ዛሬ ስለ አማራጭ መኖር ጥቅም እንዳነሳ የገፋፋኝ በቅርቡ ለቁልቢ ባህል በድሬዳዋ ከተማ ተገኝቼ የተመለከትኩት የቢራ ዋጋ ነው፡፡ ለወትሮ በቁልቢ ሰሞን ብዙም ባይሆን አንድ አንድ ጭማሪዎች ይታዩ ነበር፡፡ በዘንድሮ ግን በአብዛኛው ተጠቃሚ በሚያዘወትራቸው ሆቴሎችና ግሮሰሪዎች “የጃንቦ ድራፍት ዋጋ ዋጋ ብር 6 መሆኑን እናስታውቃለን” የሚል ማስታወቂያ ተመለከትኩ፡፡ ይህ የዋጋ ለውጥ ለምን መጣ ብሎ ሲጠየቅ መልሱ ቀላል ነው፡፡ የአማራጭ ቢራ አቅራቢዎች ወደ ገበያ መግባት ብቻ ሳይሆን፤ በመንግስት ቁጥጥር ስር የነበሩት የቢራ ፋብሪካዎች ወደ ግል ከመዛወራቸው ጎን ለጎን የግል ፋብሪካዎች ቁጥር መጨመሩ ዋነኛው ምክንያት ነው፡፡ እነዚህ የቢራ ፋብሪካዎች፣ ገበያውን ለመቆጣጠር ዋጋቸው ላይ ማስተካከያ ማድረግ ግድ ሆኖባቸዋል፡፡ የተገደዱት መንግስት ባወጣው መመሪያ ሳይሆን ፋብሪካዎቹ እያመረቱት ያለው ምርት አቅርቦት በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በቅርቡ ወደ ገበያ የገባው፤ “ዋሊያ” በመባል መታወቅ የጀመረው ቢራ ፋና ወጊ ነው፡፡ አንድ ጓደኛ “ኢትዮጵያ በምግብ እህል እራሷን ከመቻሏ በፊት በቢራ እራሷን የቻለች ሀገር ነች” ይላል እኔም ይሄን አስተያየት እጋራለሁ፡፡ ለቅንጦት ካልሆነ ቢራ ከውጭ ኢትዮጵያ ማስገባት የግድ ስለማይላት ማለቴ ነው፡፡
እርግጥ ነው በሀገራችን የነፍስ ወከፍ የቢራ ፍጆታ አሁንም አነስተኛ ቢሆንም፣ ከወተት ይልቅ ቢራ በብዛት በገበያ የሚታይባት ሀገር እንደሆነች የእለት ከእለት ህይወታችን ይመሰክራል፡፡ ይህ የአቅርቦት መሻሻል በቢራው ዘርፍ ለውጥ እያመጣ እንደሆነ ቢታመንም ልጆቻችን በሚፈልጉት በወተት መስክም ሊሳካ የማይችልበት አንድም ምክንያት የለም፡፡ ለዚህ ዘርፍ መስፋፋት፣ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮ ሁሉም በየገበታው ወተት ያገኝ ዘንድ መንግስት ምቹ ፖሊሲና ስትራቴጂ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ ልጆቻችን ወተት እንዲያገኙና ጤናማ ዜጎችን ለማፍራት ከወተት የሚሰበሰብ ታክስ ቢቀርብን ምን ይለናል?
አንባቢዎች ታስታውሳላችሁ ብዬ የምገምተው፤ ስለ የገበያ ውድድር በምክር ቤት ሆኜ ሳነሳ እንደ ምሳሌ የማነሳው ሲሚንቶን ነው፡፡ “ሲሚንቶን የታደገ የነፃ ገበያ፤ ሌሎቹንም እንዲታደግ” በሚል ዘወትር እጠቅሰዋለሁ፡፡ ሁላችሁም እንደምታስታውሱት፤ “ደርባ ሲሚንቶ” ፋብሪካ፣ ወደገበያ ገብቶ የሲሚንቶ ገበያውን እስኪለውጠው ድረስ ቀደም ብለው የነበሩት ሲሚንቶ ፋብሪካዎች የተለያየ ሰበብ እየፈጠሩ ዋጋውን ሲቆልሉት እንደ ነበር ይታወሳል፡፡ እነዚህ ፋብሪካዎች፣ የመንግስት እና የፓርቲ ንብረት እንደ እንደነበሩ ልብ ማለት ይገባል፡፡ ሲሚንቶ ለማምረት የሚያስፈልጉት ግብዓቶች አንዳቸውም በገበያ ላይ ቅናሽ ባላሳዩበት ሁኔታ፤ የአቅርቦት መሻሻል ብቻ በሲሚንቶ ዋጋ ላይ ያመጣውን ከፍተኛ የዋጋ ለውጥ ማንም የሚረዳው ነው፡፡ የሲሚንቶ አቅርቦት ዝቅተኛ በሆነበት ጊዜ ስንቶቹ ለዘረፋ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸው እስከአሁን ድረስ በሙስና ክስ በወህኒ እንደሚገኙም እናውቃለን፡፡ በአቅርቦት ማነስ፣ በሸማቾች ላይ በዋጋ ንረት ከሚደርሰው ጉዳት በተጨማሪ፣ ጥቂቶች ደግሞ በሙስና እንዲጨማለቁ እድል ሰጥቶዋቸው ነበር፡፡ የነፃ ገበያ ስርዓት፣ ብዙ ችግሮችን ሊቀርፍልን ይችላል የሚል እምነት ያለን ለዚህ ነው ፡፡
