፕሬዝዳንቱ መኖሪያ በአማጽያኑ ተከቧል


(ECADF News) አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከአውሮፓ ወደ ኤርትራ ሲያቀኑ የተሳፈሩበት አውሮፕላን የመን ላይ መንገደኞችን ሊያወርድ እና ሊያሳፍር ላጭር ጊዜ ባረፈበት ወቅት ነበር በየመን ደህንነቶች ተጠልፈው ለወያኔዎች ተላልፈው የተሰጡት።
Smoke rises from a large explosion in the Yemeni capital on Monday
BBC PHOTO: Smoke rises from a large explosion in the Yemeni capital on Monday
በዚህ የተነሳ ኢትዮጵያውያን በየመን መንግስት ላይ ጥርሳቸውን እንደነከሱ ነው ያሉት።
ይሁንና የመን በራሷ የውስጥ ጉዳይ ቅጥ ባጣ ትርምስ ውስጥ የምትገኝ ደሃ የአረብ ሃገር በመሆኗና ኢትዮጵያውያኑ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በየመን መንግስት ላይ ማሳደር የሚችሉት ተጽዕኖ እምብዛም ባለመሆኑ ለጊዜውም ቢሆን አይናቸውን ከየመን ላይ ለማዞር ተገደዋል፣ ጥርሳቸውን ግን እንደነከሱ ነው!
ከትላንት በስትያ ጀምሮ ግን ከየመን ዋና ከተማ ሰንዓ በመውጣት ላይ ያሉ ዜናዎችን የሚከታተሉ ኢትዮጵያውያን ፊታቸው ላይ ፈገግታ ሊነበብ እንደሚችል መገመት ብዙም አያስቸግር። ምናልባት የየመን ወዳጅ ለሆኑት ወያኔዎች ዜናው ሊፈጥር የሚችለው እንደምታ የተለየ ሊሆን ይችላል።
የመን ቀውጢ ሆናለች፣ የየመን ፕሬዚዳንት ዋና አማካሪም በአማጽያኑ ቁጥጥር ስር ውለዋል፣ የሺዓ አማጽያን የፕሬዝዳንቱ አማካሪ በእጃቸው እንደሚገኙ አሳውቀዋል። በሰንዓ በሚገኘው የፕሬዝዳንቱ መኖሪያ ላይ አማጽያኑ ተኩስ ከፍተዋል፣ ማንኛውም አይነት ተሽከርካሪ ከፕሬዝዳንቱ መኖሪያ ብቅ ባለ ቁጥር ከባድ መሳሪያ እየተኮሱ ፕሬዝዳንቱን በገዛ ሃገራቸው እና መኖሪያቸው የቁም እስረኛ አድርገዋቸው ይገኛሉ።
የዜና አውታሮች እንደሚሉት ከሆነ የየመን መንግስት አይደለም መላው የመንን ዋና ከተማዋን ሰንዓን እንኳ አይቆጣጠርም።
የምእራባውያን ፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ ደግሞ የየመን መንግስት መሬት እየከዳው ነው፣ አብቅቶለታል።
ይህ በዚህ እንዳለ የአሜሪካ መንግስት በሰንዓ የሚገኙ የአሜሪካ ኢምባሲ ሰራተኞቹ በተጠንቀቅ እንዲጠብቁና በማንኛውም ሰዓት ሂሊኮፕተሮች በኢምባሲው ቅጥር ግቢ አርፈው ሰራተኞቹን የማውጣት ዘመቻ ሊጀምሩ እንደሚችሉ አሳውቋል። ለዚህም ተግባር ዩኤስኤስ አይዎ ጂማ የምትባለው የአሜሪካ የጦር መርከብ በገልፍ ኦፍ ኤደን ቦታ ይዛ ትጠባበቃለች።

ካድሬዎች በየሜዳው የምርጫ ካርድ በግዳጅ እየሰጡ ነው

election












(ዘ-ሐበሻ) በአዲስ አበባ ከተማ ከ2 ምርጫ በፊት በ0 የተሸነፈው የገዢው ስርዓት ባለፈው ምርጫ 96.6% አሸንፍኩ ማለቱን ተከትሎ ምርጫው መሳቂያ እንደሆነበት ብዙዎች ሲተቹበት የቆየ ጉዳይ ነው:: በባለፈው ዓመት ምርጫ ብዙ ሰው “ብንመርጥም ስለሚጭበረበር ግዜዬን አላጠፋም” በሚል ካርድ ያልወሰደ ሲሆን ዘንድሮ በግድ እንዲወስዱ እየተደረገ ነው::
የዘ-ሐበሻ ዘጋቢዎች ያነጋገሯቸው ምንጮች እንደሚሉት ስርዓቱ ያዘጋጃቸው ካድሬዎች በየቤቱ እየሄዱ የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ እያስገደዱ ሲሆን ከታክሲና አውቶቡስ መውረጃ ቦታዎች ላይ ወንበር እና ጠረጴዛ አስቀምጠው አላፊ አግዳሚውን በግድ የምርጫ ካርድ እንዲውስድ እያስገደዱት ነው::
የምርጫ ካርድ የሚሰጡት የኢህአዴግ ካድሬዎች በመሆናቸው ካርድ ሲሰጡ ኢሕ አዴግን ምረጡ እንደሚሉ የደረሰን መረጃ ያመለክታል::

በአማራ ክልል የደቡብ ወሎ ዞን የደህንነት ቢሮ ሀላፊ አቶ ፍትዊ ግደይ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ተገደሉ፤

newsየአማራ ወጣቶች የጋራ ንቅናቄ (አወጋን) አመራሮች በዛሬው እለት እንደገለጹልኝ ከሆነ የደቡብ ወሎ ዞን የደህንነት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ፍትዊ ግደይ ወረኢሉ ከተማ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ የአቶ ፍትዊ ባለቤት ባሉበት በአወጋን አባላት በጥይት መገደላቸው የታወቀ ሲሆን አቶ ፍትዊ የደቡብ ወሎን ሠው በከፍተኛ ሁኔታ ሲያስሩ ሙስሊሙን «ፅንፈኛ»፣ ክርስቲያኑን «የድሮ ስርዓት ናፋቂ» በማለት በወሎ ክፍለ ሐገር ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የወሎ ሙስሊምና ክርስቲያንን ለመከፋፈል የሞከረ ግለሠብ እንደነበረ የተገለፀ ሲሆን የአቶ ፍትዊን ግድያ ተከትሎ በወረኢሉ ከተማ ፍተሻው በከፍተኛ ሁኔታ መጠናከሩን ለመታዘብ መቻሉን አመራሮቹ ይገልፃሉ።
በመጨረሻም የአቶ ፍትዊ ግደይ ግድያ ለሌሎች የህወሓት አመራሮች እና ጀሌዎች ትምህርት ይሆን ዘንድ የሟቹን ግለሠብ በሞተበት ሠዓት የተነሳውን ፎቶ ከነሙሉ መረጃው በድህረ ገፆች እና በማህበራዊ ሚዲያዎች እንደሚለቀቅ አስታውቀዋል።

ሥርዓቱ የምርጫ ካርድ ያልወሰዱትን ስኳር በመከልከል ማስፈራራት ጀምሯል

ነገረ ኢትዮጵያ) በምስራቅ ጎጃም ዞን አነደድ ወረዳ የቦቀል ቀበሌ ነዋሪዎች የምርጫ ካርድ ስልልወሰዳችሁ ስኳር አይሰጣችሁም መባላቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ በአካባቢው ስኳርን ጨምሮ ሌሎች አቅርቦቶች በስፋት እንደሚጠፉ የተናገሩት ነዋሪዎቹ ዛሬ ጠዋት የቀበሌ ካድሬዎች በድምጽ ማጉያ ‹‹ዛሬ ስኳር ስለመጣ ቀበሌ ድረስ መጥታችሁ እንድትወስዱ፡፡ የመጣው ስኳር ውስን በመሆኑ ሊያልቅ ስለሚችል ዛሬውኑ መጥታችሁ እንድትወስዱ እናሳስባለን፡፡ ከዛሬ ውጭ ላታገኙ ትችላላችሁ፡፡›› እያሉ ሲለፉ እንዳረፈዱ ተናግረዋል፡፡
election




















ሆኖም መጥቷል የተባለው ስኳር ለማግኘት ወደ ቀበሌው ያመሩት ነዋሪዎቹ ስኳሩን ለመውሰድ ሲጠይቁ ‹‹የምርጫ ካርድ ወስዳችኋል?›› የሚል ጥያቄ እንደሚቀርብላቸው ግልጸዋል፡፡ የምርጫ ካርድ የሚያሳዩ ነዋሪዎች ስኳሩ ሲሰጣቸው፤ ያላወጡት በአስቸኳይ ምርጫ ካርድ አውጥተው እንዲመለሱና ስኳር እንዲወስዱ ተነግሯቸዋል ተብሏል፡፡ በአንጻሩ ስኳር ለመውሰድ የምርጫ ካርድ ማውጣት የለብንም ያሉት ነዋሪዎች ስኳር እንደማያገኙ የተነገራቸው ሲሆን ‹‹እንደዜና የምርጫ ካርድ ወሰድንም አልወሰድንም ስኳር የማግኘት መብት አለን›› ያሉ ዜጎች በፖሊስ ተደብድበው እንደተባረሩ ከቦታው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡
በጠዋቱ የቀበሌ ነዋሪዎች ያሰሙት የነበረውን ለፈፋ ሰምቶ ወደ ቀበሌ ያመራ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ መምህር የምርጫ ካርድ ካላመጣ ስኳር እንደማይሰጠው ተነግሮት መመለሱን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡ መምህሩ ‹‹የምርጫ ካድር የመውሰድና ያለመውሰድ መብት አለኝ፡፡ የማምንበት ፓርቲ ሲኖር የምርጫ ካርድ እወስዳለሁ፡፡ ካልሆነ ግን አልወስድም፡፡ ብወስድም ስኳር ለማግኘት ብዬ አይደለም፡፡ እንደማንኛውም ዜጋ ስኳር የማግኘት መብት አለኝ፡፡›› በሚል የቀበሌ ሰራተኞቹን ለማስረዳት ቢሞክርም ‹‹እኛ ስኳር ስጡ የተባልነው ካርድ ለወሰደ ብቻ ነው፡፡ ካርድ ካልወሰድክ አይሰጥህም›› ተብሎ እንደተመለሰ ገልጾልናል፡፡

የሬድዋን የአሜሪካ ቅሌት በስዊድንም ተደገመ

redwon Husseinቀደም ሲል በስዊድን ለቦንድ ሽያጭ ወያኔ ባዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ ቦታ ላይ ኢትዮጵያውያን ተሰባስበው የሽያጩን ዝግጅት በተቃወሙበት ግዜ በስዊድን የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆነችው ወ ወይንሸት ታደሰ ድብደባ ደረሶብኛል በማለት ለፖሊስአመልከታ ክስ ለመመስረት ሙከራ አድርጋ ነበር ሆኖም የስዊድን ፖሊስ ሁኔታውን አጥንቶ ለክስ የተጠራችውን የስዊድን ኢትዮስዊድን ግብር ሃይል ሃላፊና አክቲቪስት ወ መቅደስ ወርቁና አቶ ሞላ የኢትዮጵያ ዴሞክራት መድረክ ምክትል ሊቀመንበር ለፖሊስ የህውአትን ማንነተና አስረድተው የተደረገውም ተቃውሞ በኢትዮጵያ ውስት የሚደረገወን የሰባዊ መብት ጥሰትን በመቃወም በመሆኑና የስዊድን ህግም ይሄንን አይነት ተቃውሞ ማሰማት ህገወጥ ስላልሆነና ወ ወይንሸት ታደሰ ያቀረበችውን ክስ ሚዛን የማይደፋ በመሆኑና መረጃ ለማቅረብ የማይቻል በመሆኑ የስዊድን ፖሊስ ክሱን ውድቅ አድርጎታል፡፡
ወ ወይንሸት ወደ ስብሰባው በመጣች ግዜ እንቁላልና በገማ አሳ ተቃውሞ እንደገጠማትና ከመኪና ለመውጣት አለመቻሏ የሚታወስ ነው።
በዚህ በያዝነው ሳምንት አቶ ሬድዋን ሁሴን የህውሃት ሚኒስቴር በ አሜሪካ ያደረገው ክስ በቂ እንዳልሆነ ተረጋግጦ ክሱ ውድቅ መሆኑ የታወሳል፡፡
የህውሃት ባለስልጣኖች በየሄዱበት ውርደትን ከመከናነብ በቀር እንደ ኢትዮጵያ የራሳቸው ህግ አይነት የአውሮፓም ሆነ የአሜሪካን ህግ ሊረዳቸው አልቻሉም
ትግሉ ይቀጥላል የህውሃትም የዲሞክራሲ ክስረት ይጋለጣል
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር
EthioSweden Taskforce

“ጋዜጠኝነት ወንጀል አይደለም” – በኢትዮጵያ የመገናኛ-ብዙሃን ነጻነት ላይ የሚፈፀም የመብት ጥሰት (የሂውማን ራይትስ ዋች መግለጫ)

