Sunday, May 29, 2016

ጎንደር ህብረት አስቸኳይ መግለጫ – “የወልቃይት ጠገዴ፣ ቃፍቲያ፣ ሁመራና ጠለምት ህዝብ ፈጥኖ ደራሽ አጋር ይሻል




Gondor Hibret
ወያኔ ገና ካፈጣጠሩ ጀምሮ፤ አገር ሸንሽኖ፤ ህዝብን ከፋፍሎ፤ ለዘለዓለም የሥልጣን ዘመኑን ለማራዘም አለሞ እና ሸርቦ የተነሳውን ህልሙን ለማሳካት፤ የመጀመርያ የጥቃት ኢላማው ያደረጋት የጎንደር ክ/ሀገርን ነው። የዚም የመጀመርያው የግፍ ሰቆቃን እየተጋቱ ያሉት፤ ደግሞ ሰሜን ምዕራብ ክ/ሀገራችን ኗሪ የሆኑት የወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ፀለምት ወገኖቻችን ናቸው።
ይሁን እንጂ፤ ከሰላሳ ዓመት በላይ የአካባቢዋን እና የዘር መሰረታቸውን ታሪክ ነጋሪ እንኳ እንዳይኖር፤ አንድ በዓንድ ለቅሜ አጥፍቻለሁ፤ ብሎ ያስብ የነበረውን ከንቱ የወያኔ ቅዠት አዲሱ ትውልድ፤ ለማንነቱ፤ ፍርሃትን ሰብሮ ወደ ትግል ከወጣ ውሎ ቢያድርም፤ አሁን ግን የነዚህ ወገኖቻችን የትግል ምዕራፍ የመጨረሻው የሞት ሽረት ደረጃ ላይ ደርሷል።

(ሁመራ ከተማ)

