Sunday, May 22, 2016

ፈላስፋው መምህር (መላከ መንክራት) ግርማ ወንድሙ ቀጣይ ጉዞ

በባሌ ክፍለ ሀገር ጎባ እንደተወለዱና የልጅነት ጊዜያቸውንም በዛው እንዳሳለፉ የሚናገሩት መምህር (መላከ መንክራት) ግርማ ወንድሙ ለበርካታ አመታት ክፉ መናፍስትን ከሰዎች ልጆች በማስወጣት የሚታወቁ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነት የሐይማኖት አባት ነቸው፡፡ መምህሩ በዚህ አገልግሎታቸው በብዙ ሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ከክፉ መናፍስት እስራት እዳላቀቁ ይነገርላቸዋል፡፡ የዚሁ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑትም በርካታ ሰዎች ስለዚሁ ይመሰክራሉ፡፡ የክፉ መናፍስትን ከማስወጣቱ በተጨማሪ መምህሩ በኢትዮጵያ ለዘመናት የተዘነጉና ሕዝብን ለመናፍስት ወረራ የዳረጉ የሚሏቸውን የተለያዩ መረጃዎችን  ፈውስ በሚሰጡባቸው በጉባዔያትና አሜሪካን አገር በሚገኝ ራዲዮ አቢሲኒያ በሚባል ሬድዮ ለሕዝብ ያስተምራሉ፡፡ በዚህም አገልግሎታቸው ብዙዎች ልዩ ዕውቀት እንዳገኙና ራሳቸውንም እንደቀየሩ ይናገራሉ፡፡


girma wendimu

እኔ እንደ አስተዋልኩት እኚህ ሰው ከብዙ የዘመኑ የቤተክርስቲያኗ አገልጋዮች የሚለይዋቸው ፍልስፍናዎች አሉ፣ ተግባሮች አሉ፡፡ ምንዓልባትም በመናፍስት ላይ ያላቸው ኃይል ከዚህ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል አስባለሁ፡፡ በመድረክም ከላይ በጠቀስኩትም ሬዲዮ መምህሩ ሲያስተምሩ ከተለመደው የሀይማኖት ስብከት ከሚባለው ለየት ያለ ነው፡፡ ትምህርታቸው የመጽሐፍ ጥቅስ በማብዛት ሳይሆን ከመጽሐፉ ክፍል አንድ ወይም ጥቂት ዓረፍተ ነገር በመውሰድ እሱን ከነባራዊው የሰዎች አኗኗር ጋር በመተንትን ነው፡፡ በእርግጥም ብዙ ጊዜ አንብበንው ያለፍነው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እሳቸው ሲተነትኑት ራሳችንን እስከምንታዘብ ድረስ እንዳልገባን ይሰማናል፡፡ መምህሩ ሲያስተምሩ በመጻሐፍ ያለውን ዛሬም እየሆነ እደሆነ በመስረገጥ ነው በማለት እንጂ እንደሌሎች ይላል በሚል አይደለም፡፡ የሚናገሩትም እንደ ፈላስፋ እንጂ እንደ ሰባኪም አይደለም፡፡ በበርካታ ትምህርቶቻቸውም አብዝተው ስለ ሕዝብና አገር በቁጭት ይናገራሉ፡፡
መምህሩ ባሳለፏቸው የአገልግሎት ዘመናት አግልግሎት የሚሰጡት በነጻ ነው፡፡ በነጻ ያገኛችሁትን በነጻ ስጡ የሚለው ቃል በተግባር የገባቸው ይመስላል፡፡ ለበርካታ ዓመታትም አገልግሎታቸውን ለመፈጸም ሲሉ በኑሮ ብዙ ተፈትነዋል፡፡ ብዙ ሕዝብ እያገለገሉም ይሄው የኑሮ ችግራቸው የከፋ ነበር፡፡ በተገኙበት ጉበኤ ሁሉ በብዙ ሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ ለሚያገለገሉበት ደብር እየስገቡ እሳቸው  በማጠት የተቸገሩባቸውን ብዙ አመታት መምህሩ ይዘክራሉ፡፡  ከብዙ ዘመን በኋላ ነበር ታዲያ  ከሚሰጡት አገልግሎት አንጻር ኑሯቸውን ያስተዋሉ አንዳንድ ግለሰቦች በኑሮ እንዳይፈተኑ ያገዟቸው፡፡ ቤት የገዙላቸው ባልና ሚስት በመምህሩ እንደ ልዩ የእግዚአብሔር መልክተኞች ይታያሉ፡፡ ለዘመናት በቤት ጉዳይ ተፈትነዋልና፡፡ የሚሰጡትንም የአጋንንት ማስወጣቱን ተግባር ከሌላ አንጻር እየተመለከቱባቸው ቤት አከራዮቻቸውም ብዙ ፈትነዋቸዋል፡፡ ወደ መጨረሻ እንደውም ቤት የሚያከራያቸው ራሱ እንዳጡ መምህሩ ይናገራሉ፡፡ እንግዲህ እሳቸው ጋር ያለ ኃይል እንዲህ ባለ ፈተና ካልሆነ አፀና ይሆን; በዚህ ሁሉ ግን መምህሩ እጅ ሳይሰጡ፣ ገነዘብም፣ ዝናም፣ ሰውም ሳይጥላቸው አሁን ያሉበት ደረሱ፡፡  አሁን ፈተናው ቢኖርም እንደ ድሮው አይደለም፡፡ ብዙ ሕዝብም የፈተናቸውም ተጋሪ ሆኗል፡፡
ብዙ ሕዝብ በትክክል እየተረዳቸው ሲመጣ ፈተናው በዛው ልክ መዋቅራዊ ሆኖ ዛሬ ቤት፣ ልብስ፣ ምግብ ሳይሆን የሚያገለገልሏት ቤተክርስቲያን ኃላፊዎች ዋና ፈተና ሆነውባቸዋል፡፡ ብዙ ያሴሩባቸዋል፡፡ ሆኖም አሁን እየገጠማቸው ያለው ፈተና በሕዝብ ዘንድ ብዙ የታወቁበት ዘመን በመሆኑ ፈታኞቹ መምህሩን በሚከሱበት ሁሉ ትዝብት ውስጥ እየገቡ ይመስላል፡፡ ብዙዎችም እውን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ለዘመናት ዋና ሆነው ያሉት እነማን ናቸው የሚል ጥያቄን እያነሱ ነው፡፡ በቅርቡ መምህሩ በተለያየ የሐሰት ክሶች ለእስር ተዳርገው እንደነበር ይታወቃል፡፡ ክሶቹ መጀመሪያ የግለሰብ እንዲመስሉ ቢደረግም እየቆየ ከቤተክርስቲያኒቱ ዋና ከተበሉት እንደሆነ ተረዳን፡፡ የፖለቲካ አንድምታም እንዳለውም በማሰብ፡፡ ዛሬ በቤተክርስቲያኒቱ የተለያየ ቦታ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ ዋናው ችግር ከገንዘብ ጋር የተያየዘ ነው፡፡ ከሳቸው ጋር ያለው ችግር ግን ትንሽ ረቀቅ ያለ ይመስላል፡፡ በሥጋ በማይገለጥ የመንፈሳዊ ጦርነት ይመስላል፡፡ ለብዙዎች የመምህሩ አጋንንትን ከሰው ልጆች ማውጣት ሠላም እየሰጣቸው ያለ አይመስልም፡፡ የቤተክርስቲያኗን መንፈሳዊ አገልግሎት ዕውቀት ያላቸውና በመንፈሳዊ ሕወታቸውም ጠንካራ የሚባሉት የሲኖዶስ አባላት ጳጳሳት ሳይቀር መምህሩ ትክክለኛ እንደሆኑ በብዙ መድረኮች ሲናገሩ እንሰማለን፡፡ ሌሎች ግን ሥራቸውን ከጥንቆላ ጋር አገናኝተው ሊያወግዙ ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ግን በሕዝብ ዘንድ ሌላ ጥያቄን ፈጥሮ ይገኛል፡፡ በቤተክርስቲያኗ ተንሰራፍቶ ያለው የጥንቆላ ሥራ የበለጠ ስለሚታመንበት በእግዚአብሔር ኃይል ለሚደረግ አገልግሎት ዋጋ መስጠትን እንደተረሳ ብዙዎች ተረድተዋል፡፡ መምህሩን ዛሬ ፈታኝ የሆኑባቸውም ራሳቸው በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ዋና ሆነው በጥንቆላ ሥራ የሚታወቁ ናቸው የሚል ትዝብትን አምጥቷል፡፡ በእርግጥም ይህ አስተሳሰብ በሕዝብ ዘንድ ቢኖር አይገርምም፡፡
