Wednesday, August 26, 2015

ኢሕአዴግ ራሱን ይመልከት! ጋዜጣው ሪፖርተር ርዕሰ አንቀጽ

85e2b2dbb35ca49ffb94675c848f9135_Lኢሕአዴግ አሥረኛውን ድርጅታዊ ጉባዔ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ በመጪው መስከረም ወር አራተኛ ሳምንት ላይ ደግሞ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት አገሪቱን ለመምራት የሚያስችለውን ፓርላማ ሥራ ያስጀምራል፡፡
ላለፉት 24 ዓመታት አገሪቱን በማስተዳደር ላይ ያለው ኢሕአዴግ አሁን ቆም ብሎ በአንክሮ ራሱን መገምገም አለበት፡፡ ውስጡን አብጠርጥሮ መፈተሽ አለበት፡፡ የተሸከማቸውን ጉድፎች አራግፎ በሥርዓት አገር ማስተዳደር አለበት፡፡ በስኬቶቹ የሚመፃደቀው ኢሕአዴግ በጣም በርካታ ጉድለቶች ስላሉት መፍትሔ ያስፈልገዋል፡፡ ኢሕአዴግ ራሱን ያጥራ! ራሱን ይመልከት!
ኢሕአዴግ በአሥረኛው ድርጅታዊ ጉባዔው የመጀመሪያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም በመገምገም፣ ሁለተኛውን ዕቅድ አጠናክሮ ለመቀጠል ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ባለፉት 12 ዓመታት በኢሕአዴግ አመራር የተመዘገበውን ዕድገት ለማስቀጠል፣ ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ለውጥና ትራንስፎርሜሽን ቀጣዩ ትኩረት እንደሚሆንም እንዲሁ ትልቅ ግምት የተሰጠው አጀንዳ ነው፡፡ ይህ ለአገር ጠቃሚ በመሆኑ ድጋፍ ይሰጠዋል፡፡ ነገር ግን ዕድገቱም ሆነ ትራንስፎርሜሽኑ ሰው ሰው ካልሸተተ፣ የዜጎችን መሠረታዊ መብቶች ካላከተተ፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ካልተመቸ፣ የሕዝቡን የነቃና በፍላጎት ላይ የተመሠረተ ተሳትፎ ካላረጋገጠ፣ ሙስናን ከሥሩ መንግሎ ካልጣለ፣ ፀረ ዴሞክራሲ ተግባራትን ካላስወገደ፣ ሕገወጥ ተግባራትን ካላጠፋ፣ ወዘተ ልፋቱ ሁሉ ከንቱ ነው፡፡
አንድ አገር ሰላሟና ብልፅግናዋ ዘላቂና አስተማማኝ የሚሆነው የሕግ የበላይነት በተግባር ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ ዜጎች በሕግ ፊት እኩል መሆናቸውን ሲያምኑ፣ ሕግም ለሁሉም ዜጎች እኩል ጥበቃ ሲያደርግ፣ ፍትሕ ለሁሉም ተደራሽ ሲሆንና የፍትሕ ሥርዓቱ በነፃነት ሲንቀሳቀስ የሕግ የበላይነት መኖሩ ይረጋገጣል፡፡ ‹‹አንድን ንፁኅ ዜጋ ከማሰር ይልቅ አንድ ሺሕ ዜጎችን መፍታት የተሻለ ነው›› የማለው የሕግ ጽንሰ ሐሳብ በአንድ አገር ውስጥ ተግባራዊ ሲደረግ፣ ዜጎች በነፃነት በአገራቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ውስጥ በንቃት ይሳተፋሉ፡፡ ነገር ግን በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት ሰበብ እየተፈለገላቸው በሚከሰሱና በሚታሰሩ ዜጎች ምክንያት አገራችን ውስጥ በፍትሕ ላይ መተማመን ጠፍቷል፡፡ ኢሕአዴግ ይኼ ካላሳሰበው ሌላ ምን ያሳስበዋል? ሰዎች ያለጥፋታቸው ታስረው የቀረበባቸው ክስ የማያወላዳ በመሆኑ በነፃ ሲሰናበቱ አሁን መታየት ጀምሯል፡፡ የአንዳንዶችም ክስ ሲቋረጥም ተስተውሏል፡፡ ከመነሻው እንዲህ ዓይነት አሳዛኝ ተግባር ለምን ይፈጠራል? የፍትሕ ሥርዓቱስ ለምን ይሳጣል? ለሕግ የበላይነት ለምን ቅድሚያ አይሰጥም? ብዙ ማለት ይቻላል፡፡