የዚህም አንዱ እና ዋንው ሀቅ፤ ወያኔ በጎንደር ህዝብ ላይ በጉልበት የጫነዉ የመስፋፋት እና የመሬት ቅርምት አባዜን ለመገደብ፤ በሁሉም የጎንደር ሕዝብ ቆራጥነት ድጋፍ ማግኘቱ ነው። ከእንግዲህ በኋላ፤ የቃፍቲያ ሁመራ፤ ወልቃይት ጠገዴ እና ጠለምት ህዝብ የወያኔን የዘር አጥፊ በደል መሸከም ከሚችለዉ በላይ በመሆኑ፤ ትግስቱን ጨርሶ በአንድ ድምጽ ተማምሎ “የትግራይ ነፃ አዉጭ ግንባር ተከዜን ተሻግሮ አያስተዳድረንም” ከሚል ዉሳኔ ላይ ደርሶ፤ የራሱን መሪና የጎበዝ አለቃ መርጧል። በጎንደሬነቱ፤ በአማራነቱ፤ በባህሉ፤ ለዘመናት በኖረበት መሬቱና በጠቅላላ ማንነቱ ላይ ግፍና መከራ ስለተፈጸመበት፤ በአንድ ድምጽ በቃለ መሃላ ነጻነቱን አዉጇል። ተወደደም፤ ተጠላም፤ ይህ የቃፍቲያ ሁመራ ወልቃይት፤ ጠገዴ፤ እና የጠለምት ህዝብ “ጎንደሬም አማራም ነን” በሚል መፈክር ለነፃነቱ ያቀጣጠለውን ትግል፤ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በቅንነት መቀበል ሰባአዊነት ነው። በተለይ ደግሞ፤ ለዘመናት የጎንደር እና የትግራይ ሕዝብ፤ በጉርብትና ሲኖሩ፤ ተዋደው እና ተፈቃቅረው ያጋኙትን ተካፍለው ከመኖር ባሻገር፤ አንድም ቀን እንኳ፤ የመሬት ይገባኛል ግጭት አድርገው እንደማያውቁ እየታወቀ፤ በአሁኑ ሰዓት፤ የትግራይ ወገኖቻችን፤ ዘመን ካሳበጣቸው፤ ጥቂት ከውሥጣቸው በወጡ ቡድኖች ምክንያት፤ የተጠነሰሰውን፤ ታሪክን መሰረት ያላደረገ፤ የመሬት ሥግብግብነት፤ ተንኮል፤ በዝምታ፤ መመልከት፤ እጅግ አሳዛኝ የሆነ፤ የታሪክ ስህተት መሆኑን ለማስገንዘብ እንወዳለን።
ስለሆነም፤ የትግራን እና የጎንደርን ሕዝብ የወደፊት አብሮነት ታሪክ ለማስቀጠል ሲባል፤ ማንኛውም የትግራይ ተወላጅ፤ ወገኖቻችን ይዘው የተነሱበትን የማንነት ጥያቄ፤ የታሪክ እውነት መሆኑን፤ ማክበር እና መቀበል እንዳለበት ከወዲሁ ልናሳስብ እንወዳለን። አፈጣጠሩ እና ባህሪው አይፈቅድለትም እንጂ፤ ልብ ሰጥቶት የገዥዉ መደብም ቢሆን፤ ይህን የሕዝብ ውሳኔ ማከበር የጎንደርን ህዝብ ማክበር ነዉ የሚል እምነት አለን። ለዓመታት የጠዬቀዉ የጎንደሬነት ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ ጭቆናዉ በዝቶበት እራሱ በመረጣቸዉ መሪወች ለመተዳደር መወሰኑ ፍህታዊ እና ህዝባዊ እርምጃ ነዉ። መከበር ይገባዋል!!
ከእንግዲህ ይህንን ህሊናዉ የቆሰለ እንግዳ ተቀባይ ደግ ህዝባቸን ላይ፤ ተከዜን ተሻግሮ ከአድዋ በመጣ ፀረ ሽምቅ ሰራዊት ተኩሶ በመግደል፤ የበለጠ ሕዝባችንን ወደከፋ መተላለቅ የሚገፋ መሆኑን ተገንዝቦ፤ ጣቱን ከመሳሪያ ምላጭ አንስቶ፤ የወገኖቻችን ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ምላሽ እንዲሰጥ እናሳስባለን።
ይህ ግፍ እና በደል የወለደውን፤ የጎንደሬ/የአማራ ማንነት ጥያቄ፤ ቆመንለታል ብላችሁ፤ ለ25 ዓመት በወያኔ፤ እየተሽከረከራችሁ ያላችሁ፤ የብ.አ.