ኖርዌይ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ጥገኝነት ጠያቂዎችን በግዳጅ ወደ ሀገራቸው ለመመሰስ ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ያደረገችውን ስምምነት የሚቃወም ታላቅ ሰልፍ ተካሄደ::
ኢትዮጵያውያን በስደት ከሚኖሩባቸው የተለያዩ የአውሮፓና ስካንዴኔቪያን ሀገሮች አንዷ የሆነችው ኖርዌይ ስትሆን በኖርዌይ ሃገር ቁጥራቸው አነስተኛ የማይባል ኢትዮጵያውያን የፓለቲካ ስደተኞች ይገኛሉ። እነዚህ ስደተኞች ከሌላው ሀገር ለየት የሚያደርግ ጠንካራ የፓለቲካ አቋም ያላቸው መሆኑም ይታወቃል። ስደተኞቹ በተለያየ ጊዜያት የገዢውን ፓርቲ ብልሹ አስተዳደር የሚያጋልጡ የፓለቲካ ስራዎችን ሲሰሩ መቆየታቸው ይታወሳል።
ሆኖም ግን የኖርዌይ መንግስት እ.ኤ.አ በ2012 ከቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ መለስ ዜናዊ ጋር በኖርዌይ የሚኖሩ ጥገኝነት ጠያቂዎችን አስገድዶ ወደ ሃገር ለመመለስ የሚያስችል ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል። ሆኖም ግን ይህ ስምምነት በተለያዩ ምክንያቶች ተግባር ላይ ሳይውል ቀርቷል። ኖርዌይ በድጋሚ አሁን በያዝነው አመት በፌብርዋሪ ወር እንደገና ስደተኞችን አስገድዶ ወደ ሀገር የመመለሱ ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ከውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ቴዎድሮስ አደሃኖም ጋር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን በኖርዌይ የሚገኙ ታላላቅ የዜና አውታሮች ሲዘግቡ ሰንብተዋል።
ይህንኑ ስምምነት አስመልክቶ በኖርዌይ የሚገኘው የኢትዮጵያውያን ስደተኞች ማህበር ስምምነቱ ትክክል እንዳልሆነ ተቃውሞውን ለመግለፅ በሜይ 10፣ 2016 ታላቅ ሰልፍ አዘጋጅቷል። ይህ የተቃውሞ ሰልፍ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከተለያዩ የኖርዌይ ከተሞች በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተካሂዷል። ስደተኞቹ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተከናወኑ ያሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በተለይ በቅርቡ በሀገራችን በአደባባይ እየተገደሉ ያሉ ወገኖቻችንን የያዙ ምስሎችንና የኖርዌይ ዜግነት ያላቸውና ከደቡብ ሱዳን ታፍነው በኢትዮጵያ እስር ቤት እየማቀቁ ያሉንትና አሁን ለዘጠኝ አመት የተፈረደባቸው የአቶ ኦኬሎ አኳይ ፎቶግራፍ እንዲሁም የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ፎቶግራፎች በመያዝ ስለነሱም አያይዞ ለኖርዌይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካይ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ እየታወቀ ሰዎች በየሰከንዱ እየተገደሉ ባለበት ወቅት ሀገሪቱ በብዙ አቅጣጫ የህዝብ አመፅ ባለበትና ገዢው ፓርቲም ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ ሰዎችን እየገደለና እያሰረ ባለበት ሁኔታ ስደተኞችን አስገድዶ ለመመሰል ስምምነት ማድረጉ ለምን እንዳስፈለገ፤ እንዲሁም የኖርዌይ መንግስት ለኖርዌጅያን ዜጎች በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች መዘዋወር አደገኛ መሆኑን መግለጫ እየሰጠ ባለበት ሁኔታ የፓለቲካ ስደተኞችን አሳልፎ መስጠት ሰብአዊነት የጎደለውና የስደተኛ መብት ህግን የሚጥስ መሆኑን ኢትዮጵያውያኑ በሰልፉ ላይ ተናግረዋል።
በሰላማዊ ሰልፉ ላይ የስደተኞቹን ጉዳይ የሚከታተሉ የግብረ ሃይሉ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ አያሌው ይመር ንግግር ያደረጉ ሲሆን ዝግጅቱም በተያዘለት ሰአት በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር
የኢትዮጵያ ስደተኞች ማህበር በኖርዌይ
No comments:
Post a Comment