Tuesday, August 11, 2015

በሞስሊሙ ማኅበረሰብ መሪዎች ላይ የተወሰነውን እስራት ሸንጎ ያወግዛል።

shengoሰኞ  ሐምሌ 27፣ 20017  (ኦገስት 3፣ 2015) በሞስሊሙ ማኅበረሰብ መሪዎች ላይ የህወሓት/ኢህአዴግን ፍላጎት በማስፈጸም የሚታወቀው ፍርድ ቤት ከሰባት ዓመት እስከ 22 ዓመት የሚደርስ እስራት እንደበየነባቸው ይፋ ሆኗል። የሞስሊሙ ኅብረተሰብን የተቃውሞ ድምጽ መሠረት በማድረግ በሰላማዊ መንገድ መፍትሄ በማፈላለግ ተግባር ላይ ተሰማርተው የነበሩት እነአቡበከር አህመድ የታሰሩት ከሁለት ዓመት በፊት የህወሓት/ኢህአዴግ መንግሥት በሙስሊሙ ማኅበረሰብ እምነት ውስጥ ጣልቃ በመግባት አመራሩን ለመቆጣጠርና እሱ የሚፈልገውን የእምነት ፈርጅ ኢትዮጵያውያን  ሞሰሊሞች በግዴታ እንዲቀበሉ ያውጠነጠነውን ሃላፊነት የጎደለው ተግባር እምቢ ማለታቸውን ተከትሎ እንደነበር ይታወሳል። ሸንጎና ሌሎችም እጅግ በርካታ ኢትዮጵያውያን በሀገራችን ውስጥ የሞስሊሙ ማኅበረሰብ መንግሥት በሃይማኖቱ ውስጥ እንዳይገባ ያቀረበውን ጥያቄ በማክበር እጁን እንዲያነሳ በተደጋጋሚ ሲያሳስብ ቆይቷል።  ሆኖም እንደተለመደው ሁሉ ከራሱ ሌላ ማንንም ማዳመጥ ያልለመደው  የህወሓት/ኢህአዴግ ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት ሃላፊነት የጎደለው እርምጃ በሚቆጣጠረው ፍርድ ቤት በኩል ተግባራዊ እንዲሆን አድርጓል። ይህ እርምጃ የሞስሊሙን ኅብረተሰብ የሃይማኖት ነፃነት ጥያቄ ይበልጥ ያጠናክረዋል እንጂ  አያዳክመውም። እንዲያውም የሞስሊሙ ህብረተሰብ አባላትና ሌሎችንም በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ ጥያቄን አቅርቦ በሕግ መብትን ማስከበር አይቻልም ወደሚል መደምደሚያ እንዲደርሱና አላስፈላጊ በሆነ ጎዳና እንዲጓዙ የሚገፋፋ ነው። ይህ ለሀገራችን ሰላምና መረጋጋት የሚረዳ ሳይሆን አደጋን የሚጋብዝ እጅግ ሃላፊነት የጎደለው እርምጃ ነው። ሸንጎው በሞስሊሙ ኅብረተሰብ በመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ላይ የህወሓት/ኢህአዴግ መንግሥት የፖለቲካ መሳሪያ የሆነው ፍርድ ቤት የወሰደውን እርምጃ አጥብቆ ያወግዛል። የሞስሊሙ ኅብረተሰብም መሰረታዊ መብቱን በሰላማዊ መንገድ ለማስከበር በሚያደርገው እንቅስቃሴ የትግል አጋርነቱን ያረጋግጣል። ኢትዮጵያውያን ሁሉ ህወሓት/ኢህአዴግ የሚያካሂደውን በሃይማኖት ነፃነት ላይ ያነጣጠረውን ጥቃት እንዲያወግዝ  ሸንጎ  ጥሪውን ያቀርባል። የህወሓት/ኢህአዴግ ደጋፊዎችም አገዛዙ ከቀን ወደቀን ሀገራችንንና ሕዝባችንን ወደተባባሰ አደገኛ ጎዳና መውሰዱን እንደቀጠለ መሆኑን እንዲገነዘቡ እያሳሰበ፡ በዚህም ምክንያት ለሚከተል አለመረጋጋት ተጠያቂው ህወሓት/ኢህአዴግ እንደሆነ ሁሉም እንዲገነዘበው እናሳስባለን። ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ! - See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/45661#sthash.7MhGvGkq.dpuf

No comments:

Post a Comment