Friday, December 5, 2014

የወያኔ ምርጫ – ጭንጫ። (ሥርጉተ ሥላሴ

ከሥርጉተ ሥላሴ 05.12.2014 /ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ/
እንደላበዛባችሁ እዬሰጋሁ ግን የገጠመኝን መልካም ነገር ቀድሜ ላወጋችሁ ወደድኩኝ። እባክቻሁ ውዶቼ ፍቀዱልኝ? መቼም ዘንድሮ አውጊ አደራ ሁኛለሁ። …. የማንነት ጽጌረዳ ነውና አትቆርጡም ብዬም አስባለሁ።
2007 electionእንደ – በር። አልኳችሁ ትንሽዬ ቀጠሮ ኖራኝ ወደ አንድ የማላውቀው ሰፈር ተጓዝኩኝ – ዕለተ – እሮብ። የምሄድበት ቦታ አዲስ ስለነበረም ከቀጠሮዬ ሰዓት በፊት ሁለት ሰዓት ቀድሜ ነበር የደረስኩት። ከዚህ በኋላ ትንሽ ሻይም ቡናም ከተገኘ ብዬላችሁ ላይ ብል ታች ብል ፈጽሞ ምንም የሚላስ የሚቀመስ ነገር በአድባሩ የለም። እንዲህ ደግሞ ገጥሞኝ አያውቅም። ወደ ላይ ሲኬድ ቀጥ ያለ አስፓልት ወደ ታች ሲወረድም ቀጥ ያለ አስፓልት።
በዛ እንደ ባንዴራ በማተቡ በፀና ሎጋና ዠርጋዳ አስፓልት ዳር ለዳር አንዲት ሩጫ የምትለማመድ ደማም ውብ ጸዳላማ ወጣት አገኘሁና „ሻይ ወዴት ላገኝ እችላለሁ?“ ብዬ ጠዬቅኳት። „በዚህ አቅጣጫ ሁለት ሰዓት ብትጓዢ አንዲት ትንሽዬ ኪወስክ ታገኛለሽ። ቡናዋ ግን አይጣፍጥም። በስተቀር ግን ወደ ከተማ ተመልስሼ ካለሆነ በስተቀር እምታገኚው ነገር ዬለም“ ብላ ቁርጤን ነገረችኝ። አመናታሁና ለምን ከዛው ከተቀጠርኩበት አካባቢ ሰማይና መሬት ያገናኘ ዬሚመስለውን የተንጣለለ ሃይቅ እያዬሁ አልቆይም ብዬ ወደዛው አቀናሁ። ብርዱ ደግሞ አይጣል ነበር። አሳቻ ቦታ ላይ  በጣም ወደ ውስጥ ገባ ባለ የወንዝ የመንገድ ግድግዳ አንድ በር ሲከፈትና ሲዘጋ ስላዬሁ ሰዎች በሚገቡበት አቅጣጫ እኔም ዘው ማለት ….
ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ቦታው ባር ነገር ነው። በውጪ ምንም የተፃፈበት ነገር የለም። ሙዚቃው ደግሞ ምን ሊሆን ይችላል ብላችሁ እስኪ ገምቱ – በሥርጉተ ሞት? ገመታችሁ? ይግርማችኋል ለ1.30 ሰዓት ያህል ቀጠሮዬ እስኪደርስ ተቀመጥኩኝ። ሳይቋረጥ የኢትዮጵያ የመሳሪያ ቅንብር ሙዚቃ ነበር አድባሩን የተቆጣጠረው። ሻዬን ከያዝኩኝ በኋላ ጠጋ ብዬ አስተናጋጁን „ዬዬት ሀገር ሙዚቃ ነው ስል በትህትና ጠዬቅኳቸው?“ ቀጥዬም „አድራሻውን ሊሰጡኝ ይችላሉን?“ አልኳቸው፤ ቀልጠፍ ብለው። „የመሳሪያ ቅንብሩ ሙዚቃ  የኢትዮጵያ በህላዊ ሙዚቃ ነው። ከፈለጉ ደግሞ ሥሙን እሰጠወታለሁ“ አሉኝ። ግርም ብሎኝ ሌላ ጥያቄ ደግሞ ቀጥልኩ „ከዚህ ከእናንተ ባር ኢትዮጵያውያን ሠርተው ያውቃሉን? ወይንም የሚሠራ ኢትዮጵያዊ አለን?“ ስል ጠዬቅኩኝ ….
