Friday, December 5, 2014

ተስፋዬ ተስፋ ሲቆርጥ – ክፍል 3

ከሠናይ ገብረመድህን (ጋዜጠኛ)
ብርጋዴር ጄኔራል ከማል ገልቹ ወታደሮቻቸዉን በህግደፍ የተዘረፉበት ኩነት ብዙዎቻችንን በታሪካችን አንድ አስገራሚ ሆኖ ያለፈ ዜናን ማስታወሱ አልቀረም፡፡ “ኮ/ል መንግስቱ ሀይለማርያም በሱዳን አስተባባሪነት ዜጎቼን በእስራኤል ተዘረፍኩ አሉ” በሚል የተዘገበዉን የአሜሪካ ድምፅ የአማርኛ ፕሮግራም
ዜና ፡፡ ኢትዮጵያዉያኖቹ ቤተእስራኤሎች በድብቅ ወደ እስራኤል የተጉዋጉዋዙበት የሞሰስ ኦፕሬሽን ይሄዉ ሶስት አሰርት ደፈነ፡፡ የቤተእስራኤሎቹን ጉዳይ በተመለከተ ዘረፋ ወይንም የማጉዋጉዋዝ ኦፐሬሽን ተብሎ በዜና ተወርቶላቸዋል፡፡ በህግደፍ ስለተዘረፉት ኢትዮጵያዉያኖች ግን ምንም አልተወራላቸዉም፡፡ ያዉም በዘመነ ኢንፎርሜሽን፡፡ (እኔ እሆን ገና አሁን ስለመዘረፋቸዉ እያወራሁ ያለሁት ?) ከሆነም እኮራለሁ፡፡ ስለወገኖቼ በግፍ መዘረፍና ታጋችነት የሰሚ ያለህ በመናገሬ ፡፡ እነሱ ብቻም አይደሉ ህግደፍን አምነዉ ተጠልለዉ ግና ባልገመቱት ሁኔታ በህግደፍ የታፈኑ ያታገቱና የተዘረፉት፡፡ ጊዜና ሁኔታ እንደፈቀደልን የምናዉቀዉን ያለፍንበትን የእማኝነታችንን አቤት እንላለን፡፡ የነበርን ሰዎች፡፡ ፍርዱንም ለሁለቱም ህዝቦች በጎ አሳቢና አላሚዎች እንተዋለን፡፡ ላሁኑ ይህን እንቀጥል!
የኒያላ ሆቴል ሰፋፊ ሳሎኖች ቀኑን ፀጥታ ስለሚነግስባቸዉ እንደልብ እየተደማመጡ ወግ ለመኮምኮም ይመቻሉ፡፡ ተስፋየ ገ/አብም ፡ ሌ ኮ/ል አበበ ገረሱና ሌ/ኮል አለበል አማረን በጋራም ሆነ በተናጥል እያገኛቸዉ ብዙ ቀናቶችን ወግ የተቀባብሉት እዚያ ነዉ፡፡ ተቀባይ ተስፋየ ሰጪ ሌ ኮ/ሎቹ ፡፡፡ ተስፋየ ደግሞ በቢራ ጀምሮ ለጥቆም በጂን እያቀባበለ ጨዋታቸዉን አወራርዱዋል፡፡ ጨዋታን ጨዋታ ካነሳዉ በአለኮል አጃቢነት የሚወርዱ ጨዋታዎች ጡጦዋ በጨመረች ቁጥር በግነት በስሜታዊነት በቅብዥርዥርነት አይበረዙም ትላላችሁ? ተስፋየ ራሱ እንደነገረኝ እንዲህ ባሉ የጠረጴዛ ምሽቶች የሚመሰጥባቸዉን ጨዋታዎች በዉስጡ ሲያከማች ያመሽና ሌሊት ይፅፋቸዋል፡፡ ወደ አንጎሉ እንደአወጣጣቸዉ ሁሉ እንደወረዱ ስለመፃፋቸዉ ግን እንጃ! የጂን ነገር! (የኒያላ ሆቴልን ነገር ካነሳን ይቺን እንበል ፡፡ አስመራን የረገጡ አያሌ ኢትዮጵያዊያን በኒያላ ሆቴል የትግል ጎራ ተስተናግደዋል፡፡ እኔም አንዳንዴ “እስኪ ኒያላ ሆቴል ግምባር ጎራ ልበል!” እያልኩ ቀልድ ቢጤ ጣል አደርግ ነበር፡፡ የምቀልደዉ በኢትዮጵያዉያን ወገኖቼ አልነበረም፣ በህግደፍ የአጋች ታጋች ተግባር እንጂ፡፡ ኒያላ ሆቴል አፍ ቢኖረዉ … !! ከብ/ጄ ከማል ጦር ጋር ኤርትራ የገባዉ ሌኮ/ል አበበም የአስመራዉ ኦነግ ለሁለት ሲከፈል ከብ/ጄ ከማል ጋር ወገነ፡፡ ብዙም ሳይቆይ በጤና ሳቢያ ከነከማል ቡድን ተሰናበተ፡፡ ህግደፍም ኒያላ ሆቴል እንዲመሽግ ፈቀደለት፡፡ ሰንበትብት ብሎም የራሴን የፖለቲካ ድርጅት መስርቻለሁና በሚዲያችሁ ይለቀቅልኝ አለ፡፡ የማይታሰብ ነበር፡፡ ለህይወቱ ስለሰጋሁ “እረ
ባክህ እዚህ ሆነህ ድርጅት መስርቻለሁ የምትለዉ ነገር ይቅርብህ፡፡ በሰላም ከዚህ አገር መዉጫህን ፈልግ” የወንድምነቴ ተማፀኖ ነበር፡፡ አልሰማኝም፡፡ በኢንተርኔት ለቀቀዉ፡፡ ሌኮ/ል አለበል ደግሞ በከፍተኛ አመራርነት የአማራ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄ መመስረቱን ከእኔ ጋር ባካሄደዉ የቴሌቭዥን ቃለመጥይቅ ይፋ አድርጉዋል፡፡ ከኤርትራ እስከወጣሁ ድረስ ይህ ሁኔታ ነበር፡፡ ከተስፋየ ጋር በሚገናኙበት ወቅትም በዚህ ሁኔታ ላይ ነበሩ፡፡ የኒያላ ሆቴል ወጎች ልንለዉ እንችላለን (ጎበዝ ትዝታየ የጎንዮሽ ይዞኝ ሲነጉድ ራሴን ታዘብኩት)፡፡
Author Tesfaye Gebreab
Author Tesfaye Gebreab

ተስፋየ ከሌ/ኮ አበበ ገረሱና ከሌ/ኮ አለበል ጋር ሲገናኝ አንድ ነገር አዉቁዋል፡፡ ሌ/ኮ አበበ ከብ/ጄ ከማል ጋር መቆራረጡንና በህግደፍ ይሁንታ ኒያላ ሆቴል መመሸጉን ፡ ሌ/ኮ አለበል አማረ የአማራ ድርጅት ምስረታ ላይ መሆኑን ፡፡ እንዴት አያዉቅ ጎበዝ ! ኢትዮጵያን እንደ ቅርጫ ተካፍለዉ በቅዠት በሪሞት ኮንትሮል የሚገዙዋት ኮ/ል ፍፁም(ሌኒን) ኮ/ል ጠዐመ (መቀለ) ኮ/ል ጋይም፣ ኮ/ል ዮናስ እኮ ወዳጅና መሃንዲሶቹ ናቸዉ፡፡ ዋናዉ የህግደፍ ቢሮ ቤቱ ነዉ፡፡ እነ ብ/ጄ ከማልና ብ/ጄል ሀይሉ ጎነፋ ደግሞ ከህግደፍ ጋር ስለተፋቱ አላስፈለጉትም፡፡ ለህግደፍ አይመቹም ፡፡ (የህግደፍን ፊት መንሳት ካነሳን በኤርትራዊያን ላይ የሚወርደዉን ግፍ ትተን በእንግድነት የገቡትን ኢትዮጵያዉያንን ብንነቅስ፡ አነጋፋዉ የኦነግ አመራር አቶ ገላሳ ዲልቦ ከኦነግ አመራርነት ተወግደዉ አቶ ዳዉድ ከህግደፍ ጋር ሲወዳጁ አቶ ገላሳ አስመራ ላይ እንዴት እንዴት በህግደፍ ፊት እንደተነሱና በከባድ ህመም ሲሰቃዩ ችላ ተብለዉ ህይወታቸዉ በኤርትራዊዉ የቀድሞ የአ/አ ዩኒቨርሰቲ ጉዋደኛቸዉ አቶ ምህረቱ በእምነት እርዳታ መትረፉን መዘከር ይበጃል፡፡ በአስመራዉ የስደተኞች ኮሚሽን የስደት አገር ተገኝቶላቸዉ ከኤርትራ ሚግሬሽን የመዉጫ ቪዛ ስለተከለከሉት ወገኖችስ ቢሆን ማን ይሆን ያገታቸዉ ማን ይሆን ያሳገታቸዉ ? ( የታሪክ ማጣቀሻ መፅሃፍ ይወጣዋል ) እነዚህን መሰል ህግደፍ በኢትዮጵያዊያን ላይ ስለፈፀማቸዉ ወንጀሎች ፊት መንሳት…መንቀስ ይቻላል ፡፡ ግን እንዲህ ነበር የሆነዉ እየሆነ ያለዉም ፡፡ በቃ! አሁን ግን ይሄን ገታ አርገን ወደ ጀመርነዉ እንለፍ፡፡
የነተስፍሽን የአመሻሽ ማዕድ እየተጋራሁ ከጨዋታቸዉ ስጋራ ሰነበትኩ፡፡ሌ/ኮል አበበና ሌ/ኮል አለበል የቀጣዩ መፅሃፍ ባለታሪኮች መሆናቸዉን አወቅሁ፡፡በዚያዉ ሰሞን ምሽት ሌላ አንድ እንግዳ አብሮ ተገኘ፡፡በአምሳዎቹ የሚገኝ፡፡ አምቼ ኤርትራዊ ኢኒጂነር መሆኑን በትዉዉቅ ተረዳሁ፡፡ጥርት ባለ አማርኛዉ፡፡ ከጠረጴዛዉ ጨዋታ ገለል ብለን ከኢነጂነሩ ጋር ወግ ጀመርን፡፡ ወሎ ደሴ ማደጉን ከገለጠልኝ በሁዋላ ስለዝነኛዉ የወይዘሮ ስህን ት/ቤት የቀድሞ ትዝታዉ እያነሳ ጨዋታን ጨዋታ እየመዘዘዉ ነጎድን፡፡ እኔም የወሎ ልጅ [ከወረሴህና ጃንጥራሮች የምወለድ] ነኝና ጨዋታዉን በፍስሃ ስሜት ተሞለቼ አጣጣምኩት፡፡ በጥያቄ በትዉስታዎች ያቅሜን እየተሳተፍኩ፡፡በጨዋታ መሀል አስመራ ከሚገኙት የቀድሞ የስህን ት/ቤት ተማሪ ከነበሩት ከአቶ ጠሐ ሱዋሊህ ጋር ያደረግኩትን የትዉስታ ዝግጅት እንደወደደዉ ገለጠልኝ፡፡ ኢትዮጵያ ዉስጥ ተወልደዉ ያደጉና ረዥም የህይወት ዘመናቸዉን በተለያዩ ሙያ ያሰለፉና በአማርኛ ሀሳባቸዉን መግለፅ የሚችሉ ታጋዮች ኤርትራዊያንን ወደ ፕሮግራማችን በመጋበዝ የምናካሂደዉ የጨዋታ ጊዜ በበኩሌ በጣም ነበር የምወደዉ፡፡ በዉስጤ የሁለቱን ህዝቦች በፍቅር የተሞላ ግንኙነት ያንፀባርቃል ብየ ስለማምን፡፡ ከጥላቻ ፖለቲካ የራቀ በመሆኑም፡፡ “ሠናይ ከኢነጂነር ጋር የምታደርገዉን የግል ጨዋታ አቁዋርጥ” ተስፋየ በጨዋታችን መሃል አንባርቆ ገባ፡፡ “እንዴ ለምን? እንዲያዉም የፕሮግራማችን የጨዋታ እንግዳ አደርገዋለሁ፡፡ ስለ የወሎ ጣፋጭ ጨዋታዎችና በቀደምት ተማሪዎች ትግል ታሪክ አዉራ የሆነዉ የስህን ት/ቤት ትዝታዎች ባለቤት ነዉና