ከአየነው ብርሃኑ
ኢትዮጵያዉያን የዉጭ ጠላት ሲነሳባቸዉ የዉስጥ ልዩነታቸዉን ወደ ጎን በመተዉ ጠላትን ድባቅ የመምታት አቅሙ እንዳላቸዉ የሩቅም ሆነ የቅርብ ታሪካችን ነዉ።
ከቅርቡ እንኳን ብንነሳ በሻቢያና ወያኔ የጥቅም ግጭት ምክንያት በተነሳ ጦርነት ሮጠዉ ያልጠገቡ ወጣቶች የፈንጅ ማምከኛ እየሆኑ ዉድ ህይወታቸዉን አሳልፈዋል።
ወያኔ ለራሱ ህልዉና ማጠናከሪያ ቢጠቀምበትም የጦርነቱ የመጨረሻ ዉጤት ለኢትዮጵያ ያደላዉ ከኢትዮያዊነት ስሜት በመነጨ ወኔ መሆኑ አይዘነጋም።
አዎ ወያኔ እና ጀሌዎቹ ከኋላ ፤ በሺህዎች የተቆጠሩ ወጣቶች ግን በግንባር ቅደምትነት ተሰልፈዉ የቦንብ ማምከኛ በመሆናቸዉ የጦርነቱ አቅጣጫ ተቀየረ። በዚህ እልቂት ኢትዮጵያዉያን እናቶች የሃዘን ማቅ ለበሱ። ወያኔም በሥልጣን መንበሩ ላይ መቆየቱን አረጋገጠ።
ጭር ሲል አልወድም የሚለዉ ወያኔ ዛሬም የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ ነው። የማይደፈር ሃይል መሆኑን ለማሳየትም በርጥባን ከጌቶቹ ያገኘዉን የጦር መሳሪያ ከቦታ ቦታ በማንቀሳቀስ ህዝብን በማሸበር ላይ ነዉ።
በጦር ሃይሉ ዉስጥ ያሉ የሌላ ብሄር የጦር መሪዎችን በማባረር በአንድ ዘር ላይ የተመሠረተ የግድያ እና የጥፋት ሃይሉን በማዘጋጀት ላይ ዪገኛል።
ለዚህ ተግባር የሚዉል አዲስ ወታደራዊ ቅጥር ጥሪ እያደረገ መሆኑ ዪታወቃል።
የኢትዮጵያ መሰረታዊ ጠላት ከሆነችዉ ሱዳን ጋር ወታደርዊ ስምምነት አደረኩ የጋራ ጦርም መሠረትኩ በሚል ለጥቂት ቀናት አደነቆረን።
ተጠቅሞ የጣላቸዉን የቀድሞ ሰራዊት አባላት ተመልሰዉ እንዲቀላቀሉት በተለያየ መንገድ ጥሪ እያደረገ ነው። ሁሌ እኔ ብቻ ላሞኛችሁ የሚል የደንቆሮዎች ዘይቤ። መልሱ ግን ሞኚህን ፈልግ ሆነ !!
ለመሆኑ ይኸ ሁሉ የጦርነት ነጋሪት መጎሰም ከምን መጣ ? ይህ የድረሱልኝ ጥሪ መነሻዉ ምንድን ነዉ፡የዉጭ ጠላት አልወረረን!!!!!
