የብርቱካንን ሙሉ ቃል በድምጽ የተደመጠውን ለማዳመጥ እድል ለማያገኙ፣ ድምጿንም፣ መልእክቷንም ሲናፈቁ ለነበሩ ዜጎች መልእክቱ እንዲደርሳቸው በማሰብ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ መወያያ መድረክ ንግግሯን እንዳለ በጽሑፍ ከዚህ እንደሚከተለው ያቀርባል::
ንግግሯን ከማቅረባችን በፊት ግን አንባቢያን በአይነ ህሊናችሁ ሁኔታውን ለመቃኘት ያመቻችሁ ዘንድ ጥቂት ማለት እንፈልጋለን።
“መሪ ይፈጠራል እንጂ አይወለድም” ፍጡር ደግሞ አስትንፋሱ እስክትቋረጥ ድረስ ያው ፍጡር ነውና በህያውነት የተፈጠረበትን ተግባር ማከናወን ይቀጥላል:
ብርቱካን መሪ ሆና ተፈጥራለች፣ በመሪነት ተቀጥላለች።
በባህላችን ጀግና ይፈጠራል እንጂ መሪ ይፈጠራል የሚል አባባል የተለመደ አደለም: ገዥ እንጂ መሪ ኖሮን ስለማያውቅ ይሆን? ወይስ መሪነት ከእግዚአብሄር ተቀበቶ የሚሰጥ ጸጋ ስለሆነ፣ ወይም ታሪክ ሓላፊነት የሚጥልበት ስለሆነ? አለዚያም መሪነት የሚገኘው በትግል አሸንፎ ነው ስለሚባል?
መልሱን አንባቢያን እንዲያሰላስሉት እንለፈውና ወደ ተነሳንበት አንኳር ጉዳይ እንመለስ። ብርቱካን ተናገረች ንግግሯ አጭር ነው፣ በሕጻናት ቡረቃና ጫወታ የታጀበ ነበር፣ የነገ ተረካቢዎች ናቸውና እሰየው የሚያሰኝ ነው: ከንግግሯ የበለጠ ግን አካላዊ ቋንቋዋ (body language) የበለጠ ጮሆ ይደመጥ ነበር: በእስር ቤት በነበረችበት ጊዜ በአገር ቤት እና በመላው አለም ተበትነው የሚገኙ ወገኖቿ ላደረጉላት ሞራላዊም ሆነ ቁሳዊ ደጋፍ ስታመሰግን፣ አሁንም ወገኖችዋ እያሳዩአት ያለው ፍቅር እንክብካቤ ስትገልጽ በታላቅ ትህትና ከአንገቷ አጎንበሳ ሳይሆን ለጥ ብላ እጅ ነስታ ነበር:: ለህዝብ ያላትን አክብሮት፣ ፍቅር ለመግለጽ ተቸግራ ጭንቅ ጥብብ ስትል ማየት የህዝብ ፍቅር ልክፍት መሆኑን መረዳት ይቻላል::
ከምስጋና ቀጥላ ወደ እለቱ በዓል አላማ ነበር የገባችው: የዛሬው በዓል አላማ ኢትዮጵያዊነትን እናክብር፣ “ሰለብሬት” እናድርግ የሚል ነው: ግን እትዮጵያዊነት መከበር ያለበት ጊዜ ላይ ነን ወይ የሚለውን ጥያቄ ራሷ አንስታ ስትመልሰው፣ ከቃላቶቿ በላይ ፊቷ ላይ ያንዣበበው የሐዘን ዳመና ከውሰጧ ማዕበል የሚንጣት መሆኑን ፍንትው አርጎ ያሳይ ነበር።
ከሐዘኗ መልስ ግን የኢትዮጵያን ታላቅነት ገልጻ፣ ተሰፋን ከራሷ እንድንማር ስትመክር: ካመት በፊት የነበረችባትን ጠባብ ሽንት ቤት አይሏት ባኞ ቤት አስቃኝታን፣ ጥላሁን ሲሞት የደረሰባትን አስታውሳ “ሀዘንም ከሰው ጋር ነው” “የሚሉትን ባላውቀዉም ዋርድያዎቹ ሲነጋገሩ ስሰማ ቀለል ይለኝ ነበር” እነዚህ ቃላቶች ከፊቷ ገጽታ መለዋወጥ ጋር ሲሰሙ አጥንት ድረስ ዘልቆ የመግባት ሓይል ነበራቸው።