Jail
እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 2015 ዓ.ም. ማጠቃለያ
የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) እ.ኤ.አ. በ2010 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ 99.6 በመቶ የፓርላማ መቀመጫን ካሸነፈ ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግስት ሃሳብን የመግለጽ ነጻነትን እና መረጃ የማግኘት መብትን በመገደብ በግል መገናኛ-ብዙሃን ላይ እያሳደረ ያለውን አሉታዊ ተጽዕኖ አባብሶታል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ቢያንስ 60 ጋዜጠኞች ሃገር ለቀው የተሰደዱ ሲሆን ሌሎች 19 ጋዜጠኞች ደግሞ በእስር ላይ እየተሰቃዩ ይገኛሉ፡፡ መንግስት በደርዘኖች የሚቆጠሩ ህትመቶችን ዘግቷል፤ እንዲሁም አብዛኛዎቹን የቴሌቪዥን እና የሬድዮ ስርጭቶች በቁጥጥሩ ስር በማድረግ ኢትዮጵየዊያን የሀገር ውስጥ የፖለቲካ ጉዳዮችን በተመለከተ ነጻ መረጃ እና ትንታኔ የሚያገኙበትን እድል አጣቧል። በግንቦት 2007 በሚካሄደው ምርጫ መገናኛ-ብዙሃኑ ህዝቡን በወሳኝ ጉዳዮች ላይ በማስተማርም ሆነ መረጃ በመስጠት ረገድ ቁልፍ ሚና ሊጫወቱ ይችሉ ነበር፤ እንዲሁም የመከራከሪያ መድረክ በመሆን ሊያገለግሉ ይችሉ ነበር፤ ይሁን እንጂ መንግስት በሃገሪቱ ላለው ብቸኛ የበላይነት የግሉን መገናኛ-ብዙሃን እንደ ስጋት አድርጎ በመውሰድ የግሉን መገናኛ-ብዙሃን፣ ነጻ ጋዜተኝነትን እና ተቺ ትንታኔን ለማጥፋት የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ላይ የሚገኝ ሲሆን ይህም የከፋ ውጤት አስከትሏል።
የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ የሆነው የኮሚቴ ቱ ፕሮቴክት ጆርናሊስትስ (Committee to protect Journalists) መረጃ እና የሂዩማን ራይትስ ዎች ጥናት እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ ከኢራን በመቀጠል በዓለም ላይ በርካታ ቁጥር ያላቸው ጋዜጠኞችን ለስደት የምትዳርግ ሀገር ሆናለች። የመንግስት አካላት አፋኝ ህጎችን መሰረት አድርገው ጋዜጠኞች በየወቅቱ ያሉ ክስተቶችን እና ጉዳዮችን አስመልከተው በሚሰሩት ዘገባ እና ትንታኔ ምክንያት በተደጋጋሚ ክስ ይመሰርቱባቸዋል፤ ፍርድ ቤቶችም ክሱን ተከትለው የጥፋተኝነት ውሳኔ ያስተላልፋሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት እስክንድር ነጋን እና ርዕዮት ዓለሙን የመሰሉ ግለሰቦች በአዲስ አበባ እና በክልሎች የሚገኙ ተለይተው የሚታወቁም ሆነ የማይታወቁ ከደርዘን በላይ የሚሆኑ ጋዜጠኞች እየደረሰባቸው የሚገኘውን ፈተና የሚያሳዩ ምልክቶች ሆነዋል። ጋዜጠኞቹ በርካታ ስጋት ውስጥ የሚገኙ፣ ማስፈራሪያ የሚደርሳቸው፣ አልፎ አልፎም አካላዊ ጥቃት የሚፈጸምባቸው እና ፖለቲካዊ ይዘት ያለው የወንጀል ወይንም የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው ናቸው፡፡ የፍርድ ቤት ክርክራቸው ፍትሃዊ የፍርድ ሂደትን የሚጥሱ አሰራሮች የሚታዩበት ሲሆን ፍርድ ቤቶቹም በያዟቸው ጉዳዮች ላይ የሚሰጧቸው ውሳኔዎች ገለልተኛ እንዳልሆኑ የሚያሳይ ነው።
በኢትዮጵያ የሚገኙት አብዛኛዎቹ የህትመት መገናኛ-ብዙሃን ከመግስት ጋር የቀረበ ትስስር አላቸው፤ በወሳኝ ጉዳዮች ላይ ከመንግሰት የተለየ አቋም እምብዛም አያንጸባርቁም።የግል የህትመት መገናኛ-ብዙሃን በርካታ ከቁጥጥር ጋር የተያያዙ ችግሮች ያጋጥማቸዋል እንዲሁም በደህንነት ሰራተኞች ተከታታይ ወከባ ይደርስባቸዋል፡፡ መንግስትን የሚተቹ የህትመት ውጤቶች በየጊዜው ይዘጋሉ፣ የበሰለ ትችት የሚያቀርቡ የህትመት ውጤቶችን የሚያትሙ እና የሚያከፋፍሉ አሳታሚዎች እና አከፋፋዮችም ተዘግተዋል፡፡ የመንግስት ፖሊሲዎች ላይ ትችት የሚሰነዝሩ ጋዜጠኞች እና የቤተሰብ አባሎቻቸው ጭምር የጥቃት፣ የመታሰር እና የገቢ ምንጫቸውን የማጣት ዘላቂ ስጋት ላይ ይወድቃሉ፡፡ መንግስት አብዛኛውን የመገናኛ-ብዙሃን ተቆጣጥሮ የሚገኝ ሲሆን የቀሩት ጥቂት የግል መገናኛ-ብዙሃንም በተለይ ለአሳሳቢ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ በሚሰጡት ሽፋን ራሳቸው ላይ ቅድመ ምርመራ የሚያደርጉ ያደርጋሉ ይህም እንዘጋለን ከሚል ፍርሃት የመነጨ ነው፡፡
ይህ ሪፖርት የኢትዮጵያ መንግስት ነጻ ጋዜጠኝነትን እና ትንታኔን ለመቆጣጠር እንዲሁም መረጃ የማግኛ መንገድን ለመገደብ የተጠቀማቸውን ዘዴዎች የሚዘግብ ነው፡፡ ሪፖርቱ ከ70 የሚበልጡ የአሁን እና የቀድሞ ጋዜጠኞችን እና የመገናኛ-ብዙሃን ባለሙያዎችን ቃለ-መጠይቅ በማድረግ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን የሚገኝበትን አስከፊ ሁኔታ እና በዚህም ምክንያት ሃሳብን በመግለጽ ነጻነት እና መገናኛ-ብዙሃን ላይ የደረሰውን አሉታዊ ተጽዕኖ ይዘረዝራል፡፡
በስፋት በተዘገቡ ጉዳዮች ላይ ከዓለምዓቀፍ ማህበረሰብ የተሰነዘሩ ውግዘቶች ቢኖሩም የኢትዮጵያ መንግስት ለገለልተኛ የመገናኛ-ብዙሃን ድምጽ ምንም አይነት የመለሳለስ ምልክት አላሳየም፤ እ.ኤ.አ. በ2014 ዓ.ም የግል መገናኛ ብዙሃን ላይ የሚደርሰው አሉታዊ ተጽዕኖ በእጅጉ ተባብሷል፡፡ አስር ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን ክስ የተመሰረተባቸው ጋዜጠኞችን ዝርዝር ተቀላቅለዋል እንዲሁም አምስት መጽሄቶች እና አንድ ጋዜጣ በመንግስት የዛቻ እና የማስፈራሪያ ዘመቻ ከተካሄደባቸው በኋላ እንዲዘጉ ተደርጓል፡፡ ዘመቻው በመንግስት በሚተዳደረው የቴሌቪዥን ጣቢያ የህትመት ውጤቶቹ ሽብርን እንደሚደግፉ አስመስሎ ማቅረብ፣ የህትመት ውጤቶቹን የሚያትሙ ማተሚያ ቤቶችን ማዋከብ፣ በህትመት ውጤቶቹ የማከፋፈል ስራ ላይ የመንግስት ጣልቃ ገብነት፤ እንዲሁም ከደህንነት ባለስልጣናት በርካታ ዛቻዎችን መሰንዘርን ያካትታል፡፡ ይህም በመጨረሻ በደርዘን የሚቆጠሩ ጋዜጠኞች እና በርካታ የህትመት ውጤቶች ባለቤቶች ሃገር ለቀው እንዲሰደዱ እና ባለቤቶቹ የወንጀል ክስ እንዲመሰረትባቸው በማድረግ ተከናወኗል። ፍርድ ቤቶች ሌላ ምንም አይነት ተጨባጭ ማስረጃ ሳይቀርብ መንግስትን የሚተቹ ጽሁፎችን ብቻ መሰረት በማድረግ በሶስት የህትመት ባለቤቶች ላይ በሌሉበት እያንዳንዳቸው ከሶስት አመት የሚበልጥ እስር እንዲቀጡ ወስነውባቸዋል፡፡ የሌሎች የህትመት ባለቤቶች ክስም በሂደት ላይ ነው፡ ፡
መንግስት ከሚፈፅማቸው ትኩረትን የሚስቡ እስሮች በተጨማሪ መገናኛ-ብዙሃንን ለማዳከም እና ለመዝጋት ሌሎች በርካታ በግልጽ የማይታዩ የእጅ አዙር መንገዶችን ይጠቀማል፡፡ የደህንነት ሰራተኞች በአሳሳቢ የፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ የሚጽፉ ጋዜጠኞች ላይ ተከታታይ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ያደርሱባቸዋል፡፡ እነዚህ ዛቻዎች ብዙውን ጊዜ ከጋዜጠኞቹም አልፎ ወደ ቤተሰባቸው እና ጓደኞቻቸው ድረስ ይዘልቃሉ፡፡ የሚደርስባቸውን ማስፈራሪያ ተቀብለው በሚሰሩት ዘገባ ላይ ቅድመ-ምርመራ የማያካሂዱት በአብዛኛው ክስም ሳይመሰረትባቸው በዘፈቀደ ይታሰራሉ እንዲሁም ተጨማሪ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ይደርሳቸዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ውጭ በሚገኙ አካባቢዎች በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰው ያልተገባ አያያዝ እና ድብደባ የተለመደ ሆኗል፤ በአብዛኛው ጊዜም የወነጀል ክስ ተከትሎ ይመጣል። ብዙዎቹ ለረዥም ጊዜ ያገለገሉ የግል ጋዜጠኞች በርካታ ጊዜያት እስር ተፈጽሞባቸዋል፤ እንዲሁም ከደህንነት ባለስልጣናት፣ ከገዢው ፓርቲ ካድሬዎች፣ እና ከቀድሞው የኢትዮጵያ ማስታወቂያ ሚኒስቴር አሁን ደግሞ የመንግስት ኮምዩኒኬይሽን ጉዳዮች ቢሮ ከተባለው መስሪያቤት ባለስልጣናት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዛቻዎችን ተቀብለዋል፡፡
ይህም በመጨረሻ ላይ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች በራሳቸው ላይ ቅድመ-ምርመራ በማድረግ የገዥውን ፓርቲ አጀንዳ ከማራገብ ወይንም ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ዘገባ እና እና ትንታኔ ማቅረብ ከመቀጠል አንዱን የመምረጥ ከባድ ፈተና ውስጥ እንዲወድቁ ያደርጋል።
በግለሰብ ጋዜጠኞች ላይ ከሚደርሰው ጥቃት በተጨማሪ የግል መገናኛ-ብዙሃን ባለቤቶች የህትመት ውጤቶቻቸውን የሚያሳትሙባቸውን ማተሚያ ቤቶች ለማዳከም ባለስልጣናቱ የተለያዩ መንገዶችን ይጠቀማሉ፡፡ በመግስት ስር የሚተዳደረው እና በመደበኛነት ጋዜጦችን የማተም አቅም ያለው ብቸኛ ማተሚያ ቤት የግል ህትመት ውጤቶችን ስራ ያዘገያል ወይንም አይቀበልም፣ በአንድ አጋጣሚ መንግስት በጣም አሳሳቢ ነው ባለው ጉዳይ ላይ ዘገባ ያሳተመን ጋዜጣ 40,000 ኮፒ ህትመት አቃጥሏል፡፡ የደህንነት ሰዎች የግል ህትመት ውጤቶች አከፋፋዮች ላይም የሚያደርጉትን ክትትል እና የሚያደርሱትን ጥቃት ጨምረዋል፡፡ የጋዜጠኞች የመረጃ ምንጮች በተደጋጋሚ ለጥቃት እየተጋለጡ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ለመነጋገር ፍርሃት የሚያድርባቸው ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ ነው።
መንግስት የግል ጋዜጠኞች ማህበር ለማደራጀት የሚደረግን ሙከራ ያግዳል እንዲሁም የግል የህትመት ውጤቶች ያላቸውን ፖለቲካዊ ትስስር በተመለከተ የደህንነት ባለስልጣናት ሰፊ የኋላ ታሪክ ጥናት ያካሂዳሉ፡፡ የመንግስት ወይም የገዥው ፓርቲ ሙሉ ደጋፊ ያልሆኑ የግል ህትመቶች ለሚያቀርቡት የህትመት ፈቃድ አሊያም እድሳት ጥያቄ ባለስልጣናት ምላሽ ለመስጠት ይዘገያሉ፡፡
የድረ-ገጽ መገናኛ ብዙሃንም በተሻለ መልኩ የተያዙ አይደሉም፡፡ በውጭ ሃገራት በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የሚመሩ በርካታ ጦማሮች እና ድረ-ገጾች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታዩ ተደርገዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2014 ዓ.ም ዞን ዘጠኝ በመባል የሚታወቁት በሃገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ትንታኔ የሚያቀርቡ የጦማሪያን ስብስብ 80 ቀናት ክስ ሳይመሰረትባቸው በእስር ከቆዩ በኋላ በጸረ-ሽብር አዋጁ እና የወንጀል ህጉ መሰረት ተከሰዋል፡፡ በቀረበው ክስ መሰረት በክስ ዝርዝር ሰነዱ ከተጠቀሰባቸው ማስረጃ መካከል አንዱ ቴክኒካል ቴክኖሎጂ ኮሌክቲቭ በተባለው በኢንተርኔት ላይ የሚገኝ የግላዊ መረጃዎችን ሚስጥራዊነት ለመጠበቅ የሚረዱ ተግባራትን እና መሳሪያዎችን በሚያቀርበው ዓለም ዓቀፍ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የዲጂታል ደህንነት ጥበቃ ስልጠና ወስደዋል የሚል ነው፡ ፡ የዞን ዘጠኝ አባላት መታሰር እና መከሰስ በሃገሪቱ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ላይ የፍርሃት ድባብ ፈጥሮአል። ይህም ጦማሪዎች እና የኢንተርኔት ላይ ተሟጋቾች በፌስቡክና በመሳሰሉ እና ሌሎች ማህበራዊ ድረ-ገጾች በሚለጥፏቸው ትችቶች ምክንያት ችግር ውስጥ ልንገባ እንችላለን የሚለውን ስጋታቸውን በእጅጉ ከፍ አድርጎታል፡ ፡
በሬድዮ እና ቴሌቪዥን ስርጭት ላይ ያለውም ሁኔታ ተመሳሳይ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ የሃገሪቱ ሬድዮ እና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች በመንግስት ስር የሚገኙ ሲሆን ገለልተኛ የዜና ዘገባ እና ትንታኔ አይቀርብባቸውም፡፡ ከ80 በመቶ የሚበልጠው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚኖረው በገጠራማ አካባቢዎች በመሆኑ እና ሬድዮ እስከአሁን ዋናው የዜና እና መረጃ ማግኛ ምንጭ ከመሆኑ አንጻር ይህ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ዘገባ የሚያቀርቡ ጥቂት የግል ሬድዮ ጣቢያዎች ዝግጅቶቻቸውን አየር ላይ ከማስተላለፋቸው ከቀናት በፊት የመንግስት ባለስልጣናት እንደሚገመግሙት እና እንደሚያጸድቁት ለሂውማን ራይትስ ወች ተናግረዋል፡፡ ተቀባይነት ካገኘው ይዘት የሚያፈነግጡ አሰራጮች በመንግስት ባለስልጣናተ የሚፈጸም እስር እና ወከባ ጋር መጋፈጥ ሊኖርባቸው ይችላል።
በርካታ ጋዜጠኞች ከማያቋርጥ የማዋከብ እና የፍርሃት ሕይወት ለመገላገል ሲሉ ከመንግስት ጋር ትስስር ባለው መገናኛ-ብዙሃን ተቀጥረው መስራት ይመርጣሉ፡፡ አንዳንዶች የመንግስት ባለስልጣናትን እስከማያስቆጣ ድረስ ባለው መለያ መስመር ላይ ሆነው ትችቶችን የሚያቀርቡ ሲሆን ሌሎች ደግሞ የመንግስትን የልማት ውጤቶች በማስተዋወቅ እና በማጋነን የመንግስት ፕሮፖጋንዳ አራጋቢዎች ሆነው ይሰራሉ፡፡ በእነዚህ መገናኛ ብዙሃን የኢህአዴግ አባልነት እድገት ለማግኘት የሚጠየቅ መስፈርት ነው፡፡
በኢጥዮጵያ የሚገኙት የውጭ መገናኛ ብዙሃን ውሱን ናቸው። የአሜሪካ ድምጽ ቮይስ ኦፍ አሜሪካ (ቪኦኤ) እና የጀርመን ድምጽ ዶቼቬሌ የቴሊቪዥን እና የሬድዮ ሽፋን በመስጠት በርካታ የዲያስፖራ ጣቢያዎችን ተቀላቅለዋል፡፡ ሆኖም የአየር ሞገዳቸውን በማገድ፣ በሰራተኞቻቸው እና የመረጃ ምንጮቻቸው ላይ ዛቻ እና ጥቃት በማድረስ እንዲሁም በቅርቡ ደግሞ የዲያስፖራ መሰረት ያላቸውን ስርጭቶች የሚመለከቱ እና የሚያዳምጡ ግለሶቦችን በማጥቃት እና በማሰር ጭምር መንግስት የሃገር ውስጥ ተከታታዮቻቸውን ለመገደብ የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማል፡፡
እ.ኤ.አ. ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማሕበራት ላይ በደረሰው ጫና ምክንያት በርካታ የሲቪል ማሕበራት ስራ ለማቆም የተገደዱ ሲሆን ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ ጥብቅ ገደብ ተጥሎባቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ንቁ እና ነጻ የመገናኛ-ብዙሃን ዘርፍ በመንግስት አስተዳደር ላይ ተሳትፎን ለማበርከት እና የሰብዓዊ መብቶች በተሻለ ሁኔታ እንዲከበሩ ለማገዝ ያለውን አስፈላጊነት የበለጠ ያጎላዋል። አለመታደል ሆኖ በፖለቲካ ሁነቶች ላይ ገለልተኛ ሽፋን እና የዜና ትንታኔ ለመስጠት ያለውም ጥቂት ክፍተት እ.ኤ.አ. በ2014 ዓ.ም. የበለጠ ተጣቧል፡፡ ከግንቦት 2007 ምርጫ መቃረብ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያዊያን የተለያዩ የፖለቲዊ አተያዮች እና ትንታኔዎችን የሚያገኙበት እድል እየተመናመነ ነው።
በኢትዮጵያ የሚገኙ መገናኛ-ብዙሃን ሁኔታን ለማሻሻል በአጭር እና በረጅም ጊዜ አሁንም ብዙ ሊደረግ ይችላል፡፡ እንደ መጀመሪያ እርምጃ መንግስት ክሶችን በአስቸኳይ በማንሳት የታሰሩ እና የተፈረደባቸው ጋዜጠኞች እና ጦማሪያንን ክስር ሊለቅ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ መሪዎች ንቁ እና ገለልተኛ የመገናኛ ብዙሃን መኖር ለሃገሪቱ እድገት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ሊገነዘቡት ይገባል፡፡ እንዲሁም በመጪዎቹ ሳምንታት እና ወራት መንግስት የጸረ- ሽብር ህጉን ጨምሮ ሌሎች መገናኛ ብዙሃኑ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ የሚያሳድሩ አፋኝ ህጎችን ማረም አለበት፡፡ የሚወጡ ህጎች እና የሚፈጸሙ ተግባራት የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት እና ዓለምዓቀፍ መለኪያዎች ጋር በሚጣጠም መልኩ መሆኑን ባለስልጣናት ማረጋገጥ አለባቸው፡፡
ለኢትዮጵያ መንግስት
ምክረ ሃሳቦች