ዜጎች በገዛ አገራቸው ሰብዓዊ መብታቸው ሲጣስ ዝም ይባላል፡፡ በአመለካከታቸው ምክንያት መደብደብ፣ መታሰር፣ መንገላታት፣ ከሥራ መባረር፣ የቤተሰብ መበተን፣ ወዘተ ሲደርስባቸውና ጩኸቱ ሲበረክት በተደጋጋሚ ተሰምቷል፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላቶቻቸው እንደተገደሉባቸው በተደጋጋሚ ተናግረዋል፡፡ በታዳጊ ዴሞክራሲ ውስጥ የሚያጋጥም ነው እየተባለ ዜጎች በገዛ አገራቸው ሲሰቃዩ እስከ መቼ ይቀጥላል? የመልካም አስተዳደር እጦት ምሬት ከዳር እስከ ዳር ሲያስተጋባ ይሰማል፡፡ ሥራ መሥራት ያቃታቸው ሹማምንት የተመደቡበት ኃላፊነታቸውን መወጣት ሳይችሉ በመቅረታቸውና ለአገር ደንታ የሌላቸው ሹማምንት የግል ጥቅማቸውን እያሳደዱ ሕዝብ ሲያስለቅሱ ዝምታው ምንድነው? ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ እነዚህን ችግሮች መፍታት ያቃተው ለምንድነው? ችግሮቹስ ለምን ይድበሰበሳሉ? በርካታ ጥያቄዎች አሉ፡፡
የዴሞክራቲክ ተቋማት አለመጠናከርና በፍርኃት ቆፈን መያዝ፣ የሲቪል ማኅበረሰቡ ደብዛው መጥፋት፣ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱ ደብዝዞ የአውራ ፓርቲ ሥርዓት መንገሥ፣ የሕዝብ ተወካዮችና የክልል ምክር ቤቶች ሕግ የማውጣትና አስፈጻሚውን የመቆጣጠር አቅም አለመጠንከር፣ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉ መገናኛ ብዙኃን የገዥው ፓርቲ ብቻ አገልጋዮች መሆን፣ የግሉ ሚዲያ መፍረክረክ፣ ወዘተ ግልጽነትና ተጠያቂነትን እያጠፋ ነው፡፡ በየቦታው ትንንሽ አምባገነኖች እየተፈለፈሉ ነው፡፡ ለአገር አደጋ ነው፡፡
ሙሰኞች የአገር ሀብት እየዘረፉ ሲከብሩ ዞር ብሎ የሚያያቸው የለም፡፡ ጭራሽ በድርጅት አባልነት ከለላ፣ በሹማምንት ትውውቅና ኔትወርክ ዕውቅና የተሰጠው ሙስና ግለሰቦችን በቀናት ውስጥ ሚሊየነር ሲያደርግ ዝም ይባላል፡፡ የፀረ ሙስና ትግሉ የለም እንዳይባል ያህል እዚህም እዚያም በአለፍ ገደም አንዳንድ የሚጠየቁ ግለሰቦች ቢኖሩም፣ ሙስና የሥርዓቱ መግለጫ እስኪመስል ከተራ ዜጋ እስከ ውጭ ኢንቨስተር ድረስ የምሬት ምክንያት እየሆነ ነው፡፡ በሕገወጥ የመሬት ወረራ፣ በሕንፃ ግንባታና ዕድሳት ፈቃድ፣ በወጪና ገቢ ንግድ የጉምሩክ ኬላዎች፣ በአገር ውስጥ ገቢ፣ በአነስተኛና በትልልቅ ግዢዎችና ጨረታ፣ በንግድ ፈቃድ ምዝገባና በብቃት ማረጋገጫ፣ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በጀት ምዝበራ፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዝርፊያ፣ በኤሌክትሪክ፣ በውኃና በስልክ መሠረተ ልማት ዝርጋታዎች፣ በመንገድ ግንባታዎችና በመሳሰሉት አገሪቱንም ሕዝቡንም ራቁታቸውን የሚያስቀሩ የሙስና ተግባራት እየተፈጸሙ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ሆይ የት ይሆን ያለኸው? አባላትህና ደጋፊዎችህ ምን እያደረጉ ነው? የምዝበራው ተሳታፊ ወይስ የዳር ተመልካች? ይኼም በደንብ ይፈተሽ፡፡ ራስህን ተመልከት፡