በመጨረሻም “አሁንም ተሰፋ አረጋለሁ፣ አሁንም አልማለሁ” ስትል ጸዳሏ እንደገና ፈክቶ ነበር።
አሁን ቀጥታ ወደ ንግግሯ
“ስቴዲየሙ ይዘጋል ብለው በጣም አስፈራርተውኛል! ነገር አላበዛም: እኔ ሁለት ነገር ነው ማለት የምፈልገው:ከሁሉ አሰቀድሞ ቅድምም ለመናገር እንደፈለኩት የዚህን ፐሮግራም አዘጋጆች በጣም አመሰግናለሁ: እግዚአብሄር ያክብርልኝ ስላከበራችሁኝ እላለሁ: ከዚያ በላይ ደግሞ እናንተ ሁላችሁም እዚህ የተገኛችሁም፣ ያልተገኛችሁም ኢትዮጵያውያን ደርሶብኝ በነበረው ችግር ከጎኔ ስለቆማችሁ፣ የማቴሪያል የሞራል እርዳታ ስላርጋችሁልኝ በጣም፣ በጣም፣ በጣም፣ ከልብ፣ ከልብ ላመሰግናችሁ አወዳለሁ።
እውነቴን ነው ለስሜት መግለጫ ሌላ ነገር፣ ልላ ቃላት ቢኖር ጥሩ ነበረ፣ ..ከተፈታሁበት ጊዜ ጀምሮ አገር ውስጥ ያሉ ወገኖቼ፣ በየቦታው አገር ቤትም እያለሁ እዚህም ድረስ መጥተው ያላቸውን ስሜት፣ ለኔ የነበራቸውን ሃዘኔታ፣የጸለዩትን ጸሎት ያደረጉትን ድጋፍ ሲገልጹ እኔም በጣም የሚከብደኝ ነገር ነበረ: እዚህም በናንተ መሃል ተገኝቼ ይህንኑ ነው የተረዳሁት: እኔም ባልነበርኩበት ጊዜ የሆነውን ሁሉን ነገር አውቃለሁ: ዛሬ ሻምበል እኔ ባለሁበት በመዝፈኑ የተሰማውን ስሜት መገመት እችላለሁ ምክንያቱም እያለቀሰ ዘፍኖታል ይህንን ዘፈን: ዘፈኑን መስማት ግን ለኔ በጣም ይከብደኛል ከሚገባኝ በጣም የሚያለፍ ነው ብዬ የምር ስለማምን ነው: አና ሁላችሁም ያደረጋችሁልኝ ፍቅር ያሳያችሁኝ መልካም ስሜት ለኔ ከሚገባኝ በላይ ነው ብዬ ነው የማምነው አሁንም ደግሜ ሁላችሁንም እግዚአብሄር ያክብርልኝ::
ልላ አንድ ነገር መናገር የምፈልገው የዚህ ፕሮግራም ዋና አላማ እንደገባኝ ከሆነ ኢትዮጵያዊነትን ማወደስ የሚል አላማ ያለው ነው: እያሰብኩ ነበረ፣ ኢትዮጵያዊነት ዛሬ ኢትዮጵያ የምትወደስ ነች ወይ? አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት እኛ ያለንበት ሁኔታ የሚወደስ ነገር ነወይ? የሚከበር ነገር ነው ወይ? የሚለውን ነገር ሁላችንም ብንጠይቅ መለሱ አሉታዊ ነው ብዬ አምናለሁ: ምክንያቱም ኢትዮጵያ የነጻነት አገር አደለችም፣ ኢትዮጵያ የፍትህ አገር አደለችም: ኢትዮጵያ አሁንም ዜጎቿ ከድህነት ጋር የሚኖሩባት፣ በእፍረት የሚያቀረቅሩባት፣ እንደናንተ እንደብዙዎቻችሁ በስደት የሚሸሹባት አገር ነች: ስለዚህ አናወድሳት ወይ? ብለን ብንጠይቅ አይ ማወደስስ አለብን ነው መልሱ: ስናወድሳት ግን ምንን አስበን ነው? ኢትዮጵያ ታላቅ ሐገር ነበረች ስለሱ እኔ የምናገረው ነገር አደለም ታሪክ ያሰተምረናል: ግን ኢትዮጵያ ታላቅም ትሆናለች ብለን ማመን እንችላለን ማመንም አለብን በዬ በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ መወደስ አለባት።
