Saturday, December 20, 2014

ይድረስ ለጎንደር ሕዝብ ቁ. 3

ጎንደር ተወልደን ያደግን ሁሉ እንደምናዉቀዉ ህዝባችን እንግዳ ተቀባይ፤ ሽራፊ እንጀራውን ተካፍሎ አዳሪ፤ እንዲሁም በደስታም ሆነ በመከራ አብሮ ከመቆም ባህሪው በመለስ፤ በየዘመኑ ሊያጠቁን እና እናት አገራችን ሊወሩ የመጡብንን ጠላቶቻችን፤ መሪ ሲኖረው ከመሪው ጋር። መሪ ሳይኖረው ጀግኖቹን የጎበዝ አለቃ አድርጎ በመምረጥ እራሱን በራሱ አደራጅቶ እሴት ወንድ፤ ትንሽ ትልቅ ሳይል እንደማንኛዉም ኢትዮጵያዊ የነጻነት አርበኛ ሆኖ፤ የብዙ ጀግኖችን ህይወት ሰውቶ ትልቅ ታሪክ ሰርቷል። በዚህ በፈሰሰው ደሙ እና በተከሰከሰው አጥንቱ ለዛሬ መመኪያ የሆነችንን ጎንደርንም፤ ኢትዮጵያንም አዉርሶናል። ለሶስት መቶ አመታት 27 ነገስታት ያገለገሉበትን በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ኩራት የሆነውን የመጀመሪያዉን የጎንደር ቤተ መንግስት የገነባዉም ይኽው በአንድነቱ ሲወደስ የኖረው አማራዉ፤ ቅማንቱ፤ አገዉ፤ ቤተ እስራኤሉ፤ ክርስቲያኑ፣ እስላሙ እና ሃይማኖት የሌለዉም ጎንደሬ ጭምር ነዉ።
Fasil , Gonder
ስለ ኋላ ታሪካችን ከአሁን በፊት በወጡት መግለጫዎቻችን ላይ ብዙ ስላልን፤ ለዛሬ ከ“አብዮት” በኋላ የደረሱብንን ማንነታችን አንድነታችን ፈታኝ የሆኑ አሥቀያሚ ገጽታዎችን ማንሳቱ በቂ ነው። ከስልሳ ስድስት አብዮት በኋላ፤ በተፈጠረው የመሥመር ልዩነት፤ ወደ ትጥቅ ትግሉ ለመግባት ከተመረጡት ቦታዎች አንዱ በዚሁ በጎንደር ክ/ሀገር ነበር። በመሆኑም፤ ወደ ትጥቅ ትግሉ ለመግባት የወሰኑትን ከመላ ኢትዮጵያ የሚመጡ ዜጎቻችን ያሥተናገደው እና በዚሁም ሰበብ ከፍተኛውን የደርግ ቀይ ሽብር ጭፈጨፋ መራራ ጽዋ ከተጎነጩት ክፍለ ሀገራት አንዱ የጎንደር ክ/ሀገር ህዝብ ነው። የማይረሳው የቅርብ ጊዜ አሥከፊው ትዝታችን ደግሞ፤ የትግራይ ክ/ሀገሩ ተወላጅ ገብርህይወት ገ/እግዚአብሔር በፊት የወገራ፤ ሰሜን እና ጭልጋ አውራጃ የጦር አበጋዝ፤ በመጨረሻም የጎንደር ክፍለ ሃገር የደህነት ሃላፊ፤ ግን የወያኔ ሰርጎ ገብ የዉስጥ ነጻ አዉጭ፤ የደርግ ተወካይ በመምሰል ከነመላኩ ተፈራ ጋር ተባብሮ በከተማም ሆነ በገጠር እጅግ ብዛት ያላቸው ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን መጨረሱ ነው። ይህን ሁሉ የቅጣት ዋጋ ያስከፈለን፤ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ወንድማችን እህታችን ብለን ማስተናገዳችን ብቻ ነዉ። ጎንደር ሌላ ጥፋት የለዉም፤ በዘር ሳይደራጅ ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ! በማለቱ እንጂ። አሁን ግን በዛብን፤ ባበላን ተነከስን፤ ባስተናገድን ተወረርን። ፍቅራችን እና ትብብራችን ያሥደነገጣቸው ከፋፋዮች ሊያለያዩን ጎሳ ሥለታቸውን ሰነዘሩበን።