የወንድ ልጅ ሞቱ የሚጀምረዉ ያደረገዉን የረሳ ጊዜ ነው ይላሉ አበዉ ሲተርቱ።
ሃብት አደንቁሮአቸዋልና !! ወያኔን ለማጥፋት አዲስ አበባም ጫካ መሆኑን ለመገንዘብ የዕዉቀት አድማሳቸዉ አልፈቀደላቸዉም ።
ያም ሆነ ይህ ግን ምኞታቸዉ የተሳካ ጥያቂያቸዉም በአግባቡ እየተመለሰላቸዉ ባለበት ጊዜ ላይ ደርሰዋል። የስብሃት ነጋ የዘር ጥላቻ፡ የአባይ ጸሃየ የዕምነት ተቋማትን የማፈራርረስ ሴራ፤የአዲሱ ለገሰ ከጡረታ መመለስ ከውዲያ ወዲህ መፈራገጥ፤ የበረከት በስብሰባ ላይ ራሱን ጥሎ ከመዉድቅ ዉጭ ፋይዳ ያለዉ ሥራ ለመከወን ከማይችልበት ደረጃ ላይ መድረስ ወይም ደግሞ ብአዴን በግንቦት ሰባት ኦህዴድንም በኦነግነት መፈረጅ ከዉድቀት አያድናቸዉም ።
የእነ ደብረጽዮን እና ጌታቸዉ አሰፋ ድንበር ዘለል የዉንብድና ተግባር አልፈየደም ። የህዝብ ወገኖችን እያደኑ መያዝ፡ በአለም ላይ አለ የተባለ የማሰቃያ መንገድ ሁሉ በታጋዮች ላይ እንዲፈጸም ማድረግ በተጠናወታቸዉ የዘር ጥላቻ እየተወጠሩ ለመኖር እና ያለ አግባብ በተካበተ የሀገር ሃብት እየተንደላቀቁ ለመኖር መፍትሄ አልሆነም።
በሌላ መልኩ የመሃል አገር ህዝብ የወያኔን የከፋፍለህ ግዛ ዘይቤ በመበጣጣስ አንድነቱን አጠናክሮ ወያኔን ጥግ ማስያዝ ከጀመረ ሰነባበተ ። የህዝብ ጉልበትም መጎልበትና መፈርጠም ጀምሮአል ።
ሰላሙና ተቻችሎ መኖሩ ይበጃል በሚል እንጂ ለሌላዉማ ከእናንተ በተሻለ እኛም እናዉቅበታለን የሚሉ አንበሶች ብቅ ብቅ ማለት ከጀመሩ ሰነባብተዋል። አንድነታቸዉንም አጠናክርው ለመጨረሻዉ ፍልሚያ በትጠንቀቅ ላይ ይገኛሉ ።
ለዚህም የትግራይ ረመጦች በአንድ በኩል የግንቦት 7 ፤ የአርበኖች ግንባርና ሌሎችም አንበሶች በሌላ በኩል ለዎያኔ እኩይ ተግባር ምላሽ ለመስጠት ዝግጅታችንን ጨርሰናል በሚል የድል ችቦ እየለኮሱ ያሉት ህያዉ ምስክር ነው።
ወያኔ አንድ አርጋቸዉንና ሌሎችንም በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ያዘ፤ አሰቃየ ፤ የአካልም የመንፈስም ጉዳት አደረሰ ይህን ሲያደርግ ግን ያለኪሳራ አይደለም። መቃብሩን እየቆፈረ መሆኑን ራሱ ወያኔም ያዉቀዋል ።
ለትግራይ ረመጦችና ለግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይል መጠናከር መሠረት የሆነዉን አንዳርጋቸዉ ነዉና ። አንዳርጋቸዉን መያዝና ማሰቃየት ዉድቀቱን እያፋጠነለት መሆኑን ወያኔ ራሱ ከተረዳዉ ቆይቶአል።
በሌላ በኩል እስኪ የዘርኝነት መሃንዲሶቹን አንድ አንድ ጥያቄዎች እንጠይቅ፡
ይኸ የህዝብ ትግል የጦርነት ነጋሪት በመጎሰምና የድረሱልኝ ለቅሶ በማላዘን ወደ ኋላ ይቀለበስ ይሆን እንዴ አቶ ስብሃት?
የስንት ቀን ፋታ የምታገኙ ይመስልሃል አቶ አባይ?
በርግጥ የአንተና የስዩም መስፍን ማገገም፡ ወደ ሥራ መመለስና መንፈራገጥ መፍትሄ ይሆን እንዴ አቶ አዲሱ ለገሠ?
ሃዉልትህ ምትሃታዊ ሃይል ኖሮት የልቀቁኝ በቃኝ ጥያቄህን ወደ ኋላ እንድትል ይረዳህ ይሆን ጀኔራል ሳሞራ?
በአፈናና በስቃይ ተግባራችሁ ግለሰቦችን ከማሰቃየት በዘለለ የህዝብን ትግል አፍናችሁ ከዛሬ ነገ ምን ይከሰት ይሆን ከሚለዉ የፍርሃት ቆፈናችሁ የምትላቀቁ ይመስላችኋል እነ ደብረ ጽዮን ፤ ጌታቸዉ በላይ እና የአፈና ቡድናችሁ?
በጭራሺ ከንቱ ድካም። ከንቱ ልፋት። የኢትዮጵያ ህዳሴ መቃረቡን የህዝብ የነጻነት ጮራ እየፈነጠቀ መሆኑን ምነዉ ያኔ የሱዳኑ አባታችሁና የአምልኮት ጣኦታችሁ ሲሞት በቀብር የተገኙት እነስዩም መስፍን አልነገሯችሁም ነበር እንዴ?
