Wednesday, January 14, 2015

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ_ክርስቲያን ይዞታዎችና በአማኞቿ ላይ በልማት ሰበብ የሚፈጸመውን ግፍና በደል አጥብቀን እናወግዛለን::

Ethiopian Orthodox Churchesበኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ_ክርስቲያን ይዞታዎችና በበዓላት ማክበሪያ ሥፍራዎች እንዲሁም በእምነቷ ተከታዮች ላይ በልማት ሽፋን የሚፈጸመውን የቦታ ቅሚያና የክርስቲያኖች ግድያ በማስመልከት ከዓለም ዓቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ_ክርስቲያን እምነት ተከታዮች አንድነት የወጣ መግለጫ
 “እንግዲህ አትፍሩአቸው የማይገለጥ የተከደነ የማይታወቅም የተሰወረ ምንም የለምና:: በጨለማ የምነግራችሁን በብርሃን ተናገሩ:: በጆሮም የምትሰሙትን በሰገነት ላይ ስበኩ:: ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ:: ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ:: ስለዚህ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት ዕመሰክርለታለሁ:: በሰው ፊትም የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለሁ::” የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ፲ ከቁጥር ፳፮ እስከ ፴፫
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ_ክርስቲያን ከተመሰረተችበት ጊዜ ጀምሮ ሕልውናዋን የሚፈታተን የጠላት ጦር በተለያየ መልኩ ሲወረወርባት የቆየ ሲሆን ዛሬም የሰይጣንን ተልዕኮ በሚያስፈጽሙና እኩይ ተግባር የዘወትር ሥራቸው በሆነ ቡድኖች የሚሰነዘርባት ጥቃት በከፋ መልኩ እንደቀጠለ ነው:: ይልቁንም ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን የመምራት ሥልጣኑን ከተቆጣጠረበት ጊዜ አንስቶ ክልላችሁ እዚህ አይደለም፣ በዚህ አካባቢ መኖር አትችሉም ተብለው ዘራቸው ምክንያት ሆኖ ወደ ገደል የተጣሉት፣ ከነቤታቸው የተቃጠሉት፣ አንገታቸውን የተቆረጡት፣ በመትረየስ የተረሸኑት፣ በድብደባ አካላቸውን ያጡት፣ በአጠቃላይ በተለያየ የጭካኔ ተግባር ሕይወታቸው ያለፈና አካለ ጎደሎ የሆኑ ክርስቲያኖች እጅግ ብዙ ናቸው::
ይህ የጭካኔ ተግባር አሁን ደግሞ የልማት ሽፋን ተሰጥቶት ገዳማውያን አባቶች ከበአታቸው እንዲወጡ፣ ምዕመናን ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ፣ ቅድስት ቤተ_ክርስቲያናችን ይዞታዋን እንድታጣ፣ በዓል ማክበሪያዋን እንድታጣ እየተደረገ ነው:: ለዚህም በአዲስ አበባና በሌሎቹም የሀገሪቱ ክፍሎች በየጊዜው የሚሰማው ቅድስት ቤተ_ክርስቲያናችን ላይ ተነጣጥሮ የሚፈጸመው አረመኔያዊ ተግባር በቂ ምሥክር ነው:: ሰሞኑንም በባህር ዳር ከተማ ውስጥ የታቦት ማደሪያ ቦታችን አይነካ ብለው ጥያቄ ይዘው ከወጡ ሰላማዊ ሰልፈኞች ኦርቶዶክሳውያን መካከል ከአራት በላይ ሰዎች በመንግሥት ታጣቂዎች መገደላቸውና በእድሜ የገፉ መነኵሴ እናት ሳይቀሩ መደብደባቸው መንግሥት በቅድስት ቤተ_ክርስቲያናችንና በተከታዮቿ ምዕመናን ላይ ለሚያደርሰው ግፍና በደል ጉልሕ ማስረጃ ነው::