በ1991 ወያኔ አዲስ አበባ ሲገባ ዉስጥ ዉስጡንም ሆነ በይፋ ሰርቶ ባዘጋጀዉ ካርታ መሰረት የጎንደር ክልል የነበረውን የሁመራን፤ ወልቃይት ጠገዴን እና የጠለምት መሬታችንን በጉልበት በመውረር ወሰደ። ከቦታዉ የነበረዉን ለዘመናት የኖረ ህዝብ አፈናቀለ። የዘር ማጥፋት ዘመቻዉ አሁንም ቀጥሏል። በአብደራፊ፤ በመተማ እና በቋራ ዘይትና ወርቅ ብሎም የርሻ ልማት ያለበትን የጎንደር መሬት ለመዉሰድ በኢንቬስተር (INVESTOR) ስም ለወያኔ ካድሬዎች በገፍ እዬቸበቸበ ነዉ። ተወላጁ የጎንደር አራሹ ገበሬ እየተፈናቀለ፤ እየታሰረ፤ እየተገደለ፤ እየተሰደደ፤ አንዴ የትግራይ መሬት ነዉ፤ ሲያሰኛቸዉ በመተማ በኩል ያለውን ደግሞ የቤኒሻንጉል ነዉ፤ እያሉ ግማሹን ለራሳቸዉ የቀረዉን ለሱዳን ቆርሰዉ እያስረከቡ ደካማ እና ታሪክ የሌላት ጎንደርን በፈለጉት መንገድ ሊሥሏት እየተዘጋጁ ነዉ። አሁን ያመጡት የመጨረሻዉ ጥቃት ደግሞ ግማሹን የጎንደር መሬት ሲነጥቁ የቀረዉን ጎንደሬ ቅማት እና አማራ በሚል ማለያየት የጠነሰሱት እኩይ የጥፋት ሴራ ነዉ። አማራዉን በኢትዮጵያ በአራቱ ማዕዘን አዳክሞ አገር የማጥቃት እስትራቴጂ ዋንኛው አካል ነዉ። ላለፉት 23 ዓመታት መላዉ የጎንደር ህዝብ ጎንድር አንድ ነዉ፤ ጎንደር የቅማንት የአማራ፤ የቤኒሻንጉል፤ የአገዉ፤ የቤተ እስራኤል አገር ነዉ ብሎ በዘር መከፋፈልን በጽኑ ተቃዉሞ ቆይቷል። በወቅቱ ወያኔ የመለመላቸዉ በጣት የሚቆጠሩ የቅማት ተወላጆች በዋና ከተማዋ ጎንደር ሲኒማ አዳራሽ ስብሰባ ሲጠሩ ሁሉም የከተማዉ ህዝብ ቅማንት ነን ብሎ ከአዳራሹ ገብቶ ግራ እንዳጋባቸዉ ሁላችሁም ታዉቃላችሁ።
አሁን ግን እነሱ ከገቡ የተወለዱና ሲገቡ ወጣት እድሜ የነበራቸው የተወሰኑ ወጣቶችን፤ እንዲሁም ጥቂት አዛዉንት እና ምሁራንን ለሂደቱ አዳማቂ እንዲሆኑ በዘረኛነት አጥምቀዉ ጎንደርን፣ አማራ እና ቅማንት በሚል ካርታ ለይተዉ የጎሳ እሳት መለኮስ ጀምረዋል። ለበለጠ ጥፋትም ተዘጋጅተዋል። ይህን እሳት ማጥፋት አለብን። የሥራአቱ መራሽ የሆኑት ወያኔወችከጀርባ እዬሰሩት ያለዉ ሃቅ ግን እኛን እያዋጉ መሬት ለመንጠቅ እንድሆነ ግልጽና በተግባር የታየ ነዉ። እዉነተኛዉ እኛ የምናዉቀዉ ጎንደሬ የቅማንት ተወላጅ፤ ሁመራን ወልቃይት