መቼም ኢትዮጵውያን የጠረናችን ነገር አይሆንልንምና። „ኢትዮጵያዊ ተቀጣሪ የለንም“ አሉኝ። „ኖሮንም አያውቅም።“ በማለትም አከሉልኝ። ቀጥለው ትንሽ እንደማሰብ ብለው „ ነገር ግን እዚህ የጃፓን፣ የቲቤት፤ የቻይናና የኢትዮጵያ የመሳሪያ ሙዚቃዎች የተለመዱ ናቸው። እንግዶቻችን በፍቅር ይወዷቸዋል“ አሉኝ። እኔም ለካንስ የነዚህ ሀገሮች የመሳሪያ ቅንብር ሙዚቃ ለእኔም በግሌ የሚስቡኝ ተመሳሳይ ዬቃና ቅኝት ስላላቸው ይሆን ብዬ ራሴን ጠዬኩኝ። አዎን የአንገቴን ጌጥ በስንድድ የተሠራውን አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ገለጥ አድርጌ „እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ“ ብዬ ነገርኳቸው። ደፍረው የሚናገሩት፤ አንገትን የማያስደፋ – ባርነት ያልጎበኘው፤ የነጠረ ማንነቴ ኢትዮጵያዊነት አለልኝና። ቀጥዬም … „ይህ አክብሮታችሁ የሰማይ ነው እንጂ የምድርም አይደለም። እግዚአብሄር ይስጥልን አልኳቸው።“ ትክ ብለው በመገረም አይተው „እኔም አመሰግናለሁ“ አሉኝ።
እስከ አሁን ይገርመኛል። ደስታውም አልቀቀኝም። እኛ ያልሠራንበትን ጥበበኛው አምላክ እንዲህ አሳምሮ ይሠራልናል። ያግዘናል – የቃል ኪዳን ሃገሩ ናትና – ኢትዮጵያ! የሚደንቀው ነገር የመሳሪያ ቅንብሩ የእነማን እንደ ሆነ፤ ባንዶችን ሳይቀር በዝርዝር ነበር የነገሩኝ። በተጨማሪም ኢትዮጵውያንና ሆላንዳውያንም የጋራ ባንድ እንዳላቸው መረጃውን ሰጡኝ። እንግዶቻቸውም በጣም የሚወዱት ስለሆነ ሙሉ ጊዜውን ሲያዳምጡት ቢውሉ እንደማይሰለቻቸው ገለጹልኝ። እንዲህ ያልተወለደን በፍቅር የሚገዛ ውስጣችሁን ባላሰባችሁበት ቦታና ጊዜ ሲገጥም ከቶ ምን ትላላችሁ? እጅግ ደስ ያለኝና የወደድኩት ጊዜ ነበር። በጋ ላይም ሥራዬ ብዬ እሄዳለሁ። …. ክብራችን – ፍቅራችን ለመጎብኘት …። እንዲህ እንደ ተፈለገ የማይንዘገዘግ ማንነት ያለው ነው ኢትዮጵያዊነት ማለት። ”ኢትዮጵያ ብዙ የተደከመባት እና ብዙ ትላልቅ ሰዎች የተሰዉባት ሀገር ነች!” – ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት (የጉዳያችን ማስታወሻ)http://www.zehabesha.com/amharic/archives/36814 እኔም እላለሁ ኢትዮጵያዊነት ረቂቅ ቅዱስ መንፈስ ነው።
እጅግ የሚገርም ነበር። ውስጤን አብዝቶ ፈተሸኝ። ባህላዊ ምግብ ቤት ገብቼ አዳምጬ ስለማላውቅ ማለት ከሀገሬ ከወጣሁኝ፤ ሀገሬ የገባሁ ያህል ነበር የተሰማኝ ለዛውም በነጮች ባር። ወግ አበዛሁ አይደል ክብሮቼ? ተፈርዶብኝ ነው። ደስ ስላለኝ ነው። ይቅርታ … እኔም ቋጥሬ የሄድኩት የእምዬን ዕንባ ስለነበረ … አገጣጠመችው …. ወፊቱ …
የወያኔ ምርጫ – ጭንጫ።
አሁን ወደ ተነሳሁበት ግን አጠር፣ ደንበል አድርጌ – ጭንጫና ቁም-ነገር መንገድ ላይ እንኳን ተገናኝተው አያውቁም። ጭንጫና ፍቅር ሆነ ጭንጫና አብሮነትም እንዲሁ። ጭንጫና ፍትህ ሆነ ርትህም አይጥና ድመት ናቸው። ውዶቼ እስኪ በርከት ያሉ ጭንጫዎችን ከመዳፋችሁ ላይ ኮልኮል አድርጋችሁ እዮዋቸው። ምን ይመስላሉ? ኮልኩሏቸውም፤ – ይስቃሉን? ለመሆኑ ነፍስ ቢጤ አላቸውን? ይተነፍሳሉን? አባብሏቸው – አቆለማምጧቸው? የሚረዱት የሚገባቸው ነገርስ – ይኖራልን?