• ሁሉንም ክሶች በአስቸኳይ ማንሳት እንዲሁም በወንጀል መቅጫ ህጉ እና በጸረ-ሽብር አዋጁ መሰረት ተከሰው በዘፈቀደ የታሰሩ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን በሙሉ መፍታት።
• የጸረ-ሽብር አዋጁ እና የመገናኛ-ብዙሃን እና የመረጃ ነጻነት አዋጁ መሰረዝ አሊያም በኢትዮጵያ ህገ- መንግስት እንዲሁም በክልላዊ እና ዓለምዓቀፋዊ የሰብዓዊ መብት ህጎች ላይ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት መብት ከተቀመጡ መስፈርቶች ጋር በሚጣጣም መልኩ ከፍተኛ መሻሻያ ማደረግ፡፡
• የስም ማጥፋትን የወንጀል ቅጣት እንዲያስከትል ተደርጎ በወንጀል መቅጫ ህጉ አንቀጽ 613 ላይ የተደነገገውን ማሻሻል።
• በህትመት እና ብሮድካስት መገናኛ ብዙሃን ላይ መንግስት ያለውን የባለቤትነት ድርሻ መገደብ ፤ እንዲሁም የግል መገናኛ-ብዙሃን ባለቤትነትን የሚገድቡ ጉዳዮችን ለማስቀረት እና ገለልተኛ እና ንቁ መገናኛ-ብዙሃንን ለማበረታታት የሚያስችሉ የህግ እና የፖሊሲ ማስተካከያ እርምጃዎችን መውሰድ።
• አዳዲስ የህትመት እና የሬድዮ ስርጭቶች ቁጥጥርና ፈቃድ አሰራር ቀልጣፋ ማድረግ እና ከፖለቲካዊ ይዘት ነጻ ማድረግ። ቁጥጥር አድራጊ ባለስልጣን አካላት ገለልተኛ መሆን አለባቸው፤ እንዲሁም አስተዳደራዊ እና ተግባራዊ እንቅስቃሴያቸው ከመንግስት የደህንነት አካላት አና ከመንግስት ኮምዩኒኬይሽን ጉዳች ቢሮ መለየት አለበት፡፡
• የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ገለልተኛነትን ለማረጋገጥ ማሻሻያዎች ማድረግ።
• የሃገር ውስጥ እና የውጭ ጋዜጠኞች በመላው ሃገሪቱ በነፃነት የመንቀሳቀስ መብታቸውን የሚገድቡ አሰራሮችን ማስወገድ፣ ይህም ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመባቸው ይገኛሉ በሚባሉ አካባቢዎች በነጸነት መንቀሳቀስን እንዲጨምር፣ ፖሊስ እና የደህንነት ሰዎች መገናኛ-ብዙሃን በነጻነት ይንቀሳቀሱ ዘንድ ፈቃድ እንዲሰጡ መመሪያ መስጠት፤ በዛቻ፣ በማስፈራራት እና በማሰር የጋዜጠኞችን እንቅስቃሴ የገደበ ማንኛውም ፖሊስ በያዘው የማዕረግ እርከን ልዩነት ሳይደረግ መቅጣት።
• የፖለቲካ ፓርቲ ፣ የመገናኛ ብዙሃን እና የጦማሪያን ድረ-ገጾችን ማፈን እና ቅድመ ምርመራ ማድረግን ማቆም እንዲሁም ለወደፊት እንደዚህ አይነት ድረ-ገፆችን ላለማፈን በይፋ ቃል መግባት።
• የሬድዮ እና የቴሌቪዥን አየር ሞገዶችን ማፈን ማቆም ፤ ለወደፊቱም የሬድዮ እና ቴሌቪዥን አየር ሞገዶችን ላለማፈን በይፋ ቃል መግባት።
• አስተያየት የመስጠት እና ሃሳብን የመግለጽ ነፃነት መብቶችን ለማዳበር እና ለመጠበቅ የሚንቀሳቀሰው የተባበሩት መንግስታት ልዩ ራፖርተር ኢትዮጵያን እንዲጎበኝ እና የግል የህትመት እና የብሮድካስት መገናኛ-ብዙሃን ያሉበትን ሁኔታ እንዲገመግም እንዲሁም በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞችን ሁኔታ እንዲያጠና ግብዣ ማቅረብ።
የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት እና ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ ለዓለምዓቀፍ የኢትዮጵያ ለጋሾች
• በዘፈቀደ የታሰሩ እና በወንጀል ህጉ እና በጸረ-ሽብር አዋጁ መሰረት የተከሰሱ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን በሙሉ እንዲፈቱ በይፋ ጥሪ ማቅረብ አና በተናጥል ጫና ማሳደር።
• የጋዜጠኞች የፍርድ ቤት ክርክር ሂደት ዓለምዓቀፍ የፍርድ ሂደት መስፈርቶችን ያሟላ መሆኑን ለማረጋገጥ የፍርድ ሂደት ክትትሉን ማሻሻል እና መጨመር።
• የታሰሩ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን የሚገኙበትን ሁኔታ ለመገምገም እስር ቤቶችን እና ማቆያ ጣቢያዎችን ለመጎብኘት ጥያቄ ማቅረብ።
• ሃሳብን የመግለጽ ነፃነትን የተመለከቱ አሳሳቢ ጉዳዮች እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ልማትን እና ደህንነትን እንደሚጎዱ ያላቸውን ስጋት ለመንግስት ባለስልጣናት በይፋ እና በግል መግለፅ።
• ገለልተኛ የጋዜጠኝነት ማህበር የሚፈጠርበትን መንገድ ጨምሮ የኢትዮጵያ መገናኛ-ብዙሃን የሙያ ብቃት እንዲዳብር ድጋፍ ማበርከት፤ ከአዲስ አበባ ውጭ ለሚገኙ ለግል መገናኛ-ብዙሃን ጋዜጠኞች የተለዩ እድሎች መኖራቸውን ማረጋገጥ እና የመገናኛ-ብዙሃን አቅምን ለማሳደግ ያለሙ እንቅስቃሴዎች እንዲካተቱ ልዩ ጥረት ማድረግ።
• ነጻ ጋዜጦች እና ሌላ አይነት ህትመቶች መንግስታዊ ያልሆኑ ወይም በመንግስት ቁጥጥር ስር ያልገቡ ማተሚያ መሳሪያዎችን የሚያገኙበትን መንገድ ለማመቻቸት ድጋፍ ማድረግ።
በመንግስት ለተያዙ እና ከመንግስት ጋር ትስስር ላላቸው ማተሚያ ቤቶች
• ከመንግስት ጋር የተለየ ትስስር ያላቸው ህትመቶች ከሚታተሙበት የጊዜ ሰሌዳ በሚጣጠም መልኩ ሁሉንም ፈቃድ ያላቸው የግል መገናኛ ብዙሃን ህትመቶችን በተገቢው የጊዜ ገደብ እና አግባብ ባለው ሁኔታ በገለልተኝነት ማተም።
በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ የውጭ ሬድዮ እና ቴሌቪዥን አስተላላፊዎች
• የተለየ አደጋ ያለባቸውን የመረጃ ምንጮች ለመለየት የሚጠቀሙበትን አሰራር ማጠናከር እና አደጋውን ለመቀነስ የሚወስዱትን እርምጃ ማዳበር፤ ይህም የግለሰቡ ማንነት እንዳይታወቅ ማድረግ፣ ማንነታቸውን በተመለከተ ያላቸውን መረጃ ሚስጥራዊ አድርጎ ማስቀመጥ እና ከፍተኛ ታዋቂነት ላላቸው ግለሰቦች ያለውን አደጋ እንዲገነዘቡት ማድረግን ይጨምራል፡፡
ለኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ዩጋንዳ መንግስታት
• ጋዜጠኞች እና ሌሎች የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን ጨምሮ ጥገኝነት ጠያቂዎች ለጥገኝነት ማመልከቻቸው በአፋጣኝ ምላሽ መስጠት እና ሊደርስባቸው ከሚችለው ጥቃት ከለላ እንደተሰጣቸው ማረጋገጥ።

በሐመር አርብቶ አደሮች እና የፖሊስ ግጭት የሞቱና የቆሰሉ ወገኖቻችን ዝርዝር – ኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ኅብረት /ኦህዲኅ/ ባለ 4 ነጥብ መግለጫ አወጣ