መምህሩ ተግባራቸው በግልጽ በኃያሉ በእግዚአብሔርና በቅዱሳኑ ሥም አጋንንትን ሲያሶጡ የሚያሳይ ነው፡፡ ለገንዘብ ቦታ የላቸውም፡፡ ዘር ጎሳ ሐይማኖት ጭምር ሳይለዩ በተሰጣቸው ጸጋ ሁሉንም ያገለግላሉ፡፡  በዚህም በትምህርታቸውም ሆነ በፈውስ አገልግሎታቸው ተጠቃሚ እየሆነ ያለው የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ብቻም ሳይሆን ሁሉም ነው፡፡  ለአገርና ሕዝብ ያላቸው ቁጭት እጅግ ታላቅ ነው፡፡  በዘር የተከፋፈለች በመሆኗ ያዝነሉ፡፡ በአደባባይም ይሄንኑ በቁጭት ይናገራሉ፡፡  በአንድ ወቅት በጊምቢ ምዕራብ ወለጋ በአንድ ደብር የተናገሩት በብዞዎች ይታወሳል ከጎጃም የመጣ በሬና ከወለጋ የመጣ በሬ አብረው አንድ ላይ ሳር ይግጣሉ እኛ ግን ዘር እየቆጠርን እንናከሳለን ብለው ነበር፡፡ በብዙ መድረክም እንዲህ ያለውን ነገር ይናገራሉ፡፡ የኤርትራውያን ከኢትዮጵያ ተገንጥሎ ድሮ በአውቶብስ እንደልብ የሚገናኙ ሕዝቦች ዛሬ ያለፍላጎታቸው ታግደው በሌላ አገራት ሲገናኙ በማየታቸው እጅግ ያዝናሉ፡፡ ብዙም ጊዜ ይናገሩታል፡፡ እንዲህ ያለው በዘር መከፋፈል አስከፊነቱን ለአገልግሎት በተንቀሳቀሱባቸው የውጭ አገራት ትልቅ ትኩረት ሰጥተው ተናግረውታል፡፡ ይሄ ግን አሁን በሥልጣን ላይ ላለው መንግስትና በዘርና በተለያየ ጥቅም ለተበከሉ የቤተክርስቲያኒቱ ባለስልጣኖች እንደ ክፉ ሳይታይባቸው አልቀረም፡፡ በቅርብ የታሰሩበት መሠረታዊ ምክነያቱም የሕዝብ እንድነትን መስበካቸው ይመስላል፡፡ ከእስር ከተፈቱም በኋላ በሲኖዶስ አባል በሆኑ ጳጳስ በምድብ አገልግሎት እንዲሰጡ ደብዳቤ ቢጻፍላቸውም ከዋናው ፓትሪያርክ በወጣ ሌላ ደብዳቤ ታግደዋል፡፡  ከዚህም በፊት ብዙ ደብዳቤ ተጽፎላቸዋል ተጽፎባቸዋልም፡፡
በአሁኑ ወቅት  መምህሩ በየትኛውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እንዳያገለግሉ ታግደው ቀድሞ ይስጡት የነበሩትን አገልግሎት አቋርጠዋል፡፡ ሆኖም ትምህርታቸው አቢሲኒያ በሚባለው ሬደዮ ቀጥሏል፡፡ እሳቸውም ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ወገኖችን ይዘው የበለጠ ወደሚሆን ልዩ አገልግሎት እየገቡ ያለ ይመስላል፡፡ ከዚህ በፊት ለየደብሩ ብዙ ገንዘብ በማስገባት የሚተወቁት እኝህ መምህር አሁን የተጎዱ ወገኖቼን በሚል ወደበጎ አድራጎት ድርጅቶች ፊታቸውን አዙረዋል፡፡ በቅርብ የአንድ የድኩማንና አንድ ሌላ ወላጅ የሌላቸው ሕጻናት የሚማሩበትን ተቋማት መረዳታቸውን እናስታውሳለን፡፡ ሰሞኑን