Page 1 of 2
ሚስጢረኛ መፅሐፍ ተናግሮ አናገረኝ
ተነስ ተነስ ብሎ ከእንቅልፌ ቀሰቀሰኝ::
ዕድሜ ለሰጣቸው በሂይወት ለኖሩ
መቆየት ደግ ነው ማየት ቁም ነገሩ
በግፍ ያለቁ በከተማ በገጠሩ
አስታዋሽ አጥተው ተጥለው የቀሩ
በሲኦል ጨለማ ወህኒ ቤት የታጎሩ
ጊዜ ዳኛ ነው ታሪክ ምስክሩ
በቀለም ተከትቦ አየነው ሚስጢሩ
ለካስ ደምም አፍ አለው ይናገራል ብዕሩ::
ጉራንጉሩን አልፎ መሰናክል ሰብሮ
ግራ ቀኙን አይቶ በሰከነ አእምሮ
ያባቶች ጀግንነት በሃዲስ ቀምሮ
ሀቁን ለማውረስ ትውልድን ተሻግሮ
ገብሩ ታሪክ ፃፈ መቃብር ቆፍሮ::
እሰይ እልል ትንሳኤ ሙታን ተበሰረ
አዲስ ዘመን ብሩህ ተስፋ ተጀመረ
ያንድነት ምሰሶ የማዕዝን ድንጋይ አኖረ
የጥላቻ የቂም ድንበር አጥሩ ተሰበረ
ወንድም ከወንድሙ ጋር አበረ አበረ አበረ
ሚስጢረኛው መፅሐፍ ተናግሮ አናጋረ
ገብሩ ደስ ይበልህ የልብህን ሰመረ ሰመረ ሰመረ::
እልል ይባላል በተለምዶ
ሰው ሲያይ ልጅ ወልዶ
ድልድይ ሲሰራ ሁሉም አዋህዶ::
አዎ ገብሩ!! ደስ ይበልህ ደስ ብሎናል
ጥሪህን ሰምተናል ስራህን አድንቀናል
ካንተ ፅናት ፍቅር ጥበብ ተምረናል
አንተም ኩራ እኛም ባንተ ኮርተናል::
ታጋይ እንደ ሻማ ራሱን እያቀለጠ
ሂይወቱን ሁሉ ለትግል የሰጠ
ከንሮው በላይ ሀገሩን የመረጠ
በይቅርታ መንፈስ ራሱን የለወጠ
በዚህ ዓለም ምን አለ ከዚህ የበለጠ::
በቂም በቀል ያልከረረ
በፍቅረ ንዋይ ያልታወረ
ህልናው ያልሸጠ ስብእናውን ያልቀየረ
ያልተንበረከከ ለጥቅም ያላደረ
በስልጣን ሱስ ያልሰከረ ያልተደናበረ
እምቢ ባይ ለሀገሩ ፍርሃትን የሰበረ
ምን ነው እንዳንተ ሚሊዮን ሰው በተፈጠረ::
ታዲያ!! ማን ብዬ ልጥራህ ምን ብዬ ልናገር
አንዳለም ልበልህ ወይስ እስክንድር
ብርቱኳን ልበልህ የናትነት ፍቅር
አብርሃ ወይስ አረጋዊ የፅናት መምህር::
እኮ ንገሩኝ ማን ልጥራ ምን ብዬ
በላይ ልበለው ጀግናው በላዬ
ባልቻ ልበለው ወይስ ገብርዬ
ጣይቱ ብየ ልጥራው እምዬ::
አቶ ገብሩ አስራት “ሉኣላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮያ” በሚል ዓቢይ ርእስ የፃፉትን ድንቅ መፅሐፍ ምክንያት በማድረግ በዋሽንግተንና
አከባቢዋ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮያውያን በመተባበር ዲሰምበር 7, 2014 ዓ.ም ለአቶ ገብሩ አስራት ታላቅ የሽልማት" የአድናቆትና
የምሳ ዝግጅት አድርጓል:: በዕለቱ ከተለያየ ቦታ የመጡ ምሁራንና ሌሎች ታዳሚዎች ተራ በተራ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ለአቶ ገብሩም
ላደረጉት የላቀ አስተዋፀኦ የተዘጋጀውን የክብር ሽልማት ተሰጥቷቸዋል:: ከዚያም አቶ ገብሩ ንግግር በማድረግ ቤቱን አመስግኗል:: ስነ
ስርዓቱ ከቀኑ 2 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ 8 ሰዓት በመቀጠል የተለያዩ ዝግጅቶችን በማከናወን የበዓሉን ፍፃሜ ሆኗል:: በዓሉን
የሚመለከቱ ዝርዝር የኦዲዮና የቪድዮ ሪፓርታጅም በቅርቡ በሚዲያ ስለሚወጣ እንድትከታተሉ እንጋብዛለን::
በበዓሉ ቀን አቶ ገብሩ አስራትን ለማድነቅና ለማመስገን ከተለያዩ ግለሰቦች ከቀረቡት በርካታ ዝግጅቶችና አስተያየቶች ውስጥ ከዚህ
ቀጥሎ ያለውን ምርጥ ግጥም መርጥንላችሗል::
ሚስጢረኛ መፅሐፍ ተናግሮ አናጋሪ
Page 2 of 2
አሉላ መሰልከኝ መረብ ተሻጋሪ
ባድመ ፆሮና የመጣው ወራሪ
ምድረ ከሃዲ የውስጥ ቦርባሪ
ድባቅ የምትመታ የማፍያ አከርካሪ
ሚስጢረኛ መፅሐፍ ተናግሮ አናጋሪ
የልቡን ሰርቶ ድል አብሳሪ::
አዎ!! ገብሩ የሁሉም ነህ በመላ
ስልጤ ወላይታ ሃዲያ ዶርዜ ጋምቤላ
አኝዋክ ሱማሌ አደሬ አርጎባ አሰላ
የሐንስ መተማ ቴድሮስ በመቅደላ::
አንተ የሀገር ልጅ ኢትዮያዊ እማማ
ትግራይ አፋር አገው ሳሆ ኩናማ
አማራ ኦሮሞ ጉራጌ ሲዳማ::
ያምራል ቀለሙ እንደ ነብር
ጉንጉን አበባ ዝንጉርር
ያንድነታችን ተፈጥሮኣዊ ሕብር
ሚስጢረኛ ፅሑፍ ተናግሮ የሚያናግር
መፅሐፍህ የኛ ነው የማንነት ክብር::
ገብሩ!! ስራህ ድንቅ ነው ያኮራል
ድልድይ ሆኖ ያሸጋግረናል ያስተባብረናል
የትግል ችቦ ያቀጣጥላል ይደምቃል ይበራል
ሃያል ነው ሚስጢሩ ገና ተናግሮ ያናግራል::
ደስ ይበልህ ደስ ብሎናል
ጥሪህን ሰምተናል ስራህን አድንቀናል
ካንተ ፅናት ፍቅር ጥበብ ተምረናል
አንተም ኩራ እኛም ባንተ ኮርተናል
አለን ከጎንህ አብረን ቁመናል::
ከበላይ ገሰሰ
Belgesse@aol.com
No comments:
Post a Comment