news
ከኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ኅብረት /ኦህዲኅ/
በጥር 7/2007 ሐሙስ ዕለት በሐመር ወረዳ በ‹‹ላላ›› ቀበሌ በሐመር ብሔረሰብ አርብቶ አደሮችና ፖሊስ መካከል በተፈጠረ ግጭት የደረሰዉ ጉዳት የሚከተለዉን ይመስላል፤
ሀ/ የሞቱ–
1. ሻምበል ለማ አሸናፊ
2/ ወ/ር ሙሴ ማቱሳላ
3/ ወ/ር ደፋሩ ጦና
4/ ወ/ር ካሬ
5/ ወ/ር በኃይሉ
6/ ስሙ ለግዜዉ ያልታወቀ የልዩ ኃይል ባልደረባ
7/ ስሙዋ ለግዜዉ ያልታወቀ ሴት ባለሙያ
8/መምህር መሳይ ነሽ መርነህ
ለ/ የቆሰሉ
1/ አቶ ቹሜሬ የረር /የደቡብ ኦሞ ዞን ፍትህ ጸጥታና ደንብ ማስከበር ምክትል ሀላፊ
2/ ምክትል ሣጅን ጌታሁን ቶላ
3/ ወ/ር ተሰማ መሰረት
4/ ወ/ር ጌታቸዉ ጻንቃ
5/ ወ/ር ቱላ ኪያ
6/ ባሻ ወንድማገኝ ጨነቀ
7/ ወ/ር ሚልኪያስ ግራኝ
8/ ወ/ር ዘለቀ (አባታቸዉ ያልታወቀ)
9/ አቶ ደምሳሽ ሞላ (የዞኑ ሴቶችና ሕጻናት መምርያ ሾፌር)
የሐመር ወረዳ ፍትህ ጸጥታና ደንብ ማስከበር ሃላፊ ኮማንደር ቡራ ካሎ የኦፕሬሽኑ አዛዥ ሲሆኑ ትእዛዝ የሚሰጡት ዲመካ ሁነዉ መሆኑንም ከስፍራዉ ከነበሩ መረዳት ተችሏል፡፡ በአርብቶአደሩ በኩል ስለደረሰው ጉዳት መረጃ ለማግኘት አልተቻለም፡፡
ከዞኑ መስተዳድር የውስጥ ምንጮች በደረሰን መረጃ መሰረት በነገው ዕለት የዞኑ ሲቪል ሠራተኞች ከስከሬን አንሺ የቀን ሠራተኞች ይዘው ወደ ቦታው በመሄድ አሰከሬኖችን ለማምጣት እንደሚንቀሳቀሱና በዚህ ጉዞም ወታደራዊ ኃይል እንዳይኖር/እንዳያጅባቸው መወሰኑን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በአሁኑ ሰዓት በሃመር ወረዳ ዋና ከተማ ዲመካ ምንም የፖሊስ ኃይል ለመኖሩና አንዳንድ የወረዳውና ከዞኑ የተንቀሳቀሱ ፖሊሶች የፖሊስ ልብሳቸውን በመቀየር/ከአካባቢው ሲቪል ሠራተኞች በመውሰድ/ በእግር ጫካ ለጫካ በመጓዝ ከዞኑ ከተማ ጂንካ መድረሳቸውንና የከተማው ነዋሪም ‹‹እንኳን ለቤታችሁ አበቃችሁ›› እያለ እየጠየቃቸው እንደሆነና እነርሱም ‹‹ በማናውቀው አስገብተውን ሊያስቸርሱን ነበር፣ የተፈጠረው ሁኔታና በወንድሞቻችን ላይ የደረሰው በእጅጉ አሳዛኝ ነው›› በሚል ቁጭታቸውን ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ የከተማው ነዋሪዎችና ከቦታው ተመላሾች ኢሣት መረጃውን ለኢትዮጵያዊያን በማድረሱ ባለውለታችን ነው በማለት ሲያመሰግኑ ተደምጠዋል፡፡
የግጭቱ ምክንያቶች ብዙ ቢሆኑም የሚከተሉት በስፋት በአርብቶ-አደሩ የሚነሱ ናቸዉ፤
ወቅታዊው/ኢሚዲየት/ መነሻው የወረዳው ፖሊስ በለመደው መንገድ የአካባቢውን ባህላዊ አባቶች በ‹‹ንቀት›› አልፎ የሀመር ወጣቶች ላይ ኃይሉን ለማሳየት ያደረገው ሙከራ ቢሆንም–
1/ በአካባቢዉ ስም ከመነገዱ ውጪ ያየነዉ ለዉጥ ባለመኖሩ ሐመር ከ23 አመት በፊት በነበርንበት መገኘታችን፤
2/ እኛን ባላማከሩበት የግጦሽና ውኃ ማጠጫ ቦታችንን ከፓርኩ ክልል አስገብተው ባለበት አርብቶ አደርነታችን እየታወቀ ለከብቶቻችን ዘመናዊ የግጦሽ ስፍራ ሳይዘጋጅልን በበጋ ወደ ፓርክ ለግጦሽና ለዉሃ እንዳናስገባ መደረጉ ሀብቶቻችንን እንድናጣ መገደዳችን፤
3/ የወረዳዉ ፖሊስ አዛዥ መቶ አለቃ ጋዲ በርቂ በመኪና ገጭተዉ በገደሉት ሀመር በህግ አለመጠየቃቸዉ፤በተመሳሳይ ወ/ር ዋዶ የተባሉ ሀመሩን ደረቱ ላይ ረግጠዉ ሲገሉ በህግ አለመጠየቃቸዉ፣በተቃራኒው ደግሞ በቂ ዕውቀትና መረጃ የሌለዉ የሀመር እረኛ ጎሽ ገደለ ተብሎ ወህኒ መወርወሩ፤ የኛ ሰውነት ከእንሰሳ/ጎሽ ያነሰ ተደርጎ በራሳችን ልጆች ጭምር መታየቱ፤…. የሚሉት በህዝቡ ውስጥ ይብላሉ የነበሩና በተደጋጋሚ ተነስተው ምላሽ የተነፈጉ ጉዳዮች ናቸው፡፡
በተፈጠረው ሁኔታ በወረዳው ብቻም ሳይሆን በዞኑ ውጥረትና ያለመረጋጋት ነግሷል፣የተፈጠረው ችግር መቼና እንዴት መፍትሄ እንደሚያገኝ አይታወቅም፣የማኅበራዊ አገልግሎት ተቋማት አገልግሎት አቋርጠዋል፡፡ አስቸኳይ አሳታፊ መፍትሄ ካለገኘም የመስፋትና መዛመት ዕድሉ ሰፊ እንደሆነ የአካባቢው ነዋሪዎች ሥጋታቸውን እየገለጹ ነው፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ ድርጅታችን የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ኅብረት /ኦህዲኅ/ ባለፉት 23 ዓመታት በዞኑ ያለውን ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎችንና ምስቅልቅል በአጠቃላይ፣ በተለይም በየጊዜው በዞኑ ነዋሪዎች የሚነሱ ጥያቄዎችንና እነዚህ ከላይ የተጠቀሱትን የመሳሰሉ የአርብቶአደሩን ጥያቄዎችና በዞኑ ያለጥናት የሚደረጉ ሰፈራዎችን እንዲሁም ከስኳር ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ የሚደረጉ የህዝብ ማፈናቀሎችንና ይህንኑ ተከትሎ የሚነሱ ጥያቄዎችን መንግሥት በአግባቡና የአካባቢውን ባህላዊና አካባቢያዊ ግጭት አፈታት ዘዴዎችን ባገናዘበ መንገድ መልስና መፍትሄ እንዲሰጠቸው፣በመሣሪያ ኃይል ጥያቄዎችን ለማፈን የሚደረገው ሙከራ ዘላቂ መፍትሄ ካለማስገኘቱም ግጭት ሊያስከትል እንደሚችል በተደጋጋሚ ለዞኑ መንግሥት ባለሥልጣናት ስንገልጽ ለችግሮቹ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ ጥያቄዎቹን በማንሳታችን ሊያስፈራሩና ሊወነጅሉ ሲሞክሩ ተመልክተናል፡፡ የዚህ አካሄድና አስተሳሰብ የመጨረሻ ውጤቱ ይህ ሆኗል፡፡ ስለዚህ ድርጅታችን መንግሥት–
1. በግጭቱ ስለደረሰው ጉዳት መጠንና ዓይነት/ የሰው ህይወት፣አካል ጉዳት…/፣የንብረት ውድመት፣…. ላይ በቂ መረጃ እንዲሠጥና የድርጊቱ አዛዞች፣ፈጻሚዎች….ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ፤
2. በግጭቱ ለተጎዱ ወገኖችና ለደረሰው የንብረት ውድመት ካሳ እንዲከፍል፤
3. ግጭቱ ከመጪው ምርጫ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ስለሆነ አፋጣኝ አሳታፊ መፍትሄው እንዲፈልግለት፤የፖሊስ ተግባራትና ማኅበራዊ አገልግሎቶች ወደቦታቸው/ተግባራቸው እንዲመለሱ እንዲያደርግ፣
4. ለችግሩ ሥረ-መንስኤዎች ሕብረተሰቡን ያሳተፈና በማኅበረሰቡ ተቀባይነት ያለው አካባቢያዊ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያበጅና ችግሩ እንዳይባባስና እንዳይስፋፋ አስቸኳይ የማረጋጋት እርምጃ እንዲወስድ፤
የማንአለብኝነት ኃይል እርምጃ መቼውንም መፍትሄ አይሆንምና ለቀጣይም መንግሥት ከዚህ ዓይነቱ አካሄድ እንዲታቀብ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን:

Wednesday, January 14, 2015

ወያኔ ኢትዮጵያን አፍርሶ ወደ ጉሬው ለመግባት

ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት     ቅዳሜ ጥር ፪ ቀን ፪ሺህ፯  ዓ.ም.                         ቅፅ ፫ ፣ ቁጥር ፰
የመጨረሻ መሠናዶውን እያደረገ ነው
· የትግሬ-ወያኔዎች ከተለያዩ ጎሣዎች እና ነገዶች ሰዎችን መልምለው እና አደራጅተው፣ እንዲሁም የወታደራዊ፣ የደህንነት፣ የአደረጃጀት፣ የአመራር እና የቁጥጥር ሥራ የሚሠሩ የትግሬ-ወያኔዎች መድበው በከፍተኛ ሚሥጢር ኢትዮጵያን የማፈራረስ ሤራ እየተዶለቱ መሆኑን በተጨባጭ መረጃዎች አረጋግጠናል።
ethiopia-map
የትግሬ-ወያኔ የመጨረሻ ግብ ኢትዮጵያን በመበታተን፣ የትግራይ ረፑብሊክ መመሥረት መሆኑን በ1968 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ፕሮግራሙ መሠረት ላለፉት ፵(አርባ) ዓመታት ያደረገው ጉዞ ያሣያል። በጉዞው የኢትዮጵያን የረጅም ዘመን ታሪክ ክዶ በመቶ ዓመት መገደቡን፣ የትግሬ-ወያኔ መሪዎች እና አባሎች በተደጋጋሚ በጻፉዋቸው መጻሕፍት እና በየአጋጣሚው ባደረጉዋቸው ንግግሮች ለሕዝብ ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል። «ኤርትራ በኢትዮጵያ በቅኝ ግዛትነት የተያዘች ናት፤ ስለሆነም ሻዕቢያ የሚያካሂደው የመገንጠል እና የነፃነት ጥያቄ ተገቢ እና ትክክል ነው።» ብለው፣ ከሻዕቢያ በላይ ሻቢያ ሆነው፣ የትግራይን ልጆች የጦር ማገዶ በማድረግ ኤርትራን ማስገንጠላቸው ማንም ሊያስተባብለው የማይችለው ሃቅ ነው። ኢትዮጵያውያንን እንደ አንድ ሕዝብ ያስተሳሰሩ የወል ዕሴቶችን፥ «የኢትዮጵያዊነት አገራዊ እና ብሔራዊ ስሜት የሁሉም በኢትዮጵያ የሚኖሩ ነገዶች እና ጎሣዎች ሳይሆኑ፣ የዐማራው ብቻ የማንነት መገለጫዎች ናቸው፤ ዐማራው ጨቋኝ እና በዝባዥ ነገድ ነው፤ እርሱን ሁሉም ነገዶች እና ጎሣዎች በወያኔ መሪነት ተባብረው ማጥፋት አለባቸው።» በማለት በከፈቱት የዘር ማጥፋት እና የዘር ማጽዳት ጦርነት፣ የኢትዮጵያዊነት የወል ዕሴቶችን፣ ተቋሞችን፣ ግንኙነቶችን፣ አሠራሮችን ወዘተርፈ በማጥፋታቸው ዛሬ አገሪቱ እና ሕዝቧ የሚገኙበት ሁኔታ በግልጽ ያሣያል። የአገሪቱ ዘመን-ጠገብ መልከዐ-ምድራዊ መለያ ስሞች እና ወሰኖች ተሽረው በተወሰኑ ነገዶች ማንነት ብቻ ላይ የተመሠረቱ ስሞች በመስጠት፣ የኢትዮጵያውያንን ተዘዋውሮ በፈለጉት ቦታ እና አካባቢ የመኖር እና የመሥራት ተፈጥሮአዊ፣ ታሪካዊ፣ ባህላዊ እና ሰብአዊ መብቶቻቸውን ገፍፈው፣ አንድነታቸውን አሣጥተው፣ አብሮነታቸውን ክደው፣ በጠላትነት እንዲተያዩ አድርገዋቸዋል። ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ከሕዝቡ ስሜት ፈጽሞ እንዲጠፉ መጠነ ሠፊ የሆነ የሥነልቦና ጦርነት ከፍተው አገሪቱን ከመጨረሻው የጥፋት ጠርዝ ላይ አድርሰዋት ይገኛሉ።


Tigray_Map~0የትግሬ-ወያኔ እና ተከታዮቹ በኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ ጥቅም፣ እንዲሁም በሕዝቧ ኢትዮጵያዊ ማንነት ላይ ታሪክ፣ ትውልድ፣ ሕግ እና ማናቸውም ዓይነት ሥነ-ምግባር ይቅር ሊለው የማይችል የክህደት ተግባሮችን የፈጸሙ መሆኑን ከማንም ይበልጥ ራሣቸውም አይክዱም። ይህም በመሆኑ የኢትዮጵያ አንድነት ተጠብቆ ከዘለቀ በየትኛውም ጊዜ በአገር ክህደት ወንጀል ተጠያቂ እንደሚሆኑ ያውቃሉ። ከዚህ ተጠያቂነት ለመዳን እንችላለን ብለው የሚምኑት ሁለት ነገሮችን ጎን ለጎን ማከናወን ሲችሉ ብቻ ነው። እነዚህም፦ አንደኛ የወያኔ ትውልድ ለሚቀጥሉት መቶ ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሕይዎት ላይ የወሳኝነቱን ሚና ይዞ የሚቀጥልበት አስተማማኝ ሁኔታ ሲረጋገጥ፤ ይህ የመጀመሪያው ዕቅድ በተለያዩ ምክንያቶች ባይሣካ ሁለተኛው አማራጭ ዕቅድ ትግራይን ከኢትዮጵያ በመገንጠል የትግራይ ረፑብሊክ በመመሥረት ጎጆ መውጣት፤ የሚሉ ናቸው።
R_of_Tigrai
ሁለተኛውን ግብ ለማሣካት በኢትዮጵያ ላይ ሥልጣን ከተቆጣጠሩ ጊዜ ጀምሮ ለምትገነጠለው ትግራይ ቁሣዊ፣ ቴክኒካዊ እና ኅሊናዊ ሁኔታዎች እንዲሟሉ የሚያስችሉ ተግባሮችን ማከናወን እንዳለባቸው ታሣቢ አድርገው መንቀሣቀሣቸው ባለፉት ፳፫(ሃያ ሦሥት) ዓመታት የሥልጣን ዘመናቸው ትግራይ ውስጥ አያሌ የመሠረተ ልማት ሥራዎች መሥራታቸው ይታወቃል። በዚህም መሠረት የትግራይ ክልል ከጎንደር እና ከወሎ ክፍለ ሀገሮች መሬት ነጥቀው በታሪክ የትግራይ አካል ሆነው የማያውቁ አካባቢዎችን አጠቃልለው ጥንተ-ነዋሪውን የዐማራ ነገድ አባላት የሚገድሉትን በመግደል፣ ቀሪውን በማሠር እና በማሰደድ ትግሬን አስፍረውበታል። ይህ የያዙት ግዛት ወደፊት ለምትገነጠለው ትግራይ ይጠብባል በማለት ከሰቲት ወደ ደቡብ ምዕራባዊ የጎንደር እና የጎጃምን የሱዳን አዋሳኝ ወረዳዎችን ከቤንሻጉል ጉምዝ እና ጋምቤላ ክልሎች ጋር በማገናኘት የታላቋ ትግራይን የመሥፋፋት ዓላማ ዕውን በማድረግ ላይ ይገኛሉ (አባሪ ካርታውን ይመልከቱ)።
135435316423122164197559-1
በዚህም መሠረት ለወደፊቷ ትግራይ ለምትጠቀልለው ሠፊ ግዛት፣ ከውጭው ዓለም ጋር የሚያገናኙ የመገናኛ መሥመሮችን ዘርግተዋል፣ ተጨማሪ መሥመሮችንም በፍጥነትም በመገንባት ላይ ይገኛሉ። የትግራይን ምርት ወደ ውጭ ለመላክ እና ከውጭ የሚፈለጉ ሸቀጦችን ወደ ውስጥ ለማስገባት፣ ከጅቡቲ እስከ መቀሌ፣ ከሱዳን ጠረፍ እስከ መቀሌ የሚያገኛኙ የባቡር ሐዲድ ግንባታዎች በመፋጠን ላይ ናቸው። ሁለት ታላላቅ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ጣቢያዎች መቀሌ እና አክሱም ላይ ገንብተዋል። ቀበሌዎችን ከወረዳ ከተሞች፣ ወረዳዎችን ከአውራጃዎች (ዞኖች)፣ አውራጃዎችን ከዋና ከተማዋ ከመቀሌ ጋር የሚያገናኙ፣ ክረምት ከበጋ ያለምንም እንከን አገልግሎት የሚሠጡ መረብ-መሰል አውራ መንገዶች ተገንብተዋል። ድርቅን ለመቋቋም የክረምት ዝናብን ለማቆር የሚያስችሉ በርካታ ግድቦችን ሠርተው አገልግሎት ላይ አውለዋል። የትግራይን አዲሱን ትውልድ ከኢትዮጵያዊነት ስሜት አውጥቶ የትግራዊነት ስሜት እንዲገነባ የሚያስችሉ፣ በተቀነባበረ ሁኔታ ቅስቀሣ እና ትምህርት በማያቋርጥ መልኩ የሚሰጡ ተቋሞች ተገንብተዋል። በርካታ ትምህርት ቤቶች፣ ኮሌጆች፣ የቴክኒክ እና የሙያ ትምህርት ቤቶች፣ ዩኒቨርስቲዎች ተከፍተዋል። በኢንዱስትሪ ግንባታ ረገድ የነባሮቹን የኢትዮጵያ ፋብሪካዎች ሕልውና የሚያጠፉ የመድኃኒት፣ የጨርቃጨርቅ፣ የስሚንቶ፣ የመጠጥ እና የብረታ ብረት ፋብሪካዎች በሁሉም የትግራይ አውራጃዎች ተቋቁመዋል። ከእነዚህ መካከል፦ የአዲግራት መድኃኒት ፋብሪካ፣ እንዲሁም መቀሌ የተገነቡት የመሰቦ ስሚንቶ ፋብሪካ፣ የአልሜዳ የጨርቃጨር ፋብሪካ፤ የመሥፍን ኢንጂነሪንግ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ፣ ወዘተርፈ ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው። አሽጎዳ አካባቢ በአፍሪቃ በግዙፍነቱ ቀዳሚ የሆነ እና በነፋስ ኃይል ኤሌክትሪክ የሚያመነጩ ተርባይኖች በብዛት ተገንብተዋል።