በእውነቱ እንደዚህ ዓይነቱ ወገን በወገኑ ላይ ሊፈጽመው የማይገባ ጭካኔ የተሞላበት ዘግናኝ ድርጊት ሊወገዝ የሚገባው ሰይጣናዊ ተግባር በመሆኑ ዓለም ዓቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ_ክርስቲያን እምነት ተከታዮች አንድነት አባላት በሙሉ አጥብቀን እናወግዘዋለን:: በተጨማሪም ይህንን በሰውም ሆነ በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያስጠይቅ ወንጀል የፈጸሙ ባለሥልጣናትና ግለሰቦች ለፍርድ እንዲቀርቡ አበክረን እንጠይቃለን::
በመጨረሻም እነዚህ በባሕር ዳር ከተማ ስለ ሃይማኖታቸው ሲሉ የሞቱትም ሆነ የተደበደቡት እንዲሁም በእስር ቤት መከራና ሥቃይ እየተፈጸመባቸው የሚገኙት ኦርቶዶክሳውያን ሁሉ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሰማዕታት እንደመሆናቸው መጠን ደማቸው ከንቱ ሆኖ እንደማይቀርና መከራና ሥቃያቸውም ሰማያዊ ዋጋ እንዳለው የምናምን ሲሆን የንጹሃንን ደም የሚያፈሱትና በሕዝብ ላይ ግፍና በደል የሚፈጽሙት ደግሞ የክፉ ሥራቸውን ዋጋ ከእውነተኛው ዳኛ ከልዑል እግዚአብሔር እንደሚቀበሉ ምንም ጥርጥር የለንም:: ምክንያቱም ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ በየመግለጫዎቻችን እንደገለጽነው ቅድስት ቤተ_ክርስቲያንን የሚቃወሙና በምዕመናኖቿ ላይ ግፍ የሚፈጽሙ እንዲሁም ገዳማውያን አባቶችን ከበአታቸው የሚያፈናቅሉና የሚያሳድዱ ሁሉ ውጊያቸው ከጌታችንና ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነውና::
ለሐዋርያነት ከመመረጡ በፊት የክርስቲያኖች አሳዳጅና የቤተ_ክርስቲያን ጠላት የነበረው ቅዱስ ጳውሎስ ወይም በቀድሞ ስሙ ሳውል ወደ ደማስቆ ሲሔድ በመንገድ ያጋጠመው ይህን ያረጋግጥልናል:: ቃሉ እንደሚከተለው ነው፦
“ሲሔድም ወደ ደማስቆ በቀረበ ጊዜ ድንገት በእርሱ ዙሪያ ከሰማይ ብርሃን አንጸባረቀ በምድርም ላይ ወድቆ ሳለ ሳውል ሳውል ስለምን ታሳድደኛለህ የሚለውን ድምጽ ሰማ:: ጌታ ሆይ ማን ነህ? አለው:: እርሱም አንተ የምታሳድደኝ እኔ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ፤ የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል አለው::” የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ፱ ከቁጥር ፫ እስከ ፮
ስለዚህ የመንግስት ባለሥልጣናትም ሆኑ ሌሎች ግለሰቦች በአጠቃላይ በቅድስት ቤተ_ክርስቲያንም ሆነ በኦርቶዶክሳውያን ላይ ግፍና በደል የሚፈጽሙ የሃይማኖታችን ተጻራሪዎች ሁሉ ይህንን የእግዚአብሄር ቃል በመመልከትና የፊተኞቻቸው የሆነባቸውን በማስታወስ ወደ ልባቸው ተመልሰው ቆም ብለው በማሰብ ከክፉ ሥራቸው እንዲታቀቡ እንደተለመደው ለማሳሰብ እንወዳለን::

ልዑል እግዚአብሔር ሀገራችንን ኢትዮጵያንና ቅድስት ቤተ_ክርስቲያናችንን
ይጠብቅልን::
አሜን
ታኅሳስ ፳፯ ቀን ፳፻፯ ዓ/ም

No comments:

Post a Comment