ደግሞ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ዕርዳታ የሚሆን ከሁለት ሚሊየን ብር በላይ በ15 ቀን ውስጥ አሰባሰበው ለኢትዮጵያ ቀይመስቀል ማህበር አበርክተዋል፡፡  የመምህሩ በእንደዚህ ያለ አጭር ጊዜ ይሄን የሚያህል ገንዘብ ማሰበሰብ መቻል ለብዙዎች ሊገርም ይችላል ሆኖም መምህሩ ለየደብራቱ በተገኙበት አጭር ሰዓታት የሚያስገቡትን ላየ ብዙም አይገርምም፡፡  በአንድ ደብር ከግባሽ ሚሊየን ብር በላይ የአስገቡበትን አንድ ከ2-3ሰዓት የሆነ ጉባዔያቸውን ብዙዎች በአይናቸው አይተዋል፡፡ መምህሩ እንደተናገሩትም አገር ውስጥ ያለው ጉባዔያቸው ቀጥሎ ቢሆን አሁን ለቀይመስቀል ያበረከቱት ከአምስት ሚሊየን በላይ ይሆን ነበር፡፡
ቀጣዩ የመምህሩ ጉዞ ከዚህ በላይ ቢሆን ተመኘሁ፡፡ ከላይ እንደጠቆምኳችሁ፡፡ መምህሩ ለአገርና ሕዝብ ትልቅ ቁጭት አላቸው፡፡ የሕዝብ ኑሮ ከአገር መሰደድ ብዙ ይሰመቸዋል፡፡ በእሳቸው ዘንድ ኢትዮጵያዊነት (ለእሳቸው የኤርትራን ሕዝብ ጨምሮ ነው) ትልቅ ሥፍራ አለው፡፡ በዛው ልክ ትምህርታቸውን በሚከታተሉትም ዘንድ እንደዛው ነው ኤርትራውያኑን ጨምሮ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዘር (አሮሞ፣ አማራ ትግሬ… ምናምን)፣ ሐይማኖት (ኦርቶዶክስ፣ እስላም፣ ፕሮቴስታንት) ሳይል ሁሉም ይወዳቸዋል፡፡ ቀጥሎ የመምህሩ ጉዞ በዘር የተከፋፈለውን ሕዝብ አንድ የሚያደርግና ዜጎች በሰላም፣ በሠላም፣ በብልፅግና ፍትሕ የሰፈነባት አገር ለመገንባት ወደሚያስችል ተግባር ቢሆን ተመኘሁ፡፡ መምህሩ ከጠለቀ የሀይማኖትና የሰውልጅ ደህንነት ፍልስፍናቸው አንጻር ተቃራኒ ቡድኖችን በማቀራረብ፣ ሕዝብንም ለሠላምና አገርን በአንድነት ለመገንባት የማነሳሳት አቅሙ እንዳላቸው አሰብኩ፡፡ መምህሩ የሚከተሉት እንደተረት የምንሰማቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ያነበብናቸውን ፈላስፋዎች እንደነ ቅዱስ ጳውሎስ ያለውን ፍልስፍና ነው፡፡ በዚያ ዘመን ያለች ጥበብ አሁንም እንዳለች በቃልም በተግባርም እያሳዩን ነው፡፡  ወገኔ ሕዝቤ የሚሉትን ዛሬ ተከታዮቻቸውን በማስተባበር ለዕለት ችግሩ የሚሆን ዕርዳታ እያበረከቱ ያሉትን ተግባር በዘላቂነት ኑሮው የተሻለ እንዲሆን አሁን የሚከታተሏቸውን ሌሎችንም ወገኖች በመያዝ ወደ አንድነትና አገር ልማት ለማመጣት ተጽኖ መፍጠር ከሚችሉ ሰው አንዱ ሆነው ይታዮኛል፡፡ እሳቸውም በዚህ ሂደት ተሳታፊ ቢሆኑ ደስተኛ እንደሚሆኑ ይሰማኛል፡፡ ከሁሉ በላይ ዘለቀታዊ የሆነ ሠላም፣ ፍትሕ፣ እንድነትና ልማት ኢትዮጵያ ያስፈልጋታል፡፡ ዜጎች በብዙ መልኩ አእምሮ በሚያም ሁኔታ እተጎዱ ነው!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ! አሜን!

No comments:

Post a Comment