የአገሪቱ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ መዋቅሮች ያላአንዳች ይሉኝታ በወያኔች የተያዙ ናቸው። የአገሪቱን የአየር እና የምድር ኃይል መከላከያ የማዘዣ ማዕከሎች ከአዲስ አበባ እና ከደብረዘይት በማስወጣት ማዕከላዊ ዕዛቸውን ትግራይ ላይ እንዲሆን በማድረግ ወሣኝ የሆኑት የመከላከያ መሣሪያዎች ትግራይ ውስጥ እንዲከማቹ ተደርጓል። የከባድ ሮኬቶች መተኮሻ መንኮራኩሮች ትግራይ ውስጥ ተገንብተዋል። የአገሪቱ የመከላከያ ኃይል ከጓድ እስከ ጠቅላይ ኤታማጆር ሹም ድረስ ያሉት ቁልፍ የአዛዥነት፣ የመገናኛ፣ የድርጅት፣ የሎጂስቲክ ኃላፊነቶችን በሙሉ በትግሬዎች በማስያዝ የወታደራዊ ተቋሙ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴው የትግራይን መገንጠል ዕውን በሚያደርግ መልኩ ወደፊት እየተባለ ይገኛል።
በአጠቃላይ የትግራይን ግንጠላ ዕውን መሆን ሂደቱ የተመቻቸ እንዲሆን፣ በ«ሽግግር ዘመን» ተብየው «ልማት ቅድሚያ በጦርነት ለተጎዱ ክልሎች» በሚል ስም የአገሪቱ አጠቃላይ በጀት ለትግራይ ልማት ተመድቦ ለአምስት ዓመታት ከላይ ለተጠቀሱት ተግባሮች እንዲውል መደረጉ ይታወቃል። ከሽግግር መንግሥቱ ፍጻሜ በኋላም የተዘጋጀው «ሕገመንግሥት» ተብየው የሽግግር መንግሥቱ ቻርተር ተከታይ ሆኖ በመዘጋጀቱ፣ አጠቃላይ ያለፉት ፳፫(ሃያ ሦሥት) ዓመታት ሲሠራ የኖረው ከፍ ሲል የተጠቀሱትን ሁለት ግቦች ለማሟላት፣ ማለትም፦ የትግሬ-ወያኔ ትውልድ ለመቶ ዓመታት በኢትዮጵያ ሥልጣን ላይ የሚቆይበትን ሁኔታ እያረጋገጡ መጓዝ፣ ይህ የማይሆን ከሆነ ለምትገነጠለው ትግራይ ቁሣዊ፣ ቴክኒካዊ እና ኅሊናዊ መሠረት ሊሆኑ የሚችሉ የሁለንተናዊ ግንባታ ተግባሮችን በተጓዳኝ ማከናወን የሚለው በተደጋጋፊ መልኩ ሲሠራ መቆየቱ ይታወቃል።
ይህ ሁሉ ሤራ ቢጎነጎንም፣ የትግሬ-ወያኔ ባልጠበቀው መልኩ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ከሕዝቡ ኅሊና ውስጥ ከመፋቅ እና ከመደብዘዝ በተቃራኒ፣ የበለጠ እየጠነከረ መሄዱ የአደባባይ ምሥጢር ነው። ለዚህ ማረጋገጫዎች በተከታታይ በሚነሱ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች እና በተቃዋሚ ኃይሎች መበራከት ናቸው። ስለዚህ የትግሬ-ወያኔ ቡድን «ለመቶ ዓመታት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥልጣን ላይ እቆያለሁ» የሚለው ዓላማው ሊሣካ የማይችል እንደሆነ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በ፲፱፻፺፯ (1997) ዓ.ም. ብሔራዊ ምርጫ በማረጋገጡ፣ አጠቃላይ እንቅስቃሴውን «ትግራይን ከቀሪዋ ኢትዮጵያ መገንጠል» በሚለው ሁለተኛ ግቡ ላይ እንዲያተኩር ሁኔታዎች እንዳስገደዱት ይታያል። ለዚህ የግንጠላ ዓላማው ያጸደቀው «ሕገመንግሥት» ተብየው ዋናው መሣሪያው መሆኑ ይታወቃል። አንቀፅ ፴፱(ሰላሣ ዘጠኝ) ለማንም ጥቅም ተብሎ ሣይሆን፣ የትግራይን ግንጠላ ለማሣሳካት የተቀረጸ አንቀፅ እንደሆነ ማንም ይስተዋል አይባልም። ዛሬም ቢሆን የትግሬ-ወያኔ የተመሠረተበትን ዋናውን ስሙን (ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ) ያለመቀየሩ የሚያረጋግጠው ሃቅ ትግራይን ከቀሪዋ ኢትዮጵያ መገነጠል በይደር የቆየ የማይቀር አጀንዳው መሆኑን ነው። ይህ ዕውነት እንደተጠበቀ ሆኖ በዚህ አንቀፅ ብቻ ትግራይን ገንጥሎ በሰላም መኖር እንደማይችል የትግሬ-ወያኔ ጠንቅቆ ያውቃል። የትግሬ-ወያኔ መሪዎች ከተጠያቂነት መዳን የሚችሉት፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ የዘረፉትን ንብረት መጠቀም የሚችሉት፣ የትግራይ መገንጠል ለጊዜውም ቢሆን ዕውን ሊሆን የሚመችለው፣ በቀሪዋ ኢትዮጵያ ነገዶች መካከል መበታተን ሲፈጠር፣ ከሁሉም በላይ ዐማራ የተሰኘውን ነገድ ሌሎች ነገዶች በጠላትነት ፈርጀው እርሱን ማዳከም ሲችሉ፣ እንዲሁም «ዐማራ» ሲል የከለለውን ክልል ከውጭ አገር ጋር እንዳይገናኝ ዝግ በማድረግ ብቻውን አቁሞ ኅልውናውን ማጥፋት ሲቻል እንደሆነ ብቻ መሆኑን ይህ ቡድን አቅዶ በተግባር ሲንቀሣቀስ ቆይቷል። ለዚህም ባለፉት ዓመታት ሁሉም በሚባልበት ደረጃ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙት ነገዶች ዐማራውን በአውራ ጠላትነት ፈርጀው የጥፋት እጃቸውን እንዲያነሱበት አድርጓል።
የትግሬ-ወያኔ ምዕራባዊውን «የዐማራውን ክልል» ለም እና ድንግል መሬቶች ለሱዳን በገጸበረከት ሰጥቷል። በቀረው ምዕራባዊ ዳርቻ የትግራይን ግዛት በማስፋት ከቦ፣ ከቤንሻጉል ጉምዝ እና ከጋምቤላ ክልሎች ጋር አገናኝቷል (አባሪ ካርታውን ይመልከቱ)። ከ5 ሚሊዮን የማያንስ ዐማራ ከምድረ ኢትዮጵያ አጥፍቷል። አያሌ ዐማሮች በአገር ውስጥ ሠርቶ የመኖር መብታቸውን በመገፈፋቸው ለስደት ሕይዎት ተዳርገዋል። በስደት በዓለም ዙሪያ ከሚኖረው ኢትዮጵያዊ መካከል ከመቶ ፷(ስድሣ) እጁ በላይ ዐማራ መሆኑ የሚያመለክተው፣ ዐማራው በገዛ አገሩ ሠርቶ የመኖር መብቱን የተገፈፈ መሆኑን ብቻ ሣይሆን፣ ዐማራው በመጥፋት ሂደት ላይ መሆኑን የሚያሣይ ነው።
ሰሞኑን ለሞረሽ ወገኔ ዐማራ ድርጅት ከደረሱት እጅግ አስተማማኝ መረጃዎች መካከል፣ ወያኔ በኢትዮጵያ ፖለቲካ አናት ላይ የመቆየት ዓላማው የማይሣካ መሆኑን ተገንዝቦ፣ ወደ ሁለተኛው እና የመጨረሻ ግቡ፣ ማለትም፦ ትግራይን ለመገንጠል በከፍተኛ ሚስጢር እየሠራ መሆኑን የሚያረጋግጡ ናቸው። ይህም የትግራይ ግንጠላ ዕቅድ ለማሣካት እንዲቻል፣ ከአገር ውስጥ ተቃዋሚ ኃይል እንዳይነሣ፣ ኢትዮጵያን በሽግግር ዘመኑ ከፋፍለዋት በነበረው ፲፬(አሥራ አራት) እና ከዚያም በላይ የሆኑ የክልል ወሰኖችን የሚያመለክቱ ካርታዎችን አዘጋጅተው፣ ከየጎሣው ሰዎችን መልምለውና አደራጅተው፣ ለነዚህ ሰዎች የወታደራዊ፣ የደህንነት፣ የአደረጃጀት፣ የአመራር እና የቁጥጥር ሥራ የሚሠሩ የትግሬ-ወያኔዎች ተመድበው በከፍተኛ ሚሥጢር ፀረ-ኢትዮጵያ ሤራ እየተዶለተ መሆኑን አረጋግጠናል። ይህም ከ1997 የምርጫ ሽንፈታቸው ማግሥት ጀምሮ በመከናወን ላይ ያለ ተግባር እንደሆነ የመረጃ ምንጮቻን ገልፀውልናል። «ይህ አይሆንም፣ አይደረግም፣ አይታሰብም» ሊባል የማይችል እንደሆነ የወያኔ ጉዞ እና ተግባር ከጥርጣሬ ውጭ በሆነ መንገድ ያስረዳናል። ለዚህ ሤራቸው ማረጋገጫዎቹ በነባር ኢትዮጵያዊ እምነቶች መካከል እየሰራ ያለው የማጥፋት ሥራ፤ በጎጃም፣ በጎንደር፣ በአዲስ አበባ፣ በሶማሌ፣ እየተካሄዱ ያሉት የጥፋት እርምጃዎች የዚህ ዕቅድ አካሎች መሆናቸውን ልብ ሊባል ይገባዋል።
ሌላው የትግሬ-ወያኔ ኢትዮጵያን የማፈራረስ ተልዕኮው የማይቀር እና የፍጻሜው የመጨረሻ ደረጃ ላይ መድረሱን ማሣያው፣ የምዕራቡ ዓለም የመረጃ እና የስትራቴጂክ ጥናቶች ተቋም ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት አጋማሽ ላይ በ2030 እ.አ.አ. ከዓለም ካርታ ላይ ከሚጠፉ አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗን ይፋ ማድረጉን እናስታውሳለን። በተመሣሣይ ሁኔታ በኅዳር ወር ፪ሺህ፯ ዓ.ም. ሞስኮ ውስጥ የተካሄደ የዓለም አቀፍ ቀውሶች ጥናት ተቋም ባዘጋጀው ስብሰባ፣ በምሥራቅ አፍሪካ የሚታየውን ብጥብጥ ለዘለቄታው ለማስወገድ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ኮንፌደሬሽን መመሥረት እንዳለበት ግፊት የሚያደርግ ጥናት ቀርቧል። የኮንፈደሬስሽኑ አባል አገሮች ጥንት እንግሊዝ «ከኢትትዮጵያ ተቆርሶ ወደ ሱዳን ይካተት» ትለው የነበረው የኤርትራ ምዕራባዊ ክፍል ወደ ሱዳን ተካልሎ ሱዳን ከሦስት እንድትከፈል፣ የኤርትራ ደጋማው ክፍል ከትግራይ ጋር ተቀላቅሎ ትግራይ ትግርኝ የተሰኘ ግዛት እንዲፈጠር፣ የአፋርኛ ተናጋሪዎች በአንድ ግዛት ተጠቃለው አንድ ግዛት እንዲሆኑ፣ በአምስቱ ዓመት የአርበኛነት ዘመን ፋሽስት ጣሊያን «ዐማራ» ብሎ ሰይሞት የነበረው ክልል አንድ የዐማራ ግዛት እንዲሆን፣ የቀሩት አካባቢዎች የፋሽስት ጣሊያንን ክፍፍል መሠረት አድርገው የየራሳቸውን ግዛቶች እንዲመሠረቱ እና በነዚህ አገሮች መካከል ኮንፌደሬሽን ይመሥረት የሚል ነው። የእነዚህ ጥናቶች ግብም ከወዲሁ ኢትዮጵያዊው የኢትዮጵያን መፍረስ አይቀሬነት እንዲለማመደውና «ድሮም ተብሎ ነበር» በማለት የአገሩን መፍረስ በፀጋ እንዲቀበል የሥነ- ልቦና ሰለባ ከወዲሁ መሠራቱን የሚያመለክቱ ናቸው።
ካርታ፦ ለወደፊቱ «የትግራይ ሪፑብሊክ» ተብሎ በትግሬ-ወያኔ የሚገነጠለው የኢትዮጵያ አካል በአረንጓዴ ቀለም የተቀለመው ነው።
የትግሬ-ወያኔ እና ዕኩይ ዓላማው ኅልው ሆነው የሚዘልቁት ኢትዮጵያውያን ሠፊውን ለቀን ጠባቡን፣ ኢትዮጵያዊነትን ትተን ጎሣዊ ማንነትን ስንላበስ፣ ዕውነትን ከድተን ከውሸት ጎራ ስንሰለፍ፣ ዘላቂውን ትተን አላቂውን እና ጠፊውን ስንይዝ፣ አኩሪውን ትተን ነገ የሚያሳፍረውን ስንከተል፣ ለኅሊና ሳይሆን ለጥቅም ስንገዛ ነው። እስካሁን የትግሬ-ወያኔ ያለ ልጓም የጋለበን በነዚህ ምክንያቶች ብቻ ነው። አሁን ግን የትግሬ-ወያኔ አጥፍቶን ሊጠፋ ከመጨረሻው ጠርዝ ላይ ቆሟል። የመጥፋቱም ያለመጥፋቱም ጉዳይ የሚወሰነው በእኛ ብቸኛ ምርጫ ነው። ምርጫችን በኢትዮጵያዊነታችን መቀጠል ከሆነ፣ ወያኔ ያጠመደልንን የመነጣጠል መንገድ ትተን በአንድነት በመቆም ኢትዮጵያን ከመጥፋት ለመታደግ ቁርጠኛ አቋም ልንይዝ ይገባል። ቢመሽም፣ እጅግ ብንዘገይም፣ ፈጽሞ ከመቅረት ይሻላል እና እጅ ለጅ ተያይዘን አገራችን እንድናድን ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ጥሪውን ያቀርባል።
ከሁሉም በላይ የትግሬ-ወያኔ ወደ መጨረሻ እርምጃው ሲያመራ አጥፍቶ የሚጓዘው፣ ከጽንሱ ጀምሮ በአውራ ጠላትነት ፈርጆ ላለፉት ፵(አርባ) ዓመታት ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሲገድለው፣ ሲያስረው፣ ሲያሰቃየው እና ሲያሳድደው የኖረውን ዐማራ እስትንፋስ ሳያቋርቋጥ ከጉሬው እንደማይገባ አውቀን፣ ከተደገሰልን ጥፋት እራሳችን መከላከል እንድንችል ከምንጊዜውም በላይ ነቅተንና ተደራጅተን ኅልውናችን ለማስጠበቅ ቁርጠኛ ሆነን እንድንቆም ሞረሽ-ወገኔ አደራ ይላል።
ዐማራን ከፈጽሞ ጥፋት እንታደጋለን!
ፈለገ አሥራት የትውልዳችን ቃል ኪዳን ነው!
ኢትዮጵያ በጀግና እና ቆራጥ ልጆቿ መስዋዕትነት ታፍራ እና ተከብራ ለዘለዓለም ትኖራለች!