እንደምታውቁት ብዙ ስኳር ፋብሪካዎች በመንግስት እየተገነቡ ነው፡፡ እነዚህ የስኳር ፋብሪካዎች ተጠናቀው ስራ ሲጀምሩ፣ አሁን በቢራ ላይ መታየት የጀመረው ለውጥ ቀደም ሲልም በሲሚንቶ ያገኘነውን የነፃ ገበያ ትሩፋት ልናገኝ እንችላለን የሚል እምነት የለኝም፡፡ የስኳር ዋጋ ባለበት ከፍተኛ ደረጃ እንዲቀጥል ይደረጋል ብዬ ነው የማምነው፡፡ ይልቁንም በሀገር ውስጥ ምርቱ ትርፍ ቢሆን እንኳ ወደ ውጭ በርካሽ ተልኮ የውጭ ምንዛሬ ማስገኛ ይደረጋል እንጂ፤ ዜጎች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙት ይደረጋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ የሚገነቡት ፋብሪካዎች የመንግስት ናቸው፡፡ እነዚህን ፋብሪካዎች የሚመሩት አካላት፣ በምርቱ ላይ ባላቸው ቁጥጥር የተነሳ፤ ምንናአልባትም እንደ ቴሌ “የሚታለብ ላም” ተብሎ ከሚመደቡት ተቋማት እንደ አንዱ ይቆጥሩታል፡፡
በህገ-ወጥ መንገድ ያገኙትን ገቢ አስልተው፣ ትርፍ በትርፍ ሆንን ሊሉን ይችላሉ፡፡ አንባቢ መረዳት ያለበት መንግስት በንግድ ውስጥ ሲገባ፣ በተለይ ደግሞ በዋነኝነት ሲቆጣጠረው ውድድር የሚባለውን ነገር አጥፍቶ በኢኮኖሚክስ፤ “ሞኖፖሊ” የሚባለውን መጥፎ የገበያ ስርዓት ይዘረጋል፡፡ መንግስት ዋና ተግባሩ “ሞኖፖሊ” እንዳይኖር መቆጣጠር መሆኑ ቀርቶ፣ በመንግስት የሚመራ “ሞኖፖሊ” ዘርግቶ ህዝብን ይዘርፋል ማለት ነው፡፡
ከላይ ያነሳኋቸው ነጥቦች በሀገራችን ኢኮኖሚ ውስጥ የነፃ ገበያ በስርዓቱ ቢተገበር፣ ዜጎች ምን ያህል ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ጉልህ ማሰያዎች ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ አማራጭ እና ውድድር ሲኖር፣ ሸማቾች ጥራት ያለው ምርት እንዲያገኙ እድል ይሰጣል ማለት ነው፡፡
ከላይ ያነሳኋቸው ነጥቦች በሀገራችን ኢኮኖሚ ውስጥ የነፃ ገበያ በስርዓቱ ቢተገበር፣ ዜጎች ምን ያህል ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ጉልህ ማሰያዎች ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ አማራጭ እና ውድድር ሲኖር፣ ሸማቾች ጥራት ያለው ምርት እንዲያገኙ እድል ይሰጣል ማለት ነው፡፡
በተመሳሳይ፣ በፖለቲካው መስክም መንግስታችን አማራጭ እንዳይኖረን ሰንጎ ይዞናል፡፡ የኢትዮጵያ ሀገራችን የፖለቲካ አልፋና ኦሜጋ፣ “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” ብቻ ነው እየተባል ነው፡፡ ለይስሙላ የመድበለ-ፓርቲ ስርዓት እንዲገነባ እንፈልጋለን ቢባልም፣ በተግባር ግን የመድበለ-ፓርቲ ስርዓት የሚፈልጉትን መደላድሎች በማጥበብና በመዝጋት፣ ገዢው ፓርቲና መንግስት የፖለቲካ “ሞኖፖሊ” ለማስፋፋት በቁርጠኝነት ተሰልፈዋል፡፡ ለዚህም የቅርብ ምሣሌ የሚሆነው የመንግስት ስትራቴጂ ለህዝብ ማስጨበጥ በሚል የሽፋን ስም በመላው ሀገሪቱ ዜጎችን በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ለማጥመቅ እየተሄደበት ያለው መንገድ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር ይህ ካለፈው ዓመት ማገባደጃ ጀምሮ በዘመቻ መልክ የአብዮታዊ ዴሞክራሲን በህዝብ ዘንድ ለማስረፅ የተሄደበት መንገድ፣ የህዝብን ሀብት ከማባከን ውጭ የታለመለትን አብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብን ገዢ የማድረግ ትልም ያሳካ ነው የሚል ግምገማ የለኝም፡፡ ይህ ዜጎችን አማራጭ የማሳጣትና ፖለቲካውን በ “ሞኖፖል” የመያዝ ፍላጎት፣ ዞሮ ዞሮ ይህችን ሀገር አላስፈላጊ አዙሪት ውስጥ ከመክተት ውጪ የተሳካ የፖለቲካ ስርዓት ለመገንባት ያስችላል የሚል እምነት የለኝም፡፡
በግሌ፣ እንደ አንድ ንቁ የፖለቲካ ተሳታፊ ባለፈው የተደረገውን እና አሁን በመደረግ ላይ ያለውን አብዮታዊ ዲሞክራሲን በህዝቡ ውስጥ የማስረፅ እንቅስቃሴ፤ አማራጭ ይዘን የሀገራችን ፖለቲካ ምርጫ ይኑረው ለምንል ዜጎች እንደ አንድ ጥሩ እድል ወስጄዋለሁ፡፡ ገዢው ፓርቲ፣ በመንግስትነት ያለውን መስመር ያለአግባብ ተጠቅሞ የሄደበት መንገድ፣ በቀጣይ ገዢው ፓርቲ ይህን ይመስላል የሚለውን ስራችንን አቅልሎታል፡፡ ቀጣዩ ስራችን የራሳችንን አማራጭ በማቅረብ፣ ህዝቡ ‘ይበጀኛል’ የሚለውን እንዲመርጥ ማድረግ ነው፡፡ ጊዜያችንን ማሳለፍ ያለብን ገዢው ፓርቲ በመንግስትነቱ ለዜጎች ነፃነት፣ ለነፃ የኢኮኖሚ ስርዓት ግንባታ፣ ለህገ-መንግስታዊ ስርዓት መከበር፣ ለህግ የበላይነት፣ ወዘተ የዘጋውን በር እንዴት አድርገን እንደምንከፍተው እና ዜጎች አማራጭ ያላቸው መሆኑን በማስገንዘብ መሆን ይኖርበታል፡፡
በቀጣዩ የ2007 ምርጫ አንድነት ፓርቲ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የኢህአዴግ የፖለቲካ “ሞኖፖሊ” መሰበር አለበት ብሎ ያምናል፡፡ ነገር ግን ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድ ጊዜ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ወግድ ብሎ ሲያበቃ፣ የአንድነትን ሊብራል ዲሞክራሲ ይመርጣል ማለት አይደለም፡፡ ሁለቱም የፖለቲካ አማራጮች ምንናአልባትም ሌሎችም አማራጮች ተጨምረው በፖለቲካ ገበያው ውስጥ ስፍራ ያገኛሉ ማለት ነው፡፡ ዜጎች፣ የተመቻቸውን በመምረጥ ቢያንስ በህገ-መንግስት በግልፅ የተቀመጡትን የመደራጀት፤ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ፣ በመላው ሀገሪቱ ተንቀሳቅሶ የመስራትና የመኖር፣ ከሁለም በላይ ሀሉም ሰው በህግ ፊት እኩል የሚታይበት ስርዓት ለመዘርጋት፣ ወዘተ.. እድል ይፈጠራል፡፡
ይህ አማራጭ ያለው የፖለቲካ ስርዓት በፖለቲካ ገበያው ውስጥ እንዲኖር ምቹ ሁኔታ መፍጠር የመንግስት ዋነኛ ተግባር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህ ሳይሆን ሲቀር እንዲሆን የማድረግ ሀይል ያለው ግን በዜጎች ቁጥጥር ስር ነው፡፡ ዜጎች፣ በሀገራችን በውድድር ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ስርዓት እንዲኖር ቁርጠኛ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚሁም ዛሬ ነገ ሳይሉ የመራጭነት ካርድ መውሰድ፤ በምርጫው ዕለት ተገኝቶ ድምፅ መስጠት እና ድምፁን ማስከበር አለባቸው፡፡ ይህ ደግሞ ይቻላል፡፡ የህዝብ ኃይል ከምንም ኃይል በላይ ነው!!!!
ቸር ይግጠመን!!
No comments:
Post a Comment