ዴን አባላት እና ካድሬዎች፤ የማንነታችሁ መፈተኛ ወቅት ላይ በመሆናችሁ እና፤ የመጨረሻ እጣ ፈንታችሁ ወቅት ላይ በመድረሳችሁ፤ ከእንቅልፋችሁ የምትነቁበት ደወል፤ እየተደወለ ነው። በዚያው እንዳታሸልቡ፤ ከወገኖቻችሁ ጋር ለማንነታችሁ አብራችሁ በመቆም እስካሁን የበደላችሁትን ወገናችሁን ልትክሱ የግድ ነው። እንዲሁም፤ የሰባቱ አዉራጃ የጎንደር ህዝብ፤ ጥያቄው፤ የራሱ ማንነት ጭምር መሆኑን በማመን፤ በአስቸኳይ፤ በሚፈለገው ሁሉ ትብብሩን ማሳየት፤ የግድ እሚልበት ደረጃ ላይ በመሆኑ፤ እስቸኳይ ታሪካዊ ምላሽ፤ ለወልቃይት ጠገዴ፤ ጠለምት ወገኖቻችን እንዲያሳይ የጎንደር ሕብረት ታሪካዊ እና ወቅታዊ ጥሪያችንን ለማስተላለፍ እንወዳልንለን። የጎንደር ሕብረት የተመሰረተበት ቋሚ ዓላማም፤ ሁላችንም በሰላም እና በፍቅር ታሪካዊ፤ መልካዓ ምድራችንን ጠብቀን በጋራ እንድንኖር የሚያስችለንን ታሪክ ለማስጠበቅ ነው። በመሆኑም፤ ስማችን ጎንደር ነክ ይሁን እንጅ፤ ለትግራይም ሆነ፤ ለመላ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን እኩል ፍቅር፤ እኩል፤ ተቆርቋሪነት እና ኃላፊነት ይሰማናል።
ሌላዉ ሳንጠቅስ የማናልፈዉ እጅግ አሳዛኝ ሁኔታ ደግሞ ባለፈው ወር የጋምቤላ ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመዉ የጀምላ ጭፍጨፋ ነዉ። የኢትዮጵያን መሬት አሳልፎ ለመስጠት በተሸረበ ሴራ ምክንያት ወያኔ፤ ጠረፍ ጠባቂ፤ ፀጥታ አስከባሪ፤ የነበሩትን የታጠቁትን የአካባቢ ሚሊሻዎች፤ ትጥቃቸውን አስፈትቶ፤ ካምፕ ውስጥ እንደከብት በመዝጋቱ ምክንያት፤ አካባቢዉን ክፍት መሆኑን የተረዱ፤ ከ እንሰሳት ዝርፊያ አልፈው የሰው ህይወት ለማጥፋት ተዳፍረው የማያውቁ የደቡብ ሱዳን ኗሪ የሙርሊ ብሔረሰቦች በወሰዱት አሰቃቂ ርምጃ ከ200 በላይ ኢትዮጵያዊያን ተጨፍጭፈዉ፤ 150 ታፍነዉ ሲወሰዱ፤ እጅግ ብዛት ያላቸውን ቤት እና ንብረት አቃጥለው፤ በሺ የሚቆጠሩ የቀንድ እና የጋማ ከብቶችም ተዘርፈው ተወሥደዋል።
እንዲሁም በተመሳሳይ መልኩ በመተከል ቁጥራቸዉ ወደ 70 የሚደርሱ አርሶ አደሮች በሱዳን መንግስት ተጠልፈዉ መዳረሻቸዉ ጠፍቶ፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቀንድ ከብቶችም ተዘርፈው ሲወሰዱ፤ እርምጃ የሚወስድ ቀርቶ፤ የሚጠይቅ መንግስት እንኳ አልተገኘም።
ይህ የሚያሳየው፤ አገራችንም ሆነ ሕዝባችን፤ መንግሥት ተብዬ አገር በቀል ጠላት ቅንብር፤ በውጭ ታሪካዊ ጠላቶቻችን የጥቃት አደጋ እንደተደቅነብን ነው። በመሆኑም፤ ኢትዮጵያ አገራችንም ሆነ የህዝባችን ደህንነት የሚጠብቅ መንግስት እንደሌለ አዉቀን በሞቱት ወገኖቻችን መሪሪ የሆነ ሃዘናችንን በሃገራዊ ቁጭት እየገለጽን፤ ለዘመድ አዝማድ ሁሉ መጽናናትን ይስጥልን እንላለን። የደቡብ ሱዳንም ሆነ የሰሜን ሱዳን መንግስት በወያኔ ቅጥረኞች ታፍነዉ የተወሰዱ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን ከነንብረታቸዉ ወዳገራቸዉ በአስቸኳይ እንዲመለሱ፤ ወንጀለኞችም ለፍርድ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን። የመላዉ ኢትዮጵያ ህዝብም፤ በዬአካባቢው የራሱን መሪ መርጦ፤ ደህንነቱን ጠብቆ፤ ዳር ደንበሩን እንዲያስከብር ጥብቅ መልክታችን እናስተላልፋለን። ከዉጭ አገር ጋር ተባባሪ የሆነዉ የወያኔን መንግስት እንደ አገር መሪ ቆጥሮ ህዝባችን እንዳይዘናጋ አደራ እንላለን።
በመጨረሻም በጎንደር ክፍለ ሀገር በቋራ ወረዳ የጓንግን ወንዝን ተሻግሮ ከኢትዮጵያ መሬት የሰፈረዉ የሱዳን ወታደር በአስቸኳይ እንዲለቅ እንጠይቃልን።
ጀግናዉ የጎንደር ህዝብ ዳር ድንበሩን ያስከብራል!!!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!!
ጎንደር ህብረት

No comments:

Post a Comment