ሰሚ ያጣ ጮኸት ከካርቱም – አጥናፉ መሸሻ

751sudan1   በመላው አለም ለምትገኙ ኢትዮጽያዊያኖች ሁሉ    ፤ በተለያዩ ግዜያት  ሰብአዊ  መብታችን  ይከበር ዘንድ ፤  ከምድር ሱዳን የሲቃ ጮኸታን ሰምታችሁ  በተቻላችሁ መጠን ትታደጉን ዘንድ ደጋግመን በፁሁፍ አሰምተናል ፤ እንሆ  በአሁኑ ሰአት ወያኔ ከምንግዜውም በላይ በከፋ መልኩ  ፤ ካርቱም ውስጥ  ስደተኛውን አንደተለመደው እያሳፈሰ ፤ ወዳልታወቀ እስር ቤት እያሳወሰደ ይገኛል ፤ በተለይ ጀዋዛት እየተባለ በሚገኘው እስር ቤት ውስጥ ፤ በሸህ የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ታጉሮው ይገኛሉ ፤ ከእነዚህም ውስጥ ለልደት ደሮ ለመግዛት ገበያ የሔዱ እህቶቻችን ከነደሮቸው ፤ ልደትን መድሀኒአለም ቤተክርስትያን አክብረው የሚመለሱ ነጭ የለበሱ ወገኖች  እስር ቤቱን ሞልተውታል ፤ በተጨማሪ ዴም እየተባለ ከሚጣረው ሰፈር ውስጥ አንድ ወጣት ሀለፎም አዲሱ ተካልኝ የተባለ የአንገት መስቀሉን በጥሰው መኪና ላይ ጭነው እስር ቤት አጎረውት ይገኛል ፤ መታወቂያ ለማውጣት እድሜው የማይፈቅድ ወጣት ሳይቀር  ያለ አንዳች እርህራሔ አስር ቤት ይገኛል ፤ ይህን ወጣት እንደምሳሌ ተጠቀምንበት እንጅ በርካታ ወጣቶች መኖራቸውን አናሳስባለን;;
ዛሬ አንባገነኑ ወያኔ ፤ በከፍተኛ መረበሸ ውስጥ አንዳለ ፤ እድሜው እያጠረ ፤ የቆመበት መሬት እየከዳው መሆኑን  እንገነዘባለን ፤ ለዚህም ሱዳን ሀገር የሚኖረውን ስደተኛ ፤ ከኤርትራ በኩል ከሚንቀሳቀሱትና ከሌሎች በነፍጥ ከሚታገሉት ጋር ግንኙነት አላቸው ብለው ስለሚየምኑና ፤  እንዲሁም ሰሞኑን በሱዳን አጎራባች አርማጭሆ አካባቢ በተፈጠረው ሁኔታ በመስጋት ፤ ካርቱም የሚኖረውን ስደተኛ ሕጋዊ የሰደተኛ መታወቂያ ፤ በየሶስት ወር የሱዳን መንግስት ሲያድስ የነበረውን፤ ኢትዮጽያዊ ስደተኛ የለም በማስባል ፤ መታወቂያችን ወያኔ ከፍተኛ ገንዘብ በመክፈል መታወቂያ እንዳይታደስ አስደርጎል ፤ ይህም ማለት ፤ የሚፈልጉትን ስደተኛ   በአፈሳ መልክ አፍነው እንዲወስዱ ያስችላቸዋል ፤ ባሳለፈነው ወር የወያኔ ምክር ቤት ያፀደቀወን  በአሸባሪና ወንጀለኛን ስም ስደተኛውን አሳልፍ በመስጠት የተደረገውን የትብብርን ውል ልብ ይሎል ፤ በተጨማሪ ጀዋዛት እየተባለ በሚገኘው እስር ቤት ውስጥ   የታጎሩትን የስደተኛ መታወቂያ የያዙትን እያሳነጠቁ ፤  ወያኔ ከሱዳን መንግስት ጋር በመመሳጠር ፤ አለማአቀፍ የስደተኞችን ህግ በመጣስ ፤ ስደተኛ መብትን በመንፈግ  ሕገ ወጥ በሆነ  አሰራር መታወቂያ አስር ቤት ውስጥ አስገድደው ፎቶ እያስነሱ ስደተኝነትን የማይገልፅ መታወቂያ በመሰጠት ላይ  መሆናቸውን አጥብቀን እንናስገነዝባለን ;;
ባሳለፍነው ወር የወያኔን መሰሪ ተንኮል ማጋለጣችን ይታወቃል ፤ ይኸውም ስደተኛውን ማህበረሰብ ቅጥ ባጣ አፈሳ በማስመረር በወያኔ ሰላዮች አማካኝነት የወያኔ ኢንባሲ ካርቱም ውስጥ በ28/11/2014 ሰላማዊ ሰልፍ አስደርገውል ፤ የሰልፉም አላማ   የኢሳትን ሚዲያ በመጠቀም ፤ ወደ ሀገራች አንግባ የሚለውን መልእክት ለማስተላለፍ የታቀደ ነበር ፤ እነዚህ ሰብአዊ ክብር ያልፈጠረባቸው ቅጥረኞች  በግፍአን እንባ አንዳላገጡ እንረዳል ፤ በተጨመማሪ እነዚህ በደል የበዛባቸው ወገኖቻችን ፤ለጥያቂቸው መልስ የሚያገኙ መስሎችው ተመልሰው ወያኔ ኢንባሲ በሳምንቱ ሔደው ማንም ሳያናግራቸው በመጡበት አኾሖን ተመልሰዋል;;
ውድ ወገኖቻችን ፤ ሱዳን ሀገር ውስጥ የሚደረሰውን በዝምታ የማይታለፍ በደል ከከፈ ደረጀ ከመድረሱ  በፊት ፤ በመላው ዓለም የምትገኙ ለሰብአዊ መብት መከበር የምትታገሉ   አለም አቀፍ ትብብር የፈጠራችሁ ወገኖች ሁሉ ፤ዛሬም ጨኻታችን ጣራ አልባ እንዳይሆን ፤ ለሱዳን መንግስትና ለዩ ኤን ኤች ስ አር በተቀነባበረ መልኩ ሰብአዊ መብታች ይከበር ዘንድ ፤  በሱዳን ሀገር የምንገኝ ኢትዮጽያዊያን ልሳን ትሆኑን ዘንድ  በአክብሮት እንማፀናለን ;;       ባሳለፍነው ወር 2000 ወገኖቻችን  የ ኤች አይቭ ና የሀቢታይትስ በሸተኞች ናቸው ተብለው ፤ ገንዘብ ንብረታቸውን ሳይውሰዱ ከሱዳን ሲባረሩ  አንድም ተቆርቆሪ ዜጋ የነዚህ ግፍአን     ልሳን ሳይሆን በመቅረቱ  ልብን ያደማል ፤   አሁንም ፤ አሁንም ፤ ይኽ የወያኔ ተንኮል በሰፊው ሳይደገም አፋጣኝ ወገናዊ ትብብራችሁን አንጠይቃለን;;
አጥናፉ መሸሻ

በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ የተቋቋመው የሃገር ፍቅር የሥነ ጥበብ መድረክ ጥር 16 ቀን 2007 ያቀርባል

በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ የተቋቋመው የሃገር ፍቅር የሥነ ጥበብ  መድረክ ሁለተኛ ዝግጅቱን ጥር 16 ቀን 2007/ ጃንዋሪ 24 /2015 በፍራንክፈርት ከተማ ያቀርባል። ስለ ዝርዝሩ የተያያዘውን ማስታወቂያ ያንብቡ ።
ty

በጀርመን ፍራንክ ፈርት ሰላማዊ ሰልፍ ተካሄደ

demonstration germeny
በዳዊት መላኩ
በጀርመን ፍራንክ ፈርት በዛሬው ዕለት ማለትም 12/01/2015 እ.ኤ.አ ከጠዋቱ 11፡00 ሰዕት ጀምሮ መነሻውን የዶቼ ባንክ ዋና ጽ/ቤት ከሚገኝበት አድርጎ መድረሻውን የወያኔው ቆንስላ ጽ/ቤት ያደረገ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሄደ፡፡
በዚህ ሰላማዊ ሰልፍ በርካታ ቁጥር ያላቸው የሰልፉ ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን የዶቼ ባንክ ቦርድ ለወያኔ መንግስት ሊሰጥ ያሰበውን የሶቨርንግ ቦንድ ሽያጭ እንዲያቆም የሚተይቁ የተለያዬ መፈክሮችን ያሰሙ ሲሆን ለበርካታ ነዋሪዎች ይህን በሚመለከት በራሪ ወረቀቶችን አድለዋል፡፡ሰልፈኞች ያሰሟ ቸው ከነበሩ መፈክሮች መካከል፡- ጀርመን የዜጎችን መፈናቀል አትደግፊ፤የመሬት ወረራን እንቃወማለን፤ ጀርመን ላንባገነን መንግስት የሚትሰጪውን ድጋፍ አቁሚ፤የፖለቲካ እስረኞች ያፈቱ የሚል ይገኝበታል፡፡ በተጨማሪም ሰልፈኞቹ የነጻነት ታጋዩ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን አስመልክቶ በፍራንክፈርት የእንግሊዝ ኢምባሲ ቆንስላ ጽ/ቤት ፊት ለፊት የተለያዩ መፈክሮችን ያሰሙ ሲሆን እንግሊዝ ዜጋዋ የሚፈታበትን መንገድ አጠናክራ እንድትጠይቅ አሳስበዋል፡፡በተወካያቸው በኩልም ደብዳቤ አስገብተዋል፡፡በመጨረሻም ሰልፈኞቹ ጉዟቸውን ወደ ኢትዮጵያ ኢምባሲ በማምራት የፖሊተካ አስረኞች ይፈቱ፤ ነጻነት እንፈልጋለን፤ፍትህ ለፖለቲካ እሰረኞች፤ፍትህ ለሞስሊም ተወካዮች ፍትህ ለጋዜጠኞች፤ወያኔ ስልጣኑን ይልቀቅ፤መንግስት ዜጎችን ማሸበሩን ያቁም ወዘተ የመሳሰሉ መፈክሮችን ያሰሙ ሲሆን ባለ አንባሸውን የወያኔ ሰንደቅ አላማ አውርደው በትክክለኛው የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ለመተካት የተደረገው ጥረት በፖሊሶች ከፍተኛ ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ_ክርስቲያን ይዞታዎችና በአማኞቿ ላይ በልማት ሰበብ የሚፈጸመውን ግፍና በደል አጥብቀን እናወግዛለን::

Ethiopian Orthodox Churchesበኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ_ክርስቲያን ይዞታዎችና በበዓላት ማክበሪያ ሥፍራዎች እንዲሁም በእምነቷ ተከታዮች ላይ በልማት ሽፋን የሚፈጸመውን የቦታ ቅሚያና የክርስቲያኖች ግድያ በማስመልከት ከዓለም ዓቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ_ክርስቲያን እምነት ተከታዮች አንድነት የወጣ መግለጫ
 “እንግዲህ አትፍሩአቸው የማይገለጥ የተከደነ የማይታወቅም የተሰወረ ምንም የለምና:: በጨለማ የምነግራችሁን በብርሃን ተናገሩ:: በጆሮም የምትሰሙትን በሰገነት ላይ ስበኩ:: ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ:: ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ:: ስለዚህ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት ዕመሰክርለታለሁ:: በሰው ፊትም የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለሁ::” የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ፲ ከቁጥር ፳፮ እስከ ፴፫
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ_ክርስቲያን ከተመሰረተችበት ጊዜ ጀምሮ ሕልውናዋን የሚፈታተን የጠላት ጦር በተለያየ መልኩ ሲወረወርባት የቆየ ሲሆን ዛሬም የሰይጣንን ተልዕኮ በሚያስፈጽሙና እኩይ ተግባር የዘወትር ሥራቸው በሆነ ቡድኖች የሚሰነዘርባት ጥቃት በከፋ መልኩ እንደቀጠለ ነው:: ይልቁንም ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን የመምራት ሥልጣኑን ከተቆጣጠረበት ጊዜ አንስቶ ክልላችሁ እዚህ አይደለም፣ በዚህ አካባቢ መኖር አትችሉም ተብለው ዘራቸው ምክንያት ሆኖ ወደ ገደል የተጣሉት፣ ከነቤታቸው የተቃጠሉት፣ አንገታቸውን የተቆረጡት፣ በመትረየስ የተረሸኑት፣ በድብደባ አካላቸውን ያጡት፣ በአጠቃላይ በተለያየ የጭካኔ ተግባር ሕይወታቸው ያለፈና አካለ ጎደሎ የሆኑ ክርስቲያኖች እጅግ ብዙ ናቸው::
ይህ የጭካኔ ተግባር አሁን ደግሞ የልማት ሽፋን ተሰጥቶት ገዳማውያን አባቶች ከበአታቸው እንዲወጡ፣ ምዕመናን ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ፣ ቅድስት ቤተ_ክርስቲያናችን ይዞታዋን እንድታጣ፣ በዓል ማክበሪያዋን እንድታጣ እየተደረገ ነው:: ለዚህም በአዲስ አበባና በሌሎቹም የሀገሪቱ ክፍሎች በየጊዜው የሚሰማው ቅድስት ቤተ_ክርስቲያናችን ላይ ተነጣጥሮ የሚፈጸመው አረመኔያዊ ተግባር በቂ ምሥክር ነው:: ሰሞኑንም በባህር ዳር ከተማ ውስጥ የታቦት ማደሪያ ቦታችን አይነካ ብለው ጥያቄ ይዘው ከወጡ ሰላማዊ ሰልፈኞች ኦርቶዶክሳውያን መካከል ከአራት በላይ ሰዎች በመንግሥት ታጣቂዎች መገደላቸውና በእድሜ የገፉ መነኵሴ እናት ሳይቀሩ መደብደባቸው መንግሥት በቅድስት ቤተ_ክርስቲያናችንና በተከታዮቿ ምዕመናን ላይ ለሚያደርሰው ግፍና በደል ጉልሕ ማስረጃ ነው::
በእውነቱ እንደዚህ ዓይነቱ ወገን በወገኑ ላይ ሊፈጽመው የማይገባ ጭካኔ የተሞላበት ዘግናኝ ድርጊት ሊወገዝ የሚገባው ሰይጣናዊ ተግባር በመሆኑ ዓለም ዓቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ_ክርስቲያን እምነት ተከታዮች አንድነት አባላት በሙሉ አጥብቀን እናወግዘዋለን:: በተጨማሪም ይህንን በሰውም ሆነ በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያስጠይቅ ወንጀል የፈጸሙ ባለሥልጣናትና ግለሰቦች ለፍርድ እንዲቀርቡ አበክረን እንጠይቃለን::
በመጨረሻም እነዚህ በባሕር ዳር ከተማ ስለ ሃይማኖታቸው ሲሉ የሞቱትም ሆነ የተደበደቡት እንዲሁም በእስር ቤት መከራና ሥቃይ እየተፈጸመባቸው የሚገኙት ኦርቶዶክሳውያን ሁሉ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሰማዕታት እንደመሆናቸው መጠን ደማቸው ከንቱ ሆኖ እንደማይቀርና መከራና ሥቃያቸውም ሰማያዊ ዋጋ እንዳለው የምናምን ሲሆን የንጹሃንን ደም የሚያፈሱትና በሕዝብ ላይ ግፍና በደል የሚፈጽሙት ደግሞ የክፉ ሥራቸውን ዋጋ ከእውነተኛው ዳኛ ከልዑል እግዚአብሔር እንደሚቀበሉ ምንም ጥርጥር የለንም:: ምክንያቱም ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ በየመግለጫዎቻችን እንደገለጽነው ቅድስት ቤተ_ክርስቲያንን የሚቃወሙና በምዕመናኖቿ ላይ ግፍ የሚፈጽሙ እንዲሁም ገዳማውያን አባቶችን ከበአታቸው የሚያፈናቅሉና የሚያሳድዱ ሁሉ ውጊያቸው ከጌታችንና ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነውና::
ለሐዋርያነት ከመመረጡ በፊት የክርስቲያኖች አሳዳጅና የቤተ_ክርስቲያን ጠላት የነበረው ቅዱስ ጳውሎስ ወይም በቀድሞ ስሙ ሳውል ወደ ደማስቆ ሲሔድ በመንገድ ያጋጠመው ይህን ያረጋግጥልናል:: ቃሉ እንደሚከተለው ነው፦
“ሲሔድም ወደ ደማስቆ በቀረበ ጊዜ ድንገት በእርሱ ዙሪያ ከሰማይ ብርሃን አንጸባረቀ በምድርም ላይ ወድቆ ሳለ ሳውል ሳውል ስለምን ታሳድደኛለህ የሚለውን ድምጽ ሰማ:: ጌታ ሆይ ማን ነህ? አለው:: እርሱም አንተ የምታሳድደኝ እኔ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ፤ የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል አለው::” የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ፱ ከቁጥር ፫ እስከ ፮
ስለዚህ የመንግስት ባለሥልጣናትም ሆኑ ሌሎች ግለሰቦች በአጠቃላይ በቅድስት ቤተ_ክርስቲያንም ሆነ በኦርቶዶክሳውያን ላይ ግፍና በደል የሚፈጽሙ የሃይማኖታችን ተጻራሪዎች ሁሉ ይህንን የእግዚአብሄር ቃል በመመልከትና የፊተኞቻቸው የሆነባቸውን በማስታወስ ወደ ልባቸው ተመልሰው ቆም ብለው በማሰብ ከክፉ ሥራቸው እንዲታቀቡ እንደተለመደው ለማሳሰብ እንወዳለን::