ኢትዮጵያዉያንን እርስ በርስ ለማገዳደል እያሰባችሁ ያላችሁት የጥፋት ድግስ የማይሳካ ጊዜዉ ያለፈበት ዘዴ ነው። የተበላ እቁብ !!!
በሀገራዊ ስሜትም ሆነ በግል የኢኮኖሚ ችግርህ አሁን ያለዉን የመከላከያ ሠራዊት የተቀላቀልክ ጭቁን የኢትዮጵያ ሠራዊት አባል ቆም ብለህ አስብ። እነዚህ የቀን ጅቦች ለጥፋት እያዘጋጁህ መሆኑን ለአንዲት ደቂቃም ቢሆን መዘንጋት የለብህም።
የባህር በር እጠብቃለሁ እንዳትል ወያኔ አገርህን የባህር በር አልባ አድርጎልሃል። ድንበር አስከብራለሁ እንዳትል ወያኔ የአገርህን ድንበር እየቆራረጠ ለአገራችን ጠላቶች ለገጸ በረከትነት እያቀረበልህ ነው።
ወያኔ ወኔህን ሰልቦ ብሄራዊ ወኔህን ገፎታል። እንድ ለአምስት እንድትደራጅ ፡መሪህ ከወርቁ ዘር የወጣዉ ብቻ እንዲሆንና አንተ አንድ ካርታ ጥይት ብቻ እንዲኖርህ መሪህ ግን እስካፍንጫዉ እንዲታጠቅ እየተደረገ ያለዉ ለምን ይመስልሃል። በዚህ አይነት ጥርነፋ ከወገኖችህ ጋር እንድትዋጋ ከኋላ ሆነው ሊነዱህ እንደሆነ ግን ተገንዝበኸዋል?
ይኸን ከንቱ የወያኔ ምኞት ለማክሸፍ ከነጻነት ታጋዮች ወገኖችህ ጋር ጊዜ ሳትሰጥ ተቀላቀል።
ይህን በማድረግህ አገርህን ከነዚህ የባንዳ ዉላጆች ነጻ ታወጣለህ ። በስቃይ ላይ የለዉን ወገንህን እንባ ትጠርጋለህ።
በዘር ማንነት ፖለቲካ ተሰብካችሁ ከሌላዉ በበለጠ ጀግንነት የእናንተ ብቻ እንደሆነ እየተሰበካችሁ ያደጋችሁ የመሪነት ቦታዉን የያዛችሁና እኛ ከኋላ ሆነን ሌላዉን ኢትዮጵያዊ ከፊት በማሰለፍ የጌቶቻችንን የስልጣን ዕድሜ እናራዝማለን ብላችሁ በዘር ላይ የተመሠረተ ቃለ መሃላ የፈጸማችሁ ። ይህ መሃላ ግን መፈራረሱን ወደ ህዝብና ወደ ህሊናቸዉ ተመልሰዉ ወደ ዕዉነታዉ ዓለም በተቀላቀሉት ሻምበል ግደይ ሳሙእል እና ቴክኒሺያን ፀጋብርሃን ግደይ ላይ ያዎረዳችሁት የከሃዲነት ዉንጀላ አብይ ምስክር ነው።
በከንቱ ዉዳሴ ተወጥራችሁ ህዝብን አሸንፈን በሥልጣናችን እንቀጥላለን ብላችሁ የምታስቡ የጦር መሪ ነን ባዮች ወደ ህሊናችሁ ተመለሱ። የኢትዮጵያ ህዝብ ከእናንተ ጋር ምንም ችግር የለበትም። ታሪኩ፡ ባህሉ ወጉና ልምዱ በአብሮ መኖር በኩል ችግር እንደሌለበት ምስክሮች ናቸዉና!!!