ጠገዴን ጠለምት እራስ ዳሸንን ወያኔ ወሮ ዘመቻ በከፈተበት የጥፋት ዘመን ላይ መሆናችንን እያዬ፤ ለቅማንት ጎሳ ሌላ ክልል ልፍጠር ብሎ ለአዲስ ካርታ ጦርነት ይገባል ብለን ፍጹም አናምንም። ወያኔ መራሹ መንግሥት ግን ይህን ለማስፈጸም እየሰራ እንደሆነ አንጠራጠርም። እኛ የጎንደር ተወላጆች የገንደርን አብሮነት የጎንድርን ዳር ድንበርና አንድነት ለማስከበር ሃይማኖት ጎሳ ወይም ቋንቋ ሳይለያየን እስከመጨረሻዉ መታገል የግድ ይላል። ከዚህ ያነሰ አማራጭ ጎንደርን የሚያዳክም ብሎም የሚያጠፋ ነዉ ሊሆን የሚችለው። የታሪክ ተወቃሽ እንዳንሆን ወያኔወችንም ተከታዮቻቸዉንም አምርረን ቁርጡን እንገራቸዉ። ሁሉም ጎንደሬ አማራ፤ ቅማንት፤ ቤተ እስራኤል፤ አገዉ፤ ክርስቲያን ወይም እስላም ሆኖ የመኖር ማንነት ማንም የመንፈግም ወይም የመስጠት መብት የለዉም። ይህ አብዛኛዉ የአማረኛ ተናጋሪ ህብረተሰብ ጠንካራ አይበገሬ የኢትዮጵያዊነት አቋም በመያዙ የጥፋት ማዕበል የአገራችን እምብርት በሆነችው ጎንደር ላይ የመከፋፈል ዘመቻ ከፍተዋል። የክፍፍል ማዕበሉ የወያኔን ጎጠኞች እና የዘረኛነት ማቃቸዉን ጠራርጎ እንዲወስድ የጎንደር ህዝብ ተባብሮ መነሳት አለበት።
ወያኔ ቅማንት የሚለዉን የነገድ ስም ከኢትዮጵያ ማህደር ከወረቀት እንዲፋቅ ያደረገዉ፤ ዘረኝነትን ያልተቀበለዉ ጎንደሬዉ ቅማት ዘራፍ ብሎ አምጾ አንቀጽ 39 እንዲቀበል የተጠነሰሰ ሴራ ነዉ ብለን እናምናለን። የቅማንት ምንነት ቋንቋ ወይም የስነ ልቦና ባህላዊ አኗኗር የጎንደር ታሪክ ነዉ ብሎም ተቀብሎ የቆየበት ዘመን እጅግ እረጅም ነዉ ከ፪፬፻፲ (2410) ዓመተ ዓለም ጀምሮ የኢትዮጵያ ነገዶች ቅርስ ሁኖ ቆይቷል። ይህም ኩሽ በተባለዉ ንጉስ የኢትዮጵስ አባት ዘመነ መንግስትም እረዘም ያለ ወደ አራት ሺህ ዓመታት ገደማ ያስቆጠረ ነዉ። አንዳዶች በቅርብ ቀን አንዴ ከኢሽያ፤ ሌላ ጊዜ ከግብጽ መጣ ይላሉ። ግን ኢትዮጵያ 200 ዓመታት 2335 ዓ. ዓ ግብጽን ማስተዳደራን ጠቅሰዉ አይጽፉም።
የጎንደር ህዝብ፤ በተለይም ይህ ትዉልድ የቅማንትን የምንነት መልካም ታሪክ የራሴ ነዉ ብሎ እዉነተኛ ጎንደሬነቱን ይቀበላል። የዘመኑ ዘረኛ ጎጠኞች ግዛታቸዉን ለማራዘም አንዱን ትንሽ ሌላዉን ትልቅ እያደረጉ ያለስም ስም የመስጠት አጉል እና ኋላ ቀር ባህል ፍጹም የዚህ ትዉልድ አቋም አይደለም፤ አይቀበለዉም። ይልቁንም ያለፉትም ሆነ፤ አሁን በግፍ ላይ ግፈ ሞልቶ እስኪፈሥ እየተደራረበ ያለው የመጥፎ አስተዳደር ዉጤት ነዉ ብለን ሁላችንም እናምናለን። የወያኔን የመሬት ወረራ የመስፋፋት ፖሊሲን ለማሳካት