አገር በቀል የሆነው፤ የቅኝ አገዛዝና ዘረኛው የወያኔ ሰርአት በባህር ዳር የሚኖሩ ወገኖቻችንን ላይ በትናንትናው እለት ያደረገውን የጅምላ ግድያና ድብደባ አሁንም በታላቅ ቁጭትና ሀዘን ለማየት ተገደናል። በተለይ አካለ ስንኩላንና በእድሜ የገፉ አዛውንት በድብደባ ቆስለው ማየት ምን ያህል ልብ የሚያደማና የስርአቱን ኢሰብአዊነትና ጨካኝነት አሁንም ደግሞ ደጋግሞ የሚያረጋግጥ ከመሆኑም በላይ ይህንን ዘግናኝ ወንጀል የፈጸሙት የስርአቱ አራማጆች አንድ ቀን ለፍርድ በሚቀርቡበት አደባባይ በመረጃነት የሚያዝ ይሆናል። ምንም እንኳን የመሳሪያና የዱላ እሩምታውን ቢያወርድበት፤ ቆራጡ የባህር ዳር ህዝብ ይህንን ተቋቁሞ ምሬቱን መግለጽ ብቻ ሳይሆን ከትግል አጋሩ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር፤ ይህንን የበሰበሰ ስርአት ከተከሻው አሽቀንጥሮ የሚጥልበት ጊዜ ሩቅ አይደለም። የወያኔ ሰርአት ላለፉት 23 አመታት በተለያዩ ክልሎች ተመሳሳይና ከዚህም የከፉ የጅምላ ጭፍጨፋና የዘር ማጥፋት ድርጊቶች በኢትዮጵያውያን ላይ ሲፈጽም ቆይቷል። የአንዱ ኢትዮጵያዊ ጥቃት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጥቃት መሆኑን አምነን በአንድነት በመቆም ስርአቱን ለማስወገድ ካልታገልን፤ ወያኔ ስልጣኑን ለማራዘም ወደፊት ከዚህ የከፉ ድርጊቶች እንደሚፈጽም ያሳለፍነው የ23 አመት የመከራ ታሪክ ማሳያ ሊሆነን ይገባል።
ይህን አገር በቀል የቅኝ አገዛዝ፤ ዘረኛና ጨካኝ ሰርአት ለማስወገድ የኢትዮጵያን ሕዝብ መሰረት ያደረገ ሁሉንም አካላት የሚወክልና ትግሉን በአንድ ማእከል የሚመራ ጠንካራ የአንድነት ሃይል መክሮና ተስማምቶ ማቋቋም አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑን ድርጅታችን በጽኑ ያምናል። በዚህም መሰረት የሽግግር ምክር ቤቱ ይህንን የትግል አስተባባሪና መሪ አካል በጋራ ለማቋቋም ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶችን በማድረግ ላይ ይገኛል። በዚህ አጋጣሚ ሀገር ወዳድና ነጻነት ናፋቂ ወገን ሁሉ ተመሳሳይ ጥረትና ግፊት እንዲያደርግ ሀገራዊ ጥሪ እናቀርባለን።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሽግግር ምክር ቤት
No comments:
Post a Comment