ባስተናግደዉ እኔንም ፕሮግራማችንንም ያኮራናል” ስል መለስኩለት፡፡ “ኢነጂነርም ፈቃደኛ ነዉ” አከልኩ፡፡ ተስፈየ ተወራጨ ፡፡ ሞቅታም አለ፡፡ ከዚያም ወደኔ ቀረብ አለና በልመና መልክ “እኔ ታሪኩን በቀጣዩ መፅሃፌ ላካትተዉ ስለሆነ እባክህ ተዉ፡፡” ሲል ተማፀነ፡፡ “ያንተ በመፅሃፍ ስለሆነ ረዘም ልታደረገዉ ትችላለህ እኛ ግን በዉስን የአየር ሰዓት ነዉ የምናስተናግደዉ፡፡
አቀራረቡ ደግሞ የተለያየ መሆኑን ከኔ በላይ ታዉቃለህ፡፡” ተስፋሽ አልተዋጠለትም፡፡ “በእናነተ መጀመሪያ ከቀረበ ለኔ ጥሩ አይመችም” ሌላ ሰበብ አከለ፡፡ “አሁን የመፅሀፍህ አካል የሚሆኑት ኮ/ል አበበና ኮ/ል አለበልም እኮ በእኛ ፕሮግራም ተስተናግደዋል፡፡ አሁን የኢነጂነር ልዩነቱ ምንድን ነዉ?” ጥያቄየ ነበር፡፡ አልመለሰልኝም፡፡ የንትርካችን ምክንያት አልታይህ አልዋጥልህ አለኝ፡፡ በመሀል አጣብቂኝ የገባዉ ኢነጀር “ሠናይ ግድ የለም፤ መጀመሪያ ከተስፋየ ጋር እንስራና ከእናንተ ጋር በቀጣይ አደርጋለሁ፡፡ እዚሁ ስለሆነ ያለሁት ችግር የለም” ሲል የሽምግልና ሀሳብ አቀረበ፡፡ እየሳቅሁ ጣጣ የለዉም አልኩ፡፡ የኢነጂነርን ሁኔታ በመረዳት፡፡ ተስፍሽ ፊቱ ፈካ አለና “በእሪኩም ዘመዳ.. አባብለህ ባለታሪኬን ልትማርክ” ቀለደ፡፡ እኔም ትዝብቴ ጦዘ፡፡ ይሄዉ ጥቂት ወራት ቆጥሮ የስደተኛዉ ማስታወሻ ወጣ፡፡ ተስፍሽና ህግደፍ መፅሃፉን አሰራጩት ቸበቸቡት፡፡ እኔም ባለታሪኮቹም አነበብነዉ፡፡ አንድ ምሽት ኒያላ ሆቴል ጎራ ስል ሌ/ኮ/ል አለበልና አበበን አገኘሁዋቸዉና “እህሳ አማን ነዉ? እንዴት እንዴት ተነበበ መፃፉ?” መፅሃፉ ዉስጥ እንዳገኘሁዋቸዉ በሚያመላከት ወንድማዊ ሰላምታ ወግ ከፈትኩ፡፡ በአንዳች ስሜት ተያዩና “ሆድ ይፍጀዉ አለ ጥላሁን” አቤ ተነፈሰ ከቀጭን ፈገግታ ጋር ፡፡ “እዚሁ በህይወት እያለን ያልተባለ ነገር መፃፍ በጣም ነዉር ነዉ” አለበል ተከተለዉ በትንታግ ስሜት፡፡ ከሁለቱም ኮሎኔሎች ጋር ደረግነዉ ቆይታ ለተሰፋየ ያጫወቱትን በተዛባ መልኩ ማቅረቡንና ከቶወኑም ያላሉትን ጨማምሮ መፃፉ እጅግ እንዳሳዘናቸዉ በሚገልፅ ምሬት የተሞላ ነበር፡፡ “ከብዙ ወዳጆቼ ትችት ደረሰበኝ፡፡ የኦሮሞን ህዝብ ክብር አዋረድክ አሉኝ ፡፡ እኔ ያላለኩትን ጨማምሮበታል ብልም ሰሚ አጣሁ። ስለዚህ ከመፅሃፉ ታሪክ በታሪክ እየጠቀስኩ በዉጭ በሚዲያ አጋልጠዋለሁ” የሚለዉን የተሰበረ የሌኮ/ል አበበን ስሜት አስታዉሳለሁ፡፡ “አሁን ባለህበት ሁኔታ በዉጭ ሚዲያ ተስፋየን መተቸቱ ላንተ ህይወት ጥሩ ስለማይሆን እስኪ ታገስ” ከማለት በቀር በበኩሌ የምለዉ አልነበረም ፡፡ ነዉርነቱን በማጠናከር ፡፡ “ያልሰማ ጆሮ ከጎረቤት ያጣላል” ብለዋል አበዉ ፡፡ ጆሮ ዳዋ ልበስ ከሆነ ግን ሆን ተብሎ ለነገር እንጂ ለሌላ ምን ይሉታል፡፡ የሆነ ሆኖ ኮ/ሌኖሎቹ ተስፋየ ላይ
ንዴታቸዉን በግል እንዳይተነፍሱ በከተማዉ ፈልገዉ አጡት ፡፡ ከኤርትራ ወደ ዉጭ በመሄዱ፡፡ እንዲሁ እየተብሰከሰኩ ወር ሁለት ወር ካሳለፉ በሁዋላ ታዲያ ከተስፋየ የተዘዋዋሪ መልዕክት ደረሳቸዉ፡፡ ለእያንዳንዳቸዉ 5 ሺህ ናቅፋ ጠቅላላ 10ሺህ ናቅፋ(200 ዶላር) ፡፡ በተግባሩ ማዘናቸዉን ሰምቶ አፍ መዝጊያ ከባህር ማዶ ብር እንደላከላቸዉ እየቀለዱ አወጉኝ ፡፡ ይበልጥም አዘኑበት ፡፡ ጉርሻዉንም አልተቀበሉትም፡፡ ገንዝብ እንደሚያስፈልጋቸዉ ባያጠያይቅም ክብረ ነክ በሆነ መልኩ መቀበልን አልመረጡም፡፡ በዉነት ከኩሩወቹ ወገኖቼ በመሆናቸዉ ኮራሁባቸዉ ፡፡
እነ ሌኮ/ል አበበና አለበል ይህን ቅያሜያቸዉን ካካፈሉኝ በሁዋላ ወሎ አደጉን ኢነጂነር አግኝቼ የሚለዉን መስማት ፈለግሁ፡፡ “ኢኒጂነር የነ ኮ/ሎኔልን ታሪክ አነበብኩት ያንተን ታሪክ ግን አጣሁት፡፡ ስለ ወሎ የአንድ ሰዉ ታሪክ ትዝታ ግን አንብቢያለሁ፡፡ አንደ ልጅ በኢንተርኔት በብዙ ድርድር ያደረሰኝ የወሎ አባት ታሪክ ነዉ በሚል ያቀረበዉን ፡፡ ያንተስ የታለ?” እንዳገኘሁት ያቀረብኩት ጥያቄ ነበር፡፡ “እሱ እኮ ነዉ እኔ ያካፈልኩት ታሪክ ፡፡ በዚህ መልኩ እንደሚቀርብ አልገመትኩም፡፡ ስሜ ይጠቀሳል እንጂ አይጠቀስም ብየ አልጠበቅኩም” ሲል ኢነጂነር ያልጠበቅኩትን ገልፆ ቅሬታዉን አዘነበዉ፡፡ “የታሪኩ ባለቤት አንተ እዚሁ እያለህ ከሌላ በደጅ ጥናት እንደደረሰዉ አስመስሎ በሌላ ስም አቀረበዉ ነዉ የምትለኝ ?” የሰማሁትን ማመን አልቻልኩም፡፡ ዕዉቁ የብዕር ሰዉ በዓሉ ግርማ ጋሼ ስብሃትና ሌሎችም ደራሲዎች ከሰዎች እዉነተኛ ታሪክና እዉኑ አለም ሰዎች ባህሪያት ተመስርተዉ ልቦለድ የመፃፍ ክህሎታቸዉን አዉቃለሁ አንብቢያለሁ፡፡ የጋሼ ስብሃት ትኩሳት ሌቱም አይነጋልኝ አጋፋሪ እንደሻዉ የበአሉ የቀይ ኮኮብ ጥሪ መፅሃፉ ላይ ያሉት እነ እምአእላፍና ደርቤ በቅርብ ከሚያዉቃቸዉ መሆኑን፡፡ ደራሲዉ ከፊል የደራሲ ስብሃት