አገሪቱ ከነበረችበት የድህነት አረንቋ ውስጥ ለማውጣት የሚደረገውን ጥረት ሕዝቡ መስዋዕትነት እየከፈለበት ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ሕዝብ አሁንም በከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እየተመታ ነው፡፡ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች በየቀኑ ዋጋቸው እየጨመረ ኑሮን መቋቋም ተስኖታል፡፡ የልጆች ትምህርት ቤት ክፍያ ከአቅም በላይ እየሆነበት ነው፡፡ የቤት ኪራይ ክፍያ ከሚቋቋመው በላይ ነው፡፡ በትራንስፖርት እጦት በፀሐይና በዝናብ ይንገላታል፡፡ ፈረቃ በይፋ ያልታወጀላቸው ኤሌክትሪክና ውኃ ለቀናት እየጠፉበት ይሰቃያል፡፡ ይህንን ሁሉ ጫና ተቋቁሞ አገሩን የሚገነባ ሕዝብ እንዴት ነው ድጋፍ ማግኘት ያለበት? በስሙ በድጎማ የሚመጡትን ዘይትና ስንዴ በጥቅም የተሳሰሩ ሌቦችና ደላሎች አየር በአየር ይሸጡበታል፡፡ የግብይት ሥርዓቱ እጅግ በጣም ኋላቀርና ተቆጣጣሪ የሌለው ከመሆኑ የተነሳ ሕዝቡን በቁሙ እየገደለው ነው፡፡ ኢሕአዴግ እስከ መቼ ጆሮ ዳባ ልበስ ይላል? አስቸኳይ መፍትሔ ያስፈልጋል፡፡ ኢሕአዴግ ራሱን ይመልከት፡፡
ዜጎች በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችም ሆነ በተለያዩ መንገዶች የሚያቀርቡዋቸው አቤቱታዎችና ብሶቶች አይደመጡም፡፡ ቅሬታዎች በአግባቡ አይስተናገዱም፡፡ ችግሮች ሲፈጠሩ ጥድፊያው ለማድበስበስ እንጂ መፍትሔ ለመፈለግ አይደለም፡፡ ኢሕአዴግ ስኬቱን እያወደሱ የሚያሞካሹትን ጆሮውን ሰጥቶ የሚያዳምጠውን ያህል ለምን ተቃውሞዎችን፣ ምክሮችንና ቅሬታዎችን ለማዳመጥ አይተጋም? በቅርቡ በተካሄደው ምርጫ ከነአጋሮቹ ያገኘው መቶ በመቶ የፓርላማ መቀመጫዎችን እንጂ፣ መቶ በመቶ የሕዝቡን ይሁንታ አይደለም፡፡ ካገኘው የሕዝብ ድጋፍ ጋር ባይወዳደርም የማይናቅ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ይቃወሙታል፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ኢሕአዴግ በውስጡ ከሕግ በላይ የሆኑ ግለሰቦችን በመያዙ፣ አድርባዮችና ሌቦችን በማቀፉ፣ ፀረ ዴሞክራሲና አምባገነን በህሪያት ይንፀባረቁበታል በሚል ነው፡፡ ይኼም በተደጋጋሚ ተተችቶበታል፡፡ አገራቸውንና ሕዝባቸውን በቅንነት የሚያገለግሉ እየተገፉና ዕድገት እየተከለከሉ ወረበሎች አገር እየበደሉ ነው፡፡ ኢሕአዴግንም እያስተቹት ነው፡፡ ይኼም መፍትሔ ይፈልጋል፡፡
ኢሕአዴግ አሥረኛውን ድርጅታዊ ጉባዔ ሲያካሂድ ወሳኝ የሆነ የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ጨክኖ መወሰን አለበት፡፡ ፀረ ዴሞክራቲክ ተግባራት ይወገዱ፡፡ የተዘጋጋው የፖለቲካ ምኅዳር ይከፈት፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት ይንቀሳቀሱ፡፡ ጦር አንስተው የሚፎክሩ ኃይሎች ሳይቀሩ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ እንዲመለሱ ሁኔታዎች ይመቻቹ፡፡ ሰብዓዊ መብቶች ይከበሩ፡፡ ኢትዮጵያ ማንም እየተነሳ የሚፈነጭባት አገር እንዳትሆን የሕግ የበላይነት በተግባር ይረጋገጥ፡፡ ሙሰኞችና ሌቦች ለሕግ ይቅረቡ፡፡ ብቃት የሌላቸው ይሰናበቱ፡፡ አቅም ያላቸው ለሹመት ይታጩ፡፡ ሕዝቡን ደስ የሚያሰኙ ተግባራት ይከናወኑ፡፡ አስመሳዮችና አድርባዮች ይወገዱ፡፡ ኢትዮጵያ የሰላም፣ የነፃነትና የብልፅግና አገር ትሁን፡፡ ኢሕአዴግም ራሱን ይመልከት!
- See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/46125#sthash.ORsIe1j6.dpuf

No comments:

Post a Comment