ቅማንት እና አማራ ብሎ የጎንደር ክፍለ ሃገርን ሕዝብ ከሁለት ግዛት ለመክፈል የሚካሄደዉን ሴራ አጥብቀን እናወግዛለን። “ጎንደር አንድ ነዉ” በሚል ተንቀሳቅሰን እና ተደራጅተን የጎንደርን መሬት ለማስመለስ እና አንድነታችን ለማስከበር በጎንደር አንድነት (አብሮነት) ጥላ ስር ተሰባስበን ከመታገል ሌላ ምርጫ የለንም። ጎንድር እንደነበረዉ ያልተሸራረፈ ጎንደር ይሆናል። አገራችን ኢትዮጵያም እንደነበረች ለዘለዓለም በአንድነቷ ተከብራ ትኖራለች።
ይህን ዕራያችን እዉን ለማድረግ ለአንድ ዓመት ጠንክረው በኮሚቴ ደረጃ ሲንቀሳቅውሱ የቆዩት የጎንደር የቅማት ብሔረሰብ ተወላጆች እ. ኢ. አ በ 11/23/14 ዓ. ም በጠሩት የህብረት ጥሪ ተሰባሥበን እጅግ መሳጭ እና የጎንደርንም ሆነ የኢትዮጵያን ታሪክ ጠንቅቀው በሚያውቁ እውቅ ምሁራንና እድሜ ጠገብ ተወላጆችን ያካተተ ውይይቶት አድርገን እንደገና ለበለጠ መጠናከር ለሁለተኛ ጊዜ ሁሉን ጎንደሬ አቀፍ ኮሚቴ ከመሰረትን በኋላ በ12/07/14 እጅግ ብዛት ያላቸውን የጎንደር ተወላጆች ቴሌፎን ሰብሰባ (Tele conference) በመጥራት አራት ሰዓት የፈጀ ጥልቅ ውይይት አደረግን።
በነዚህ ሁለት ቀናት የሥልክ ሥብሰባዎች የተገኙት የጎንደር ተወላጆች የመነጋገሪያ አጀንዳቸው የነበረው ከወልቃይት እና ከራስ ዳሸን ወደ ትግራይ መከለል በኋላ ሌላ የጎንደርን አንጀት እንደመዘርገፍ የሚያስቆጥረውን የቅማንትን ብሔረሰብ ከሌላው ወገኑ ለይቶ ለማዋቀር የሚደረገውን አደገኛ እና ወደ ተግባር ሊቀዬር ሲሞከር ሊያመጣ የሚችለውን የሕብረተሰብ ቀውሥ በተመለከተ ነበር።
በነዚህ ሥብሰባዎች፤ የታየው ብሔራዊ ስሜት የተጠበቀም ቢሆን፤ በየአንዳንዱ ተናጋሪ አንደበት ይወጣ የነበረው ፍቅር የተላበሰ፤ ከአንድነት እና ከአብሮነት የተወረሰ ወኔ ቀሥቃሽ ሐሳብ በሲቃ እና በሃዘን የተቀላቀለ ነበር። በተለይም፤ ከታች አርማጭሆ እና ከላይ አርማጭሆ የቅማንት ተወላጅ ካልሆኑ የእድሜ ብቃት ካላቸው አዛውንቶች የተሰማው ልብ የሚበላ ሃሳብ እንዲህ የሚል ነበር፤ “እነ ፊታውራሪ አየለ አባ ጓዴ፤ እነ ደጃዝማች ጣሹ፤ አገራቸው ሲደፈር አሻፈረኝ ብለው፤ ሰላቶን ለረዥም አመታት የተዋጉት የቅማንትን ተወላጅ ብቻ ይዘው አልነበረም። አገሬን ለሰላቶ አላሥደፈርም፤ ለነጭም አልገዛም ያለውን ኩሩ ኢትዮጵያዊ በመምራት እንጂ። በዘመነ ኃይለሥላሴም ዘመነ መንግሥት፤ እነ ሹምዬ በቀለ፤ እንደሻው ቦጋለ፤ ግራዝማች ካሰኝ አለማዬሁ፤ ልጅ ደምረው ጣሹ፤ ተፈሪ ንጉሴ እና የመሳሰሉት ለፓርላማ አባልነት በጎንደር ከተማ እና የተለያዩ አውራጃዎች