ተሰፋ ማድረግ በጣም አሰቸጋሪ እንደሆነ ግን አውቃለሁ: ብዙዎቻችን ፖለቲካ ውስጥ ያለንም የሌለንም፣ ያገራችን ጉዳይ ግድ የሚለን ዜጎች በሙሉ ያየናቸው፣ ያጋጠሙን ነገሮች አገራችን ያለችበትን ሁኔታ ስናይ፣ ስንገመግም የምናገኘው ነገር ተስፋ ለማድረግ በጣም አሰቸጋሪ መሆኑን አውቃለሁ:: ቅድም ክሪስ እዚህ ስለ ሌሎች አገሮች ሲነግራችሁ ነበረ: ብዙ ምሳሌዎች ማነሳት ይቻላል ተሰፋ ለማረግ ምክንያቶች: የሰው ልጆች በታሪክ ውስጥ ያሸነፏቸው ተግባራቶች ማንሳት ይቻላል:
እኔ ግን ተሰፋ ለማረግ እኔን እዩ እላለሁ! ከዛሬ አመት በፊት በጣም ጠባብ የሆነች ክፍል ውስጥ ለብቻዬ ተቀምጬ በብቸኝነት እሰቃይ ነበር: ስቃዩ ደግሞ ዘሬ ስናወራው ሊቀል ይችላል ግን በጣም፣ በጣም ጥልቀት ያለው ስቃይ ነበር: አልረሳውም አንድ ጋዜጠኛ እዚህ እየጠየቀኝ ነበር ስለ ጥላሁን ምን ሃሳብ አለሽ? የሞተ ጊዜ የት ነበርሽ? አለኝ: የሞተ ጊዜማ ባዶ ቤት ነበርኩ፣ የሚያናግረኝ ስው አጥቼ ለማን እንደምተነፍሰው፣ ስለስራው ምን እንደምል? የተሰማኝን ሰሜት ለማ እንደምናገረው ግራ ገብቶኝ ፖሊስ መጥቶ በሬን አስከሚከፍት እጠብቅ ነበር: መቶ በሬን ሲከፍተው ሞተ አደል? ሰማችሁ አደል? ሰማሽ አደል? ስላት ቆልፋብኝ ሄደች: ሀዘንን እንኳ ማዘን የሚቻለው የሚጋራህ ሰው ሲገኝ ነው! እውነቴን ነው የምላችሁ በዚያን ሁኔታ ውስጥ ቁጭ ብዬ የነበረኩበት ነገር ለዘላለም ሊቀጥል እንደሚችል በጣም ብዙ ቀን አሰቤያለሁ: ለብዙ ጊዜ የማያቸው ነገሮች ግድግዳዎች፣ መታጠቢያ ቤት በሉት ሽንት ቤት በሉት በጣም አነስተኛ ነገር አለ: በቆርቆሮ ነው የታጠረው: ያ ቆርቆሮ፣ ከዚያ ደግሞ አልፎ የሚሰማው የዋርድያዎች ድምጽ ዛሬ ስለዋርድያዎች ድምጽ ግን ሳነሳ እንደቅሬታ ሊሆን ይችላል የኔ ግን ትንሽ ያስደስተኝ ነበር: ከጸጥታ የነሱ ድምጽ ይሻለኝ ነበር ምን እንደሚሉ እንኳ ባይገባኝ:
ምን ልላችሁ ነው? ከዛ መከራ ከዛ ብቸኝነት ወጥቼ ዛሬ አንድ ብቻ የነበርኩት በጣም ብዙ በሚወዱኝ ሰዎች መሃከል ተከብቤ እገኛለሁ: ዛሬም ተስፋ አረጋለሁ ስላገሬ፣ ዛሬም ህልም አልማለሁ፣ አጠንከሬ አልማለሁ፣ በናንተ አምናለሁ፣ በራሴ አምናለሁ፣ በልጄ አምናለሁ፣ በሚመጡት የልጅ ልጆች ሁሉ አምናለሁ: ስለዚህ ኢትዮጵያ ታላቅ ነች እላለሁ: ልትወደስ ይገባታል እላለሁ: እናንተም በዚህ ሃሳብ እንደምትስማሙ አምናለሁ: መልክቴ ይኸው ነው: ኢትዮጵያ ልትወደስ የሚገባት ታላቅ ሐገር ነች: ታላቅነቷን ለማየት ግን ሁሌም ተስፋ ይኑረን፣ ሁሌም ባንድነት እንቁም: አንድነታችን ሁሉንም የሚያቅፍ፣ ሁሉንም የሚያሰባስብ፣ የኢትዮጵያን የጋራ መኖሪያነት የሚያወድስ ይሁን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
No comments:
Post a Comment