ቀጥላችሁ ደግሞ ጭንጫውን ውሃ ውስጥ ጨምሩት። ከቶ ሟሟን? ተቀላቀሉን? እንዲያው ምንስ መልክ ኖረው ከቶ? እ … ቡላማ …. አመዳም? ወይንስ የንፁሁን ውሃ ተፈጥሮ ብክል አደረገው ይሆን? አወና! …. መልከ ጥፉ ስለ ሆነ ደህናውን የውሃንም ተፈጥሮ አጎሽቶ አይሆኑ አደረገው አይደል? አንዷን ጭንጫ አፈፍ አድርጋችሁ ደግሞ በጥርሳችሁ እስኪ ሞካክሯት? ታዲያ እንደ እኔ ፈንጠርጣራ ካልሆነ ነው። ደግሞ በህግ እንዳልጠዬቅ …. ባለ ጠንካራ ጥርሶች ፍንክች አለላችሁ ይሆን ሞገደኛው – ጭንጫ?
ጭንጫ ቀዳዳም አልሰራለትም፤ መተንፈሻ ቧንቧም የለውም። ውስጡንም ከፍቶ ማዬትም አይቻልም። ለግሞ  – ሎግሞየሚይዘው የራሱን ኩረት ተፈጥሮውን ብቻ ነው። ከራሱ ኩረት ተፈጥሮ ውጪ የሚያስጠጋውም አንዳችም ነገር የለም። ውስጡ በልዞ – አሮ ጠንዝሎ – ቢከስልም ያችኑ እሮውን ተሸከሞ እንደ ኳረት ዘመኑን ይሸኛል።
ጭንጫውን አስተካክላችሁ ወደ አንድ ሰው ዓይን ብትወረውሩት ግን …. አደጋ ያመጣል። አደራ እንዳትሞክሩት። ጭንጫ ለመጉዳት ብቻ የተፈጠረ.፣ ቃና የለሽ፤ ወዝ የለሽ፤ ለዛ ቢስ፤ ምንም የማይገባው፤ ለምንምና ለማንም የማይሆን ብቻ ከብለል እያለ እያሾፈ ዘመኑን በተፋቀ ተፈጥሮው እንደ ከብት የበላውን መልሶ እያወጣ ሲያመንዥክ የሚኖር …. መንቻካ  – ጥጥር ያለ የጓጓለ ተፈጥሮ አለው። በጭንጫ ውስጥ አዲስ ተስፋን ማብቀል ሆነ ማጽደቅ የተከለከለ መንገድ ነው። ፍርፋሪ ወይንም ኦፋ ሊወረውር ይችል ይሆናል። ይህም ቢሆን ከሥጋ በይ እንሰሳ ጥርስ ውስጥ ሥጋን የማስለቀቅ ያህል ጣር ነው —– ጣጣውም ምጥ፤
የአቶ ወያኔ ዬምርጫም ማንፌስቶም ጭንጫማ ነው። አይገመስ፤ አይጋጥ፤ አይጣጣም፤ ብጥቅ የምትል ነገር አተወጣውም። አስልቶ ለማጥቃት ብቻ የተሠራ ወይንም የተድቦለቦለ ቅርጽ – ቀለም – ፎርም – ያልፈጠረለት፤ ስድና መደዴ ነገር ነው። በዚህ እንድርቺ – እንድርቺ ጨዋታው ግን ስልቦ ወይንም ሰንጎ* ፍላጎቱን ያስፈጽማል። ጭንጫ የሚመቸው – ለጭንጫ ብቻ ነው። ጭንጫ ግጥሙ አምሳዬው ጭንጫ ነው። ጭንጫ መልኩ ጭንጫ ነው። ጭንጫ ደምና ሥጋው ጭንጫ ነው። ጭንጫ – ቅልቅሉም ሆነ ግጥግጡ ከጭንጫ ከመሰሉ ጋር ነው – ጋብቻውም። ከአምሳያው ውጪ የሚመጣ ቀናዊ ሂደት እንደ ጸጉረ ልውጥ ያዬዋል። እንደ ጠፍርም እስኪበቃው በቂም በቀል ያሸዋል። ይደቃዋል። ይሰልቀዋል። ይፈጨዋል … እንጂ ብጣቂ ርህራሄ አያጎራርሰውም። ጭንጫ ይሉኝታ የለውም – ፈጽሞ።
ጭንጫ ህግ የለውም። ህግ አልባ ነው። ጭንጫ መርህ የለውም – ዳሪ አዳሪ ነው። ጭንጫ የመንፈስ ጥግ አልፈጠረለትም – ሜዳ በቀል ነው። ህግ አልባነቱ በጥሰት መሄዱ ብቻ ሳይሆን፤ ተፈጥሮው በሆነው ብቀላ ተቀናቃኙን እዬዳጠና እዬዳመጠ ነው የሚጓዘው። ይህ የጭንጫ ውስጥ ደግሞ በበቀልና በቁርሾ ኩረት የተሞላ ነው። ህልሙ ማጥቃትን አስልቶ፤ ማቁሰልን አልሞ በመሆኑ ከእሱ በተቃራኒ ያሉ ማናቸውም ሰዋዊ በጉ ሕይወታዊ ዝንባሌዎች ሆኑ አስተሳሰቦች ሁሉ ካለይግባኝ የጥቃቱ ሰለባ ይሆናሉ። አይምሬ ነውና።
በጎጠኝነት ዶክተሪን ሰብዕዊነት የሚባል ነገር የለም – ፈጽሞ። ደረጃው አይፈቅድለትምና። ጎሰኝነት ወይንም ዞገኝነት እኮ ታች ያለ የአስተሳሰብ የታቆረ ድህነት ነው። በአንዲት ምድጃ ዙሪያ ብቻ የተከለለ፣ በተወሰነ ጉዳይ የታጠረ ወይንም የተከተረ ስለሆነ ስለ ሰፊው ዓለምና ስለ ሥልጡኑ ዓለም ዕይታው ሆነ ነገረ ሥራው ጭንጫማ ነው። ዕድገትም አያውቀውም። ዕድገቱ የምድር እንቧይ* ነው። በዚህ የግንዛቤ ደረጃ ላይ የሚገኝ ቡድን ሌላውን የሚሰማበት ወይንም የሚያዳምጥበት ወይንም የሚያስተውልበት ጸጋውን ላልተመጣጠነ ዕድገት ላለው ለኋለቀር አስተሳሰቡ ገብሮታልና።
ይህ ባህሬው ደግሞ ነጭናጫና ቁጡነትን፤ ተጣራጣሪነትን፣ አድብቶና አነጣጥሮ ማጥቃትን፤ ጥላቻና ክፋትን አብቅሎ …. ዘመንን ጠቀራ ያለብሳል። አልብሷልም። ስለሆነም ጠቀራማውን ዘመን ለመቀዬር የመብት ግዴታው ከጭንጫ ጋር አለመዶለትን፤ ማዕደኛ አለመሆንን በእጅጉ ይጠይቃል። መስሪያው* የተለዬ ነውና። እንዴትና እንዴት … ተብሎ?የማይገናኝ መንገድ የወል አድራሻ የለውም። የማይገናኝ ተስፋም የወል እርገት የለውም። አምሳያ ከአምሳያው ጋር ቢወዳደር ቢፎካከር – ወሸኔ ነው። ማለፊያ! …. ከጭንጫ ጋር ግን ….. ምርቱ ሆምጣጤ ብቻ ነው። ከቶ የጭንጫ ማኒፌስቶ በዬትኛው ተፈጥሮው ነው መርህን አክብሮ በመርህ የሚዳኘው?!