ተወዳድረው ሲያሸንፉ የነበሩት፤ በቅማንትነታቸው ፤ በቅማንቱ ሕዝብ ብቻ ተመርጠው ሳይሆን፤ ሁሉም የጎንደር ሕዝብ የዘር ሃረጋቸውን ሳይመዝ በእውቀታቸው እና በችሎታቸው ይወክሉኛል፤ ጉዳዬን ያሥፈጽሙልኛል በሚል መርጧቸው እንጂ” በማለት የአንድነት ኩራታችን የሆነውን የሩቅ ጊዜ ትዝታ ታሪክ በመጥቀሥ፤ በዚያን ዘመን የነበሩትን ታሪክ ሰሪዎች በማወደሥ፤ አንድነታችን ዛሬም በሚያልፍ መንግሥት፤ የማያልፍ ሥም እንዳንፅፍ፤ በሚል ለዚህ ትውልድ አደራነታቸውን አሥተላልፈዋል።
በአጠቃልይ፤ በነዚይ ሁለት ቀናቶች በተደረገው የሥልክ ስብሰባ (Teleconference) በሚከተሉት ዋና ዋና ነጥቦች ላይ በመሥማማት፤ አገር ውሥጥ ለሚገኙ ወገኖቻችን እንደሚከተለው የውሳኔ ሃሳባቸውንን አሥተላልፈናል።
1. በአገራችን ኢትዮጵያ ለሃያ ሦስት ዓመት የአገሪቱን ሰላም እያመሰ ያለው የጎሳ ክልል፤ ወደ ጎንደር ሲመጣ ደግሞ እጅግ የከፋ እንደሚያደርገው ተገንዝበው፤ የቅማንት ማንነትን ከማሥከበር በመለሥ፤ ራሥን በራሥ የማሥተዳደር ጥያቄን ያነሱ ወገኖች፤ እንደገና ዓላማችውን እንዲመረምሩ።
2. በሰሜን አሜሪካ የደላ ኑሮአቸውን እየኖሩ፤ ከዬትም ዓለም የተሰባሰቡ ህዝቦች፤ ያለ ልዩነት ሲኖሩ፤ የሰው ልጅ በዘሩ ሳይሆን፤ በሰባዊነቱ መከበሩን መረዳት አቅቷቸው፤ ተግባር ላይ ሊውል የማይችለውን የወገኖቻችን የወሰን ጥያቄ እንቅሥቃሴ በገንዘብ የሚያግዙ ሰሜን አሜሪካ ያሉ፤ የቅማንት ተወላጅ ወገኖቻችን፤ የአገር ቤቱ እንቅሥቃሴ ወደ ፈራነው አቅጣጫ ሄዶ የደም መፋሰሥ ችግር ቢፈጥር፤ በታሪክ እንደሚያሥጠይቃቸው አውቀው፤ የያዙትን አቋም እንደገና እንዲመረምሩ እና ከእኛ ጋርም ተቀራርበው እንድንመካከር በዚህ አጋጣሚ ጥሪ እናደርጋልን።
3. የቅማንት እና የአማራ ብሔረሰብ በልማድ በየጎሳቸው ተዋውቀው ቢኖሩም፤ በእምነት፤ በባህል፤ በቋንቋ፤ በታሪክ እንዲሁም በቦታ የተሳሰሩ በመሆናቸው፤ ለያይቶ ለማሥቀመጥ የማይቻል ከምሆኑም በላይ ሙከራው ራሱ የከፋ ታሪክ ጽፎ ከማለፍ በሥተቀር፤ በተግባር ላይ ሊውል የማይቻል መሁኑን የሁለቱ አካባቢዎች ተረድተው አሥቸኳይ መፍትሔ እንዲፈልጉለት።
4. የኢትዮጵያ ገዥው መንግሥትም ሆነ የክልል መሪዎች፤ ይህን ራሥን በራሥ የማሥተዳደርን ጥያቄ ያሥነሳውን የቅማንት ብሔረሰቦች ብሶት በቀናነት ከመፍታት አልፈው፤ ብሶቱን እውነት የክልል ጥያቄ አሥመሥሎ ማሥተናገድ፤ እጅግ ለአካባቢው
4 አለመረጋጋት ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸው ተገንዝበው በሁለንተናዊ መልኩ የተዋህደውን ህብረተሰብ ሰላም፤ በራሥ አሥተዳደር ሥም ከማደፈረሥ እንዲቆጠቡ።