ልዑል እግዚአብሔር ሀገራችንን ኢትዮጵያንና ቅድስት ቤተ_ክርስቲያናችንን
ይጠብቅልን::
አሜን
ታኅሳስ ፳፯ ቀን ፳፻፯ ዓ/ም

የአማራጭ መኖር ትሩፋት በኤኮኖሚና በፖለቲካ – ግርማ ሠይፉ

Girma-Seifuዛሬ ስለ አማራጭ መኖር ጥቅም እንዳነሳ የገፋፋኝ በቅርቡ ለቁልቢ ባህል በድሬዳዋ ከተማ ተገኝቼ የተመለከትኩት የቢራ ዋጋ ነው፡፡ ለወትሮ በቁልቢ ሰሞን ብዙም ባይሆን አንድ አንድ ጭማሪዎች ይታዩ ነበር፡፡ በዘንድሮ ግን በአብዛኛው ተጠቃሚ በሚያዘወትራቸው ሆቴሎችና ግሮሰሪዎች “የጃንቦ ድራፍት ዋጋ ዋጋ ብር 6 መሆኑን እናስታውቃለን” የሚል ማስታወቂያ ተመለከትኩ፡፡ ይህ የዋጋ ለውጥ ለምን መጣ ብሎ ሲጠየቅ መልሱ ቀላል ነው፡፡ የአማራጭ ቢራ አቅራቢዎች ወደ ገበያ መግባት ብቻ ሳይሆን፤ በመንግስት ቁጥጥር ስር የነበሩት የቢራ ፋብሪካዎች ወደ ግል ከመዛወራቸው ጎን ለጎን የግል ፋብሪካዎች ቁጥር መጨመሩ ዋነኛው ምክንያት ነው፡፡ እነዚህ የቢራ ፋብሪካዎች፣ ገበያውን ለመቆጣጠር ዋጋቸው ላይ ማስተካከያ ማድረግ ግድ ሆኖባቸዋል፡፡ የተገደዱት መንግስት ባወጣው መመሪያ ሳይሆን ፋብሪካዎቹ እያመረቱት ያለው ምርት አቅርቦት በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በቅርቡ ወደ ገበያ የገባው፤ “ዋሊያ” በመባል መታወቅ የጀመረው ቢራ ፋና ወጊ ነው፡፡ አንድ ጓደኛ “ኢትዮጵያ በምግብ እህል እራሷን ከመቻሏ በፊት በቢራ እራሷን የቻለች ሀገር ነች” ይላል እኔም ይሄን አስተያየት እጋራለሁ፡፡ ለቅንጦት ካልሆነ ቢራ ከውጭ ኢትዮጵያ ማስገባት የግድ ስለማይላት ማለቴ ነው፡፡
እርግጥ ነው በሀገራችን የነፍስ ወከፍ የቢራ ፍጆታ አሁንም አነስተኛ ቢሆንም፣ ከወተት ይልቅ ቢራ በብዛት በገበያ የሚታይባት ሀገር እንደሆነች የእለት ከእለት ህይወታችን ይመሰክራል፡፡ ይህ የአቅርቦት መሻሻል በቢራው ዘርፍ ለውጥ እያመጣ እንደሆነ ቢታመንም ልጆቻችን በሚፈልጉት በወተት መስክም ሊሳካ የማይችልበት አንድም ምክንያት የለም፡፡ ለዚህ ዘርፍ መስፋፋት፣ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮ ሁሉም በየገበታው ወተት ያገኝ ዘንድ መንግስት ምቹ ፖሊሲና ስትራቴጂ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ ልጆቻችን ወተት እንዲያገኙና ጤናማ ዜጎችን ለማፍራት ከወተት የሚሰበሰብ ታክስ ቢቀርብን ምን ይለናል?
አንባቢዎች ታስታውሳላችሁ ብዬ የምገምተው፤ ስለ የገበያ ውድድር በምክር ቤት ሆኜ ሳነሳ እንደ ምሳሌ የማነሳው ሲሚንቶን ነው፡፡ “ሲሚንቶን የታደገ የነፃ ገበያ፤ ሌሎቹንም እንዲታደግ” በሚል ዘወትር እጠቅሰዋለሁ፡፡ ሁላችሁም እንደምታስታውሱት፤ “ደርባ ሲሚንቶ” ፋብሪካ፣ ወደገበያ ገብቶ የሲሚንቶ ገበያውን እስኪለውጠው ድረስ ቀደም ብለው የነበሩት ሲሚንቶ ፋብሪካዎች የተለያየ ሰበብ እየፈጠሩ ዋጋውን ሲቆልሉት እንደ ነበር ይታወሳል፡፡ እነዚህ ፋብሪካዎች፣ የመንግስት እና የፓርቲ ንብረት እንደ እንደነበሩ ልብ ማለት ይገባል፡፡ ሲሚንቶ ለማምረት የሚያስፈልጉት ግብዓቶች አንዳቸውም በገበያ ላይ ቅናሽ ባላሳዩበት ሁኔታ፤ የአቅርቦት መሻሻል ብቻ በሲሚንቶ ዋጋ ላይ ያመጣውን ከፍተኛ የዋጋ ለውጥ ማንም የሚረዳው ነው፡፡ የሲሚንቶ አቅርቦት ዝቅተኛ በሆነበት ጊዜ ስንቶቹ ለዘረፋ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸው እስከአሁን ድረስ በሙስና ክስ በወህኒ እንደሚገኙም እናውቃለን፡፡ በአቅርቦት ማነስ፣ በሸማቾች ላይ በዋጋ ንረት ከሚደርሰው ጉዳት በተጨማሪ፣ ጥቂቶች ደግሞ በሙስና እንዲጨማለቁ እድል ሰጥቶዋቸው ነበር፡፡ የነፃ ገበያ ስርዓት፣ ብዙ ችግሮችን ሊቀርፍልን ይችላል የሚል እምነት ያለን ለዚህ ነው ፡፡
እንደምታውቁት ብዙ ስኳር ፋብሪካዎች በመንግስት እየተገነቡ ነው፡፡ እነዚህ የስኳር ፋብሪካዎች ተጠናቀው ስራ ሲጀምሩ፣ አሁን በቢራ ላይ መታየት የጀመረው ለውጥ ቀደም ሲልም በሲሚንቶ ያገኘነውን የነፃ ገበያ ትሩፋት ልናገኝ እንችላለን የሚል እምነት የለኝም፡፡ የስኳር ዋጋ ባለበት ከፍተኛ ደረጃ እንዲቀጥል ይደረጋል ብዬ ነው የማምነው፡፡ ይልቁንም በሀገር ውስጥ ምርቱ ትርፍ ቢሆን እንኳ ወደ ውጭ በርካሽ ተልኮ የውጭ ምንዛሬ ማስገኛ ይደረጋል እንጂ፤ ዜጎች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙት ይደረጋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ የሚገነቡት ፋብሪካዎች የመንግስት ናቸው፡፡ እነዚህን ፋብሪካዎች የሚመሩት አካላት፣ በምርቱ ላይ ባላቸው ቁጥጥር የተነሳ፤ ምንናአልባትም እንደ ቴሌ “የሚታለብ ላም” ተብሎ ከሚመደቡት ተቋማት እንደ አንዱ ይቆጥሩታል፡፡
በህገ-ወጥ መንገድ ያገኙትን ገቢ አስልተው፣ ትርፍ በትርፍ ሆንን ሊሉን ይችላሉ፡፡ አንባቢ መረዳት ያለበት መንግስት በንግድ ውስጥ ሲገባ፣ በተለይ ደግሞ በዋነኝነት ሲቆጣጠረው ውድድር የሚባለውን ነገር አጥፍቶ በኢኮኖሚክስ፤ “ሞኖፖሊ” የሚባለውን መጥፎ የገበያ ስርዓት ይዘረጋል፡፡ መንግስት ዋና ተግባሩ “ሞኖፖሊ” እንዳይኖር መቆጣጠር መሆኑ ቀርቶ፣ በመንግስት የሚመራ “ሞኖፖሊ” ዘርግቶ ህዝብን ይዘርፋል ማለት ነው፡፡
ከላይ ያነሳኋቸው ነጥቦች በሀገራችን ኢኮኖሚ ውስጥ የነፃ ገበያ በስርዓቱ ቢተገበር፣ ዜጎች ምን ያህል ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ጉልህ ማሰያዎች ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ አማራጭ እና ውድድር ሲኖር፣ ሸማቾች ጥራት ያለው ምርት እንዲያገኙ እድል ይሰጣል ማለት ነው፡፡
በተመሳሳይ፣ በፖለቲካው መስክም መንግስታችን አማራጭ እንዳይኖረን ሰንጎ ይዞናል፡፡ የኢትዮጵያ ሀገራችን የፖለቲካ አልፋና ኦሜጋ፣ “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” ብቻ ነው እየተባል ነው፡፡ ለይስሙላ የመድበለ-ፓርቲ ስርዓት እንዲገነባ እንፈልጋለን ቢባልም፣ በተግባር ግን የመድበለ-ፓርቲ ስርዓት የሚፈልጉትን መደላድሎች በማጥበብና በመዝጋት፣ ገዢው ፓርቲና መንግስት የፖለቲካ “ሞኖፖሊ” ለማስፋፋት በቁርጠኝነት ተሰልፈዋል፡፡ ለዚህም የቅርብ ምሣሌ የሚሆነው የመንግስት ስትራቴጂ ለህዝብ ማስጨበጥ በሚል የሽፋን ስም በመላው ሀገሪቱ ዜጎችን በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ለማጥመቅ እየተሄደበት ያለው መንገድ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር ይህ ካለፈው ዓመት ማገባደጃ ጀምሮ በዘመቻ መልክ የአብዮታዊ ዴሞክራሲን በህዝብ ዘንድ ለማስረፅ የተሄደበት መንገድ፣ የህዝብን ሀብት ከማባከን ውጭ የታለመለትን አብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብን ገዢ የማድረግ ትልም ያሳካ ነው የሚል ግምገማ የለኝም፡፡ ይህ ዜጎችን አማራጭ የማሳጣትና ፖለቲካውን በ “ሞኖፖል” የመያዝ ፍላጎት፣ ዞሮ ዞሮ ይህችን ሀገር አላስፈላጊ አዙሪት ውስጥ ከመክተት ውጪ የተሳካ የፖለቲካ ስርዓት ለመገንባት ያስችላል የሚል እምነት የለኝም፡፡
በግሌ፣ እንደ አንድ ንቁ የፖለቲካ ተሳታፊ ባለፈው የተደረገውን እና አሁን በመደረግ ላይ ያለውን አብዮታዊ ዲሞክራሲን በህዝቡ ውስጥ የማስረፅ እንቅስቃሴ፤ አማራጭ ይዘን የሀገራችን ፖለቲካ ምርጫ ይኑረው ለምንል ዜጎች እንደ አንድ ጥሩ እድል ወስጄዋለሁ፡፡ ገዢው ፓርቲ፣ በመንግስትነት ያለውን መስመር ያለአግባብ ተጠቅሞ የሄደበት መንገድ፣ በቀጣይ ገዢው ፓርቲ ይህን ይመስላል የሚለውን ስራችንን አቅልሎታል፡፡ ቀጣዩ ስራችን የራሳችንን አማራጭ በማቅረብ፣ ህዝቡ ‘ይበጀኛል’ የሚለውን እንዲመርጥ ማድረግ ነው፡፡ ጊዜያችንን ማሳለፍ ያለብን ገዢው ፓርቲ በመንግስትነቱ ለዜጎች ነፃነት፣ ለነፃ የኢኮኖሚ ስርዓት ግንባታ፣ ለህገ-መንግስታዊ ስርዓት መከበር፣ ለህግ የበላይነት፣ ወዘተ የዘጋውን በር እንዴት አድርገን እንደምንከፍተው እና ዜጎች አማራጭ ያላቸው መሆኑን በማስገንዘብ መሆን ይኖርበታል፡፡
በቀጣዩ የ2007 ምርጫ አንድነት ፓርቲ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የኢህአዴግ የፖለቲካ “ሞኖፖሊ” መሰበር አለበት ብሎ ያምናል፡፡ ነገር ግን ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድ ጊዜ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ወግድ ብሎ ሲያበቃ፣ የአንድነትን ሊብራል ዲሞክራሲ ይመርጣል ማለት አይደለም፡፡ ሁለቱም የፖለቲካ አማራጮች ምንናአልባትም ሌሎችም አማራጮች ተጨምረው በፖለቲካ ገበያው ውስጥ ስፍራ ያገኛሉ ማለት ነው፡፡ ዜጎች፣ የተመቻቸውን በመምረጥ ቢያንስ በህገ-መንግስት በግልፅ የተቀመጡትን የመደራጀት፤ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ፣ በመላው ሀገሪቱ ተንቀሳቅሶ የመስራትና የመኖር፣ ከሁለም በላይ ሀሉም ሰው በህግ ፊት እኩል የሚታይበት ስርዓት ለመዘርጋት፣ ወዘተ.. እድል ይፈጠራል፡፡
ይህ አማራጭ ያለው የፖለቲካ ስርዓት በፖለቲካ ገበያው ውስጥ እንዲኖር ምቹ ሁኔታ መፍጠር የመንግስት ዋነኛ ተግባር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህ ሳይሆን ሲቀር እንዲሆን የማድረግ ሀይል ያለው ግን በዜጎች ቁጥጥር ስር ነው፡፡ ዜጎች፣ በሀገራችን በውድድር ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ስርዓት እንዲኖር ቁርጠኛ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚሁም ዛሬ ነገ ሳይሉ የመራጭነት ካርድ መውሰድ፤ በምርጫው ዕለት ተገኝቶ ድምፅ መስጠት እና ድምፁን ማስከበር አለባቸው፡፡ ይህ ደግሞ ይቻላል፡፡ የህዝብ ኃይል ከምንም ኃይል በላይ ነው!!!!
ቸር ይግጠመን!!

የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዳይጠብ ጥንቃቄ ይደረግ!

የአንድ አገር ሉዓላዊነት ባለቤት ሕዝብ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ከምንም ነገር በላይ የአገር የሥልጣን ባለቤት ሕዝብ ነው ማለት ነው፡፡ እንደ እኛ ባለ አገር መቼም ቢሆን ምርጫ ሲከናወን የሥልጣን ባለቤት ሕዝብ መሆኑ ተክዶ አያውቅም፡፡
9f82c54a890bb560467ea1718ee4a9e5_Lነገር ግን ሕዝብ ወሳኝ ሊሆንባቸው በሚገባ የምርጫ ሒደቶች ውስጥ ከሕዝቡ ይልቅ ጎልተው የሚታዩት የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ ምንም እንኳ የሕዝብ ድጋፍ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች መሆናቸው ቢታመንም፣ በትንሽ በትልቁ በሚደረጉ ክርክሮችና ውዝግቦች የሕዝቡ ድምፅ ዝቅተኛ ሆኖ በጉልህ የሚሰማው የፓርቲዎች ድምፅ ነው፡፡ ሕዝብ ዳር ቆሞ ተመልካች ሳይሆን ወሳኝ መሆኑ አጽንኦት ሊሰጠው ይገባል፡፡
ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሁሌም ወሳኝ የሆነው የፖለቲካ ምኅዳሩ ጉዳይ ነው፡፡ ምኅዳሩ ሲሰፋና ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት ሲንቀሳቀሱ ለመራጩ ሕዝብ ይበጃል፡፡ በአንፃሩ ምኅዳሩ ጠቦ አማራጭ ሳይኖር ሲቀር ምርጫ ጣዕም አልባ ይሆናል፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ሰፍቶ ፓርቲዎች በነፃነት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ፣ ምርጫ በእውነትም ትክክለኛው የውሳኔ መስጫ ሒደት ይሆናል፡፡ ሕዝብም የፈለገውን ፓርቲ ያለምንም መሸማቀቅ በነፃነት የመምረጥ መብቱ ይከበርለታል፡፡
አገሪቱ ባለፉት ሃያ ዓመታት አራት በውዝግብ የተቋጩ ምርጫዎችን አካሂዳ አሁን ለአምስተኛው ጠቅላላ ምርጫ በዝግጅት ላይ ናት፡፡ ምርጫ በመጣ ቁጥር የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሕዝብ ታዛቢዎች ምርጫ፣ ከዕጩዎች ምዝገባ፣ ከመራጮች ምዝገባ፣ ከምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ እስከ ድምፅ መስጠት ቀንና ውጤት ይፋ መሆን ድረስ ለወራት በተለያዩ ሥራዎች ይጠመዳሉ፡፡ በእነዚህ ሒደቶች ውስጥ በርካታ ጭቅጭቆችና ውዝግቦች ይከሰታሉ፡፡ ግጭቶች ይካሄዳሉ፡፡ የሰው ሕይወትም ይጠፋል፡፡ እነዚህ አሳዛኝ ድርጊቶች በተደጋጋሚ ተከስተዋል፡፡
በአገራችን በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለልተኝነት ላይ ከሚነሱ ጥያቄዎች ጀምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ገዥው ፓርቲ ጭቅጭቃቸው አሁንም እንዳለ ነው፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ ምኅዳሩ ጠቦ ጠቦ በፍፁም የማይላወሱበት ደረጃ ላይ መሆናቸውን በስፋት እየገለጹ ነው፡፡ በአንድ በኩል ከገዥው ፓርቲ፣ በሌላ በኩል ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጫና እየደረሰብን ነው እያሉ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲና ምርጫ ቦርድ ይህንን አቤቱታ እያጣጣሉ ናቸው፡፡ እንዲህ ዓይነት ፈፅሞ የማይጣጣም ቅራኔ ባለበት ሁኔታ ምርጫ ማካሄድ በጣም ከባድ ነው፡፡ የከበደውን ለማቅለል ከተፈለገ ዴሞክራሲ ሒደቶችን ለመተግበር ምን ያቅታል?
እንደሚታወቀው ከ17ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በሥራ ላይ ያለው ዘመናዊው የውክልና ዲሞክራሲ ገቢራዊ መሆን የጀመረው በምርጫዎች አማካይነት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሒደት ደግሞ የሚሠራው መንግሥት ለመመሥረት ብቻ ሳይሆን ለተለያዩ የግል የቢዝነስ ተቋማት፣ ለተለያዩ ዓላማዎች ለሚመሠረቱ ማኅበራት፣ ለበጎ ፈቃደኞች ስብስቦችና ለትላልቅ ኮርፖሬሽኖች ጭምር ነው፡፡ ለዚህም ነው ምርጫ የብዙኃኑን ሕዝብ ወኪሎች ለመምረጥ እንደ ሁነኛ መሣሪያ የሚታየው፡፡ ምርጫም ነፃ፣ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒ የሚሆነው በተወዳዳሪዎች መካከል እኩል የመፎካከሪያ ሜዳ ሲኖር ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ምርጫ አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በምርጫ ቦርድና ዋነኛ በሚባሉት የተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል እየታየ ያለው ውጥረት የተሞላበት ግንኙነት መርገብ ይኖርበታል፡፡ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ነፃና ፍትሐዊ አድርጌ አስፈጽማለሁ ሲል ቢያንስ ቢያንስ የፖለቲካ ፓርቲዎቹን በቅርበት ማነጋገር አለበት፡፡ አለ የሚሉትን ችግር መስማት ይኖርበታል፡፡ የገለልተኝነቱ ጥያቄ እንዳለ ሆኖም የምርጫው ተዋናዮች እስከሆኑ ድረስ ሊደመጡ ይገባል፡፡ ከሕጋዊና ከሰላማዊ ጥያቄዎቻቸው በተጨማሪ በምርጫ እንቅስቃሴያቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ መሰናክሎች እንዳይጋረጡባቸው መከላከል አለበት፡፡ ለምርጫው ሰላማዊነት፣ ነፃነት፣ ፍትሐዊነትና ተዓማኒነት የሚጠቅመው ይህ ዓይነቱ መንገድ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ሕጎችን አስከብራለሁ ሲል ሁለገብ የሆኑ ጥያቄዎችን በብቃት ሊመልስ የግድ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ‹‹በሆደ ሰፊነት…›› እያለ የሚገልጻቸው አባባሎች ግራ ያጋባሉ፡፡
ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ መንግሥት እንደመምራቱ መጠን ለምርጫው ስኬት ከልቡ ካልተነሳ ለዓመታት የዘለቁ ችግሮች ተባብሰው ይቀጥላሉ፡፡ በምርጫ ተሳታፊነቱ ራሱን እንደ አንድ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲ ማየት ከተሳነው ችግር አለ፡፡ ሠራዊቱንና የፀጥታ ኃይሎችን በሕገ መንግሥቱ መሠረት ገለልተኝነታቸውን መጠበቅ፣ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት በምንም ዓይነት ሁኔታ ለምርጫ ቅስቀሳ እንዳይውል ማድረግ፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ከመድፈቅ መታቀብና ምርጫው ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የበኩሉን ሚና መጫወት አለበት፡፡ በርካታ የተለያዩ ፍላጎቶችና ስሜቶች ባሉበት አገር ውስጥ አንድ ፓርቲ ሁሉንም ጠቅልሎ ወሰደ ሲባል ያስነቅፋል፡፡ ምርጫ ትርጉም ከማጣቱም በላይ ባይኖርስ ያስብላል፡፡ ይህ ዓይነቱ መንፈስ ደግሞ በዚህ ዘመን ተፈላጊ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ የኋላ ቀርነት ምልክትም ነው፡፡
የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዲሰፋ ሲፈለግ የአገሪቱ ዴሞክራቲክ ተቋማት በሙሉ ከምንም ነገር ነፃ መሆን አለባቸው፡፡ ምንም እንኳ ነፃነት በምሉዕነት ተሟልቶ ሊገኝ ይችላል ተብሎ ባይታመንም፣ ቢያንስ ቢያንስ እነዚህ ተቋማት የገለልተኝነት ሚናቸውን እንዲወጡ መደገፍ ያስፈልጋል፡፡ ሚዲያውም ከወገንተኝነት ነፃ ሆኖ የምርጫውን እንቅስቃሴ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው እንዲዘግብ የማመቻቸት ትልቁ ኃላፊነት የመንግሥት ነው፡፡ ይህ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ የሚታመንበት እንደሆነ ተደጋግሞ ቢነገርም፣ በተግባር ባለመረጋገጡ ለምርጫ ሒደት እንቅፋት ሆኗል፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ መስፋት የሚፈለገውም ለዚህ ነው፡፡
ለምርጫ እንደ ፈተና ከሚታዩ ችግሮች መካከል አንዱ የሕግ የበላይነት ደካማ መሆን ነው፡፡ በብዙ ታዳጊ አገሮች ምርጫዎች ዓለም አቀፍ ደረጃን ያልጠበቁ ናቸው የሚባለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ምርጫ ነፃና ፍትሐዊ እንዲሆን ሲፈለግ ከምንም ነገር በላይ የሕግ የበላይነት ክብደት ሊሰጠው ይገባል፡፡ የሕግ የበላይነት ሲኖር የፖለቲካ ምኅዳሩ ይሰፋል፡፡ ምርጫም ነፃና ዴሞክራሲያዊ ይሆናል፡፡ ተወዳዳሪ ፓርቲዎችም ለሕግ ተገዥ ይሆናሉ፡፡ መንግሥት የአገሪቱ ሕገ መንግሥትና ሌሎች ተያያዥ ሕጎችን ማክበርና ማስከበር አለበት፡፡ ሕጎች ባልተከበሩት ስለዴሞክራሲያዊ ሥርዓትም ሆነ ስለምርጫ መነጋገር ፋይዳ የለውም፡፡ የሕግ የበላይነት መኖር ወሳኝ ነው፡፡
የፖለቲካ ምኅዳሩን በማጥበብ በኩል ከገዥው ፓርቲ በተጨማሪ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም የራሳቸው ድርሻ አላቸው፡፡ ገዥው ፓርቲ ችግሮች አሉበት ሲባል የተገዳዳሪዎቹም መጠቀስ አለበት፡፡ ይህ የሚጠቅመው ደግሞ ጉድለቶቻቸውን አርመው ወደ ምርጫ እንዲገቡ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች ከአደረጃጀታቸው፣ ከአቻ ፓርቲዎች ጋር ባላቸው ግንኙነት፣ ዓላማቸውን በበቂ ሁኔታ ለሕዝብ በማሳወቃቸው፣ ውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲን ተግባራዊ በማድረጋቸው፣ እርስ በርስ በመጠላለፋቸው፣ ወዘተ ያላቸው ይዞታ መመርመር አለበት፡፡ ሕዝቡን ግራ የሚያጋቡ ብዙ ችግሮች አሉባቸውም፡፡ ውጫዊ ችግሮችን ከሚፈቱባቸው ሥልታዊ አካሄዶች ድክመት አንስቶ የተለያዩ ተግዳሮቶች ይታዩባቸዋል፡፡ በመተባበር፣ በመቀናጀት፣ ግንባር በመፍጠርና በመዋሀድ ሒደቶች ውስጥ በሚፈጥሯቸው ችግሮች ምክንያት ሲጠላለፉ ይታያሉ፡፡ ለችግሮች መፍትሔ በማፈላለግ በኩልም አዝጋሚ ናቸው፡፡ የገዥውን ፓርቲ ጫና ብቻ እየተረኩ ሌሎችን ድክመቶች ያድበሰብሳሉ፡፡ የዳያስፖራው ተፅዕኖ እግር ተወርች ሲያስራቸው በፅናት ሲታገሉ አይታዩም፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች ለፖለቲካ ምኅዳሩ መስፋት ጥርሳቸውን ነክሰው መታገል ሲችሉ ይብረከረካሉ፡፡ አንዳንድ ወገኖች የተቃዋሚዎች ችግር ለምን ይነሳል ይላሉ፡፡ በዚህ ዓለም ፍፁምነት የለምና ለሰላማዊ ፖለቲካ ትግሉ መሳካት ራሳቸውን በቅጡ ቢያዩ ይበጃቸዋል፡፡ አንድ ነገር ላይ ብቻ በማተኮር ጊዜያቸውን በማጥፋት የፖለቲካውን መንገድ መሳት የለባቸውም፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዲሰፋ ሲፈልጉ ማንኛውንም ችግር ችለው መልፋት አለባቸው፡፡
የመጪው ግንቦት ምርጫ ከወዲሁ ሲገመገም ካሁኑ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ መፍትሔ ያሻዋል እንላለን፡፡ በተደጋጋሚ ምርጫው ነፃ፣ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒ ይሆናል ሲባል በተግባር መረጋገጥ አለበት፡፡ ኢትዮጵያ አገራችን የአብሮ የመኖርና የመቻቻል ተምሳሌት በመሆኗ ወሳኙ ሕዝብ ሊከበር ይገባዋል፡፡ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ከሚያስፈልጉ ግብዓቶች አንዱ ሕጋዊ ምርጫ ሲሆን፣ ይህ ምርጫ የሕዝባችንን ፍላጎት የሚያማክል መሆን አለበት፡፡ ሕዝብ የሥልጣን ምንጭ እስከሆነ ድረስ ድምፁ ሊከበር እንደሚገባ ሁሉ፣ የምርጫ ሒደቱም ከእንከን የፀዳ እንዲሆን የሚመለከታቸው ወገኖች ሁሉ መረባረብ አለባቸው፡፡ ዳር ሆኖ ግለት መፍጠር ሳይሆን እውነተኛ ምርጫ እንዲኖር አስተዋጽኦ ማድረግ የአገር ወዳድ ዜጎች ኃላፊነት ነው፡፡ ለዚህም ነው የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዳይጠብ ጥንቃቄ ይደረግ የሚባለው