ገ/እግዚአብሄር ታሪክ ስለመሆኑ፡፡ ጋሼ ስብሃት ስለ በአሉ ሲናገርም ይህንኑ ማብራራቱን ሰምቻለሁ፡፡ በሌሎችም በልቦለድ ዉስጥ የእዉኑ አለም ሰዎች ገፀባህሪያት ተላብሰዉ መቅረባቸዉ የተለመደ አፃፃፍ ነዉ፡፡ ግለታሪክ ከሆነ ግን እንደወረደ መቅረብ የሚኖርበት ይመስለኛል፡፡ ባለታሪኩ በዘመኑና በቦታዉ ጀልባ ዉስጥ አሳፈሮ በትዝታ ባህሩ ዉስጥ እየተመላለስን እንድንሳፈፍ ከማድረጉም ባሻገር ዘመኑንና ቦታዉን እንደነበረ ለማየት እንድናጣጥም ይረዳል እላለሁ፡፡እናምነዋለንም፡፡ ለባለ ግለታሪኩም እዉቅናን ሰጥተን እናከብራልን፡፡ የደራሲ ሀዲስ አለማየሁ ግለታሪክ የደራሲና ገጣሚ መንግስቱ ለማ ታሪክ የዘነበ ወላ የስብሃት ማስታዎሻ የፍቅሩ ኪዳኔ የአራዳ ልጆች …… ; የመሳሰሉት ግለታሪክ መፃህፍት ባለታሪኮቹ በራሳቸዉ ስለሚተርኩልን መሳጭነታቸዉ አያጠያይቅም፡፡ ተስፋየ እንዳደረገዉ ግለ ታሪክ ብለን ያነበብነዉ ልብወለድ ሆኖ ስናገኘዉ እንዴት እናምነዋለን? “አይነጋ መስሉዋት ….. “ አበዉ ያሉት ነገር ፡፡ እንጃ እንግዲህ ከብሂሉ ባሻገር ሌላዉ የስነፅሁፍ ባለሙያዎችን ይመለከታል፡፡
ከህይወት ዘመኑ የወሎ ትዝታዉን ለተስፋየ ያካፈለዉ ኢነጂነር እነሆ እዉቅናና አክብሮቱ ቀርቶ ስሙን እነኩዋን ከደራሲዉ ማስታወሻ ላይ ማግኝት ሳይችል ቀረ፡፡ “በጣም ያሳዝናል፡፡ ተስፋየ በእኛ የቴሌቭዥን ፐሮግራም ላይ የጨዋታ እንግዳ ሆነህ እንዳትቀርብና ስለወሎ ደሴ ወ/ሮ ስህን ት/ቤት መልካም ትዝታህን ቀድመህ እንዳታካፍል የፈለገዉ ከሌላ የደረሰዉ አስመስሎ ለማቅረብ ስለፈለገ መሆኑ ነዉ ፡፡ ለነገሩ እሱ መች ሆነና …..” ንግሬን አልጨረስኩትም፡፡ ስሜቴን መቆጣጠር ተገቢ መሆኑን ዉስጤ ነገረኝ፡፡ “ይሄዉ ተስፋየ ታሪኬን በአደባባይ ዘረፈዉ “ ኢነጂነር መራራ ቀልድ ቀለደ ፡፡ በክህደት የተሞላዉ ህግደፍ ያመኑትን ኢትዮጵያዉያን ወታደሮችን ዘረፈ ፡፡ መዝረፉንም ቀጠለ ፡፡ ተስፋየ ገ/አብም ግለ ታሪክ ዘረፈ ፡፡ ‹የአባት ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ› መሆኑ ይሆ ? ለዛሬ በዚሁ ይብቃን፡፡ ለቀጣዩ የዚያ ሰዉ ይበለን !
ቸር እንሰንብት፡፡
ሠናይ ገብረመድህን (ጋዜጠኛ)
አዉስትራሊያ ሜልበርን
ለግል አስተያየታችሁ ከአክበሮት ጋር ፡ Wosenmarta_2010@yahoo.com

No comments:

Post a Comment