5. መላው የጎደር ህዝብ፤ በቅማንት ብሔረሰብ ወገኖቻችን የተነሳውን፤ የራሥን በራሥ የማሥተዳደር ጥያቄ አደገኛነት ተገንዝቦ፤ ለዚህ ጥያቄ ያነሳሳቸውን በደል በጋራ እንዲመረምር እና ችግሩን በጋራ ለመፍታት በጋራ እንዲቆም።
6. ሁለቱም የቅማንት እና የአማራ ቤተሰቦች፤ በዚህ በሰለጠነው ዘመን፤ ኋላ ቀር የሆኑ፤ የሰውን ልጅ እንደ ሰው የማያስቆጥሩ አፈ ታሪኮች አሥወግደው፤ የመናናቅ እና ያለመከባበር አጉል ባህል ተላቀው፤ ሥድብ እና ዛቻ፤ ጠብ እና ጥላቻን፤ ብሎም እስከ መገዳደል ከሚያደርሱ ፉክክሮች ተቆጥበው፤ ይህ ሥራዓቱ ያመጣባቸውን የዘር ጣጣ፤ በብልሃት ይዘው ጊዜውን እንዲሻገሩ።
7. ይህን አጋጣሚ ተጠቅመው በሰላም ያለ ወሰን ለረዥም ምዕተ ዓመታት የኖሩትን ህብረተሰቦች እሥከ ወዲያኛው እንዲለያዩ ከሁሉም አቅጣጫ የውጡልኝ ጥያቄ ያነሱ ቡድኖች፤ እየሰሩ ያሉትን እጅግ ትርጉም የሌለው እንቅሥቃሴ አቁመው፤ በዚህ ምክንያት በአካልም ሆነ በህሊና የበደሏችውን ወንድሞቻቸውን፤ በአካባቢው በተመረጡ ሽማግሌዎች አማካኝነት ይቅርታ ጠይቀው፤ የአካባቢውን ሰላም እንዲያረጋጉ።
8. እጅግ አሳዛኝ እና ከሰባዊ ተፈጥሮ ውጭ በሆነ መልኩ፤ ዛሬ የሰው ህይዎት ቀርቶ፤ የእንሰሳት ህይዎት ክብር እያገኘ በመጣበት ዘመን፤ በኮምፒተር ጀርባ፤ በፌሥ ቡክ፤ “የማን አባት ጎበጠ” አይነት ፉክክር የሳይበር ጦርነት የከፈቱ የቅማንት ተወላጆች ነን የሚሉ ጥቂት ግለሰቦች፤ ወደ ህሊናቸው ተመልሰው፤ ጦርነት ጥፋትን እንጂ ልማትን እንደ ማያመጣ ተረድተው፤ ወደ ሰላማዊ ህሊናቸው እንዲመለሱ።
የሚሉትን እና የመሳሰሉትን የውሳኔ ሃሳቦች ከተሰነዘሩ በኋላ፤ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን በመላ አገሪቱ እያመሰ ያለውን ጊዜው ያለፈበት የጎሳ ፖለቲካ ፋሽን በመተባበር አውልቆ እንዲጥል እና ሁሉም በጎሳ በረት ሳይዘጋ፤ በመላው የኢትዮጵያችን ክልል ተከባብሮ እና ተፋቅሮ በፈለገበት ቦታ በኩራት የሚኖርበትን ሥርአት እንዲፈጥር የትግል ጥሪያችን እናሥተላልፋለን።
እንዲሁም መላ የጎንደር ተወላጆች፤ ይህን የሕዝባችን አንድነት የመጠበቅ ቅዱሥ ዓላማ፤ ያላችሁን የአገርቤት ግንኙነት መሰመር በመጠቀም፤ የበኩላችሁን ድርሻ በመወጣት እንድትተባበሩ አደራ እንላለን።
በጎንደር ክ/ሀገር እየተለኮሰ ያለው የጎሰኝነት እሳት ያሳሰበን በውጭ አገር የምንተኝ የጎንደር ክ/ሀገር ተወላጆች ጊዚያዊ አስተባባሪ ኮሚቴ።

No comments:

Post a Comment