በሌላ በኩል ግን የትግራይ ረመጦችም ሆኑ የግንቦት ሰባት አንበሶች ለአንድ አላማ ለኢትዮጵያዊነት እና በሰላም ተቻችሎ ለመኖር ነዉ እየዘመሩ ያሉት።
ይህ ሲባል ግን ስብሃት ነጋ ከዘር ጥላቻዉ እንዲላቀቅ ሱባኤ እንዲገባ አይደረግም ማለት አይደለም።
አባይ ጽሃይም ላለበት ሃይማኖትን የማፍረስ አባዜ በአርባ ቀን ጥምቀት ለመንጻት ቄስ አያጠምቀም ወይም ሼህ እይጎበኘዉም ማለት አይደለም። የትኛዉ እንደሚፈዉሰዉ ምርጫዉ የራሱ ነው።
የነ ደብረጽዮን ፤ ጌታቸዉ አሰፋና አምስቱ የአፈና ቡድናችዉ የመሰረቷቸዉን ድብቅ ያማሰቃያ ቦታዎች ይፋ እንዲያደርጉ ፤ ያጠፏችዉን ኢትዮጵያዉያን ዝርዝር እንዲያቀርቡ ህዝብ አይጠይቃቸዉም ማለትም አይደለም።
ሳሞራ የኑስ ምን ኣልባት ለዚያ ከደረሰ የጀኔራልነት ሃዉልቱን ተሸክሞ በአደባባይ በመዞር ለዚህ ያበቃዉን ገድል እንዲተርክለት ህዝብ ይጠቅ ይሆናል ።
የብአዴን፤ ኦህዴድና ኦህዴድ ፈረሶችም ቢሆኑ በሀገር ላይ ክህደት ከፈጸመዉ ደመቀ መኮነንና በንጹሃን ደም እጁ ከተጨማለቀዉ ሃይለ ማርያም ደሳለኝ እና ከመሳሰሉት በስተቀር ሌሎቹ የማስመሰያ የዘር ጭምብላቸዉን አዉልቀዉ ለአጠፉትም ጥፋት ይቅርታ ጠይቀዉ ወደ እዉነተኛ ማንነታቸዉ እንዲመለሱና የ 24 ዓመት ድራማዉን እንዲተርኩለት የኢትዮጵያ ህዝብ መጠየቁ የሚቀር አይመስለኝም።
የትናት ሺፍቶች የዛሬ ሚሊዮነር ጀኔራሎች የሃብት ምንጫቸዉን እንዲነግሩን መጠየቅ የኢትዮጵያዊነት መብታችን መሆኑም መዘንጋት ያለበት አይመስለኝም።
ዕዉነት ዕዉነት እላችኋለሁ ። ዛሬ ወገኖቻችን እየታደኑ በተገኙበት እርምጃ የሚወሰድባቸዉ ፤ ወደ ወህኒ የሚወረወሩት እና ሁሉም ስቃይ በህዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለዉ ወያኔ በጣዕር ላይ በመሆኑ እርምጃዎቹ ሁሉ የደመነፍስ በመሆናቸዉና በዚያዉ ከዘር ጥላቻ በመነጨዉ ጥላቻዉ ነው።
እናም እላችኋለሁ ግንቦት ወር የወያኔ የምርጫ ድራማ የምናደምቅበት አይሆንም። በሌላ በኩል ግን ወያኔን አሽቀንጥረን ጥለን ለመቻቻል አብሮ ለመኖርና ያገራችንን የወደፊት አካሄድ የምወስንባት ወር ነው መሆን ያለባት ግንቦት ወር።
ይህን ዕዉን ለማድረግ በጥቅማ ጥቅም ተገዝተህ ለዘረኛዉ ቡድን ሰግደህ ያደርክ ሁሉ ወደ ህሊናህ ተመልሰህ ከህዝብ ተቀላቀል።
ለግል ጥቅምህ ተገዥ በመሆን ከዚህም ከዚያም አይደለሁም እያልክ ሌላዉ ሳይሆን ራስህን እያታለልክ የምትኖር የወገንህን ብሶት አስብ ከጎኑም ለመሰለፍ ጊዜ አትዉሰድ።
ባጋጠማችሁ መልካም አጋጣሚ ሥልጣን ላይ ተኮፍሳችሁ ያካበታችሁት ያገር ሃብት የማሰብ ህሊናችሁን ለሸፈነው ዘረኞች የእስካሁኑ ይበቅል ። የያዛችሁትን ለመብላት ከበቃችሁ ከበቂም በላይ ሁሉንም አድርጋችኋል። ይህ ግን እንዳይቀጥል ህዝብ በቃ ብሎአል እና ለሁሉም አይንት ጥፋት ብላችሁ ከምርጥ ዘራችሁ ዉስጥ ያዘጋጃችሁት የጥፋይ ሃይል አያድናችሁምና ለንስኃ ሞት የምትበቁበትን መንገድ ፈልጉ የምነት ድሃዎች ። ህዝብ በቃ ብሎአልና!!!
የጥፋቱን መጠን መቀነስ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ነኝ ለሚል የሆነ ሁሉ ሃላፊነት ነዉ።
ከዚህ በተረፈ ግን ሁሉንም ሥራዉ ያዉጣዉ !!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !!!
No comments:
Post a Comment