ክብረቶቼ – እርገት ይሁን፤ ከሚጠበቅ ራዕይ ተስፋን መጠበቅ – መልክ አለው። ከማይጠበቅ ምክነት ግን ማለም ተስፋን ማራቆት ወይንም የብዙኃንን ምኞት እርቃኑን እንዲቀር መመቸት ወይንም ዬዕንባን ፍላት ፈቅዶ እራስ ማፈን ይመስለኛል።
የትናንት 04.12.2014 ጸጋዬ ራዲዮ Tsegaye Radio ዝግጅት ሲጀመር ችግር ነበረው – የቴክኒክ። በኋላም 33 ደቂቃ ብቻ ነበር አዬር ላይ የቆዬው። ስለሆነም ታላቅ ይቅርታ በትሁት መንፈስ እጠይቃለሁ፤ ችግሩ እኔ የፈጠርኩት ባይሆንም። የቴክኒክ ችግር ስለ ገጠመ ነበር። በኋላ ግን ከ16 – 17 ቀጣዩን የራዲዮ ዝግጅት ሰርዘው ራዲዮ ጸጋዬ እንደ አዲስ ተጀመረ። ለፈጣኑ እርማትና ለአክብሮቱ ራዲዮ ሎራ እያመሰግነኩኝ ዓይናማዋን፣ ደመ ግቡውን የጋዜጠኛ ተመስገን ወንድም ዬአቶ ታሪኩን እናታችን ፋናዬና ተመስገን በዝዋይ’” መንፈስ ጋር ጸጋዬ ራዲዮ ቆይታውን አድርጓል። ከፈቀዳችሁ አርኬቡ ላይ ማድመጥ ትችላለችሁ።  ኑሩልኝ!
መሸቢያ ሰንበት – ለእኔዎቹ።
መፍቻ።
  • ሰንጎ … በኃይል – በጎልበት – በጡንቻ – በብረት ድጋፍ – አስገድዶ፣ ደም አስፍቶ፣ አንቆ ይዞ ፍላጎትን ማስፈጸም – ለወመኔዎች በትክክል የተፈጠረ ቃል ነው።
  • መስሪያ … በጋራ – በሌማት፤ በሞሰብ – በወልዮሽ፤ በጥራር – በአንድነት፤ ወይንም በትሪ – በአኃታዊነት የጋራ ማዕዶት …
  • ጥራር … ከሰንበሌጥ በእጅ የሚሰራ መመገቢያ ባህላዊ ዕቃ … ተወዳጅም።
  • የምድር እንቧይ … እንቧይ ሁለት ዓይነት ተክል አለው። አንዱ በትክክል በቅሎ እንደ አጋም እንደ ቃጋ የሚያድግ እድገቱ የሚታይ ፍሬውም እንደ እንኮይና ኮሽም ዓይነት ሲሆን። ሌላው የምድር ዕንቧዩ ግን እንደ ሥሙ ዕድገቱ መሬት ላይ ነው የሚቀረው። ሀረጉም ብዙ አይጓዝም – ድካም ያሸነፈው ተፈጥሮ ነው ያለው። ፍሬው ቀለሙ ያልበሰለ ወይራ መሰል ቆባ ዱባ ወይንም ዝኩኒ ነገር ነው። ከመሬት በቅሎ ጫጭቶ እዛው ተሰክቶ – አሮም ይቀራል።
ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር ኢትዮጵያዊነት!
ለእኔስ ሰው መሆኔ ብቻ ይበቃኛል!
እግዚአብሄር ይስጥልኝ – ኑሩልኝ!

No comments:

Post a Comment